ሰሙነ ሕመማት

‹‹በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸክሟል›› (ኢሳ.፶፫፥፬)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሚያዚያ ፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? የዐቢይ ጾም ወቅትንስ እንዴት እያሳለፋችሁ ነው? ይህ ጾም ጠላታችን ዲያቢሎስ ያፈረበት፣ ትዕቢት፣ ስስት፣ፍቅረ ንዋይ ድል የተደረጉበት፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጹሞ እንጾም ዘንድ ባርኮ የሰጠን ታላቅ ጾም ነው፡፡ ታዲያ ይህን ወቅት መልካም ሥራ እየሠራን፣ ለሀገር፣ ለቤተ ክርስቲያን እየጸለያችሁ እንዳሳለፋችሁ ተስፋ እናደርጋለን! መልካም!

ውድ የእግአብሔር ልጆች! ባለፉት ጊዜያት በዐቢይ ጾም ስለሚገኙ ሳምንታት ስያሜ ባስተማርናችሁ መሠረት በርካታ ቁም ነገሮችን ስንማማር እንደነበር ታስታውሳላችሁ አይደል? አሁን ደግሞ ስለ ሰሙነ ሕማማት ጥቂት ልናካፍላችሁ ወደድን፤ መልካም ቆይታ!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከሆሣዕና ማግሥት ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ድረስ ያሉ ዕለታት በቤተ ክርስቲያናችን የራሳቸው ስያሜና መታሰቢያ አላቸው፡፡ እነርሱንም በቅደም ተከተል እንመለከታለን፡፡

ሰሙነ ሕማማት፡- የሕማማት ሳምንት ማለት ነው፡፡ ጌታችን ከዲያቢሎስ ቁራኝነት ነጻ ሊያወጣን ወዶና ፈቅዶ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራን የሚያመለክት ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስ በልተው ከገነት በተሰደዱ ጊዜ ጠላታችን ሰይጣን ብዙ መከራ አደረሰባቸው፡፡ በኃጢአት ሠንሰለት ታሥረው በጨለማ ሕይወት ወደቁ፡፡ ለ ፭፻፭፻ (አምስት ሽህ አምስት መቶ) ዘመን በመከራ ኖሩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በገባልን ቃል ኪዳን ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፤ መከራ ተቀብሎ በመስቀል ተሰቅሎ አዳነን፡፡

ታዲያ ልጆች ይህን አዳምና ልጆቹ የኖሩበትን የመከራና የሥቃይ ዘመን በሳምንቱ ይታወሱበታል፡፡ ሰሙነ ሕማማት የሚባለው በዐብይ ጾም ከሠርክ ሆሣዕና ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንት ነው፡፡ (እስከ ዕለተ ዓርብ ይኸውም የስቅለት ቀን ድረስ ነው) ቀናቶቹም ሲቆጠሩ አምስት ቀን ተኩል ይሆናሉ፡፡ ይኸውም ምሳሌነቱ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ መጥቼ አድንሃለሁ ያለውን ነው፡፡ (ማቴ. ፲፪፥፴፱ አንድምታ ትርጓሜ) በእግዚአብሔር አንድ ቀን በእኛ አንድ ሽህ ዓመት በመሆኑ ከአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን በኋላ መጥቶ አድኖናል፡፡ እኛም በዚህ ሰሙነ ሕማማት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን ጽዋቶዎ መከራ እናስብበታለን፡፡

በሰሙነ ሕማማት ያሉ የሳምንቱ ዕለታት ስያሜዎች

ሰኞ መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ተራበ፤ ፍሬ ባገኝባት ብሎ ከመንደር ዳር የነበረችውን በለስ ተመለከተ፤ ፍሬ ስላጣባት ‹‹ለዘለዓለሙ ፍሬ አይገኝብሽ›› ብሎ ረገማት፡፡ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የዚህም ትርጉም ወይም ምሥጢሩ ከበለስ ፍሬ መሻቱ ከሰው ፍቅር ተርቦ ለማጣቱ ለመግለጽ ነው፡፡(ማቴ.፳፩፥፲፱፣ማር.፲፩፥፲፪-፲፬) እንግዲህ ከዚህ የምንማረው እግዚአብሔር አምላክ ከእኛ የመልካም ምግባር ፍሬ ለማግኘት እንደሚመጣ ነውና መልካም ፍሬን ልናፈራ ይገባል፡፡

ማክሰኞ የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች መጥተው ‹‹ከምድራውያን ካህናት አይደለህ፣ ከምድራውያን ነገሥታት ወገን አይደለህ ይህን የምታደርግ በምን ሥልጣን ነው›› ብለው ጠየቁት፤ እርሱም መልሶ ጠየቃቸው ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነው?›› እነርሱም ከሰማይ እንዳይሉ አያምኑበትም፤ ከምድር እንዳይሉ ሕዝቡን ፈሩና ‹‹አናውቅም›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹እኔም አልነግራችሁም›› ብሎ ረታቸው፡፡ (ማቴ.፳፩፥፲፫-፳፫፣ማር. ፲፩፥፳፯፣ሉቃ.፳፥፳፩-፵) ‹‹በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋልና ያዘዙአቸሁን ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ፤ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ፡፡ ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፤ እነርሱ ግን በጣታቸውስ እንኳ ሊነኩት አይወዱም›› በማለት እየወቀሰ ተናግሯል፡፡ በዚህም ዕለቱ የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል፡፡

ረቡዕ የምክር ቀን ይባላል፡፡

የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰብስበው ጌታችንን ኢየሱስን እንዴት እንደሚይዙትና እንደሚያስገድሉት ምክር የጀመሩበት ዕለት ነው፡፡ ነገር ግን የፋሲካ በዓል ቀርቦ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጠር እንዴት መያዝ እንዳለበት ሲጨነቁ ከጌታችን ደቀ መዛሙርት መካከል ይሁዳ ከምክራቸው በመቀላቀሉ ጥያቄአቸውን አቀለለላቸው፡፡ (ማቴ. ፳፯፥፫-፭፣ሉቃ. ፳፪፥፩-፪፣ማር.፲፬፥፩-፪) እንዲሁም እንዲሞት የወሰኑበት ዕለት ነው፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፫-፭)

ልጆች! ይህ ዕለት አንጽኦተ ቤተ መቅደስም ይባላል፡፡ ምክንያቱም በቤተ መቅደስ የተለያዩ ቁሳ ቁሳችን ሲሸጡ የተመለከታቸውን ሻጮች የገሠጸበትና የቤተ መቅደሱን ሥርዓት ያከበረበት ቀን መታሰቢያም ስለሆነ ነው፡፡ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ረቡዕን የምንጾምበት ምክንያት ጌታችን ላይ የሞት ፍረድ የተፈረደበት (የተወሰነበት) ስለሆነ ነው፡፡

ሐሙስ ጸሎተ ሐሙስ፣የምሥጢር ቀን፣ ሕጽበተ እግር ይባላል፡፡

በዚህች ዕለት ጌታችን በፍጹም ትሕትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ሕይወት ማሕተም የሆነውን ምሥጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው፡፡

ጌታችን በዚህ ዕለት ‹‹እናንተ ለወንድሞቻችሁ እንደዚህ አድርጉ›› ለማለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ‹‹እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለው፤ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤መልክተኛም ከላኪው አይበልጥም፤ ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ›› በማለት ትሕትናውን አሳይቷል፡፡ (ዮሐ.፫፥፮-፯) አባቶችንም በዚህ ዕለት ጌታችንን አብነት አድርገው በቤተ ክርስቲያን የምእመናኑን እግር ያጥባሉ፤እኛም ልጆች ከጌታችን ትሕትናን እንማራለን፤በሕይወታችን ታዛዦች፣ትሑት፣ቅን ልሆንና ከእርሱ እንድንማር ባስተማረን መሠረት አርአያውን ልንከተል ይገባል፡፡

ውድ የእገዚአብሔር ልጆች! በዚህ ዕለት ጉልባን ይበላል፤ ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላዊያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህንን ለማሰብ በስሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡ (ዘፀ.፲፪፥፴፱)

ዕለተ ዓርብ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥንተ ተፈጥሮ አዳምን በዕለተ ዓርብ ፈጥሮታል፤ ዳግመኛም በዚያው ዕለት አዳምን ለማዳን ራሱን መሥዋዕት ሆኖ ቀርቧል፤ በመስቀል ላይም ተሰቀለለት፡፡ በመሆኑም ከዕለተ ሐሙስ ምሽቱ ሦስት ሰዓት እስከ ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ አይሁድ በጌታችን ላይ ብዙ መከራን ያጸኑበት ሰዓት ሆኗል፡፡ ለዚህም ነው አንድ ቆራቢ ወይም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ለመቀበል የተዘጋጀ ሰው ለዐሥራ ስምንት ሰዓት የሚጾመው ምክንቱም ከሐሙስ ምሽት ሦስት ሰዓት እስከ ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ዐሥራ ስምንት ሰዓት ነውና፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ‹‹ሥጋዬን በበላችሁ ጊዜ ደሜንም በጠጣችሁ ሰዓት መከራዬንና ሞቴን ትናገራላችሁ›› ብሏልና፡፡ ከሐሙስ ሦስት ሰዓት እስከ ዓርብ ስድስት ሰዓት ብዙ መከራን ሲያፈራርቁበትና ሲያንገላቱት ከቆየ በኋላ ዓርብ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ መስቀል ላይ ቢሰቅሉት ሰባት ታላላቅ ተአምራት ተፈጽሟል፡፡ እነርሱም የፀሐይ መጨለም፣ የጨረቃ ደም መሆን፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ በመካከሉ ለሁለት መሰንጠቅ፣ የአለቶች መሰንጠቅ፣ የመቃብራት መከፈት፣ የከዋክብት መርገፍና የሙታን መነሣት ናቸው፡፡ (ማቴ.፳፯፥፵፭-፶፫) በዚህች ዕለት (በዕለተ ዓርብ) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐሥራ ሦስት ሕማማተ መስቀልን ተቀብሏል፡፡

ውድ የእገዚአብሔር ልጆች! ጌታችን ኢየሱስ የተቀበለው መከራ ተዘርዝሮ አያልቅም፤ ቃላትም አይገልጹትም፡፡ በዚህ ዕለት ለስቅለት መታሰቢያ አጎበር ተዘርግቶ ከርቤ እየታጠነ ስቅለቱን የሚመለከት ምንባባት ሲነበብና ሲሰገድ ይዋላል፡፡ በመጨረሻም ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ጥፋት ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቻወን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሣፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጣብ የሚደረግለት ሰው በሕማማቱ ወቅት የፈጸመውን በደል ወይንም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡ ይህ በስቅለት ቀን የሚፈጸም ሥርዓት ሲሆን ጥብጣብ ማለት ደግሞ ‹ቸብ ቸብ› ማድረግ ማለት ነው፡፡ በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምእመን ጀርባውን ቸብ ቸብ መደረጉ የጌታችንን ግርፋት ያስታውሳል፡፡ (ማቴ. ፲፯፥፲፮-፷፮) ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕለተ ስቅለት ሲሰግድ፣ ሲጸልይ እንዲሁም ሲያነብ ከዋለ በኋላ ሰርሆተ ሕዝብ (የሕዝብ መሰናበቻ) ይሆናል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው በሰሙነ ሕማማት የምናስበው የብሉይ ኪዳን ጊዜ የነበረውን የመከራ ዘመን ነው፡፡ በመሆኑም ያንን ለማስታወስ በእነዚህ ቀናት የማይከናወኑ የአምልኮ ሥርዓቶች አሉ፡፡

  • መስቀል መሳለም የለም፤ (ጌታችን በመስቀል ተሰቅሎ የሰላም አርማችንንና ጠላታችን ሰይጣንን ድል የምናደርግበት ቅዱስ መስቀልን ለእኛ ከመስጠቱ በፊት የነበረውን ጊዜ ለማስታወስ በሰሙነ ሕማማት መስቀል አንሳለምም፡፡)
  • ቅዳሴ አይቀደስም (ምሴተ ሐሙስን አስመልክቶ ግን በዕለተ ሐሙስ ቅዳሴ ይቀደሳል)
  • ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ጸሎተ ፍትሐት አይደርስለትም፡፡ (አስቀድሞ የሆሣዕና ዕለት ለክርስቲያን ሁሉ ፍትሐት ደርስለታል)
  • በመሳሳም ሰላምታ አይገለጽም፤ ይሁዳ ጌታን በአይሁድ ለማስያዝ ‹‹እኔ የምስመው እርሱ ነው ያዙት›› ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው፡፡ ስለዚህ ይሁዳ ጌታችንን በመሳም አሳልፎ እንደሰጠው ለማዘከር ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰላምታ ልውውጥ የለም፡፡ (ማቴ.፳፮፥፵፰)

ቅዳም ስዑር (ሹር) የተሻረ ሰንበት ማለት ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ደቀ መዛሙርቱ ‹‹የጌታችንን ትንሣኤ ሳናይ እህል አንቀምስም›› ብለው በአክፍሎት ስለጾሙበት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ነፍሳት ከሲኦል ወጡ፤ አንቀጸ ገነት፣ ርስት ገነት ተከፈተልን፡፡ አባታችን አዳም ከፈጣሪ ታረቀልን በማለት በመስቀሉ ሰላምን አደልን እያልን የተድላና የደስታ ምልክት ወይም መግለጫ ቄጠማ ይዘን የምሥራች እንባባላለን፡፡ (ግብረ ሕማማት)

በቀዳሚ ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል (ቃለ ዓውዲ) እየመቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ አገሀደ ትንሣኤሁ፤ በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፤ በትንሣኤውም ገለጠልን›› የሚለውን ያሬዳዊ ዜማን በመዘመር፣ ጌታችን በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመን ይሰጣሉ፡፡ ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቁ ምእመናን ብሥራት ይሆናሉ፡፡ ምእመናኑም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሠቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾክ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡ (ጾመ ድጓ፤ ቀዳም ስዑር ዜማ)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ስለ ሰሙነ ሕማማት በጣም በአጭሩ በዚህ መልኩ አቅርበንላችኋል፤ ይህን ወቅት የጌታችንን መከራ ሞቱንና ያደረገልንን ሁሉ እያሰብን እኛም ለሰዎች መልካም በማድረግ፣ እየሰገድንና አብዝተን እየጸለይን እናሳልፈው፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር በረከቱን ያድለን፤ ለብርሃነ ትንሣኤው ያድርሰን! ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!