ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር

ጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በዐሥራ ስምንት ዓመት ዕድሜው የመነኮሰ፣ ትዕግሥቱ እጅግ የበዛ እንዲሁም የመታዘዝ ጸጋ የተሰጠው ቅዱስ አባታችን ዮሐንስ ሐጺር የዕረፍት መታሰቢያ ጥቅምት ሃያ ቀን ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚገልጹትም ይህ ጻድቅ ከቅዱሳን አባቶች መካከል በቁመት እንደ እርሱ አጭር ስላልነበረ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር፤ አጭሩ አባ ዮሐንስ›› ተብሏል፡፡ የእርሱን ቁመትና የቅድስና ሕይወቱን ሲያነጻጽሩም ‹‹ቁመቱ እጅግ ያጠረ ጽድቁ ግን ከሰማይ የደረሰ ቅዱስ ዮሐንስን ሰላም ሰላም እንለዋለን›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር የትውልድ ሀገሩ ግብጽ ሲሆን የተወለደው ደግሞ በዐራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከክርስቲያናዊ ቤተሰብ ነው:: ወላጆቹ ድሆች ቢሆኑም በጎ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይህን ቅዱስ አባትም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አስተምረው አሳድገውታል::

ቅዱሱም ዐሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነው የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት አነሣሥቶት ይመነኲስ ዘንድ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሄደ፤ ታላቁ አባ ባይሞይም ወጣትነቱን አይቶ ‹‹የገዳም ኑሮ ጭንቅ ነውና ላንተ አይሆንህም›› በማለት ቢከለክለውም ቅዱስ ዮሐንስ ግን እንዲቀበለው ለመነው፡፡ ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ለአባ ባይሞይ ተገልጾ ‹‹ምርጥ ዕቃ ይሆናልና ተቀበለው›› አላቸው፡፡ ከዚያም በልብሰ ምንኲስናው ላይ ለሦስት ቀናት ጸለየበት፤ ያን ጊዜ መልአኩ ተገልጦ በልብሱ ላይ በመስቀል ምልክት አማተበበት፤ ከዚያም አባ ባይሞይ ለአባ ዮሐንስ ሐጺር አለበሰውና ተጋድሎውን ጀመረ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በወቅቱ ከነበሩ ቅዱሳን ከቁመቱ ባሻገር በትሕትናው፣ በትዕግሥቱና በመታዘዙ ይታወቅ ነበር:: ትዕግሥቱን ለመፈተንም አባ ባይሞይ ይጠራውና ያለ ምንም ምክንያት ደብድቦ ያባርረው ነበር:: እርሱ ግን ‹‹ምን አጠፋሁ?›› በማለት እንኳን ሳይጠይቅ ‹‹አባቴ ሆይ! ማረኝ?›› እያለ ከእግሩ ሥር ይወድቅ እንደነበር ገድሎ ይመሠክራል:: ለብዙ ጊዜ በተመሳሳይ ሲደበድበው እርሱም ተደብድቦ ይቅርታን ሲጠይቅ ኖረ:: አባ ባይሞይ ይህንን ሁሉ የሚያደርገው ጠልቶት ወይም ክፉ ሆኖ አልነበረም:: ሆኖም ግን ሰው የሌላኛውን ግፍ መቀበል ካልቻለ ሰይጣንን ድል መንሣት እንደማይችል ስለሚይምንበት ነበረ::

በዚህም ሁኔታ ሲኖር አንድ ቀን አባ ባይሞይ እንደ ልማዱ ሊገርፈው ሲሄድ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ከበውት በመመልከቱ ደንግጦ ተመልሷል፡፡

ከዕለታት በአንድ ቀንም ቅዱስ ዮሐንስ ወደ መምህሩ ቀርቦ ‹‹አባቴ ጅብ ካገኘሁ ምን ላድርግ?›› በማለት ጠየቀው:: አባ ባይሞይ ሊፈትነው በማሰብ ‹‹ይዘህልኝ ና›› አለው:: ትእዛዝ ነውና ቅዱሱ ወደ በርኃ ወርዶ ጅብ አልምዶ ይዞለት መጥቷል:: ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር የመታዘዝ ጸጋ በእጅጉ የተሰጠው እንደሆነም በአባ ባይሞይ ዘንድ የተመሠከረለት ነው፤ ስለዚህ ነገር ዐውቆ በድጋሜ ሊፈትነው ደረቅ ዕንጨት ለቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ከሰጠው በኋላ ‹‹ይህነን ዕንጨት ትከለውና እስከሚያፈራ ድረስ ውኃን አጠጣው›› በማለት አዘዘው፤ ቅዱስም በመታዛዝ ወስዶ ተከለው፤ ዐሥራ ሁለት ምዕራፍ ወደሚርቀው የውኃ ጒድጓድ እየተመላለሰም በየቀኑ ሁለት ሁለት ጊዜ  ያጠጣው ጀመረ፤ ከሦስት ዓመትም በኋላ ያ ዕንጨት አቈጥቊጦ በቀለ፤ አበበ፤ አፈራ፤ ቅዱሱም ካፈራው በኩረ ሎሚ ወስዶ ለመምህሩ ‹‹አባቴ! እንካ ብላ›› ብሎ ሰጠው፤ አባ ባይሞይ ግን ማመን ተስኖት እጅግ አደነቀ፤ አለቀሰም:: ወዲያውም ያን ፍሬ ታቅፎ ወስዶ ለገዳሙ መነኮሳትና ለቅዱሳን አረጋውያን ‹‹የታዛዡንና የትሑቱን ፍሬ እነሆ ብሉ፤ በረከትንም አግኙ:: ይህ የዛፍ ሳይሆን የመታዘዝ ፍሬ ነው›› ብለው ሰጥተዋቸዋል፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ አባ ቴዎፍሎስም የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ብቃት ዐውቆ የገዳሙ አበምኔት አድርጎ ሊሾመው እጆቹን በላዩ ላይ ሲጭን ‹‹ይገባዋል›› የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰምቷል፤ በሌላ ቀን ደግሞ አንድ መነኮስ ሊጐበኘው ወደ በዓቱ በመጣበት ጊዜ  የእግዚአብሔር መልአክ ክንፎቻቸውን በቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ላይ ሲያርገበግቡ ተመልክቶ በመደነቅ አምላክን አመስግኗል፡፡

ቅዱሰ ዮሐንስ ሐጺርም በቅድስና ሕይወት ሲኖር በአንድ ወቅት መምህሩ ታመመና ለዐሥራ ሁለት ዓመት አስታመመው:: አባ ባይሞይም የዕረፍት ጊዜው ሲደርስ መነኮሳቱን ሰብስቦ የቅዱስ ዮሐንስን እጅ ካስጨበጣቸው በኋላ ‹‹ይህ የያዛችሁት እጅ የሰው ሳይሆን የመልአክ እጅ ነው›› ብለቸዋል፤ ከዚያም ዐረፈ::

ከአባ ባይሞይም ዕረፍት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ ለብዙ ዘመናት በተጋድሎ ኖሯል፡፡ የገዳሙ አበ ምኔት ሆኖም አገልግሏል:: በዚህም ጊዜ መላእክት ስለ ንጽሕናውና ቅድስናው ደስ በመሰኘት አብረውት ይውሉ ነበር:: ሲተኛም ተራ በተራ ክንፋቸውን አልብሰውት ያድራሉ:: ምጽዋትን በጣም ይወድ ስለነበረም ሰፌድ እየሰፋ በመሸጥ ገንዘቡን ለነዳያን ይመጸውት ነበር::

አንድ ቀንም እንደ ልማዱ ወደ ገበያ በወጣበት ጊዜ ተመስጦ መጣበት:: ሰማያት ተከፍተውም ቅዱሳን ሊቃነ መላእክት ሚካኤልና ገብርኤል በግርማ በጌታ ፊት ቆመው ተመለከተ:: ‹‹እጹብ: እጹብ›› እያለ ሲያደንቅ አንድ ገዢ መጥቶ ‹‹ባለ እንቅብ ዋጋው ስንት ነው?›› ሲለው ‹‹ከሚካኤልና ከገብርኤል ማን ይበልጣል?›› በማለት ጠይቆታል:: ገዢውም ደንግጦ ‹‹እብድ መነኩሴ›› ብሎት ጥሎት ሄዷል::

በአንድ ወቅት ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ወደ ባቢሎን (የአሁኗ ኢራቅ) ተጉዞ ነበር፤ ከዚያም እንደተመለሰ በበርበሮች ምክንያት ከአስቄጥስ ወደ ቁልዝም ተሰዷል:: በዚያም በአባ እንጦንስ በዓት ውስጥ ለዐራት መቶ ዓመታት ቆይቷል::

ቅዱሱ የዕረፍቱ ጊዜ በደረሰ ጊዜም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባ እንጦንስን፣ አባ መቃርስን፣ አባ ጳኲሚስንና አባ ባይሞንን ወደ ርሱ ላካቸው፤ እነርሱም አረጋግተውትና ባርከውት ተመለሱ፤ በዕረፍቱ ቀንም ሠራዊተ መላእክትና የቅዱሳን ማኅበር ወደ እርሱ ሲመጡ ባያቸው ጊዜ ደስ ብሎት ጥቅምት ፳ በጌታ እጅ ነፍሱን ሰጠ፤ መላእክትም እየዘመሩ በታላቅ ክብር ነፍሱን አሳርገውታል፡፡

የቅዱስ አባታችን ምልጃና ጸሎት እንዲሁም በረከት አይለየን፤ አሜን፡፡