በዓለ ጰጦስ

        ዲያቆን ልሳነጽድቅ ኪዳነ

 

መንፈስ ቅዱስ ከሚጠራባቸው ስሞች አንዱ ጰራቅሊጦስ ናዛዚ መጽንዒ መስተፍሥሒ፤ የሚያጽናና፣ የሚመክር፣ የሚረዳ፣ የሚታደግ የሚል ትርጉም አለው፡፡ አጽናኝም የተባለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ‹‹አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋ›› ብሎ ተናግሯል፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ ‹‹እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል›› እንዲል። (ዮሐ.፲፬፥፳፮፤ ፲፭፥፲፮)

ጰራቅሊጦስ የሚለው የመንፈስ ቅዱስ ስም የሚያጽናና፣ የሚመክር፣ የሚረዳ፣ የሚታደግ መሆኑም ከማሳየት በላይ፤ ፍጹም አካል ያለው አምላክ እንደሆነ አመልካች ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጰራቅሊጦስ ማለት መሪ፣ አጽናኝ፣ ረጂ ማለት መሆኑን በስፋት ካስተማሩ ሊቃውንት በቀዳሚነት ይነሳል።  ጰራቅሊጦሰ የተባለው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው። ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ያላትን እምነቷን ስትገልጥ ‹‹ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ ዘሠረፀ እም አብ ንሰግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ››፤ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን እርሱም ጌታ ሕይወትን የሚሰጥ ከአብ የሠረፀ ከአብ ከወልድ ጋራ በአንድነት እንሰግድለታለን፣ እናመሰግነዋለን፤›› የሚል ነው።

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ፤ የቅድስናም ምንጭ ነው። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ‹‹ወስመ መንፈስ ቅዱስ ነቅዐ ቅድሳትየ፤ የመንፈስ ቅዱስም ስም የቅድስናየ መገኛ ነው›› በማለት ገልጾታል። (መጽሐፈ ምሥጢር)

ቅዱስ ባስልዮስም በቅዳሴው ‹‹ሃሌ ሉያ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስ መጽንዒ ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር መንፈስ ቅዱስ ንጹሕ ክቡር ልዩ ነው›› በማለት አምላካዊ ስሙን ጠርቶ አመስግኖታል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ዕለት ዕለት በምታከናውነው ሥርዓተ ቅዳሴ ‹‹መንጽሒ ወመጽንዒ የሚሆን መንፈስ ቅዱስ ክቡር ምስጉን ነው››  እያለች የአምላክነት ስሙን ጠርታ ታመሰግነዋለች።

ሊቃውንተ  ቤተ ክርስቲያን  ሃይማኖት  ሊያጸኑ  ከሓድያንን  ሊለዩ  (ሊያወግዙ) ሲሰባሰቡ በመካከላቸው ተገኝቶ ውሳኔ ያስወስናቸው የነበረው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ሲገልጹ ጰራቅሊጦስ የተባለ ስሙን ጠርተው እንዲህ ብለዋል፣ ‹‹ወሀሎ ምስሌሆሙ ኅብረ መንፈስ ቅዱስ …. ጰራቅሊጦስ የሚያነጻና የሚያጸና መንፈስ ቅዱስም በጉባኤያቸው ነበረ፡፡›› (መጽሐፈ ምሥጢር)

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ ሰባ ሁለቱ አርድእት እና ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በኢየሩሳሌም ከተማ በአንድነት ሆነው በጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ ጌታችን በሚያርግበት ጊዜ ‹‹እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ  ግን  ከላይ ኃይል እስክትለብሱ  ድረስ  በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤›› ሲል ለሐዋርያቱ በሰጣቸው የተስፋ ቃል መሠረት በዐረገ በዐሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል (ሉቃ. ፳፬፥፵፱)፡፡ ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰባስበው ሳሉ እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ ወርዶ የነበሩበትን ቤት ሞላው፡፡ ከዚያም የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች በሁሉም ላይ አረፉባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሁላቸውም መንፈስ ቅዱስ ባደላቸው መጠን በየሀገሩ ቋንቋዎች ሁሉ ተናገሩ፡፡ (ሐዋ.፪፥፩-፬)

ጌታችን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት ይህ ዐቢይ በዓል ዐሥራቱን፣ በኵራቱን፣ ቀዳምያቱን ካህናተ ኦሪት ስለሚቀበሉበት በብሉይ ኪዳን በዓለ ሠዊት ተብሎ ይከበር ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ስለ ተቀበሉበት በበዓለ ሠዊት ምትክ በዓለ ጰራቅሊጦስ ተብሎ ይከበራል፡፡ የበዓለ ትንሣኤ መነሻው የአይሁድ የፋሲካ በዓል ማለትም በግብጽ፣ እስራኤል ከሞት የዳኑበት የመታሰቢያ በዓል እንደ ሆነው ሁሉ፣ ለበዓለ ጰራቅሊጦስም መነሻው ይኸው የአይሁድ የፋሲካ በዓል ነው፡፡ የአይሁድ ፋሲካ ከተከበረ ከሰባት ሳምንታት በኋላ በኀምሳኛው ቀን የሩቆቹ ከከተሙበት ወጥተው፣ የቅርቦቹ ከተሰባሰቡበት ተገናኝተው ለበዓሉ ፍጻሜ የሚሆነውን በዓለ ሠዊት (የእሸት በዓል) ያከብሩ ነበር፡፡

ሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን ተሰባስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወርዶ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትና ጸጋን አድሏቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላም በአእምሮ ጐልምሰዋል፤ ጥቡዓን (ቈራጦች)፣ ጽኑዓን ሆነዋል፤ ለስብከተ ወንጌል የሚፋጠኑበትንና ለሰማዕትነት የሚዘጋጁበትን ልቡና ታድለዋል፡፡ ቀድሞ ይናገሩት ከነበሩት ቋንቋ በተጨማሪ ፸፩ ቋንቋዎች ተገልጠውላቸው ምሥጢራትን በልዩ ልዩ ቋንቋ መተርጐም ጀምረዋል፡፡ ሐዋርያት በየሀገሩ ቋንቋ ሲናገሩ የሰሙ በዚያ የነበሩ ሰዎችም በሐዋርያት ተገረሙ፡፡ አንዳንድ የአይሁድ ወገኖች ግን በሐዋርያት ላይ ያዩት ክሥተት አዲስ ነገር ስለሆነባቸው  ‹‹ጉሽ  ጠጅ  ጠጥተው  ሰክረው የሆነ ያልሆነውን ይቀባጥራሉ››  እያሉ ሐዋርያትን ያሟቸው ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ሐሳባቸውን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ  ‹‹ሰክረዋል  የምትሉ  እናንተ እንደምትጠራጠሩት  አይደለም፡፡ ጊዜው ማለዳ፣  ሰዓቱም ገና  ሦስት  ሰዓት  ነውና፡፡  ግን  በነቢዩ  ኢዩኤል ከዚህም በኋላ  እንዲህ  ይሆናል፤  መንፈሴን  በሥጋ  ለባሽ  ሁሉ  ላይ  አፈሳለሁ፤  ወንዶችና  ሴቶች  ልጆቻችሁም  ትንቢት ይናገራሉ   ተብሎ  የተነገረው  ትንቢት  ይፈጸም  ዘንድ፣ ይህንን ድንቅ  ተአምር  ያደረገው  እናንተ  የሰቀላችሁት  ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤››በማለት ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥቷቸዋል፡፡ (ኢዩ.፪፥፳፰)

በትምህርቱም ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት፣ምሳሌ የመሰሉለት አምላክ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን፣ማረጉንና ዳግም በክብር በምስጋና መጥቶ በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈረድ መሆኑን ሐዋርያት እንደሚመሰክሩ በአይሁድ ፊት አሰምቶ ተናገረ፡፡በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት የተማረኩ አሕዛብም ‹‹ምን እናድርግ?››ብለው በጠየቁት ጊዜ ከክፋታቸው ተመልሰው፣ንስሓ ገብተው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ ነገሯቸዋል፡፡ በዚያችም ሰዓት ሦስት ሺህ ሕዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል፡፡(ሐዋ.፪፥፩-፵፩)

ቅዱሳን ሐዋርያት፤ ‹‹በዚህች  ቀን  በሦስት  ሰዓት  ኢየሱስ  ክርስቶስ  ጰራቅሊጦስን  ልኮልናልና  በላያችን  ኃይልን  ሞላ፡፡  ኢየሱስ  ክርስቶስ  የእግዚአብሔር  ልጅ  በሕያዋንና  በሙታን  ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው በአዲስ ቋንቋ ተናገርን፤›› በማለት በዕለቱ ያዩትንና የተደረገላቸውን፣ እንደዚሁም የበዓሉን ታላቅነት ከመሰከሩ በኋላ ይህንን በዓል ማክበር እንደሚገባ አዝዘዋል፤ በዚህ ወቅት መጾምና ማዘን ተገቢ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ (ዲድስቅልያ ፴፥፴፰-፴፱፤ ፴፩፥፷፱-፸)

ቅዱሳን ሐዋርያትም ‹‹ከአብ የሠረፀ የሁላችንም መጽናኛ የሚሆን ዓለሙንም ሁሉ ያዳነ ከአብና ከወልድ ጋር ህልው የሚሆን መንፈስ ቅዱስን ላከልን፡፡ መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስም አንድ ነው›› ብለዋል። በሌላም ነቢዩ ዳዊት ስለመንፈስ ቅዱስ ‹‹መንፈስህን ከእኔ አታርቅ አለ፤ ዳግመኛም በሰውነቴ እውነተኛ መንፈስን አጽናልኝ፣ ከሁሉ በሆነ መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ አለ›› በማለት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መንፈስ ቅዱስን ጰራቅሊጦስ አጽናኝ መካሪ መባሉን አስተምሯል። (መዝ. ፶፥ ፲-፲፪፤ መጽሐፈ ምሥጢር)

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በበዓለ ኀምሳ ምንባብ ላይ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስ ስለተባለበትና ተስፋ በተሰጣቸው በኀምሳኛው ቀን ወርዶ ስለ ሠራው ሥራ እንዲህ በማለት ያብራራል። ‹‹ወመንፈስ ቅዱስኒ ኢተሰምየ ጰራቅሊጦስሃ ዘእንበለ አመ ይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ለአርዳኢሁ እፌኑ ለክሙ ካልአ ጰራቅሊጦስሃ። ጰራቅሊጦስ ብሂል ናዛዚ ብሂል በነገረ ጽርዕ ……መንፈስ ቅዱስም ጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሌላውን አጽናኝ እልክላችኋለሁ›› ከማለቱ በፊት ጰራቅሊጦስ አልተባለም ጰራቅሊጦስ ማለት በጽርዕ ቋንቋ አጽናኝ ማለት ነው ስለምን አጽናኝ ተባለ ደቀ መዛሙርቱ ወልድ ካረገበት ቀን ጀምሮ ጰራቅሊጦስ እስከ ወረደበት ቀን ድረስ  ያለቅሱ ነበረና ስለዚህም ወልድ መንፈስ ቅዱስን ጰራቅሊጦስ አለው። የስሙ ትርጓሜ ግን አስቀድመን እንደተናገርነው አጽናኝ ማለት ነው። (ዮሐ. ፲፬፥፲፭)

በዓለ ጰራቅሊጦስ የሚከበረው ርደተ መንፈስ ቅዱስን መሠረት በማድረግ በመሆኑ ምክንያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ለመቀበል ነው፤ በዕለቱም ኢየሩሳሌም በተባለችው ቤተክርስቲያን ስለመጽናት፤ ከግለኝነት ይልቅ መንፈሳዊ አንድነትን ስለማስቀደም እና ስለመጸለይ  እንማራለን፡፡

በዓለ ትንሣኤውን በቸርነቱ በሰላም እንድናሳልፍ ፈቅዶ እስከ ዛሬ ድረስ ስለ ጠበቀን፣ አሁን ደግሞ በጾም፣ በጸሎት ሆነን እርሱን የምናመሰግንበትን ወቅት ስላመጣልን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ለዘለዓለሙ የተመሰገነ ይሁን፤ አሜን፡፡

ምንጮች፤

  • መዝገበ ታሪክ፣ ክፍል ፪፤ መምህር ኅሩይ ኤርምያስ፤ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም፤ ገጽ ፹፬-፹፭፡፡
  • መጽሐፈ ስንክሳር ግንቦት ፲፰ ቀን፣ መጽሐፈ ምሥጢር፡፡
  • መጽሐፈ ግጻዌ፡፡
  • ማኅቶተ ዘመን፣ መምህር በሙሉ አስፋው፤ ፳፻፩ ዓ.ም፤ ገጽ ፻፺፭-፪፻፬፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር