አዳም አርብ ቀን ተፈጠረ (ዘፍ.፩፥፳፯)

መ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

አዳም ማለት፡- ያማረ መልከ መልካም ውብ ፍጡር ማለት ነው፡፡ አዳም የተፈጠረው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ እና ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ነው፡፡ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ የሚባሉት ውኃ፣ እሳት፣ ነፋስ፣ መሬት ሲሆኑ ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የሚባሉት ደግሞ ለባዊት(የምታስብ)፣ ነባቢት(የምትናገር)፣ ሕያዊት(የምትኖር) ወይም በሌላ አገላለጽ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ማለት ነው፡፡

እግዚአብሔር  አምላክ  እሑድ  ፍጥረትን  መፍጠር  የጀመረባት  ቀን  ናት፡፡  ለዚህም  ነው በሥነ ፍጥረት ታሪክ እሑድ የመጀመሪያ ቀን ተብላ የምትጠቀሰው፡፡ የዕለቱ ስያሜም አሐደ፣ አንድ አደረገ ከሚለው የግእዝ ግስ እሑድ የሚለው ቃል የወጣል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እሑድ ቀን ፍጥረትን መፍጠር አሰበ ሊፈጥር ያሰበውንም እሑድ መፍጠር ጀመረ፡፡ አዳምንም በመጨረሻዋ የሥራ ዕለት በዕለተ ዐርብ በነግህ ከኅቱም ምድር ሚያዝያ አራት ቀን የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ አድርጎ እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ ፈጠረው፡፡ አዳም የተፈጠረውም በምድር መካከል በምትገኘው ኤልዳ እየተባለች በምትጠራ ስፍራ ነው (ኩፋ.፭.፮)፡፡

“እግዚአብሔርም አለ ሰውን በአርአያችንና በአምሳላችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሣዎችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችን እንስሳትን እና ምድርን ሁሉ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ይግዛ፤ እግዚአብሔርም ሰውን በእግዚአብሔር አምሳል ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ …እግዚአብሔርም የፈጠረውን ሁሉ እጅግ መልካም እንደሆነ አየ፤ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ ስድስተኛም ቀን ሆነ፡፡”(ዘፍ.፩፥፳፮-ፍ)

እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ ፈጥሮ ከጨረሰ በኋላ ነው አዳምን በዕለተ ዐርብ የፈጠረው፡፡ ይህም እግዚአብሔር አምላካችን “ቸር አምላክ” ስለ ሆነ ነው፡፡ በጎ አባት ለልጁ የሚበላውን፣ የሚጠጣውን፣ የሚኖርበትን፣ የሚገዛውን፣ የሚመራውን፣ የሚያርስበትን ጥማድ፣ የሚያርሰውን መሬት፣ ወ.ዘ.ተ እንደሚያዘጋጅ ሁሉ ቸር የሆነው አምላካችንም ሁሉን ከፈጠረና ካዘጋጀለት በኋላ ሁሉን ወራሽ ሊያደርገው በዕለተ ዐርብ አዳምን አክብሮና አልቆ በአርአያውና በአምሳ ፈጠረው፡፡ በአዘጋጀለት በከበረ ስፍራም የፈጠረለትን ሁሉ እንዲገዛ በሁሉ ላይ አሠለጠነው፡፡

እንዲሁም አንድ ሰው ድግሥ ደግሦ ታላቅ የሚለውን ሰው ሲጠራ በክብር የተጠራው ታላቅ እንግዳ ከመምጣቱ አስቀድሞ ቤቱን ጎዝጉዞ፣ ሰንጋውን ጥሎ፣ እንጀራውን፣ ወጡን አሰናድቶ እንዲጠብቅ እና ያ በክብር የተጠራ ታላቅ እንግዳ በተዘጋጀበት መጥቶ ደስታውን እንዲካፈል አዳምም በእግዚአብሔር የተወደደ፣ የከበረ ታላቅ እንግዳ ፍጡር ሆኖ ፍጥረት ሁሉ ተፈጥረው በተጠናቀቁበት ሊገዛቸው፣ ሊነዳቸውና ሊኖርባቸው፣  ሊሠለጥንባቸውም በመጨረሻ ተፈጠረ፡፡

አባታችን አዳም በዕለተ ዐርብ ሲፈጠር  እንደ መላእክት ንጹሕ ነበር፡፡ በዚህ ንጽሕናውም ረዳት ሆና ከጎኑ ከተፈጠረችለት ሔዋን ጋር በገነት ለሰባት ዓመት ያህል ኖረ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በዲያብሎስ አሳችነት ምክንያት ወደ ምድረ ፋይድ ተሰደደ፡፡ ከገነት ተሰዶም ለመመለስ የፈጀበት ጊዜ ከነ ልጅ ልጆቹ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔር የሰጠው የተስፋ ቃል እስኪፈጸም ማለት ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ እንዳለው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ አዳምን ቀድሞ በፈጠረበት ዕለት በዕለተ ዐርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ በደሙ ፈሳሽነት ሰውን ከበደል ሁሉ አነጻው፡፡ ወደ ቀደመ ክብሩም መለሰው፡፡ አዳምና የልጅ ልጆቹ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ገነትን ሊወርሱ ችለዋል፡፡

አዳም በዕለተ ዐርብ ተፈጥሮ በበደል ምክንያት ያጣትን ገነት በዕለተ ዐርብ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል መሞት ዳግም ሊወርሳት ችሏል፡፡ ስለዚህ ዕለተ ዐርብ የተፈጠርንባትም፣ የዳንባትም ዕለት ናትና ዕለቲቱን በጾም በጸሎት አስበናት እንውላለን፡፡ ከዚሁ በተያያዘም ዕለተ ረቡዕም እንዲሁ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በአይሁድ ዘንድ ተመክሮ የዋለበት ነው፡፡

ረቡዕ ምክረ አይሁድ፣ ዐርብ ስቅለተ ክርስቶስ የተፈጸመበት ቀን ስለ ሆነ ዐርብ እና ረቡዕ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ በጾም ታስበው ይውላሉ፡፡ ወሩ የፍስክ ጊዜ ቢሆን እንኳ ከበዓለ ኀምሣ ውጪ ዐርብ እና ረቡዕ በጾም ሁል ጊዜ ይታሰባሉ፡፡ ልደትና ጥምቀት ዐርብ ወይም ረቡዕ ላይ በዋሉ ጊዜ ተለዋጭ ቀን ጾመ ገሃድ ተብሎ በዋዜማቸው ይጾማል፡፡ ይህም ከበዓሉ ታላቅነት የተነሣ በደስታ በዓላቱ እንዲከበሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሠራችው ሥርዓት መሠረት ነው፡፡

ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዐርብና ረቡዕ በክርስቲያኖች ዘንድ ከሌሎች ቀናት ተለይተው ቅዳሴውም ከሰዓት እንዲቀደስ እና በእነዚህ ዕለታት አራስ ከሆነች እናት፣ ከሰባት ዓመት ዕድሜ በታች ካሉ  ከሕፃናት እና ሕመም ከጸናበት ሰው በቀር ሁላችንም መጾም እንዳለብን የምታስተምረን፡፡ ይህ ሁሉ እግዚአብሔር ለሰው ያሳየውን ታላቅ ፍቅር የምናይበትና የምናስተውልበት  ስለሆነ ምስጋና ይድረሰው አሜን፡፡

እንዴት እንጸልይ?

ክፍል ፬

በእንዳለ ደምስስ

ባለፈው ዝግጅታችን “የጽድቅን ጥሩር ልበሱ” በሚል ርእስ ክፍል ሦስትን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በዛሬው ዝግጅት ደግሞ ቀጣዩን ክፍል ፬ ወደ ድረ ገጻችን ተከታታዮች የምናቀርብ ይሆናል፣ ተከታተሉን፡፡

ጸሎት መለመን፣ ማመስገን፣ በንጽሕና በእግዚአብሔር ፊት መቆም፣ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስንነጋገር ደግሞ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎችና ይዘን መገኘት የሚገቡን መንፈሳዊ ምግባራትን ማወቅና መረዳት፣ በአጠቃላይ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ጠንቅቀን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ እንኳን ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ለመነጋገር ቀርቶ ከማንኛውም ሰው ጋር ከመነጋገራችን በፊት ምን ማለት እንዳለብን፣ በምን ጉዳይ ላይ እንደምንነጋገር ለይተን ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን በጸሎት ለመጠየቅና ለመነጋገር ስናስብ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ በሃይማኖት ቆመን፣ ሰማያዊውን ነገር እያሰብን ለጸሎት መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

በዚህም መሠረት  ልናከናውናቸውና ይዘን መገኘት የሚገቡን መንፈሳዊ ምግባራት ምን ምን እንደሆኑ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በወንጌል አምስቱ ልባም ሴቶች ያደረጉትንም ማስተዋል ይገባል፡፡ “ያን ጊዜም መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመቀበል የወጡ ዐሥሩን ደናግል ትመስላለች፡፡ ከእነርሱም ውስጥ አምስቱ ሰነፎች፣ አምስቱም ልባሞች ነበሩ፡፡ ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ዘይት አልያዙም ነበር፡፡ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮዎቻቸው ዘይት ይዘው ነበር” እንዲል(ማቴ.፳፭.፫)፡፡ ሃይማኖት፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ትሕትናና ፍቅር መያዛቸውን ሲያመለክት አምስቱን ልባሞች አላቸው፡፡ ስለዚህ ከመጸለያችን በፊት እነዚህን ይዘን በመገኘት ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ነጥቦች ትኩረት ልንሰጥ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም፡-

፩. ኀጢአተኛ መሆናችንን ማሰብ፡-

ጢአት በኀልዮ(በማሰብ፣ በነቢብ(በመናገር)፣ በገቢር(በማድረግ) ሊፈጸም ይችላል፡፡ ያደረግነው ጥፋት ትክክል እንዳልበር፣ በሠራነው ኀጢአትም እግዚአብሔርን፣ ሌሎችን ሰዎች፣ እንዲሁም ራሳችንን መጉዳታችንን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ራሳችንን እንዴት እንጎዳለን ስንል እግዚአብሔር በአርአያውና በምሳሌው ፈጥሮን፣ በሠራልን ሕግና ሥርዓት እንጓዝ ዘንድ ሲገባን ቃሉን አፍርሰናልና ሥጋችንን እናረክሳለን፡፡ ፈሪሳውያን አንዲት ሴትን ዝሙት ስትፈጽም አግኝተናታል ብለው በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ አቅርበዋት ነበር፡፡ ኀጢአት ስትሠራ አግኝተናታልና በሙሴ ሕግ መሠረት በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት አስበው፣ እንዲሁም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመፈተን ይህንን አድርገዋል፡፡ የራሳቸውን ኃጢአት ዘንግተው የሌላውን ኃጢአት ለመመልከት ፈጥነዋል፡፡ ነገር ግን የጌታችን መልስ እንደጠበቁት አልነበረም፡፡ ሊፈትኑት ቀርበዋልና ልብንና ኵላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ ድንጋይ ይጣልባት” አላቸው፡፡ እነርሱም ኅሊናቸው ወቀሳቸው፡፡ “ከሽማግሌዎች እስከ ኋላኞቹ ድረስ አንዳንድ እያሉ ወጡ” እያለ ይነግረናል፡፡ ቀድሞ ከሌሎች ይልቅ የራስን ኃጢአት ማሰብ፣ ንስሓም መግባት ሲገባቸው የሌሎችን ኃጢአት ለመቁጠር ልባቸውን አስጨክነው ቀረቡ፡፡ ነገር ግን ያልጠበቁት ጥያቄ ሲቀርብላቸው ወደ ራሳቸው ኀጢአት ተመለከቱ፣ እንደበደሉም አወቁ፡፡(ዮሐ.፰.፯-9)፡፡

በደላችንን ማሰብ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለዚህ ለጸሎት ከመቆማችን በፊት እኛ በእግዚአብሔር ፊት መቆም የማንችልና የማይገባን እንደሆንን ማሰብና መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት በእኛ ሥልጣንና ፍላጎት ሳይሆን በእግዚአብሔር ቸርነት በተሰበረ ልብ መቆማችንን ልናስተውል፣ ይህንንም አምነን ተቀብለን ተግባራዊ ልናደርግ ግድ ይለናል፡፡ አይሁድ ከጌታችን ጋር እርሱ ወደሚሄድበት መሄድ እንደማይችሉ ከነገራቸው በኋላ “እኔ እሄዳለሁ፣ ትሹኛላችሁም፣ ነገር ግን አታገኙኝም በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ” ብሏቸዋል፡፡ ኃጢአት ወደ ሞት እንደሚወስድ አመልክቷቸዋል፤ ኃጢአተኞች ሆነው ሳለም በትዕቢት ልባቸውን በማደንደን ተፈታትነውታልና ገሰጿቸዋል፡፡(ዮሐ.፰.፳፩)፡፡

አይሁድ የአብርሃም ዘሮች ነን እያሉም ይመኩ ስለነበር ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው የመቁጠር፣ ከፍ ከፍ ማለትንም መውደድ የተጠናወታቸው በመሆናቸው እንደ ቃሉ መኖር ሲገባቸው ጌታችንን ተፈታትነውታል፡፡ ጌታችንም የልቡናቸውን መደንደን ተመልክቶ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ኃጢአትን የሚሠራ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው፡፡ ባሪያ ዘወትር በቤት አይኖርም፣ ልጅ ግን ለዘለዓለም ይኖራል” ሲል ከኃጢአታቸው ተመልሰው የእግዚአብሔር ልጆች ይባሉ ዘንድ፣ እንደ ልጅም በቤቱ ይኖሩ ዘንድ ነግሯቸዋል፡፡

“ኃጢአትን የሚሠራት ሁሉ እርሱ በደልን ደግሞ ያደርጋል፣ ኃጢአት በደል ናትና”(፩ኛዮሐ.፫.፬) እንዲል እኛም በደለኞች መሆናችንን እያሰብን፣ በደላችንንም ይቅር ይለን ዘንድ ለጸሎት መቆም ይገባናል፡፡

፪. የበደሉንን ይቅር ለማለት የተዘጋጀ ልብ፡-

አንድ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር የሚፈልገው ነገር እንዳለ ሁሉ እግዚአብሔርም ከሰው ልጆች የሚፈልጋቸው ነገሮች አሉት፡፡ እነርሱም ዐሥርቱ ትእዛዛትና ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን መፈጸም ናቸው፡፡ እነዚህም በአንድ መሠረታዊ ትእዛዝ ይጠቃለላሉ፡- ይህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ፤ የሚለው ቃል ሕግን ሁሉ  ይፈጽማልና፡፡” እንዲል(ገላ.፭.፲፬)፡፡ ወንድማችንን በመውደድ ቢበድለን እንኳን በይቅርታ በማለፍ ይቅር ባይነትን ለሌሎች ማስተማር ያስፈልጋል፤ ለነፍስም ዕረፍትን ይሰጣልና፡፡ የበደልነው ሰው ይቅር እንዲለን የምንሻ ከሆነ እኛም የበደሉንን ይቅር ለማለት የፈጠንን መሆን ይገባናል፡፡ “በምትጸልዩበትም ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲላችሁ በወንድማችሁ ያለውን በደል ይቅር በሉ፡፡ እናንተ ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም” እንዲል፡፡(ማር.፲፩.፳፭)፡፡

ልባችንን በግብዝነትና በእልከኝነት ማሠቃየት የለብንም፡፡ በዘወትር ጸሎታችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አባታችን ሆይ ብለን ዘወትር ስሙን እንጠራ ዘንድ ካዘዘን ትእዛዛት ውስጥ “. . . በደላችንን ይቅር በለን፣ እኛም የበደሉንን ይቅር እንል ዘንድ” እያልን እንጸልያለን፡፡ ይህንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ በመስቀል ላይ በሰቀሉት ጊዜ ከተናገራቸው “ሰባቱ አጽርሐ መስቀል” መካከል “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እንዳለ እኛም ለጸሎት ስንዘጋጅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን አብነት አድርገን ሌሎች ይቅር እንዲሉን እኛም ይቅር ለማለት የፈጠንን መሆን አለብን፡፡ ልባችንንም ለዚህ ማዘጋጀት ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ መሆኑን ከአምላካችን ተምረናልና፡፡

፫. ትሕትና፡-

አንድ ክርስቲያን በክርስቲያንነቱ ሊያሟላቸው ከሚገቡ መልካም ምግባራት መካከል ትሕትና እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ ነኝና ልቤም ትሑት ነውና ለነፍሳችሁም ዕረፍትን ታገኛላችሁ፣ ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና” (ማቴ.፲፩.፳9) በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን እኛም ትሑታን ሆነን መገኘት ይገባናል፡፡

አምላካችን በሸላቾቹ ፊት እንደሚቆም በግ በትሕትና ቆሟልና እኛም ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ትሕትና ዲያብሎስን ድል ማድረጊያ መንፈሳዊ መሣሪያችን ነው፡፡ በትዕቢት የሚመጣውን በትሕትና ማሸነፍ ስለሚቻል፡፡ ለዚህም ቅዳሳን፣ ፃድቃን ሰማዕታት አምላካችንን አብነት እንዳደረጉ ሁሉ እኛም እነርሱ በተጓዙበት መንገድ ልንከተላቸው ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ጸሎት እንዴት መጸለይ አለብን ስንል በእግዚአብሔር ፊት ስንቆም በፍጹም ትሕትና ሊሆን ግድ ይላል፡፡ በትሕትና የምንጸልየው ጸሎት ቅድመ እግዚአብሔር እንደሚደርስም ማመን ከእኛ ይጠበቃል፡፡

፬. አለባበስን ማስተካከል፡-

ለጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ለመጸለይ በምንቆምበት ወቅት ልናደርጋቸው ከሚገቡን ነገሮች ሌላው ጉዳይ አለባበስን በተገቢውና ክርስቲያናዊ ሥርዓትን በተከተለ ሁኔታ መልበስ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ስንቆም ነጠላችንን መስቀልያ አጣፍተን መልበስ ስንል ነጠላውን በቅድሚያ ከቀኝ ወደ ግራ፣ እንዲሁም ከግራ ወደ ቀኝ ማጣፋት ይገባል፡፡ ይህም ከቀኝ ወደ ግራ ማጣፋታችን አዳም አባታችን በበደሉ ምክንያት ከገነት ወጥቶ እንደነበር ሲያመለክተን፣ ከግራ ወደ ቀኝ ማጣፋታችንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ወደ መቃብር መውረዱን፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱንና ዲያብሎስን አሥሮ፣ አዳምንና ልጆቹን ከሲኦል በማውጣት ወደ ገነት መመለሱን ሲያመለክተን ነው፡፡ ስለዚህ ለጸሎት በምንቆምበት ጊዜ ነጠላችንን መስቀለኛ አጣፍተን በተመስጦ ኅሊናችንን በመሰብሰብ፣ ለጸሎት በሁለት እግራችን ቀጥ ብለን በመቆም ልንዘጋጅ ይገባል፡፡

፭. የምንጸልየውን ማወቅ፡-

ለጸሎት ከመቆማችን በፊት ስለምንጸልየው ጉዳይ ማወቅና መረዳትም ያስፈልጋል፡፡ አንድ ክርስቲያን ዘወትር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደነገገችው ሥርዓት መሠረት የጸሎት ሰዓት ወስኖ መጸለይ እንደሚገባው የታወቀ ነው፡፡ ከጸሎት ተለይቶ ጽድቅ የለምና፡፡ ጸሎት የማይጸልይ ሰው በየቀኑ በውኃ እጦት እየጠወለገ እንደሚሄድ ዛፍ ነው፡፡ ለመጸለይ ደግሞ የምንጸልየውን ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ለምንድነው በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም የፈለግሁት ብሎ ራሱን መጠየቅ፣ ለጥያቄውም ራሱ ምላሹን መስጠት አለበት፡፡

የምንጸልየውን ካወቅን እንዲደረግልን የምንፈልገው ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ሳይሆን እስከ ዛሬ ውጣ ውረዱን አሳልፎ እዚህ ላደረሰን፣ እንዲሁም እንደበደላችን ሳይሆን በቸርነቱ ታድጎን ስላደረገልን መልካም ነገር ምስጋና ማቅረብን መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለ ራሳችን ብቻም ሳይሆን ስለ ሀገር፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለታመሙትና ስለ ተሰደዱት፣ . . . ሁሉ መጸለይ ተገቢ ነው፡፡

በተቃራኒው የምንጸልየውን አለማወቅ ከተግሣጽ አያድነንም፡፡ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ማርያም ባውፍልያ ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቿን ያዕቆብና ዮሐንስን ይዛ በመቅረብ  “. . . እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ፣ አንዱም በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ” አለችው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “የምትለምኑትን አታውቁም፣ እኔ የምጠጣውን ጽዋ መጠጣት ትችላላችሁን? እኔስ የምጠመቀውን ጥምቀት ትጠመቃላችሁን?” ሲል ገሥጿቸዋል፡፡  እናታቸው የለመነችው ልመና ምድራዊ ንጉሥ መስሏት ምድራዊውን ሥልጣን ይሰጣቸው ዘንድ ጠየቀች፡፡ ነገር ግን በዕለተ ዐርብ በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ በቀኝና በግራ ይሰቀሉ ብላ የመለመኗን ምሥጢር አልተረዳችም፡፡ ይህንን ሥጢር ባለመረዳትም ለልጆቿ ሕይወትን ሳይሆን ሞትን ለመነች፡፡ ይህም ለእኛ የማይገባና ያልተረዳነውን ልመና ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ እንደሌለብን የሚያስተምረን ነው፡፡

፭. እንደ አቅማችን መጸለይ፡-

በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውስጥ ልናየው ከሚገባን ነገር አንዱ ለመጸለይ ያለንን አቅም ነው፡፡ በእርግጥ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በእኩል መንፈሳዊ ብቃት ላይ ይገኛል ማለት አይቻልም፡፡ ከማይጸልዩ ክርስቲያኖች አንስቶ ግርማ ሌሊቱን፣ ጸብአ አጋንንቱን፣ ድምጸ አራዊቱን ታግሰው ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ቅጠል በጥሰው ወደ እግዚአብሔር ያለማቋረጥ እስከ ሚጸልዩት አባቶች ድረስ የተለያየ መንፈሳዊ ብቃትና ጸጋ ይኖራል፡፡ ስለዚህ ጸሎት ባለን መንፈሳዊ አቅም ይወሰናል፡፡

ገና ወጣኒ ሆኖ ይህንንም፣ ያንንም ሁሉንምየጸሎት መጽሐፍ ካላጸለይኩ ማለት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ቀስ በቀስ ማደግ ሲገባ በስሜታዊነት የተጀመረ በመሆኑ እየቀነሱ፣ እየተሰላቹ በመምጣት ጨርሶ ጸሎትን እስከማቋረጥ ሊያደርስ ይችላልና፡፡ በሃይማኖት ጽናት የሚጸለይ ጸሎት እንደ ዛፍ ነው፡፡ ቀስ በቀስ የሚያድግ፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ መንፈሳዊ ጸጋ ነው፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊነት በራሱ ደረጃ አለውና ለታይታ ሳይሆን ለራሳችን ብለን እንደ አቅማችን ልንጸልይ ይገባል፡፡ “በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፣ እነርሱ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በአደባባይ መዓዘን መቆምና መጸለይን ይወዳሉና፣ እውነት እውነት እላችኋላሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል” እንደተባለ፡፡ (ማቴ.፮.፭)፡፡

፮. ከችኮላ መራቅ፡-

ለጸሎት በእግዚአብሔር ፊት በቆምን ጊዜም ራሳችንን አረጋግተን በተመስጦ ሆነን መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ መቸኮል በማንኛውም የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ቢሆን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ የቆምነው በእግዚአብሔር ፊት እንደሆነና የምንነጋገረውም ከእግዚአብሔር ጋር መሆኑን በማሰብ ጸሎትን ሊያቋርጡ ከሚችሉ ነገሮች ከሥጋዊ ፍላጎትና ከንቱ ሐሳብ ርቀን ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ጸሎት በዘፈቀደ የሚፈጸም ሳይሆን ዓላማ ኖሮት መከናወን አለበት፡፡ የጀመሩትን ጸሎትም ሳይጨርሱ ጉዳይ አለብኝ፣ እንቅልፍ መጣብኝ፣ አሞኛል የመሳሳሉትን ምክንያቶች በመደርደር ለማረፍ መቸኮል ወይም ለሌላ ጉዳይ ተጣድፎ ማቋረጥ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንን ድርጊት ከመፈጸምም መቆጠብ ከአንድ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ በችኮላ የምንገነባው ማንኛውም ነገር አወዳደቁ የከፋ ስለሚሆን ከችኮላ መራቅ አለበት፡፡

እነዚህ ከላይ ያየናቸው ነጥቦች ከብዙው በጥቂቱ ሲሆን በሚቀጥለው በክፍል ፭ ዝግጅታችን ደግሞ የጸሎት ሰዓታትን እንመለከታለን፡፡ ይቆየን፡፡

 

 

 

 

 

 

 

“የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ”/ኤፌ.፮.፲፬/

በእንዳለ ደምስስ

ክፍል ሦስት

“የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ” በሚል ርእስ በክፍል አንድ ዝግጅታችን ስለ ጾም በጥቂቱም ቢሆን ያቀረብን ሲሆን በክፍል ሁለት ደግሞ ጸሎትና የጸሎት ጥቅሞችን ማየት ጀምረን እንደነበር ይታወሳል፡፡ በክፍል ሁለት ዝግጅታችንም የጸሎት ጥቅሞችን በተመለከተ ከተጠቀሱት ውስጥ፡- በጸሎታችን ስለተደረገልን ሁሉ ምስጋና ማቅረብ፣ ስለ በደላችን ይቅርታን እናገኛለን፣ እንዲሁም መንፈሳዊ ኃይልን እናገኛለን በሚል አቅርበን ነበር፡፡ ቀሪዎቹ የጸሎት ጥቅሞችን ደግሞ ቀጥለን እናቀርባለን፡፡

. . .የጸሎት ጥቅሞች፡-

ምሥጢር ይገለጽልናል፡- ምሥጢር አመሥጠረ፣ አራቀቀ ካለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ረቂቅ፣ የማይታይ፣ ኅቡእ፣ ሽሽግ፣ ማለት ነው፡፡ ምሥጢር የሰው ልጅ በራሱ ጥበብ መርምሮ ሊደርስበትና ሊያውቀው የማይችል፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ሊገለጥ የሚችል ነው፡፡ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና” እንዲል(ዮሐ.፲፭.፭)፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕር ላይ በታንኳ ወጥቶ ሳለ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፡፡ ጌታችንም የሰዎቹን መሰብሰብ በተመለከተ ጊዜ ስለ ዘርና ዘሪው በምሳሌ አስተማራቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ስለምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት፡፡ ጌታችንም ለደቀ መዛሙርቱ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ በውጭ ላሉት ግን በምሳሌ ይሆንባቸዋል” አላቸው፡፡ (ማቴ.፲፫.፲፩፤ ማር.፬.፲፩)፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር እየዋሉ እያደሩ የቃሉን ትምህርት፣ የእጁን ተአምራት እየተመለከቱ ኖረዋልና የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር የማወቅ ጥበብ እንደሰጣቸው ነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ለቀረቡና እንደ ቃሉም ለሚጓዙ እንደ አቅማቸውና መንፈሳዊ ጥንካሬያቸው ምሥጢርን ይገልጻልና ለሕዝቡም በሚገባቸውና በሚረዱት ምሳሌ ገልጾ አስተማራቸው፡፡

ሰው ከወዳጆቹ፣ ከሚወዳቸውና ከሚወዱት በውስጡ የያዘውን(የደበቀውን) ምሥጢር ነው ብሎ የያዘውን ጉዳይ ገልጾ ላይናገር ይችላል፡፡ ለሌሎች ፍቅር አለኝ ቢልም እንኳን ሸሽጎ የሚያስቀምጠው ምሥጢር ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ከሰዎች ቢደበቅም ከእግዚአብሔር ሊሰወር አይቻለውም፡፡ እግዚአብሔር ግን ለመረጣቸውና ለፈቀደላቸው ብቻ በሚችሉት መጠን ምሥጢርን የሚገለጥ ነው፡፡ ለተመረጡት ስንል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ይገልጥላቸው ዘንድ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መካከል ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን መርጦ ወደ ታቦር ተራራ እንደወሰዳቸው ቅዱስ ወንጌል ያስተምረናል፡፡ ሌሎቹን ግን በእግረ ደብር ትቷቸው ሦስቱን ብቻ ይዞ ሲወጣ ቀሪዎቹ እኛን ከምሥጢሩ ሸሸገን ብለው ከመከተል ወደ ኋላ አላሉም፣ እነርሱ ተለይተው በመቅረታቸው ስላላዘኑም ለሦስቱም ረቀ መዛሙርት የተገለጸው ምሥጢር ለቀሩትም ተገልጾላቸዋል፡፡ “ከስድስት ቀንም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ወንድሙ ዮሐንስን ይዞ ለብቻቸው ወደ ረጅም ተራራ አወጣቸው፡፡ መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፣ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ፡፡ እነሆ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው”(ማቴ.፲፯.፩) እንዲል፡፡ ምሥጢር ዝም ብሎ አይገለጥም በመንፈሳዊ ሕይወት መጋደል፣ ዲያብሎስንም ድል የምንነሣበት ዕቃ ጦር መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህም መንፈሳዊ መሣሪያዎች ውስጥ አንዱ ጸሎት ነው፡፡ ስለዚህ በጸሎት መትጋት ከእኛ ክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆላስይስ በላከው መልእክቱ “ስለ እርሱ የታሰርሁለትን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንድናገር እግዚአብሔር የቃሉን በር ይከፍትልን ዘንድ ለእኛም ደግሞ ጸልዩልን፣ ለምኑሉንም፡፡ ልናገርም እንደሚገባኝ እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ” እያለ ሲማጸን እንመለከታለን፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ቃል ምሥጢሩን ተረድተን፣ እንደሚገባው እንዲገለጥና ለሌሎች ብርሃን ለመሆን ጸሎት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ያሳየናል፡፡

ከፈተና እንድናለን፡- ፈተና በተለያዩ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል፡፡ የማይገባንን ምኞት በመመኘትና ይህንንም ለማሳካት በምናደርገው ውጣ ውረድ ውስጥ ወደ ማንወጣው ፈተና ውስጥ እንገባለን፡፡ ቅዱስ ዳዊት የጦር አለቃውን የኦርዮንን ሚስት በማይገባ ሁኔታ ተመኘ፣ ምኞቱንም ለማሳካት ባደረገው ጥረት ውስጥ ወደ ሌላ ፈተና ተሸጋገረ፡፡ ከቤርሳቤህ ጋር ዝሙትንም ፈጸመ፣ ኦርዮንንም እስከማስገደል አደረሰው፣ በዚህ አላበቃም በኃጢአት የተወለደውንም ልጅ በሞት አጣ፣ እግዚአብሔርንም አሳዘነ፡፡ በማይገባ ሁኔታ መመኘቱ ለከፋ ኃጢአት አሳልፎ ሰጠው፣ ፈተናውንም መቋቋም ተሳነው፡፡ በመጨረሻም ወደ ልቡናው ሲመለስ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ፣ በትረ መንግሥቱን ጥሎ ትቢያ ለብሶ፣ ዐመድ ነስንሶ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፣ ጩኸቱንም እግዚአብሔር ተቀበለው፣ ይቅርም አለው፡፡ (ሳሙ.፲፩ እና ፲፪)፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ጌቴሴማኒ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ሔዶ ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ ይጸልይ ነበር፡፡ ሐዋርያት ግን ከእርሱ ጋር በጸሎት ከመትጋት ይልቅ እንቅልፍ አሸንፏቸው ተኝተው አገኛቸው፡፡ በዚህም ምክንያት “አንድ ስዓት እንኳ ከእኔ ጋር እንዲህ ተሳናችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” ሲል ነግሯቸዋል፡፡ ከፈተና ለመጠበቅም ሆነ ከፈተና ለመውጣት ጸሎት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያመለክተናል፡፡ (ማቴ.፳፮.፵፩)፡፡ መከራ ሲመጣ መሸሽ ሳይሆን በጽናት በሃይማኖት መቆምን ይጠይቃል፣ በሃይማኖት ለመቆም ደግሞ ጸሎት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ዲያብሎስን ድል እንዳደረገው አባቶቻችንም አምላካቸውን አርአያ አድርገው በጸሎት በመትጋት ፈተናውን ታግሠው ድል ነስተው ተሻግረውታልና እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን ተግተን መጸለይ ይገባል፡፡ ፍጻሜው መንግሥተ ሰማያት ነውና፡፡

የጎደለንን እናገኛለን፡- የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ አንዱ ሲሞላለት ሌላው ሲጎድልበት በድካም ይኖራል፡፡ የጎደለውን ለማግኘትም ሰማይን ካልቧጠጥኩ፣ ምድርን ካልቆፈርኩ እያለ ይባዝናል፡፡ ይህ ደግሞ ከንቱ ድካም ነው፡፡ ነገር ግን ሥጋዊ ፍላጎታቸውን በመግታት፣ በጸሎት በመትጋት የጎደላቸውን መንፈሳዊ ሕይወት ይሞላላቸው ዘንድ አምላካቸውን እየተማጸኑ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ያስገዙ ቅዱሳን፣ ፃድቃን ሰማዕታት ይህንን ኃላፊውን ዓለም ድል ነሥተውታል፣ የጎደላቸውንም አግኝተዋል፡፡

የጎደለንን ለማግኘት በእግዚአብሔር መታመንን ይጠይቃል፣ ዘወትር በዓለማዊው ጥበብ ያጣነውን ለማግኘት ከመማሰን ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ የሚገኘውን በረከት መጠበቅ መልካም ነው፡፡ ሳምራዊቷ ሴት ጎዶሎዋን ይሞላላት ዘንድ፣ ዳግመኛም ወደ ወንዝ እየወረደች ውኃ እንዳትቀዳ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተማጽናለች፡፡ “ጌታ ሆይ እንዳልጠማ ዳግመኛም ውኃ ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ እባክህን ከዚህ ውኃ ስጠኝ” ስትል ጌታችንን የጎደላትን ነገር ጠየቀችው፡፡ (ዮሐ.፬.፲፭)፡፡

በቅድሚያ የጎደለንን ነገር ለይተን እንወቅ፣ የጎደለንን ለማግኘትም እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በጸሎት መትጋት ከእኛ ኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡ ሕዝቅያስ ታሞ ለሞትም በደረሰ ጊዜ በልቅሶና በዋይታ ከሞት ያድነው፣ ጤናውንም ይመልስለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፣ እግዚአብሔርም የሕዝቅያስን ጸሎት ተቀብሎ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስን ልኮም “የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፣ ዕንባህንም አይቻለሁ፣ እነሆ እኔ እፈውስሃለሁ፣ . . . በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ” ሲል ተናግሮታል፡፡ ያጣነው ጤና ቢሆን፣ የመንፈሳዊ ሕይወት ጉድለት ቢሆን፣ . . . ጉድለታችን ወደሚሞላው ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ነው፡፡ ሕዝቅያስ ጸልዮ እንደተከናወነለት እኛም ብንጸልይ እግዚአብሔር ይሰማናል ጉድለታችንንም ሞልቶ ይሰጠናል፡፡(፪ነገ.፳.፭)፡፡

ይቆየን፡፡

“የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ሥልጣን (ዮሐ.፩፥፲፪)

መ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ሥልጣን የሚገኘው በእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ በራስ ጥረትና በሹሙኝ ቅስቀሳ አይደለም፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደገለጸው “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው”(ዮሐ.፩.፲፪) በማለት ለተቀበሉት እና ላመኑት በጸጋ የሚሰጥ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ይህም የሚገኘው ዳግም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ በመወለድ ነው፡፡

ዳግም ልደት ማለት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ማለትም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ መወለድ ሲሆን፣ የሥላሴ ልጅነትን ያስገኛል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወንዱ በተወለደ በዐርባኛው ቀን፣ ሴቷ በተወለደች በሰማንያ ቀኗ ዳግም ከውኃና ከመንፈስ እንዲወለዱ ታደርጋለች፡፡ ለዚህም መነሻዋ መጽሐፍ ቅዱስን አስረጅ በማድረግ  አዋልድ መጻሕፍትን እና ትውፊታዊ አስተምህሮዋን ተከትላ ነው(ኩፋ.፬፥፱)፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሌሊት ወደ እርሱ እየመጣ ይማር ለነበረው ለኒቆዲሞስ ስለ ዳግም ልደት ሲያስተምረው እንዲህ አለው፡፡ “እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” ካለው በኋላ ኒቆዲሞስ ስላልገባው በነገሩ ግራ በመጋባቱ ሰው ዳግመኛ እንዴት መወለድ ይችላል? ሲል ጠየቀው፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡፡ “እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና፤ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውና” (ዮሐ.፫፥፫-፮) በማለት አስረዳው፡፡

የሰው ልጅ ዳግም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ስለሚያድርበት የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ ለእግዚአብሔር የተለየ ዙፋን፣ የእግዚብሔር ቤተ መቅደስ ይባላል፡፡ በዘመነ አበውም ሆነ በዘመነ ኦሪት ራሳቸውን ከርኩሰትና ከኃጢአት ለይተው ለእግዚአብሔር ክብር ከተለዩ ምእመናን ጋር እግዚአብሔር በረድኤት ነበረ፡፡

በሐዲስ ኪዳንም የእግዚአብሐር ልጅ የመሆን ሥልጣንን ያገኘ ሰው አካሉ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ማደሪያ ይሆናል፡፡ ይህንን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነ አካል በንጽሕና በቅድስና መያዝ የሚያድርበትን እግዚአብሔርን ማክበር ነው፡፡ እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነውና ያድርበት ዘንድ ንጹሕ ነገርን ይወዳል፡፡ በኃጢአትና በበደል በተጐሳቆለ አካል ላይ እግዚአብሔር አያድርም፡፡ የእርሱ ማደሪያ፣ ለመሆን በኃጢአት ያደፈውን ማንነት በንስሓ ማጠብና ማንጻት ያስፈልጋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በላከላቸው መልእክቱ “ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር ለተቀበላችሁት በእናንተ አድሮ ላለ ለመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ለራሳችሁ አይደላችሁም በዋጋ ተገዝታችኋልና ስለዚህም እግዚአብሔርን በሥጋችሁ አክብሩት” (፩ኛቆሮ ፮፥፲፱) ይላልና፡፡

ሐዋርያው እንደገለጸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተሰቀለውና ደሙን ያፈሰሰው በዲያብሎስ ግዛት ሥር ወድቆ የነበረውን፤ የሰው ልጅ ነጻ ለማውጣት ነው፡፡ በሲኦል የነፍስ መገዛትን፤ በመቃብር የሥጋን መበስበስ፣ አስወግዶ በፊቱ ሕያዋን አድርጎ ሊያቆመን ስለ በደላችን የደሙን ዋጋ ከፍሎ ገዝቶናልና የራሳችን አይደለንም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆናችን እያስተዋልን ከኃጢአት ልንርቅና ከበደል ልንነጻ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡-
“እናንተ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔር መንፈስም በእናንተ ላይ አድሮ እንደሚኖር አታውቁምን? የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚያፈርሰውን ግን እርሱን ደግሞ እግዚአብሔር ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነውና፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም እናንተ ራሳችሁ ናችሁ፤ እንግዲያስ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አታርክሱ”   (፩ኛቆሮ.፫፥፲፮)ያለን፡፡

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆን እጅግ የከበረ ማንነት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ምን ያህል እንዳከበረውና እንደወደደው ነው፡፡ ለሰው ልጅ ወደር የሌለው ፍቅሩን የገለጠበትም ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ እግዚአብሔርን ያህል በባሕርዩ ቅዱስ የሆነ ጌታ በእኛ በደካሞችና፣ በበደለኞች አካል ማደሩ እጅግ የሚያስደንቅ ቸርነት ነው፡፡ ይህንን ስንረዳ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን ምሕረት እናደንቃለን፡፡

በወንጌል እንደ ተጻፈው በእርሱ ሕይወት ይሆንልን ዘንድ የሚወደውን አንድያ ልጁን ወደ ጎስቋላዋ ዓለም ልኮታል፡፡ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና”(ዮሐ.፫፥፲፮)፡፡

እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍጹም ፍቅሩን ማስተዋል ከቻልን የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ የሆነ አካላችንን የኃጢአት መሣሪያ ለማድረግ አንደፍርም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ብለን እንዳየነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በዋጋ ተገዝታችኋልና የራሳችሁ አይደላችሁም” በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋጋ የገዛን ገንዘቡ እንደሆንን አስገንዝቦናል፡፡

የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ከተረዳን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እንደሆንን መገንዘብ አለብን፡፡ ይህንን ከተረዳን ደግሞ አካላችን በኃጢአት ማቆሸሽ እንደሌለብን፤ በንጽሕና በቅድስና መኖር እንደሚገባን አውቀን ራሳችንን በንስሓ ታጥበን ንጹሓን መሆን ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ነንና ስለ ኃጢአታችን እንዳይፈረድብን አካሎቻችንን ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ልናውላቸው ያስፈልጋል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ግን ይህንን ባለ መረዳት ሰውነታቸውን ሲያረክሱና ሲያቆሽሹ ራሳቸውን ከእንስሳት በታች ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት የሰው ልጅ ቢያውቅበት ምንኛ ታላቅ እንደሆነ በመዝሙሩ ሲገልጽ፡- “ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም፣ ልብ እንደሌላቸው እንስሶችም ሆነ፣ መሰላቸውም” (መዝ.፵፰፥፲፪)ይላል፡፡

የሰው ልጅ ክብሩ(የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ) እውን የሚሆነው ያከበረውን እግዚአብሔርን በሰውነቱ ማክበርና፣ አካሉ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆኑን ተረድቶ ከኃጢአት ሲለይ ብቻ ነው፡፡ ሰው በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ሥልጣንን ስለሚያገኝ ከእግዚአብሔር ቸርነት የተነሣ የተቀደሰና የተከበረ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም” (ዮሐ.፩፥፲፪)ያለው፡፡

የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ሥልጣን የተሰጣቸው ሁሉ ድካም ገጥሟቸው ኃጢአትን በመሥራት የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነ አካላቸውን በሚያሳድፉበት ወቅት ወዲያውኑ ንስሓ በመግባት ከኃጢአት መንጻት አለባቸው፡፡ ንስሓ ኃጥኡን ጻድቅ፣ ዘማዊውን ድንግል ያደርጋልና፡፡ ኃጢአትን የሠሩ ምእመናን ንስሓ በገቡ ጊዜ ከኃጢአታቸው ይነጻሉ፡፡ በሚነጹበትም ጊዜ ንጹሓን የእግዚአብሔር ማደሪያዎች ናቸውና ቅዱሳን ይባላሉ፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

በጊዜው ሁሉ ጸልዩ(ፊል.፬.፮)

ክፍል ሁለት

በእንዳለ ደምስስ

ጸሎት ጸለየ፣ ለመነ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን መለመን፣ ማመስገን፣ በንጽሕና በእግዚአብሔር ፊት መቆም፣ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ “ጸሎትስ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚናገርባት ናት” (ፍትሐ. ነገ. አንቀጽ ፲፬) እንዲል፡፡

አዳም አባታችን ተግቶ በመጸለዩ ዲያብሎስ ሊፈትነው በቀረበ ጊዜ ድል ነስቶታል፣ ሔዋን ግን ሥራ ፈትታ፣ እግሯን ዘርግታ በመቀመጧ በቀላሉ በዲያብሎስ ተረትታለች፣ ዕፀ በለስንም በልታ አጋርዋን አዳምን እስከማብላት ደርሳለች፡፡ በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፈዋልና ተረግመው፣ ስደተኛ ሆነው ከገነት ተባረሩ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተግተን መጸለይ እንደሚገባን ሲያስረዳ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “እግዚአብሔር ቅርብ ነው፣ ምንም ምን አታስቡ፣ ነገር ግን በጊዜው ሁሉ ጸልዩ፣ ማልዱ፣ በምታመሰግኑበትም ጊዜ ልመናችሁን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ” ይለናል፡፡ ዲያብሎስን ድል መንሣት የምንችለውም በጸሎት ኃይል እንደሆነ አስረድቶናል፡፡(ፊል.፬.፮)፡፡

ጸሎት ለመንፈሳዊ ሰው አስፈላጊና ትልቁ መሣሪያው ሊሆን ይገባል፡፡ በዓለም ውስጥ ያለን ሰው  በመውጣት በመውረድ፣ ጥሮ ግሮ ይበላ ዘንድ በታዘዘው መሠረት በርካታ ነገሮች ማለትም በጎም ሆነ መጥፎ ነገር ሊገጥመው ይችላል፡፡ ለገጠመው ክፉ ነገር እግዚአብሔር ችግሩን እንዲያስወግድለት በትጋት መጸለይ፣ እንዲሁም ለተደረገለት መልካም ነገር ሁሉ በጸሎት እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ በደስታችን ወቅት ሳይሆን በችግራችን ጊዜ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ጥረት ስናደርግ እንታያለን፡፡ ነገር ግን በጊዜውም ያለጊዜውም  ቢሆን ወደ እግዚአብሔር መጸለያችንን መቀጠል ያስፈልጋል፡፡  እርሱንም መለመንና ማመስገን ለሰው ልጅ የተሰጠ ስጦታ ነውና፡፡

ለመሆኑ በጸሎት ምን እናገኛለን? ጥቅሙስ ምንድነው? ቀጥለን እንመለከታለን፡-

የጸሎት ጥቅም

ስለተደረገልንና ለሚደረግልን ሁሉ ምስጋና ለማቅረብ፡- ከላይ እንደጠቀስነው በችግራችን ጊዜ ብቻ ሳይሆን በደስታችንም ጊዜ ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ ከአንድ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ ተቀብለኸኛልና የጠላቶቼ መዘባበቻ አላደረግኸኝምና አመሰግንሃለሁ” በማለት ምስጋና ሲያቀርብ እንመለከታለን፡፡(መዝ.፳9.፩)፡፡ ምስጋና ማቅረብ በእግዚአብሔር እንድንታመን፣ የነገ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲቃና ያለው ጥቅም ከፍተኛ ነው፣ ተስፋ ከመቁረጥ ይታደገናልና፡፡ ተስፋ ባለመቁረጥ የምናቀርበው የምስጋና ጸሎት ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ ስላለው ዘወትር መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው ሁለተኛው መልእክቱ “ስለማትመረመርና ባላሰቡአት ጊዜ ስለምትመጣው ጸጋው እግዚአብሔር ይመስገን” እንዲል(፪ቆሮ.9.፲፭)፡፡

ስለበደላችን ይቅርታን እናገኛለን፡- ይቅርታ ከዚህ በፊት ስለተፈጸመና ወደፊት ደግመው ሊያደርጉት በማይገባ በደል ምክንያት የሚጠየቅ ትሕትናን የተላበሰ፣ በተሰበረ መንፈስ ለተበዳይ የሚቀርብ ነው፡፡ ሰዎችን ብንበድል ከእግዚአብሔር ትእዛዝ አፈንግጠናልና በማይገባ መንገድም ተጉዘናልና ተበዳዩን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርንም ጭምር ነው ያሳዘንነው፡፡ ስለዚህ ለፈጸምነው በደል በግለሰቡ ፊት ወድቀን ይቅርታ ስንጠይቅ ግለሰቡም እግዚአብሔርም ይቅርታውን ይቀበላሉ፡፡ “ይህን አስቡና አልቅሱ፣ የተሳሳታችሁ ሆይ ንስሓ ግቡ፣ ልባችሁንም መልሱ” ይለናል(ኢሳ.፵፮.8)፡፡ ልብን መመለስ፣ በቀናውም መንገድ መጓዝ ቀድሞ ስለበደሉት በደል መጸጸትና ማልቀስ፣ በተሰበረ ልብም ሆኖ ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ መሆኑን ያስረዳናል፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት “አንተን ብቻ በደልሁ፣ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፣ በነገርህ ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ታሸንፍ ዘንድ” እያለ ስለ በደሉ ይቅርታ ሲጠይቅ እናያለን፡፡ (መዝ.$..፬)፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤልም “ማቅ ለብሼ በዐመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ፡፡ ወደ አምላኬም ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ … አቤቱ ስማ፣ አቤቱ ይቅር በል፣ አቤቱ  አድምጥና አድርግ አምላኬ ሆይ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና ስለ ራስህ አትዘግይ” እያለ እግዚአብሔርን ይማጸናል ይቅር ማለት የሚችል እግዚአብሔር ነውና፡፡ ይቅርታ የኅሊና ዕረፍትን ይሰጣል፣ ይቅርታ ለአድራጊውም፣ ለተደረገለትም ሰላማዊ ግንኙነታቸውን የሚቀጥሉበት የሰላም ድልድይ ነው፡፡ ከኅሊናችን ጋር ታርቀን፣ ንስሓ ገብተን የወደፊት ሕይወታችንን ልንመራ የምንችለው ይቅርታን ስናገኝና እኛም የበደሉንን ይቅር ስንል ነው፡፡ ጸሎታችንም ይህ ሊሆን ይገባል፡፡ “አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ” እንዲል(ማቴ.፳፩.፳፪)፡፡

ንጉሡ ሕዝቅያስ በታመመና ለሞትም በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ነቢዩ ኢሳይያስን ልኮ “ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል” አለው፡፡ ሕዝቅያስም ይህንን በሰማ ጊዜ ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡- “አቤቱ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደሄድሁ፣ መልካም ነገርንም እንዳደረግሁ አስብ” በማለት አልቅሷል፡፡ እግዚአብሔርም የሕዝቅያስን ጸሎት ተቀበለ፡፡ እንዲህም አለው፡- “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፣ ዕንባህንም አይቻለሁ፣ እነሆም እኔ እፈውስሃለሁ፣ … በዕድሜህም ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ” ሲል መልካሙን ዜና ለመስማት በቅቷል፡፡(፪ኛ ነገ.፳.፩)፡፡ ስለዚህ በጸሎት ኃይል ይቅርታን እናገኛለን፡፡

መንፈሳዊ ኃይልን እናገኛለን፡- መንፈሳዊ ኃይል በአንድ ጀምበር የሚገኝ አይደለም፡፡ ማመን፣ ለአመኑትም አምላክ መገዛት፣ ዘወትር በሚያምኑት አምላክ ፊት መቆምንና መጸለይን ይጠይቃል፡፡ መንፈሳዊ ኃይል መንፈሳዊ ልምምድ በማድረግ፣ በጸሎት በመበርታት የሚገኝ ጸጋ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “እርስ በእርሳችሁ ኃጢአታችሁን ተናዘዙ፣ እንድትድኑም ለወንድሞቻችሁ ጸልዩ፣ የጻድቅ ሰው ጸሎቱ ብዙ ትረዳለች፣ ግዳጅም ትፈጽማለች” ይላል ከራስ አልፎም ስለ ሌሎች መጸለይ እንደሚገባ ሲያስረዳን፡፡(ያዕ.፲፭.፲፮)  ይህም ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ጸጋ ነውና፡፡ ጸሎት በንጹሕ ኅሊና ሆነው ቢጸልዩ “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ” እንዲል ቅዱስ ዳዊት የለመኑትን የማይነሣ አምላክ በጸጋ ላይ ጸጋንም ያላብሰናል፡፡(መዝ.፻፵፥፪)፡፡ ይቆየን፡፡

“የሰላም መንገድ” (መዝ.፲፬፥፮)

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ሰላም ማለት ጸጥታ፣ ዕረፍት፣ እርጋታ፣ እርካታ ማለት ሲሆን የእርስ በእርስ ስምምነት፣ በአንድነት አብሮ መኖር፣ መቻልና የዕረፍት ስሜት እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ያስረዳል፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ክፉዎች የሰላምን መንገድ የማያውቁ መሆናቸውን “ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፣ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው አለ፣ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም” (መዝ.፲፬፥፮) ሲል ይገልጻል፡፡

በሌላም ክፍል በጎ ዘመንን ሊያይ የሚወድ ቢኖር ሰላምን መፈለግና የሰላምን መንገድ መከተል እንደሚገባው ሲያስረዳን፡- “ልጆቼ ኑ ስሙኝ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችሁ ዘንድ፤ ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፣ ከንፈሮችህም ሸንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ፣ መልካንም አድርግ፣ ሰላምን ሻት ተከተላትም” በማለት ሰላምን መከተል እንደሚገባ ያስረዳናል፡፡ (መዝ.፴፫፥፲፫-፲፬)

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ልጆቹ ለምንሆን ለእኛ ሲያስተምረን እግዚአብሔር የፈቀደለትንና እርሱ በሕይወቱ ገንዘብ አድርጎት በእግዚአብሔር እንደ ልቤ ተብሎ የተመረጠበትን ጥበብ ሲነግረን “እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ” አለ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔርን መፍራት ከሁሉ ይልቅ ቀዳሚ ነውና፡፡ ለዚህም ነው አባትና ልጅ ተባብረው(ተቀባብለው) የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ የነገሩን (መዝ.፻፲፥፲፤ ምሳ.፩፥፯፤9፥፲)፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ በሕይወታችን እግዚአብሔርን መፍራት አስፈላጊ ነው፡፡ ሰላምን የምንሻበት መንገድ እርሱ ነውና፡፡ ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔርን መፍራት ሕይወትን የሚያስገኝና በጎ ዘመንን ለማየት የምንችልበት የጥበብ (የዕውቀት) ሁሉ መሠረት እንደሆነ ከገለጸ በኋላ “ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው?” ብሏል፡፡ ከላይ እንዳየነው ሕይወትን ለማግኘት የሚሻ በጎ ዘመንንም ለማየት የሚፈልግ ጥበብን (ማስተዋልን) ገንዘብ ያደረገ ሰው ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን የሰላምን መንገድ መከተል፣ ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የሚሻ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት ስንመለከትም፡-

ኛ. አንደበትን  ከክፉ መከልከል፡-

የሰው ልጅ በልቡ ያሰበውን በአንደበቱ ይናገራል፡፡ በልብ የታሰበውን መልካምም ይሁን ክፉ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ሲሆን፣ ነገር ግን የታሰበው ነገር በውጫዊ ሰውነት ላይ በሚታዩ ምልክቶች(ገጽን በማየት) መታወቅ የሚችልበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ወይም በአንደበት ቢነገርና በሥራ ቢተገበር ሰዎች ይረዱት ይሆናል፡፡

አንደበትን ከክፉ ካልከለከሉት ሰዎችን የሚጎዳና የማይሽር ጠባሳ ጥሎ የማለፍ፣ በዚያም ሰበብ ተናጋሪውን ሳይቀር ለሞት የማብቃት ዕድል አለው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “ምላስም እሳት ናት እነሆ ትንሽ ምላስ በሰውነታችን ውስጥ  ዐመፅ የተመላበት ዓለም ናት ሥጋችንን ትበላዋለች፣ ውስጣዊ ሰውነታችንንም ትጠብሰዋለች፣ ከገሃነምም ይልቅ ታቃጥላለች” በማለት የገለጸው፡፡(ያዕ.፫፥፮) ስለዚህ ሕይወትን የሚፈቅድና በጎ ዘመንን ለማየት የሚፈልግ ሰው አንደበቱን ከክፉ ነገር መከልከልና መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ተናግሮ ሰውን ላለማስቀየምና ላለማስከፋት መጠንቀቅ፣ ሌላውንም ሰው ወደ ጥፋት ላለመምራት ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ አንደበት ኃያል ነው ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል ይባላልና፡፡

አንደበትን ከክፉ ካልከለከልነው ስድብንና ሐሜትን እናበዛለን፡፡ ይህ ደግሞ ከሕይወት ጎዳና የሚያወጣ ክፉ ተግባር ነው፡፡ በጓደኛ፣ በባልና ሚስት፣ በአንድ ሀገርና በሌላው ሀገር፣ በጎሳና በጎሳ፣ በጎረቤትና በጎረቤት መካከል ሐሜትና መነቃቀፍ፣ ስድብና ጥላቻ ካለ በጎ ዘመንን ማየት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ሕይወትንም ሆነ በጎ ዘመንን ለማየት አንደበትን ከክፉ መከልከልና በጎ ነገርን መናገር አስፈላጊ ነው፡፡

ኛ. ከክፉ መሸሽ፡-

ከክፉ  መሸሽ  ማለት  ክፉን  ከማድረግ  መቆጠብና  ክፉ  ከሚያደርጉት  ጋር  በክፋታቸው አለመተባበር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ሁል ጊዜም ቢሆን ከክፉዎች ጋር ኅብረት የለውም፡፡ አባታችን ያዕቆብ ልጆቹን በሚመርቅበት ጊዜ ክፉ ሥራ ከሠሩ ከልጆቹ የክፋት ሥራ ጋር እንደማይተባበርና ከክፋት ጋር ኅብረት እንደሌለው ገልጧል፡፡ “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ በጭቅጭቃቸውና በጦራቸው ዐመፅን ፈጸሟት፣ በምክራቸው ሰውነቴ አትገናኛቸው፣ ሐሳቤም በዐመፃቸው አትተባበርም፣ በቊጣቸው ሰውን ገድለዋልና በገዛ ፈቃዳቸውም የሀገርን ሥር ቆርጠዋልና ቁጣቸው ርጉም ይሁን፣ ጽኑ ነገርና ኩርፍታቸውም ብርቱ ነበርና በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ” (ዘፍ.፵፱፥፭)፡፡ ያዕቆብ ምንም እንኳ በሥጋ የወለዳቸው ልጆቹ ቢሆኑም በፈጸሙት ክፉ ሥራ ግን እንደማይተባበር ከክፉ ሥራቸው የራቀና ከክፋት የተለየ መልካም ሐሳብ እንዳለው ገልጧል፡፡

ዛሬም ቢሆን የሰው ልጆች ክፋትና በደል እየበዛ ባለበት ሰዓት የእግዚአብሔር ልጆች ከክፋት፣ ከተንኮል፣ ከውሸት፣ ከሌብነት፣ ከቅሚያ፣ ከዝርፊያ፣ ከጭካኔ፣ ከሴሰኝነት፣ ከዘማዊነት፣ ከዘረኝነት በአጠቃላይ ለራስም ሆነ ለሀገር ከማይበጁ እኩይ ምግባራትና ከሚፈጽሟቸው ሰዎች ጋር መተባበር የለብንም፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን ሕይወትን ለማግኘት የምንሻና በጎ ዘመን ለማየት የምንፈልግ ሁሉ ከክፉዎች ጉባኤ መለየትና አለመተባበር ያስፈልጋል፡፡

ኛ. መልካም ማድረግ

ሕይወትን ለማግኘትና በጎውንም ዘመን ለማየት የሚሻ ሰው ሁሉ መልካምን ሊያደርግ ያስፈልገዋል፡፡ ከክፉ መሸሻችንና ከክፉዎች ጋር አለመተባበራችን መልካም ሥራ ለመሥራት መሆን አለበት እንጂ ከሥራ ርቀን እንዲሁ እንድንኖር አይደለም፡፡ ያለ በጎ ሥራ መኖር ስንፍና ነውና፡፡

እግዚአብሔር የሰውን ውድቀቱንና መጥፋቱን የማይሻ አምላክ ስለሆነ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በክፉ ሥራ ተጠምዶ የነበረ ሁሉ ሊመለስና በሕይወት ሊኖር ይገባዋል፡፡ በቀደመው ስሕተቱ ወንድሙን ያሳዘነ፣ ሰው የገደለ፣ አካል ያጎደለ፣ ግፍን የፈጸመ፣ የድሃውን ገንዘብ በተለያየ ሰበብ የዘረፈ፣ ጉቦ የተቀበለ፣ በእነዚህና መሰል እኩይ ሥራዎች ሀገሩን የጎዳ፣ እግዚአብሔርን የበደለ ሁሉ ከልብ በመጸጸት በልቅሶና በዋይታ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ ሕዝቅኤል ላይ አድሮ ኃጢአተኛው ከኃጢአቱ ተመልሶ በሕይወት መኖር እንዳለበት አስገንዝቦናል፡፡

“እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው (በደለኛው) ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ ከከፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለምንስ ትሞታላችሁ?” (ሕዝ. ፴፫፥፲፩) እንዲል፡፡

እግዚአብሔር በነቢዩ ላይ አድሮ እንደ ነገረን በደለኛ ሰው በበደሉ ቀጥሎ መጥፋት የለበትም፡፡ መመለስና በሕይወት መኖት ያስፈልገዋል እንጂ፡፡ እሱም እንደ በደሉ ዓይነት ይቅርታ ጠይቆ፣ ንስሓ ገብቶ፣ የበደለውን ክሶ፣ የሰረቀውን መልሶ፣ የሰበረውን ጠግኖ፣ ያጎደለውን መልቶ በፍጹም መጸጸት ሊመለስና መልካም በመሥራት ሌት ተቀን ከሚተጉት ጋራ በመልካም ሥራ ሊተባበር ያስፈልገዋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን “ስለዚህ ሐሰትን ተውአት ሁላችሁም ከወንድሞቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ እኛ አንድ አካል ነንና አትቆጡ፣ አትበድሉም፣ ፀሐይ ሳይጠልቅም ቊጣችሁን አብርዱ፣ ለሰይጣንም መንገድን አትስጡት፣ የሚሰርቅም እንግዲህ አይስረቅ ነገር ግን ድሃውን ይረዳ ዘንድ በእጆቹ መልካም እየሠራ ይድከም” (ኤፌ.፬፥፳፭) ይላል፡፡

ኛ.ሰላምን መሻት

ሰላም ለሁሉ ነገር አስፈላጊና ሁሉን ለማድረግ የምንችልበት የመልካም ነገር ሁሉ በር ነው፡፡ ሰላምን መፈለግ ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንንም ለማየት ያስችላል፡፡ ሰላምን በሁለት መልኩ እናያለን፡፡ እሱም የውስጥ ሰላምና የውጭ ሰላም ወይም ውስጣዊ ሰላምና ውጫዊ ሰላም ተብሎ ይመደባል፡፡

የሰው ልጅ ለመኖር ውስጣዊ ሰላምም ሆነ ውጫዊ ሰላም ያስፈልጉታል፡፡ ውስጣዊ ሰላም የምንለው አንድ ሰው ከፍርሃት፣ ከጭንቀት፣ ከመረበሽ፣ ከሥጋት… ወዘተ ነጻ ሆኖ መኖር ሲችል ውስጣዊ ሰላም አለው ይባላል፡፡ ይህም የውስጥን ሰላም ከሚያደፈርሱ፣ አእምሮን ከሚረብሹ፣ ልብን ከሚያቆስሉ፣ የጸጸት እሮሮን ከሚያስከትሉ ነገሮች ስንርቅና ለአእምሮ የሚመች ሥራ ስንሠራ ውስጣችን ሰላም ይሆናል፡፡

ውጫዊ ሰላም የምንለው ደግሞ፡- ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከጎረቤት፣ ሀገራት ጋር ተስማምተንና ተግባብተን ተቻችለንና ተረዳድተን በፍቅር ተሳስረን በመኖር ከጥል ከመለያየት፣ ከመጠላላት፣ ከመገፋፋት፣ ከመነቃቀፍ ተቆጥበን የጠብንና የጦርነትን ወሬ ባለመስማትና በስምምነት ተግባብቶ በመኖር የሚገለጥ ነው፡፡ ስለዚህ ሰላም ለሁሉ እንደሚያስፈልገው ካወቅን የሰላም መገኛ ማን እንደሆነና ሰላም ከየት እንደሚገኝ ማወቅ ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡

ሰላም የሚገኘው የሰላም ባለቤት ከሆነው ከልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጠው እውነተኛ ሰላም ከእግዚአብሔር ይገኛል፡፡ እርሱ የሰላም አምላክ ነውና (ሮሜ.፲፭፥፴፫)፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም አለቃ ተብሏል፡፡ “ሕፃን ተወዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ. 9፥፮) እንዲል፡፡

ዓለም ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ያህል ሰላሙን አጥቶ በመቅበዝበዝ ይኖር የነበረ ሲሆን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን፣ እውነተኛውን ሰላም አግኝቷል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ሞት ምክንያት ፍርሃት ጸንቶባቸው ለነበሩት ደቀ መዛሙርት “ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፣ ልባችሁ አይደንግጥ አትፍሩም” (ዮሐ.፲፬፥፳፯) በማለት ፍርሃትን፣ ስጋትን፣ ጭንቀትን፣ ሁከትን፣ መረበሽን የሚያርቀውን (የሚያስወግደውን) እውነተኛውን ሰላም አደለን፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እንዳለው ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የምንሻ ሁሉ ሰላምን መሻት ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም ሰላምን መሻት ብቻ ሳይሆን መከተል ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም መሻት ብቻውን ዋጋ ሊኖረው ስለማይችል፡፡ መሻታችን ወደ ማግኘት የሚደርሰው የምንሻውን ነገር ለማግኘት ወደ መገኛው መጓዝና መቅረብ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰላምን ሻት ካለ በኋላ ተከታላትም በማለት በሰላም መንገድ መጓዝ፣ የሰላም ወሬ ማውራት፣ ለሰላም የሚስማማ ሥራ መሥራት፣ የራሳችንን ሰላም መጠበቅና የሌላውንም ሰላም አለማደፍረስ ማለት እንደሆነ የነገረን፡፡ የእግዚአብሔር ሰላም ለሁላችን ይሁንልን፡፡ ይቆየን፡፡

“የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ”/ኤፌ.፮.፲፬/

ክፍል አንድ

በእንዳለ ደምስስ

መንፈሳዊ ሰው ርስት መንግሥተ ሰማያትን ይወርስ ዘንድ፣ ራስን ለእግዚአብሔር ማስገዛት፣ ትእዛዙንም መፈጸም ይጠበቅበታል፡፡ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ለመሸጋገርም አንድ ክርስቲያን መንፈሳዊ የተጋድሎ መሣሪያዎችን ይዞ መገኘት ይገባዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ ቁሙ፣ የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ” እንዲል/ኤፌ.፮.፲፬/፡፡

ሃይማኖትን፣ መልካም ምግባርን፣ ፍቅርን፣ የንስሓ ሕይወትን፣ ወዘተ የያዘ ሰው ራሱን ከዲያብሎስ ውጊያዎች ለመከላከል መንፈሳዊ የተጋድሎ መሣሪያዎችን መያዝ ወይም መታጠቅ ያስፈልገዋል፡፡ እነዚህም፡- ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ እነዚህን በቅደም ተከተል በጥቂቱ የምናቀርብ ይሆናል፡፡

ጾም

ጾም ክርስቲያን የሆነ ሰው ሁሉ ከሰባት ዓመት የሕፃንነት ዕድሜው ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜና ሰዓት ከእህል፣ ከውኃ ተከልክሎ መቆየት ማለት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ከወተት፣ ከሥጋ፣ ከቅቤና፣ ከእንቁላል የአጽዋማቱ ሳምንታት እስኪጠናቀቁ ድረስ የምንከለከልበት ነው፡፡ /ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፭/፡፡

ጾም ዓይን ክፉ ከማየት፣ ጆሮ ክፉ ከመስማት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር፣ እጅ ክፉ ከመሥራት በአጠቃላይ የኃጢአት ሥራ ከመሥራት መከልከል ማለት ነው፡፡ /ቅዱስ ያሬድ/

ጾም የአዋጅ እና የግል/የፈቃድ/ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡

. የአዋጅ ጾም፡ ይህ ጾም በቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ሁሉ በሥውር ሳይሆን በይፋ የሚጾሙት ጾም ነው፡፡ ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል “በጽዮን መለከትን ንፉ፣ ጾምንም ቀድሱ፣ ጉባኤውንም አውጁ” በማለት እንደተናገረው (ኢዩ 2፡፲፭)፡፡

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የደነገገቻቸው የአዋጅ አጽዋማት ሰባት ሲሆኑ፣ እነዚህም እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡-

፩. የነቢያት ጾም                          ፭. የሐዋርያት ጾምየገሃድ ጾም                ፮. ጾመ ድኅነት (ረቡዕና ዓርብ)

2. የነነዌ ጾም                            ፯. ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡

፬. ዐቢይ ጾም

. የግል/ፈቃድ/ ጾም፡  የግል ጾም ስንል አንድ ሰው በሠራው ኃጢአት ምክንያት ወደ ንስሓ አባቱ በመቅረብ  በጸጸትና በተሰበረ ልብ ሁኖ ኃጢአቱን በመናገር የሚሰጠው የንስሓ ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም በፈቃድ የሚጾም ሲሆን አንድ ሰው ስለ በደሉ፣ ስለደረሰበትና በእርሱ ላይ ስለሆነ ነገር፣ እንዲሁም ስለሚፈልገው ጉዳይ እግዚአብሔር ተገቢውን መልስ እንዲሰጠው የሚጾመው ጾም ነው፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዳዊት የልጁን መታመም በሰማ ጊዜ ጾሟል፡፡ /2ኛ.ሳሙ.፲2፡፲2/፡፡ ነገር ግን በግል ጾም ጊዜ ጾሙ ይፋ ስላልሆነ ራስን መሠወር እንደሚያስፈልግ ታዟል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ “ስትጾሙም እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፣ እነርሱ እንደ ጾሙ ለሰው ይታዩ ዘንድ መልካቸውን ይለዋውጣሉና፣ እውነት እላችኋላሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ እናንተስ በምትጾሙበት ጊዜ  ራሳችሁን ቅቡ፣ ፊታችሁንም ታጠቡ፡፡ በሥውር ለሚያይ ለአባታችሁ እንጂ ለሰዎች እንደ ጾማችሁ እንዳትታዩ በሥውር የሚያያችሁ አባታችሁም ዋጋችሁን በግልጥ ይሰጣችኋል” ብሏል፡፡(ማቴ.፮፡፲፮-፲፰)፡፡ በዚህ መሠረት የግል ጾምን ከጿሚው ሰው እና ከእግዚአብሔር ውጪ ማንም ሊያወቅ አይገባም፡፡

2. ጾም ለምን ያስፈልጋል?

ጾም ያስፈለገበት ምክንያት የሥጋን ፍላጎት በመግታትና ከኃጢአት ሥራዎች የሚጠብቀን በመሆኑ ነው፡፡ ሰው እንደፈለገው የሚበላና የሚጠጣ፣ ሁል ጊዜ ሳይጾም የሚኖር ከሆነ በኃጢአት ይወድቃል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ “ሥጋዊ ፍትወትን ያደክም ዘንድ ጾም ታዘዘ” እንዲል፡፡ ጾም ረኀብን፣ ችግርን እንድናውቅ፣ ለተራቡና ለተጠሙ በአጠቃላይ ለተቸገሩ ሁሉ እንድናስብና እንድናዝን፣ ባለን አቅም ሁሉ እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ “ጿሚ ሰው የረኀብን ችግር ያውቅ ዘንድና ለተራቡ ይራራ ዘንድ ጾም ታዘዘ” ይላል፡፡(ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭)

ስለዚህ ጾም ለተራቡ፣ ለጠጠሙ እንዲሁም ለተቸገሩ ሁሉ መራራትን፣ በጎ ማድረግን በማስተማር የምግባር፣ የትሩፋት፣ የትሕርምት ሰዎች ያደርገናል፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ፊት የጽድቅ ሥራ ሆኖ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሰናል፡፡

ቀድሞ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ካዘዛቸው ትእዛዛት መካከል “መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፣ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” /ዘፍ.2.፲፮///////// ብሎ ሥርዓት ቢሠራላቸውም አዳምና ሔዋን ግን ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል አፈረሱ፣ ገነትን ከሚያህል ሥፍራም ተሰደዱ፡፡ ለመሰደዳቸው ምክንያት የሆነው ይጾሙት ዘንድ የተሠራላቸውን ሥርዓት በማፍረሳቸው፣ ዕፀ በለስንም በመብላታቸው ነው፡፡ መብል ከእግዚአብሔር አንድነት የሚለይ ከሆነ ጾም ደግሞ ለእግዚአብሔር ትእዛዛት እንድንገዛ፣ መንግሥቱንም እንድንወርስ ድርሻ እንዳለው ያመለክተናል ማለት ነው፡፡ “ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው፡፡ በደሉን ለማስተሥረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት፣ እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ፣ ለነባቢት ነፍስም ትታዛዝ ዘንድ” እንዲል /ፍትሐ ነገ. አንቀጽ ፲፭/፡፡

አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “ስለ ጽድቅ ብለው የሚራቡና የሚጠሙ ንዑዳን ክቡራን ናቸው፣ እነርሱ ይጠግባሉና” /ማቴ ፭.፮/ ሲል ተናግሯል፡፡ ስለዚህ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ጾም ድርሻ እንዳለው ያመለክተናል፡፡

ጾም በሀገር ላይ የታዘዘ መቅሠፍትን ያርቃል፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሀገር ላይ ሊመጣ ያለውን መቅሰፍት በጾም አማካይነት እንደሚርቅ ያስተምረናል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የነነዌ ሰዎችን መመልከት እንችላለን፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ትምህርት መሠረት በማድረግ ሕፃናቱን ጨምሮ እንስሳቱ ሁሉ ለሦስት ቀናት ጾመዋል፡፡ እግዚአብሔርም ሊመጣ የነበረውን መቅሰፍት አርቆ ለእነርሱ የታዘዘው እሳት የዛፉን ጫፍ አቃጥሎ ተመልሷል፡፡ (ዮና.፫)፡፡ “አምላካችሁም እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፣ ቁጣውም የዘገየ፣ ምሕረቱም የበዛ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና” እንዲል /ኢዩ.2.፲፫///፡፡

ጾም ሰይጣንን ድል የምንነሣበት መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡- ከላይ እንደተጠቀሰው ጾም ፈቃደ ሥጋችንን ለነፍሳችን የምናስገዛበት፣ ለመልካም ነገር የምንነሳሳበትና ክፉውን የምናርቅበት መሣሪያ በመሆኑ ዲያብሎስ በእኛ ላይ አይሠለጥንም፡፡ ክፉ ከማሰብ፣ ክፉ ከማድረግ እንድንቆጠብም ያደርገናል፣ ለመንፈሳዊ ተጋድሎም ያዘጋጀናል፡፡ ሥጋዊ ፍላጎታችንን እየገታን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እንበረታለን፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች፣ ደስተኞች ከንፈሮቼም ስምህን ያመሰግናሉ” በማለት እንደተናገረው፡፡(መዝ.፷፪፥፭)፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ባለመጾማችንና ለመንፈሳዊ ተጋድሎ ራሳችንን ባለማዘጋጀታችን ዲያብሎስ እንዲሠለጥንብን፣ ለኃጠአት እንድንሣሣና ከእግዚአብሔር እንድንለይ ያደርገናል፡፡ “እንዲህ ዓይነት አብሮ አደግ ጋኔን ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም” /ማቴ.፲፯፤፳1/ ሲል ጌታችን በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረው ሰይጣንን ድል መንሳት የምንችለው በጾምና በጸሎት እንደሆነ ያስረዳናል፡፡

ጾምፈተና እና መከራ ያድናል፡- ፈተና እና መከራ በገጠመን ጊዜ ሱባኤ ይዘን እንጾማለን፣ እንጸልያለን፤ ነገር ግን ብዙዎቻችን ፈተና ወይም መከራ በራቀልን ጊዜ ደግሞ ጾም ጸሎት እናቆማለን፡፡ የምንሻውን ነገር እስክናገኝ፣ ከደረሰብንና ሊደርስ ካለብን ፈተና ለመዳን እንጨነቃለን፣ እንጠበባለን፡፡ ይህ ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እንጾምባቸው ዘንድ የደነገገችልን የአዋጅ አጽዋማት እንዳሉ ሁሉ የግል/የፈቃድ/ ጾምም እንዳለ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ክርስቲያን በቀን ውስጥ ሊጸልይባቸው የሚገቡ ሰዓታት እንደተወሰኑ ሁሉ ጾምም አስፈላጊና ዋነኛው ነው፡፡ ሊመጣ ካለው ፈተናም የምንጠበቀው በጾምና ጸሎት ነው፡፡ “ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም፣ እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ” (ዳን.9.፫) እንዲል ነቢዩ፡፡

በጾም ኃጢአት ይሠረያል፡- ቅዱስ ያሬድ “በጾም ወበጸሎት ይሠረይ ኃጢአት፣ በጾምና በጸሎት ኃጢአት ይሠረያል” እንዳለ ጾም ትልቅ ኃይል አለው፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ትምህርት መሠረት በማድረግ ሦስት ቀን ጾመው ጸልየው ኃጢአታቸው ተሠርዮላቸዋል፡፡/ዮና.፫/፡፡ነቢዩ ዳንኤል በጾም ከአፈ አናብስት /ከአንበሶች አፍ/ የዳነው በጾምና በጸሎት ነው፡፡ /ዳን.፮/፡፡  ሶስናም በጾም ከሐሰት ምስክሮች ድናለች፡፡ /ሶስ.1/ ሌሎችም ቅዱሳን በጾም ከፈተና እና ከመከራ ድነዋል፡፡

ጾም ከላይ የተዘረዘሩት ብቻ ሳይሆን በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ኃጢአት በመብል አማካይነት ወደ ዓለም እንደገባ በጾም ደግሞ ዲያብሎስን ድል እናደርጋለን፡፡ ዲያብሎስም ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልሶ “ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንዳይደለ ተጽፏል” /፬.፬/ አለው እንዲል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያብሎስን በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና ሌሊት ጾሞ ድል ነስቶታልና እኛም እርሱን አርአያ አድርገን በመጾም በመንፈሳዊ ሕይወት በመጽናት ድል ልናደርገው ይገባል፡፡

ይቆየን፡፡

ጾመ ነቢያት

ጾመ ነቢያት ቅዱሳን ነቢያት ጌታ ለአዳም በሰጠው ተስፋ መሠረት ይወርዳል፣ ይወለዳል ብለው ሱባዔ በመቁጠር የክርስቶስን ልደት በመጠበቅ የጾሙት ጾም ነው፡፡

በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በተሰጣቸው ጸጋ ትንቢት  የራቀው ቀርቦ፣ የረቀቀው ገዝፎ ያዩት ነገር እንዲደርስላቸው ጾሙ፣ ጸለዩ፡፡ ነቢያት ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስደት፣ ሞቱና ትንሣኤው፣ እንዲሁም ጨለማ የሆነውን የሰው ልጆችን ልቡና በትምህርቱ ስለ ማብራቱ፣ ጨለማውን ዓለም በብርሃኑ ስለ መግለጡ፣ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት ጸዋወ መከራ ስለ መቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ  ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረዋል፡፡

እንደዚሁም ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍጻሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን በየዘመናቸው “አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ” እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሣምንታት፣ በወራት፣ በዓመታት ቆጠሩ፡፡

ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም “እግዚአብሔር የማያደርገውን አይናገር፣ የተናገረውን አያስቀር” ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ ዘመኑ ሲደርስም በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትንቢቱ ተፈጸመ፡፡ ስለዚህ ነቢያት ይወርዳል፣ ይወለዳል እያሉ የጾሙት በመሆኑ “ጾመ ነቢያት” ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት ስለሆነም “ጾመ ስብከት” ይባላል፡፡ ጾመ ነቢያት ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ሲሆን፣ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እንዲጾም ደንግጋለች፡፡

ጾም ቃላዊ ትርጉሙ ጾመ፣ ተወ፣ ታረመ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ነው፡፡ በታወቀ ጊዜ ከምግብ መከልከል፣ መጠበቅ ማለት ነው፡፡ በአጭሩ ጾም ለሰውነት ከሚያስፈልገው ኃይል ከሚሰጡ ምግቦች፣ ከክፉ ሐሳብና ድርጊት በመከልከል ከእግዚአብሔር ጋር በፍቅር የመኖር ሕይወት ነው፡፡ ለክፉ ሥራ/ኃጢአት ከሚያነሣሱና ሰውነትን ከሚገነቡ ምግቦችና መጠጦች በመከልከል በጾም፣ በጸሎት በመወሰን ልቡናችንን ለእግዚአብሔር ሰጥተን፣ በፍጹም ትኅትና የምንጾመው ጾም ነው፡፡ በዚህ ወቅት በመንፈሳዊ ሕይወታችን የምንበረታበት፣ ንስሓ የምንገባበትና ለቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የምቀርብበት በመሆኑ ጊዜውን በዋዛ ፈዛዛ ማሳለፍ አይገባንም፡፡ ከቅዱሳን ነቢያት በረከት እንሳተፍ ዘንድ የትሩፋት ሥራዎችን እየሠራን ልናሳልፈውም ይገባል፡፡

አርባዕቱ እንስሳ

ኅዳር ስምንት ቀን “ሥጋ የሌላቸው የአርባዕቱ እንስሳ በዓላቸው ነው፡፡ እነርሱም የእግዚአብሔርን መንበር የሚሸከሙ ሠረገላዎቹ ናቸው” በማለት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነው መጽሐፍ ስንክሳር ይገልጻል፡፡  ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይህንኑ በራእይ ያየውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፡- “በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ፤ በዙፋኑም መካከል፣ በዙፋኑ ዙሪያም አራት እንስሶች አሉ፣ እነርሱም በፊትም በኋላም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው፡፡ ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፣ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፣ ሦስተኛውም እንስሳ ሰውን ይመስላል፣ አራተኛውም እንስሳ የሚበር ንስርን ይመስላል፡፡ ለእነዚህም አራቱ እንስሶች ለእያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሏቸው፤ በሁለንተናቸውም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው፡፡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረውና ያለው፣ የሚመጣውም፣ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም፡፡ እነዚህ እንስሶችም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴን ምስጋናንም ይሰጣሉ”(ራእ.፬.፮-9፣ ስንክሳር ዘኅዳር ገጽ 2፻፸፯) በማለት ገልጿቸዋል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም “እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፣ ምስጋናውም ቤቱን ሞልቶት ነበር፡፡ ሱራፈልም በዙሪያው ቆመው ነበር፣ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፣ በሁለቱ ክንፎቻቸው ፊታቸውን ይሸፍኑ ነበር፣ በሁለቱም ክንፎቻቸው እግሮቻቸውን ይሸፍኑ ነበር፣ በሁለቱም ክንፎቻቸውም ይበርሩ ነበር፡፡ አንዱም ለአንዱም ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች፣ እያለ ይጮኸ ነበር፡፡”(ኢሳ.፮.፩-፫፤ ስንክሳር ገጽ 2፻፰) እያለ የእግዚአብሔርን ዙፋን ስለሚሸከሙት አርባዕቱ እንስሳ ተናግሯል፡፡ አገልግሎታቸውም በዙፋኑ ፊት እግዚአብሔርን  ሃያ አራት ሰዓት “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” እያሉ ማመስገን ነው፡፡

ከአራቱ ዐበይት ነቢያት መካከል አንዱ የሆነው ነቢዩ ሕዝቅኤል በምርኮ ሳለ ያየውን ራእይ እንዲህ በማለት ይገልጻል፡- “የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ በእኔ ላይ ሆነች፣ እኔም አየሁ፣ እነሆም በሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና፣ የሚበርቅም እሳት መጣ፣ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፣ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ የሚብለጨለጭ ነገር ነበረ፣ ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ፡፡”(ሕዝ.፩.፫-፭) እንዲል፡፡

ስለ አርባዕቱ እንስሳ ልዕልናቸውና ክብራቸው ከብሉይና ከሐዲስ ብዙ መጻሕፍት መስክረዋል፤ መሐሪና ይቅር ባይ እግዚአብሔርም ስለ ሁሉ የሰው ፍጥረት ይለምኑት ዘንድ ቀራቢዎቹ አደረጋቸው፡፡ ገጸ ሰብእ ስለ ሰው ፍጥረት ይለምናል፣ ገጸ አንበሳ ስለ አራዊት ይለምናል፣ ገጸ ላሕም ስለ እንስሳት ይለምናል፣ ገጸ ንስርም ስለ አዕዋፍ ይለምናል፡፡ ከሠማይ ሠራዊት ሁሉ እነርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ በባለሟልነት እጅግ የቀረቡ ናቸውና፡፡

ስለዚህም በዓለሙ ሁሉ በስማቸው አብያተ ክርስቲያን እንዲታነጹ በዚህችም ቀን መታሰቢያቸው እንዲደረግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ፣ እነርሱ ስለ ሰው ወገን በእግዚአብሔር ዘንድ ይማልዳሉና፡፡ (ስንክሳር ገጽ 2፻፸9)፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ኪሩቤል አማላጅነት ይማረን፣ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር፣ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ግቢ ጉባኤያትን ለማጠናከር በጋራ እንሥራ

በእንዳለ ደምስስ

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ለማነጽ በምታደርገው ጥረት ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ማስታጠቅ ዋነኛ ተግባሯ ነው፡፡ ለዚህም ከላይ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ድረስ ባለው መዋቅር ምእመናን ስለ እምነታቸው እንዲረዱ፣ ሕይወቱንም እንዲኖሩት በማድረግ ላለፉት ፳፻ ዓመታት ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ስታከናውን ቆይታለች፡፡ በእነዚህ ዘመናት ሁሉ መውደቅ መነሣት ቢያጋጥማትም በክርስቶስ ደም በዐለት ላይ ተመሥርታለችና ፈተናውንና መከራውን ተቋቁማ ዘልቃለች፤ እስከ ዕለተ ምጽአትም ትቀጥላለች፡፡

ወንጌልን መሠረቷ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን የሚገጥሟትን ፈተናዎች ለመቋቋምና አገልግሎቷን ለማስፋፋት ደግሞ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በሃይማኖት የጸኑ፣ በሥነ ምግባር የታነጹ ወጣቶች ለማፍራትም ዘመኑን የዋጀ ትምህርት በየሰንበት ትምህርት ቤቶች ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከዚህም አልፎ በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ የሚማሩ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ላይ መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ ካለፉት ፳9 ዓመታት ጀምሮ ማኅበረ ቅዱሳን ከቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ፈቃድ መሠረት ኃላፊነት ወስዶ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ከሰባት መቶ ሺሕ በላይ ተማሪዎችን አስተምሮ ለማስመረቅ ችሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መንፈሳዊ ትምህርቱን ለመስጠት ጥረት ቢደረግም የሀገራችን የፖለቲካና የመንግሥት መለዋወጥ በዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ በሚማሩ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ያለመረጋገትና ጫና ፈጥሯል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተማሪዎች በጎሰኝነትና፣ በብሔር በመከፋፈል አንዱ አንዱን ማጥቃት በመበራከቱ የበርካቶች ሕይወት አልፏል፣ እንዲሁም ቆስለዋል፡፡ ለስደትና እንግልት የተዳረጉትም ቁጥራቸው ከፍተኛ ነው፡፡ መደበኛ ትምህርታቸውንም ሆነ መንፈሳዊ ትምህርቱን መከታተል የሚያስችሉ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ብዙዎች ከችግሩ ስፋት አንጻር ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ለመመለስ ተገደዋል፡፡

ይህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ከ፳፻፲2 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘውና የሰውን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ኮቪድ ፲9 (ኮሮና ቫረስ) በመከሠቱ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ሁሉ ተዘግተው ቆይተዋል፡፡ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች በኮቪድ ፲9 ሕመም ለተጠቁ ወገኖቻችን ማገገሚያ እንዲሆኑ ተደርጎ ነበር፡፡

በ፳፻፲፫ ዓ.ም መጀመሪያ ግን ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በማገገሚያ ማእከልነት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት ተቋማቱ መደበኛ ትምህርት እንዲቀጥል ለማድረግ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የኢትያጵያ ጤና ኢንስቲቲዩትና የጤና ሚኒስቴር በሚሰጡት አቅጣጫ መሠረት ዝግጁ የሆኑ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችን ከመስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ጀምሮ መቀበል እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ቅድመ ዝግጅት በማድረግ አንዳንዶቹ ተማሪዎችን ለመቀበል ጥሪ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡና ያለፉት ዓመታት ችግሮች መልሰው እንዳያገረሹ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከተማሪዎች፣ ከአስተዳደር አካላትና ከመንግሥት የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡-

ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ጽንፈኛ የፖለቲካ ማእከላት እንዳይሆኑ መሥራት፡-

ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች የተቋቋሙበት የራሳቸው የሆነ ዓላማ አላቸው፡፡ በሥነ ምግባርና በዕወቀት የታነጸ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት፣ በተሰማራበት የሥራ መስክም ብቁና የኅብረተሰቡን ችግር መፍታት የሚችል፣ ሀገር ወዳድና ወደ ተሻለ የዕድገት ጎዳና መምራት የሚችል ትውልድን የመፍጠር ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ነገር ግን ዩኒቨርስቲዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠሩ አደገኛ የሃይማኖትና የፖለቲካ ጎራዎች ምክንያት ተማሪዎች ጠርዝ የረገጠ ስሜታዊነት ውስጥ ገብተው እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል የረብሻና የግድያ ማእከላት እስከመሆን ደርሰው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዓላማቸውን የሳቱ ግብሮችም ሲፈጸሙባቸው ቆይተዋል፡፡

ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት በመሥራት ዩኒቨርስቲዎችን ለተቋቋሙለት ዓላማ ብቻ በማዋል ብቁ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ተፈጥረው የነበሩ ችግሮችን በመለየት፣ በመወያየት፣ በችግሮቹም ላይ ጥልቅ ጥናቶችን በማድረግ፣ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማቅረብና ወደ ተግባር በመለወጥ ተማሪዎችም ከሥጋት ውስጥ በመውጣት ጤናማ የተምሮ ማስተማር ሂደቱ ሊቀጥል ይገባል፡፡

ከብሔርና ጎሰኝነት የጸዱ ማድረግ፡-

ላለፉት በርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ በመንደር፣ በብሔርና ጎሰኝት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ በሀገሪቱ ላይ ጎልቶ በመታየቱ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ከዚህ ችግር አላመለጡም፡፡ እርስ በእርስ የእኔ እበልጥ የእኔ እበልጥ ሽኩቻ በርካቶች ተጎድተዋል፣ ሕይወታቸውንም አጥተዋል፣ በብሔር ጥላ ሥር በመከለል ኢትዮጵያዊ አንድነትን ዘንግተዋል፡፡

ለተለያዩ ጽንፈኝነት ላይ ያተኮሩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በመጋለጣቸውም በሚያገኙአቸው የተሳሳቱ አመለካከትን ባዘሉ መረጃዎች በመታለል ከትምህርታቸው ይልቅ ሃይማኖትና ብሔር ተኮር እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት የመማር ማስተማሩን ሂደት እንቅፋት እንዲገጥመው አድርገዋል፡፡

እነዚህ ተቋማት በተለያዩ ክልሎች እንደመገኘታቸው ከሌሎች ክልሎች ለሚመጡ ተማሪዎች ስጋት ሲሆኑም ተስተውሏል፡፡ ክልሎች በብሔርና በቋንቋ ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ለብሔርና ጎሰኝነት ልዩ ትኩረት በመስጠት የእልቂት መነሻ ማእከላትም ሆነዋል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ለግቢ ጉባኤያት ሲሰጥ የነበረው መንፈሳዊ ትምህርትም የብሔርና የቋንቋ፣ እንዲሁም አክራሪ የእምነት ተቋማት በሚፈጥሩት ትንኮሳና ጥቃት ምክንያት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡

በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተፈጠሩትን ችግሮች ለማስወገድ በቅድሚያ ሰላምና መረጋገትን ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ከትምህርት ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ ተቋማቱ ድረስ የዘለቀ ውይይት በማድረግ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል ችግር ፈቺ አሠራር መዘርጋት ይገባልና ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ዩኒቨርስቲዎች ከብሔርና ጎሳ እንዲሁም ከአከራሪ የሃይማኖት እንቅስቃሴ ወጥተው የዕውቀት መገብያ ማእከላት ሊሆኑ ይገባል፡፡

በሃይማኖታቸው ምክንያት ተማሪዎችን ከማግለልና ከማሳደድ መቆጠብ፡-

ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በመሆናቸው ብቻ እየተመረጡ የተለያዩ አድሎና ጥቃት ሲፈጸምባቸው የቆየ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ይህ ችግር ድጋሚ አገርሽቶ ወደ ግጭትና ጥቃት እንዳያመራ ሁሉም የበኩሉን በመወጣትና ዩኒቨርሲቲዎችን የሰላምና የአንድነት ተምሳሌት ማድረግ ይጠበቃል፡፡ በተለይም በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች አስተዳደር አካላት በግልጽና በስውር በኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ ከሚያደርሱት የማግለልና የጥላቻ ዘመቻ መሰል ጥቃት መታደግ ያስፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ስለ ልጆቿ መብት ልትከራከርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ልታሰጥ ይገባል፡፡

ለዚህም ተማሪዎች ከተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባሕልና ሃይማኖት ይዘው ወደ ዩኒቨርስቲዎች ስለሚገቡ አንዱ በአንዱ ላይ ጫና ከማድረግ ይልቅ ተግባብቶና ተፋቅሮ ሰላማዊ እንቅስቃሴን በማስፈን ዓላማቸውን ማሳካት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የሃይማኖት ነፃነታቸው ተጠብቆ በሥነ ምግባር የታነጹና ውጤታማ እንዲሆኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መሥራትን ይጠይቃል፡፡

ተማሪዎችን ከሥነ ልቡናዊ ጫና መታደግ፡-

ባለፉት ዓመታት በሀገራችን በተፈጠረው አለመረጋጋት ከተጎዱ አካላት መካከል የዩኒቨርስቲና የኮሌጆች ተማሪዎች ትልቁን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከዚህ ቀደም ወደማያውቁትና አዲስ አካባቢ ሲሄዱ የሚፈጠረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ አዲስ ጓደኛ፣ አዲስ አካባቢ፣ ውጥረት የበዛበት ትምህርት፣ በዚህ ላይ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት በማጣት በሚደርሱ ጥቃቶች የባይተዋርነት ስሜት ስለሚሰማቸው ለሥነ ልቡና ቀውስ ይዳረጋሉ፡፡ ፍርሃትና ሁሉንም የመጠራጠር ስሜት ውስጥ ስለሚገቡ ውጤታማ የመማር ማስተማሩ ሂደት በተጠበቀው መንገድ እንዳይጓዝ እንቅፋት ይሆናል፡፡

ተማሪዎችን ከዚህ የሥነ ልቡና ውጥረትና ጫና ለመታደግ ሰላማዊ አካባቢን መፍጠር፣ ከተማሪዎች ጋር ውይይቶችን ማድረግ፣ በተለይም በባለሙያ የተደገፈ ሥልጠና በመስጠት በራስ መተማመናቸውን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡

ከሚመለከታቸው አካላት ምን ይጠበቃል?

ከመንግሥት፡-

መንግሥት ሀገርን በሰላም የማስተዳደርና የመምራት ኃላፊነት አለበት፡፡ ችግሮች ከመከሠታቸው በፊት የመፍትሔ እርምጃ የመውሰድ፣ ችግሮች ከተፈጠሩም በኋላ በፍጥነት ፍትሓዊ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ እንዳይደገም ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በተለይም በየክልሉ የሚገኙ አንዳንድ የፖሊስና የመከላከያ ኃይላት ከሚወስዱት ያልተገባና ተመጣጣኝ ያልሆነ ወንጀለኛንና ንጹሐኑን ሳይለዩ በጅምላ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ ይገባቸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት እነዚህ ችግሮች ጎልተው የታዩ በመሆኑ አሁንም እንዳይቀጥሉ መንግሥት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ከአስተዳደር አካላት፡-

የዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች አመራር አካላት ችግር ፈቺ እንጂ የችግሩ አባባሽ ከመሆንና በእሳት ላይ ነዳጅ ከመጨመር መታቀብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአንዳንድ ተቋማት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመዘንጋት ተማሪዎችን በጎሳና በብሔር በመከፋፈል ኦርቶዶክስ ጠል የሆኑ አመራሮች በፈጸሙት ችግር በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡

ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲዎች በሚገቡበት ወቅት ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩት ችግሮች እንዳያገረሹ ሁሉንም ተማሪዎች በእኩል ዓይን በማየትና ሚዛናዊ አስተዳደር በማስፈን ሰላማዊ የማመር ማስተማር ሂደትን መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥት የሚመድባቸውን ኃላፊዎች ማንነት በማጥራት የተሻለ አስተዳደር እንዲሰፍን ተግቶ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

ከወላጆች፡-

ወላጆች ልጆቻቸው የግጭት አካል እንዳይሆኑ የመምከር፣ የመገሠጽና ትክክለኛውን ጎዳና የመምራት ኀላፊነት አለባቸው፡፡ ዓላማቸው ትምህርት ብቻ እንደሆነ በማስረዳት ከሁሉም ጋር በሰላም ተግባብተው በመኖር የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ አቅጣጫ ማሳየት ይገባቸዋል፡፡ ልጆች መነሻቸው ቤተሰብ ነውና እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ በሃይማኖታቸው የጸኑ ሆነው እንዲያድጉ ቤተሰብ፣ በተለይም የኦርቶዶክሳውያን ወላጆች ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርስቲዎች ከመላካቸው በፊትም ሆነ በኋላ የመምከር፣ የመከታተል ግዴታ አለባቸው፡፡ ከጽንፈኛ አስተሳሰብ በመውጣት ለሥነ ምግባር ትልቅ ትኩረት እንዲሰጡ ማበረታታት፣ ከነፈሰው ጋር እንዳይነፍሱና በስሜታዊነት እንዳይነዱ በመቆጣጠር የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ከማኅበረ ቅዱሳን፡-

ማኅበረ ቅዱሳን ላለፉት ፳9 ዓመታት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን ሃይማኖታቸውን እንዲያውቁ፣ በሥነ ምግባር ታንጸው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፣ በዕውቀት የበለጸጉ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት ያደጉ እንዲሆኑ መንፈሳዊውን ትምህርት እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡ ይህን አገልግሎቱን በቀጣይነት በማጠናከር፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመስጠት የድርሻውን ሊወጣ ያስፈልጋል፡፡

ብቁ መምህራንን በመመደብ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ሆነው እንዲወጡ፣ ከወጡም በኋላ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ለሌሎች አርአያነታቸውን እንዲያሳዩ በማበረታታት የተሰጠውን ኀላፊነት መወጣት ይገባዋል፡፡

ከተማሪዎች፡-

ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለምን እንደገቡ መረዳት፣ የገቡበትንም ዓላማ ፈጽመው ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን በተማሩበት የትምህርት መስክ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው በመርዳት ያስተማራቸውን ኅብረተሰብ መልሰው የማገልገል ግዴታ አለባቸው፡፡ ዋነኛ ዓላማቸውም ይህ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡

ከውጪም ከውስጥም ለሚነዙ ውዥንብር ለበዛባቸው መረጃዎች ሳይንበረከኩ ከብሔርና ከጎሣ አደገኛ አስተሳሰብ ራሳቸውን በማግለል ሰላማዊ የተምሮ ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ ተማሪዎች ወደ የኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች መመለሳቸው የማይቀር በመሆኑ ሰላማዊ የትምህርት ማእከላት እንዲሆኑ ከጽንፈኛ አስተሳሰብ በመራቅ፣ በዕውቀትና በሥነ ምግባር የታነጸ የተማረ ትውልድ በመፍጠር ረገድ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ይጠበቃል፡፡ ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ ደግሞ ለሀገርና ለወገን የሚቆረቆር፣ ለአንድነትና ለሰላም የሚተጋ ማኅበረሰብ መፍጠር ያስችላልና ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ለዚህም የግቢ ጉባኤያት ድርሻ ከፍተኛ ነውና ከዚህ በፊት ከነበረው አገልግሎት በተሻለ ተጠናክሮ መቅርብ ያስፈልጋል፡፡ የግቢ ጉባኤያት መጠናከር ሀገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለውና በተለይም ቤተ ክርስቲያንና ማኅበረ ቅዱሳን ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላምንና አንድነቱን ያድልልን፡፡ አሜን፡፡