ትንሣኤ ሥጋሃ ለእግዝእትነ ቅድስት ድንግል ማርያም
ከመምህር ተስፋማርያም ክንዴ
ሐዋርያት በአንድነት ሁነው ትንሣኤዋን ያዩበትን ዕለት እኛም ሁልጊዜ እናከብር ዘንድ ተአምረ ማርያም ከነሐሴ ፲፮ እስከ ፳፩ ቀን ድረስ እንደ ልጇ ትንሣኤ አድርገው ያክብሩ ብሎ አዞናል። (የተአምረ ማርያም መቅድም)
ይህም በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ፴፫ቱ የእመቤታችን በዓላት አንዱ ሁኖ ይከበራል። ለዚህ መነሻ ይሆነን ዘንድ ወደ ጥንት ታሪኩ ተመልሰን የእመቤታችንን ጉዳይ ስናነሣ ወደ ትንሣኤዋ ከመድረሳችን በፊት ወደ ድኅነት መንገድ አድርሶ ይመልሰናል። “እግዝእትነ ማርያም እምቅድመ ዓለም ነበረት በኅሊና አምላክ፤ እመቤታችን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር” እንዲል ተአምረ ማርያም እመቤታችን ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር። እመቤታችን ቅድመ ዓለም የታሰበችው የሰው ልጅ ድኅነት ቅድመ ዓለም ስለታሰበ ያ ድኅነት በኋላ በጊዜው ጊዜ የሚከናወንባት ስለሆነች ነው። ድኅነት ቅድመ ዓለም መታሰቡን መጻሕፍት ይነግሩናል። ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘለዓለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህን ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለእኔ ተሰጠ” እያለ ገልጧል። (ኤፌ. ፫፥፰-፱)
ቅድመ ዓለም በአምላክ ኅሊና የነበረች እመቤታችን በኋላ አዳም ሲፈጠር በአዳም ባሕርይ ውስጥ ነበረች። “ማርያምሰ ተሐቱ እምትካት ውስተ ከርሡ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ፤ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራ ነበር” እንዳለ ቅዱስ ያሬድ በድጓው
“አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንች ነሽ” እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም አዳም ሲሰደድ በመትከፈ ልቡ(በኅሊናው) ይዟት የወጣ አለኝታ ስንቁ ድንግል ማርያም ናት።
ይህች ንጽሕት ዘር ጥንተ አብሶ (የውርስ ኃጢአት) ሳይኖርባት ከአዳም ጀምሮ ባሉት ቅዱሳን አበው አብራክ ተጠብቃ መጥታ በንጽሕና በቅድስና ከሐናና ከኢያቄም ተወልዳለች።
በተወለደች በ፫ ዓመቷ ቤተ መቅደስ ገብታለች። በቤተ መቅደስ መላእክት እያረጋጓት ኅብስት ሰማያዊ ጽዋ ሰማያዊ እየተመገበች ፲፪ ዓመት ኑራለች። ለዚህም ሊቁ “ኦ ድንግል አኮ ኅብስተ ምድራዌ ዘተሴሰይኪ አላ ኅብስተ ሰማያዌ እምሰማየ ሰማያት ዘበሰለ ኦ ድንግል አኮ ስቴ ምድራዌ ዘሰተይኪ አላ ስቴ ሰማያዌ እምሰማየ ሰማያት ዘተቀድሓ እንዲል፤ ድንግል ሆይ ምድራዊ የሆነ ምግብን የተመገብሽ አይደለም ሰማያዊ ምግብን ነው እንጂ፣ ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም ከሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን ነው እንጂ” ብሎ በቅዳሴው አመስግኗታል።
ከእናት አባቷ ጋር የኖረችው ፫ ዓመት ሲደመር በቤተ መቅደስ የኖረችው ፲፪ ዓመት አጠቃላይ ፲፭ ዓመት ይሆናል። በ፲፭ ዓመቷ አይሁድ ከቤተ መቅደስ በቅናት ስላስወጧት ወደ ዮሴፍ ቤት ሄዳ በዚያ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ጌታን ፀንሳ በ፱ ወር ከ፭ ቀን የበኵር ልጇን ወልዳለች።
ከዚያም ጌታችን ወደዚህ ምድር የመጣበትን ዓላማ እስከሚፈጽም ድረስ ከእሱ ጋር ፴፫ዓመት ከ፫ ወር ኑራለች። የፀነሰችበት ፱ወር ከ፭ ቀን እና ከጌታ ጋር የነበረችበት ፴፫ ዓመት ከ፫ ወር በአንድ ላይ ፵፱ ዓመት ይሆናል።
በኋላም ጌታ በመስቀል ላይ ሆኖ ይወደው ለነበረው ደቀ መዝሙር ለዮሐንስ ወንጌላዊ እናት ትሆነው ዘንድ በእርሱም ለእኛ ሁሉ እናት እንድትሆነን ስለሰጠው ከእርሱ ጋር ፲፭ ዓመት ኑራለች። (ዮሐ. ፲፱፥፳፮) መላው የእመቤታችን ዕድሜ ፷፬ ዓመት ነው። የእመቤታችን ፍቅር የበዛላቸው አባቶቻችንም በዕድሜዋ ልክ ስሟን እየጠሩ አመስግነዋታል። ለምሳሌ የመልክአ ማርያም ቁጥር ፷፬ ነው፤ ቅዱስ ኤፍሬምም ጸሎተ እግዝእትነ ማርምን ይደግም የነበረ በዕድሜዋ ልክ ፷፬ ጊዜ ነበር።
እመቤታችን በተወለደች በ፷፬ ዓመቷ በ፵፱ ዓ.ም በዘመነ ማቴዎስ ጥር ፳፩ እሑድ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም አርፋለች። “ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የቅዱሳን ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው” እንዳለ ክቡር ዳዊት (መዝ. ፻፲፭፥፲፭) የጻድቃን መመኪያቸው የእመቤታችንም ሞት ጻዕር የበዛበት ሳይሆን በደስታ በእልልታ በይባቤ መላእክት እንደሆነ መጻሕፍት ይነግሩናል። “ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ፣ እንዘ ይዜምሩ በቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ፣ ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ፤ ማርያም ሆይ ሞትሽ ሰርግ ይመስላል፤ ምክንያቱም የራሳቸው ክብርና ዝና የማያስጨንቃቸው ብዙ የሆኑ የሰማያውያን ጭፍራ መላእክት በፊትሽም በኋላሽም የሚዘምሩ ናቸውና።” እንዳለ አርኬ ጥር ፳፩ ስንክሳር።
ባረፈችም ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት አስከሬኗን ይዘው ወደ ጌቴሴማኒ መቃብር ለማሳረፍ ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና “ቀድሞ ከዚች የተወለደውን ሞተ፤ ተነሣ፤ ዐረገ፤ እያሉ ዓለሙን ሲያውኩት ኖሩ፤ ደግሞ ዛሬ ይችን ሞተች፤ ተነሣች፤ ዐረገች፤ እያሉ ይህን ዓለም ሲያውኩት ሊኖሩ አይደለምን? ንዑ ናውዕያ በእሳት፤ ኑ በእሳት እናቃጥላት” ብለው ሲመጡ የእግዚአብሔር መልአክ እሳተ መለኮትን በመሸከም የከበረውን የእመቤታችንን ሥጋ ከዮሐንስ ጋር ነጥቆ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀምጧታል።
በገነት ዕፀ በለስ፣ ለአዳም ምግብነት የተሰጡ ዕፀዋት እንዲሁም ብላም አትብላም ያልተባለችው ዕፀ ሕይወት ይገኛሉ። ለዚህም ምስክሩ አዳም በኃጢአት ሳለ ዕፀ ሕይወትን ቢበላ የማይሞት ምውት ይሆን ነበርና እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነት ሞት እንዳያገኘው በቸርነቱ ከዚች ዕፅ እንዳይበላ ገነትን በምትገለባበጥ ሰይፍ አስጠብቋት ነበር። “ወአዘዞሙ ለሱራፌል ወኪሩቤል ከመ ይዕቀቡ ፍና ዕፀ ሕይወት … ከመ ኢይባእ አዳም ተሀቢሎ ውስተ ገነት፤ አዳም ተደፋፍሮ ወደገነት እንዳይገባ ሱራፌልና ኪሩቤልን የገነት መግቢያ በርን ይጠብቁ ዘንድ አዘዛቸው።” እንዲል (የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ ዘፍ. ፫፥፳፬)
የእመቤታችንን ሥጋ በዕፀ ሕይወት ሥር ማስቀመጡም ዕፀ ሕይወት ምሳሌዋ ስለሆነች ነው። ያች ሕይወትን እንደምትሰጥ እመቤታችንም ሕይወት የሚሰጠውን ክርስቶስን ወልዳ ለዓለም ምክንያተ ድኅነት ስለሆነች ነው። “ከፈለነ ንብላዕ እምዕፀ ሕይወት ዘውእቱ ሥጋሁ ለክርስቶስ ወደሙ ክቡር፤ ዳግመኛም ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን፤ ይኸውም ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ የተወለደው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ ነው” ብሎ ቅዱስ ኤፍሬም በግልጽ ቋንቋ አስቀመጠው። (የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ)
በሕይወት ዘመኗ ያገለገላት ዮሐንስ ከሞተችም በኋላ በገነት የከበረ ሥጋዋን በማዕጠንት እያጠነ አገልግሏታል። “ዮሐንስም መጥቶ ወንድሞቹ ሐዋርያትን እመቤታችን እንጂ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አለች አላቸው” ሐዋርያትም “እንዴት ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ እንቀራለን?” ብለው በነሐሴ ሱባኤ ገቡ። በዚያን ጊዜ ነሐሴ በጥር ብተት (ጥር በባተበት) ሰኞ ይብታል ከሰኞ እስከ ሰኞ ፰ ከሰኞ እስከ ሰኞ ፲፭ አንዱን ቀን ታግሦ በ፲፬ እሑድ አምጥቶ ሰጥቷቸው ዕለቱን ቀብረዋታል። በሦስተኛው ቀን ተነሥታለች። “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ የማርያም ትንሣኤ እንደ ልጇ ትንሣኤ ነው’’ ያሰኘው ቅሉ እንደ ክርስቶስ ትንሣኤ ዳግም ሞት የሌለበት ፍጹም ትንሣኤ መነሣቷ ነው። ይህም መሆኑን የሚታወቀውአሁን በመንግሥተ ሰማያት መሆኗ ነው።
አንድም ከመ ትንሣኤ ወልዳ ያሰኘው ቅሉ የክርስቶስ ትንሣኤ ለሙታን ሁሉ ትንሣኤ መሠረት እንደሆነ ሁሉ፣ በልጇ በወዳጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ኃይል በፍጹም ትንሣኤ ማለትም ዳግመኛ ሞት በሌለበት ትንሣኤ መነሣቷ ከሰዎች ሁሉ የመጀመሪያዋ በመሆኗ በዕለተ ምጽአት ለምንነሣው ትንሣኤ ተስፋ የሚሰጥ በመሆኑ ነው። ከሁሉም እመቤታችን ትቀርበናለችና።
ታሪኩም እንዲህ ነው። ከላይ እንዳልነው እመቤታችን ስታርግ ሐዋርያው ቶማስ ሀገረ ስብከቱ ህንደኬ ነበርና ከዚያ ሲያስተምር ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ሲመለስ አገኛት። “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ፤ ተበጻብጾ ከደመናው ሊወድቅ ወደደ” ይላል፤ እመቤታችንም “አይዞህ ይህን ዕርገቴን ያየህ አንተ ነህ፤ ሌሎች ሐዋርያት አላዩም” ብላ ሰበኗን ሰጥታ ሰደዋለች። ይህንን ይዞ ሄዶ ለሐዋርያት ነግሯቸው ሐዋርያትም ሰበኗን ለበረከት ተከፋፍለው ወስደው ድውይ ሲፈውሱበት ሙት ሲያስነሡበት ኑረዋል።
ሐዋርያትም መንፈሳዊ ቅናት አደረባቸውና “ቶማስ አይቶ እንዴት እኛ ሳናይ እንቀራለን” ብለው በዓመቱ በ ፶ ዓ.ም በዘመነ ማርቆስ ዜና ትንሣኤዋን በዐይናቸው ለማየት እንደገና በነሐሴ ወር ሱባኤ ጀመሩ። በነሐሴ ፲፮ ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በክብር ተገልጦ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቆርቦ አቁርቧቸዋል። (ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ የዲማ አብነት)
“ትእምርተ ፍልሰትኪ እምድረ ጽጌ ኦ ድንግል በክልኤ፣ ድንግል ሆይ የአበባ ምድር ከሆነችው (ከምድረ ገነት) የፍልሰትሽ ምልክት በሁለት መልኩ ታየ፤ በደመና ሰማይ አርአየ ዘሐዋርያት ጉባኤ፣ የሐዋርያት ጉባኤም በሰማይ ደመና ተሰብስቦ ታየ፤ ወእለ ሞቱ አንቅሐ እምከርሠ መቃብር ቀርነ ጽዋዔ፣ የመለከት ድምፅ እንደተነፋባቸው ሁሉ ከዚህ በፊት ሞተው የነበሩትን ከከርሠ መቃብር ቀሰቀሳቸው፤ ለነሰ እስከ ይብሉ ሶበ ሰማእነ ውዋዔ መሰለነ ዘበጽሐ ትንሣኤ፣ እኛንስ ድምፁን ጩኸቱን በሰማን ጊዜ የትንሣኤ ሰዓት (ዕለተ ምጽአት) የደረሰ መሰለን። እያለ አባ ጽጌ ድንግል በሰቆቃወ ድንግል ዜና ትንሣኤዋን አመሥጥሮታል።
የበዓሉ ታላቅነት የሚታወቀው አባቶቻችን ከነሐሴ ፲፮ ጀምረው እስከ ፳፩ ቀን ድረስ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ በዓል አድርገን እናከብር ዘንድ በተአምረ ማርያም መቅድም ላይ ማዘዛቸው ነው። ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን “በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ሐዋርያትን እዘዣቸው” አላት፡፡ ጌታም እናቱ ድንግል ማርያምን በዚች ቀን መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ቅዱስ ቁርባን የሚቀበለውን ሁሉ ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ፡፡ የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም፤ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውትም ቸርነቴ ትጎበኘዋለች›› ብሎ ቃል ኪዳን ሰጥቷት ተመልሷል።
የክርስቲያን ወገኖች ሆይ! እኛም ሁላችን በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡ እርሷ ስለ እኛ ወደ ተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና። ልመነዋ ክብሯ የልጅዋም ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!