“ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ።” (ማቴ. ፪፥፳)
ከመምህር ተፈሪ መንገሻ
የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የግቢ ጉባኤ ወጣቶች፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ፣ ወንድሞችና እኅቶች ሁላችሁም ኦርቶዶክሳውያን ሰላም ለእናንተ ይሁን። እንኳን ለበዓለ ቁስቋም አደረሳችሁ።
ሰማይን እንደ መጋረጃ የዘረጋ ጌታ በእናቱ ጉያ ተሸፍኖ በሌሊት ሲሸሽ፣ ዓለምን የሚመግብ ሲራብ፣ የነገሥታት ንጉሥ በባዕድ ምድር እንደ ስደተኛ ሲንከራተት ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር በግብጽ ምድር ቆየ። ይህ ሽንፈት አይደለም፤ ከእኛ ጋር የመሰደድ ምሥጢር ነው እንጂ፤ ዛሬ ግን መልአኩ ከስደቱ በኋላ የከበረ ዜና ይዞ መጣ፦
“ሄሮድስም ከሞተ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ፤ የሕፃኑን ነፍስ የሚሹት ሞተዋልና አለው።” (ማቴ. ፪፥፲፱-፳)
“የሚሹት ሞተዋል።” ይህችን ዐረፍተ ነገር እስኪሰሙ የግብጽ ስደተኞች የመከራ ዓመታትን አልፈዋል።
፩. ዙፋኑ የሚፈራው ሕፃን
ሄሮድስን ያንቀጠቀጠው ሠራዊት አልነበረም፤ በግርግም የተወለደው የሕፃን ዜና ነበር። “ንጉሡ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ተናወጠ፤ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር” (ማቴ. ፪፥፫) ምሥጢሩ ይህ ነው ክፋት ጦር አይፈራም፤ እውነትን ይፈራል። ሰይፍና ጎራዴ እንዲሁም ሠራዊት የያዘ ንጉሥ በአንድ ሕፃን ስም ተሸበረ።
ይህ ሰው የገዛ ሚስቱንና የገዛ ልጆቹን የገደለ ደም አፍሳሽ ነበር፤ ዙፋኑን ለሚያሰጋው ነገር ሁሉ ደምን እንደ ውሃ ያፈስስ ነበር። ታዲያ እንዲህ ያለው ሰው ለሰብአ ሰገል “እኔ መጥቼ እሰግድለት ዘንድ ንገሩኝ” ሲል (ማቴ. ፪፥፰) ትሕትና የለበሰ መጣ። የገዳይ የመጀመሪያው መሣሪያ ሰይፉ አይደለም፤ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲሉ የሚነዛው ወሬ (ጭምብሉ) ነው።
ሰብአ ሰገል በሌላ መንገድ ሲመለሱ “እጅግ ተቈጣ”፤ ከሁለት ዓመት በታች የሆኑትን የቤተልሔም ሕፃናት ሁሉ አስፈጀ (ማቴ. ፪፥፲፮) ጌታ ግን እዚያ አልነበረም። ሄሮድስ የፈለገውን ሕፃን አላገኘም ነበር፤ ግን በንጹሓን ደም እጁን አጠበ።
፪. የራማ ልቅሶ ዛሬም አልተቋረጠም
“ልቅሶና ብዙ ኀዘን ዋይታም በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና መጽናናትን አልወደደችም።” (ኤር. ፴፩፥፲፭)
አንዲት እናት ልጇ ከዕቅፏ ተነጥለው ሲታረድ ያየችበትን ቀን አስቡት። ገና ቃል ያለመደ፣ በፈገግታው እናቱን የሚያሞቅ ሕፃን በጦር ተወግቶ ሲወድቅ ጥፋቱ በተወለደበት ቦታና ጊዜ መገኘቱ ብቻ ነው።
ይህ የሁለት ሺህ ዓመት ታሪክ ብቻ አይደለም፤ ዛሬ በዐይናችን ፊት ይደገማል። በአርሲ ዞን ክርስቲያኖች በክርስትናቸው ምክንያት ይገደላሉ፤ ይታረዳሉ፤ ከቀዬአቸው ይፈናቀላሉ። አብያተ ክርስቲያናት ይቃጠላሉ፣ ቤቶች ይዘረፋሉ፣ ሕጻናት ያለ አባትና ያለ እናት ይቀራሉ። ራሔል ዛሬም በየመንደሩ አለች፤ ልጆቿን እየቀበረች “መጽናናትን አልወድም” ትላለች።
መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን ግድያ ሲዘግብ ምድር ምስክር እንደ ሆነች ይናገራል፦ “የወንድምህ ደም ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል።” (ዘፍ. ፬፥፲)። የተገደሉት ወገኖቻችን ደም ዝም አላለም፤ ወደ ሰማይ ይጮኻል። ዮሐንስ በራእዩ በመሠዊያው ሥር ያሉትን ነፍሳት አየ፤ በታላቅ ድምፅ “ጌታ ሆይ ቅዱስና እውነተኛ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም?” ይሉ ነበር (ራእ. ፮፥፱-፲) “የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት ክቡር ነው” (መዝ. ፻፲፮፥፲፭) ሰዎች የረሱትን እርሱ አይረሳም፤ ማንም መዝገብ ባይዝ በሰማይ መዝገብ ስማቸው የተመዘገበ ነው፡፡
፫. ሄሮድስ አልሞተም፤ ልብሱን ቀይሯል፡፡
ሄሮድስ በሥጋ ሞተ፤ ሄሮድሳዊነት ግን በየዘመኑ ይነሣል። ጌታ ቀድሞ ነግሮናል፦ “የሚገድላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል።” (ዮሐ. ፲፮፥፪) ዘመናዊው ሄሮድስ ሰይፍ ብቻ አይዝም፤ የተለየ የጭካኔ ጥበብ አለው፦
➜ ያቅዳል፦ ድንገተኛ የሚመስለው ብዙው ጥቃት ቀድሞ በሴራ የተጠነሰሰ ነው።
➜ ያጥላላል፦ የተገደለውን ተጠያቂ ያደርጋል፤ ለቅሶውን ወንጀል ያስመስላል፤ ጩኸት ይቀማል።
➜ ያደበዝዛል፦ ጭፍጨፋን “ተራ ግጭት” ብሎ ይሰይማል፤ አሳዳጅና ተሳዳጅ ጎን ለጎን ይቆማሉ።
➜ ያለ ቅጣት ይለቃል፦ ገዳይ ያለ ፍርድ ሲያልፍ ጭካኔ ከቀድሞው ይበዛል።
➜ ይከፋፍላል፦ ምእመናንን እርስ በእርስ በማናቆር ቤተ ክርስቲያን ከውስጧ እንድትደማ ይሠራል።
ጌታ ይህንን ሁሉ የሚያንቀሳቅሰውን ገልጦልናል፦ “እርሱ ከጥንት ነፍሰ ገዳይ ነበረ” (ዮሐ. ፰፥፵፬) ሐዋርያውም “የምንጋደለው ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም፤ ከአለቆችና ከሥልጣናት ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር ነው” ይላል (ኤፌ. ፮፥፲፪) ስለዚህ ኀዘናችን እርስ በርሳችን ላይ ጥላቻ እንዲወልድ አንፍቀድ፤ ጥላቻ የሄሮድስ ሌላኛው ድል ነውና። ጥቃት አድራሾችንና የሚያቀነባብሩትን እንቃወማለን፤ የሰውን ልጅ ግን አንጠላም። እያዩ ዝምታ ሲሆንስ…..
፬. ዝምታ ተባባሪነት ነው
ከገዳዩ ሰይፍ ቀጥሎ የሚያስፈራው የተመልካቹ ዝምታ ነው። እግዚአብሔር ለነቢዩ ሕዝቅኤል ጠባቂ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ መለከት ባይነፋ የሚጠፋው ሰው ደም ከጠባቂው እጅ እንደሚፈለግ ነገረው (ሕዝ. ፴፫፥፮)። ሰሎሞንም እንዲህ ጽፏል፦ “ለሞት የተወሰዱትን አድን፥ ለመገደልም የሚጐተቱትን ከመታደግ አትተው። ‘እነሆ አላወቅንም’ ብትል ልብን የሚመዝን እርሱ አያስተውልምን?” (ምሳ. ፳፬፥፲፩-፲፪) መርዶ ሲነገር “የእኔ አይደለም” ማለት፣ ዜና ሲሰማ ማድበስበስ፣ መቃብር ሲቆፈር ወደ ሌላ ማየት፣ ይህ ሁሉ የሄሮድስ ተባባሪነት ነው። መርዶክዮስ ለአስቴር የተናገረው ለእኛ ነው፦ “በዚህ ጊዜ ፈጽመሽ ዝም ብትዪ፥ እፎይታና መድኃኒት ከሌላ ስፍራ ለአይሁድ ይነሣል፤ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ለዚህ ጊዜ እንደ ደረስሽ ማን ያውቃል?” (አስ. ፬፥፲፬)
፭. “አትግደል” ማለት “አትከላከል” ማለት ነውን?
ጥያቄው ከባድ ነው፤ መልሱ ከስሜት ሳይሆን ከቃሉና ከአመክንዮ መምጣት አለበት።
ሀ) ትእዛዙ ምንን ይከለክላል?➜ “አትግደል” (ዘፀ. ፳፥፲፫) የሚለው ሕግ የተሰጠው ሕይወት የእግዚአብሔር ስጦታ ስለ ሆነች ነው፦ “እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጥሮታልና” (ዘፍ. ፱፥፮)። ዳሩ ግን ይህንኑ ትእዛዝ የሰጠው አምላክ በዚያው ሕግ ውስጥ እንዲህ ይላል፦ “ሌባ ሲሰርቅ ተገኝቶ ቢመታና ቢሞት ስለ እርሱ ደም የለበትም።” (ዘፀ. ፳፪፥፪) “አትግደል” ማንኛውንም ግድያ ቢከለክል እግዚአብሔር በአንድ ሕግ ውስጥ ራሱን ይቃረናል፤ እርሱ ግን አይቃረንም። የተከለከለው ንጹሓንን በግፍ መግደል ነው እንጂ ንጹሓንን ለማዳን ገዳይን መግታት አይደለም።
ለ) ሕይወት የተቀደሰች ናት። ንጹሓንን የሚገድል ሰው ይህንን ቅድስና ይደፍራል። ደፋሪውን መግታት የሕይወትን ቅድስና መጠበቅ ነው። ስለዚህ መከላከል ለሕይወት ካለ ክብር የሚወጣ እንጂ የሚቃረን አይደለም። ሕይወትን የሚያከብር ብቻ ነው የሚከላከለው። ገዳይ ሲመጣ ውጤቱ ሁለት ብቻ ነው፦ ንጹሑ ይሞታል፤ ወይም ጥቃቱ ይገታል። ሦስተኛ መንገድ (ማምለጥ፣ ማሸማገል፣ የፀጥታ አካል መድረስ) ካለ መጀመሪያ እርሱን እንፈልጋለን። ከሌለ ግን “እጄን ከደም አጸዳለሁ” ብሎ የንጹሑን ሞት መምረጥና ዝም ብሎ መቆምም ራሱ ምርጫ ነው። ግን ዝምታም ድርጊት ነው፤ ሐዋርያው ያዕቆብ “መልካም ማድረግን እያወቀ የማያደርገው ሰው ኃጢአት አለበት” ይላል (ያዕ. ፬፥፲፯)
ሐ) ምስክሮች
• አብርሃም የተማረኩትን ዘመዶቹን ለማዳን የሠለጠኑ ሰዎቹን አስከትሎ ጠላትን መታ፤ ከዚያ በኋላ የልዑል እግዚአብሔር ካህን መልከጼዴቅ ባረከው (ዘፍ. ፲፬፥፲፬-፲፱)። ከድሉ በኋላ ኩነኔ ሳይሆን በረከት መጣለት።
• ዳዊት መንጋውን ከአንበሳና ከድብ ነጥቆ አዳነ (፩ሳሙ. ፲፯፥፴፬-፴፮) ጌታም “መልካም እረኛ እኔ ነኝ” ብሎ ተኩላ ሲመጣ የሚሸሸውን ቅጥረኛ ከእውነተኛ እረኛ ለየ፡፡ (ዮሐ. ፲፥፲፩-፲፫)
• ነህምያ ቅጥር በሚሠሩት ሕዝብ ላይ ጠላት ሲነሣ በአንድ እጅ ሥራ በሌላው ሰይፍ ያዙ፤ “ለወንድሞቻችሁ ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻችሁ ለሚስቶቻችሁና ለቤቶቻችሁ ተዋጉ” አላቸው፡፡ (ነህ. ፬፥፲፬፣ ፲፯-፲፰) መገንባትና መጠበቅ አይጋጩም፤ የግቢ ጉባኤ ወጣትም በአንድ እጁ መጽሐፍ ቅዱስ በሌላው ሃይማኖቱን ሊከላከል ይገባል።
• በአስቴር ዘመን ንጉሡ የተከበቡት አይሁድ ራሳቸውን እንዲከላከሉ ፈቀደ፡፡ (አስ. ፰፥፲፩)
• ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የግድያ ሴራ ሲሰማ ለሻለቃው አሳወቀ፤ ሻለቃውም ብዙ ጦረኞችን ላከለት፡፡ (ሐዋ. ፳፫፥፲፪-፳፫) ሐዋርያ የታጠቀ ጥበቃን አልናቀም።
• ዮሐንስ መጥምቅ ወታደሮችን “ሥራችሁን ተዉ” አላለም (ሉቃ. ፫፥፲፬)፤ ሐዋርያትም ወታደሩን ቆርኔሌዎስን አጠመቁ፡፡ (ሐዋ. ፲)
መ) ተቃውሞዎችና መልሶቻቸው
“ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” (ማቴ. ፳፮፥፶፪)። ጌታ ይህንን ያለው ጴጥሮስ ከፈቃደኛ መሥዋዕትነቱ ሊከለክለው ሲሞክር ነው፤ “አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣምን?” (ዮሐ. ፲፰፥፲፩) የራስን ሕይወት በፈቃድ መስጠት የራስ መብት ነው። የሌላውን፣ የሕፃንና የእናትን ሕይወት አሳልፎ የመስጠት መብት ግን የለንም።
“ሌላውን ጉንጭህን ስጥ” (ማቴ. ፭፥፴፱) ጌታ የራስን ክብር በትዕግሥት ስለ መሸከም አስተማረ። ሰማዕትነት በፈቃድ የሚመረጥ ክብር ነው፤ ሕፃናትና እናቶች ግን ሰማዕትነትን አልመረጡም።
“ጌታ ሸሸ እንጂ አልተዋጋም።” መሸሽ ራሱ ራስን መጠበቅ ነው። ቅድስት ቤተሰብ ወደ ግብጽ የሸሸችው ሕይወት እንድትጠበቅና ሥራውን ሳይሠራ እንዳይሞት ነው፤ ጌታም “በአንዲቱ ከተማ ሲያሳድዱአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ” ብሏል (ማቴ. ፲፥፳፫) መንገዱ ሲኖር መሸሽ፣ መንገዱ ሲዘጋ መከላከል፤ መርሑ አንድ ነው፤ ሕይወት ትጠበቃለች።
“መንግሥት ነው የሚጠብቀው።” እውነት ነው፤ ሥልጣን “ሰይፍን በከንቱ አይታጠቅም” (ሮሜ ፲፫፥፬) መጀመሪያ የምንጠይቀው መንግሥትን ነው፤ ቅዱስ ሲኖዶስም ይህንኑ ጠይቋል። ነገር ግን ጠባቂው ሳይደርስ ገዳይ ደጅ ላይ ሲቆም የመኖር መብት አይሰረዝም።
ሠ) አባቶችና ታሪክ
ታላቁ አትናቴዎስ በጦርነት ጠላትን መግደል ሕጋዊ እንደ ሆነ አስተምሯል። ቅዱስ ባስልዮስ ደግሞ ደም ያፈሰሱ ሰዎች ለጊዜው ከምሥጢረ ቁርባን እንዲታቀቡ መክሯል፤ ይህ ኩነኔ አይደለም፤ የነፍስ ፈውስ ነው፤ ደም ማፍሰስ ከባድ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታውቃለችና ከመከላከል በኋላ ንስሓና ምክር ትሰጣለች። ኢትዮጵያም በዐድዋ ካህናት ታቦት ይዘው ከሕዝቡ ጋር ቆሙ፤ ሀገርና ሃይማኖት በሁለቱም ተጠበቁ።
፮. ከፍ ብሎ የታየው ይወድቃል
ታዲያ ተስፋ አለን? አዎን፤ ዳዊት የክፉዎችን መጨረሻ አስቀድሞ አይቶ ነበር፦
“ኃጢአተኛን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዛፍም ረዝሞ አየሁት፤ ብመለስ ግን አጣሁት፤ ፈለግሁት፥ ቦታውንም አላገኘሁትም።” (መዝ. ፴፯፥፴፭-፴፮)
የሊባኖስ ዝግባ የዓለም ረጅምና ብርቱ ዛፍ ነበር። ሄሮድስም እንዲሁ ነበር፤ ግምቡና ሠራዊቱ ሰማይ ለመንካት ሲሞክር ታየ። ታሪክ ጻሓፊው ዮሴፍ እንደሚናገረው ግን መጨረሻው በሰውነቱ ውስጥ በበሰበሰ ደዌ መሠቃየት ሆነ፤ ያቆመው ሁሉ አልታደገውም። ዳዊት ቀጥሎ እንዲህ ይላል፦ “ስለ ክፉዎች አትቅና… እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፥ እንደ ለምለም ቅጠልም ይረግፋሉ።” (መዝ. ፴፯፥፩-፪)
ይህ ሕግ ለጠላቶቻችን ብቻ አይደለም፤ በሕይወታችን እንደ ተራራ ገዝፈው ጥላ የጣሉብን ነገሮችም ያልፋሉ፦
• ስሜታዊነት፦ እንደ እሳት ይነድዳል፤ ከዚያ ወደ አመድነት ይቀራል። በቁጣ የተነገረ ቃል በጸጥታ ሲታሰብ ያሳፍራል።
• ተስፋ መቁረጥ፦ በማንነት ስደት ውስጥ ሆነን የሚሰማው ጩኸት “ሁሉም አብቅቶለታል” የሚል ድምፅ ነው፤ መልአክ “ተነሣ” ሲል ግን ድምፁ ይዘጋል። ተነሥተን ሕፃኑንና እናቱን ይዘን በተስፋ እንመለስ።
• የቤተሰብ ሐሳብ፦ ነገን ለመፍራት የሚጨነቅ ልብ ዛሬን ይበላል። “ለነገ አትጨነቁ፤ ነገ ለራሱ ይጨነቃልና” (ማቴ. ፮፥፴፬)።
እግዚአብሔር ዮሴፍን “ተነሣ” አለው፤ ዮሴፍም ተነሣ። ተስፋ በዚያች አንድ ቃል ይጀምራል፦ ጥላው ሲያልፍ ሄሮድስ ሲሞት ተስፋ ይዞ የሚነሣ ሰውም ይፈለጋል።
፯. በልባችን ያለውን ግብጽ እናጽዳ
ጌታ ወደ ግብጽ ሲገባ ኢሳይያስ እንደተነበየው ጣዖታት ተንቀጠቀጡ፦ “እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት ከፊቱ ይናወጣሉ፤ የግብጽም ልብ በውስጡ ይቀልጣል።” (ኢሳ. ፲፱፥፩) እመቤታችን ፈጣን ደመና ናት፤ በሥጋዋ ፈጣሪን ተሸክማለችና። “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” (ሆሴ. ፲፩፥፩) የተባለው አምላክ ባዕድ አምልኮን ሰብሮ ተመለሰ።
የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ፣ ጥያቄው ለእኛ ነው፦ ክርስቶስ በልባችን ሲገባ በውስጣችን ምን ይፈርሳል? ኢያሱ በጋይ ጦርነት የተሸነፈው ጠላት ስለበረታ አልነበረም፤ በሰፈሩ ውስጥ የተደበቀ እርም ነገር ስለነበረ ነው (ኢያ. ፯፥፲፫)። ዛሬም ከውጭ የሚያሸንፉን ከውስጥ ባለው እርም ምክንያት ነው። ሐዋርያው እንዲህ ብሏል፦ “ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖት ማምለክ የሆነ መጎምጀት።” (ቆላ. ፫፥፭) በዘመናችን እነዚህ ስማቸውን ቀይረዋል፦ በስልክ የሚታዩ ልቅ እይታ፣ ክርስትናንና የኢትዮጵያን ኀፍረት የሚሸረሽር አለባበስና አኗኗር፣ ስካርና ዕፅ፣ የሐሜት ስብስብ፣ የዘር ኩራት፣ የማንነት ልዕልና ማጣት ሆነዋል። ሰማዕታቱ ለእምነታቸው ደማቸውን ሲከፍሉ እኛ ማንነታችንን በነጻ አሳልፈን የምንሰጥ ከሆነ ለእነርሱ ክብር አንመጥንም። “የሚያታልለውን ምኞት ተከትሎ የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፤ እግዚአብሔርን የሚመስለውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” (ኤፌ. ፬፥፳፪-፳፬)
ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ የሚቆም ወጣት መጀመሪያ በራሱ ልብ ያለውን መሠዊያ ማጽዳት አለበት፤ በጭቃ የተበከለ እጅ ለሌሎች ውሃ ማቅረብ አይችልም።
፰. ምን እናድርግ?
፩) ጸሎት
ጴጥሮስ በእስር ቤት ሳለ “ቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር በትጋት ትጸልይ ነበር” (ሐዋ. ፲፪፥፭)፤ መልአክም ሰንሰለቱን ሰበረ። እስር ቤቱ ብረት ነበር፤ ጸሎቱ ግን ብረቱን ሰበረ። “እናንተ ደግሞ አብራችሁ እንደ ታሰራችሁ የታሰሩትን አስቡ፤ በሥጋም እንዳላችሁ የሚሠቃዩትን አስቡ።” (ዕብ. ፲፫፥፫)
፪) ኅብረት፦ ብትበተኑ ይበሉአችኋል
ተኩላ መንጋውን የሚያጠቃው ሲበታተን ነው። “እርስ በርሳችን መሰብሰባችንን አንተው” (ዕብ. ፲፥፳፭)። የግቢ ጉባኤ ኅብረት ተማሪዎች የሚገናኙበት ክበብ ብቻ አይደለም፤ እርስ በርስ የሚተሳሰሩበት የደም መስመር ነው። ከዚህ የሚወጡት ወጣቶች፦ የተፈናቀሉትን መርዳት፣ የተጎዱ ቤተሰቦችን በጋራ መያዝ፣ እውነተኛውን መረጃ ብቻ ማሰራጨት (ሐሰት የሄሮድስ ቋንቋ ነውና)፣ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ድምፅን ማሰማት ናቸው። “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፤ እነሆም ያማረ ነው። እንዲል።(መዝ. ፻፴፪፥፩)
፫) ለቤተ ክርስቲያን ጥብቅና ቁም፦ በእውቀትና በቅድስና
ዘመናዊው ሄሮድስ የሚፈራው የተማረ፣ የጾመ፣ የጸለየ፣ በእምነቱ የጸናና አቋም ያለው ቆራጥ ትውልድን ነው። ስለዚህ ሐዋርያው “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ… በእውነት ወገባችሁን ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ… የመንፈስንም ሰይፍ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።” (ኤፌ. ፮፥፲፩-፲፯) እንዲል በዚህ ነው መጠንከር ያለብን፡፡
መደምደሚያ፦ “አትፍሩ”
ወገኖቼ የጌታችን ቃል ይህ ነው፦ “ሥጋን የሚገድሉ ነፍስን ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ።” (ማቴ. ፲፥፳፰) ከሞት የሚከፋው ፍርሃት ነው። የሰማዕታት ደም ቤተ ክርስቲያንን አላጠፋትም፤ አበቀላት እንጂ። ጌታ ቃል ገብቷልና፦ “በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የሲኦልም ደጆች አይችሉአትም።” (ማቴ. ፲፮፥፲፰)
እመቤታችን ምድረ በዳ በገባች ጊዜ እግዚአብሔር ቦታ አዘጋጀላት (ራእ. ፲፪፥፮)፤ ዛሬም በስደት ላሉት ቦታ ያዘጋጃል። ሄሮድስ ተነሥቶ ወድቋል፤ ዛሬም ይወድቃል። መልአኩ “ተነሣ” የሚልበት ቀን ይመጣል፤ ስደተኞቹ ማርያምና ልጇ ወደ እስራኤል ተመልሰዋል፤ ዛሬም የተሰደዱት ወደ ቀዬአቸው ይመለሳሉ፤ የፈረሰው ይታደሳል። “እግዚአብሔርም ዕንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ ኀዘንም ወይም ጩኸት ወይም ሕመም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።” (ራእ. ፳፩፥፬)
ስብሐት ለእግዚአብሔር

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!