ስምና የስም ዓይነቶች

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

ስም “ሰመየ፤ ስም አወጣ፣ ጠራ፣ ለየ” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መጠሪያ መለያ፣ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስም ማለት መጠሪያ፣ መለያ፣ አንድን አካል ከሌላው አካል የምንለይበት ማለት ነው፡፡ “እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ደግሞ ከምድር ፈጠረ፤በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤    አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደጠራው ስሙ ያው ሆነ፡፡ አዳምም ለእንስሳት ሁሉ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣለቸው” (ዘፍ፪፥፲፱-፳) እንዲል፡፡ በመጽሀፈ ቀሌምንጦስም “ወሰመዮሙ ለኵሎሙ በበአስማቲሆሙ ወተአዘዙ ሎቱ ኵሉ ፍጥረት ወዓቀቡ ቃሎ፤ አዳም ለሁሉም በየስማቸው ሰየማቸው፣ ስም አወጣላቸው፤ ፍጥረት ሁሉ ለአዳም ይታዘዝና ቃሉንም ይጠብቅ ነበር” (ቀሌ፩፥፵፪) በማለት ተጽፎ እናገኛለን

የስም ዓይነቶች ፡-

ባለፈው እትማችን እንደገለጽነው ስም ከቃል ክፍሎች አንዱ ሲሆን በውስጡ ደግሞ የራሱ የሆኑ ክፍፍሎች አሉት በስም ውስጥ የሚካተቱትን የስም ዓይነቶች ከተለያየ አንጻር የተለያየ አከፋፈል አለ፡፡ ለምሳሌ ከአገልግሎት አንጻር፣ከአመሠራረት አንጻር እና ሌሎችም ሁለቱን በዚህ ርእሰ ጉዳይ እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

 የስም ዓይነቶች ከአመሠራረት አንጻር በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነሱም፡-

፩. ዘር(ምሥርት ስም)፡-

ከግስ የሚመሠረቱት ስሞች ምስርት ስሞች ይባላሉ፡፡ የግስ ዘር ያላቸው ወይም አንቀጽ ያላቸው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አምላክ፣ ፈጣሪ፣መልአክ፣ ሐራሲ፣ ሐናጺ፣ ቤት፣ ወዘተ

. ነባር ስም፡-

አንቀጽ የሌለው ሁሉ ነባር ይባላል፡፡ ነባር ማለት እርባታ የሌለው በቁም ቀሪ ማለት ነው፡፡ እቤርት፣ ዕብን፣ ዳዊት፣ ወዘተ

ማስታወሻ፡- ነባር ስም የሚባል እንደሌለ አንዳንድ ሊቃውንት ያስረዳሉ ከእነዚህ መካከል ኪዳነ ወልድ ክፍሌ አንዱ ናቸው፡፡ ምንጩ ማለት ቃሉ የተመሠረተበትን ግስ ስለማይታወቅ፣ ስላልተለመደ እንጂ ነባር የሚባል ስም የለም፡፡ ሁሉም የግሰ አንቀጽ አለው ባይ ናቸው፡፡

. የስም ዓይነቶች ከአገልግሎት አንጻር በአምስት ይከፈላሉ፡፡ እነሱም፡-

፩. ስመ ባሕርይ (የባሕርይ ስም)

፪. ስመ ተቀብዖ (የሹመት ስም)

፫. ስመ ግብር (የግብር ስም)

፬. ስመ ተጸውኦ (የመጠሪያ ስም)

፭.ስመ ተውላጥ (መራሕያን)

የባሕርይ ስም ፡-  አምላክ፣ ፈጣሪ፣ እግዚእ፣ወዘተ

ስመ ተጸውዖ (የመጠሪያ ስም) ፡-

ይህ ስም እያንዳንዱ ሰው፣ እንስሳ፣ አራዊት፣ ዕፅዋት፣ ቦታ፣ ወዘተ ተለይቶ የሚጠራበት ስም ነው፡፡ “ፍጡር የሆነ ሁሉ ለግሉ የሚጠራበት ሰውም እያንዳንዱ ከእናት ከአባቱ ተሰይሞ እገሌ፣ እገሊት ተብሎ የሚጠራበት ይህን የመሰለ ሁሉ ነው” (መጽሐፈ ሰዋስው መጽሔተ አእምሮ፣ ገጽ ፮) እንዲል፡፡ ለምሳሌ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኢሳይያስ፣ ይድራስ፣ ሲና፣ ታቦር፣ ዘይት፣ ኢትዮጵያ፣ ኢየሩሳሌም፣ ከነአን

ስመ ተቀብዖ (የሹመት ስም) ፡-

ሰዎች ሲሾሙ የሚያገኙት ወይም የሚሰጣቸው የክብር ስም ነው፡፡ “የተቀብዖ ስም ሹመት ያለው ሁሉ …በመንፈሳዊና በሥጋዊ ነገር የሹመት ስም እርሱን የመሰለ ሁሉ ነው” ((መጽሐፈ ሰዋስው መጽሔተ አእምሮ፣ገጽ ፮) እንዲል፡፡ ለምሳሌ፡- ንጉሥ፣ ጳጳስ፣ ካህን፣ ዲያቆን፣ ሀቤ ምእት፣ መልአከ ሰላም፣ መለአከ ኃይል ወዘተ

ስመ ግብር (የግብር ስም) ፡-

ሥራን የሚገልጽ ስም ነው፡፡ “ፍጥረት ሁሉ በሥራው በግብሩ በአካሄዱ በነገሩ ሁሉ የሚጠራበት ነው ነው” (መጽሐፈ ሰዋስው መጽሔተ አእምሮ፣፮) እንዲል፡፡ ሐራሲ፣ ሐናጺ፣ መምህር፣ ለብሀዊ፣ ነጋዲ፣ ጸራቢ፣ ወዘተ

ስመ ተውላጥ፡- (መራሕያን) በስም ፈንታ የሚገቡ እንደስም የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

አነ፣ ንሕነ፣ አንተ፣ አንትሙ፣ አንቲ፣ እንትን፣ ውእቱ፣ ውእቶሙ፣ ይእቲ፣ ውእቶን ናቸው፡፡ መራሕያን

ከላይ የተገለጸውን ጽንሰ ሐሳብ በምሳሌ እንመልከተው፡፡

                        ጉባኤ ቃና

ኢክህለ ሞት ሐራሲ ዐዲወ  ዕርገት ቀላይ፤

እስመ ለቀላይ ዕርገት ይመልኦ ደመና ዘቦ ሰማይ፡፡

ትርጉም

   ሞት ገበሬ   በዕርገት ወንዝ መሻገርን አልቻለም፤

ዕርገት ወንዝን ያለ የሆነ የሰማይ ደመና ይመላዋልና፡፡

ምሥጢሩ

ሰሙ፡- አንዳንድ ወንዝ እርሱ እንኮ ገና በደመና ነው የሚመላ ይባላል፡፡

ወርቁ፡- ጌታችን  በደመና  ማረጉን ለማስረዳት ነው፡፡

በዚህ ጉባኤ ቃና ከላይ በተመለከትነው ማብራሪያ መሠረት ነባርና ዘር(ምሥርት) ብለን በስም ክፍል ብቻ የሚመደቡትን እንጥቀስና የስም ክፍሎቻቸውን እንገልጻለን፡፡

ስም፡- ሞት፣ ሐራሲ፣ ቀላይ፣ ደመና፣ ዕርገት፣ ወልድ፣ አብ፣

ከአመሠራረት አንጻር የስም ዓይነት

ነባር ስም፡- ቀላይ

ምሥርት ስም፡- ሐራሲ፣ ደመና፣ ዕርገት፣ ወልድ፣ አብ፣

ከአገልግሎት አንጻር የስም ዓይነት

ስመ ተጸውዖ ፡- ወልድ፣ አብ፣

የግብር ስም ፡- ሐራሲ

እንዲሁ ሌላም እንጨምር

ሰላም ለኪ ፤እንዘ ንሰግድ ንብለኪ፤ ማርያም እምነ ናስተበቊዐኪ፤ እምአርዌ ነዐዊ ተማኅፀነ ብኪ፤ በእንተ ሐና እምኪ፤ ወኢያቄም አቡኪ፣ ማኅበረነ ዮም ድንግል ባርኪ፡፡

ስም፡- ማርያም፣ እምነ፣ አርዌ፣ ነዐዊ፣ ሐና፣ ኢያቄም፣ አቡኪ፣ ድንግል፣

ከአመሠራረት አንጻር የስም ዓይነት

ነባር ስም፡- ማርያም፣ ሐና፣ ኢያቄም ፣እምነ

ምሥርት ስም፡- አርዌ፣ ነዐዊ፣ አቡኪ፣ ድንግል፣

ከአገልግሎት አንጻር

ስመ ተጸውዖ ፡- ማርያም፣ ሐና፣ ኢያቄም

የግብር ስም ፡- ነዐዊ

የስምን ምንነትና የስም ዓይነቶችን ለአሁኑ እንዲህ ዓይተናል፡፡ በሚቀጥለው ደግሞ በየወገኑ በየወገኑ ከፋልፈልን የስምን ዓይነት ለምሳሌ ተዘምዶን የሚያመለክቱ፣ የአካል ክፍሎችን የሚያመለክቱ፣ የቁሳቁስ ወዘተ በማለት ከምሳሌ ጋር እንመለከታለን፡፡ እስከዚያው ግን ውድ አንባቢ የሚከተለውን መልመጃ ሠርተው እንዲቆዩ እናሳስባለን፡፡

መልመጃ

በሚከተለው ምንባብ ውስጥ ያሉትን ስሞች አውጥተህ/ሽ የስም ክፍላቸውን ዘርዝር/ሪ

ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ታዐብዮ ነፍየ ለእግዚአብሔር ወትትሐሠይ መንፈስየ በአምላኪየ ወመድኃኒየ እስመ ርእየ ሕማማ ለአመቱ ናሁ እምይእዜሰ ያስተበፅዑኒ ኵሉ ትውልድ እስመ ገብረ ሊተ ኃይለ ዐቢያተ ወቅዱስ ስሙ ወሣህሉኒ ለእለ ይፈርህዎ ወገብረ ኃይለ በመዝራዕቱ ወዘረዎሙ ለእለ የዐብዩ ኅሊና ልቦሙ ወነሰቶሙ ለኃያላን እመናብርቲሆሙ አዕበዮሙ ለትሑታን ወአጽገቦሙ እምበረከቱ ለርኁባን ወፈነዎሙ ዕራቆሙ ለብዑላን ወተወክፎ ለእስራኤል ቊልዔሁ ወተዘከረ ሣህሎ ዘይቤሎሙ ለአበዊነ ለአብርሃም ወለዘርዑ እስከ ለዓለም፡፡

ስም………………………….

የስም ዓይነት

ስመ ተጸውዖ ………………..

ስመ ግብር …………………..

ስመ ባሕርይ…………………….

ስመ ተቀብዖ፡………………….