መልካም አስተዳደር እና ቤተ ክርስቲያን

ክፍል ሦስት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ታኅሣሥ ፳፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

፫. መልካም አስተዳደር እጦት በቤተ ክርስቲያን፡-

የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች! እንዴት ሰነበታችሁ? በክፍል ሁለት ጽሑፋችን ‹‹የቤተ ክርስቲያን መልካም አስተዳደር እጦት መንሥኤዎች›› በሚለው ርእስ ከተራ ቁጥር አንድ እስከ አምስት የዘረዘርናቸውን ምክንያቶች ታስታውሳላችሁ፡፡ በዚህ ክፍልም ከዚያው የቀጠለውን ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም ንባብ!

፮ኛ. በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሹመት ከካህናት ይልቅ ለመነኮሳት ቅድሚያ መሰጠቱ

ይህ አሠራር ሹመት ፈላጊዎች እንዲበዙ፣ ገዳማዊ ሕይወት ቦታ እንዲያጣ፣ የሹመት ፍቅር የወደቀባቸው መነኮሳት ለመሾም ሲሉ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት እንዲመዘበሩና ሲሞናዊነት በቤተ ክርስቲያን እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡

ሲሞናዊነት የእግዚአብሔርን ጸጋ በገንዘብ ለመግዛት መሞከር ነው፡፡ (የሐዋ ሥራ ፰፥፱) ጵጵስና እና ቁምስና ለመሾም ከፖለቲካ የሚወግኑ፣ የብሔር አጀንዳ የሚያነሡ፣ ጉቦ የሚከፍሉ  ከደላላ ጋር የሚደራደሩ፣ ለመሾም እንቅፋት ናቸው ብለው ያሰቧቸውን ወንድሞቻቸውንና መንፈሳዊ ልጆቻቸውን ሲከሱ የሚውሉ፣ በየጉራንጉሩ የሐሰት ክስ ሲያዘጋጁ የሚውሉ በርካቶች ተፈጥረዋል፡፡

መነኩሴ ሥልጣንን መሻት እንደሌለበት በፍትሕ መንፈሳዊ  ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ጌታ በወንጌል ‹‹ፍጹም ልትሆን ትወዳለህን? ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለነዳያን፣ መጽውተህና ተከተለኝ››፡፡ (ማቴ.፲፱፥፳፩) ያለውን ቃል ሰምቶ ፍጹም ሊሆን ዓለምን ትቶ የመነነን፣ ሚስትና ልጆቹን በማስተዳደር ትዕግሥቱና ብቃቱ ያልተመሰከረለትን፣ ምድራዊ መልአክ ሰማያዊ ሰው ይሆን ዘንድ የመነኮሰውን በገንዘብና በንብረት ላይ መሾም ገዳማዊ ሕይወት እንዲዳከም፣ መናንያን በፈተና እንዲወድቁ  አድርጓል፡፡

ፍትሐ ነገሥት ‹‹መነኩሴ ሹመት መውደድ የለበትም፤ የሹመት ፍቅር ሰይጣናዊ በሽታ ነው፡፡ በዚህ በሽታ ላይ የወደቀ ሰው ሹማምንት ለመሆን በሚገባቸው ላይ ቅንዓተኛ ይሆናልና፡፡ ሰው ጠቅሶ ያነሳሳባቸዋል፤ በራሱ ይተካቸው ዘንድ ሞታቸውን ይወዳል›› /ፍ/መ አንቀጽ ፲፤፫፻፹፭/ የሚለው አሁን ያለውን የቤተ ክርስቲያናችን እውነታ የሚገልጽ ይመስለናል፡፡

፯ኛ. ችግር የፈጠሩ መሪዎች/አገልጋዮች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ አለመሆን

በቤተ ክርስቲያን ቀኖና ጥሰት፣ አስተዳደራዊ ችግር ፈጥረው፣ የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት መዝብረው፣ ምእመናንን አሳዝነው፣ ካህናትን አስለቅሰው፣ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ጉድለት ተገኝቶባቸው፤ የመምራት ዓቅም ማነስ ኖሮባቸው ወዘተ. በምእመናን አቤቱታ ሲቀርብባቸው የሚወሰድ መፍትሔ አለመኖር ወይም የሚወሰደውም እርምጃ አስተማሪ አለመሆን ሌላው መንሥኤ ነው፡፡ በተጨማሪም ዘርፎ የተባረረን ሰው ከፍተኛ የሚዘረፍ ሀብት ወዳለበት ቦታ መመደብ፣ ይህም በጥፋታቸው እንዲገፉበት፣ ምእመናን አንገታቸውን እንዲደፉ፣ ሲከፋም ከእምነት እንዲወጡ ምክንያት ሲሆኗቸው፣ ካህናትም ተሸማቀው “ምን ፍትሕ አለ” ብለው እንዲቀመጡ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ችግር በደብር አለቆች ላይ ወይም በመምሪያ ኃላፊዎች ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ አሁን አሁን በሊቃነ ጳጳሳትም ጭምር እየተስተዋለ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልዓተ ጉባኤ  በምእመናን፣ በሰንበት ተማሪዎችና በካህናት አቤቱታና ሰልፍ ታጅቦ መከናወኑ ለዚህ ችግር አንዱ ማሳያ ነው፡፡

፰ኛ.ቤተ ክርስቲያንን እንደ አገልግሎት ቦታ አለማየት

ቤተ ክርስቲያን ምናልባትም ለአንዳንዶች የሥራ ቦታና የዕለት እንጀራቸውን የሚያገኙባት ልትሆን ትችላለች፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ቦታም ጭምር ናት፡፡ ጌታ በወንጌል ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች›› ቢልም እንደ ንግድ ቤት፣ እንደ ዓለማዊ መሥሪያ ቤት የሚመለከቷት ብዙ ናቸው፡፡ (ማቴ.፳፩፥፲፫) በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀጥረው በሚሠሩ አገልጋዮች ቤተ ክርስቲያንን እንደ ሥራ ቦታ እንጂ እንደ መንፈሳዊ የአገልግሎት ቦታ አለማየት ይንጸባረቃል፡፡

በአገልግሎቱ ሰማያዊ ዋጋ ስለማግኘት ሳይሆን ሥራ ስለሆነ ብቻ የሚያገለግሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በመገፋፋትና በሽኩቻ የተሞላ፣ ፍጹም ፈጣሪን መፍራት የሌለበት አገልግሎት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ጥቅምንና ሹመትን መሻት፣ በሌላው በልጦ ለመገኘት የሚደረግ ሥጋዊ፣ ደማዊ አስተሳሰብ የመልካም አስተዳደር እጦት መፍጠሩ ግድ ነው፡፡

፱ኛ. በመንፈሳዊ ሕይወት መድከም፡-

በአገልጋዮች መንፈሳዊ ሕይወት ላይ የሚታየው መዛል (መድከም) አንዱ የመልካም አስተዳደር እጦት መንሥኤ ነው፡፡ በአንዳንዶች ላይ የሚስተዋል የምእመናንን አንገት የሚያስደፋ ከአገልጋዮች የማይጠበቅ ፍጹም መንፈሳዊነት የጎደለው ተግባር ይፈጸማል፡፡ በዚህም የተነሣ አንዳንዶች በልዩ ልዩ ወንጀሎች ማረሚያ ቤት ገብተዋል፡፡ ‹‹እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን›› የሚለውን የሐዋርያት ቃል ተዘንግቶ ራሳቸውን የሚያገለግሉ ብዙዎች ተፈጠሩ፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፮፥፬) ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንንም፣ አገልጋዮችንም ችግር ላይ እየጣለ ይገኛል፡፡ እንደነዚህ ያሉ አገልጋዮችና መሪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካሉ ደግሞ በሚያገለግሉት ምእመን ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር መፍጠራቸው የሚገመት ነው፡፡

 ፫.፩.የመልካም አስተዳደር እጦት ያሰከተለው ጉዳት

የመልካም አስተዳደር እጦት በቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ይህን ብዙዎች የሚስማሙበት ሐሳብ ነው፡፡ በቀላሉ ለሁሉም የሚታዩትን ጥቂቶቹን አንሥተን እንመልከት፡፡

፩ኛ. ምእመናንን ከቤተ ክርስቲያን አርቋል፡፡

ምእመናን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲዝሉ እና ከቤተ ክርስቲያን ወደ ኋላ እንዲሉ ከሚያደርጋቸው አንዱ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡

፪ኛ. የገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶችን መዳከም አስከትሏል፡፡

ብዙ ገዳማት መሠረታዊ መገልገያ ቁስና መናንያኑ ሕይወታቸውን የሚያቆዩበት መቁነን ይቸግራቸዋል፡፡ ይህን ለመቅረፍ በሚል ወደ ከተማ ይገባሉ፡፡ በዚያው ለምደው የቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በቅርቡ የታላቁ የበልበሊት ኢየሱስ ገዳም አበምኔት በአንድ ሚድያ ላይ ቀርበው ‹‹ከተማ ስንቱን መናኝ መነኩሴ በላው›› ሲሉ መደመጣቸው ይህን እውነት የሚያስረዳ ነው፡፡

አብነት መምህራን ወንበራቸውን አጥፈው፣ ተማሪዎቻቸውን በትነው ሕይወታቸውን ለማስቀጠል ከተማ ይገባሉ፡፡ ብዙዎቹ ያሰቡትን ሕይወት ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ለተሐድሶ መናፍቃን ቅሰጣ ይዳረጋሉ፡፡ ተማሪዎቻቸውም በጉልበት ሥራና በሎተሪ አዟሪነት ይሰማራሉ፡፡

፫ኛ. በገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን የአገልጋይ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል፡፡ 

በሁሉም የገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የአገልጋይ ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም መምህራን እጥረት አጋጥሟል፡፡ ብዙዎቻችን የአገልጋይ እጥረት ያለው በደቡቡና በምዕራቡ የሀገሪቱ አካባቢ ብቻ ይመስለናል፡፡ እውነታው ግን ይህ አይደለም፤ የብዙ አገልጋዮች ምንጭ በሚባለው የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጭምር ከከተሞች ወጣ ስንል በሰንበት ቀንም በወርም የማይቀደስባቸው አብያተ ክርስቲያናት የትየለሌ ናቸው፡፡

፬ኛ ምእመናንን ያለ እረኛ አስቀርቷል፡፡

ወንጌል የናፈቃቸው አጥምቆ ልጅነትን የሚሰጣቸው፣ ፈትቶ ሥጋ ወደሙ የሚያቀብላቸው፣ በኀዘን፣ በደስታ የሚያጽናናቸው አባት፣ መምህር፣ መካሪ፣ ጠባቂ እረኛ አጥተው የሚቅበዘበዙ ብዙ ናቸው፡፡ ሀብቱም፣ አገልጋዩ የተከማቸው ከተማ ላይ ነው፡፡ ኢሳይያስ በትንቢቱ ‹‹አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ››  ይላል፡፡ (ኢሳ.፵፥፩) ወደ ተቸገሩት አጽናኝ ወደሚሹት፣ ፈተና ውስጥ ወዳሉት ለማጽናናት፣ ለመምክር፣ ለማስተማርና ችግራቸውን ለመጋራት የሚላክ አገልጋይ ግን በጣት የሚቆጠር ነው፡፡

ብዙኃኑ ወደ ከተማ እየፈለሱ ነው፡፡ ‹‹ዳሩ ሲፈታ መሐሉ ዳር ይሆናል›› የሚለውን ብሂል የሚያስብ ጠፍቷል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ‹‹አሁን ግን ቅዱሳንን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ›› ነበር ያለው፡፡ (ሮሜ ፲፭፥፳፭) አሁን ግን ራስን ለማገልገል ወደ ተሰሎንቄ መከማቸት ነው ያለው፡፡ ይህ ሁሉ የመልካም አስተዳደር እጦት ውጤት ነው፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍል፣ የሰው ኃይል ስምሪት፣ ማእከላዊነቱን የጠበቀና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር ቢኖር ኖሮ የችግሩ ስፋት እንዲህ ጎልቶ ባልታየ ነበር፡፡

፭ኛ.ለውጭ አካላት ትችትና ጣልቃ ገብነት ተጋላጭ አድርጓታል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በየሚድያው ስትብጠለጠልና የመነታረኪያ ርእስ ሆና እንድትቀጥል፣ ሕገ ወጦች አጥር እንደሌለውና ውሻ እንደማይጮኽበት ቤት ዘው ብለው ገብተው ስውር ዓላማቸውን እንዲፈጽሙ፣ የመንግሥት አካላትም ጣልቃ እንዲገቡ ዕድል የሰጠው የመልካም አስተዳደር እጦት ባለ መቀረፉ ነው፡፡

፮ኛ.ክብረ ክህነት እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና እንዲሸረሸር አድርጓል፡፡

ክብረ ክህነት እንዲቀንስ፣ አባቶች እንዳይከበሩ፣ ውሳኔያቸው እንዳይፈጸም፣ የታፈሩ የተከበሩ እንዳይሆኑ ካደረጉ ችግሮች ዋናው የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፡፡

፯ኛ.ሠራተኛና ሥራ እንዳይገናኙ አድርጓል፡፡

የመልካም አስተዳደር እጦት ቤተ ክርስቲያን በዐወቁ በጠነቀቁ ሙያን ከምግባር ባስተባበሩ፣ የአገልጋይነት መንፈስ በተላበሱ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዳትገለገል ችግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡

፰ኛ.መሪና ተመሪን በመንፈስ አለያይቷል፡፡

የአባቶቹን ኃጢአት የሚዘክር፣ ለካህናት የማይገዛ፣ ልቡ ከሐሳባቸው የራቀ በመተቻቸትና መነቃቀፍ የተሞላ ግንኙነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡

፱ኛ.ቤተ ክርስቲያንን አጀንዳ ተቀባይ እንድትሆን አድርጓል፡-

መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም እየተነሣ አጀንዳ ይሰጣታል፡፡ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን እንዳትወጣ በየጊዜው በሚፈጠርላት አጀንዳ እንድትጠመድ አድርጓታል፡፡ ለሙስና፣ ለዘመድ አዝማድ አሠራር፣ ለሀብት ብክነት ዳርጓታል፡፡

የመልካም አስተዳደር እጦት እነዚህንና መሰል ጉዳቶች አምጥቷል፡፡ በዚህ የተነሣ እነዚህን የተወሳሰቡ ችግሮች ለመፍታት አሁን ላይ የቤተ ክርስቲያን ትልቁና ዋናው ተልእኮዋ መልካም አስተዳደርን ማስፈን መሆን አለበት፡፡ይህም በርካታ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡

ውድ የዚህ ጽሑፍ ተከታታዮች! በቀጣይና የመጨረሻ በሆነው ክፍል አራት ጽሑፋችን የመልካም አስተዳደር ጥቅሞችን ይዘንላችሁ እንቀርባለን፤ እስከዚያው ሰላሙን ያድለን!!