በዓለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ

ጳጉሜን ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበት ዕለት መስከረም ሁለት የተከበረ ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጥምቁን ክብር ‹‹እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም” በማለት መሥክሮለታል፡፡ (ማቴ. ፲፩፥፲፩፣ ሉቃ ፯፥፳፰)

በዚህም መሠረት ቅዱስ ገድሉ ላይ እንደተጠቀሰው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጥምቁ ዮሐንስ ዓሥር እጅግ አስደናቂ ቃል የድኅነት ኪዳኖችን እንደገባለት ከቅዱስ ገድሉ ላይ ያገኘነውን ቀጥሎ እንናገራለን፡፡ አስቀድሞ መሐላ መማል ፈጽሞ ተገቢ እንደልሆነ፡- ‹‹የኄሮድያዳ ልጅ ንጉሥ ኄሮድስን በዘፈኗ በጣም አድርጋ ስላስደሰተችው እርሱም በተራው ሊያስደስታት ፈለገ፡፡ እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ይሰጣት ዘንድ በሕዝቦቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት እንዳይከዳት በጽኑ ቃልኪዳን ማለላት፡እንዲህም እያለ የፈለግሽውን ጠይቂኝ፣ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁ ምን ላድርግልሽ? እያለ በመሐላ ባላት ጊዜ በእናቷ ምክር የዮሐንስን አንገት ቆርጦ ይሰጣት ዘንድ ለመነችው፡፡ ንጉሥ ኄሮድስም ይህን ልመና ከአፏ በሰማ ጊዜ የፈለግሽውን እሰጥሻለሁ ብሎ በሕዝቡ ፊት ስለማለ ለሰው ይምሰል አዘነ፤ ተከዘ፡፡ ኀዘኑም ስለ ዮሐንስ መሞት አይደለም፤ ዮሐንስን ሕዝቡ ይወደው ስለነበር እነርሱን ስለ መፍራቱና መሐላ ምሎ ከዳ እንዳይባል ነው እንጂ፡፡ ስለ ዮሐንስ አዝኖ ቢሆን ኖሮ ቀድሞውንም በግፍ እንዲታሰር ባላደረገው ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ ወታደሮች ሰይፍ ይዘው የዮሐንስን አንገት ይቆርጡ ዘንድ ወደ መኅኒ ቤት ሄዱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የኄሮድስ ጭፍሮች ሊገድሉት እንደመጡ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ስላወቀ ከጨለማው ቤት ውስጥ አንገቱን በመስኮት አውጥቶ እንደሚመቻቸው አድርጎ ጠበቃቸው፡፡ የኄሮድስን ቃል እንዳያቃልሉ ጭፍሮቹም የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስን አንገት ስለ መሐላው ቆረጡት፡፡ በመሐላ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ኄሮድስ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ባላስገደለው ነበር፡፡ ስለዚህ ‹‹ወንድሞቸ እኅቶች ሆይ! እናንተም ከመሐላ የተነሣ መፍራት ይገባችኋል፤ ፈጽማችሁም መማል የለባችሁም፡፡›› ስካርና ዘፈን ከሚገኙበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፤- ‹‹ወንድሞችና እኅቶች ሆይ! አለ ልክ መብላና መጠጣት ካለበት ቦታ እግዚአብሔርን መበደል፣ ማስቀየምና ማስቆጣት ይገኝበታል፡፡ ስካር ከሚገኝበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፡፡ ስካርና ዘፈን ከሚገኝበት ቦታ የእግዚአብሔር መቅሠፍት የፈጣሪያችን ቁጣና በቀል ይፈጸምበታልና፡፡ እናንተ ሕዝበ ክርስቲያኖች ሆይ! ከስካር፣ ከዘፈንና ከዝሙት መራቅ ይገባችኋል፡፡ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ያስገደለው ዘፈን፣ ስካርና የዘማ ፍቅር መሆኑን ልብ በማለት መገንዘብ አለባችሁ፡፡››

መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለመጥምቁ ዮሐንስ የሰጠው ልዩ ቃልኪዳን የሚከተሉት ናቸው፤

፩. ‹‹…ከሚበላውና ከሚጠጣው ከፍሎ በስምህ ለነዳያን ለሰጠ ሥጋዬን ደሜን እሰጠዋለሁ፤ በሃይማኖት ጸንቶ፣ በምግባር ኖሮ ሥጋዬን ደሜን እንዲቀበል አደርገዋለሁ፤ ለሥጋዬ ለደሜ የሚያበቃ ሥራ እንዲሠራ አደርገዋለሁ፤ እስከ ሃምሣ አምስት ትውልድም ድረስ እምረዋለሁ፡፡››

፪. ‹‹ሰው ሁሉ ወደ ሥጋዊ ተግባርም ሆነ ወደ መንፈሳዊ ተግባርም ቢሆን ሲሄድ ይህ የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ነው ብሎ ቅጽሩን፣ ገራገሩን ቢሳለም የተሳለመው ሰው ቢኖር እኔ መንበረ መንግሥቴን አሳልመዋለሁ፡፡ የገድልህንም መጽሐፍ የተሳለመ ቢኖር እኔ መንበረ መንግሥቴን አሳልመዋለሁ፡፡››

፫. ‹‹ከቤተ ክርስቲያንህ የተቀበረውን ሰው ከመከራ ሥጋ፣ ከሲኦል እሳት አድነዋለሁ፤ እኔ ከተቀበርኩበት ኢየሩሳሌም ሄዶ ከእኔ መቃብር ውስጥ እንደተቀበረ አደርገዋለሁ፡፡››

፬. ‹‹ቤተ ክርስቲያንህ ከታነፀችበት፣ ስምህ ከሚጠራበት፣ መታሰቢያህ ከሚደረግበት፣ የተአምርህ ዜና ከሚነገርበት፣ የገድልህ መጽሐፍ ተነቦ ከሚተረጎምበት፣ እኔ በረድኤት ከዚያ እገኛለሁ፤ ከዚያ ቦታ አልለይም፡፡ የገድልህ መጽሐፍ ከሚተረጎምበት ቦታ አጋንንት አይደርሱም፤ ከዚያ ቦታ ሰይጣናት ይርቃሉ፡፡››

፭. ‹‹የገድልህ የተአምርህ መጽሐፍ የተነበበትን ውኃ እኔ እንደተጠመቅሁበት እንደ ማየ ዮርዳኖስ አደርገዋለሁ፡፡ የገድልህ መጽሐፍ በተነበበት ውኃ የተጠመቀበት ሰው ቢኖር የሰማንያ ዓመት ኃጢአቱን አስተሠርይለታለሁ፤ ወንዱን የአርባ ቀን፣ ሴቷን የሰማንያ ቀን ሕፃን አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ በተጠመቅሁበት ማየ ዮርዳኖስ እንደተጠመቀ ሆኖለት ከኃጢአቱ ይነጻል፡፡››

፮. ‹‹ሰውም ሆነ እንስሳ ቢታመም በጽኑ እምነት ይደረግልኛል ብሎ አምኖ ያለ ጥርጥር ውኃ አቅርቦ የገድልህን መጽሐፍ በላዩ ላይ አንብቦ የተነበበበትን ውኃ ቢታጠብበት ወይም ቢጠጣ ያለ ጥፋት ፈጥኖ ከደዌው ይፈወሳል፡፡››

፯. ‹‹የገድልህ መጽሐፍ የተነበበትን ማየ ጸሎት በቤቱ ውስጥ ቢረጭ ከዚያ ቤት በረከቴን እመላበታለሁ፤ ተድላን፣ ደስታን፣ ጥጋብን በዚያ ቤት አሳድራለሁ፤ እስከ ዘለዓለም ድረስ በቤቱ ውስጥ የእህል መታጣትና ረኃብ፣ የውኃ ጥማት፣ ተላላፊ በሽታ አይገባበትም፤ ፈጽሜም አላመጣበትም፡››

፰. ‹‹ደስ ብሎት በተድላ በደስታ በዓለህን ያከበረውን ሰው ሁሉ በቅዱሳን መላእክቶቼና በሰማያዊ አባቴ በአብ ማሕያዊ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ ፊት እኔ ደስ አሰኘዋለሁ፡፡ እነሆ እኔም ከበዓልህ ቦታ ላይ አልለይም፤ በዓልህንም ከሚያከብሩት ጋር እኔ አብሬያቸው እቀመጣለሁ፤ እስከ ሃምሣ አምስት ትውልድም እምረዋለሁ፡፡››

፱. ‹‹ለቤተ ክርስቲያንህ ዕጣን፣ ሻማ፣ ጧፍ፣ ልብሰ ተክህኖ፣ መጎናጸፊያ፣መጋረጃ፣ ነጭ ስንዴ የሰጠ ሰው ቢኖር እስከ ሃምሣ አምስት ትውልድም ድረስ እምረዋለሁ፡፡››

፲. ‹‹ሥጋዬን ደሜን መቀበል ያልተቻለው ሰው ቢኖር ለመታሰቢያህ ዝክር ከተደረገው ፍርፋሪ ይቅመስ፤ ሥጋዬን ደሜን እንደተቀበለ እኔ አደርግለታለሁ፡፡ ፍርፋሪውን ባያገኝ እንጀራውና ዳቦው የተበላበትን ገበታ፣ ጠላው የተጠጣበትን ጽዋ በምላሱ ይላስ፤ እኔ ኢየሱስ ቃሌ የማያብለው ሥጋዬን ደሜን እንደተቀበለ አደርግለታለሁ፤ ስለ እምነቱ ሥጋዬን ደሜን ለመቀበል የሚያበቃውና እውነተኛውን ምግባር የጽድቅ ሥራ እንዲሠራ አደርገዋለሁ፡፡››

ቅዱስ ዮሐንስ በምልጃው አይለየን፤ ረድኤትና በረከቱ ይደርብን፤  አሜን!

ምንጭ፡-ገድለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ (በጎል ሰከበ ደብረ መንክራት ሚጣቅ ቅዱስ አማኑኤል ማኅበረ ሰላም አንድነት ገዳም ያሳተመው፤፳፻፫ .)