‹‹ትነብር ውስተ ቤተ መቅደስ፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ትኖር ነበር›› ቅዱስ ያሬድ

ታኅሣሥ ፪፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ዓለም ሁሉ ተሰብስቦ ቢመዘን አንድ የራሷን ፀጉር የማያህል ደግ ፍጥረት፣ ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች፣ ንጽሕናዋንም ይሁን ቅድስናዋን ፍጥረት በአንደበቱ ተናግሮም ሆነ ጽፎ የማይጨርሰው፣ የአምላክ ማደሪያ፣ እመ አምላክ፣ እመ ብዙኃን፣ ሰዓሊተ ምሕረት፣ አቁራሪተ መዓት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ዕለት የከበረ በዓል ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ትነብር ውስተ ቤተ መቅደስ፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ትኖር ነበር›› በማለት ስለ እርሷ የቅድስናና የንጽሕና ሕይወት ገልጿል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፈቃደ እግዚአብሔር ከአባቷ ቅዱስ ኢያቄምና ከእናቷ ቅድስት ሐና በስእለት የተገኘች መሆኗ ታሪኳ የተመዘገበበት የነገረ ማርያም መጽሐፍ ይገልጻል፡፡

ቅድስት እናታችን ድንግል ማርያም በተለወደች በስድስት ወሯ ከእናቷ እቅፍ ወርዳ በመቆምና  ሰባት እርምጃን ተራምዳ ዳግም ወደ እናቷ እቅፍ ውስጥ በመግባት ሐናን አስደንቃታለች፡፡ አንድ ዓመት ሲሆናትም አባቷ ኢያቄም ታላቅ ድግስ አዘጋጅቶ ካህናቱንና ሕዝብን ጠርቶ ጋበዘ፡፡

ከዚህም በኋላ እመቤታችን ሦስት ዓመት በሆናት ጊዜ እናቷ ሐና የልጇን ስእለት አስታውሳ ለቤተ መቅደስ አገልጋይ እንድትሆን መስጠት እንዳለባቸው ለባሏ ለኢያቄም እንዲህ ብላ አወሳችው፤  ‹‹ይህቺ ብላቴና የስእለት ገንዘብ እንደሆነች ታውቃለህ፤ ወስደን ለቤተ እግዚአብሔር እንስጣት፤›› እርሱም ‹‹ፍቅርሽ ይለቅልሽ ብዬ ነው እንጂ እኔማ ፈቃዴ ነው›› አለ፤ ኢያቄም ይህን ማለቱ ሐና እመቤታችንን በመካንነት ኖራ ያገኘቻት አንዲት ልጇ ናትና ከፍቅሯ ጽናት የተነሣ ተለይታት አታውቅም ነበርና ነው፡፡

ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐናም የእግዚአብሔርን ስእለት ለመፈጸም ዘመዶቻቸውንና ባልንጀሮቻቸውን በመጥራት ልጃቸውን ልዩና ንጹሕ ልብስን አልብሰው በመንፈሳዊ ዝማሬ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ መብራትን በእጆቻቸው ይዘው እያበሩ ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ ወሰዷት፤ በዚያን ጊዜም ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ከካህናቱ ጋር በመሆን እነርሱን ለመገናኘት ከመቅደስ ወጣ፡፡

በቤተ መቅደሱ ባሉት የሊቀ ካህናቱ መግቢያ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ የሚያስወጡ ፲፭ ደረጃዎች ነበሩ፤ በእነዚያም በእያንዳንዱ ደረጃዎች መዝሙረ ዳዊት ተደጋግሞ የሚደረስባቸው ናቸው፤ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐናም ልጃቸው እመቤታችን ማርያምን ከአንደኛው ደረጃ ላይ ቢያኖሯት መንፈሳዊ ኀይልን ተመልታ ያለምንም ረዳት ብቻዋን ደረጃዎቹን በመውጣት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወዳለበት ስፍራ ሄደች፤ እርሱም በእጅጉ ተደንቆ ባረካት፤ በዚያን ጊዜም ለሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ መንፈስ ቅዱስ ምሥጢርን ገለጠለት፤ ነቢያት ትንቢት የተናገሩላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ አስገነዘበው፤ መኖሪያዋም በዚሁ ቤተ መቅደስ እንዲሆን የአምላክ ፈቃድ መሆኑን አወቀ፡፡

እርሱም ይህንን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራን በማድነቅ ‹‹ይህቺን የመሰለች ልጅ ምን እናደርጋታለን? ምን እናበላታለን? ምንስ እናጠጣታለን? ምን እናነጥፍላታለን?›› ብሎ ሲጨነቅ ቸርነቱ የማያልቅ ልዑል እግዚአብሔር መልአኩ ፋኑኤልን ላከላት፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤልም ኅብስት ሰማያዊን በብርሃን ጽዋዕ ስቴ ሕይወትን ይዞ ረብቦ ታየ፤ ካህኑ ዘካርያስም ለእርሱ የመጣ ኅብስተ መና እንደሆነ አስቦ ታጥቆና እጅ ነሥቶ ቢቆም ወደ ላይ ራቀበት፡፡ የተሰበሰበው ሕዝብ በተራ በተራ ቢሞክሩም በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ላይ ራቀባቸው፡፡  ሐና እና ኢያቄምም ለእነርሱ የመጣ እንደሆነ ለማወቅ ቢቀርቡም ወደ ላይ ከፍ አለባቸው፤ ከዚህ በኋላ ካህኑ ዘካርያስ ሐናን ‹‹እግዚአብሔር የሚያደርገውን የሚያውቅ የለምና ልጅቷን ትተሸ ወደዚህ ነይ›› አላት፡፡ በዚህ ጊዜም መልአኩ በመውረድ አንድ ክንፉን አንጽፎ፣ አንዱን ክንፉን አጐናጽፎ ከመሬት የሰው ቁመት ያህል ከፍ አድርጓት ኅብስቱን መገባት፤ ጽዋውን አጠጣት፤ በኋላም ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ ሊቀ ካህናቱም ‹‹የምግቧ ነገር ከተያዘልን  ቦታዋ ከቤተ መቅደስ ይሁን›› ብለው ምንጣፉን አንጥፈው፣ መክዳውን ግራና ቀኝ፣ መጋረጃውን አድርገው ወደ ቤተ መቅደስ አስገቧት፤ ይህም ታኅሣሥ ፫ ቀን ነበር፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ሰማያዊ ኅብስት እየተመገበች፣ ስቴ ሕይወት እየጠጣችና ከመላእክት ጋር እየተጫወተች ፲፪ ዓመት በቤተ መቅደስ ኖረች፡፡ ሆኖም ግን በቤተ መቅደስ ሳለች አይሁድ ተሰብስበው ክፉ ምክርን መከሩባት፤  “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለችና እርሷም እንደ ባሪያ ልትገዛን ነው” በሚል ለማስገደል ሰዎችን ላኩ፡፡ እነዚያም አይሁድ የላኳቸው ሰዎች ሊገድሏት ሲሄዱ ቤተ መቅደሱ አራት ማዕዘን እሳት ሆኖ፣ መላእክትም ሰይፋቸውን መዘው፣ ረበው ታዩአቸው፡፡ ይህን ሲመለከቱ እመቤታችን በእሳት እንደ ተቃጠለች አስበው በመደሰት ወደ መጡበት ተመልሱ፤ በማግስቱ ግን በቤተ መቅዱስ በደኅና አገኟት፡፡

አይሁድ በዚህን ጊዜ እንዲገድሏት ወዳዘዙአቸው ሰዎች በመሄድ ለምን እንዳልገደሉአት ጠየቁአቸው፤ እነርሱም የሆነውን ባለ መረዳት በድጋሜ ሊገድሉአት ሄዱ፤ ዳግመኛም መንገዳቸው ዱር፣ ገደልና ባሕር ሆነባቸው፡፡ ይህን ጊዜ በአስማት እንዲህ የምታደርጋቸው እንደሆነ በማሰብ የእርሷን አስማት የሚበልጥ ለመፈለግ ተስማምተው መጥቁል የሚባል መተተኛ ጋር ሄዱ፡፡ እርሱም ‹‹ዋጋዬን ከሰጣችሁኝ እሺ፤ እርሷንስ አጠፋላችኋለሁ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ብዙ ወርቅ፣ ፈረስ፣ በግ፣ ፍየል፣ ጊደርና አልባሳት ሰጡት፡፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ ሀብት ለማግኘት መለስ ቢል ብሩ፣ ወርቁና ሁሉ ነገር ዝጎና አፈር በልቶት አገኘው፡፡ ይህን ጊዜ ‹‹የኢያቄምና የሐና ልጅ ሳልቀድማት ቀደመችኝ›› ብሎ እጅን ጸፋ፡፡ ከዚያም ለእነርሱ ሲያሳያቸው ‹‹እኛማ ቀድመን አላልንህምን?  አንተ ነህ እንጂ ሁሉን ማድረግ ይቻለኛል ያልከው›› አሉት፡፡ ገንዘባቸውንም እንዲመልስላቸው አስጨንቀው ያዙት፤ መጥቁልም ‹‹ቆዩኝ፥ የእርሷንስ ነገር አሁን በመንፈቀ ሌሊት አሳያችኋለሁ›› ብሎ ከእነርሱ መካከል ጎበዝ ጎበዙን መርጠው ፫፻፸ ሰው እንዲሰዱለት በጠየቃቸው መሠረት ሰጡት፤ ከእነርሱም መካከል ወንዝ ወርዶ አንዱን አርዶ ፫፻፸ አጋንንት ስቦ ካወጣ በኋላ እንዲረዱት ጠየቃቸው፤ በጠየቃቸው ነገር ደስ በመሰኘትም አጋንንቱ ከፊት፣ መጥቁል በመካከል አይሁድ በኋላ ሆነው ነጋሪት እየተመታ፣ እምቢልታ እየተነፋ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለመግደል ቤተ መቅደስ ሊደርሱ ሁለት ምንዳፈ ሐጽ ሲቀራቸው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከዚያ ድረስ ያልተደረገ መብረቅና ነጎድጓድ ወርዶ አጋንንትን፣ መጥቁልንና አይሁድን ቀጥቅጦ አጠፋቸው፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያምም በማግስቱ ይህን አይታ ‹‹መጥቁል ሆይ፥ እኔን አጠፋ ብለህ መጥተህ አንተ እንዲህ ሆንክ? ከአንተ መከራና መዓት ያወጣኝ አምላክ ይክበር ይመስገን›› ብላ አመሰገነች፡፡ ‹‹ዮሰሜር፣ አድሜሽ፣ ድቸር፣ አዶናዊስ፣ ሰራሰቅሰሬል›› ብላ የጌታን ኅቡእ ስሙን ብትጸልይበትም መሬት ተከፍቶ ከእነ ሥጋቸው ዋጣቸው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከዚህ በኋላ ተፈራች፤ ለመልካም ሰው ወዳጅ ለክፉ ሰዎችም ጭምር አማላጅ የሆነችው እናታችን ለጠንቋይና ለአስጠንቋይ ግን በሕይወተ ሥጋ እስካሉ ድረስ ንስሓ ካልገቡ በስተቀር እንደማታማልዳቸው ከዚህ ታሪክ እንረዳለን፡፡

እናታችን፣ አማላጃችንና ተራዳኢያችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጠላት የተነሡባት በዚህ ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ ፲፭ ዓመት ሲሞላትም ‹‹ለአቅመ ሔዋን በመድረሷ ከቤተ መቅደስ መውጣት አለባት›› በሚልም አይሁድ በጠላትነት ተነሥተውባት ነበር፡፡ ካህኑ ዘካርያስም ይህን ሰምቶ እመቤታችንን እንዲህ ብሎ ጠየቃት፤ «ኦ ወለተ እስራኤል እፎ ትፈቅዲ ትንበሪ፤ ልጄ እንደምን ሆነሽ ልትኖሪ ትወጂያለሽ?» አላት፡፡ እርሷም «ከእግዚአብሔር በታች ያለኸኝ አባት አንተ ነህ፤ በዚያውም ላይ እናትና አባቴ አደራ ያሉህ አንተን ነው፤ ወደ እግዚአብሔር አመልክትልኝ» አለችው፡፡ ዘካርያስም ጸለየ፤ አምላካችን እግዚአብሔርም ለካህኑ ዘካርያስ ከነገደ ይሁዳ መካከል ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን ሰዎች በመምረጥ በትራቸውን ሰብስቦ በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት ከቤተ መቅደስ አግብቶ ሲጸልይ እንዲያድር እንዲሁም በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት አውጥቶ ምልክቱን እንዲመለከት ነገረው፡፡ እርሱም እንደታዘዘው አድርጎ በማግስቱ ካህናቱን ሰብስበው በትሮቹን አውጥተው ቢያዩ የዮሴፍ በትር አብባና አፍርታ ተገኘች፡፡ ከበትሩ ጫፍ ላይም «ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ዕቀባ ለማርያም ፍኅርትከ፤ ዮሴፍ ሆይ እጮኛህ ማርያምን ጠብቃት» የሚል ጽሑፍ በመገኘቱ ርግብም መጥታ በራሱ ላይ አርፋ ነበርና ለእርሱ ተጠሰች፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያምም ከዚህ በኋላ ከቤተ መቅደስ ወጥታ ከጻድቁ ዮሴፍ ጋር ኖረች፡፡ እርሱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፀንሳ ስትወልድ፣ በስዳቷ ወቅትም ወደ ግብጽና ኢትዮጵያ ስትጓዝ እንዲሁም መከራ ስትቀበል ሁሉ ከጎና ሳይለይ የጠበቃት ነው፡፡ ይህን ሁሉ ግን አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ለእኛ ድኅነት ሲል ያደረገው በመሆኑ በእመቤታችን በኩል የተፈጸመውን የክርስቶስ የማዳን ሥራ በእምነት በመቀበል አማላጀነቷንና ተራዳኢነቷን ተስፋ በማድረግ ልንኖር ይገባል፡፡

በዓሉን የምሕረት፣ የበረከትና የረድኤት ያድርግልን፤ አሜን!

ምንጭ፡- “ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን” በመጋቤ ሐዲስ መምህር ሮዳስ ታደሰ