“ባሕር አየች፣ ሸሸችም” (መዝ. ፻፲፫፥፫)

በዲ/ን አሻግሬ አምጤ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ተነሥቶ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ፣ በዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ ባሕር ሸሸች፣ ዮረዳስም ወደ ኋላ ተመልሷል፡፡ ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የወረደው በጥምቀቱ ክብር ሊያገኝበት፣ የጎደለው ነገር ኖሮ ሊመላበት ሳይሆን እኛም ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን ልጅነትን እንድናገኝ፣ በኃጢአት ምክንያት ጎድሎብን የነበረው እንዲሞላልን፣ አጥተነው የነበረው ልጅነት እንዲመለስልን ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “አጥምቀኒ በማይ ከመ ይትቀደስ ማይ በማእከለ ሰማይ” በማለት የዘመረው ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ የወረደው በአንጻረ ዮርዳኖስ ውኃዎችን ሁሉ ለመባረክ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ረግቶ የሚኖር ውኃ በማዕበል ሲመታ እንደሚጠራ ሁሉ የሰው ልጅ ከአምላኩ በመጣላቱ ውኃ የሞት ምክንያት ሆኖ ስለነበር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ በመጠመቁ የሕይወት መድኅን አድርጎ ባሕርይውን ሳይሆን ግብሩን ለወጠው፡፡

የጌታችን ጥምቀት ልጅነት ያገኘንበት ቢሆንም በየዓመቱ ወንዝ ዳር ወርደን የምንጠመቀው ግን   ልጅነትን ለማግኘት ሳይሆን የተከፈለልንን ዋጋ ለማስታወስ ነው፡፡ በየዓመቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓል እና በውኃ መረጨታችን በረከት ለማግኘት፣ ትውፊቱን ለማስቀጠል እና የተከፈለልንን ውለታ ለማስታወስ የምንፈጽመው ነው፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት የሥላሴ አንድነትና ልዩ ሦስትነት የተገለጠበት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት በተመለከተ በተለያዩ መንገዶችና ሁኔታዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ታላቅ ምሥጢር በይፋ ከተገለጠባቸው መንገዶች አንዱ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ፣ በማእከለ ዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ አብ በደመና ሆኖ ተገልጧል፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ወንጌል “ጌታችን ኢየሱስም ወዲያው ከውኃው ወጣ፡፡ እነሆ ሰማይ ተከፈተ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ እነሆም ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ” በማለት የረገልጸዋል፡፡ በዚህም የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት እንረዳለን፡፡ (ማቴ.፫፥፲፮-፲፯)

የዮርዳኖስ ውኃ ፈርታ ወደ ኋላዋ መመለሷ ሰማይና ምድር መሸከም የማይቻላቸውን እኔ እንዴት እችለዋለሁ? ብላ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጌታችን ለዚህ ክብር ስለመረጣት ደስታዋን መቋቋም ተስኗት ወደ ኋላዋ ተመልሳ፣ ለዝማሬ አሸብሽባለች፡፡ ነቢዩ ዳዊት “ባሕር አየች ሸሸችም ፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ” በማለት የዘመረው ለዚህ ነው፡፡ (መዝ. ፻፲፫፥፫)

የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ እንዲሁም ትሕትናንን ለማስተማር (አርአያ ሊሆነን)  በዮርዳሰኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔርንም የመምስል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፡፡ በሥጋ የተገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ» (፩ኛ. ጢሞ. ፫፥፲፮) በማለት የተናገረለት ጌታ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በዮሐንስ እጅ መጠመቁን ትውፊት አድርገው ታቦታት ከመንበራቸው ተነሥተው ወንዝ ዳር አድረው ውኃውን ባርከው ይመለሳሉ፡፡ በዚህም መሠረት “በዓለ ጥምቀት የሚከበረው ከወንዝ ዳር ነው፡፡ ወንዝ ከሌለ ግን ክብ ቅርጽ ባለው ነገር ውስጥ ውኃ ይዘጋጃል፡፡ በከተራ ከማደሪያቸው የሚወጡ ታቦታት በወንዝ ወይም በተዘጋጀ የውኃ አካባቢ ያድራሉ፡፡ ይህም ክርስቶስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመውረዱ ምሳሌ ነው፡፡ እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን የሚመሰለው በገሊላ ነው፡፡ ታቦታቱ የሚያድሩባቸው ሁሉ በዮርዳኖስ ይመሰላሉ፡፡

ጌታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በመሄዱ በአንጻረ ዮርዳኖስ ውኃዎች ሁሉ እንደተባረኩ፣ ታቦታትም መንበረ ክብራቸውን ለቀው ወንዝ ዳር አድረው ውኃውንም፣ አካባቢውንም ባርከው ወደ መጡበት ይመለሳሉ፡፡ በዓሉን የምናከብረውም ይህን ትውፊት አድርገን በረከት እናገኝ ዘንድ ነው፡፡

በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመን ታቦታት ጥር ፲፩ ቀን ከመንበራቸው ወጥተው በዕለቱ ተመልሰው እንዲገቡ ሥርዓት ተሠርቶ ነበር፡፡ በቅዱስ ላልይበላ ዘመን ደግሞ በከተራ ዕለት ወይም በዋዜማው ከመንበራቸው ወጥተው ጥምቀተ ባሕር ከሚፈጸምበት ቦታ አድረው በማግስቱ ይመለሱ ነበር፡፡ በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ደግሞ ሁሉም አካባቢ በረከት እንዲያገኝ ወይም እንዲባረክ ታቦታት በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ የሚል ሥርዓት ተሠራ፡፡ ይህም በዓሉን ለማክበር በመሄዳችን ከመንበራቸው ወጥተው ወንዝ ዳር አድረው በሚመለሱ ታቦታት የምንባረክ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *