“እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።” (ማቴ. ፲፥፲፮)
ከዲ/ን ሄኖክ ሽመልስ
“እባብ እግር የሌለው በሆዱ የሚሄድ መርዛማ የሆነ የሰው ጠላት ተንኮለኛ አውሬ ነው። (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 181 ) በመጽሐፍ ቅዱስ እባብን አስመልክቶ ሁለት ዐይነት ብያኔዎችን መኖራቸው ስንመለከት ፦
የመጀመሪያው ተንኮለኛ መሆኑን ሲሆን “ወአርዌ ምድርሰ ይጠበብ እምኩሉ አራዊተ ምድር፤ እባብም ከምድር አራዊት ሁሉ ተንኮለኛ ነበር” (ዘፍ. ፫፥፩) “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርሷ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” (ዘፍ. ፫፥፬) በሚለው በሀሰት ስብከቱ ታውቋል፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔር የሙሴን በትር ወደ እባብነት ለመለወጥና ሕዝቡንም ለመቅጣት ተናዳፊ እባብ እንደላከባቸው መረዳት ይቻላል፤ (ዘፀ. ፬፥፳፭)
ሁለተኛው እባብ በብልህነቱ ይታወቃል፡፡ ይህም የነሐስ እባብ እስራኤል በምድረበዳ ሳሉ በማጉረምረማቸው ምክንያት በእባብ መቅሠፍት ከተቀጡ በኋላ ግን ሙሴ የነሐስ እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ እንዲሰቅል ታዘዘ፤ እባብም የነደፈው ሁሉ የነሐሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ፡፡ (ዘኁ. ፳፩፥፬-፱)
በእዚህ በእባቡ አንጻር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ ለሰው ልጅ ድኅነት በቀራንዮ አደባባይ ሲሰቀል ሞተው በመቃብር ያሉት “እለ ውስተ ሲዖል ጻኡ ወእለውስተ መቃብር ተከስቱ፤ በሲዖል ውስጥ ያላችሁ ውጡ፤ በጨለማ ውስጥ ያላችሁ ተገለጡ” ብሎ ሲናገር ለዘመናት በሲዖል በእግረ አጋንንት ሲቀጠቀጡ የነበሩ ነፍሳት ሁሉ ድነዋል፡፡ በሕይወተ ሥጋ ላለነውም በሥጋና ደሙ ተቤዠን፤ “በከመ ሰቀሎ ሙሴ ለአርዌ ብርት በገዳም ከማሁ ሀለዎ ለወልደ እጓለእመሕያው ይሰቀል፤ ሙሴ የነሐሱን እባብ እንደሰቀለው የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ አለው” ተብሎ በወንጌል የተገለጸው ለዚህ ነው፡፡
እባብ ብልህ የተባለበትን ምክንያት ሊቃውንት እንደሚከተለው ያስረዳሉ፦
1. ውሀ ለመጠጣት ሲል መርዙን ከየብስ አኑሮ ነው የሚሄደው፤ ከውኃው መርዙ የገባ እንደ ሆነ ተሰራጭቶ ያጠፋዋልና እናንተም ቂም በቀል ይዛችሁ አትጸልዩ ሲል ነው፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በሥርዓተ ቅዳሴዋ “ትእዛዘ አበዊነ ሐዋርያት ኢያንብር ብእሲ ውስተ ልቡ ቂመ ወበቀለ ወቅንዓተ ወጽልአ ላዕለ ቢጹ ወኢላዕለ መኑሂ፤ ሰው በልቡናው ቂምና በቀልን ቅናትና ጠብን በጓደኛው ላይ በማንኛውም ላይ ቢሆን አይያዝ” የምትለው ይህንን ሲያመሰጥር ነው።
2. ሲያረጅ አዲስ ሰውነት ለመተካት ይጾማል። እኛም በንዝህላልነት በኃጢአት የጎሰቆለ ሰውነታችንን በንስሓ ሕይወታችን እንዲተካ መጾምና መጸለይ እንደሚጠበቅብን ያስተምረናል።
3. ከመንገድ ዳር ሲተኛ ራሱን ቀብሮ ይተኛል። ጌታችንም ራሳችሁ የምሆን እኔን(፩ኛ ቆሮ. ፲፩፥፫) አትካዱኝ፤ ርትዕት የሆነችውን ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችሁን አጥብቃችሁ ያዙ ሲለን ነው።
4. የዕፀ ዘዌ ፍሬ ሲበላ ጥላው እንዳያደክመው ጧት በምሥራቅ ማታ በምዕራብ ሆኖ ይመገበዋል፡፡ ዕፀ ዘዌ የሚባለው ዛፍ ሬውን ይወደዋል የዛፉ ጥላ ሲያርፍበት ግን ያደክመዋል፤ ብልህ ነውና ጧት በምሥራቅ ማታ በምዕራብ ሆኖ ይመገበዋል፤ ሰይጣን ምክንያት አድርጎ እናንተን የሚያደከምበትን ሥራ አትሥሩ ሲለን ነው፡፡
5. ጥግ ሳይዝ አይጣላም፡፡ ሰይጣን ምክንያት አድርጎ እናንተን የሚጣላበትን ሥራ አትሥሩ ሲለን ነው፤ ይህም ከክፉ ምግባራት ርቀን የመንፈሳዊ የጦር ዕቃ የሆኑትን እንድንላበስ ነው።
አምላካችን እንደ እባብ ብልሆች ብቻ ሆነን እንዳንቀር “እንደረግብ የዋሀን ሁኑ” አለን፡፡
እንደ እባብ ብልሆች እንድንሆን የታዘዝንበት ምክንያት፦ተኩላ በተሰኙ ዘመናዊነትና መሰል ዕሳቤዎች ምክንያት ኦርቶዶክሳዊ ማንነታችን እንዳይሸራሸር በዓለማዊ ማዕበል እንዳንሰጥም የአሕዛብና የመናፍቃን ፍላጸ እንዳያቆስለን ነው።
ርግብ የዋህ የተባለችበት ምክንያት፦
ሀ) ኀዳጌ በቀል ናት፡፡ ርግብ የዋህ ናት በቀል የለባትም፤ እናንተም ኅዳግያነ በቀል ሁኑ ሲለን ነው፤ በኖኅ ጊዜ ዋሻ መስሏት ከዘንዶ አፍ ገብታ በየውሃት ተጠብቃለች፤ እናንተም በየውሃት ሁናችሁ ተጠብቃችሁ ኑሩ ሲለን ነው።
ለ) የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ናት። ርግብ ገርና ንጽሕት ፍጥረት ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ንስሓ ከገባን በደልን የማይቆጥር ነውና በርግብ አምሳል ተገለጠ፤ ርግብ ክንፏን ቢመቷት ዕንቁላሏን ቢሰብሩባት ቤቷን ካላፈረሱባት አትሄድም። መንፈስ ቅዱስም ኃጢአት ቢሠሩ ፈጽመው ካልካዱት አይለይምና። ዳግመኛም በኖኅ ዘመን ዓለም በንፍር ውኃ ስትጥለቀለቅ የሰው ዘርም ሊጠፋ ጥቂት ብቻ ሲቀረው “የጥፋት ውኃ ጎደለ” ስትል የወይራ ዝንጣፊ በአፍዋ ይዛ ተገኝታለችና፤ የምሥራቹን ይዛ ታይታለችና፤ ይህም በኋላ ሊደረግ ላለው ነገር ምሳሌ ነው፡፡
እንደ ርግብ የዋሀን መሆን ማለት የቀደመ ሰብእናችንና ሀይማኖታችን ያለመልቀቅ እኛም በሚኖረን በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን ክርስቲያናዊ ምግባራችን ለሕዝብ ለአሕዛብ ለፕሮቴስታንት ለሁሉም ወንድሞች እና እህቶች መሆን መቻል አለበት፡፡ ክርስቶስም በወንጌሉ ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ ስለሚል፤ የእኛን ምግባር አይተው ሰማያዊ አባታችንን እንዲያመሰግኑት ማለት ነው፡፡
እንደ ርግብነታችን ስንቀርባቸው ግን የእነርሱ ክፉ ምግባር በሰውነታችን ተሰራጭቶ እንዳያጠፋን ብልህነትን መጠቀም ያሻል፡፡ በመከራ ውስጥ ብንሆንም ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ የሚተካበት ሥራ መሥራት እንደሚገባን ያስገነዝበናል፡፡
ሌላው ርግብ የኃጢአት ማዕበል ባለበት በሚያስፈራው በንፍር ውኃ ውስጥ ሆና ኖኅ ሲልካት እውነተኛ ታዛዥነቷን አስመስክራለች ፤ ምንም እንኳን የትምህርቱ ጫና ፡ የጓደኛ ተጽእኖ ቢኖርብንም እንደ ርግብ መልካም ሥራ ሠርቶ ለትውልድ ማሳለፍ ይገባል፡፡
እንዳጠቃላይ “እንደ ርግብ የዋሀን ሁኑ” ሲለን ለበጎ ድርጊት መሆኑ እና እንደ እባብ ልባሞች ሁኑ ያለን ደግሞ እኛን ሊጎዳን በሚችል ድርጊት ላይ መሆኑን በሚገባ ተገንዝበን “ኦሆ በልዎ ለእግዚአብሔር ወእምብየ በልዎ ለጋኔን ወይሴስል እምኔክሙ፤ እግዚአብሔርን እሺ በሉት ሰይጣንን ግን እምቢ በሉት ከእናንተ ይርቃል” (ያዕ. ፬፥፯) እንዲል በግቢ ያሉ ሰብእናችንን የሚያረክሱ ክፉ ድርጊቶች ሁሉ በሰውነታችን ተሰራጭተው ከጥልቁ ገዢ ከዲያብሎስ ከሚያቆራኙን እኩይ ተግባራት ሁሉ ርቀን፤ መንፍሳዊ ተገባራት ሁሉ ተሳትፈን ለተፍጠርንለት ዓላማ ለመንፈሳዊ አገልግሎትና ለእግዚአብሔር መንግሥት እንድንበቃ መሆን ይጠበቅብናል፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!
