“ቄስ” ገዳሙ ደምሳሽ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተለዩ

ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም

በዲ/ን ፍቃዱ ዓለሙ

በኑፋቄ ትምህርታቸው ምእመናንን ሲቀስጡና የማኅበረ ካህናቱንና ምእመናኑን አንድነት ሲጎዱ የቆዩት “ቄስ” ገዳሙ ደምሳሽ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ከቅስናና ከቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት እንዲሁም ከማንኛውም ክህነታዊ አገልግሎትና ትምህርተ ወንጌል ከመስጠት ታገዱ፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ ሰኔ 18 ቀን 2006 ዓ.ም ውሳኔውን ያስተላለፈው ግለሰቡ ግልጽ ባልኾነ ሁኔታ የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ኾነው ከመቀመጣቸው በፊት ወደ ፕሮቴስታንት የእምነት ተቋም ሔደው በቆዩባቸው ጊዜያት ጽፈው ያሳተሟቸው መጻሕፍት ይዘት በሊቃውንት ጉባኤ እንዲመረመር ካደረገ በኋላ መኾኑ በመግለጫው ታትቷል፡፡

 

በተጨማሪም ግልጽ ባልኾነ ሁኔታ ተመልሰዋል ተብሎ በሀገረ ጀርመን ካሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት አንዱ በኾነው ቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሾሙም በኋላ በልዩ ልዩ የጀርመን ግዛቶች እየተዘዋወሩ ሲያስተምሩ የነበረውን ፀረ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት በመቃወም በየጊዜው ከምእመናንና ካህናት የተላኩትን አቤቱታዎች እንደመረመረ መግለጫው ያብራራል፡፡

 

በሊቃውንት ጉባኤው ምርመራ መሠረት ጽሑፎቻቸው ግለሰቡ “የቤተ ክርስቲያናችንን የአብነት ትምህርት በውል ያልተማሩና ምሥጢራትን ያልተረዱ መኾናቸውን” የሚያሳዩ ከመኾናቸው በላይ የተሳሳቱና ኦርቶዶክሳዊ ያልኾኑ የኑፋቄ አስተምህሮዎችን የያዙ ናቸው፡፡ በመኾኑም እነዚህ መጻሕፍት በማንኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እንዳይሠራጩና ለማስተማሪያነትም እንዳይቀርቡ ታዝዟል፡፡ ይህ በቅዱስ ሲኖዶስ ተላልፎ ለደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የተላከው ውሳኔ መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም በፍራክፈርት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ ሰብሳቢነት በተደረገ አጠቃላይ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች ስብሰባ በውሳኔው የተለዩት ግለሰብም ባሉበት በንባብ መሰማቱን፤ በዚህም ወቅት ግለሰቡ ጉባኤውን ረግጠው መውጣታቸውን መግለጫው ያትታል፡፡ 

 

እኒህ ሰው በሀገረ ጀርመን ሲፈጠሯቸው የነበሩ ችግሮችን አስመልክቶ ከቦታው በሚደርሱን መረጃዎች በመመሥረት በኅትመቶቻችን ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ዝርዝር በሚቀጥለው የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ እናቀርባለን፡፡