p1180004

ሁለቱ የዘመነ አስተርዮ ክብረ በዓላት በዳግማዊት ኢየሩሳሌም

ጥር 11/2004ዓ.ም

ዲ/ን ጌታየ መኮንን

የ2004 ዓ.ም የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ከርስቶስ የልደት (የገና) እና የጥምቀት በዓላት አከባበር እንደወትሮው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀና ያማረ ነበር፡፡

p1180004

ካህናቱ ከታኅሣሥ 27 ቀን ጀምሮ በመድኀኒዓለም ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን፤ የአማኑኤል በዓል ዋዜማ ጠዋት ደወል ተደውሎ በጣም በደመቀ ሁኔታ ዋዜማው ተቆሞ ውሏል፡፡ 7 ሰዓት ሲሆን ቅዳሴ ተገባ እስከ 9 ሰዓት ቅዳሴ ተጠናቀቀ፡፡ ማታ 2 ሰዓት ማሕሌት ተደውሎ እስከ ለሊቱ 10 ሰዓት የቀጠለ ሲሆን ከ10 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት የቅዳሴው ሥርዓት ተከናውኗል፡፡ ጠዋት 3 ሰዓት የልደት በዓል ዋዜማ ተደውሎ እስከ 10 ሰዓት እንደቦታው ትውፊትና ሥርዓት መሠረት የቦታው ቀለም እየተባለ የዋዜማው ቅኔ ለባለ ተራዎቹ እየተሰጠ ተከናውኗል፡፡ ማታ 2 ሰዓት የበዓሉ ደወል ተደውሎ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የመጡ ምእመናን፣ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ የቤተ ማርያምን የውስጥና የውጭ ቦታ ማሜ ጋራ የተባለውን ቦታ ከበው በእልልታ በጭብጨባ ጧፍ እያበሩ ማኅሌቱ በመዘምራኑ፣ በካህናቱ፣ በዲያቆናቱ በድምቀት ቃለ እግዚአብሔሩ እየተዘመረና እየተወረበ አድሯል፡፡

 

ከቦታው ቀለሞች   «ክርስቶስ መጽአ ውስተ ዓለም»

«ኮከብ ርኢነ ወመጽአነ ንሰግድ ሎቱ ለዘፈለጠ ብርሃነ»

 

 

ሥርዓተ ቅዳሴው እንዳለቀ የአስራ አንዱም አብያተ ክርስቲያናት ካህናትና ዲያቆናት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው መስቀል፣ ጥላ፣ ስዕላት ይዘው ወደ ማሜ ጋራ ይወጣሉ መዘምራኑ ከሁለት ተከፍለው ከላይና ከታች ሆነው ምሳሌውም የመላእክትና የኖሎት በአንድነት እግዚአብሔርን ያመሠገኑበት ሲሆን «ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ» እያሉ እየተቀባበሉ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ አክብረውታል፡፡ ልክ 3 ሰዓት ሲሆን ቤዛ ኩሉ አልቆ ትምሀርትና ቃለ ምዕዳን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ  ቄርሎስ ተደርጎ ልክ 4 ሰዓት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

 

በዘንድሮው ክብረ በዓል ምንም እንኳን የሀገር ውስጥ ምዕመናን ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም፣ ከውጭ የመጡት ቱሪስቶች ቁጥር ግን ከቀድሞው የበለጠ እንደነብር ታውቋል፡፡

የጥምቀት በዓልም እንደ ልደት በዓል በቅዱስ ላሊበላ ለየት ባለ መልኩ የሚከበር በዓል ነው፡፡ ገና በዋዜማው ጠዋት 3 ሰዓት  ዋዜማ ተደውሎ እስከ 7 ሰዓት  ድረስ ዋዜማ ከተቆመ በኋላ ከ7 ሰዓት  እስከ 9 ሰዓት ድረስ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኗል፡፡

 

ልክ 10 ሰዓት ታቦታቱ ከአስራ አንዱም አብያተ ከርስቲያናት ተነስተው በቦታው ሥርዓት መሰረት ወደ 750 የሚጠጉ ካህናትና ዲያቆናት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው መምህራኑና መዘምራኑ ጥንግ ድርብ፣ ካባ፣ ሸማ ለብሰው ጠምጥመው መቋሚያና ፀናጽል ይዘው በተራ፤ ምዕመናኑ በእልልታና በሆታ ወደ ጥምቀት ባሕሩ ተጉዘዋል፡፡

p1180055

ጥምቀት ባሕር እንደደረሱ ውዳሴ ማርያም፣ መልክዓ ማርያም፣ መልክዓ ኢየሱስና፣ መልክዓ ላሊበላ ተደግሞ ስለ ጥምቀት ትምህርት ተሰጥቶ ለውጭ ሀገር ዜጎችም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ገለጻ ተደርጎ በጸሎት ከታረገ በኋላ ታቦታቱ ወደ መንበረ ክብራቸው ገብተዋል፡፡

 

በአጠቃላይ የጥምቀት በዓል በቅዱስ ላሊበላ ከጥንት ጀምሮ ባማረና በደመቀ ሁኔታ የሚከበር ሲሆን የውጭ ሀገር ዜጎችም በተለያዩ ጊዜያት ከዓመት ወደ ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በከተማው ያሉ ሆቴሎች ሁሉም ተይዘው በርካታ ቱሪስቶች ድንኳን ተከራይተው በጥምቀተ ባሕሩ ዙሪያ ማረፋቸው ታውቋል፡፡

በዚህ ዓመትም ወደ 6 የሚጠጉ የውጭ ዜጎች በጥምቀት የእግዚአብሔርን ልጅነት እንዳገኙ የቅዱስ ላሊበላ ደብር ዋና ጸሐፊ ሊቀ ሥዩማን መንግሥቴ ወርቁ ገልጸውልናል፡፡

ምሽት 2፡00 ሰዓት የበዓሉ ደወል ተደውሎ አገልግሎት የሚጀመር ሲሆን 10 ሰዓት ሲሆን ቅዳሴ ይገባል፡፡  ልክ 12፤00 ሰዓት ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ይኬድና ጸሎቱ ይቀጥላል፡፡ 3፡00 ሰዓት ፍጻሜ ይሆናል፡፡ 5፤00 ሰዓት ሲሆን ታቦታቱ ይነሱና ወደ አብያተ ክርስቲያናቱ ይሄዳሉ፡፡ 9፡30 አካባቢም የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል፡፡

በዚህ ሁሉ ሂደት ልክ እንደ ቤዛ ኩሉ በዓል መዘምራኑ የክብር ልብሳቸውን ለብሰው በዝማሜ በወረብ በእልልታ በሆታ በትውፊቱና በሥርዓቱ መሠረት ይከናወናል፡፡

 

በዕለቱ ታቦታቱ ሲነሱ « ሀዲጎ ተሥዐ ወተስዐተ ነገደ» የሚለው ቃለ እግዚአብሔር ተወርቦ ይጀመርና «ወወጽአ በሰላም ቆመ ማእከለ ባሕር ገብዐ » በሚለው ወረብ ይደመደምና ታቦቱ በተለምዶ ማርያም ጥንጫ  በሚባለው ቦታ በደብሩ አለቃ ምዕዳንና ፀሎት ከተደረገ በኋላ ታቦታቱ ወደ አብያተክርስቲያናቱ ይገባሉ፡፡

ካህናቱ እንደ መላእክት ያለ ድካም በዝማሬ በዝማሜ በወረብ በአንድ ድምጽ ይዘምራሉ፡፡ የወጭ አገር ዜጎችና የሀገር ውስጥ ምእመናን ካሜራቸውን በመያዝ ቪዲዮና በፎቶ ይቀርጻሉ ያነሳሉ፡፡ እንደዚሁ ሁሉ የቃና ዘገሊላ የቅዱስ ሚካኤልና የቅዱስ ላሊበላ ታቦታት እንደቦታው ሥርዐት እንደ ጥምቀቱ ምሉዕ ካህናት አጅበውት ቃለ እግዚአብሔሩ እየደረሰ ይመለሳሉ፡፡

በከተራ የሚወርዱት 12 ታቦታት ሲሆኑ አስሩ የጥምቀት ዕለት ሲመለሱ ሁለቱ የቃና ዘገሊላ ዕለት ይመለሳሉ፡፡ አካሄዳቸውም እንደቦታው ሥርዓት ሲሆን ይህም ከጥንት የተገኘ ለመሆኑ ገድለ ላሊበላ ላይ ተገልጾ  ተቀምጦአል፡፡

ሥርዓቱ አባቶቻችን ጠበቀው በማቆየታቸው ዛሬም በዚሁ ሥርዓት ይቀጥላል፡፡ ለምሳሌ የታቦታቱ ቅደም ተከተል ይሄውም በየተራ በሰልፍ የሚሄዱበት መንገድ፣ የመዘምራን ዝማሜ፣ ጥንግ ድርብ ሻሽና ካባ ለባሽ ሆነው በሁለት ተከፍለው በተራ ይዘማሉ፡፡ ወረቡ በተራ በሊቃውንቱ እየተቃኘ ሌሎች እየተቀበሉ ይደርሳል፡፡

 

p1180070ቱሪስቶች ከዓመት ወደ ዓመት ፍሰታቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም ዝማሜው፣ አልባሳቱ፣ የበዓሉ ድምቀት ፣ የቦታው ሥርዓት ለየት ያለ እንዲሁም በእግዚአብሔር ድንቅ ጥበብ በቅዱስ ላሊበላ የታነጸው ህንጻ ከሊቃውንቱ፣ ሊቃውንቱ ከህንጻው ጋር አብረው የሚታዩና የማይጠገቡ በመሆናቸው እንደሆነ ሊቀ ሥዩማን ገልጸውልናል፡፡

ከሌሎች ቦታ ለየት የሚያደርገው በዓሉ የተለየ ቃለ እግዚአብሔርም አለ፡፡ ይህም በአባቶች ከቦታው ጋር እንዲስማማ ሆኖ በመደረሱ ነው፡፡

 

ለምሳሌ፡- «ዘከለሎ ብርሃን ዘከለለሎ»

«ወወጽአ በሠላም ቆመ ማዕከለ ባህር ገባዐ»

«አይኑ ዘርግብ ልብሱ ዘመብረቅ»የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡


በአጠቃላይ በዓሉ አመት እስኪደርስ የሚናፈቅ የሚወደድ ባላለፈ ባላለቀ ጥምቀት ለምን አንድ ጊዜ ብቻ ሆነ የሚያሰኝ ነው፡፡ ሁሉም ህብረተሰብ ወደ ቦታው ሄዶ አይቶ በረከት ቢቀበል በጣም ጥሩ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር