ቅድስት መስቀል ክብራ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ሐምሌ ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? ወርኃ ክረምቱ እንዴት ነው? መቼም ዝናቡና ቅዝቃዜው እንደፈለግን እንዳንጫወት አድርጎናልና ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስም አያመችም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ቤት ውስጥ እንደምንቆይ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም መጻሕፍትን ማንበብ፣ ለቀጣዩ ዓመት የትምህርት ጊዜ የሚረዱንን ጥናቶች በማድረግ ልንዘጋጅ ያስፈልጋል፤ ጊዜያችንን በአግባቡ በቁም ነገር ላይ ማዋል አለብን! ደግሞም በጉጉት የምንጠብቃት ጾመ ፍልሰታም እየደረሰች ነው!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ያዘጋጀንላችሁ የቅድስት መስቀል ክብራን ታሪክ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሀገራችን በሃይማኖት ጸንተው በምግባራቸው ተመስክሮላቸው ለቅድስና የበቁ አባቶቻችንና እናቶቻችን አሉ፤  ከእነዚህም እናቶቻችን አንዷ ቅድስት መስቀል ክብራ ናት፤ እናቷ ሶፊያ፣ አባቷ ስምዖን ይባላሉ፡፡ የትውልድ ሀገሯ ኢትዮጵያ በወሎ ላስታ ቡግና ነው፤ ወላጆቿ  ወንጌል እያስተማሩ በጥሩ ሥነ ምግባር አሳደጓት፤ ልጆች! ወላጆቻችን እኛን ለማሳደግ ብዙ ይደክማሉ፤ እኛ መልካም በሰዎች የተወደድን፣ ጎበዞች እንሆን ዘንድ ይመኛሉ፤ የሚችሉትን ሁሉ በአቅማቸው ያደርጋሉ ለምን መሰላችሁ? እኛን በጣም ስለሚወዱን ነው! ታዲያ እኛ እነርሱን የምንወዳቸው ከሆነ እኛ እንድንሆንላቸው የሚፈልጉትን ነገር ለመሆን መበርታት አለብን፡፡ በሥነ ምግባር የታነጽን ጥሩዎችና ታላላቆቻችን የሚደሰቱበትን ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ታዲያ ሰዎች በእኛ መልካምነት ደስ ሲላቸው ፈጣሪም ደስ ይለዋል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች!  በመጽሐፍ ቅዱስ  ‹‹ልጆች ሆይ! ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፤ ይህ የሚገባ ነውና፤ መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትና እናትህን አክብር›› ተብሎ እንደተጻፈው (ኤፌ.፮፥፩) ቅድስት መስቀል ክብራ ወላጆቿን እያገለገለችና እየታዘዘች በመልካም አስተዳደግ አደገች፡፡

ከዚያም በዕድሜ ከፍ ስትል ሰው (ወጣት) ስትሆን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ባል አገባች፡፡ ይገርማችኋል ልጆች! ባለቤቷ ማን መሰላችሁ? ቅዱስ ንጉሥ ላሊበላ ነው! ቅዱስ ላሊበላ ከአለት (ከድንጋይ)  ላይ ፈልፍሎ ቤተ መቅደስ ያነጸው፣ ዛሬ ዓለም የሚያደንቀውና እኛ የምንኮራበትን ድንቅ ሥራዎችን የሠራልን አባታችን ነው፤ ቅድስት መስቀል ክብራ መልካም ሥነ ምግባር የነበራት ጾመኛ፣ በጸሎት በስግደት ፈጣሪን የምታመሰግን ነበረች፤ ከንጉሥ ቅዱስ ላሊበላም ጋር ከተጋቡ በኋላ ልጅ ወለዱ፤ ስሙንም ይትባረክ አሉት፤ ይቀደስ፣ መልካም ይሁን፣ይመስገን ማለት ነው:: አያችሁ ልጆች! ስም መጠሪያ ብቻ ሳይሆን ወላጆቻችን እግዚአብሔር ያደረገላቸውን መልካም ነገር ውለታም ያስታውሱበታል፣ ልጆች! ሌላው ደግሞ ስም የሚያወጡልን ምክንያት እንደ ስማችን እንድንሆንላቸው ስለሚመኙም ነው፡፡ ስለዚህ እንደስማችን ሆነን ለመገኘት መጣር፣ መጎበዝ፣ ማስተዋል አለብን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እናታችን ቅድስት መስቀል ክብራ ቅዱስ ላሊበላ ከአለት (ከድንጋይ) ቤተ መቅደስ ሲሠራ እርሷም በጸሎት ፈጣሪን ትማጸን ነበር ፡፡ በሱባኤ ሆና ፈጣሪ የሚገልጽላትን የሕንጻ ጥበብ ትነግረው ነበር ፡፡ ከቅዱስ ላሊበላ የቤተ መቅደስ አስደናቂ ሕንጻ ተግባር ጉልህ ሚና የነበራት እናታችን ናት፡፡ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከብዙ ድንቅ ታሪኮች ጀርባ የእናቶቻችን አስተዋጽኦ አለ፡፡ ቅድስት መስቀል ክብራ በእግዚአብሔር ፈቃድ ቤተ አባ ሊባኖስ የተባለውን ቤተ መቅደስ ሠርታለች፤ ይህም መልካም ሥራዋ በተጻፈላት የገድል መጽሐፏ እንዲሁም በቅዱስ ላሊበላ ገድልም ተመዝግቧል፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ፣ የምታገለግልና ሕጉን ትእዛዙን የምትፈጽም በመሆኗ ቅዱሳን መላእክት ይጠብቋት ነበር፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከመልካም ሰው ጋር አብሮ መሆን መልካምነት ይገኛል፤ በእግዚአብሔርም ዘንድ ክብርን ያሰጣል፤ ሁል ጊዜ ሕይወታችን የተቀደሰ እንዲሆን አብረናቸው የምንሆናቸው ሰዎች በመልካምነታቸው የተመሠከረላቸው ሊሆኑ ይገባል፤በትምህርት ቤት፣ በሠፈር ውስጥ ከእኛ ጋር ያሉ ጓደኞቻችን ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ታላላቆቻቸውን የሚያከብሩ ልጆች መሆን አለባቸው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ‹‹ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል…›› (፩ ቆሮ. ፲፭፥፴፫) ተብሎ እንደተጻፈልን ከክፉ ልጆች ጋር የምንውል ከሆነ አመላችን ይበላሻል፡፡ ስለዚህ መልካሞች እንድንሆን ከመልካም ሰዎች ጋር እንዋል፤ እናታችን ቅድስት መስቀል ክብራ ከቅዱስ ላሊበላ ጋር አብራ በመሆኗ እንግዶችን የምትቀበል ሰዎችን የምታስተምር እውነትን የምትቀበል ቅድስት ሴት ነበረች፡፡ በጾምና በጸሎት በትሩፋት ሥራ ጸንታ ኑራለች፤ በሀገራችን የሰሜኑ ክፍል በትግራይ ሽሬ ዞባ ሙዳባይ ታብር ከተባለ ቦታ በእርሷ ስም የተሠራ ገዳም አለ ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹…ወንድሞቼ ሆይ እኔን የምትመስሉ ሁኑ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ…›› (ፊሊ.፫፥፲፯)

እንግዲህ ልጆች! የቅዱሳንን ታሪክ የምንማረው ምሳሌ ልናደርጋቸው፡፡ ነውና እንደ እነርሱ መልካም ሠርተን የክብርን ሕይወት ለማግኘት መትጋት ይኖርብናል፤ ከእናታችን ከቅድስት መስቀል ክብራ ምን እንማራለን? በሥነ ምግባር የታነጸ፣ እምነቱ የጸና ልጆች ሆነን ማደግ እንዳለብን እንማራለን፡፡ ቅድስት መስቀል ክብራ የክርስትና ትምህርት በደንብ ተምራ ስለነበር በመልካም ሕይወት ተገኝታ ለቅዱስ ንጉሥ ላሊበላ ሚስት ሆነች፤ እንደርሱ ተመርጣ ቤተ መቅደስ ሠራች፤ ሌላው ከመልካም ሰዎች ጋር በመዋል፣ በመንፈሳዊ ሕይወትና በትምህርት በጸሎት ጸናች፤

አያችሁ ልጆች! የተማርነውን ትምህርት ሳንረሳ በሕይወታችን መተግበር ይገባናል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ከእኛ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖቸ እንዴት ይኖሩ እንደ ነበረ ጠይቀን በመረዳት እንደ እርሱ ልንሆን ይገባል፡፡

አምላከ ቅድስት መስቀል ክብራ  በረከቷን ያድለን አሜን!!!  ቸር ይግጠመን ይቆየን !!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!