ሀገር ዕርቃኗን እንዳትቀር

መጋቢት 25/2004 ዓ.ም.

ከጥቂት ዓመታት በፊት በታተመ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ጥናት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2020 ሙሉ በሙሉ ደን አልባ አገር ትኾናለች፡፡ እንደ ጥናቱ ከ40 ዓመታት በፊት የሀገሪቱ 40 በመቶ መሬት በደን ተሸፍኖ ነበር፡፡ ጥናቱ በታተመበት ዓመት ግን ወደ 2.7 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ ጥናቱ ማስረጃን በመጥቀስ እንዳስቀመጠው ቁጥሩ በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዲህ ያሽቆለቆለው በሀገሪቱ 200,000 ሄክታር መሬት በልዩ ልዩ መንገድ ስለሚወድም ነው፡፡ የዚህን ጥናት ግኝት ሌሎች ጥናቶችም ይጋሩታል፡፡ ይህ መረጃ አስደንጋጭ ነው፡፡ በልምላሜና ልምላሜው በሚያመጣው በረከት ለሚኖር እንደኛ ዓይነት ሕዝብ ደግሞ ሁኔታው አስጨናቂ ነው፡፡

ከሀገራችን የተፈጥሮ ደኖች ውስጥ 35 ሺ የሚኾኑት በአድባራትና ገዳማት ዙሪያ ያሉ ደኖች እንደኾኑ ልዩ ልዩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ እነዚህ ደኖች የሚገኙት በተለይ በሀገሪቱ የሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብና መካከለኛው ክፍል እንደመኾናቸው አካባቢው ተፈጥሮ ካደረሰበት መራቆት የተነሣ የችግሩን ስፋትና ግዝፈትም ባያህል የቻሉትን ያህል ሲታደጉት ኖረዋል፤ አሁንም በመታደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እነዚህ ባለውለታ ደኖች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አደጋ እንደተቃጣባቸው ወይም እንደደረሰባቸው እናያለን፤ ከሰሞኑ እንኳን በአሰቦት ደብረ ወገግ አቡነ ሳሙኤልና ቅድስት ሥላሴ ገዳም፤ እንዲሁም ደግሞ በዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ደን ላይ ላይ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በዚህም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችንም ብቻ ሳይኾን እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ደንግጠናል፤ ተጨንቀናልም፡፡ ለምን?

ደኖቻችን የመንፈሳዊ ሀብታችን ምንጮች ናቸው፡፡ ለቅዱሳን አበውና እመው የተመስጧቸው መሠረት፣ የጸሎታቸውም ትኩርት፣ ለዐጽማቸው ማረፊያ ለስውራኑም መናኸሪያ ከተማ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ ጥበብ፣ ፍልስፍናና ዕውቀትም በእነሱ በኩል አግኝተናል፤ እናገኛለንም፡፡ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ዕውቀትን ያገኘው በዐጸድ መካከል ነው፡፡ የቅኔው ፍልስፍና፣ የአቋቋሙ ጥበብ፣ የመጻሕፍት ምሥጢር የፈላውና በመልክ በመልኩ የተደራጀው በደኖቻችን ሆድ ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ ከሀገራችን አልፎ በዓለም ሊቃውንት ቢቀዱና ቢጠኑ የማያልቁት ቅዱሳት ድርሰቶች በአበው ሊቃውንት የተጻፉት ደኖቻችን ቀለምና ብርዕ ኾነው ነው፡፡ ሀገሪቱ በበርካታ ጦርነቶች ያለፈች እንደመኾኗ ደኖቻችን በየዘመኑ በርካታ ቅርሶችን በአደራነት ተቀብለው አኑረዋል፡፡ የተገኙት ተገኝተዋል፡፡ አደራ መቀበላቸውን ያየ ወይም የሰማ ጠፍቶ አደራ በሊታ ላለመኾን ዛሬም ሰንቀዋቸው ይገኛሉ፡፡ የሚመረምር ጠቢብ ትውልድ ቀርቦ እስከሚቀበላቸው ድረስ፡፡ ደኖቻችን ምግቦቻችንም ናቸው፡፡ ይህን ዓለም ንቀው በምናኔ ለሚኖሩ አባቶቻችን በምግብ ምንጭነት ከማገልገላቸውም አንጻር መንፈሳዊ ጥቅማቸው የጎላ ነው፡፡ ደኖቻችን የምድር ልብሶች ናቸው፡፡ በልብስነታቸው በውስጣቸው ላሉ ብርቅዬ የኾኑ እንስሳትና አራዊት መጠጊያ ኾነው ያገለግላሉ፡፡ በመኾኑም በውስጣቸው በያዟቸው ሀብታት ደኖቻችን የተቀደሱ ናቸው፡፡

ደኖቻችን ላቅ ያለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምም አላቸው፡፡ በውስጣቸው ሕዝብ ቢመገባቸው የሚያጠግቡ፤ ቢጠጣቸው የሚያረኩ ፍራፍሬዎች፣ እንስሳትና ማዕድናት የያዙ ናቸው፡፡  እነዚህ ሀብታት በአግባቡ ቢያዙ ከሀገር አልፈው ወደ ዓለም ዐቀፍ ገበያ ቀርበው ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት ይችላሉ፡፡ በሌላው ዓለም የሌሉ የእንስሳትም ኾነ የዕጸዋት ዝርያዎችን የያዙ ከመኾናቸው አንጻርም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ፡፡ ደኖቹ በሚፈጥሩት ልምላሜ አየር የተነሣም ሀገርን የሚያለመልም ጠለ በረከት እንዲወርድ ያደርጋሉ፡፡ ጠለ በረከት ሲወርድ ሕዝብ ጠግቦ ያድራል፤ ኢኮኖሚውም ይገነባል፡፡

ደኖቻችን መድኃኒቶቻችን ናቸው፡፡ በዚህም የሀገርን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አኳያ ጥቅማቸው የጎላ ነው፡፡ እንደነ መጽሐፈ መድኃኒት፣ ዕጸ ደብዳቤ፣ መጽሐፈ አዕባን ወዘተ. ዓይነት ደገኛ የነገረ ሕክምና መጻሕፍት በአበው ተጽፈው ለእኛ የደረሱን፤ አባቶቻችን በእነዚህ ደኖች ቤተ ሙከራነት ባደረጉት ምርምር ነው፡፡ የዛሬው ትውልድ ልብ ገዝቶ ከላይ የተጠቀሱትን መጻሕፍት ተጠቅሞ መድኃኒት ልሥራ ብሎ ቢነሣ ንጥረ ነገሮቹን የሚያገኘው ከዚህ ነው፡፡ ሀገር ለራሱ ሕዝብ በራሱ መድኃኒት ፈበረከ ማለት ደግሞ፤ ሕዝቡ ስሙን እንኳን አንብቦ የማይረዳውን መድኃኒት በብዙ ሚልዮን ዶላር ገዝቶ ከማምጣት መዳን ይቻላል ማለት ነው፡፡

ደኖቻችን ከማኅበራዊና ባሕላዊ ጥቅማቸውም አንጻር ድርሻቸው ሰፊ ነው፡፡ የተጣላ የሚታረቀው፣ በሀገርና በወገን በመጣ ችግር ላይ ተወያይቶ መፍትሔ የሚሰጠው፣ ወጣት ኮረዳው በተፈጥሮ የተሰጠውን ችሎታ ፈትሾ የሚያዳብረው በደኖቻችን ነው፡፡

በመኾኑም በምናየውና በምንሰማው መልኩ በተፈጥሮ ደኖቻችን ላይ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ የሚቃጣውና የሚደርሰው አደጋ በሕዝብና በሕዝቡ ማሕደር በኾነው አገር ላይ የሚቃጣና የሚደርስ አደጋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ደኖቻችን አልቀው አገር ዕርቃኗን ከመቅረቷ በፊት የሚመለከተን አካላት በሙሉ ርብርብ ልናደርግ ይገባል፡፡

ደን እንደ ኢትዮጵያ ከሰሐራ በታች ላሉ ሀገራት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በመኾኑም መንግሥታችን የእነዚህን የተፈጥሮ ደኖች ጥቅም በሚያራምደው የልማትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ አብሮ መቀመር ይኖርበታል፡፡ ይህን ስንል ግን እስከ አሁን ምንም ዓይነት ሥራ አልተሠራም በማለት አይደለም፡፡ በእኛ እምነት ቀመሩ አደጋ ለተቃጣባቸውና እየተጎዱ ላሉ ደኖች አስቸኳይ የማዳንና የመጠበቅ እርምጃ በመውሰድ ይጀምራል፡፡ ከዚህም ጋር ሁሉንም ተጠያቂ የሚያደርግ ጠንካራ የደን ሀብት አጠቃቀም ፖሊሲ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች ሀገራት እንደሚታየው ባለ ሀብቶችና ተቋማት የተፈጥሮ ደኖችን በማልማት ተግባርም እንዲሰማሩ በልዩ ልዩ መንገድ ቢያበረታታና መንግሥታዊ ድጋፍም ቢያደርግ መልካም ነው፡፡ ከዚህም ጋር ደኖቹን ለዘመናት ጠብቀው ላቆዩ /በእኛ ረገድ ለገዳማትና አድባራት/ ሙሉ የባለቤትነት መብት ቢሰጥ ለደኖቹ መጠበቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል እንላለን፡፡

ቤተ ክህነታችንም በስሩ በሚገኙ አድባራትና ገዳማት ተጠብቀው ከመንፈሳዊ ጥቅማቸው አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ሲሰጡ ለቆዩ ደኖች ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ደኖች ለቤተ ክርስቲያኗም ኾነ ለሀገር ሲሰጡ ከኖሩትና እየሰጡ ካሉት መጠነ ሰፊ ጥቅም አንጻር ቤተ ክህነቱ ለደኖች የሚሰጠው ትኩረት የበለጠ መኾን አለበት፡፡ እንደሌላው ሀብቷ ሁሉ ደኖቿ እንደትላንትናው በሁሉም ርብርብ ተጠብቀው ይቆያሉ ብሎ መቀመጥ የዋሕነት ነው፡፡ ዛሬ ሌላ ቀን ከመኾኑ አንጻር እነዚህ ደኖች የሚጠበቁበትን ሥልት መንደፍና ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ሥልቱም በዋና መሥሪያ ቤቱ ደረጃ በጉዳዩ ላይ የሚሠራ ጠንካራ ተቋም ማቋቋምንም ይጨምራል፡፡

ደኖቻችንን በመጠበቅ ረገድ በባለቤትነት ለዘመናት ተንከባክበው ከጠበቁ ገዳማትና አድባራትም የሚጠበቅ ተግባር አለ፡፡ የመጀመሪያው ተግባር ከአካባቢያቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመተባበር የደን ይዞታቸውን ሕግ ባወቀው መንገድ እንዲከበሩ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለልዩ ልዩ አገልግሎት ለማዋል በሚል ደኖቹን ከመጨፍጨፍ ተግባር መታቀብ ነው፡፡

ለዘመናት ተጠብቀው የኖሩት ደኖች ተጠብቀው እንዲኖሩ በደኖቹ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብም ከፍተኛ ሓላፊነት አለበት፡፡ ደኖቹን ከነሙሉ ሀብታቸው ጠብቀው ያቆዩት ገዳማውያን ወይም የአድባራቱ አለቆችና ካህናት ብቻ አይደሉም፡፡ አሁን በደኖቹ አካባቢ ያለው ሕዝብ አያቶችና ቅድመ አያቶች ጭምር እንጂ፡፡ በመኾኑም ሕዝቡ ከመካከሉ ደኖችን በመቁረጥ ለማገዶና ቦታውን ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚያውለውን በተለመደ ባሕሉ ማረምና ችግሩን የሚያቃልልበትን አማራጭ መፍትሔ አብሮ መዘየድ ያስፈልገዋል፡፡ ደኑ ዛሬ ተቆርጦ የዛሬን ችግር ሊያቃልለት ይችላል፡፡ ነገር ግን በደኑ መቆረጥ መሪር ዋጋ የሚከፍሉት ልጆቹና የልጅ ልጆቹ መኾናቸውን ሊረዳ ይገባዋል፡፡
በአጠቃላይ ደኖቻችን /በተለይ በተራቆተው የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙት/ ለአካባቢው ሕዝብ ምግብ፣ መጠጥ፣ መድኃኒት፣ የማኅበራዊ እሴቶቹ ማከናወኛ፣ ለሀገርም የኢኮኖሚ ዋልታና የዕውቀት አፍላጋት ስለኾኑ ሁሉም ጥብቅና ሊቆምላቸው ይገባል እንላለን፡፡ ከተለያዩ ሪፖርቶች እንደምንረዳው የቀሩትን ጥቂት ደኖች ማጥፋት ሳይኾን፤ ቆዳው ተልጦ፣ ሥጋው ተበልቶ፣ የገጠጠው አጥንቱም እየተፈረፈረ ያለውን መሬታችንን ዕርቃን የሚሸፍኑ ደኖችን ባስቸኳይ ማልማት አለመጀመር፤ የተጀመሩትን ጥረቶችም ውጤታማ የሚኾኑበትን አግባብ አለማፋጠን የትውልድ ወንጀል ነው፡፡ ስለዚህ መሬታችን ዕርቃኑን እንዳይቀር፤ ዕርቃኑንንም ለልጆቻችን እንዳናስረክብ አደራ አለብን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር