ፅንሰታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
ከመምህር አዲሱ በዛብህ
ጰጥሪቃ እና ቴክታ የሚባሉ ደጋግ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህም በእግዚአብሔር የሚያምኑ የተወደዱ ጻድቃን ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህም ሰዎች በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ የተመሰከረለላቸው ባለጸጎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መካን ስለነበሩ ሀብታቸውን የሚወርስ ልጅ አልነበራቸውም፡፡
አንድ ቀን ጴጥርቃ ቴክታን እንዲህ አላት፡- ‹‹እኅቴ ሆይ! ይህን ሁሉ የሰበሰብነውን ገንዘባችንን ምን እናደርገዋለን? ልጅ የለን የሚወርሰን አንቺም መካን ነሽ፣ እኔም ካንቺ በቀር ሌላ ሴት አላውቅም›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ወንድሜ ሆይ! አምላከ እስራኤል ለእኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደኔው ሆነህ ትቀራለህን? ከሌላ ውለድ እንጂ›› ብላ ብታሰናብተው እርሷ ለእርሱ አስባ እንዲህ ያለ ምክር ብትሰጠው እርሱም ለእርሷ አስቦ ‹‹እንደዚህ ያለ ነገር እንኳንስ ላደርገው በልቡናዬም እንዳላስበው አምላከ እስራኤል ያውቃል›› አላት፡፡
እርሷም ‹‹አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን የሚያውቅ የለም፣ ትናንትና ማታ በሕልሜ ነጭ ጥጃ ከማሕፀኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ ሰባት ትውልድ ሲዋለዱ ሰባተኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ፣ ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ አየሁ›› አለችው፡፡ እርሱም በጠዋት ከሕልም ፈቺ ዘንድ ሄዶ የነገረችውን ሁሉ ነገረው፡፡
ያም ህልም ፈቺ ‹‹እግዚአብሔር በምሕረቱ አይቷችኋል በሣህሉ መግቧአችኋል፣ ሰባት አንስት ጥጆች ሰባት ሴቶች ልጆችና የልጅ ልጆች ትወልዳላችሁ፣ ከቤታችሁ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ፤ የፀሐይ ነገር ግን አልታወቀኝም›› አለው፡፡
እርሱም የነገረውን ሁሉ ሄዶ ለሚስቱ ነገራት፡፡ እርሷም ‹‹እንጃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል!›› ብላ ዝም አለች፡፡
ከዚያም ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ስሟንም ሔሜን ብለው አወጡላት፤ ሔሜንም አድጋ ለአካለ መጠን ስትደርስ ባል አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች፣ በስምንተኛ ቀኗም ዴርዴ ብለው ስም አወጡላት፡፡ ዴርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ወለደችና ቶና አለቻት፣ ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሲካር አለቻት፣ ሲካርም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሴትና አለቻት፣ ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሔርሜላ አለቻት፣ ሔርሜላም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ንጽሕት ቅድስት ክብርት የምትሆን እመቤታችንን የወለደቻትን ቅድስት ሐናን ወለደች፡፡
ይህችም ቅድስት ሐና በሥርዓት አድጋ ለአእምሮ ስትበቃና አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ መንግሥት ወገን ከነቅዱስ ዳዊት ወገን ከሆነው ከቅዱስ ኢያቄም ጋር አጋቧት፡፡
እነዚህ ቅዱሳን ኢያቄምና ሐና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ፡፡ እነርሱም እጅግ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ አንድ ልጅ እንኳ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ይለምኑት ነበር፡፡ መባ ይዘው ለሊቀ ካህኑ ሲሰጡት ሊቀ ካህኑም እንኳ ሳይቀር ‹‹እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ያለውን ሕግ በእናንተ ላይ እንዳይፈጸም አድርጎ ልጅ የከለከላችሁ ኃጢአተኛ ብትሆኑ ነውና መባችሁን አልቀበልም›› ብሎ በእጅጉ አሳዝኗቸዋል።
እነርሱም በሊቀ ካህኑ እያዘኑና እየተከዙ ሲመለሱ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ዛፍ ሥር ተቀመጠው ሳለ ርግቦች ጫጩቶቻቸውን ሲያጫውቱ ተመልክተው ‹‹ለእነዚህ ወፎች እንኳ ልጆችን የሰጠህ አምላክ ለእኛስ መች ይሆን ልጅ የምትሰጠን?›› ብለው እጅግ አምርረው አለቀሱ፡፡
ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀ ካህናቱ ሄደው ‹‹አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሔርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ ሴት ልጅም ብንወልድ ውኃ ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን›› ብለው ስእለት ተሳሉ፡፡
ዘካርያስም ‹‹እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ይስማችሁ ስለታችሁን ይቀበልላችሁ፤ የልቡናችሁን ሐሳብ ይፈጽምላችሁ›› ብሎ አሳረገላቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ቅድስት ሐናና ቅዱስ ኢያቄም ዕለቱን ራእይ አይተው አደሩ፡፡ ራእዩስ እንዴት ነው ቢሉ
ኢያቄም ‹‹ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› አላት፡፡ ‹‹ወፍ›› የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባህሪው ነው፤ ‹‹ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› ማለቱ የኢያቄምን (የሰውን) ባህርይ ባህርይ እንዳደረገው ዕወቅ ሲል ነው፡፡ ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ምልአቱ ስፍሐቱ ርቀቱ ልዕልናው ነው፡፡
ቅድስት ሐናም ‹‹እኔም ደግሞ አየሁ እንጂ›› አለችው፡፡ ‹‹ምን አየሽ?›› ቢላት ‹‹ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ›› አለችው፡፡ ‹‹ርግብ›› የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፣ ነጭነቱ ንጽሕናዋ ቅድስናዋ ድንግልናዋ ነው፡፡ ‹‹ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ›› ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መፅነሷን የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህንኑም ራእይ ያዩት ሐምሌ ፴ ቀን ነው፡፡
እነርሱም እንዲህ ያለ ራእይ ካየን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም ይልቁንም ፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆን ብለው አዳምንና ሔዋንን ‹‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሏት› ብሎ አምላክ ለእኛስ ይልክልን የለምን!›› ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ሰባት ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ፡፡ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ‹‹ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁና ዛሬ በሩካቤ ሥጋ ተገናኙ ብሏችኋል ጌታ›› ብሎ መልአኩ ለሐና ነገራት፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔር በብሥራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም ተፀነሰች፡፡
እግዚአብሔር አምላክ አብርሃምንና ሣራን የተመለከተ አምላክ በኢያቄምና ሐና አማካኝነት ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነችውንና ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር የነበረች፣ የተነገረላት ትንቢት ሊፈጸም የአባት የእናቷ የቅድመ አያቶቿ ራእይ ሊተረጎም ጌታ የፈቀደበት ጊዜ ሲደርስ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሑድ ዕለት ነሐሴ ሰባት ቀን በ፶ወ፬፻፹ወ፭ ዓ.ዓ ተፀነሰች፡፡
እመቤታችን ከተፀነሰች በኋላ አይሁድ ቀንተው ተነሡባቸው፡፡ ቅናቱ እንዴት ነው ቢሉ ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ከአጎቱ ቤት ሄዶ ሞተ፡፡ እነርሱም እንቀብራለን ብለው በአልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት፡፡
ቅድስት ሐናም የአጎቷ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቿ ሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆዩአት፤ እርሷም አብራ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ብድግ ብሎ ተነሥቶ ‹‹ስብሐት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሐየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስ ቅዱስ ጽርሐ ቤቱ ተፈሥሒ ደስ ይበልሽ” ብሎ ሰገደላት፡፡
አይሁድም ይህ ተአምር ሲደረግ ከዚያው ነበሩና ‹‹ምነው ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ?›› ቢሉት እርሱም ‹‹ከዚህች ከሐና ማሕፀን የምትወለደው ሕፃን ‹ሰማይን ምድርን አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች› እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኗት ሰማሁ›› አላቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹እኔንም ያነሣችኝ የፈወሰችኝ ያዳነችኝ እርሷ ናት›› አላቸው፡፡ አይሁድም ‹‹በል ተወው ሰማንህ›› ብለው ቅናት ጀመሩ፡፡ ቅድስት ሐና በእርጅናዋ ጊዜ መፅነሷን የተመለከቱ ዘመዶቿና የሀገሯ ሰዎች ተገርመው እየመጡ ይጠይቋት ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በፅንስ እያለች ብዙ ተአምራትን አድርጋለች። ከእነዚህም መካከል ዐይነ ስውር የነበረችው የአርሳባን ልጅ ወደ ሐና መጥታ ሐና መፅነሷን ለማረጋገጥ ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ እርሷም ሳታስበው ዐይኗን ስትነካ ዐይኗ በራላት፡፡ እመቤታችንም በተፀነሰች በ፱ የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት ፩ ተወለደች፡፡
✍️ የድንግል ማርያም መወለድ በነገረ ድኅነት (በመዳን ታሪክ) ያለው ሚና በብሉይ ኪዳን፣ በሐዲስ ኪዳን እና በሊቃውንት አንደበት።
የድንግል ማርያም ሚና በነገረ ድኅነት (The Role of Virgin Mary in Salvation)
የድንግል ማርያም መወለድ የሰው ልጅ የመዳን ታሪክ (ነገረ ድኅነት) ማእከላዊ አካል ነው። እርሷ የሰውን ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ የተዘጋጀች ተንከተም፤ ድልድይ፣ የአምላክ ማደሪያ እና የሕይወት እናት ናት። ይህ ታላቅ ሚናዋን በብሉይ ኪዳን፣ በሐዲስ ኪዳንና በሊቃውንት አንደበት ብለን ከፋፍለን እንመልከተው።
- በብሉይ ኪዳን
ብሉይ ኪዳን የክርስቶስን መምጣት እና የድንግል ማርያምን ሚና በጥላ /በምሳሌ/ (Typology) ያሳያል። እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ከገነት ከተባረሩበት ጊዜ አንሥቶ የሰውን ልጅ ለማዳን ዕቅድ ነበረው።
✍️ ትንቢት (Prophecy): የመጀመሪያው ትንቢት የተሰጠው ነው። (ዘፍ. ፫፡፲፭) እግዚአብሔር ለእባቡ (ለሰይጣን) ሲናገር፣ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኮናውን ትጠብቃለህ“ ይላል። እዚህ ላይ “ሴቲቱ” ድንግል ማርያም ስትሆን፣ “ዘርዋ” ደግሞ ዲያብሎስን ድል ያደረገው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
✍️ የኢሳይያስ ትንቢት:- ኢሳይያስ ፯፥፲፬ ላይ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወለዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብለው ይጠሩታል“ በማለት ከድንግል መወለዱን በግልጽ ተነገሯል። ይህ ትንቢት ማርያም የአምላክ እናት እንደምትሆን ያረጋግጣል።
✍️ ምሳሌዎች (Typologies): ብሉይ ኪዳን ማርያምን የሚመስሉ ብዙ ሴቶችን እና ነገሮችን ይዟል፡
✍️ የሙሴ ቍጥቋጦ: ሙሴ በነበልባል የተዋሐደች ነገር ግን ያልተቃጠለች ቍጥቋጦ አየ (ዘጸአት ፫)። ይህች ቍጥቋጦ አምላክ በድንግልና የፀነሰችውን ማርያምን ትመስላለች፤ እሳተ መለኮትን ተሸከመች፤ ግን አልተቃጠለም፤ ድንግልናዋም አልተለወጠም።
✍️ የኖኅ መርከብ: የሰው ልጅን ከጥፋት ውኃ እንዳዳነች፣ ማርያምም የዓለምን መድኀኒት በመያዝ የሰው ዘርን ከዘላለማዊ ጥፋት አድናለች።
✍️ የኪዳኑ ታቦት: ታቦቱ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ጽላት እንደያዘ፣ ማርያምም የብሉይ ኪዳን ፍጻሜ የሆነውን ክርስቶስን በማሕፀኗ ተሸከመች።
- በሐዲስ ኪዳን
በሐዲስ ኪዳን የብሉይ ኪዳን ጥላዎች እና ትንቢቶች እውን ሆነዋል። የድንግል ማርያም መወለድ እና ሕይወት ከመዳን ሥራው ጋር በቀጥታ የተሳሰረና የተገናኘ ነው።
✍️ ብሥራት (The Annunciation – ሉቃስ ፩): መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ተልኮ መጥቶ “ደስታ ይገባሻል፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው“ አላት። ማርያምም በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ ያላትን ሙሉ ሱታፌ “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ“ በማለት አረጋገጠች (ሉቃስ ፩፥፴፰) ይህ ቃል የሰው ልጅ መዳን የተረጋገጠበት ታላቅ ቃል ነው።
✍️ የኤልሳቤጥ ምስክርነት: ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?” በማለት ማርያም የአምላክ እናት መሆኗን አውጃለች (ሉቃስ ፩፥፵፫)
✍️ የማርያም ምስጋና: ማርያም እግዚአብሔር ላደረገላት ታላቅ ነገር ስትዘምር “እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል“ አለች (ሉቃስ ፩፵፰) ይህም ማለት ትውልደ ሴም ፣ ትውልደ ካም ፣ ትውልደ ያፌት ብፅዕት ፣ክብርት፣ ውድስት፣ ቅድስት ፣ የአምላክ እናት ፣ የሰማይና የምድር ንግሥት ብለው ያመሰግኑኛል በማለት የተናገረችው የትንቢት ቃል ነው ።
✍️ ከክርስቶስ ጋር ያላት ኅብረት: ማርያም ክርስቶስን ወለደችው፣ አሳደገችው፣ እናም በመስቀል ላይ እስከመስቀል ድረስ ከእርሱ ጋር አልተለየችም። ዮሐንስ ፲፱፥፳፭-፳፯
- በሊቃውንት አንደበት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እና የዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ስለ ድንግል ማርያም ታላቅነትና ሚና በስፋት አስተምረዋል።
✍️ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ: “ሁለተኛዋ ሔዋን” በማለት ይጠራታል። የመጀመሪያዋ ሔዋን ለሞት ምክንያት ስትሆን፣ ድንግል ማርያም ግን ለሕይወት (ለክርስቶስ) መግቢያ በር ሆናለች። “ማርያም የሰማይ ደጅ ናት፤ በእርሷ አምላክ ወደ ምድር ወርዷል“ ይላል።
✍️ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ: “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ አምላክን በማሕፀኗ ተሸክማለች“ በማለት ክብሯን ይገልጻል። እርሷ የእግዚአብሔር ዙፋን ናት።
✍️ የኢትዮጵያ ሊቃውንት (በቅዳሴ እና ድጓ): በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ድንግል ማርያም “እመ አምላክ” (የአምላክ እናት)፣ “ወለተ ነቢያት” (የነቢያት ልጅ)፣ “ማኅደረ መለኮት” (የመለኮት ማደሪያ) ስብከተ ሐዋርያት (የሐዋርያት ስብከት) ፣ እኅተ መላእክት የመላእክት እኅት) ፣ እሞሙ ለሰማዕታት (የሰማዕታት እናታቸው) ፣ ተብላ ትጠራለች።
✍️ ማጠቃለያ
የድንግል ማርያም መወለድ በነገረ ድኅነት ላይ ያላት ሱታፌ እጅግ ከአእምሮ በላይ የሆነ ዕፁብ ድንቅ ነገር ነው። እርሷ በብሉይ ኪዳን በአፈ ነቢያት ትንቢት የተተነበየላት፣ በሐዲስ ኪዳን በአፈ ሐዋሪያት የተገለጠች፣ እና በሊቃውንት የተመሰገነች የክርስቶስ እናት የዓለም ሁሉ እናት ናት። እርሷን ማክበር ማለት እርሷን የፈጠረውን እና በእርሷ ያደረውን አምላክ ማክበር ነው።
ክብርት እናቱን እናት አድርጎ ለሰጠን ለመድኃኔዓለም ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ይግባው! በቃልኪዳኗ በምልጃዋ ይማረን፡፡ ፍቅሯን በልባችን፣ ጣዕሟን በአንደበታችን ያሳድርብን! አሜን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!