ስለጥቂቶች

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል

ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

የምጽአት ቀን መቃረብን ሥራችን ሲመሰክር

ክፉ ግብር ሚዛን  ደፍቶ በዓለም ግፍ ሲመነዘር

ኃጢአት የወለደችው የጥፋት ቀን እንዲያጥር

ጻድቃንን ባያስቀርልን ሁላችን በጠፋን ነበር

ሥጋን ለነፍስ አስገዝተው በበረኃ ጉያ የከተሙ

ቤተ ክርስቲያን ልጆች አሏት የሚማልዱ ለዓለሙ

ሥላሴም ምሕረትን ስለ እነርሱ ያደርጋሉ

ስለተመረጡ ጥቂቶች የጥፋት ቀናት ያጥራሉ

ጥላቻ ዘውድ ደፍታ ፍቅር በባርነት ብትገዛ

ሰላም በሞት ተዋጅቶ የጦር ወሬ ቢበዛ

ሕዝብ በሕዝብ ላይ ተነሥቶ ጥሙ በደም ሲረካ

በንጹሐን ዕንባ ምድር ታጥባ ስትፈካ

የበረኃ ፍሬዎች በቃየል መንገድ ያልሄዱ

ንጹሕ ጸሎትን ይሠዋሉ ፍቅርን ለእኛ ሊማልዱ

ሥላሴም ምሕረትን ስለ እነርሱ ያደርጋሉ

ስለተመረጡ ጥቂቶች የጥፋት ቀናት ያጥራሉ

ዲያብሎስ በብርሃን ራሱን ለውጦ

ክርስቶስ ነኝ እኔ ቢል በምትሐት ተለውጦ

አንደበት በሐሰት ተቃኝቶ እውነት ቦታ ብታጣ

የአበው ገድል ተሸሽጎ ክሕደት ገሃድ ቢወጣ

ማተባቸውን ጠባቂ ሰማዕታት ዛሬም አሉ

በሚያፈሱት ደማቸው የክሕደት እሳት ያጠፋሉ

ሥላሴም ምሕረትን ስለ እነርሱ ያደርጋሉ

ስለተመረጡ ጥቂቶች የጥፋት ቀናት ያጥራሉ

በብልጭልጭ ኑፋቄ ሰው ቢስት

አርምሞ ቢዋጥ በሐሰተኛ ነቢያት ትምክህት

እምነት በክሕደት ግዞት ቤት ብትሰደድ

ቢነሣ ቤተ ክርስቲያንን ላድስ የሚል ትውልድ

ዶግማና ሥርዓት ጠብቀው ለአሁኑ ትውልድ ያቀበሉ

ሊቃውንት ዛሬም አሉ ከአርዮስ ማዕድ ያልበሉ

ሥላሴም ምሕረትን ስለ እነርሱ ያደርጋሉ

ስለተመረጡ ጥቂቶች የጥፋት ቀናት ያጥራሉ

የምጽአት ቀን አመጣጥ ቢሆንም የሚያስፈራ

በተመረጡት የዕንባ ጸሎት ይቀልላል የዓለም መከራ

በሥጋቸው ጎስቁለው በመንፈስ ልዕልና የላቁ

ይህም ትውልድ ጻድቃን አሉት ከበደል ሥራ የራቁ

ሥላሴም ምሕረትን ስለ እነርሱ ያደርጋሉ

ስለተመረጡ ጥቂቶች የጥፋት ቀናት ያጥራሉ