ሙሻ ዘር

ክፍል ሁለት

መምህር በትረማርያም አበባው

 ነሐሴ፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም  

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፉት ክፍሎች ዘመድ ሙሻ ዘርን እና ባዕድ ሙሻ ዘርን ሰዋስውን ከሰዋስው ሳቢን ከተሳቢ እያናበቡ ዘጠኝ አገባባትን ሲያወጡ አይተናል። ከዚያ ቀጥለን ደግሞ ዛሬ የመጨረሻውን ክፍል እናያለን። መልካም ቆይታ!

ሙሻ ዘር ከሚሆኑ ቀለማት አምስቱ ማለትም ቀዳማይ አንቀጽ፣ ካልዓይ አንቀጽ፣ ሣልሳይ አንቀጽ፣ ዘንድ አንቀጽ እና ቦዝ አንቀጽ ዘርዝረው ሳይናበቡ አገባባትን ያመጣሉ። ሲመጡም አንድና ብዙ ሴትና ወንድ ሩቅና ቅርብ አይለዩም። ቀጥለን በምሳሌ እንመልከተው። ሄሮድስ በልዖ ርእሶ ቢል ሄሮድስ ራሱን በላ ማለት ነው። ይህ ባዕድ በራሱ ይባላል። ባዕድ ያሰኘው በልዖ በላው ተብሎ መተርጎም የነበረበትን በላ ተብሎ በመተርጎሙ ነው። በተጨማሪም በዐሥሩ መራሕያን በመተርጎሙ ነው።

ቀዳማይ አንቀጽ

በይኔሁ፣ ሎቱ ሲወጡ:- አምላክ ፈጠሮ ኪያኪ ሔዋንሀ ይላል፤ ትርጉሙ ለእርሱ/ስለእርሱ አንቺን ሔዋንን አምላክ ፈጠረ ማለት ነው። አስተውሉ! ፈጠሮ ያለው ዝርዝር ፈጠረው ተብሎ ከመተርጎም ይልቅ ፈጠረ ተብሎ ተተርጉሟል። ባዕድ ያሰኘውም ይህ ነው።

ቦቱ፣ላዕሌሁ ሲወጡ:-ንጉሥ አንበሮ ኪያየ አክሊለ ይላል፤ ትርጉሙ በእርሱ/በእርሱ ላይ እኔን አክሊል ንጉሥ አስቀመጠ ማለት ነው።

እምኔሁ ሲወጣ:-አብ አፍቀሮ ንዑሳነ ሕፃናተ ይላል፤ ትርጉሙ ከእርሱ ትንንሽ ሕፃናትን አብ ወደደ ይላል።

ከማሁ ሲወጣ:-ንጉሥ አክበሮ ሠናያተ አንስተ ይላል፤ ትርጉሙ እንደ እርሱ የሚያምሩ ሴቶችን ንጉሥ አከበረ ማለት ነው።

ምስሌሁ ሲወጣ:-ንጉሥ አቅረቦ ምሁረ ኪያክን አንስተ ጊዜ ማዕድ ይላል፤ ትርጉሙ ከእርሱ ጋራ በማዕድ ጊዜ እናንተን ሴቶችን ምሁሩን (የተማረውን) ንጉሥ አቀረበ ይላል።

ኀቤሃ፣ እስከኔሃ ሲወጡ:- ንግሥት አብጽሐታ ዘተለወት አመተ ይላል ትርጉሙ እስከ እርሷ/ወደ እርሷ የተከተለች የሴት አገልጋይን ንግሥት አደረሰች ይላል።

ካልዓይ አንቀጽ:-

ከላይ ያየነውን ቀዳማይ አንቀጽ መስሎ የሚሄድ ሲሆን ልዩነቱ በቀዳማይ ይተረጎም የነበረውን በካልዓይ እየተረጎሙ መሄድ ነው። ለምሳሌ ከላይ ከማሁ ሲወጣ በቀዳማይ ንጉሥ አክበሮ ሠናያተ አንስተ ያለውን ንጉሥ ያከብሮ ሠናያተ አንስተ ብሎ ማውጣት ማለት ነው። ትርጉሙ እንደ እርሱ የሚያምሩ ሴቶችን ንጉሥ ያከብራል ተብሎ ይተረጎማል። ሌሎችንም አገባባት በዚህ መልኩ እያደረጉ ማውጣት ነው።

ሣልሳይ አንቀጽ (ትእዛዝ አንቀጽ)

ይህም አካሄዱ በቀዳማይ አንቀጽ ካየነው ጋር ይመሳሰላል። ለምሳሌ በይኔሁ/ሎቱ ሲወጡ ንጉሥ ይሞቅሖሙ ኪያሁ ፈያተ ቢል ትርጉሙ ስለእርሱ/ለእርሱ እርሱን ሽፍታውን ንጉሥ ይሰር ይላል። ሌላውንም በዚህ መልኩ ማውጣት ነው።

ዘንድ አንቀጽ

ዘንድ አንቀጽም በቀዳማይ አንቀጽ ካየነው ጋር ይመሳሰላል። ልዩነቱ ዘንድ መሆኑ ብቻ ነው። ለምሳሌ ለእግዚአብሔር ይምሐሮሙ ኀጥአነ ቢል በአገባብ በይኔሁ/ሎቱ ሲወጣ ለእርሱ/ስለእርሱ ኀጥአንን ይምር ዘንድ ለእግዚአብሔር ይገባል ማለት ነው።

ቦዝ አንቀጽ

ይህም ልዩነቱ ቦዝ መሆኑ እንጂ ከላይ ካየናቸው ጋር ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ ነቢያት አእሚሮሃ ምጽአተ ክርስቶስ ተነበዩ ቢል ትርጉሙ በይኔሁን/ሎቱን ሲያወጣ ለእርሱ/ስለእርሱ የክርስቶስን መምጣት ነቢያት አውቀው ተናገሩ ይላል።

ዘመድ ዝርዝር

ዘመድ ዝርዝር የሚባለው በየራሱ የሚዘረዘረው ነው። ለምሳሌ አምላክ ሞቶ ለአዳም ሲል በይኔሁ/ሎቱ ይወጣሉ ትርጉሙ ስለእርሱ/ለእርሱ ለአዳም ስለ አዳም አምላክ ሞተ ማለት ነው።

ቦቱ ሲወጣ:-አምላክ ተሰቅሎ ለመስቀል ይላል፤ ትርጉሙ በእርሱ በመስቀል አምላክ ተሰቀለ ማለት ነው።

እምኔሁ ሲወጣ:-ነጋዲ ወፅኦ ለቤት ከእርሱ ከቤቱ ነጋዴ ወጣ ይላል።

ምስሌሆሙ፣ ከማሆሙ ሲወጡ:- አምላክ ተሰቅሎሙ ለፈያት ይላል፤ ትርጉሙ እንደነርሱ ከእነርሱ ጋራ አምላክ ተሰቀለ ማለት ነው።

ኀቤሃ፣እስከኔሃ ሲወጡ:- ገብርኤል ተፈነዋ ለማርያም ይላል፤ ትርጉሙ እስከ እርሷ ወደእርሷ ወደማርያም እስከ ማርያም ገብርኤል ተላከ ማለት ነው።

ባዕድ ቅጽል

አገባቡ ዝርዝሩ ለባለቤት አንቀጹ ለተሳቢ ሲሆን ባዕድ ቅጽል ይባላል። አንድና ብዙ፣ ሴትና ወንድ፣ ሩቅና ቅርብ ሳያናግር ያናገረ ይመስላል። አንቀጽን፣ ተሳቢን እና አገባብን ይዘረዝራል።

አንቀጽ ሲዘረዝር:– ማርያም እንተ አክበሩ ሥላሴ አበው ይላል፤ ትርጉሙ ሥላሴ አባቶች ያከበሯት ማርያም ማለት ነው። ብእሲ ዘአክበረት ብእሲት ይላል፤ ትርጉሙ ሴት ያከበረችው ሰው ማለት ነው። መላእክት እለፈጠርከ አንተ ወልድ ይላል፤ ትርጉሙ አንተ ወልድ የፈጠርካቸው መላእክት ማለት ነው።

የተሳቢ ዝርዝር:- ማርያም ዘአክበሩ አበዊሃ ይላል፤ ትርጉሙ አባቶቿ ያከበሯት ማርያም ማለት ነው። መላእክት እለ ፈጠርከ አንተ እግዚኦሙ ይላል፤ ትርጉሙ አንተ ጌታቸው የፈጠርካቸው መላእክት ማለት ነው።

የአገባብ ዝርዝር:- አበው እለ ከብረት ማርያም ይላል፤ትርጉሙ ማርያም የከበረችላቸው አባቶች ማለት ነው። መላእክት እንተ ተፈጥሩ ወልድ ይላል፤ ትርጉሙ መላእክት የተፈጠሩለት ወልድ ማለት ነው። ብእሲ ዘተፈጥረት ብእሲት ይላል። ሴት የተፈጠረችለት ሰው (ወንድ) ማለት ነው።

እነዚህ በግልጸ ዘ ሲነገሩ ነው። በሳድስ ቅጽል ብቻ ሲነገሩ ደግሞ የሚከተለውን ይመስላሉ።

አንቀጽ ሲዘረዝር:-ማርያም ወይን ትክልተ ሥላሴ ገባእት ፈረየት ፍሬ ይላል ትርጉሙ ሥላሴ ምንደኞች የተከሏት/የተከላችኋት/የተከልናት ማርያም ወይን አፈራች ይላል።ወይም ሥላሴ ምንደኞች የተከሉሽ ማርያም ወይን አፈራሽ ይላል።ወይም ሥላሴ ምንደኞች የተከልንሽ ማርያም ወይን አፈራሽ ይላል። ሥላሴ ምንደኞች የተከሉኝ/የተከላችሁኝ ማርያም ወይን ፍሬን አፈራሁ ይላል።

አገባብ ሲዘረዝር:-ድንግል ንግሥት ወልድ ይላል፤ትርጉሙ ወልድ የነገሠላት ድንግል/ ወልድ የነገሥኩላት ድንግል/ ወልድ የነገሠልሽ ድንግል/ ወልድ የነገሠልኝ ድንግል/ ወልድ የነገሥክልኝ ድንግል/ ወልድ የነገሥኩልሽ ድንግል/ ወልድ የነገሥክላት ድንግል ይላል።

ተሳቢ ሲዘረዝር:– ጴጥሮስ መሀረ አርድእት ወንጌለ ይላል፤ ትርጉሙ ጴጥሮስ ተማሪዎቹ ወንጌልን አስተማረ ይላል።

የተደራጊ አንቀጽ ከአድራጊ ከአስደራጊ ተናቦ በአድራጊ በአስደራጊ አመል ይፈታል። ለምሳሌ አምላክ ተሰቃሌ ይሁዳ ሲል ትርጉሙ ይሁዳ የሰቀለው አምላክ ይሆናል። አምላክ ተሰቃሌ ይሁዳ አይሁደ ሲል ይሁዳ አይሁድን ያሰቀለው አምላክ ተብሎ ይተረጎማል።

የአድራጊ አንቀጽ ከአስደራጊ ተናቦ በአስደራጊ አመል ይፈታል። አምላክ ሰቃሌ ይሁዳ አይሁደ ይላል፤ ትርጉሙ ይሁዳ አይሁድን ያሰቀለው አምላክ ማለት ነው።

የተደራራጊ አንቀጽ ከአደራራጊ ተናቦ በአደራራጊ አመል ይፈታል ምሳሌ አምላክ ተሰቃሌ ይሁዳ ምስለ አይሁድ ይላል። ትርጉሙ ይሁዳ ከአይሁድ ጋር ያሰቀለው አምላክ ማለት ነው።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!