በኢት/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን 39ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መካሔድ ጀመረ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 39ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በጸሎተ ወንጌልና በቅዱስ ፓትርያርኩ የመክፈቻ መልእክት ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡
በመክፈቻው መርሐ ግብርም ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዮስ እና ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጀምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያ ኃላፊዎች፣ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳሚዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት መልእክትም በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያንና ኦርቶዶክሳውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና መከራ፣ በእጅ አዙር ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈልና ለማዳከም እየሠሩ የሚገኙ አካላት እንዳሉ በተለይም በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ከቀኖና ውጪ እየተደረገ ያለው ድርጊት ድፍረት የተሞላበት ስሕተት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አስከፊውን የወጣቶች ስደት፣ የአንበጣ መንጋና ልዩ ልዩ መቅሠፍት እያስከተሉት ያለውን ችግር በተመለከተም በመልእክታቸው ያነሱ ሲሆን ችግሮቹንም ለመፍታት ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በሀገራችን እየታዩ ያሉትን አለመግባባቶችም በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው እስከ ጥቅምት 7 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን ልዩ ልዩ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት እንደሚካሔድባቸውና ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ግብአት የሚሆኑ ነጥቦችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡
የቅዱስነታቸው መልእክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡-
መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
– ብፁዕ አቡነ ያሬድ
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና
የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
– ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና
የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
– ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
– የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የየመመሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች፣
– የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ልዩ ልዩ ኃላፊዎች፣ የገደማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
– በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚገኙ ልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት የመጣችሁ ሥራ አስኪያጆች፣
በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፍ ተወክላችሁ በዚህ ዓመታዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ የተገኛችሁ ክቡራንና በአጠቃላይ፤
ሁሉንም ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር አምላካችን መከራውንና ፈተናውን አስችሎ በዚህ ታላቅ ጉባኤ ስለሰበሰበን ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡
‹‹ወይኩን ቅኑተ ሐቈክው ወኅተው መኃትቂክሙ፤ ወገባችሁ የታጠቀ፣ መብራታችሁም የበራ ይሁን፡፡›› (ሉቃ.12፡35)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ኃይለ ቃል የተናገረውና ያስተማረው ለቅዱሳን ሐዋርያት እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ትምህርቱ ለጊዜው አጠገቡ ለነበሩት ሐዋርያት የተነገረ ቢሆንም ፍጻሜው እስከ ዕለተ ምጽአት ለሚነሡ ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንደሆነም እናውቃለን፡፡ ከነሱ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በየደረጃው በኃላፊነት የምንገኝ ደቀ መዛሙርትም ቃሉ በቀጥታ እንደሚመለከተን አንዘነጋውም፡፡
በመሆኑም ከዚህ እውነታ ተነሥተን፣ ጌታችን ‹‹ወገባችሁ የታጠቀ፣ መብራታችሁም የበራ ይሁን›› ሲል እኛን ያዘዘበትና ያስተማረበት ምክንያት ምን ይሆን? የሚለውን ጥያቄ አንሥተን ማየት ከሁላችንም ይጠበቃል፤ ሁላችንም እንደምንገነዘበው የትጥቅ ነገር የሚነሣው ተቃራኒ ኃይል ራስን ወይም ወገንን ለማጥቃት እንደተዘጋጀ ሲታወቅ ነው፤ መብራትን ማብራት የሚያስፈልገው ጨለማ መኖሩ ሲታወቅ ነው፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አፅራር ምንጊዜም የማይተኙ መሆናቸውን በአምላክነቱ ኃይል የሚያውቅ እግዚአብሔር አምላካችን ሁሌ ወገባችንን ታጥቀን መንጋውን እንድንጠብቅ አዞናል፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብርሃናዊት፣ ሰማያዊትና ዘለላለማዊት ብትሆንም ለጊዜው ያለችው ጠላት በብዛት ባለበትና በጨለማው ዓለም ውስጥ ነውና በጠላት እንዳትጠቃ በጨለማውም እንዳትዋጥ ሁልጊዜ መብራት እንድናበራላት ታዘናል፤ ይህ የእኛ የክርስቲኖች ቀዋሚና መደበኛ ሥራችን ነው፡፡
– ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
– ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤
በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ካለው መከራ አንጻር ከምንም ጊዜ በላይ ታጥቀን ለቤተ ክርስቲያን ህልውና መቀጠልና ለሕዝበ ክርስቲያኑ የሕይወት ዋስትና መረጋገጥ በአንድነት የምንቆምበት ነው፤
ለሦስት ሺሕ ዘመናት ሀገርን የገነባችና የጠበቀች ሁሉንም በእኩልነት ያስተናገደች በማንም ላይ ግፍን ያልፈጸመች ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ ከገጸ ምድር እናጥፋሽ የሚሉ በምሥራቅም በምዕራብም እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆናል፤ ፍትሕም ይገኝ ይሆናል እያልን በተስፋ ብንጠባበቅም ሲሆን አናይም፤ ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ነገሩ እየተባባሰ፣ ክርስቲያን ልጆቻችንም ለተደጋጋሚ ጥቃት እየተዳረጉ በክርስቲያንነታቸው ብቻ የግፍ ግፍ እየተፈጻመባቸው ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ጊዜያት ባደረገችው ጥሪ ከልዩ ልዩ በጎ አድራጊዎችና ከሕዝብ ክርስቲያኑ ለተጎዱ ምእመናን የተወሰኑ ድጋፍ ለማድረግ ቢሞከርም ከችግሩ ስፋት የተነሣ የሚያረካ አልሆነም፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤
አበው ሲናገሩ ‹‹ከራስ በላይ ነፋስ›› እንደሚሉት ቤተ ክርስቲያናችን እየገጠማት ያለውን ችግር ለመቋቋም ልጆችዋን አስተባብራና አደራጅታ ራስዋን በራስዋ ወደመጠበቅ አማራጭ ካልተሻገረች ዕጣ ፈንታዋ እጅግ አስጊ እየሆነ መጥቶአል፤ ክርስቲያን ልጆቻችን ተሸማቅቀው፣ ነጻነታቸው ተገፎ፣ በሀገራቸውና በወገናቸው መካከል የመኖርና ሃይማኖታቸውን የመከተል መብት አጥተው ባለቡት ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቅን ነው ማለት አይቻልም፡፡
ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያንን የመጠበቅና የማጽናናት ኃላፊነት ከሁሉ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ጫንቃ ላይ ያረፈ እንደመሆኑ መጠን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚዘንበውን መከራ ለመግታት ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ጉባኤ ተገቢውን መፍትሔ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው አባላት፤
‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሚባለው ሁከት፣ ለዘመናት ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የአንበጣ መንጋና ልዩ ልዩ መቅሠፍት በበዛበት በአሁኑ ጊዜ አንድ ላይ ሆነን በመቆም ሕዝበ ክርስቲያኑን በመጠበቅ ፈንታ ሌላ ተቀጥላና የቤተ ክርስቲያንን ዓቅም በመከፋፈል ለማዳከም በውስጣችን የሚደረጉ ሤራዎችም ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ጥንካሬ ከባድ ዕንቅፋቶች እየሆኑ መምጣታቸው ሌላ የጥፋት ገጽታ ሆኖ እየታየ ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ እንደዚህ ያለው ድርጊት ለዘመናት ቤተ ክርስቲያናችንን ሲፈታተኑ የነበሩ የውጭ ኃይሎች በረቀቀ ስልትና በእጅ አዙር ቤተ ክርስቲያናችንን ሊያፈራርሱ የጠነሰሱት ተልእኮ እንጂ ላይ ላዩ አጥባቂ የኦርቶዶክስ ተከታይ መሳይ ውስጡ ግን ኦርቶዶክስን በመከፋፈል ማዳከምና ማፍረስ የሆነ ድርጊት የንጹሐን ኦርቶዶክሳዊያን ተግባር ይሆናል ብለን አናምንም፤ ይህንን ደባ ሁላችንም ልናጤነው ይገባል፡፡
ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የተፈጸመው ሕገ ወጥና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆነ የኤጲስ ቆጳሳት ሢመት ይገኝበታል፡፡ እንደዚህ ያለ ድርጊት የሁለት ሺሕ ዘመን ሐዋርያዊ ቀኖና እና ሥርዓት ባላት በቤተ ክርስቲያናችን ቀርቶ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ተደርጎ የማያውቅ ድፍረትና ስሕተት ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ ድርጊት መነሻ የሆኑት ምክንያቶችና የምክንያቶች ሰለባ የሆኑ፣ እንደዚሁም ሳይላኩና ሥልጣኑ ሳይኖራቸው ዳግም ጥምቀትን ዳግም ክህነትን በማወጅ ለዚህ አደጋ መከሠት ምክንያት የሆኑ ሁሉ በማያዳግም ሁኔታ ይህ ጉባኤ የማስቆሚያ መፍትሔ እንዲያበጅላቸው በዚህ አጋጣሚ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤
የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ዛሬ በብዙ መልኩ እንግልት ላይ ወድቀው ማየት የተለመደ ሆኗል፤ ብዙ ወጣት ልጆች ለእንጀራ ፍለጋ ሲሉ ሃይማኖታቸው ወደማይወደድበት ሰብአዊ መብታቸው ወደማይከበርበት፣ የንብረትም ሆነ የሕይወት ዋስትና ወደሌለበት ሀገር በመሰደድ የምድር ሲኦል እየለበለባቸው እንደሆነ እያየን ነው፤ ይህንን እየተመለከትን ተኝተን የምናድር ኢትዮጵያውያን ካለን ክርስቲያንነቱም ሰብአዊነቱንም ዘንግተዋል የሚያሰኝ ነው፤ ስለሆነም ልጆቻችን በባዕድ ሀገር ራቁታቸው እንደቅጠል እየረገፉ ከማየት የበለጠ (የከፋ) አንገትን የሚያስደፋ ውርደት ስለሌለ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቅዋማት፣ የኢፌድሪ መንግሥትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገባውን ሁሉ በማድረግ ልጆች ወደ ሀገራቸውና ወደ ቤተሰቦቻቸው በአስቸኳይ እንዲመለሱ ያደርጉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ማሰማት አለባት፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ምግብና መጠጥ፣ ልብስና መጠለያ እንደሚሻ ሁሉ ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ የእኩልነት፣ የመብትና የፍትሕ ፍላጎቱም የላቀ ነው፤ እነዚህ ፍላጎቶቹን ባጣ ጊዜ ያላስፈላጊ ሁከትና ግጭት ይፈጠራሉ፤ በዓለማችንም በሀገራችን የሚታዩ አለመግባባቶች ይብዛም ይነስ ከዚህ የሚመነጩ ከመሆን አያልፍም፤ እነዚህ ነገሮች በተቻለ መጠን ካልተከበሩ ውጤቱ ጥሩ እንደማይሆን እያየን ነው፤ በመሆኑም በሀገራችን ያለው ያልተረጋጋ ሁኔታ ያልሆነ መልክ እንዳይዝ መንግሥታችንና የሀገራችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወንድማማቾች እንደመሆናቸው መጠን ምንም ልዩነት ሳይኖር በክብ ጠረጴዛ ሆነው በመመካከር ችግሮችን ሁሉ እንዲፈቱ እንጂ ወደ አስፈላጊ ሁኔታ እንዳይገቡ ቤተ ክርስቲያናችን በገለልተኝነትና በእናትነት መንፈስ ማገዝ አለባት፤ ማስታረቅም ማስተማርም አለባት፤ ሁሉም ነገር በሰላምና በውይይት ብቻ እንጂ ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ የሚደረግ አማራጭ ከጉዳት በቀር ውጤት አናገኝበትም፤ ከዚህ ጎን ለጎንም ፍትሕና ርትዕ እንዲሰፍን፣ ፍትሕ የተነፈጋቸው ወገኖች ካሉ ፍትሕ እንዲያገኙ ቤተ ክርስቲያን በማእከል ሆና የመምከር ሥራ መሥራት አለባት፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤
ከዚህ በላይ የጠቃቀስናቸው ችግሮች በሀገራችን ሥር እየሰደዱ የመጡበት ምክንያት በርከት ያለ ቢሆንም የድህነት ጉዳይ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ አያጠራጥርም፤ ወጣት ልጆቻችን ሥራና ዳቦ ባጡ ቁጥር ሌላውን አማራጭ በመከተል ሲታክቱ እነሆ በጣም በርካታ የሆኑ ዓመታት ተቈጠሩ፤ ስያሜውና አቀራረቡ ቢለያይም ከሕገ ንጉሣዊ ሥርዓት ማክተም ማግሥት ጀምሮ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ፀረ ድህነት የሚል አንድምታ ይዘው የተደረጉ ናቸው፤ ሆኖም ይቀረፋል የተባለው ድህነት ባላመቀረፉ፣ በዚያም ላይ ሌሎች ነገሮች በመካከሉ እየተሰነቀሩ ጉዞአችንን የኋልዮሽ አድርገውታል፡፡
ስለሆነም ድህነትን በዕድገት በመቀየር ረገድ ቤተ ክርስቲያን በልማቱ፣ በድህነት ማጥፋቱና በሰላም ማረጋገጡ ዙሪያ በርትታ መሥራት ይጠበቅባታል፤ ሰበካ ጉባኤ የተቋቋመውም ሕዝቡ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በአንዱ ወጥ አደረጃጀት ተሰብስቦ አረጋዊያንን በመጦር፣ ሕፃናትን በማስተማርና በመንከባከብ፣ የራስ አገዝ ልማትን በማስፋፋት፣ ለወጣቱ ትውልድ ሥራ በመፍጠርና የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደሆነ ይታወቃል፤ ከዚህ አንጻር ሰበካ ጉባኤ ከተቋቋመበት ዘመን አንሥቶ የተገኘው ዕድገት የማይናቅ ቢሆንም መጓዝ የሚገባውን ያህል እንዳልተጓዘ፣ ያለውም ሀብት በአግባቡ እንዳልተያዘ የአደባባይ ምሥጢር ነው፤ ከዚህም ሌላ ሌሎች ደባል ቡድኖች በየአካባባው ሲፈጠሩ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ለምጣኔ ሀብት መባከን ያለው አደጋ ሳይጤን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ፈቃድ እየተሰጠን በየፊናው ያሰማራቸውና ሁሉ በስመ ቤተ ክርስቲያን እየተሰበሰቡና ገንዘብ እየሰበሰቡ በርከት ያለ የምእመናን ሀብት እንደሚባክን መረጃዎች አሉ፤ ይህም የሚከናውነውን በሀገር ውስጥና በውጭ ጭምር ነው፤ ቅዱስ ሲኖዶስና ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን ድርጊት አርሞና አስተካክሎ መልክ ካላስያዘ በቀር ጉዳቱ የቤተ ክርስቲያንን ምጣኔ ሀብት ብቻ ሳይሆን አንድነትዋንና ህልውናዋንም ጭምር ከባድ አደጋ ላይ የሚጥል ይሆናል፤ በታሪክም ተወቃሽነትን ያስከትላል ስለዚህ እኛ የምንለው አሁንም መፍትሔ እናበጅለት ነው፡፡
በመጨረሻም፤ ይህ ዓመታዊና ዓለም አቀፋዊ የጠቅላላ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ የቀረቡትን ዓበይት ጉዳዮች በጥልቀትና በማስተዋል ተመልክቶ ለወሳኙ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ግብአት የሚሆን የውሳኔ ሐሳብ እንዲያስተላልፍ በማሳሰብ አባታዊ መልእክታችን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ጉባኤያችንን ይባርክልን፤ ይቀድስልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ