“ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ” (ማቴ. ፭፥፩)
በዲ/ን አበበ ፍቅሬ
የተወደዳችሁ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች መንፈሳዊ ሰላምታዬ ከያላችሁበት ይድረሳችሁና የተራራው ስብከት እንዲሁም አንቀጸ ብፁዓን ተብሎ በሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አምላካችንና መድኃኒታችነ ኢየሱስ ክርስቶስ “ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ” በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ለምን ወደ ተራራ እንደወጣ እንዲሁም ለእኛ ሊያስተምረን የፈለገውን ነገር እንዳስሳለን፤ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን አሜን።
- ጌታችን ወደ ተራራ ወጥቶ የተቀመጠበት ምክንያት
- ተራራ
- የከፍታ ምሳሌ ነው።
ተራራ የልዕልና ምሳሌ ነው፤ አምላካችን “ሰማይኒ መንበርየ ወምድርኒ መከየደ እገርየ፤ ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድር የእግሬ መረገጫ ነው” (ኢሳ. ፷፮፥፩) ብሎ ስለ ልዕልናው ተናገረ እንጂ “አኀዜ ዓለም በእራሁ ኵሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ፤ ዓለምን በመዳፉ የያዘ ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው” እንዲል መጽሐፈ ሰዓታት ልዑለ ልዑላን መሆኑን ሊያስረዳን ነው።
ወደ ተራራ መውጣቱም “እምከመ ተለዓልኩ እምድር እስሕብ ኵሉ ኀቤየ፤ ከምድር ከፍ ከፍ ካልሁ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።” (ዮሐ. ፲፪፥፴፩) ብሎ ከምድር ከፍ ብሎ በመስቀል እንደ ተሰቀለ ለድኅነተ ሰብእ ትሑት ሆኜ ወደ ምድር ብመጣም ልዑለ ባሕርይ ነኝ፤ ልዕልና ልቡና ያላቸው የሚያገኙኝ ነኝ፤ ከትሕትና ወደ ልዕልና የማወጣችሁ እኔ ነኝ፤ ልዕልት ሕገ ወንጌል የሠራሁላችሁ እኔ ነኝ፤ ሲል ወደ ተራራ ወጣ።
“በብዙኅ ነገር ወበብዙኅ ምሳሌ አይድዐ እግዚአብሔር ለአበዊነ እምትካት፤ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ” እንዲል (ዕብ.፩፥፩) የወልደ እግዚአብሔር አምሳል የሆነው ይስሐቅ ይሠዋ ዘንድ እግዚአብሔር ለአብርሃም ሲነግረው “የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞርያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ” (ዘፍ. ፳፪፥፪) በይስሐቅ ዓለም እንዳይድን ያውቃልና ስለሁላችን ኀጢአት በማእከለ ምድር በቀራንዮ አማናዊ የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሠዋልን። (ግብረ ሕማማት ዘሐሙስ ምዕራፍ ፵፫)
- የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነው።
አብርሃም ልጁን ይሠዋ ዘንድ ከእግዚአብሔር ታዝዞ የሄደበት ተራራ “ያህዌ ይርኤ፤ እግዚአብሔር ይታያል” ብሎ ጠራው (ዘፍ. ፳፪፥፲፬) “በዚህ ቤት ለዘለዓለም እኖራለሁ” (፪ኛ ዜና. ፴፫፥፯) እንዳለ በተራራው ላይ እንደሚገኝ ያስረዳናል። መሥዋዕት በቤተ ክርስቲያን እንደሚሠዋ ሁሉ “ያዕቆብም በተራራው ላይ መሥዋዕትን ሠዋ” (ዘፍ. ፴፩፥፶፬) እያለ ይነግረናል። ቤተ ክርስቲያን አማኞች ለአምላካችን የምናቀርበውን የአምልኮ ሥርዓት የምንፈጽምበት ቅዱስ ስፍራ ነው። “ሕዝቡን ከግብፅ በአወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ” (ዘፀ. ፫፥፲፪) ይህም ይታወቅ ዘንድ ሳምራዊቷ ሴት ለጌታችን “አባቶቻችን በዚህ ሰገዱ” አለችው። (ዮሐ. ፬፥፳) ቤተ ክርስቲያንም ማምለጫችን እንደሆነች ሁሉ “ወደ ተራራ ሸሽተህ አምልጥ” እያለ ተራራ ማምለጫ መሆኑን ያስረዳናል። (ዘፍ. ፲፱፥፲፯)
አምላካችን በምድር በተገለጠ ጊዜ ቀን ቀን ሕዝቡን ከአስተማረ በኋላ ማታ ማታ ወደ ደብረ ዘይት ወጥቶ ይጸልይ ነበር። (ማር.፮፥፵፮፤ ሉቃ. ፱፥፳፰) ልክ እንደዚሁ እኛም በግቢ ትምህርታችን ስንማርና ስናጠና ቆይተን በሚገባው ሰዓት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደን ጸሎት መጸለይ፣ መማርና ማገልግል ይኖርብናል።
- የቤተ ጉባኤ ምሳሌ ነው።
“ወይረድ ከመ ጠል ነቢብየ፤ ነገሬ እንደ ጠል ይውረድ” (ዘዳ. ፴፪፥፪) እንዲል ጌታችን ሕግና ሥርዓት ሊያስተምራቸው ወደ ተራራ ይዟቸው ወጣ። (ማቴ. ፭፥፩) በቤተ ክርስቲያናችን መምህሩ ከፍ ብሎ በዐውደ ምሕረቱ ላይ ቆሞ ይሰብካል፤ ተሰባኪው ሕዝብ ከታች ሆኖ ይቀመጣል። በጉባኤ ቤቶችም ብንመለከት መምህሩ ከፍ ባለ ወንበር ተቀምጦ ደቀ መዛሙርቱን ያስተምራል።
እኛ ኦርቶዶክሳውያን ምድራውያን ብቻ ሳንሆን ሰማያውያን፣ ሥጋውያን ብቻ ሳንሆን መንፈሳውያን ነንና የነፍስ ምግቧ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ነውና የእግዚአብሔር ቃል ከሚነገርበት ከግቢ ጉባኤ መርሐ ግብር በመሳተፍ የነፍስ ረኀባችን ልናስታግስና የነፍስ ጥማችን ልንቆርጥ ይገባናል።
ጌታችን አንቀጸ ብፁዓን በተራራ ያስተማረበት ምክንያት
- ለአርአያነት፡-
በቤተ ጉባኤ ተማሩ ሲል፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የምንማረው በዕውቀት ለመራቀቅ ብቻ ሳይሆን ተምረን በሕይወት እንድንለወጠብት ጭምር ነው። እንደ ማንኛውም ትምህርት ዐዋቂ ሆነን እንድንቀር አይደለም፤ ተምረን ተግባራዊ ክርስትና እንድንለማመድ በአምስቱ የስሜት ሕዋሳቶቻችን አማካኝነት በሚገባ መረዳት አለብን። ተግባራዊ ትምህርት ጭምር የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም ሐሳባችሁ በሚሰበሰብበት በቤተ ጉባኤ ተማሩ ሲለን በከፍታ ቦታ አስተማራቸው።
- በቤተ ጉባኤ
- መንፈስ ቅዱስ ይገኛል።
“እስመ ኀበ ሀለው ክልኤቱ ወሠለስቱ ጉቡአነ በስምየ ህየ እሄሉ አነ ማእከሌሆሙ፤ ሁለትም ሦስትም ሆነው በስሜ በሚሰባሰቡበት በመካከለቸው እገኛለሁ” (ማቴ. ፲፰፥፳) እንዲል በስሙ ስለ ስሙ በሚሰበሰቡ ሰዎች በመካከላቸው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ይገኛል። የምንማረው የእግዚአብሔር ቃል ነውና፤ ለሐዋርያት ምሥጢርን የገለጠ ምሥጢር ገላጭ እሱ ነውና (የሐ. ፪፥፩)
በግላችን አንብበን እንረዳዋለን ካልን ደግሞ “ያስተማረኝ ሳይኖር እንዴት አውቀዋለሁ” (የሐ. ፰፥፴፩) እንዳለ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ምሥጢሩን መረዳት አንችልም። ይልቁንም እንደ ፕሮቴስታንቱ ስሑት አረዳድ ውስጥ ሊከተን ይችላል።
- ሐሳባችን ይሰበሰባል።
ለመማር ወደ ቤተ ጉባኤ ስንሄድ ለመንፈሳዊ ትምህርቱ ጊዜ መድበን፣ አእምሯችን አምኖበት ስለሚሄድ ዳግመኛም ተመልሰን ያንን ትምህርት ማግኘት ስለማንችል ወደ ሌላ መርሐ ግብር በመሄድ ሐሳባችን አይከፈልም። ጉባኤው የሚጀመረው በጸሎት በመሆኑ ዕዝነ ልቡናችንም ይሰበሰባል፤ የጉባኤው መሪ መንፈስ ቅዱስ ነውና የሚረብሸን የዓለም ጉዳይ ከእኛ ያርቅልናል።
- በደብረ ሲና ሕገ ኦሪት የሠራሁላችሁ እኔ ነኝ ሲል፣
በብሉይ ኪዳን (ዘፀ. ፲፱፥፫) ላይ ሙሴ ወደ ተራራ ወጥቶ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገረ፤ እንዲሁም በዚህ ተራራ እግዚአብሔር ለሙሴ ሕጉና የቃል ኪዳኑን ታቦት ሰጠው። (ዘፀ. ፳፣ ዘፀ፣፳፭)
በኦሪቱ በተራራ ለሙሴ ሕገ ኦሪት የሰጠሁት፤ ዛሬ ሰው ሆኜ ሕገ ኦሪትን አጽንቼና ፍጹም አድርጌ አማናዊት የሐዲስ ኪዳን ሕግ የምሰጣችሁ እኔ ነኝ ሲል ነው።
- በግቢ ጉባኤ የኮርስ መጻሕፍትን በተመደበላችሁ መምህራን ባትማሩ (በኦንላይን እንማራለን ብትሉ) ብዙ ትሩፋቶች ታጣላችሁ።
ቅዱስ ሲኖዶስ ለማኅበረ ቅዱሳን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ወጣቶች ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ እንዲያስተምር ኀላፊነት ሲሰጠው መሠረታዊ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት በአግባቡ እንዲከታተሉ በትምህርቱ ዘርፍ ልሂቃን መድቦ ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ በየጊዜው እየከለሰ በሚመጥናቸው መልክ አዘጋጅቶ እያስተማረ ይገኛል።
በአሁኑ ሰዓትም ፲፫ የኮርስ መጻሕፍትን ለመማሪያነት ያገለግል ዘንድ አዘጋጅቶ በቅደም ተከተል አሰናድቶ የግቢ ቆይታቸው እስኪያጠናቅቁ ድረስ ያስተምራቸዋል።
ዲጂታል ዓለም መረጃ ለሁሉም ሰው ተደራሽ እንዲሆን የማድረግ በጎ ዕድል ቢኖረውም መረጃ ማግኘት መሠረታዊ ትምህርት መከታተል ለሚመስላቸው ወጣቶች ይዞ ብቅ ያለው ተግዳሮት ደግሞ ቀላል አይደለም። የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በተቀመጠላችሁ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ባትማሩ በጥቅሉ ከታች የተዘረዘሩ ነጥቦችን ልታጡ ትችላላችሁ።
- ስለ አንድ ኮርስ ሙሉ ሐሳብ መረዳት አትችሉም።
- በጉባኤ ከሚገኘው በረከት መሳተፍ አትችሉም።
- የሚከብዳችሁን ጥያቄ ጠይቃችሁ በአግባቡ መረዳት አትችሉም።
አንዳንዶች ባለመገንዘብ በኦንላይን መማር እንችላለን ይላሉ። ነገር ግን የኦንላይን ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት መርሐ ግብር ተይዞለት ስታንዳርድ ወጥቶለት በተቋም ተገምግሞ የሆነ አይደለም የሆነ ግለሰብ በግል ተነሳሽነት የሠራው ያልተገመገመ ብዙም ተጠየቅ የሌለበት በመሆኑ ውጤታማነቱ ብዙ አይደለም። በሌላ በኩል የኦንላይን ትምህርት ለመከታተል እንኳ ብናስብ መርሐ ግብሩ የግላችን ስለሆነ በጥቃቅን ጉዳዮች እንኳ እናጠፋዋለን፤ የኦንላይን ትምህርት በጣም ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘም የሚያገለግለው የተማሩትን እንዳይረሱት ለመከለስ ነው።
በመሆኑም ውድ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ሆይ የሚጠበቅባችሁን ፍሬ በተገቢው ሁኔታ እንድታፈሩ ኮትኩቶ ለሚያሳድጋችሁ ለግቢ ጉባኤ ሐሳባችሁን፣ ጊዜያችሁን እንዲሁም ውድ ፈቃዳችሁን በመስጠት ያዘጋጀላችሁን የሕይወት መብል በሥርዓት እንድትመገቡ ይሁን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!