“በበረከት የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል” (፪ተኛ ቆሮ. ፱፥፮)
“በበረከት የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል” (፪ተኛ ቆሮ. ፱፥፮)
ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከላቸው በሁለተኛ ክታቡ መልእክቱን ሲልክላቸው የእነርሱን ሥነ ልቡና የሕይወት ዘይቤያቸውንና ማኅበራዊ ትስስራቸውን ስለሚያውቅ የነዳያኑ ህልውና ዋስትና እንዲያገኝ ማኅበርና ጽዋ ለነዳያን ምገባ ይውል ዘንድ ሲመክራቸውና መስጠት መዝራት እንደሆነ በማስረዳት ብዙ የዘራ ብዙ ያገኛል” የሚለውን መርሕ ይዞ በብዙ እንደሚሰበስቡ ለማስረዳት ይህንን መልእክት ላከላቸው።
- ዘር የተባለው መልካም ሥራ (ምጽዋት) ነው። (፪ኛ ቆሮ. ፱፥፮-፲)
- ዘር ሲዘራ ዝናቡ ያሰቅቃል፤ ምጽዋት ሲሰጥ ስስት ያሰቅቃል።
ዘር የተባለ ምጽዋት በትጋት ከዘሩት በበጋ መንግሥተ ሰማይ እንደሚደሰቱ “እለ ይዘርዑ በአንብዕ ወበሐሤት የአርሩ፤ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ ወጾሩ ዘርዖሙ፤ ወሶበ የአትዉ መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ ወጾሩ ከላስስቲሆሙ፤ በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ፤ በሄዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ።” (መዝ. ፻፳፮፥፭) እንዲል ገበሬ የሌሊቱ ቍር፣ ዝናሙ፣ ጭቃው እነዚህ ሁሉ ምቾቱን እየነሡት ተቋቁሞ እህሉን ለቀጠና ብሎ ሳይሰስት በእምነት ወጥቶ እየተራበ እየተጠማ በእርሻው ላይ ይዘራል።
- ዘር ሲዘራ ቅንጣቷ ዘር ሠላሳ፣ ስሳና መቶ እንደሚሆን የሚታወቀው በእምነት ነው፤ ምጽዋት ሲሰጥ በሰማያዊ መዝገብ ማስቀመጥ እንደሆነ የሚታወቀው በእምነት ነው። (ማቴ. ፮፥፱)
“እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው፤ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህና።” (መክ. ፲፩፥፩) መተርጕማኑ በአንድምታ እንደሚከተለው ያስቀምጡታል።
በውኃ ውስጥ የጣሉት እንዳይታይ ሰውረኃ ሳታሳይ ስጥ። አንድም በውሀ ውስጥ የጣሉት እንዳይገኝ ከዚያ ከሰውየው ዋጋዬን አገኛለሁ ሳትል ስጥ። አንድም ከውኃ ዳር የዘራ ሰው እንዳያጣ ከእግዚአብሔር ዋጋዬን አጣለሁ ሳትል ስጥ አንድም … ውስተ ገጸ ሰማይ ይላል ምግብህን በከርሠ ርኁባን፤ በተራበ ሰው ሆድ፣ መጠጥህን በጕርዔ ጽሙዓን፤ በተጠማ ሰው ጕሮሮ፣ ልብስህን በዘባነ ሩቃን፤ ልብስህን በተራቆተ ሰው ጀርባ አኑር።
የዘሪውም ነገር ከዚህኛው በምሥጢር የሚገናኝበት ጊዜ አለ፤ ዘሪው ንፁሕ ዘሩ በእርሻው ሲዘራ በዝናም በራሰ መሬት እንደሚበሰብስ ያውቃል፤ በስብሶ እንደማይቀር እና ተነሥቶ ብዙ እንደሚያፈራ አምኖ በተስፋ ይዘራዋል።
ስለዚህ ገበሬ ሞቶ መነሣትን የሚያምን ሃይማነተኛ ነው። በስብሶ መብቀል ትንሣኤ ሙታንን የሚያስረዳን ዓይነተኛ ማስረጃ ነውና “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። (ዮሐ. ፲፪፥፳፬)
ዳግመኛ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ዳግመኛ ስለመነሣት በሚያስተምርበት በመጀመርያ መልእክቱ በዘር መስሎ “አንተ ሞኝ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ የምትዘራውም ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም” ብሎ ያስረዳቸዋል። (፩ቆሮ. ፲፭፥፴፮-፴፯)
ምጽዋትም ቢሆን ለጊዜው ስንሰጥ በውኃ እንደሟሟ እንጀራ “በከርሠ ርኁባን፤ በተራቡት ሰዎች ሆድ” እንጥለዋለን፤ እንደሚበሰብስ ዘር እንደሚበቅል አውቀን በእምነት እንዘራዋለን። ይህንንም መጽሐፍ” እስመ በብዙኅ መዋዕል ትረክቦ፤ በብዙ ዘመን ታገኘዋለህና” እያለ ከቶ እንደማይጠፋ ያሳስበናል። (መክ. ፲፩፥፩)
በውኃ የተጣለ እንጀራ እንደማይገኝ ያደረግነው በጎ ሥራ ከሰው ዘንድ ባይገኝ ከአምላክ ዘንድ በዝቶ ይገኛል። “ለዘሰአለከ ሀቦ፤ ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ”፤ “ግበር ሠናየ ለኵሉ ወፈድፋደሰ ለሰብአ ሃይማኖት፤ ለሁሉም ሰው በጎ ሥራን አድርግ ይልቁንም ለሀይማኖት ሰው አድርግ” እንዲል ትርጓሜ፤ እርዳታችንን ለሚፈልጉ ሁሉ እንድንሰጥ መጽሐፉ “ሀብ መክፈልተከ ለ፯ቱ ወለ፰ቱ፤ ገንዘብህን ለሰባትም ለስምንትም ሰው ስጥ” ይላል (መክ. ፲፩፥፪) ፤ መተርጕማኑ ሲያብራሩት፡-
ለጥቂትም ለብዙም ስጥ፤ አንድም ለ፯ቱ ለሰባ ዘመን ይሆነኛል ያልኸውን ወለ፰ቱ ለሰማንያ ዘመን ይሆነኛል ያልኸውን ስጥ፤ አንድም ለ፯ቱ በሃይማኖት ለሚመስሉህ ለፍጹማን ምእመናን ወለ፰ቱ በሃይማኖት ለማይመስሉህ ስጥ፤ በሃይማኖት የማይመስሉ መጥተው ቢለምኑ መስጠት በሃይማኖት ለሚመስሉ ባሉበት ወስዶ መስጠት ይገባል።
አስቀድመን በሃይማኖት የሚዛመዱንን መርዳት እንደሚገባን ከዚያ በኋላ ለሰው ወገን በሰብእናው ልንረዳው እንደሚገባ ያስገነዝቡናል። “በተነ ለችግረኞችም ሰጠ” (መዝ. ፻፲፪፥፱) እንዲል አምላክ ያደለንን ጸጋ እኛም ለሌሎች ችሮታችንን ለሚፈልጉ ሁሉ መድረስ ይኖርብናል።
ተማሪ ምን ሊሰጥ ይችላል?
“ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም” እንዲሉ አበው ተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን መስጠት የምንችለው ጊዜያችን፣ ሐሳባችን፣ ጉልበታችን፣ ምክራችን፣ በጎ ልቡናችን ሊሆን ይችላል፤ እንጂ የግዴታ ገንዘብ ወይም ቁሳቁስ ላይሆን ይችላል። “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው።” (ሐዋ. ፫፥፮) ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ ነዳዩ ከሚፈልገውና ሌሎች ከሚሰጡት የተሻለ ጸጋ አደለው። እኛም ከብርና ከቁስ የተሻለ አበርክቶ ልናበረክት ስለምንችል ለዚህ ራሳችንን ማዘጋጀት ብቻ ነው የሚጠበቅብን ማለት ነው። ይኸውም፡-
- ለቤተ ክርስቲያን የምናወጣው ዐሥራት ባይኖረን ገቢ የሚያስገኙ ቋሚም ሆነ ጊዜያዊ ሰብሎችን እያለማን ገቢ ማስገኘት ይቻላል።
- ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎችን የነገረ ሃይማኖት ትምህርት በማስተማር ትውልድን በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ቀርጾ በሥነ ምግባር አንጾ በሃይማኖት ማጽናት ይቻላል።
- በአስኳላ ትምህርታቸው እያገዝናቸው በትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው የሀገር ተረካቢ ትውልድን መፍጠር ይቻላል።
- የተለያዩ ግንዛቤ፣ ዕውቀትና ክሂሎትን የሚያዳብሩ ሥልጠናዎችን ማሠልጠን ያስፈልጋል።
- እኩይ ተግባራት እንዲወገድ በማኅበረሰብ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር፣ ወጣቶችን በኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ አደራጅቶ ራሳቸውን ከሱስ ነጻ ሆነው ሃይማኖታቸውን ከመናፍቃን ጥቃት እንዲከላከሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ማስታጠቅ (ኤፌ. ፮፥፲፩) ሕፃናት ያለጥመት በሃይማኖት ቀጥ ብለው እንዲያድጉ ወተት የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር እየጋቱ ማሳደግ (፩ኛቆሮ. ፫፥፪) እንዲሁም ከመጤ ባሕል መታደግ የሚያስችሉን መንገዶች መዘርጋት ይቻላል።
- ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። (ማቴ. ፲፫፥፲፱-፳፫)
“ዘእንበለ ምሳሌሰ ኢተናገሮሙ፤ ያለምሳሌ አልተናገራቸውም” እንዲል (ማቴ. ፲፫፥፴፬) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘለዓለማዊ የሆነው ወንጌለ መንግሥቱን ለሁሉም ሰው በሚገባውና በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ሲያስተምር ለገበሬዎች በዘር መስሎ አስተምሯቸዋል።
በዚህም መሠረት “ዘር” የተባለው ቃለ ወንጌል ሲሆን “ዘሪ” የተባለው ደግሞ ጌታችን ነው። ጌታችን “ሑሩ ወመሀሩ ኵሎ አሕዛበ፤ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ” ብሎ እንደአዘዛቸው (ማቴ. ፳፰) ያስተማሩ ሐዋርያትና ከእነርሱ እግር ሥር ተተክተው ዘለዓለማዊው የክርስቶስን ሕያው ቃል ለፍጥረተ ዓለም የሚያስተምሩ ሁሉ “ዘሪ” የሚለውን ስም ያገኛሉ።
“ዘር”
- ምቹ የሆነ ታርሶ የለሰለሰ ለም የሆነ እርሻ ይፈልጋል፤ ይህ ከሆነ ሥር ይሰዳል፤ ይበቅላል።
- ወፎች እንዳይለቅሙት መጠበቅ ያስፈልጋል።
- የተዘራበት ማሳ ከአረም የጸዳ መሆን አለበት፤ አረም ከሌለ ሳይቀጭጭ ደኅና ሆኖ ያድጋል፤ ስለዚህ በየጊዜው ሊታረም ይገባዋል።
- ዋግ እና መሰል ተባዮች እንዳያበላሱጽ ጸረ ተባይ መድኀኒት መርጨት ይጠይቃል።
- የተዘራበት ማሳ በሰውም ሆነ በእንስሳ መረገጥ የለበትም በአጥር ቅጥር ሊከለል ይገባዋል።
በዚህ መልኩ መንከባከብ ከተቻለ ጥሩ ምርት መሰብሰብ ይቻላል።
እነዚህ የዘረዘርናቸው ተግባራት ሁሉ የሚሠራው ዘሪው ብቻ ላይሆን ይችላል፤ ሌሎች እነዚህን ተግባራት የሚፈጽም ግብረ ኀይል ይኖራል፤ እኛም በወንጌል ዘር ሱታፌያችን የየቅል ነው፤ ድርሻችን መዝራት ብቻ ላይሆን ይችላል፤ የሚዘራው ዘር ለፍሬ እንዲበቃ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን መሥራት ይጠበቅብናል።
ሁሉም ሰው ተመሳሳይ የሥራ ድርሻ ሊኖረው አይችልም፤ “የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው፤ መንፈስ ግን አንድ ነው” እንዲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (፩ኛቆሮ. ፲፪፥፬) ሁላችንም የተለያየ ስጦታ አለን።
ስለሆነም የተለያየ ስጦታችን ተጠቅመን አንድ ወንጌልን እንሰብካለን። “አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፣ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፣ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ …” (ኤፌ. ፫፥፭) እንዲል ሐዋርያው አማኝ ሁሉ በተረዳው ልክ ያንን የተረዳውን እውነት ለሌሎች የማጋራት ግዴታ አለበት። “ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።” (ፊል. ፩፥፳፯) ይላል።
በመሆኑም ማንኛውም ሰው በወንጌል አገልግሎት “መክሊቴ ምንድነው?” የሚለውን መለየት ይኖርበታል። ሁሉም ሰው በስብከተ ወንጌል አገልግሎት የድርሻውን እንዲወጣ ኃላፊነት አለበት፣ ነገር ግን ይህንን አገልግሎት ለመተግበር የግድ ዐውደ ምሕረት ላይ ቆሞ መስበክ፣ መተርጎም፣ ለሰንበት ተማሪዎች ኮርስ መስጠት ላይጠበቅበት ይችላል። የግድ ሥልጣን ላይ መቀመጥ አይጠበቅበትም፤ ነገር ግን “ወንድሞች ሆይ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር እየጸለያችሁ ከእኔ ጋር ትጋደሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ፤” (ሮሜ ፲፭፥፴) ብሎ እንዳዘዘ ሐዋርያው መምህራንን መራዳት ታላቅ አገልግሎት ነው።
የሚማሩ ተማሪዎችን መቀስቀስ ማትጋትና የመማር ማስተማር ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ ጉባኤ እንዲዘጋጅ ማስተባበር፣ በተሰማራንበት ሁሉ ተተኪ እንዲኖር ሥልጠናዎች እንዲዘጋጁ ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር መቀናጀት ያስፈልጋል፤ እነ ፌቬን የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት ተደራሽ እንደሚያደርጉ የመምህራኑ ትምህርት ለምእመናን በተለያየ መንገድ ተደራሽ ማድረግ፣ የኢአማንያን ጥያቄ በመለየት አደራጅቶ በመምህራን ዘንድ ምላሽ በማሰጠት ትውልዱን ከስሑት አስተሳሰብ መጠበቅ ከቻልን የተዘራውን የክርስቶስ የመንግሥቱ ወንጌል ፍሬ እንዲያፈራ የድርሻችን መወጣት ችለናል።
ይህንን ለማድረግ የግቢ ጉባኤ ልጆች በክረምት ወደ ቤተሰብ ለዕረፍት ስትሄዱ በማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎት መስመር ላይ ሆናችሁ ዘር የክርስቶስ ወንጌል ሲዘራ የበኵላችሁን ተወጥታችሁ መከር ሲደርስ ከዘሪው ጋር ሐሴት ልታደርጉ ይገባል። “በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፤ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። … እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ።” (ፊሊ. ፪፥፲፮-፲፰) እንዲል ዛሬ ከእርሱ ጋር ከደከምን ነገ በመንግሥተ ሰማያት ከእርሱ ጋር ደስ ይለናል። ሁላችንም የምንሰበስበው በበተነው ልክ የምናጭደው በዘራነው መጠን መሆኑን ተረድተን ሳንታክት የወንጌልን አገልግሎት ለማስፋት መሮጥ አለብን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
አበበ ፍቅሬ

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!