አገልግሎት
በዲ/ን አብርሃም ባንቲሁን
የሰው ልጅ በፈጣሪው አምሳል ሕያው ባለአእምሮ፤ ነቢብ ሆኖ ሲፈጠር የእግዚአብሔርን ስም ይቀድስ ዘንድ እንዲሁም ዓለም ሳይፈጠር በፊት የተዘጋጀለትን ዘለዓለማዊ ክብር ይወርስ ዘንድ ነው። የእግዚአብሔርን ስም ከሚቀድስባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ሥጋ እንደ ለበሰ መልአክ ሆኖ ለአገልግሎት በመትጋት ነው። ‹‹እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን በማለት ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን›› (ኤፌ. ፪፥፲) ።
አገልግሎት ምንድን ነው?
አገልግሎት በአንድ ቃል ሊወሰን የማይችል ሰፋ ያለ ሐሳብ ነው። አገልግሎት አንድ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያደርገው ጉዞ ነው። በክርስቶስ ኢየሱስ ያመነውን እምነት፣ በሐዋርያት የተሰበከለትን ወንጌል የሚኖርበት ሕይወት ነው። ክርስትና በቃልና በኑሮ የሚገለጽ ምስክርነት ነው። አገልግሎትም ይህን ሕይወት በመኖር ሌሎች ይኖሩት ዘንድ ብርሃንን መፍጠር ነው። አገልግሎት በሕይወት ላይ ክርስቶስን ንጉሥ አድርጎ መሾም ነው።
በዚህች ምድር ላይ እንኳ ብዙ ዓይነት አገልግሎት ይስተዋላል። ሰው ለባልንጀራው የሚሰጠው አገልግሎት፣ ሰው ለገዢው የሚሰጠው አገልግሎት፣ ሰው ለማኅበረሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት አለ። እነዚህ አገልግሎቶች ሥጋዊ አገልግሎቶች ቢሆኑም የኃጢአትን መንገድ እስካልቀላቀሉ ድረስ ሰውን በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስነቅፉ አይደሉም።
እኛ ግን ከነዚህ ሁሉ የሚበልጠውን አገልግሎት እናያለን። ይህም መንፈሳዊ አገልግሎት ነው። መንፈሳዊ አገልገሎት ልዩ ልዩ ነው። ሰው እንደየጸጋው እግዚአብሔርን የሚያከብርበት መንገድ ነው። አገልግሎት ፍቅር ነው፣ አገልግሎት ትሕትና ነው፣ አገልግሎት የንጽሕና ሕይወት ነው፣ አገልግሎት በቅድስና የሚከወን ነው፣ አገልግሎት የሕይወት መንገድ ነው።
አገልግሎት ፍቅር ነው
አገልግሎት ከሰው ልብ የሚፈልቀው ፍቅር የሚገለጽበት መንገድ ነው። ፍቅር እግዚአብሔር ዓለምን ለመፍጠሩ ብሎም በኋለኛው ዘመን ለማዳኑ ምክንያት የሆነ የመንፈስ ፍሬ ነው። ፍቅር የሕግ ሁሉ የበላይ ነው። በፍቅር ውስጥ መታዘዝ እና ርኅራኄ ይሰፍናሉ። ይቅርታ እና ምሕረት ጎልተው ይታያሉ። ፍቅር በልቡ ውስጥ ያለ ሰው እግዚአብሔርን ከፍርዱ ጽናት የተነሣ ሳይሆን ከፍቅሩ ኀያልነት የተነሣ ይፈራዋል።
አገልግሎታችን በእግዚአብሔር የሚያስነቅፈን እንዳይሆን በፍቅር ላይ የተመሠረተ ይሆን ዘንድ ግድ ነው። ለዚህ አብነት ይሆነን ዘንድ ጌታ የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን የነቀፈበትን ምክንያት ማየት ይበቃል። ‹‹ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና›› (ራዕ.፪፥፬) እግዚአብሔር በአገልግሎታችን ውስጥ ፍቅርን ያይ ዘንድ ይወዳል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ዘመን ያደረጋቸው ተአምራት በሙሉ መነሻቸው ፍቅር ነበር። አገልግሎት ለእግዚአብሔር እና ለመንግሥቱ ያለን ፍቅር ነጸብራቅ ነው።
የጥበብ መጨረሻ የተባለው ፍቅር ፍቅረ እግዚአብሔር እና ፍቅረ ቢጽ በመባል ለሁለት ይከፈላል።
ፍቅረ እግዚአብሔር
እግዚአብሔርን መውደድ የአገልግሎት ብቻ ሳይሆን የክርስትና ሕይወትም መሠረት ነው። እግዚአብሔር ለሙሴ ሕግን በሰጠው ጊዜ ከትእዛዛቱ መካከል አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኀይልህ ውደድ የሚለው ዋነኛው ነው። እውነተኛ አገልጋይ እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ በመውደድ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲወዱት የሚያደርግ ነው። ፍቅር የአገልግሎት መለኪያም ጭምር ነው። ለሊቀ ሐዋርያት ለቅዱስ ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ የቀረበው የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን? የሚለው ጥያቄ እና የሐዋርያውን መልስ ተከትሎ የተሰጠው የአገልግሎት ኀላፊነት እግዚአብሔር የአገልግሎታችንን መጠን ለእርሱ ባለን ፍቅር ልክ ለመለካቱ ማሳያ ነው።
ፍቅረ ቢጽ
ይህ ዓይነቱ ፍቅር እግዚአብሔር ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ በማለት ያዘዘውን ትእዛዝ የምንፈጽምበት ፍቅር ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህችኛይቱ ፍቅር ‹‹ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና እርሱም፦ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው›› በማለት ይነግረናል። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር በቂ ሊሆን አይችልምን? ለሱ ያለን ፍቅር አገልግሎቱን ለመከወን በቂ ምክንያት አይደለምን? በማለት ሲጠይቁ ይስተዋላሉ፤ ይሁንና የፍቅር ሐዋርያ የተባለ ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይመልስላቸዋል ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ዳግመኛም ሐዋርያው ወንድሙን የሚጠላ ሰው ከነፍሰ ገዳይ የማይለይ እንደሆነ፣ የዘላለም ሕይወት እንደሌለው እና የእግዚአብሔር ፍቅር በልቡ እንደሌለ ያረጋግጥልናል። (፩ኛ ዮሐ.፫፥፲፭-)
አገልግሎት ትሕትና ነው
ትሕትና የክርስቶስ ፍቅርና መሥዋዕትነት ነጸብራቅ ነው። በትሕትና ውስጥ የሕይወትን ትክክለኛ ትርጉም እና ወደ ዘለዓለማዊ ደስታ የሚወስደውን መንገድ እናገኛለን። አገልግሎት የእግዚአብሔር ትሕትና ማሳያ ነው። እርሱ እግዚአብሔር ሁሉን ሥራ በራሱ መከወን የሚችል የሚሳነው የሌለ አምላክ ሆኖ ሳለ ይህን የተቀደሰ አገልግሎት ለእኛ በመፍቀድ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ተሳታፊ አደረገን። በመዋዕለ ሥጋዌውም ለፍጹም ትሕትና አብነት ሆነን። ‹‹ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና›› በማለት ለትሕትና ጠራን።
የታመነ አገልጋይ ልቡ በቅንነት እና በትሕትና የተሞላ ነው፤ ወንድሙ ከእርሱ እንደሚሻል በትሕትና ያስባል። አገልግሎቱም ከንቱ ውዳሴን በመሻት የሚደረግ ሳይሆን የመንፈስ ፍሬዎችን ገንዘብ ያደረገ ይሆናል።
አገልግሎት የንጽሕና ሕይወት ነው
ንጽሕናን የምትሻ ነፍስ በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት የምትጠብቅን ዕቃ ትመስላለች። የእግዚአብሔር አገልጋይ ንጽሐ ልቡና ያለው ነውርና ነቀፋን የሚጸየፍ ነው። አገልግሎት ራስን ለእግዚአብሔር መስጠት ነው። እርሱ የሰጠንን ሀብት ለእርሱ መልሰን መሥዋዕት የምናደርግበት መንገድ ነው። ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ደግሞ ንጹሕና የተመረጠ ይሆን ዘንድ ይገባል። ራሳችንን ለእግዚአብሔር ስናቀርብ በንጽሕና መሆን አለበት። መሥዋዕታችንም እንደ አቤል መሥዋዕት በአምላክ የተወደደ ይሆናል።
አገልግሎት በቅድስና የሚከወን ነው
እንደ እግዚአብሔር ያለ የቅድስና አስተማሪ ማነው? እንደ አምላካችን ያለ የሚያነጻ ማነው? እርሱ የሰውን ልጅ ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና ጠርቶታልና። በአገልግሎታችን ሂደትም ይህን የተጠራንበትን ዓላማ ማክበር ይገባናል። ሰውነቱን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ የሰጠ ሰው እግዚአብሔርን በቅድስና ያገለግል ዘንድ ግድ ነውና። አገልግሎት እግዚአብሔርን መስሎ ሌሎች እኛን ይመስሉ ዘንድ መጥራት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ በማለት እርሱን በቅድስናና በንጽሕና ወደመምሰል ይጠራናልና። እኛም እርሱን አብነት በማድረግ ለተቀደሰ አገልግሎት የተዘጋጀን መሆን አለብን።
አገልግሎት የሕይወት መንገድ ነው
አገልግሎት መንገድ ነው፤ ከአንደኛው ሰው ሕይወት ወደ ሌላኛው ሰው ሕይወት እየተሸጋገረ የሚቀጥል መንገድ። የሕይወትን እስትንፋስ ከአንዱ ወደ ሌላው እያዳረሰ የሚቀጥል ጥልቅ ጉዞ። ከሙሴ ወደ ኢያሱ የተሻገረ መንገድ፣ ከኤልያስ ወደ ኤልሳዕ የተሻገረ መንፈስ፣ ከጳውሎስ ወደ ጢሞቴዎስ የተሻገረ ጉዞ። አገልግሎት የሚቀጥል ነው። እግዚአብሔር ለቤቱ አገልጋይን ይተካል። ከትውልዱ መካከልም ብርቱውንና ደገኛውን ያስነሣል።
በእግዚአብሔር ቤት ስናገለግል በትምክህት እና በመታበይ የእግዚአብሔርንም ሕግ በመተላለፍ አይሁን። እግዚአብሔር አገልግሎታችንን ስንንቅ ለሚያከብሩት ይሰጣል። ኤሳው ብኩርናውን ንቆ ሸጠው፣ ያዕቆብ በረከቱን ወሰደ፤ ሳኦል በትዕቢት የእግዚአብሔርን ነቢይ አቃለለ ትእዛዙንም አፈረሰ፣ ዳዊት በትሕትናው ንጉሥ ሆነ፤ ይሁዳ ከክርስቶስ ደቀ መዝሙርነት ይልቅ የገንዘብ ፍቅር በለጠበት ከአገልግሎቱም ተሻረ፣ ስሙም ከሕይወት መዝገብ ተፋቀ፤ ማትያስ በትሕትና የሐዋርያነትን ጉዞ ተቀላቀለ።
ለዚህም አገልግሎታችን በፍቅር፣ በትሕትና፣ በንጽሕናና በቅድስና ያጌጠ፣ ለእግዚአብሔርም የተገባ ይሆን ዘንድ መትጋት አለብን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!