“ታቦር ወአርሞንኤም በስመዚአከ ይትፌሥሑ፤ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል”(መዝ. ፹፰፥፲፪)
ከመ/ር ተፈሪ መንገሻ
ውድ የድረገጻችን ተከታታዮችእንኳን ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ለገለጠበት የደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
በመጸሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት ተራሮች ሁሉ የየራሳቸው መገለጫ አላቸው። ሕግ ሲሰጥ የሲና ተራራ ተንቀጠቀጠ። የሞሪያ ተራራ ይስሐቅ የታሰረበትን እንጨትና የድንጋይ መሠዊያ ተሸከመ፤ ከዘመናት በኋላም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ተሸከመ። የጎልጎታ ተራራ መስቀሉን ተሸከመ፤ ጨለመ፤ በሐዘንም አለቶቹ ተሰነጠቁ። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት ተራሮች ሁሉ፣ መዝሙረኛው ለየት ያለና አስደሳች ክብርን የሰጠው ለአንዱ ብቻ ነው፦ በመንቀጥቀጡ አይደለም፣ በማዘኑም አይደለም — ነገር ግን ሐሴት በማድረጉ (በመደሰቱ) ነው። በእግዚአብሔር ስም በደስታ ይዘልላሉ (ሐሴት ያደርጋሉ)። ይህም የታቦር ተራራ ነው። የታቦር ተራራ ምንድ ነው? ለምንስ ደስ ይለዋል?
፩. ታቦር ምንድን ነው?
የታቦር ተራራ በገሊላ ከሚገኘው የኢይዝራኤል ሜዳ ላይ ብቻውን ብቅ ብሎ ይታያል። ልክ ምድር ለንጉሥዋ ዙፋን ያዘጋጀች እስኪመስል ድረስ ርቀው ለሚገኙ ሁሉ የሚታይ አረንጓዴና ጉብታና ያለው ተራራ ነው። በዘመነ መሳፍንት የጭንቀትና የእምነት ስፍራ ነበረ፦ ነቢይቷ ዲቦራ ባርቅን በዐሥር ሺህ ሠራዊት ከሲሳራ የብረት ሠረገላዎች ጋር እንዲዋጋ ወደዚያ ጠርታዋለች፤ ጌታም እስራኤልን በሰይፍ ሳይሆን በራሱ እጅ ድልን አቀዳጅቷቸዋል (መሳ. ፬፥፮–፲፭)
ከዘመናት በኋላ ደግሞ ነቢዩ ሆሴዕ ታቦር “ወጥመድ”፣ ሕዝቡ በአምልኮ የሳተበት የኮረብታ መስገጃ እንደሆነ በማዘን ተናግሯል። (ሆሴ. ፭፥፩)
እንዲሁም ኤርምያስ አሁንም እግዚአብሔር ስለሰጠው ግርማ በመመስከር፣ የሚመጣውን ንጉሥ ታላቅነት “በተራሮች መካከል እንዳለ እንደ ታቦር” በማለት መስሎታል። (ኤር. ፵፮፥፲፰)
እንግዲህ፣ ይህ ተራራ ድልንም ውርደትንም፣ ታማኝነትንም ጣዖት አምልኮንም ያየ ተራራ ነው።
ክርስቶስም “ከስድስት ቀን በኋላ” (ማቴ. ፲፯፥፩) ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ፣ ፍጥረተ ዓለም ጀምሮ ማንም ዓይን አይቶት የማያውቀውን ክብር ሊገልጥበት የመረጠው ልክ ይሄንኑ ተራራ ነው።
ጴጥሮስ ከጥቂት ቀናት በፊት በፊልጶስ ቂሣርያ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ በአፉ የመሰከረው እዚያው አካባቢ ነበርና (ማቴ. ፲፮፥፲፮) በቂሣሪያ በእምነት የተደረገ ምስክርነት ነበር፤ በታቦር ደግሞ በማየት የተደረገ ምስክርነት ሆነ። ጴጥሮስ በሸለቆው ውስጥ በከንፈሩ ያወጀው ምስክርነት ክርስቶስ በተራራው ላይ ሊያረጋግጥና ስለ እርሱ ፍጹም እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ ፈቃዱ ነውና።
፪. ታቦር ለምን ሐሴት አደረገ?
ሀ). የጌታ መለኮታዊ ባሕርይ በዚያ ስለተገለጠ
“በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ።” (ማቴ.፲፯፥፪)
ክርስቶስ ይህንን ክብር በታቦር ተራራ ላይ አዲስ የተቀበለው አልነበረም። “በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር… ራሱን ባዶ አደረገ፣ የባሪያንም መልክ ያዘ” (ፊልጵስዩስ ፪፥፮–፯) የተባለለት እርሱ፣ በበረት ከተወለደበት ዕለት ጀምሮ ክብሩን በሥጋዌው ትሕትና ውስጥ ሰውሮት ነበር። በታቦር ላይ ግን፣ ለጥቂት ጊዜያት ያህል መጋረጃው ተገለጠ። መለኮትነቱ ከዚያ በፊት ስለሌለ ሳይሆን፣ “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና” (ቆላስይስ ፪፥፱) አሁን ያ ሙላት እንደ ማለዳ ፀሐይ ከተራሮች አናት ፈነጠቀ።
ይህንን ከሙሴ ጋር እናነጻጽር፣ የሙሴም ፊት አብርቶ ነበርና፤ በሲና ተራራ ከእግዚአብሔር ጋር ከተነጋገረ በኋላ የተቀበለውና ያንጸባረቀው ብርሃን ነበር፤ ሕዝቡም ሊመለከቱት ስላልቻሉ መጋረጃ ማድረግ አስፈልጎት ነበር። (ዘጸ. ፴፬፥፳፱–፴፭፤ ፪ኛ ቆሮ. ፫፥፯)
የክርስቶስ የደብረ ታቦር ብርሃን ግን ከሌላ የተንጸባረቀ አይደለም፤ የእርሱ የባህሪው ነው እንጂ።
“ክብሩም ከአባት ዘንድ እንዳለው ለአንድ ልጅ እንደሚገባ ያለ ክብር” (ዮሐ. ፩፥፲፬)፣ እርሱ ለዘላለም የሚኖርበት የማይጠፋና ያልተፈጠረ ብርሃን ነው። (፩ኛ ጢሞ. ፮፥፲፮) ሙሴ ያበራው እግዚአብሔርን ስላየ ነው። ክርስቶስ ያበራው ግን ራሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ነው።
ለ). ምሥጢረ ሥላሴ ስለተገለጠ
“እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።” (ማቴ. ፲፯፥፭)
በዚህ ተራራ ላይ፣ እግዚአብሔር በአንድነቱ ውስጥ ያለውን ልዩ ሦስትነቱን በአንድ ቅጽበት ራሱን ገለጠ፦ ወልድ በሚታይ ክብር ተለወጠ፤ አብ ምስክርነቱን ከሰማይ በድምፅ አሰማ፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በጋረዳቸው “ብሩህ ደመና” ውስጥ ተገኘ። “ጋረዳቸው” የሚለው ቃል ድንገተኛ አይደለም ለድንግል ማርያም “የልዑል ኃይል ይጸልልሻል” (ሉቃ. ፩፥፴፭) ከተባለው ቃል ጋር አንድ ነው። የዚያን ጊዜ ለቃል ሥጋን ከፍሎ ለማዋሐድ በማርያም ማሕፀን ላይ ያረፈው (የጸለለው) ያው መንፈስ ቅዱስ አሁን ደግሞ የዚያን የሥግው ቃልን ክብር ለመግለጥ በተራራው ላይ ጋረደ (ጸለለ)።
ይህ በታቦር የተፈጸመ ሁለተኛው ታላቅ የምሥጢረ ሥላሴ መገለጥ ሲሆን፣ በዮርዳኖስ የተፈጸመው መገለጥ የሚያጸና ነው። በዮርዳኖስ ወልድ በውኃ ውስጥ ቆሞ፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ ወርዶ፣ የአብ ድምፅም “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” (ማቴ. ፫፥፲፮–፲፯) ብሎ ተናግሮ ነበር። ከጥምቀት በኋላ አገልግሎቱን ጀመረ፤ በታቦር ደግሞ ወደ መስቀል ከማምራቱ በፊት ተገለጠ።
3. ሰማያውያንና ምድራውያን በዚያ ስለ ተዋሐዱ
በታቦር ላይ፣ በሦስት የፍጥረት ዓለማት የሚገገኙ አካላት በአንድነት ቆመው ነበር። ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ሟች የሆነውን ሥጋ ለብሰው በሕይወተ ሥጋ በዚያ ቆመው ነበር። ይኸውም ገና በምድር ላይ የምትጓዘውን ቤተ ክርስቲያን ይወክላል። ሙሴ በነፍስ ሆኖ በዚያ ቆሞ ነበር፤ ምክንያቱም በናባው ተራራ ሞቶ፣ ዓለም አካላቸውን እንደ አፈር ቢቆጥረውም ለእግዚአብሔር ግን ሕያዋን የሆኑ ናቸውና በአጸደ ነፍስ ያሉትን ወክሎ፣ እስከ ዛሬ ድረስ መቃብሩን ማንም በማያውቀው ስፍራ በመላእክት እጅ ተቀብሮ ነበር። ኤልያስ ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ በዚያ ተገኘ፤ ምክንያቱም ሞትን አልቀመሰም፣ ነገርግን በእሳት ሰረገላ “በአውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ” አርጓልና (፪ኛ ነገ. ፪፥፲፩) ይኸውም የሞትን እንቅልፍ ሳያንቀላፉ ጌታን የሚጠባበቁትን ይወክላል።
ሕያዋን፣ ሞተው ነገር ግን ሕያው የሆኑት፣ እና ሳይሞቱ የተወሰዱት ሁሉም በአንዱ ክርስቶስ እግር ሥር ተሰበሰቡ፣ እርሱ “የሙታንም የሕያዋንም ጌታ” ነውና (ሮሜ. ፲፬፥፱)
ሕግ ሰጪው ሙሴና ነቢዩ ኤልያስ፣ ስለ ክርስቶስ የተጻፈው ሁሉ መፈጸሙን ለመመስከር በዚያ ቆመው ነበር፤ እርሱም ሕግንና ነቢያትን ሊፈጽም እንጂ ሊሽር አልመጣምና (ማቴ. ፭፥፲፯) ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ስለ ምን ይነጋገሩ እንደነበር ይነግረናል፦
“በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለ ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር” (ሉቃ. ፱፥፴፩)
በዚህ የሚያስደነግጥና ታላቅ የክብር መገለጥ በታየበት ሰዓት እንኳ፣ ነገረ መስቀሉ በዚያ ይነገር ነበር፤ ክብርና መከራ እንደ አንድ የማይነጣጠል ቀሚስ ተስማምተው ተሠርተዋልና።
4. ትሕትና በዚያ ስለተገለጠ
በዚህ ተራራ ላይ ሁለት ትሕትናዎች ይገናኛሉ። አንደኛው የጌታ ትሕትና ነው፦ ክብሩን ተራራ ላይ ላሉ ለሦስት ምስክሮች ካሳየ በኋላ፣ “የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” (ማቴ. 17፥9) ብሎ አዘዛቸው። ዓለምን ሁሉ ጠርቶ ክብሩን ሊያሳያቸው ይችል የነበረው እርሱ፣ የራሱን ክብር ሳይሆን የኛን ድኅነት ፈልጎ ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ መከዳት፣ ወደ መስቀል ወደ ሞት መለሰ።
ሁለተኛው የጴጥሮስ ትሕትና ነው። በግርምት ተውጦ “ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ” ብሎ ጮኸ (ማቴ. ፲፯፥፬) እዚህ ላይ ለራሱ ምንም ማደሪያ አልጠየቀም። በቂሣሪያ በድፍረት ስለ ክርስቶስ የመሰከረው ያው ጴጥሮስ፣ አሁን ግን በታቦር ጫፍ ላይ ምን እንደሚል አላወቀም፤ “እጅግ ፈርተው ነበርና” (ማር. ፱፥፮) ለኛም ክብሩ በሚገለጥባት በቤ/ክ መኖር መልካም ነው።
ሐ). የቡሄ በዓል የአከባበር ትውፊት፦ ችቦና ጅራፍ
ቤተ ክርስቲያን ይህንን የታቦርን ምሥጢር በመጽሐፍ ገጾች መካከል ቆልፋ አታስቀምጠውም፤ ከዓመት ወደ ዓመት በሚነድ እሳት፣ በዝማሬ፣ በእያንዳንዱ መንደር ጎዳናዎች ላይ ሕያው አድርጋ ይዛው ኖራለች።
ችቦ
የዚህ በዓል ምሽት ሲቃረብ፣ ችቦ ታስሮ ይለኮሳል፤ ልጆችም “ሆያ ሆዬ” እያሉ በመጫወት፣ ሽማግሌዎቻቸውን በማመስገንና ለመጪው ዓመት በረከትን በመጠየቅ በየሰፈሩ ይዞራሉ። ይህ እሳት ደቀ መዛሙርቱ ላዩት ነገር ሕያው አምሳያ ነው፦ “ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ” (ማቴ. ፲፯፥፪) በተጨማሪም ከተራራው ብርሃን የተነሣ ንጋት መስሏቸው በዚያች ሌሊት ሲጠብቁ የነበሩትን እረኞች፣ ልጆቻቸውን በጨለማ ለመፈለግ ችቦ እያበሩ ሙልሙል ይዘው የወጡትን እናቶች ያስታውሳል። በዚህ በዓል ላይ ችቦ የሚያነሣ እያንዳንዱ ልጅ፣ ሳያውቀው፣ በአንድ ወቅት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ለተገለጠላቸው ለዚያ ብርሃነ መለኮት ትንሹ ምስክርነት ይሆናል።
የጅራፍ ጩኸት
በቀን ደግሞ፣ ወጣቶች አየሩን ሰንጥቀው ጅራፍ ያስጮሃሉ፤ ድምፁም እንደ ሩቅ ነጎድጓድ ያስተጋባል ይህ እንዲሁ ልማድ ብቻ ሳይሆን በልብ ውስጥ የሚቀመጥ ትዝታ ነው። “እነሆ ከደመናው ድምፅ መጣ… ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈሩ” (ማቴ. ፲፯፥፭–፮) ይህ ድምፅ ሕግ ሲሰጥ ሲናን እንዳናወጠው ነጎድጓድ የሚያስፈራ ነው (ዘጸ. ፲፱፥፲፮) ምክንያቱም “የእግዚአብሔር ድምፅ በኃይል ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅ በግርማ ነው” እንዲል (መዝ. ፳፱፥፬) ይህ የጅራፍ ጩኸት በነጎድጓድ ድምፅ የተገለጠውን የጌታችንን ክብር ስናስታውስ በሞቱ ዕለት በዕለተ ዓርብ ጌታ የሚገረፍበትን ጅራፍ ያስታወስናል። በደብረ ታቦር የቀራንዮ ውሎ ተነግሮባታልና።
ስለዚህ በበዓል አከባበር ውስጥ እንኳን፣ ቤተ ክርስቲያን ከታቦር የሚነሣው መንገድ በመጨረሻ ወደ ጎልጎታ እንደሚያመራ አትዘነጋም።
4. ይህ ለእኛ ለምን ተሰጠ?
1. ሐዋርያትን ለመስቀል መከራ ለማዘጋጀት
ከጥቂት ቀናት በፊት ክርስቶስ ብዙ መከራ ሊቀበልና ሊገደል እንደሚገባው ለደቀ መዛሙርቱ በግልጽ ነግሯቸው ነበር (ማቴ. ፲፮፥፳፩)፤ ጴጥሮስም ይህንን መሸከም አቅቶት ገሥጾት ነበር። የታቦር ክብር የበራው ልክ በዚህ የእምነት ጭንቀት ውስጥ ነበር። አባቶች ከጥንት ጀምሮ እንደሚያስተምሩት፣ ክርስቶስ ክብሩን ለጴጥሮስ፣ ለያዕቆብና ለዮሐንስ አስቀድሞ ያሳያቸው፤ በኋላ ተይዞ፣ ተተፍቶበት፣ በእንጨት ላይ ተቸንክሮ ሲያዩት፣ የገዛ ዓይኖቻቸው በተራራው ላይ ያዩትን አስታውሰው ተስፋ እንዳይቆርጡ ነው። መስቀሉ ክብሩን መሻሪያ ሳይሆን፣ ወደዚያው ክብር የሚያደርስ መንገድ መሆኑን እንዲያውቁ ነው።
2. ገና ለሚመጣው መንግሥት ቅምሻ (መያዣ/አረቦን)
ከዚህ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ጌታ እንዲህ ብሎ ቃል ገብቶ ነበር፦ “የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ” (ማቴ. ፲፮፥፳፱) ከስድስት ቀናት በኋላም ያ ቃል ኪዳን በታቦር ላይ መፈጸም ጀመረ። ከዓመታት በኋላ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለዚያ ቀን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል… ከእርሱ ጋር በቅዱሱ ተራራ ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን” (፪ኛ ጴጥሮስ ፩፥፲፮–፲፰) ያየው ነገር ለእርሱ “እጅግ የጸና የትንቢት ቃል” ሆነለት ይህም የተዋረደው ሥጋችን “ክቡር ሥጋውን እንዲመስል” በሚለወጥበት ጊዜ (ፊልጵስዩስ ፫፥፳፩)፣ እኛም አንድ ቀን “እርሱ እንዳለ እናየዋለን” (፩ኛ ዮሐ. ፫፥፪) ለሚለው ለእያንዳንዱ አማኝ የተሰጠ ተስፋ ነው።
3. ለሁላችን በክብር ስለ መለወጥ የተደረገ ጥሪ
ቅዱስ ሉቃስ እንደሚነግረን ክርስቶስ ወደ ተራራው የወጣው “ሊጸልይ” ነው፣ ፊቱም የተለወጠው “ሲጸልይ” ነበር (ሉቃስ ፱፥፳፰–፳፱) የክብር መለወጥ የሚጀምረው በጸሎት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ይህ ክብር ለክርስቶስ ብቻ እንዳልሆነ ያስተምራል፦ “እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን” (፪ኛ ቆሮ. ፫፥፲፰)
ስለዚህም “በልባችሁ መታደስ ተለወጡ” በማለት ይመክረናል (ሮሜ. ፲፪፥፪) ታቦር የምናስታውሰው ተራራ ብቻ አይደለም፤ በጸሎት፣ በጾም፣ በቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት ምሥጢራት አማካኝነት ልንወጣው የተጠራንበት ተራራ ነው። በአንድ ወቅት በዚያ ጫፍ ላይ የበራው ብርሃን፣ አሁን ምንም ያህል ደብዛዛ ቢሆንም፣ በእኛም ውስጥ ማብራት እስኪጀምር ድረስ ይጠብቃልና።
ማጠቃለያ
እንግዲህ እኛም፣ በትንሹም ቢሆን፣ ራሳችንን ታቦር እናድርግ፦ በበደል ጎስቁሎ የነበረው፣ በራሳችን ውጊያ፣ በጠላት ወጥመድና ቀቢጸ ተስፋ ጨለማ የሞላበትን ሰውነታችን፣ ማንነታችንን፣ ሕይወታችን ልባችንን አሁን ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦበት ብርሃነ መለኮቱን እንዲያበራበት፤ እግዚአብሔር እንዲነግሥበት፣ ክብሩን እንዲገልጥበት እንፍቀድለት። ያኔ ልባችን በስሙ ደስ የሚላት ሐሴት የምታደርግ ደብረ ታቦር ትሆናለች።
ጥንት ለሌለው ለአባቱ፣ ማሕየዊ /ሕይወት ሰጪ ለሚሆን ለመንፈስ ቅዱስም ከእርሱ ጋር ክብር፣ ጌትነትና አምልኮ ይሁን፤ ዛሬም፣ ዘወትርም፣ እስከ ዘላለም ድረስ። አሜን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!