ርእሰ ዐውደ ዓመት

እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ አሸጋገረን!

ዕንቁጣጣሽ!

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ጳጉሜን ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የዕንቁጣጣሽ በዓል የሚከበረው የዓመቱ መጀመሪያ በሆነው በወርኃ መስከረም ነው፤ መስከረም ማለት የወር ስያሜ ሲሆን ከረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ እና አንዱ ዓመት አልፎ ሌላው ሲተካ ያለው የመጀመሪያ ወር፣ ሌሊት አልፎ ቀኑ ሲተካ፣ ነጋ እንደሚባለው ክረምት አልፎ በጋ ሲተካ መስከረም ጠባ ተተካ ማለት ነው፡፡ አንድም የመስከረም ወር የቀኑ እና የሌሊቱ ሰዓት እኩል የሚገጥምበት ወር ነው፤ ሌሊቱ አልፎ ቀኑ ሲተካ “እንደምን አደራችሁ?” እንደሚባለው ክረምቱ አልፎ በጋው ሲተካ “እንደምን ከረማችሁ?” ይባላልና፤ ይህች ወር ምድር ለምልማ አብባ የምትታይበት ወር ነው፤ በዚህ ወር መጀመሪያ በሚከበረው በዓል የአጽዋማቱ የበዓላቱ ዐዋጅ የሚታወጅበት ዕለት በመሆኑ ርእሰ ዐውደ ዓመት ይባላል፡፡

ወርኃ መስከረም የዓመቱ መጀመሪያ የሆነበት ምክንያት የአዳም ዐሥረኛ ትውልድ የሆነው ኖኅ የጥፋት ውኃ መጉደሉን ትመለከት ዘንድ የላካት ርግብ የጥፋት ውኃ መጉደሉን ለማብሠር  ለምለም ቄጤማ ይዛለት የመጣችው በዚህ ወር ነበርና ክረምቱ አልፎ በጋው ሲተካ ውኃው ጎርፉ ሲጎድል ያለው  ወርኃ መስከረም የዓመቱ መጀመሪያ ሆነ፡፡ (ዘፍ. ፰፥፰) አንድም ኖኅ ለልጆቹ በዕጣ ምድሪቱን ሲያከፋፍል ለካም የደረሰው ምድረ አፍሪካ ነበርና በዕጣው መሠረት ወደዚህ ምድር የመጣው ምድር በአረንጋዴ ዕፅዋት ተውባ  በአበቦች ደምቀት ተሽቈጥቁጣ በነበረበት በዚህ  በወርኃ መስከረም  ነበር፤ እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት የወጡበትን  ወር (ወረኃ ሚያዝያ) የዓመት መጀመሪያ አድርገው እንዳከበሩት ካምና ልጆቹም መጀመሪያ ወደ ምድሪቱ የገቡባትን ወርኃ መስከረም የዓመቱ መጀመሪያ አደረጓት፡፡

የዘመን መለወጫ ዕለት በዚህ ስያሜ መሰየሙ ምድር በክረምቱ ዝናብ ረስርሳ፣ ድርቅ ተወግዶ፣ በአረንጋዴ ዕጽዋት ተውባ፣ ሜዳው ሸለቆው ተራራው በአበቦች አጊጦ ተንቆጥቁጦ፣ ምድር አምራና ደምቃ የምትታይበት ዕለት ስለሆነ ወቅቱ (ዕለቱ) ዕንቁጣጣሽ ተብሏል፡፡ አንድም ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ የጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞንን ዝና ሰምታ ኢየሩሳሌም ተጉዛ ነበርና ጉብኝቷን ፈጽማ ስትመለስ ዕንቁ ለጣትሽ (ለጣትሽ ዕንቁ) በማለት የዕንቁ ቀለበት ስጦታ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን አበርክቶላት ስለነበር ዕንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜ ከዚያ እንደመጣ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡

ይህ ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ በመባልም ይታወቃል፤ በብሉይ ኪዳን ፍጻሜ እና በሐዲስ ኪዳን መግቢያ ላይ በሰማዕትነት ያለፈውን መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ለማዘከር አበው ሊቃውንቱ  በጨለማ የተመሰለው የክረምቱ ጊዜ አብቅቶ በብርሃን የተመሰለው የበጋ ወቅት የሚተካበትን ዕለት ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ብለውታል፡፡

በዚህ ወቅት ወጣት ሴቶች ባህላዊ ልብስ በመልበስ ለምለም ቄጤማ ከአደይ አበባ ጋር በመያዝ በየሥፍራው እየዞሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላልፋሉ፤ የፈጣሪን ድንቅ ሥራ ይመሠክራሉ፤ በቸርነቱ ዓመታትን የሚያፈራርቅ ጌታን ያመሰግናሉ፡፡ ፈጣሪ በቸርነቱ ዓመታትን አፈራርቆ፣ በክረምቱ ወቅት ዝናመ ምሕረቱን አውርዶ፣ ምድርን በበረከቱ ጎብኝቶ፣ ድርቀቷን  በልምላሜ ለውጦ የተዘራው ሰብል ከቅጠል ወደ አበባነት የሚለውጥበት ወቅት በመሆኑ   ወጣቶቹ በዝማሬ ‹‹አበባ አየህ ወይ፤ አበባ አየሽ ወይ…›› በማለት ያውጃሉ፤ የተዘራው ዘር በቅሎ ከቅጠል ወደ አበባ መድረሱን በመግለጥ የፈጣሪን ድንቅ ሥራ ይመሰክራሉ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በዝማሬው ፈጣሪ ይህችን ዕለት እንዴት እንደሚያስውባት እና ቸርነት ምሕረቱን እንዲሁም ገበሬው ፈጣሪን አምኖ የዘራባትን ዘር ምድር በኪነ ጥበቡ እንዴት አድርጋ እንደምትመልስና የዓመቱን ሰብል እግዚአብሔር እንደሚባርክ እንዲህ ሲል ገልጾታል፤ ‹‹…ምድርን ጎበኘኻት፤ አጠጣሃትም፤ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተሞላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ፤ እንዲሁ ታሰናዳለህና ትልሟንም ታረካለህ፤ ቦይዋን ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፤ ቡቃያዋንም ትባርካለህ፤ በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ፤ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል፤ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፤ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ፤ ማሰማሪያዎች መንጎችን ለበሱ፤ ሸለቆዎችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮሃሉ ይዘምራሉም፡፡›› (መዝ. ፷፬፥፱)

በዝናብ አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ፣ በነፋስ አሳድጎ ፍጥረቱን የሚመግብ እግዚአብሔር ዕድሜ ለንስሓ ዘመን ለፍስሐ የሰጠን መልካም እንድንሠራበት ነውና በመጪው ዘመን የትላንት ስሕተታችንን አርመን፣ የተጣላን ታርቀን፣ የበደልን ክሰን፣ ያለው ለሌለው እያካፈለ ለመኖር ልናቅድ ይገባናል፤ ለምድራዊ ኑሯችን የምንተገብራቸውን እንደምናቅድ ለመንፈሳዊ ሕይወታችንም ልናስብ ይገባል፤ የዘመናት ጌታ ብርሃንና ጨለማን፣ በጋና ክረምትን የሚያፈራርቅ ዘመንን፣ በዘመን የሚተካ የሠራዊት ጌታ የእስራኤል ቅዱስ ልዑል እግዚአብሔር ዘመነ ማርቆስን  (፳፻፲፬ ዓ.ምን አሳልፎ) ለዘመነ ሉቃስ (፳፻፲፭ ዓ.ም) አድርሶናልና ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን! ዝናመ ምሕረቱን፣ ጠለ በረከቱን ለምድር ለግሶ፣ አለስልሶ ባዶነቷን በሰብል፣  በልምላሜ፣ በጽጌአት ውበት አስጊጦ፣ እክለ በረከቱን ለእኛ የሚያድል ፈጣሪ ዘመኑን የፍቅር፣ የሰላም፣ የምሕረት ዘመን ያድርግልን!  የተሰጠንን ዘመን መልካም ልንሠራበት ይገባል! በስንፍና ያሳለፍነው ጊዜ ይብቃን! በአዲስ ዘመን በአዲስ ዕቅድ፣ በአዲስ መንፈስ ለሥራ እንነሣ! ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ እንዲህ ይለናልና ‹‹የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም፣ በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለ ልክም በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና፡፡››

መልካም አዲስ ዓመት!!!