“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” (፩ኛዮሐ. ፫፥፰)

ክፍል አራት

በመ/ር ኃይለሚካኤል ብርሃኑ

እግዚአብሔር ሰውን መውደዱ በባሕርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መገለጥ ፍጹም መሆንን ተረዳን፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በማለት ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ የመሰከረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም ቅድመ ዓለም የነበረ ዛሬም ያለ ወደፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር አልፋና ዖሜጋ ነው፡፡ ዓለምንም ለማዳን ሲል ከዘመን በኋላ ጊዜውና ሰዓቱ ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱ ፍጹም ፍቅሩ የታየበት መገለጥ ነው፡፡  የማይወሰነው አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት  ተወስኖ ሕግ ጠባይዓዊንና ሕግ መጽሐፋዊን በትክክል ሲፈጽም   የታየበት ስለ ሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ በማለት ቅዱስ ዮሐንስ ስለርሱ መስክሯል፡፡ የመገለጡ ዋና ዓላማም ምን እንደሆነ በጥቂቱ ለማየት ቀደም ብለን የተመለከትናቸው እንዳሉ ሆነው በዚሁ ክፍልም የሚከተለውን እናያለን፡፡

ከጨለማ ወደ ብርሃን ሊያወጣን

ከበደል በኋላ የሰው ልጅ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር በመሆን እረኛ እንደሌለው መንጋ ሲቅበዘበዝ ይኖር ነበር፡፡ መቅበዝበዛችንን አይቶ በፍቅሩ ይሰበስበን ዘንድ በጨለማ መኖራችንን አርቆ በብርሃኑ እንድንመላለስ ያደርገን ዘንድ አማናዊው ብርሃን በሥጋ ተገለጠ፡፡  በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የጨለማው አበጋዝ ዲያብሎስ ፈራ ደነገጠ፡፡ እንዲህ አይነት የእግዚአብሔር መገለጥ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስን ያስደነገጠ መገለጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን እንኳን አይቶት የማያውቀውን ትሕትና ያሳየበት፣ለሰው ያለው ፍቅር እስከ ምን ድረስ እንደሆነ እንድናስተውል በሥጋ መገለጡንም ዕፁብ ዕፁብ ብለን ትሕትናውን እና ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር እንድናደንቅ አድርጎናል፡፡

ሕይወታችን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ በሞት ጥላ ሥር ሆኖ በባርነት ተይዘን ነበር፡፡ የእርሱ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ ያንን አስጨናቂ የጨለማ ኑሮ አርቆ በብርሃን እንድንመላለስ አደረገን፡፡ ለዚህም ነው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ፡- “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገርም ለነበሩ ብርሃን ወጣላቸው”(ኢሳ.፱፥፪) በማለት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መገለጥ አስቀድሞ የሰው ልጅ ኑሮው በጨለማ ውስጥ እንደነበረና በኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን እንደ ወጣልን መስክሯል፡፡

ቅዱስ ኢሳይያስ ታላቅ ብርሃን በማለት የገለጸው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ እርሱ የብርሃናት ብርሃናቸው ነውና ከእርሱ ብርሃንነት ቅንጣት ሰጥቷቸው በዓለም ላይ እንዲያበሩ ፀሐይን በቀን፣ጨረቃና ከዋክብትን በሌሊት እንዲሠለጥኑ ያደረገ የዓለማት ዓለማቸው ኢየሱስ ክርስቶስ

ታላቅ ብርሃን ነውና፡፡ ብርሃናውያን ቅዱሳን መላእክትን በኀልዮ የፈጠረ የመላእክት አስገኚ፤ ሰማይንና ሰማያውያንን ምድርንና ምድራውያንን በቃሉ የፈጠረ የሁሉ አስገኚ ስለ ሆነ ታላቅ ብርሃን ተብሏል፡፡

ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፡- “ እኔ የዓለም ብርሃን  ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” (ዮሐ.፰፥፲፪ በማለት እርሱን በመንገዱ ሁሉ የሚከተል የሕይወት ብርሃን እንደሚሆንለት ከጨለማ ኑሮ ወጥቶ በብርሃን እንደሚመላለስ ያስተማረን፡፡

ብርሃን ጨለማን አርቆ ማየት የምንችለውን ሁሉ እንድናይ ዕድል እንደሚፈጥርልን ሁሉ አማናዊውን ብርሃናችንን ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ስንችል ከጨለማው ዓለም ወጥተን በዘላለም ብርሃን ውስጥ ያለውን ክብር ማስተዋል እንችላለን፡፡ ይህም ማለት የምድሩን ሳይሆን የሰማዩን፣ቁሳዊውን ሳይሆን መንፈሳዊውን፣ ጊዜያዊውን ሳይሆን ዘላለማዊውን፣ታይቶ የሚጠፋውን ሳይሆን ለዘለዓለም የሚኖረውን፣ ከሰው የሆነውን ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሆነውን በእምነት መመልከት እንችላለን ማለት ነው፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን”(መዝ.፴፭፥፱) በማለት የተቀኘለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጨለማውን ዓለም ወደ ብርሃን እንደሚያወጣው በትንቢት መነጽር በመመልከቱ ነው፡፡ በጨለማ ውስጥ መኖር ትርፉ ኀዘን፣ልቅሶ፣ዋይታ፣ሞት፣ፍርሀት፣ጭንቀት፣ጉስቁልና ወ.ዘ.ተ ነው፡፡

ከዚህ ጨለማ ከነገሠበት መራራ ሕይወት ተላቆ ብርሃን በሆነ በደስታ፣በሰላም፣በዕረፍት፣በሕይወት፣በክብር በነፃነት መኖር ምን ያህል ከፍታ እንደሆነ ሲገባን የሚያስፈራውን ድቅድቁን ጨለማ በሚደነቀው ብርሃኑ ለውጦ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ከሞት ወደ ሕይወት፣ከባርነት ወደ ነፃነት ከፍርሃት ወደ ሰላም ከመቅበዝበዝ ወደ መረጋጋት ወደ ዕረፍት ያሸጋገረን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔርን በነገር ሁሉ እናመሰግናለን፡፡ ልባችንም በፍቅሩ የተማረከ፣አንደበታችን ለምስጋና የተከፈተ ይሆናል፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረው የሰው ሰላሙ የሚረጋገጠው በብርሃን ነው፡፡ በጨለማ ውስጥ ሰላም የለም ምክንያቱም ጨለማ በራሱ በሞትና በፍርሃት እንዲሁም በባርነት ውስጥ መኖር ነው፡፡ ለዚህም ጠቢቡ ሰሎሞን የጨለማን አስከፊነትና የብርሃንን መልካምነት በገለጸበት ክፍል፡-“ብርሃን ጣፋጭ ነው ፀሐይንም ማየት ለዐይን መልካም ነው ሰው ብዙ ዘመን በሕይወት ቢኖር በሁሉም ደስ ቢለው የጨለማውን ዘመን ያስብ ብዙ ቀን ይሆናልና የሚመጣውም ነገር ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ”(መክ.፲፩፥፯) በማለት የጨለማ ኑሮ መራራ እንደሆነ ገልጾልናል፡፡ ከዚህ ጨለማ ከነገሠበት ዓለም የጨለማውን ሥልጣን ሽሮ ወደ ብርሃን የመለሰን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ማርያም ተገልጦ ነው፡፡

ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን በዓለም ሲገለጥ ጨለማው ተወገደ፣ሞት ደነገጠ፣ ፍርሃትም ነግሦ የነበረበትን የሰው ሕይወት ለቀቀ፡፡  ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴው  እንደገለጸው፡-“ ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኲሉ ሰብእ ለእለ ይነብሩ ውስተ ዓለም በእንተ ፍቅረ ሰብእ መጻእከ ውስተ ዓለም ወኲሉ ፍጥረት ተፈሥሐ በምጽአትከ እስመ አድኃንኮ ለአዳም እምስሕተት ወረሰይካ ለሔዋን አግዓዚተ እምፃዕረ ሞት ወወሀብከነ መንፈስ ልደት ባረክናከ ምስለ መላእክቲከ፤በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣው ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው አዳምን ከስህተት አድነኸዋልና ሔዋንንም ከሞት ፃዕረኝነት ነፃ አድርገኻታልና የምንወለድበትን መንፈስ (ረቂቁን ልደት) ሰጠኸን ከመላእክት ጋርም አመሰገንህ፡፡”(ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ)  በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለም የተገለጠው ጨለማ በነገሠበት ዓለም ለምንኖር ለሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ሆኖ እንደሆነ ገልጾታል፡፡

አምላካችን ልዑል  እግዚአብሔር ወደ ተናቀው ዓለም የመጣው ስለሰው ፍቅር በመሆኑ የአዳምን በደል ይቅር በማለት ሔዋንንም የሞት ተገዢ ከመሆን ነፃ በማውጣት ዳግመኛም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የምንወለድበትን ረቂቁን ልደት መሠረተልን፡፡ በዳግም ልደትም ሰማያዊውን ዜግነት አንድናገኝ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን ሥልጣን ሰጠን፡፡

ለዚህ ክብር በመብቃታችንም ደስ ብሎን እንድናመሰግነው ከቅዱሳን መላእክት ጋር በምስጋና እንድንተባበር አደረገን፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ፍጹም ፍቅሩን የገለጠበት የማዳን ሥራው ነው፡፡ እኛም እንዲህ የወደደን እግዚአብሔርን በሁሉ ነገር ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ ጨለማውን አርቆ በብርሃን እንድንመላለስ ብርሃን ሆኖ ተገልጦልናልና የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ፡፡

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡- “ከእንቅልፍ የምትነቁበት ጊዜ እንደደረሰ ዕወቁ ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ደርሳለችና ሌሊቱ አልፎአል ቀኑም ቀርቦአል እንግዲህ የጨለማን ሥራ ከእኛ እናርቅ የብርሃንንም ጋሻ ጦር እንልበስ በቀን እንደሚሆን በጽድቅ ሥራ እንመላለስ በዘፈንና በስካር በዝሙትና በመዳራትም አይሁን በክርክርና በቅናትም አይሁን ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት የሥጋችሁንም ምኞት አታስቡ፡፡”(ሮሜ ፲፫፥፲፩) በማለት የገለጸው መዳናችን ወደ እኛ ደርሳለችና የጨለማ ሥራ የተባለው ኃጢአትን አስወግደን በጽድቅ ሥራ አጊጠን መገኘት እንደሚገባን ሲያስገነዝበን ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት እንደተባልን ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን በምግባር አስጊጠን ልንገኝ ይገባናል፡፡ ሕይወታችንን በቀናው ጎዳና መርቶ በብርሃኑ እንድንመላለስ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፡፡ ይቆየን…

“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” (፩ኛዮሐ. ፫፥፰)

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ቀደም ብለን በክፍል ሁለት በተመለከትነው ዳሰሳችን ላይ የሰይጣንን ሥራ ያፈርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ የሚለውን ተመልክተን የሰይጣን ሥራ ምን እንደሆነና ሰይጣን በባሕርዩ የሚታወቅባቸው የክፋት ሥራዎቹ ምን ምን እንደሆኑ ተመልክተናል፡፡ በዚህ በክፍል ሦስት ደግሞ ቀጣዩን እነሆ ብለናል፡፡

ዳምን ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ሰው የሆነበት ዋናው ዓላማ አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ነው፡፡ አባታችን አዳም የቀድሞ ክብሩ የእግዚአብሔር ልጅነት ሲሆን ልጅነቱን በበደል ምክንያት በማጣቱ ኃጢአት ሰልጥኖበት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ሲኦል ተፈረደበት፡፡ እግዚአብሔር ቸርና መሓሪ ነውና ከዚህ ኩነኔ ያድነው ዘንድ ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆነ፡፡ በዚህም የማይታየው ታየ፣  የማይዳሰሰው ተዳሰሰ የማይወሰነው ባጭር  ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነ፣ ልዑል የሆነው አምላክ ከክብሩ ሳይጎድል በትሕትና በሥጋ ተገለጠ፡፡

ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” በማለት የመሰከረለት፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ማርያም ተገልጧልና፡፡ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ሲሆን ከዓለም (ከዘመን በፊት) አስቀድሞ በጌትነቱ የነበረ፣ከዘመን በኋላ   ባሕርየ ሰብእን ገንዘቡ አድርጎ በሥጋ የተገለጠ (ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ) ዓለሙን ለማዳን  ነው፡፡ ለዚህም ነው ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ፡-

“የነበረው የሚኖረው የመጣው ዳግመኛ የሚመጣውም ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ያለመለወጥ ፍጹም ሰው ሆነ አንዱ ወልድ በሥራው ሁሉ አልተለየም የእግዚአብሔር ቃል መለኮት አንድ ነው እንጂ”(ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ) በማለት ቅድምናውን ከገለጠ በኋላ የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት ይቅር ይልዘንድ ሰው መሆኑን መሰከረ፡፡

ይህም ሊቅ በሌላው ክፍል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እያመሰገነ ምሥጢረ ሥጋዌውን  በመመስከር  ሰውን  ያድን  ዘንድ  መወለዱን(በሥጋ  መገለጡን)  ሲያስረዳ፡- “የተባረክሽና ንጽሕት የሆንሽ አዳራሽ ሆይ እነሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ሁሉ በይቅርታው ብዛት ያድን ዘንድ ካንቺ ወጣ (ተወለደ) ፈጽመን እናመስግነው፡፡ ቸርና ሰውን ወዳጅ ነውና”(ውዳሴ ማርያም ዘቀዳሚት)በማለት ቅዱስ ኤፍሬም እንደ መሰከረው አዳም የልጅነት ክብሩን ያጣው በኃጢአት ነውና በይቅርታው ብዛት የሰውን የቀድሞ በደል ይቅር ብሎ በአዲስ ተፈጥሮ ዳግም ከማይጠፋ ዘር በእግዚአብሔር ቃል ተወልዶ የእግዚአብሔርን ልጅነት የሰው ልጅ ያገኝ ዘንድ አምላክ በሥጋ ተገለጠ፡፡

ኃጢአት ሰውን ከክብሩ ታጎድለዋለች ከእግዚአብሔርም ትለየዋለች፤ ሰው ደግሞ  ከእግዚአብሔር ከተለየ  ምንም  አይነት  ክብር የለውም፡፡ ሕይወትንም ያጣል፡፡ ሰው እግዚአብሔር በጸጋ የሰጠውን ክብር በኃጢአት ያጣል፡፡ ከክብር ወደ ጉስቁልና፣ ከነጻነት ወደ መገዛት፣ከልጅነት ወደ ባርነት፣ከከፍታ ወደ ተዋረደ ማንነት፣ ከሕይወት ወደ ሞት ይጓዛል፡፡ ይህም ሰው ከእግዚአብሔር ተለይቶ በሕይወትና በክብር መኖር የማይችል ስለሆነ ነው፡፡  “ሞታ ለነፍስ ርኂቅ እም እግዚአብሔር፤ የነፍስ ሞቷ ከእግዚአብሔር መለየት ነው” እንዲል፡፡ አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን በበላ ሰዓት ወዲያውኑ በሥጋ አልሞተም በመንፈስ ግን ሞተ፡፡  ለዚህም  ነው  ሞት  ከእግዚአብሔር  መለየት  እንደሆነ  ቅዱሳት  መጻሕፍት የሚያስረዱት፡፡ ለአዳም የተሰጠውን ትእዛዝ አለመጠበቅን ስንመለከትና ውጤቱን ስናይ የምናስተውለው ሞት የኃጢአት ውጤት መሆኑን ነው፡፡

“እግዚአብሔር አምላክም አዳምን እንዲህ ብሎ አዘዘው በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ”(ዘፍ.፪፥፲፮)፡፡ አዳም ግን ከእግዚአብሔር የተማረውን ትምህርት (የታዘዘውን) ወደ ጎን በመተው የሰይጣንን ምክር በተቀበለች በሔዋን አማካኝነት ትእዛዘ እግዚአብሔርን በመተላለፍ ዕፀ በለስን በላ፡፡ በዚህን ጊዜ “ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” እንደተባለው በሥጋም በነፍስም ሞተ፤ ክብሩን አጣ፣ጎሰቆለ፣ከጸጋ እግዚአብሔር ተራቆተ፡፡

አዳም ከጸጋ እግዚአብሔር ስለተራቆተ በነፍስ ብቻ ሳይሆን በሥጋውም መፍረስና ወደ መሬት መመለስ ዕጣ ፈንታው ሆነ፡፡ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ሲኦል ተፈረደበት፡፡ ከዚህ ፍርድ ነጻ ያወጣው ዘንድ ወደ ቀደመ ክብሩም ይመልሰው ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ፡፡

ለዚህም ነው ቅዱስ ኤፍሬም በድርሰቱ “ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነጻ ያወጣውና ወደ ቀድሞ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ”(ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ)፡፡ የአዳምና የሔዋን የልጆቻቸውም የልቡናቸው ሐዘን ስለ ሚበላ እንጀራና ስለ ሚጠጣ ውሃ ወይም ስለ ሚለብሱት ልብስና ስለሚያድሩበት ቤት ሳሆን እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ታህል ቦታ አጥቶ መኖር እጅግ የከፋ የሞት ሞት ስለ ሆነ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ቸርነቱ ብዙ ምህረቱ ሰፊ ስለሆነ የአባቶቻችንን የልባቸውን መጸጸት ተመልክቶ ሰውን ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከባርነት ወደ ነጻነት ይመልሰው ዘንድ በሥጋ ማርያም ተገለጠ፡፡  ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም የምሥጢረ ሥጋዌን ነገር ባብራራበት ክፍል ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደበትን ምክንያት ሲጠቅስ “ የነቢያት ሀገራቸው ቤተ ልሔም ሆይ ደስ በልሽ ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ በአንቺ ዘንድ ተወልዷልና፡፡ የቀድሞውን ሰው አዳምን ከምድር(ከሲዖል) ወደ ገነት  ይመልሰው  ዘንድ፤አዳም  ሆይ  መሬት  ነበርክና  ወደ  መሬት  ትመለሳለህ  ብሎ የፈረደበትንም የሞት ፍርድ ያጠፋለት ዘንድ ብዙ ኃጢአት ባለችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች”(ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ) በማለት ያስረዳል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” በማለት የመሰከረው የማይታየው መታየቱ የማይወሰነው መወሰኑ አምላክ በባሕርዩ የማይመረመር፣የማይወሰን፣የማይሞት፣የማይታመም ሲሆን የሥጋን ባሕርይ ባሕርዩ አድርጎ የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ በማድረጉ ነው፡፡ ሰውንም ያዳነውና ወደ ቀድሞ ክብሩ የመለሰው ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም ሰው ሆኖ ነው፡፤ መገለጡም በሥጋ ማርያም ነው፡፡ ሰው ሆኖ ያዳነን የተዋረድነውንና የተናቅነውን ወደ ቀደመው ክብራችን የመለሰው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው፡፡ ይቆየን…

“ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ”

በእንዳለ ደምስስ

አስተርእዮ ቃሉ አስተርአየ፤ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን መታየት፣ መገለጥ ማለት ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማሕፀኗ አድሮ የተወለደበት (በሥጋ የተገለጠበት)፣ አንድነት፣ ሦስትነቱም የተገለጠበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍትም በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚውልና ስለሚከበር “አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል።

ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞት እጅግ ተደንቆ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማንኛውም ሰው ሁሉ የተገባና የማይቀር ነው፣ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ገልጾታል።(ድጓ ዘአስተርእዮ ማርያም)፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ እንዴት ነው ቢሉ፤ ቅዱሳን አባቶቻችን ነገረ ማርያም በተሰኘው የምስጋና መጽሐፍ በስፋት ይተርኩታል፡-

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በስልሣ አራት ዓመቷ ከዚህ ዓለም ዐርፋለች፡፡ እንደምን ነው ቢሉ ሦስት ዓመት ከወላጆቿ ከሐና እና ከኢያቄም፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ ሐርና ወርቅ አስማምታ ስትፈትል ኑራለች፡፡ በዐሥራ አምስት ዓመቷ ከቤተ መቅደስ ወጥታም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኗ አድሮ ተወልዷል፡፡ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከሀገር ሀገር፣ ረሃቡንና ጥሙን ታግሳ እስከ ዕለተ ስቅለቱ አብራው ኑራለች፡፡ በስቅለቱ ጊዜም እጅግ ይወደው ከነበረው ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር በመስቀሉ ሥር ተገኝታለችና እናቱን ለቅዱስ ዮሐንስ አደራ ሰጥቷታል፡፡ ለቅዱስ ዮሐንስ ብቻ ሳይሆን በእርሱ በኩል ለክርስቲያኖች ሁሉ ተሰጥታናለች፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ ቤትም ዐሥራ አምስት ዓመታትን ኖራለች፡፡ እነዚህን ስንደምር ለስልሣ አራት ዓመታት በዚህ ምድር ላይ እንደኖረች እንረዳለን፡፡

ስልሣ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራም ጥር ፳፩ ቀን በዕለተ እሑድ ጌታ እልፍ አዕላፋት መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ “እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ” አላት።  እርሷም “ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ፣ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን?” አለችው። ወደ ሲኦል ወስዶም በሲኦል የሚሠቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ “እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ሁሉ ነፍሳት ቤዛ ይሆንላቸዋል” አላት። እርሷም በሲኦል ያሉትን ነፍሳት ሥቃይ ከተመለከተች በኋላ አዝና “ይሁን” አለችው። ቅዱስ ሥጋዋን ከቅዱስ ነፍሷ ለይቶ ነፍሷን በመላእክት ዝማሬ በይባቤ ወደ ሰማይ አሳረጋት። ደቀ መዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ “የእመቤታችሁን ሥጋዋን በክብር አሳርፉ” አላቸው። (ተአምረ ማርያም)፡፡

ሐዋርያት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴ ሰማኒ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በምቀኝነት ተነሣስተው ቀድሞ ልጇ ተነሣ፣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እርሷን ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? በእሳት እናቃጥላታለን ብለው ተነሡ። ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ በትዕቢት ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው። ጌታችንም መልአኩን ልኮ በሰይፍ እጁን ቆረጠው፣ ከአጎበሩም ተንጠልጥሎ ቀረ። ታውፋንያ የደረሰበትን ተመልከቶ በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት እጁ ተመልሶለታል። ከዚህም በኋላ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ቅዱስ ዮሐንስን አስከትሎ በደመና ነጥቆ፣ ከገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት።

ቅዱስ ዮሐንስ ሲመለስም ደቀ መዛሙርቱ በአንድነት ሆነው “እንደምን ሆነች?” አሉት፡፡ እርሱም “ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ቅዱስ ዮሐንስ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገት አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ ሁለት ሱባኤ ሲፈጸምም እሑድ አምጥቶ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ በሶስተኛው ቀን ማክሰኞ ከመ ትንሣኤ ወልዳ፣ እንደ ልጇ ተነሥታለች።

በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፣ ዛሬ ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?” ብሎ  ከሐዘኑ የተነሣ ከደመናው ላይ ወደ መሬት ሊወድቅ ወደደ፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን እነርሱ ትንሣኤዬንና ዕርገቴን አላዩም አንተ ግን አይተሃልና ተነሣች፣ ዐረገች ብለህ ንገራቸው” ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው። ከዚህ በኋላ ሄዶ ሐዋርያት በተሰበሰቡበት “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው፡፡ “አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ “ሞት በጥር፣ በነሐሴ መቃብር? ተዉ ይህ ነገር አይመስለኝም” አላቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ ሁል ጊዜ ልማድህ ነው፣ አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራልህ” ብሎ ተቆጥቶ ወደ መቃብሯ ሄደው ቢከፍቱት የእመቤታችንን ሥጋ አጡት፡፡ ሁሉም ደንግጠው በቆሙበት ሐዋርያው ቶማስም አታምኑኝም ብዬ እንጂ “እመቤታችንስ ተነሣች፣ ዐረገች” አላቸው፡፡ የያዘውንም ሰበን ሰጥቷቸው ለበረከት ተካፍለውታል። በዓመቱ ሐዋርያት “ቅዱስ ቶማስ ትንሣኤሽንና ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ” ብለው ነሐሴ አንድ ቀን ጾም ጀመሩ፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፲፮ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር አድርጎ፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ካህን፣ ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ በዚያው ላይ ቀድሶ አቁርቧቸዋል። ቤተ ክርስቲያንም ይህንን መታሰቢያ አድርጋ በየዓመቱ ታከብረዋለች። ቅዱስ ያሬድ በዚህ ተደንቆም “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፤ ሞት ለማንኛውም ሰው ሁሉ የተገባና የማይቀር ነው፣ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ተናገረ፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞታ እንደማትቀር፣ እንደምትነሣና እንደምታርግ ጠቢቡ ሰሎሞንም ምሥጢር ተገልጦለት ሲናገር “ወዳጄ ሆይ ተነሺ፣ መልካምዋ ርግቤ ሆይ ነዪ” በማለት ተናግሯል፡፡(መኃ.፪.፲)፡፡ ምንም እንኳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡናን አስተባብራ የያዘች ብትሆንም የሥጋ ሞት ለማንም እንደማይቀር ሲያስረዳም “ርግብየ ተንሥኢ ወንዒ፣ ርግቤ ሆይ ተነሺ፣ ነዪ” አለ፡፡

በተአምረ ማርያም መግቢያ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብርና ቅድስና  የተጠቀሰውን በማስከተል ጽሑፋችንን እናጠቃልል፡- “እንደ እመቤታችን እንደ ማርያም የአብ ማረፊያ የሆነ ማነው? እንደ እመቤታችን እንደ ማርያም የወልድስ ማደሪያ የሆነ ማነው? እንደ እመቤታችን ማርያም የመንፈስ ቅዱስ ቤት የሆነ ማነው? ለሰው ኃጢአት ሳይሠራ መኖር ይቻለዋልን? ከአራቱ ባሕሪያት ከተፈጠረ ሰው ከእመቤታችን በቀር እሳትን የተሸከመ፣ ኃጢአትንም ያልሠራ የለም፤ እመቤታችን ማርያም ከመላእክት ይልቅ ንጽሕት ናት፣ እመቤታችን ማርያም ከሴቶች ሁሉ ትበልጣለች፡፡ የእመቤታችን ማርያም ሐሳብ እንደ አምላክ ሐሳብ ነው፡፡ የእመቤታችን ማርያም መልኳ እንደ አምላክ መልክ ነው፣ የአምላክን መልክ ይመስላል፡፡ እመቤታችን ማርያም ንጽሕት በመሆንዋ አምላክን እንዲያድርባት አደረገችው፡፡ እመቤታችን ማርያም ለአምላክ የደስታ ማደሪያ ሆነችው፡፡ እመቤታችን ማርያም አምላክን በድንግልና ወለደችው፡፡ እመቤታችን ማርያም በነቢያት ትነገር ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በሐዋርያትም ትነገር ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በፍጥረት አንደበት ትመሰገናለች፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች አክብሯት ለእኛ ለኃጥኣን መድኃኒታችን ስለሆነች፡፡ በጎ አገልግሎትም ለሚያገለግሉት ዋጋውን ትሰጠዋለች፣ ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቡናችሁ እመኑባት እሷ መድኃኒታችን ናትና፡፡ በሥዕሏ ፊት ስገዱ ለሥዕሏም ያልሰገደ ግን ከቆመበት ቦታ ይጥፋ፣ ስም አጠራሩም አይታወቅ፡፡ (ተአምረ ማርያም መግቢያ)፡፡ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ጥምቀተ እግዚእ፣ የጌታ ጥምቀት

በመምህር ፍቃዱ ሳህሌ

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በተወለደ በ፴ ዘመኑ በማየ ዮርዳኖስ፣ በእደ ዮሐንስ መጠመቁ ይታወቃል። በዚህ ጥምቀቱም ወንጌላውያን እንደገለጹት ሰማያት ተከፍተዋል። መተርጉማኑ እንዳስተማሩን ሰማያት በርና መስኮት ኖሯቸው፣ መከፈትና መዘጋትም ኖሮባቸው አይደለም፤ ምሥጢራት ተገለጡ ማለቱ ነው እንጂ። በዕለተ ጥምቀት በዮርዳኖስ ወንዝ የተገለጡት ምሥጢራት በርካታ ናቸው። ዋና ዋናዎቹን ብቻ መርጠን በማሳያነት እናቀርባቸዋለን።

ምሥጢረ ሥላሴ፡- በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔርን ሦስትነት የሚገልጡ በርካታ ምንባባት ከቅዱሳት መጻሕፍት በአስረጂነት ይገኛሉ። ይሁንና በተረዳ ሁኔታ መጻሕፍት ይናገሩ የነበረው አንድነቱን በማጉላት ነው። “እስራኤል ሆይ ስማ! አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” እንዲል። (ዘዳ.፮፥፬) በድንግዝግዝ ዓይነት የታወቀው የእግዚአብሔር ሦስትነት በሚገባ የተገለጠው በዚህ ዘመን በክርስቶስ መጠመቅ ነው። (ማቴ. ፫፥፲፮-ፍጻሜ)፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ከወጣ በኋላ አብ በሰማይ ሆኖ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል የምስክርነት ቃሉን ገለጠ። መንፈስ ቅዱስም አርጋብ ከማደሪያቸው በማይንቀሳቀሱበት ሰዓተ ሌሊት በነጭ ርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ አርፎ ታይቷል። በዚህም መሠረት ለዘመናት ሥውር የነበረ የእግዚአብሔር የአካላት ሦስትነት ተገለጠ። በተጨማሪም ምንም እንኳ የመንፈስ ቅዱስ ግብር በጎላ በተረዳ ባይገለጥም የአብ ወላዲነት፣ የወልድም ተወላዲነት በዕለተ ጥምቀቱ ተገልጧል።

የክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፡- ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ከተገለጡት    ምሥጢራት አንዱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ነው። ሥጋን ተዋሕዶ በመገለጡ ግራ የተጋባው ዓለም ማንነቱን ያውቅ ዘንድ ከላይ እንደገለጥነው አብ “ልጄ ነው”  ብሎ፣ መንፈስ ቅዱስም በራሱ ላይ ዐርፎ (ተቀምጦ) በመሰከሩት ምስክርነት የባሕርይ አምላክ መሆኑ ተገለጠ። ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት እንደ ተነበየው ባሕር አይታ ስትሸሽ፣ ዮርዳኖስም ፈርቶ ወደ ኋላው ሲመለስ፣ ክርስቶስም በቦታው ተረጋግቶ እንዲቆም ሲያዝዘውና ፀጥ ብሎ ሲቆም በመታየቱ በዮርዳኖስ የተገኘው እርሱ አምላካቸው፣ ፈጣሪያቸው እንደሆነ ተገለጠ። (መዝ.፸፮፥፲፮፣ ፻፲፫፥፫) “…ሶበ መጽአ ቃል እምሰማይ ለተናብቦ፣ ነድ ለማየ ባሕር ከበቦ፣ ማይ ኀበ የሐውር ጸበቦ፤ቃል ከሰማይ በተሰማ ጊዜ የባሕሩን ውኃ (ዮርዳኖስን) እሳት (መለኮታዊ) ከበበው፤ ውኃውም የሚሄድበት ጨነቀው (ስፍራ ጠበበው)” እንዲል።

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ስለ እርሱ ባስተማራቸው ትምህርቶች የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ገለጠ። መጥምቀ መለኮት ነገረ ክርስቶስን ሲገልጥ፡- “ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ  በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ መንሹ በእጁ ነው፤ ዐውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፤ ስንዴውን በጎተራ ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኗል፤ ጸጋና  እውነት  በኢየሱስ  ክርስቶስ ሆነ፤ መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጅ እርሱ ተረከው፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል፤ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” እያለ የሰጠው ምስክርነት የባሕርይ አምላክነቱን ግልጽ አድርጎታል። ይህንኑ ሲያጠቃልል “እኔም አላውቀውም ነበር፤ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ  እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ።…በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፡- መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ።”  (ዮሐ.፩.፴፩፥፴፭) ብሏል።

ከላይ የገለጻቸው የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ምስክርነቶች የዕሩቅ ብእሲ (የሰው) ተግባራት እንዳይደሉ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ፍጡር ሊከውናቸው እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ለዚህ ነው መጥምቁ “እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክሬአለሁ”  በማለት ያጠቃለለው። “መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር (በተዋሕዶተ ሥላሴ) ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን”  እንዲል። (ዮሐ. ፫፥፪)

የዕዳ ደብዳቤያችን መቀደዱ፡ ከዚሁም ጋር አንዱ የዕዳ ደብዳቤ መቀደዱ ተገለጠ። ዲያብሎስ “አዳም የዲያብሎስ ባርያ፣ ሔዋን የዲያብሎስ ገረድ” በማለት መከራ አጽንቶ ያስፈረማቸው የዕዳ ደብዳቤ ነበረ። ይህንንም በሁለት ቅጅ አድርጎ አንዱን በዮርዳኖስ ጥልቅ ባሕር፣ አንዱንም በሲኦል ጥልቅ ረግረግ ቀብሮት ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ እንደ ሰውነቱ ረግጦ፣ እንደ አምላክነቱም አቅልጦ በዚህ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። ከዚህም የተነሣ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል”  በማለት ያስተማረን። (ቆላ.፪፥፲፬) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን በማድረጉም ሁሉን ማድረግ የሚችል እውነተኛው የሰው ልጆች ሐኪምና መድኃኒት መሆኑ ተገለጠ። “ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” እንዲል። (፩ኛ ዮሐ. ፫፥፰)

ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ መተባበራችን፡– በተጨማሪም ጥምቀተ ክርስቶስ ሞቱንና ትንሣኤውን እያዘከረ ሰዎች ሁሉ በሚጠመቁበት ጊዜ ከክርስቶስ ሞት (መስቀል) እና ትንሣኤ ተሳታፊ መሆናቸው የተገለጠበት ታላቅ ምሥጢር ነው። ለመጠመቅ ወደ ማዩ ሲወርዱ ሞቱን፣ መቀበሩን፣ ከውኃው ሲወጡ ደግሞ ትንሣኤውን ይመሰክራሉ። ግብሩ ሦስት ጊዜ መደጋገሙም ክርስቶስ በከርሠ መቃብር ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ማደሩንና ምሥጢረ ሥላሴን ይገልጣል።   “እንግዲህ   ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።”(ሮሜ.፮፥፬-፮) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የገለጠው ይህንን ነው። በተመሳሳይም ይኸው ሐዋርያ “በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበራችሁ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ።”  (ቆላ.፪፥፲፪) በማለት በጥምቀቱ የተገለጠውንና የተገኘውን ነገረ ድኅነት አመሥጥሮታል።

ከክርስቶስ ጋርና እርስ በእርሳችን አንድ መሆናችን፡ በጌታችን ጥምቀት ከተገለጡት ምሥጢራት መካከል ሌላኛው የሰው ልጆች ሁሉ በሥጋ ከአንድ አባትና እናት (አዳምና ሔዋን) የተገኙ እንደመሆናቸው በተጠመቁ ጊዜ ደግሞ በመንፈሳዊ ልደት ዳግመኛ አንድ መሆናቸው የተገለጠበት ምሥጢር ነው። በቀናች ሃይማኖት ሆነው የተጠመቁና የሚጠመቁ ሁሉ ምድራዊ የሆነ ማንኛውም ዓይነት መሥፈርት ሳያግዳቸው ወንድማማችና እኅትማማች ይሆናሉ።   ሁሉም ከአንድ አብራክ (ከመንፈስ ቅዱስ) የተከፈሉና በአንድ ማኅፀነ ዮርዳኖስ ማየ ጥምቀት በመንፈስ ቅዱስ ግብር ተገኝተው የተወለዱ ናቸውና። ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋል” በማለት እንዳስተማረው። (ገላ.፫፥፳፯)። እንደገናም “አይሁድ ብንሆን፣ የግሪክ ሰዎችም ብንሆን፣ ባርያዎችም ብንሆን፣ ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና፤ ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናልና” እያለ በግልጽ አስተምሮናል። (፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፲፫)።

የክርስቶስ መካነ ጥምቀት ተፈጥሮአዊ ገጽታ በራሱ የሰው ልጆች በክርስቶስ ጥምቀት  ያገኙትን  አንድነት ያሳያል። እንደሚታወቀው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊጠመቅበትና ምሥጢራትን ሊገልጥበት ከአፍላጋት ሁሉ የመረጠው ወንዝ ዮርዳኖስ ነው። ይህ ወንዝ ከላይ ነቅዑ (ምንጩ) አንድ ሆኖ ይወርዳል። ከዚያም አወራረዱ በሁለት የተከፈለ ይሆናል። እነዚህም ሁለት ወንዞች “ዮር” እና “ዳኖስ” በመባል ይታወቃሉ። ወርደው ዳግመኛ አንድ ላይ ተገናኝተው “ዮርዳኖስ”   ተብለው ይፈሳሉ። ዲያብሎስ መገናኛቸው ላይ ከተፈጠረው ጥልቅ ባሕር ነበር አንዱን የዕዳ ደብዳቤ የቀበረው። ጌታችንም ከዚሁ መገናኛ ባሕር ላይ ነው የተጠመቀው። ይህንንም በማድረጉ አንድ ሆነው ወርደው ተለያይተው የነበሩ ወንዞች እንደተገናኙ ሰዎች ሁሉ የአዳምና የሔዋን ልጆች ሆነው (አንድ ሁነው) ሳለ ሕዝብ፣ አሕዛብ፣ የተገረዘ፣ ያልተገረዘ፣…በመባባል ተለያይተው የነበሩ ሰዎች በክርስቶስ ጥምቀት ያለምንም ልዩነት አንድ መሆናቸው በምሥጢር ተገልጧል። “ዮር”  ከግዙራን ወገን፣  “ዳኖስ”ም ከኢ-ግዙራን ወገን ሆነው ሳለ አንድ ሆነው በመፍሰሳቸው ሰዎች ያለ ልዩነት በጥምቀት አንድ እንደሚሆኑ ሲመሰክር ኖሯል ይኖራልም።

ከመገለጥ ጋር በተያያዘ ጌታችን መድኃኒታችን   ኢየሱስ   ክርስቶስ ሳይውል ሳያድር ገዳመ ቆሮንቶስ ገባ። ዐርባ መዓልት ዐርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ከገዳም ወጥቷል። በሦስተኛውም ቀን ወደ ሠርግ ቤት ተጠራ።

ቃና ዘገሊላ

ከጥር ዐሥራ ሁለት እስከ ዐሥራ ስምንት ባለው ጊዜ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የምትዘምረው መዝሙር አንድ ወጥ ምሥጢር ያለው ነው። “ሖረ ኢየሱስ በትፍሥሕት ውስተ ከብካብ እንዘ ይገብር ተአምረ ወመንክረ በውስተ አሕዛብ፤ ጌታችን ኢየሱስ በደስታ ወደ ሠርጉ ቤት ሔደ፤ በአሕዛብ መካከል ድንቅ የሆነ ተአምርን እያደረገ።”  እያለ የሚቀጥል ነው መዝሙሩ። “ክብሩን ገልጦ አሳይቷቸዋልና ደቀ መዛሙርቱ አመኑበት። ውኃን ቀድታችሁ ጋኖቹን እስከ አፋቸው ድረስ ሙሏቸው አላቸው። የአሳላፊዎቹ አለቃ የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በተአምር ያደረገውን በረከት ቀምሶ አደነቀ።” ቤተ ክርስቲያንም በዚህ መሠረት አዳኛችንና ተስፋችን የሆነ ወልደ እግዚአብሔር ውኃውን ግሩም ወይን ወደ መሆን ለውጦታልና። እያለች ትዘምራለች፤ እኛም እንዘምራለን። በዚህ ሠርግ ቤት የተገለጡ ዋና ዋና ምሥጢራትም የሚከተሉት ናቸው፡፡

የድንግል ማርያም አማላጅነት፡ ይህን የቃና ዘገሊላውን የዶኪማስ ሠርግ በተመለከተ በዝርዝር የሚናገረው የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ምዕ. ፪ ቁጥር ፲፩ ላይ በግሩም ሁኔታ ነው የጠቀለለው። “ኢየሱስ ይህን የተአምራት መጀመሪያ በቃና ዘገሊላ አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” በማለት ያስረዳናል። በዚህ ሠርግ ቤት እንደሚታወቀው ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት ተፈጥሮ ነበር፤ የወይን ጠጃቸው አልቆ፣ የሚሰጡትም አጥተው በኀፍረት ተሸማቅቀዋልና። በዚህ አስቸጋሪ ሰዓት “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” በማለት በእነሱና በልጅዋ መካከል ምልጃዋን ያቀረበችው እናታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። ከአንቺ ጋር ምን አለኝ፤ ያልሽኝን ላላደርግልሽ ከአንቺ ሰው ሆኛለሁን? ባላትም ጊዜ ‹‹የሚላችሁን አድርጉ!”  ብላ በማዘዝ የሠርጉ ባለቤቶች (ደጋሾች) ከስጋትና መረበሽ ከኀፍረትም ነጻ እንዲሆኑ ምክንያት በመሆኗ የጭንቅ አማላጅነቷ ተገለጠ። ለሰው ልጆች ሁሉ ያላት ፍቅርና አዛኝነቷ፣ የጭንቅ ቀን ደራሽነቷ፣ ልመናዋም አንገት የማያስቀልስ፣ ፊት የማያስመልስ መሆኑ በግልጽ ታወቀ።

ይህን ድንቅ ምሥጢር በተመለከተ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ላይ “ድንግል ውኃውን ወይን ወደ መሆን እንደሚለውጠው አላወቀችም፤ ነገር ግን በአብ ጥላ (ጽላሎት) እንደፀነሰችው በልዑል ኃይልም እንደወለደችው ታውቃለችና፤ ስለዚህም ድንግል የምሥራቹን ከነገራት መልአክ ዘንድ አባቱ ሰማያዊ እንደሆነ ተረድታለችና ስለ ወይን ማለደችው፤ በልቧ ድንቆችን የሚያደርግ የእርሱ ልጅ እንደ አባቱ ድንቅን ያደርጋልና አለች።››  በማለት የድንግል ማርያም አማላጅነት የእርሱም (የልጇ) የባሕርይ አምላክነት መገለጡን ጽፎልናል። (የቃና ዘገሊላ ምንባብ ቁጥር. ፰)

የክርስቶስ ክብር፡- ጌታችን  አምላካችን  መድኃኒታችን  ኢየሱስ  ክርስቶስ በቅዱስ  ወንጌል  እንደተጻፈውና  ከላይ  እንደገለጽነው በዚህ ሠርግ ቤት ክብሩን ገልጧል። “የቱን ክብሩን ነው ለመሆኑ የገለጠው?” የሚል ጥያቄና ምላሽ መፈለግ ተገቢ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጠው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈልን ወንጌል ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንዲህ ሲል፡- “አርአዮሙ ስብሐቲሁ አምኑ ቦቱ አርዳኢሁ፤ አምላካዊ ተአምራቱን አሳያቸው፣ ደቀ መዛሙርቱም አመኑበት” (ቅዱስ ያሬድ)። የሥጋን እንግድነት ሲያይ “አክብረኝ” አለ እንጂ ክብሩስ ቅድመ ዓለም ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነበረና በአንድነት፣ በሦስትነት የሚሰለስ፣ የሚቀደስ አምላክ ነው። በቃና ዘገሊላ “ክብሩን ገለጠ”   ያለውም የአምላክነትን ሥራ ሠርቶ የባሕርይ አምላክ መሆኑን የገለጠበትን ነው። ጣዕም፣ መልክ፣ መዓዛ ያልነበረውን ውኃ በሐልዮ (በሐሳብ) ወደ ተደነቀ ወይን ጠጅነት የቀየረና ሊቀይርም የሚችል ያለ እግዚአብሔር በቀር ሌላ የለምና። ከዚህ ሁሉ ጋር ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውነት ጣዕም፣ መልክና መዓዛ በኃጢአቱ ወደ ተበላሸበት የሰው ልጅ መጥፎ ሕይወት መጥቶ ወደ ተደነቀው (ፈጣሪውን ወደሚመስልበት) ማንነቱ የሚመልሰው መሆኑን በዚህ ሠርግ ላይ በአደረገው ተአምር ውስጥ ገለጠልን። በዚህ የመገለጥ ዘመን መድኃኔዓለም ክርስቶስ የገለጠውና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የምታመሠጥራቸው ትምህርቶች በርካታ ናቸው። ስለዚህ አስተርእዮ ማለት መገለጥ ማለት እንደሆነና የተገለጡትም ምሥጢራት በረካታ እንደሆኑ ተመልክተናል።

ማጠቃለያ

“አሥተርአየ ዘኢያስተርኢ ኮነ እሙነ አሥተርእዮቱ ለመድኃኒነ ክርስቶስ ፤ የማይታየው ታየ፣ የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መታየቱም የታመነ ሆነ። ተገሠ ዘኢይትገሠሥ ወዘይትርአይ ተርየ፣ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ፣ የማይታየው ታየ” በማለት ቅዱስ ያሬድ የክርስቶስን መገለጥ ገልጿል።

“ዘመነ አስተርእዮ፤ የመገለጥ በዓል ነው” የሚለውን ማወቅ፤  ምን  ምን  እንደተገለጠም  መረዳት  ጠቃሚ ጉዳይ ነው። ይሁንና ዋናው ጠቃሚ ቁም ነገር ከዚህ ከፍ ያለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። የመገለጥ ሃይማኖት የሆነችውን  ክርስትናን  ይዞ፥  ክርስቲያንም  ተብሎ ተጠርቶ ተደብቆ መኖር ማክተም አለበት። ብዙዎቻችን ክርስትናችንን ከመግለጥ ይልቅ ሸፋፍነን ደብቀነዋል። ከላይ እንደገለጥነው መንፈሳዊው የሕይወት ምግብ ጠፊ በሆነ ምድራዊ መብል መጠጥ ተሸፍኗል። ዘለዓለማዊው በጊዜያዊው፣ መንፈሳዊው በሥጋዊው፣ የማይጠፋው በሚጠፋው፣. . .ወዘተ ተደብቋል። እኛም ራሳችንን በነዚህ ጭንብሎች ውስጥ ተደብቀን ራሳችንን እየደለልን ነው።

ቅዱስ ያሬድ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ “አሥርአየ ዘኢያስተርኢ ኮነ እሙነ አሥተርእዮቱ ለመድኃኒነ ክርስቶስ፤ የማይታየው ታየ፣ የጌታችን መድኃኒታን የኢየሱስ ክርስቶስ መታየቱም የታመነ ሆነ” በማለት ተናገረ። ከዚህም በተጨማሪ “ተገሠ ዘኢይትገሠሥ ወዘኢይትረአይ ተርእየ፤ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ፣ የማታየው ታየ” ብሏል።

ሃይማኖቴ የመገለጥ ነው፤ ዘመኑም የመገለጥ ነው፤ የምንል እኛ ክርስቲያኖች በነገሮች፣ በቦታና በጊዜያት ሁሉ  ሳንፈራ፣  ሳናፍርና  ሳንሸማቀቅ  ክርስትናችንን መግለጥ አለብን። ባለንበት የሰማዕታት ዘመን “ማዕተባችን ከሚበጠስ አንገታችን ይበጠስ!” እያሉ ራሳቸውን የሰጡ የተገለጡ ክርስቲያኖችን አይተናል። ከዚህ አንጻር በሰዎች መካከል አማትበንና ስመ ሥላሴን ጠርተን ማዕድ መቁረስ የሚያሳፍረንና የሚያሸማቅቀን እኛ ምን ልንባል እንችላለን?

ስለዚህ ይህ በዓል እየነገረን ያለው “የተገለጠ ክርስትና ይኑራችሁ! ክርስትና ለድርድር አይቀርብምና መስቀሉን ተሸክማችሁ  ወደ  ቀራንዮ  ተጓዙ!፣  …  በማስመሰል (ለሰው ይምሰል) የተመላለሳችሁበት ዘመን ይብቃችሁ! ለሥጋ የምትጨነቁትን ያህል ለነፍሳችሁም ቦታና ክብር ስጡ! ለምስክርነት ራሳችሁን አዘጋጁ!. . .” የሚሉትን ጭብጦች ነው። እኛ ቤተ ክርስቲያንን ጠጠር መጣያ እስኪጠፋ እየሞላን፤ ልባችን በጥላቻ፣ በዘረኝነት፣ በዝሙት፣ በስርቆት፣ በኑፋቄ፣ በትዕቢት፣. . . ከተሞላ ምን ይረባናል? ክርስቲያናዊ ሕይወታችን በፍቅር፣ በሰላም፣ በንጽሕና፣ በአንድነት፣ በምሕረት፣ በይቅርታና በቅዱሱ ምሥጢር የተገለጠና የታተመ ሊሆን ካልቻለ የተፈለገውንና ሰማያዊውን ጥቅም ሊያስገኝ አይችልም። ስለዚህ ይህን ድንቅና ልዩ ምሥጢር የጠገለጠበትን በዓል ማክበር በሚገባን መልኩ አክብረን በረከተ ሥጋ፣ በረከተ ነፍስ እንድናገኝ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን።

“ከተራ”

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

የከተራ በዓል የሚከበረው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አንድ ቀን ሲቀረው በዋዜማው ነው፡፡ ይህም ከጌታችን መድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት በዓል አከባበር የሚጀምረው ሁል ጊዜ ጥር ፲ ቀን የከተራን በዓል ከማክበር ነው፡፡ በዚህ ዕለት ታቦታቱ ወደ ተዘጋጀላቸው የማደሪያ ቦታ በልዩ ድምቀት በዝማሬ ታጅበው ይወጣሉ፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱም ምሳሌ ነው፡፡

“ያን ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ዮሐንስ ግን እኔ በአንተ ልጠመቅ እሻለሁ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ አይሆንም አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አሁንስ ተው እንዲህ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና አለው …”(ማቴ፫፥፲፫) በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄድ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም የበዓሉ ዋዜማ ከተራ በዓል ተብሎ በጾም ታስቦ የታቦታቱን መውጣትና ወደ ማደሪያቸው የመሄድ ሥርዓት በድምቀት የሚከበርበት ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው፡፡

“ከተራ” የሚለው ቃል “ከተረ ከበበ ካለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ፍቺው ውኃ መከተር፣  መገደብ ማቆም፣ ማገድ፣ መከልከል” ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽነው የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡  ድንኳንም  ከሌለ  ዳስ  ሲጥል  ይውላል፡፡  የምንጮች  ውኃ  ደካማ  በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል፡፡

ይህም በየዓመቱ ጥር ፲ ቀን የምእመናኑ አብዛኛው ሥራ ውኃውን መከተርና መገደብ በመሆኑ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውኃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር ፲፩ ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው፡፡ በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት››፣ ‹‹የታቦት ማደርያ›› እየተባለ ይጠራልና ለዚህ ሥርዓት መፈጸም አስቀድሞ በዋዜማ የሚደረግ ዝግጅት ነው፡፡ ከበዓለ ጥምቀቱ ረድዔት በረከት ይክፈለን አሜን፡፡

“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” (፩ኛዮሐ.፫፥፰)

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ክፍል ሁለት

ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የመገለጡ (ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የመወለዱ) ነገር እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ወፍ ዘራሽ ድንገት የሆነ አይደለም፡፡ አዳምና ሔዋን ከገነት ከተሰደደ በኋላ ተከትሎ እግዚአብሔርን ያህል አምላክ፣ ልጅነትን ያህል ጸጋ፣ ገነትን ያህል ቦታ አጥተን እንዴት መኖር ይቻለናል ብለው ስለ በደላቸው ንስሓ በመግባታቸው አብዝተውም በማልቀሳቸው ወደ ልባቸውም በመመለሳቸው እግዚአብሔር ምሕረት እንደሚያደርግላቸው ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይህም ተስፋ፡- “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እም ወለተ ወለትከ ወእድህክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ  በመስቀልየ ወበሞትየ፤ በአምስት ቀን ተኩል ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በሜዳህ ድሄ፣ በመስቀል ተሰቅዬ በሞቴ አድንሃለው” የሚል ነው፡፡ (መጽ. ቀሌምንጦስ)፡፡

ይህንንም ተስፋ እግዚአብሔር ለአዳምና ለሔዋን ከሰጣቸው በኋላ በየዘመኑ ቅዱሳን አበውን እያስነሣ በተለያየ ምሳሌ እያሳየ በራእይ እየገለጠ፣ በነቢያት ላይ አድሮ ትንቢት እያናገረ ሕዝቡን ሲያጽናና በተስፋ ሲጠብቅ ነበር፡፡ ያ የተስፋ ጊዜ ሲደርስ ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆነ (ተወለደ)፡፡

ለዚህም ነው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲኖች በላከላቸው መልእክቱ:- “ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ፣ የኦሪትንም ሕግ ፈጸመ፣ እኛ የልጅነትን ክብር እንድናገኝ በኦሪት የነበሩትን ይዋጅ ዘንድ ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን እግዚአብሔር አባ አባቴ ብላችሁ የምትጠሩትን የልጁን መንፈስ በልባችሁ አሳደረ”(ገላ.፬፥፬) ያለው፡፡ እንደ ተስፋ ቃሉ ከጊዜው ሳይቀድምና ሳያሳልፍ ጊዜውና ሰዓቱ ሲደርስ ተወለደ፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ተወለደ፡፡ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች”(ኢሳ.፯፥፲፬)  በማለት እመቤታችን ቅድመ ወሊድም ሆነ ድኅረ ወሊድ ድንግል እንደሆነች ጠቅሶ እርሷ እመ አማኑኤል፣ እርሱ ደግሞ አምላክ ወሰብእ መሆኑን አስረድቶ አምላክ እንዲወለድ አስቀድሞ መወለድ ነቢዩ ኢሳይያስ አብሥሮናል፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ (የመወለዱን) ዓላማ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስረዱት ከብዙ በጥቂቱ ብንመለከት፡-

የሰን ሥራ ይሽር ዘንድ

ሰይጣን (ዲያብሎስ)  የሚገለጥባቸው የራሱ  ባሕርያት  አሉት፡፡  ከእነርሱም  ውስጥ  ትዕቢት፣

ነፍሰ ገዳይነት፣ ሐሰተኝነት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ዕቢ፡- ዲያብሎስ እየተዋረደ ከብሬአለሁ የሚል፣ ወደ ጥልቁ እየወረደ ወደ ከፍታ እየወጣሁ ነው፣ የሚል ከጸጋ እግዚአብሔር ተራቁቶ ሳለ የክብር ካባ ደርቤአለሁ የሚል፣ ውድቀቱን ትንሣኤ  አስመስሎ የሚናገር ሐሰተኛ  ነው፡፡

የዲያብሎስን (የሰይጣንን) ትዕቢት ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል “አንተ በንጋት የሚወጣ የአጥቢያ ኮከብ ሆይ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ? ወደ አሕዛብም መልእክትን የላክህ አንተ ሆይ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቀጠቀጥህ! አንተም በልብህ፡- ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ ዙፋኔንም ከሰማይ ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፣ በሰሜንም ዳርቻ በረዣዥም ተራሮች ላይ እቀመጣለሁ፣ ከደመናዎችም ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፣ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ፡፡ ዛሬ ግን ወደ ሲኦል ትወድቃለህ ወደ ምድር ጥልቅም ትወርዳለህ” (ኢሳ.፲፪፥፲፫) ይላል፡፡

ይህ ስሑት የትሕትና ተቃዋሚ ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ሊሆኑ የሚወዱ ሁሉ የትዕቢትን ካባ አውልቀው ትሕትናን እንደ ልብስ ሊለብሱት እንዲገባ  ያስተማረው፡፡ አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ምንጩ ከዲያብሎስ የሆነውን ትዕቢት  እንደሚጠላና ትዕቢት የሚያዋርድ ትሕትና ግን የሚያከብር መሆኑን በወንጌል አስተምሮናል፡፡ “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና ራሱንም ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ይከብራልና” (ማቴ.፳፫፥፲፪) እንዲል፡፡

“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” በማለት ቅዱስ ዮሐንስ የተናገረውም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከከፍታ ወደ ዝቅታ ወርደን፣ በሲኦል ባርነት፣ በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዘን ወደ ነበርን ወደ እኛ ንጽሕት ዘር ከሆነች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በፍጹም ትሕትና መወለዱንነው፡፡ “አምላክ ሰው ሆነ” ስንልም የሚደንቀን በፍጹም ትሕትና በቤተልሔም በከብቶች በረት መወለዱ ነው፡፡

ፍሰ ገዳ

ዲያብሎስ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ እርሱም የመጀመሪያው ነፍሰ  ገዳይ ነው፡፡ ዲያብሎስ ነፍስን ከእግዚአብሔር እንድትለይ ኃጢአት በማሠራት እንድትበድል በማድረግ፤ ሥጋን በጭካኔ አንዱ በሌላው፣ ወንድም በወንድም፣ ልጅ በአባት፣ አባትም በልጅ ላይ፣ ወንድም በእኅቱ ላይ፣ እኅትም በወንድሟ፣ ባል  በሚስቱ፣ ሚስትም  በባልዋ  ላይ  በክፋት  እንዲነሣሱ  በማድረግ የገዳይነትን  ሥራ  ይሠራል፡፡ ይህም ከጥንት ጀምሮ  አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስን እንዲበሉና ሕገ እግዚአብሔርን እንዲተላለፉና እንዲሞቱ ያደረገ ነው፡፡ እንዲሁም በቃኤል ላይ አድሮ አቤልን ያስገደለ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዲያብሎስ ነፍሰ ገዳይነት እንዲህ በማለት ተናግሯል፡፡ “የአባታችሁንም  ፈቃድ  ልታደርጉ  ትወዳላችሁ  እርሱ  ከጥንት  ጀምሮ  ነፍሰ  ገዳይ ነው፡፡”(ዮሐ.፰፥፵፫)::

ት፡ ዲያብሎስ (ሰይጣን) ሐሰተኛ  ነው፡፡  ሐሰተኛ  ብቻም  ሳይሆን  የሐሰት  መገኛ ነው፡፡ ለመጀመሪያ  ጊዜ  በመላእክት  ከተማ  ሐሰትን  ከራሱ  አፍልቆ  ተናግሯልና  ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ እንደጠቀሰው “በእርሱ ዘንድ እውነት የለምና ሐሰትንም በሚናገርበት ጊዜ ከራሱ አንቅቶ ይናገራል ሐሰተኛ ነውና የሐሰትም አባት ነውና”(የሐ.፰፥፵፬)፡፡

ዓለሙን ሁሉ እያሳተ ኃጢአትን ጽድቅ፣ ውርደትን ክብር አስመስሎ እያሳየ ከእግዚአብሔር የሚለየው ይኸው የሐሰት አባት የተባለው ዲያብሎስ ነው፡፡ በየትኛውም ምክንያት ይሁን ሰው ኃጢአት የሚሠራው የራሱ ስንፍና እንዳለ ሆኖ በዚህ ሐሰተኛ በሆነው በሰይጣን ወጥመድ ነው፡፡

ሰይጣን(ዲያብሎስ) የሐሰት መገኛ ነው፡፡ የሐሰት አባት የተባለውም ሐሰትን ከራሱ አፍልቆ የሚናገር የሐሰት አስተማሪ ስለሆነ ነው፡፡ ዲያብሎስ(ሰይጣን) እነዚህንና መሰል ክፉ ተግባራትን የሚፈጽም እና የሚያስፈጽም በመሆኑ ይህንን እኩይ ተግባሩን ከሰው ልቡና ነቅሎ ለመጣል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠበትን ዓላማ ሁለተኛውን ክፍል በቀጣዩ ዝግጅት እንመለከታለን፡፡ እስከዚያው ቸር እንሰንብት፡፡

ግዝረት

ግዝረት ማለት መገረዝ(ከሸለፈት ነጻ መሆን) ማለት ነው፡፡ የተጀመረውም በአበ ብዙኃን አብርሃም ነው፡፡  “በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቋት ቃል ኪዳኔ ይህች ናት፣ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፡፡ የሰውነታችሁን ቍልፈት ትገረዛላችሁ፣ በእኔና በእናንተም መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል፡፡ ሕፃኑንም በስምንተኛው ቀን ትገርዙታላችሁ”(ዘፍ.፲፯.፲) በማለት እግዚአብሔር ለአብርሃም ቃል ኪዳኑን ይጠብቅ ዘንድ፣ ከእርሱም በኋላ የሚመጣው ትውልድ ይህንን ቃል ኪዳን ይጠብቅ ዘንድ ተናግሮታል፡፡

ግዝረት ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ንዑሳን በዓላት የሚባሉትም ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ፣ ግዝረት፣ ቃና ዘገሊላ፣ ልደተ ስምዖን፣ ደብረ ዘይት፣ የመስከረም ፲፯ እና የመጋቢት ፲ መስቀል የምናከብራቸው በዓላት  ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ግዝረት በየዓመቱ ጥር ፮ ቀን በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንግዲህ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ለማድረግ የአባቶቻችንንም ተስፋ ያጸና ዘንድ ለግዝረት መልእክተኛ ሆነ እላለሁ” በማለት ለሮሜ ክርስቲያኖች ጽፎላቸዋል፡፡ የክብር ባለቤት መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተ ግዝረት በመግባት የኦሪትን ሕግ ፈጽሟል፣ በሥጋው ግዝረትንም ተቀበለ፣ ለአባቶች የሰጠውንም ቃል ኪዳን ፈጸመ፡፡(ሮሜ.፲፭፥፰)፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው በስምንተኛው ቀን እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ግዝረት ይፈጸምለት ዘንድ ሕፃኑ ጌታችንን ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት፡፡ ስሙም ገና ሳይፀነስ የእግዚአብሔር መልአክ ባወጣለት ስም ኢየሱስ” ተብሎ ተጠራ(ሉቃ.፪፥፳፩-፳፬)፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ሲገረዝ የሊቀ ካህን ልጅ ነው ብለው ሊገርዙት ወደ እርሱ መጡ፡፡ ጌታችን ግን ወደ ምድር የመጣው ለትሕትና ነው እንጂ ለልዕልና አይደለምና ወሰዱት አለ (ትርጓሜ ወንጌለ ሉቃስ)፡፡

አይሁድ የአብርሃም ልጅ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ግዝረት ማኅተም ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት የሚመሩ መሆናቸውንና በአንድ አምላክ ማመናቸውን የገለጡበት ነው፡፡ አይሁድ በግዝረት የአብርሃም ልጅነታቸውን እንዳረጋገጡ፣ ክርስቲያኖችም በጥምቀት የሥላሴ ልጅነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ጥምቀት እንጂ መገረዝ፣ አለመገረዝ አይጠቅምም፡፡

ጥር ስድስት በሚነበበው ስንክሳር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አረጋዊ ዮሴፍን ሕፃኑን የሚገርዝ ባለሙያ ፈልጎ እንዲያመጣ እንደነገረችው፣ አረጋዊውም ባለሙያውን ፈልጎ እንዳመጣ ይናገራል፡፡ ባለሙያውም “ሕፃኑን በደምብ ያዙልኝ” ብሎ ለመግረዝ ሲሰናዳ “ባለሙያ ሆይ ደሜ ሳይፈስ መግረዝ ትችላለህን?” ብሎ እንደጠየቀው፣ ከስቅለቱ በፊት ደሙ እንደማይፈስ እንዳስተማረው፣ በዚህም ምክንያት ለመግረዝ የመጣው ባለሙያ፣ አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን አምኖ እንደሰገደለት፣ ለመግረዣ ያዘጋጀው ምላጭም እሳት ላይ እንደተጣደ ቅቤ መቅለጡን ይተርካል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእመቤታችንን ማኅተመ ድንግልና ሳይፈታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተፀንሶ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲሞላው በድንግልና እንደመወለዱ ግዝረቱም አይመረመርም፡፡ እንዲሁም በተዘጋ ቤት ወደ ሐዋርያት እንደ ገባና እንደ ወጣ ሁሉ እርሱ በሚያውቀው ረቂቅ ጥበብ ምንም ደም ሳይፈሰው መገረዙ በተአምር ተገለጠ፡፡

ገራዡም የጌታችንን ቃል ከመስማቱ ባሻገር በሥጋው ላይ የተደረገውን ተአምር ባየ ጊዜ እጅግ አደነቀ፡፡ ከክብር ባለቤት ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር በታች ወድቆም ሦስት ጊዜ ሰገደና “በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የእስራኤልም ንጉሥ ነህ!” በማለት በክርስቶስ አምላክነት አመነ፡፡ ከዚህ በኋላ ያየውንና የሰማውን ሁሉ እየመሰከረ ወደ ቦታው ተመለሰ፡፡ (ስንክሳር ጥር 6)፡፡

በአጠቃላይ ግዝረት በኦሪት የአብርሃም ልጅነትን፣ የአብርሃምን ሃይማኖት መያዝን ማረጋገጫ ማኅተም ሲሆን በሐዲስ ኪዳን በጥምቀት ተተክቷል፡፡ ለአማናዊው ግዝረት /ለጥምቀት/ ምሳሌ በመሆኑም በሥራ የአብርሃም ልጅነትን፣ በእምነት የሥላሴ ልጅነትን አግኝተንበታል፡፡  በዮርዳኖስ የተቀበረው የባርነታችን ደብዳቤም በጌታችን ጥምቀት የሚደመሰስ መሆኑን በምሳሌ ያወቅንበት ግዝረት ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የነቢያት ሀገራቸው ቤተ ልሔም ደስ ይበልሽ

ክፍል ሁለት

በዲ/ን ዐቢይ ሙሉቀን

ደስ ይበልሽ የተባለች ማን ናት?

ቤተ ልሔም

ደስ ይበልሽ፡ለሀገሪቱ ነው፡፡ በሀገሪቱ ሰዎችን መናገር ነው፡፡ ሰው በሀገሩ፣ ሀገሩ ደግሞ በሰው ይጠራል፡፡ ስለዚህ ቤተ ልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ ፡፡ ምክንያቱም እስራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ክርስቶስ ባንቺ ይወለዳልና፡፡ ሀገር ደግ ሰው ሲወለድበት፣ ደግ ሰው ሲወጣበት  ያስደስታል፡፡ አንዳንዴ “ሀገር ይባረክ” ተብሎ ይመረቃል፡፡ ሰው ይውጣበት ማለት ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሀገርም በሰው ክፋት የተነሣ ሰው አይውጣብሽ ተብላ ልትረገም ትችላለች፡፡ በአዳም ምክንያት ምድር ተረግማለች፡፡ “እግዚአብሔር አምላክም አዳምን አለው የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝኩህ ከዚያ ዛፍም በልተሃልና ምድር በሥራህ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ እሾኽንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ፡፡” (ዘፍ.፫፥፲፯-፲፰፡፡) ነገር ግን ከዚህ መርገም ድኖ ደግ ሰው ማስገኘት ያስደስታል፡፡ ይልቁንም ቤተ ልሔም እስራኤልን የሚያድናቸው አምላክ፣ የሚጠብቃቸው እውነተኛ እረኛ፣ እነሆ “እስራኤልን የሚጠብቀው አይተኛም፣ አያንቀላፋምም”  (መዝ.፻፳፥፬) እንዲል፤ የሚታደጋቸው መሓሪ አምላክ ነው የተወለደባትና፣ ደስ ይበልሽ ተብላለች፡፡

ቤተ ልሔም ሀገሮሙ ለነቢያት ተብላለች፡፡ ነቢያት ትንቢት ተናግረውባታልና፡፡ የተናገሩት ትንቢት፣ የቆጠሩት ሱባኤ ሲፈጸም ትንቢቱ ለተነገረባት ለሀገሪቱም፣ ትንቢቱን ለተናገሩት ነቢያትም ታላቅ ደስታ ነውና ሀገሮሙ ለነቢያት ተብላለች፡፡ ደግ ነገር በተፈጸመት ሀገር ኖሮ ሀገሪቱ የእነገሌ ናት ሲባል ሰዎችን ያስደስታል፡፡ ሀገሪቱንም የእነገሌ ሀገር ማስባል እጅግ ኩራትን ያሰጣልና ሀገሮሙ ለነቢያት ተብላ ተጠራች፡፡ ሀገሮሙ ለነቢያት ከተባለላቸው ከእነዚህ ነቢያት መካከል ዳዊትና ሚክያስ ይገኙበታል፡፡

ዳዊት ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ሲሻ ለነቢዩ ናታን እንዲህ ብሎ ነገረው፡፡ “እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጫለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ተቀምጣለች” አለው፡፡ ናታንም ንጉሡን “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ሂድና በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው፡፡ በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን እንዲህ ሲል መጣ፤ እንዲህም አለው፡- “ሒድ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም፡፡” (፪ሳሙ.፯፥፪-፭) አለው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ለዳዊት ድንቅ የሆነው የደገኛው ነገር የነገረ ድኅነት ምሥጢር ተገልጾለት “ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም፤ እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፣ ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው፡፡” (መዝ.፻፴፩፥፯) በማለት ተናገረ፡፡ ስለዚህ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገልጾለት ትንቢት የተናገረባት ቦታ ስለሆነች ሀገሮሙ ለነቢያት ተብላለች፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ሚክያስ ነው፡፡ ይህ ነቢይ ሲያስተምር ውሎ ማታ በዚህች በቤተ ልሔም በኩል ሲመለስ እስራኤላውያን በባቢሎናውያን ተማርከው ቤተ ልሔም ምድረ በዳ ሆና ተመለከታት፡፡ በዚህ ጊዜ “እነሆ የጽዮንን ሴት ልጅ ከበው ያጥሯታል፤ የእስራኤልንም ወገኖች ጉንጫቸውን በበትር ይመታሉ፡፡ አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም ሆይ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ነገር ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ከአንቺ ይወጣልኛል፡፡ ስለዚህ ወላዲቱ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ወደ እስራኤል ልጆች ይመለሳሉ፡፡” (ሚክ.፭፥፩-፬) በማለት ለጊዜው እስራኤላውያን ተማርከው እንደማይቀሩ በዘሩባቤል መሪነት በእግዚአብሔር ቸርነት ተመልሰው ወደ ርስታቸው እንደሚገቡ ተናግሯል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ሚክያስ ለጊዜው እስራኤል ዘሥጋን ያጣች ቤተ ልሔም ምድረ በዳ እንደሆነች፡፡ በዚህ ምድረ በዳነቷም እንደማትቀጥል እስራኤል ከምርኮ ተመልሰው እንደሚሰፍሩባት፣ እንደሚደሰቱባት፣ ንጉሥ ዘሩባቤል እንደሚነግሥባት ተናገረ፡፡ እንዲሁም ሆነ፡፡ እስራኤል ከምርኮ ተመለሱ፤ ተደስተውም ዘመሩባት፡፡ ፍጻሜው ግን እስራኤል ዘነፍስን ያጣች ገነት የሚገባባት አጥታ ባዶ እንደሆነች፣ ነገር ግን እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ክርስቶስ ከጠላት የሚያድን አምላክ እንደሚወለድባት ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ቤተ ልሔም ንጉሠ ሰማያት ወምድር አምላክ ተወልዶባት መላእክት ዘመሩባት፤ ሰውና መላእክት ታረቁባት፤ የእስራኤል ነጻነት ታወጀባት፡፡ “እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራችን እነግራችኋለሁና አትፍሩ አላቸው፡፡” (ሉቃ.፪፥፲) ተብሎ ተነገረባት፡፡

ለዚህም ነው ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም “ስለ ክርስቶስ ባንድ መንፈስ ቅዱስ ትንቢት የተናገሩት የእነዚህ የሚክያስና የዳዊት ነገር ምን ይደንቅ” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት የተናገረው፡፡ እውነት ነው የተነገረው ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ መሆኑን እንድንረዳ አንድ ዐይነት ትንቢት ግን በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ሰዎች ተነገረ፡፡ ደግሞ የተነገረው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባኤ ሲፈጽም የአናገረው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን የተናገሩት ነቢያት ደግሞ ደጋግ መሆናቸውን የሚያስረዳ ነውና የእነሱም ነገር ምን ይደንቅ ተባለ፣ ሀገሪቱም ከዚህ የበለጠ ደስታ ስለሌለ ደስ ይበልሽ ተባለች፡፡

እመቤታችን

ድንግል ማርያም የነቢያት ሀገራቸው ደስ ይበልሽ ተብላለች ፡፡ ለምን የነቢያት ሀገራቸው ተባለች ከተባለ የአበው ሱባኤና ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢት በእርሷ ስለተፈጸመ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ትንቢቶሙ ለነቢያት፣ እሞሙ ለሰማዕት፣ ወእህቶሙ ለመላእክት” የምትባለው፡፡  የነቢያት ትንቢት በእርሷ ስለ ተፈጸመ “ትንቢቶሙ ሀገሮሙ ለነቢያት” ተብላለች፡፡ በተጋድሎ፣ በስደት፣ በመከራ ወዘተ ስለምትመስላቸው “እሞሙ ለሰማዕት፣ የሰማዕት እናታቸው” ተብላለች፡፡ በንጽሕና፣ በቅድስና ስለምትመስላቸው ደግሞ “እህቶሙ ለመላእክት፣ የመላእክት እህታቸው” ተብላለች፡፡ ቤተ ልሔምን እና ድንግል ማርያምን የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? ቢባል የቤተ ልሔምን ከላይ በገለጽነው መንገድ መረዳት ይቻላል የድንግል ማርያምን ደግሞ እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

“ኦ ከርሥ ዘተጽሕፈ ውስቴታ መጽሐፈ ግእዛን እምግብርናት ለኩሉ ሰብእ፤ ኦ ከርሥ  ዘተረጸውረ ውስቴታ ንዋየ ሐቅል ዘይትቃወሞ ለሞት በእንቲኣነ፤ ለሰው ሁሉ ከመገዛት የነጻነት መጽሐፍ የተጻፈባት ማሕፀን እንደምን ያለች ናት፣ ስለኛ ሞትን የሚቃወም ክርስቶስን የተሸከመች ማኅፀን ወዮ እንደምን ያለች ናት፡፡” (ሃ/አበ.፵፰፥፲፭) በማለት ሊቁ ቅዱስ ኤራቅሊስ በሃይማኖተ አበው ነገረ ሥጋዌን በተናገረበት አንቀጹ ተናገረ፡፡

ይህ ለሁሉ የነጻነት መጽሐፍ የተጻፈባት የተባለች ጥንት በትንቢተ ኢሳይያስ እንዲህ ተብላ ተገልጻለች፡፡ “ደከሙ፤ ደነገጡ፤ ሰከሩም፤ በወይን አይደለም፤ በጠጅም አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስን አፍሶባቸዋል፤ ዐይኖቻቸውን የነቢያትንም ዐይን የተሰወረውንም የሚያዩ የአለቆቻቸውን ዐይን ጨፍኖባቸዋል፡፡ ይህም ሁሉ ነገር እንደታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባቸዋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ ታትሟልና “ማንበብ አልችልም” ይላቸዋል፤ ደግሞም መጽሐፉን ማንበብ ለማያውቅ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ “ማንበብ አላውቅም” ይላቸዋል፡፡ (ኢሳ.፳፱፥፱)፡፡

ከላይ በተገለጸው ምንባብ በርካታ ሐተታዎች ቢኖሩትም ከዚህ ርእስ ጋር የሚሄደውን ብቻ ለማየት እንሞክራለን፡፡ የታተመ መጽሐፍ የተባለች ድንግል ማርያም፣ ማንበብ የማይችል  የተባለ ዮሴፍ፣ ማንበብ የሚችል የተባለው ሚስቱን በግብር የሚያውቅ ማለት ነው፡፡ ማንበብ የማይችል የተባለ ደግሞ ድንግል ማርያምን በግብር የማያውቅ ማለት ነው፡፡ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷ ጭንቅ ይሆኖበታል፡፡ “ኢያእመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወልደ ዘበኲራ፤ የበኲር ልጇን እስከ ወለደች ድረስ አላወቃትም” እንዲል፡፡ እስከ የሚለውንም ቃል ፍጻሜ የሌለው እስከ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ጊዜ ድረስ አልወለደችም ይላል፤ ከሞተች በኋላ ወለደች ማለት አይደለም ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው እንጂ፡፡ ኖኅ የላከው ቁራም የጥፋት ውኃ እስከ ጎደለ ድረስ አልተመለሰም ይላል፤ ከዚያ በኋላ ተመለሰ የሚል ታሪክ አልተጻፈም ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው እንጂ፡፡

እንዲሁም መጽሐፍ ማንበብ የሚያውቅ የተባለ ዮሴፍ ሚስቱን በግብረ ሥጋ የሚያውቅ፣ መጽሐፍ እንደታተመ ሰጡት፣ አልተገለጠምና ማንበብ አልቻለም፡፡ መጽሐፍ የተባለች ድንግል ማርያም እንደ ታተመች ሰጡት ማንበብ አልቻለም፡፡ አይሁድ በቅንዓት ከቤተ መቅደስ ሲያስወጧት ከእግዚአብሔር አግኝተን እንደ ሰጠንህ ከእግዚአብሔር አግኘንተን እስክንቀበልህ ድረስ ጠብቅ ተብሎ ተሰጥቷልና፡፡ እንደ ታተመ ሰጡት ግን ማንበብ አልቻለም ተባለ፡፡ ማኅተመ ድንግልናዋን እንደ ጠበቀች እንድትኖር እንጂ በግብር ሊያውቃት አይደለምና፡፡

ማንበብ ለማይችለው የተዘረጋ መጽሐፍ ሰጡት ግን ማንበብ አልቻለም፡፡ ማንበብ ስለማይችል ነገረ ሥጋዌ በአበው ምሳሌ፣ በነቢያት ትንቢት ሲነገር የኖረና በተስፋ ሲጠበቅ የኖረ ነው፡፡ ግን ማንበብ ለማይችል ሰጡት አለ፡፡ ይህ ትንቢት የተነገረው ለማን እንደሆነ ላላወቀው ዮሴፍ ሰጡት ማንበብ አልቻለም፡፡ ድንግል የተባለች እርሷ፣ ወልድ የተባለ ከእርሷ የሚወለደው ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት፣ አበው ምሳሌ የመሰሉለት እርሱ እንደሆነ አላወቀም ነበር፡፡ ስለዚህ ማንበብ አልቻለም ተባለ፡፡

ይህም ነገር ዮሴፍን እጅግ አስጨነቀው ሊቁ ኤራቅሊስ እንደሚነግረን “የድንግል ሆዷ ገፋ፣ ያለ ዘር የፀነሰች የድንግልን የሆድዋን መግፋት ባየ ጊዜ የዮሴፍ ልቡ አዘነ፤ የንጽሕት እመቤታችንን ምሥጢሯን ፈጽሞ መረመረና በማያውቀው ምሥጢር ፀንሳ ቢያገኛት በጽኑእ ሐሳብ በማውጣት በማውረድ ተያዘ” (ሃ/አበ.፵፰፥፴፫) እንዲል፡፡ ነገሩ አምላካዊ ነውና ዮሴፍ ማወቅ አልቻለም፡፡ ባለማወቁም ተጨነቀ፡፡ ለዚህ ነው ማንበብ ለማያውቅ መጽሐፍ ሰጡት ግን ማንበብ አልቻለም፣ ያልተማረ ማንበብ የማያውቅ ነውና የተባለው፡፡

ሌላው መጽሐፍ የተባለ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ማንበብ የሚችል፣ ማንበብ የማይችል የተባሉ አይሁድ ናቸው፡፡ ማንበብ የሚችል ማለት ትንቢት የተነገረላቸው፣ ሱባኤ የተቆጠረላቸው በሕገ ኦሪት የሚመሩ የመሢሁን መምጣት የሚጠባበቁ ስለሆኑ ነው፡፡ ማንበብ የማይችል የተባሉት ሲጠባበቁት የነበረው መሢህ ትንቢቱን ሊፈጽም እነሱን ሊያድን ቢመጣ አልተቀበሉትም፡፡ ያ ትንቢት የተነገረለት፣ ሱባኤ የተቆጠረለት እርሱ እንደሆነ አምኖ መቀበል አለመቻላቸው ነው፡፡ ማንበብ ለሚችል የታጠፈ መጽሐፍ ሰጡት የተባለ ትንቢቱ የተነገረልን፣ ሱባኤው የተቆጠረልን እኛ ነን ለሚሉት ግን የታተመ መጽሐፍ ተሰጣቸው እነሱ በሚያስቡት መንገድ አለመገለጡን ሲያስረዳ ነው፡፡ እነሱ የሚያስቡት ብዙ ሠራዊት አስከትሎ፣ የጦር መሣሪያ አስይዞ ከሮማውያን ግዛት ነጻ የሚያወጣ ነበርና፡፡

ማንበብ ለማይችለው የተገለጠ መጽሐፍ ተሰጠው ግን ማንበብ ስለማይችል አላነበበውም የተባለው ደግሞ አምላክነቱን የሚያስረዱ በርካታ ተአምራትን እያደረገ ሕሙማንን እየፈወሰ፣ ሙታንን እያስነሳ ዕዉራንን እያበራ እኔ አምላክ ነኝ ቢላቸው አላመኑበትም፡፡ ምክንያቱም ማንበብ አይችሉምና፣ ማለት ሃይማኖት የላቸውምና፡፡ እርሱ ደግሞ የሚታወቅ በሃይማኖት ስለሆነ፡፡ “በሃይማኖት ነአምር ከመ ተፈጥረ ዓለም በቃለ እግዚአብሔር፤ ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠረ በሃይማኖት እናውቃለን፡፡” በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ነው፡፡

ለምን ደስ ይበልሽ አላት

የዚህ ሁሉ ምሥጢር መፈጸሚያ መዝገብ ሆናለችና ተፈሥሒ፤ ደስ ይበልሽ አላት፡፡ ከመልአኩ ከቅዱስ ገብርኤል እንደተረዳው እንዲህ በማለት “እስመ እምኔኪ ይትወለድ ክርስቶስ ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እስራኤል፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቃቸው ክርስቶስ ከአንቺ ይወለዳልና፡፡” ሰዎች በተለይም እናቶች ልጅ ወልዶ እንደ ማሳደግ ደስ የሚላቸው ነገር የለም፡፡ ስለዚህም አንዲት እናት ልጅ ስትወልድ እንኳን ደስ አለሽ፣ እንኳን ማርያም ማረችሽ ትባላለች፡፡ ሴቶች ልጅ ትወልዳላችሁ ሲባሉ ደስ ይላቸዋል፤ ይልቁንም ወንድ ልጅ ትወልዳላችሁ ሲባሉ  እጅግ ደስ ይላቸዋል፡፡ ድንግል ማርያም በብሥራተ መልአክ የተነገረችው የዓለሙን መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን ነውና መልአኩም ደስ ይበልሽ ብሏታል፡፡ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ሐዋርያትን የወለዱ እናቶችም ደጋግ ልጆች በመውለዳቸው ይከበራሉ፤ ይመሰገናሉ፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የወለደችው ዓለሙን ያዳነውን ጌታ ነውና ደስ ይበልሽ ልትባል ይገባታል፡፡

ለምን ተወለደ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነበት ሁለት መሠረታዊ ዓላማዎች አሉት፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ሰውን ለማዳን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለአርአያነት ነው፡፡ አርአያነቱንም የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ ትሕትናን፣ ለሚያሰቃዩት ጸልዮ ፍቅርን፣ ወዘተ በመግለጽ አሳይቷል፡፡ ሰውን ለማዳን እንደመጣም ሊቁ ሰው የሆነበትን ምክንያት ሲገልጥ “ልቡ የአዘነና የተከዘ አዳምን ወደቀደመ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ” ነው ያለን፡፡  ወደ ቀድሞ ክብሩ ልጅነት፣ ወደ ቀድሞ ቦታው ገነት ይመልሰው ዘንድእስመ በኀቤኪ ተወልደ ክርስቶስ ዳግማይ አዳም ከመ ያግብኦ ለአዳም ቀዳሚ ብእሲ እምድር ውሰተ ገነት፤ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ አዳምን ከሲኦል ወደ ገነት ይመልሰው ዘንድ በአንቺ ተወልዷልና ደስ ይበልሽ” አለ፡፡

አዳም ከገነት ተባሮ ስደተኛ ሆኖ ነበርና ባለ ርስት ባለ ጉልት ሊያደርገው ሰው ሆኖ በሥጋ አዳም ተገለጠ፡፡ በመሆኑም በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የመንግሥቱ ወራሾች ሆን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እምይእዜሰ ኢኮንክሙ ነግደ ወፈላሴ አላ ሰብአ ሀገሪቶሙ ለቅዱሳን ወሰብአ ቤቱ ለእግዚአብሔር፤ እንግዲህስ ወዲህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር ባለ ሀገሮችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡” (ኤፌ.፪፥፲፱) በማለት እንደገለጸልን ወደ ርስቱ ይመልሰው ዘንድ ሰው ሆነ፡፡ ስለዚህ ንጉሥ ክርስቶስ ሰውን ወደ ርስቱ ይመልሰው ዘንድ ካንቺ ተወልዷልና ደስ ይበልሽ ተባለች፡፡

በአጠቃላይ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ተፈሥሒ ኦ ቤተ ልሔም ሀገሮሙ ለነቢያት ያላት ለጊዜው ነቢያት ያመሰገኗትን ቤተ ልሔምን ሲሆን፤ ፍጻሜው ግን የነቢያት ትንቢትም ፍጻሜውን ያገኘው በድንግል ማርያም ስለሆነ ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ እያለ አመሰገናት፡፡ ለምን አመሰገናት ከተባለ ደግሞ የአምላክ እናት ስለሆነች፡፡ እኛም እንደ ሊቃውንቱ ድንግል ማርያምን አመስግነን ከድንግል ማርያም በረከት እንድናገኝ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የመላእክት ጥበቃ፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን አሜን፡፡

የነቢያት ሀገራቸው ቤተ ልሔም ደስ ይበልሽ

ክፍል አንድ

ዲ/ን ዐቢይ ሙሉቀን

የቃሉ ተናጋሪ የሶርያው ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡ በአበው የተመሰለው ምሳሌ፣ በነቢያት የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በድንግል ማርያም እና ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳንና ትንቢተ ነቢያትን ሊፈጽም ወደዚህ ዓለም በመጣው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ የትንቢተ ነቢያት መፈጸሚያ የሆነችውን ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ድርሰቱ ተናግሮታል፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም በሰኞ ውዳሴ ማርያም ድንግል ማርያምን በቀጥታ ስሟን አልጠራም፡፡ የድርሰት ትኩረቱም መከራ አዳምና ድኅነተ አዳም (ነገረ ድኅነት) ላይ ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ ነገረ ድኅነት በደጋግ አባቶችም፣ በነቢያትም፣ በብዙ ቅዱሳንም እንዳልተፈጸመ በድንግል ማርያም ብቻ እንደተፈጸመ ይገልጻል፡፡ እንዲያውም አዳምንና ሔዋንን አስከትላ መጥታ ነበርና ቢያያቸው አነሣቸው፡፡ እንዲህ በማለት “ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነጻ ያወጣውና ወደ ቀድሞ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ወደደ፡፡” በማለት፤ አዳምን እንዳነሣ ሁሉ “ሠምረ ልቡ ኀበ ፍቅረ ሰብእ ወአግዓዛ፤ ሰውን ወደደና ነጻ አደረጋት” በማለት ደግሞ ሔዋንን ጠቀሰ፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም አመስግነኝ ባለችው ጊዜ እሷን ከማመስገን አስቀድሞ ልጇ አዳምንና ሔዋንን ነጻ እንዳወጣ ይህንም ነጻ የማውጣት ሥራ ለመሥራት በራሱ ፈቃድ እንደሆነ እንዲህ ያለው ድንቅ ምሥጢር የተፈጸመባት ምሥጢራዊት ሀገር ደግሞ ድንግል ማርያም እንደሆነች ያስረዳል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርቶስ አዳምንና ሔዋንን ነጻ ለማውጣት በወደደ ጊዜ ነቢያት በመሰሉት ምሳሌ፣ በተናገሩት ትንቢት፣ ስማቸው የተጠቀሰውን ቅዱስ ኤፍሬም እያነሣሣ ሲያመሰግን ቤተ ልሔምንም አነሣት፡፡

ይህች ቤተ ልሔም ሙሴ፣ ኢያሱና ካሌብን ምድረ ርስትን ሰልላችሁ ኑ ብሎ በላካቸው ጊዜ ቤተ ልሔምን የእርሱ እንድትሆን ካሌብ ኢያሱን ለምኖት ነበር፡፡ ምድረ ርስትን ከወረሱ በኋላ ለካሌብ ሆናለች፡፡ በዚህ ጊዜ ከብታ የምትባል ሚስት አግብቶ በሚስቱ ስም ከብታ ተብላለች፡፡ ከብታ ልጅ ሳትወልድለት ቀረች፡፡ ኤፍራታ የምትባል ሚስት አግብቶ በሚስቱ ስም ኤፍራታ ብሎ አስጠርቷታል፡፡ ይህች ኤፍራታ ልጅ ወለደችለት፡፡ ሀብታቸው በዝቶላቸው ነበርና ልሔም አለው፡፡ ልሔም ማለት፡- ኅብስት፣ እንጀራ፣ ሀብት ማለት ነው፡፡ ልጁ አድጎ ፍርድ የሚጠነቅቅ፣ አስተዋይና ለተራበ የሚያበላ አዛኝ ሆነ፡፡ በእርሱም ቤተ ልሔም ተብላ ተጠርታለች፡፡ ይህም ስም ጸንቶላት ኖሯል፡፡

ከብታ፡- ከብታ ማለት ቤተ ስብሐት፤ የምስጋና ቤት ማለት ነው፡፡ ቤት የእመቤታችን፣ ስብሐት የጌታ ምሳሌ ነው፡፡ ምስጋና የባሕርዩ የሆነ አምላክ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ማሕፀኗን ዙፋን አድርጎ ተወልዷና የምስጋና ቤት ተባለች፡፡ ጌታን ፀንሳ ሳለ መላእክት በማሕፀኗ ያለውን ፈጣሪ ያመሰግኑት ነበርና የምስጋና ቤት ተባለች፡፡ እሷም ገና በሦስት ዓመቷ ቤተ መቅደስ ገብታ የመላእክትን ምስጋና ገንዘብ አድርጋ ዐሥራ ሁለት ዓመት ከመላእክት ጋር ፈጣሪዋን እያመሰገነች ኖራለችና የምስጋና ቤት ተብላለች፡፡ “ኦ መቅደስ ዘኮነ ባቲ እግዚአብሔር ካህነ፤ እግዚአብሔር ካህን ሆኖ ላገለገለባት መቅደስ አንክሮ ይገባል፡፡” (ሃ/አበው ፵፰፥፲፯) በማለት ሊቁ ኤራቅሊስ እንዳመሰገናት ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦባታልና የምስጋና ቤት ተብላለች፡፡

ሊቁ አባ ሕርያቆስም “ኦ ድንግል አኮ ወራዙት ስፉጣን ዘናዘዙኪ አላ መላእክተ ሰማይ ሐወጹኪ በከመ ተብህለ ካህናት ወሊቃነ ካህናት ወደሱኪ፤ ድንግል ሆይ የሚያታልሉ ጎልማሶች ያረጋጉሽ አይደለም፣ የሰማይ መላእክት ጎበኙሽ እንጂ፣ እንደተነገረ ካህናትና የካህናት አለቆች አመሰገኑሽ እንጂ፡፡” /ቅዳሴ ማርያም/ በማለት ምስጋና ያልተለያት፣ የምስጋና ቤት እንደሆነች አስረድቷል፡፡

     ኤፍራታ፡- ኤፍራታ ማለት ጸዋሪተ ፍሬ፤ ፍሬን የተሸከምሽ ማለት ነው፡፡ ጸዋሪት የእመቤታችን ፍሬ የጌታ ምሳሌ መልካም ፍሬ ከመልካም እንጨት ይገኛል፡፡ ባለቤቱ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያፈራል፡፡” (ማቴ ፯፥፲፯) በማለት እንዳስተማረን መልካም ፍሬ የሚገኘው ከመልካም ዛፍ ነው፡፡ በመሆኑም ንጽሕተ ንጹሓት፣ ቅድስተ ቅዱሳት ኅጥዕተ አምሳላት ድንግል ማርያም የሕይወት ፍሬን ተሸክማ ለዓለም አድላለች፡፡ ስለሆነም ኤፍራታ፣ ጸዋሪተ ፍሬ ተብላ ትጠራለች፡፡

“አብርሂ፣ አብርሂ ናዝሬት ሀገሩ ንጉሥኪ በጽሐ ዘምስለ ማርያም መጾሩ፤ አንቺ ናዝሬት ሀገሩ አብሪ፣ አብሪ ንጉሥሽ ክርስቶስ ከመጾሩ (ተሸካሚው) ማርያም ጋር ደርሷልና” በማለት የፍሬ ሕይወት ጌታ ዙፋን የተባለች ድንግል ማርያም መሆኗን አባ ጽጌ ድንግል ነግሮናል፡፡ “ይጸውር ድደ ወይነብር ጠፈረ አኃዜ ዓለም በእራኁ ኲሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ፤ በሰማያት ተቀምጦ መሠረትን ይሸከማል፤ ዓለምን በመሐል እጁ የሚይዝ ሁሉ በእጁ ያለ” /ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ/ የተባለለት ጌታ በአንዲት ብላቴና በድንግል ማርያም ማኅፀን ተወሰነ፡፡ እርሷም ጌታን ተሸከመችው ተባለ፡፡ ይህ ሁሉ ያስደነቀው ቅዱስ ያሬድም በድጓው “ሰማይ ወምድር ዘኢያገምሮ እፎ እንጋ ማኅፀነ ድንግል ጾሮ፤ ሰማይና ምድር የማይችለውን እንዴት የድንግል ማርያም ማኅፀን ቻለው” እያለ በአድናቆት ይነግረናል፡፡

እንዲሁም ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በሃይማኖተ አበው “መኑ ርእየ ወመኑ ሰምዐ እስመ እግዚአብሔር ዘኢይትገመር ተገምረ በከርሠ ብእሲ ዘኢይጸውርዎ ሰማያት ኢያጽዐቆ ከርሣ ለድንግል አላ ተወልደ እምኔሃ እንዘ ኢይትዌለጥ መለኮቱ ወኢኮነ ዕሩቀ እመለኮቱ፤ የማይወሰን እግዚአብሔር በድንግል ማሕፀን እንደተወሰነ ማን አየ? ማን ሰማ? ሰማያት ለማይወስኑት እርሱ የድንግል ማሕፀን አልጠበበውም፣ ባሕርዩ ሳይለወጥ ከእርሷ ተወለደ እንጂ ከመለኮቱ የተለየ ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፡፡” /ሃ.አበ.፷፮፥፭/ በማለት ማሕፀኗን ዙፋን አድርጎ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ እንደ ተወለደ ዙፋኑ ማደሪያው እንደ ተባለች ያስረዳናል፡፡

ፍሬ የተባለው ጌታ ነው፣ ያውም የሕይወት ፍሬ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ እንዲህ ይለናል፡፡ “አንቲ ውእቱ ዕፅ ቡሩክ ዕፀ ሕይወት ወዕፀ መድኃኒት ህየንተ ዕፀ ሕይወት ዘውስተ ገነት ዘኮንኪ ዕፀ ሕይወት በዲበ ምድር ፍሬኪኒ ፍሬ ሕይወት ውእቱ ወዘበልዐ እምኔሁ ሕይወተ ዘለዓለም የሐዩ፤ አንቺ የተባረክሽ ዕፅ ነሽ፣ የሕይወትና የደኅንነት ዕፅ ነሽ፣ በገነት ውስጥ ባለው ዕፀ ሕይወት ፈንታ በዚህ ዓለም የሕይወት ዕፅ ሆንሽ፣ ፍሬሽም የሕይወት ፍሬ ነው፤ ከእርሱም የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል፡፡” እንዲል፡፡

ቤተ ልሔም፡- ቤተ ልሔም ማለት ቤተ ኅብስት ማለት ነው፡፡ ቤት የእመቤታችን፣ ኅብስት የጌታ ምሳሌ ነው፡፡  በቤት ብዙ ነገር ይገኛል፣ እርሷም ሁሉን ለሚችል ጌታ መገኛ ናትና፡፡ በቤት ውስጥ ከሚገኙት መካከል ምግብ አንዱ ነው፡፡ ድንግል ማርያምም የምግበ ሕይወት ጌታ መገኛ ናት፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስ “ኦ ማርያም በእንተ ዝ ናፈቅረኪ ወናዐብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን፣ ከፍ ከፍም እናደርግሻለን፣ እውነተኛውን መብል፣ እውነተኛውን መጠጥ አስገኝተሽልናልና፡፡” በማለት በቅዳሴው ያመሰግናታል፡፡

ኅብስት የተባለ ጌታ ነው፡፡ “ከሰማይ  የወረደ ኅብስት እኔ ነኝ፤ ከዚህ ኅብስት የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው ይህ ኅብስት ሥጋዬ ነው፡፡” (ዮሐ.፮፥፶፩) በማለት ራሱ ባለቤቱ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ እንደነገረን፤ ኅብስት ያውም ሰማያዊ ኅብስት፣ ያውም ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያድለው ኅብስት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህ ኅብስት ደግሞ ከድንግል ማርያም የነሣው ሥጋ ስለሆነ ድንግል ማርያም ቤተ ኅብስት ተብላለች፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም “አንቲ ውእቱ መሶበ ወርቅ ንጹሕ እንተ ውስቴታ መና ኅቡእ ኅብስት ዘወረደ እምሰማያት፤ የተሠወረ መና ያለብሽ ንጹሕ የወርቅ መሶብ አንቺ ነሽ፣ መናም ከሰማይ የወረደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡” (ውዳሴ ማርያም ዘእሑድ) በማለት እንደተረጎመልን የተሠወረ መና የተባለው ባሕርዩ የማይመረመር ኢየሱስ ክርስቶስ፣ መሶበ ወርቅ የተባለች ደግሞ ድንግል ማርያም ናት፡፡ ስለዚህ ለዚህ ለተሠወረው መና መገኛ ቤተ ኅብስት ድንግል ማርያም ናት፡፡

ይቆየን፡፡

“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” (፩ኛዮሐ. ፫፥፰)

መ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ  “የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” በማለት የመሰከረው የመገለጡን ምክንያትም አያይዞ በመጥቀስ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን ምስክርነት የሰጠውም ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ከዓለም አስቀድሞ ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሆነ ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ በባሕርይ አባቱ በአብ፣በባሕርይ  ሕይወቱ  በመንፈስ  ቅዱስ፣በራሱም  ፈቃድ  ለድኅነተ  ዓለም  ከድንግል ማርያም በሥጋ እንደተወለደ እንረዳ ዘንድ ነው፡፡ በዚህም ቅድመ ዓለም ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት በመወለዱ ድኅረ ዓለም ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደተወለደ እንረዳለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት፡፡እሱም ከላይ የተመለከትነው ሲሆን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መስክሯል፡፡ “ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶልናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፡፡ ስሙም ድንቅ፣ መካር፣ ኃያል አምላክ የዘለዓለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል”(ኢሳ.፱፥፮)፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኢሳይያስ ሕፃን ተወልዶልናል ያለው ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም መወለዱን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል በባሕርዩ  ሲመሰገን   ሲወደስ   የነበረው   በአምላካዊ   ባሕርዩ በመፍጠር፣  በመግዛት፣ በመመለክ፣ በመፍረድ፣ በጌትነት ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር መንፈስ   ቅዱስ ጋር በአንድነት የነበረው፣ ያለው፣ የሚኖረው እርሱ እግዚአብሔር ወልድ ዓለምን ያድን ዘንድ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ መወለዱን  ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” ያለው የኢየሱስ ክርስቶስን ከድንግል ማርያም መወለድ መሆኑን በግልጽ የሚያስረዳ ነው፡፡

ይህው ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ሁሉም በእርሱ ሆነ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም… ያም ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ ለአባቱ አንድ እንደሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን ጸጋንና እውነትን የተመላ ነው”(ዮሐ.፩፥፩-፲፬)፡፡

“የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” ማለትም አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ፤ አካላዊ ቃል ሥጋን በመዋሐዱ (ሰው በመሆኑ) የማይታየው ታየ፣ የማይወሰነው ተወሰነ፣ ረቂቁ ገዝፎ (ጎልቶ) ታየ፣ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ ማለት ነው፡፡ ይህ የሆነውም በደኀራዊ ልደቱ ነው፡፡ በደኀራዊ ልደቱ ዓለምን ለማዳን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በሥጋ በመገለጡ ቀዳማዊ ልደቱ ታውቋል፡፡

የሰው ልጅ ድኅነትን ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅ ዳግም በመወለዱ ነው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ተለያይተው የነበሩትን ሰውና መላእክት አንድ ያደረገ፤ ሕዝብና አሕዛብን አንድ ወገን ያደረገ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ መገለጡም የሰው ልጅ በበደሉ ምክንያት በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ፣ በሞት ጥላ ሥር ወድቆ፣ ሳለ አማናዊው ብርሃን መታየቱ ሰውን የመውደዱ  ምሥጢር ነው፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” (ኢሳ.፯፥፲፬) ያለው   መፈጸሙን ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ደግሞ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፡፡ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው” (ማቴ.፩፥፳፫) ሲል ተርጉሞታል፡፡

ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ መገለጥ (ሰው መሆን) እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በምሕረት መመልከቱ፣ ከጽድቅ ተራቁቶ ለነበረው የጸጋ ልብስ ስለመሆኑ ብርሃን ሆኖ ድቅድቁን ጨለማ ያራቀ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡

ለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ በመጀመሪያው መልእክቱ “ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን ከአብ  ዘንድ  የነበረውንም ለእኛም  የተገለጠውን የዘለዓለምን ሕይወት እናወራላችኋለን” (፩ኛዮሐ.፩፥፪) በማለት ምስክርነቱን ገልጾልናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ እንዳለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትንና በሥጋ የተገለጠበትን ምክንያት ሲጠቅስም በርእሳችን መነሻ ያደረግነውን የእግዚአብሔር ልጅ የመገለጡን ዓላማ ሲያብራራም፡-

“ኃጢአትን የሚሠራት ሁሉ እርሱ በደልን ደግሞ ያደርጋል ኀጢአት በደል ናትና እርሱም ኀጢአትን ያስወግድ ዘንድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ በእርሱም ኀጢአት የለም በእርሱም የሚኖር ሁሉ አይበድልም የሚበድልም ሰው አያየውም አያውቀውምና ልጆቼ ሆይ ማንም አያስታችሁ እርሱ ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ጻድቅ ነው ኀጢአትን የሚሠራትም ከሰይጣን ወገን ነው ጥንቱን ሰይጣን በድሎአልና ስለዚህ የሰይጣንን ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ”(፩ኛዮሐ.፫፥፬-፱)እንዲል፡፡

በአምላክ ሰው መሆን(መወለድ) ከኀጢአት ማሰሪያ፣ከዲያብሎስ ቁራኝነት፣ከሲኦል ባርነት ነጻ ወጥተናል፡፡እግዚአብሔር በፍጹም ፍቅሩ ወደ ራሱ አቀረበን፣አባ አባት ብለን እንጠራው ዘንድ በልጅነት ጸጋ አከበረን፣የሞትን ቀንበር ከላያችን አንከባሎ ጣለልን፣በማዳኑ ሥራ ከጨለማው ገዢ ታደገን፣ወደ ቀድሞ ክብራችንም እንመለስ ዘንድ ከራሱ ጋር አስታረቀን፣እርሱ ከእኛ ጋር ሲሆን ሞት ከፊታችን ተወገደ በዚህ ሁሉ ክብርና ጸጋ የጎበኘን ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም ሰው ሆኖ ነውና ክብርና ምስጋና ለእርሱ ለልዑል እግዚአብሔር ይሁን፡፡ በሚቀጥለው ክፍል  የመገለጡን ምሥጢር በስፋት የምንመለከት ይሆናል እስከዚያው ይቆየን፡፡