“ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።” (ኤፌ. ፭፥፲፮)

ዲ/ን በረከት አዝመራው

መግቢያ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን “ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ናት፤ በዓለም ውስጥም ትኖራለች፤ ነገር ግን ዓለማዊ አይደለችም”፡፡ (ዮሐ.፲፯፥፲፮) ለመሆኑ ጌታ ከቤተ ክርስቲያን በተቃራኒ ያቆማት “ዓለም” ምንድር ናት? ኦርቶዶክሳዊ ክርስትናችን ከዓለም ጋር የሚቃረንባቸው ዕሴቶቹ ምን ምን ናቸው? በዓለም ስንኖር ክርስትናችንን ሳንጎዳ ለመኖር ምን እናድርግ? በዚህ ጽሑፋችን እነዚህን ነጥቦች በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

ሀ. ዘረኝነትን በጽናት መቃወም፡-

ዘረኝነት የሰውን ልጅ ድንቅ እና ክቡር ተፈጥሯዊ አንድነት የሚያስክድ እና ከክርስትና በተፃራሪ የቆመ አስተሳሰብ ነው። ልዩ ልዩ ቋንቋዎች፣ ቀለሞች፣ ታሪኮች እና ባህሎች በሰው ልጆች መካከል ቢኖሩም ክርስትና ግን ከዚህ ሁሉ ከፍ ባለ በአዲስ ተፈጥሮ ሰውን አንድ የሚያደርግ ነው። (ራእ.፭፥፱) በአሁኑ ዓለም የተፈጥሮ ሀብትን እና ሥልጣንን ለመቀራመት የሚፈልጉ አካላት ዘረኝነትን እንደ መሣሪያ እየተጠቀሙ በመሆናቸው ክርስቲያኖችን እርስ በእርስ የሚያባላ መጥፎ በሽታ ሆኗል። እኛ ክርስቲያኖች ግን ከዚህ ወጀብ በተቃራኒ በመቆም የሰውን ልጅ ሁሉ በመስቀሉ ወደ አንዲት ዘለዓለማዊት መንግሥቱ የሚሰበስበውን የአምላካችን ክርስቶስን ፈቃድ መፈጸም ይገባናል። (ዕብ.፲፪፥፳፪)

ለ. ዓለማዊነት (Secularism) በብስለት መምራት፡-

“ዓለማዊነት (Secularism)” ማለት ይህን የሚታየውን ዓለም መዳረሻ አድርጎ መኖር ነው፡፡ ዓለማዊነት እግዚአብሔርን መጥላት እና የሚታየውን እና ጊዜያዊውን ተድላ ደስታ መውደድ ነው፡፡ ዓለማዊነት ፍጥረታትን ወድዶ ፈጣሪያቸውን መጥላት ነው፡፡ (፩ኛዮሐ. ፪፥፲፭፣ ያዕ.፬፥፬) ይህ ዓለም በራሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት ስለሆነ ክፉ ነገር አይደለም፡፡ (ዘፍ. ፩፥፴፩) ፍጥረታትን በራስ ወዳድነት መበዝበዝ (Utilitarianism) እንጂ እንጠቀምባቸው ዘንድ እግዚአብሔር የፈጠረልንን ፍጥረታት በሥርዓት ከምስጋና ጋር በፍቅር መጠቀም ዓለማዊነት አይደለም፡፡ በአጭር አገላለጽ ዓለማዊነት ማለት በሥጋዊ ፈቃድ የዓለምን መሻት በመፈጸም በኃጢአት ውስጥ መኖር ነው፡፡

እግዚአብሔርን እንኳ ለዚህ ዓለም ብቻ ተስፋ አድርገው ‘ሊበዘብዙት’ የሚሞክሩ “’መንፈሳውያን’ ዓለማውያን (‘Spiritual’ Seculars)” እንዳሉ ይታወቃል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፲፱) ከላይ በዘረዘርናቸው ምክንያቶች ዓለማዊነት በልቡ ውስጥ ያደረበት ሰው ለኃጢአት ሁሉ የተጋለጠ ነው፡፡ ለኃጢአት የተጋለጠ መሆን ብቻም ሳይሆን ኃጢአትን ማስተባበልንም እና ራሱን ትክክል አድርጎ መቁጠርም ይጠናወተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ዓለማዊነት ከክርስትና እሴቶች ጋር የሚጋጭ አስተሳሰብ በመሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ራሳችንን ከዓለማዊነት እንድንጠብቅ ደጋግመው ይመክሩናል፡፡ (፩ኛዮሐ.፪፥፲፭፣ ያዕ.፬፥፬)

ሐ. በኦርቶዶካሳዊ ክርስትናችን መጽናት፡-

ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ያልተበረዘ ያልተከለሰ ጥንታዊ እና ርቱዕ (ቀጥ ያለ) ክርስትና ማለት ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ስንል ሰዎች በዕውቀታቸው ልክ ያላጠበቡት፣ ለሥጋ ድካማቸው እንዲመች አድርገው ያላሻሻሉት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው፣ ሐዋርያት የሰበኩት ቅዱሳን ሊቃውንት አበው የጠበቁትን ንጹሕ ክርስትና ማለታችን ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ክርስትና “አንድ ጊዜ ለቅዱሳን ፈጽማ የተሰጠች” ሃይማኖት ናት፡፡(ይሁዳ ቁ.፱)

ኦርቶዶክሳዊነት እውነተኛ ሃይማኖት፣ እውነተኛ አምልኮ እና እውነተኛ አኗኗር የተካተቱበት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው እኔ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነኝ ሲል የሐዋርያትን ሃይማኖት፣ የሐዋርያትን ሥርዓተ አምልኮ እና ሐዋርያት የኖሩትን እና በጽሑፍም በቃልም ያስተማሩትን ክርስቲያናዊ አኗኗር እከተላለሁ እያለ ነው፡፡ (ገላ ፩፥፰፣፪ኛተሰ.፪፥፲፭)

ሐዋርያት የኖሩበት እና በጽሑፍም በቃልም አስተምረውት ለእኛ በትውልድ ቅብብል የደረሰው ክርስቲያናዊ አኗኗር ምን ዓይነት ነው? ሐዋርያት ያስተማሩን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያነቱን እና ትምህርቱን ተከትሎ በተግባር መፈጸም፣ በኃጢአትና በክሕደት ላለመያዝ ራስን ገዝቶ መኖር፣ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር መሳተፍ፣ ይህ ዓለም ለሚመጣው ዓለም መሻገሪያ እንጂ መጨረሻ አለመሆኑን አምኖ በሰማያዊ ልቡና እና በአምላካዊ ተስፋ መኖር ተገቢ ነው፡፡

ማንኛውም በዚህ ዓለም ያለ ነገር ከዚህ እምነታችን እና አኗኗራችን ካናወጠን እና መሰናክል ከሆነን ዓለማዊነት እያጠቃን ነው እንላለን፡፡ ምንም እንኳ ዓለማዊነት በየዘመናቱ ያለ ቢሆንም በተለይ በዘመናችን ለዓለማዊነት እንድንጠቃ የሚያደርጉን ከዘመኑ ተግዳሮቶች (challenges) መካከል ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር የሚመጡ ተግዳሮቶች፣ በሉላዊነት (Globalization) ምክንያት እንግዳ የሆኑ አስተሳሰቦች መስፋፋት፣ ኃጢአትን የተለማመደ የባህል ወረራን መፍትሔያቸውንም እየጠቆምን እንመለከታለን፡፡

መ. ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ  ያመጣቸውን ተግዳሮቶች መቋቋም፡-

ሳይንስና ቴክኖሎጂ በራሱ መልካም የሆነ እና ኑሮን የሚያቀል የሰው ልጆች ውጤት በመሆኑ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ መስፋፋት የተነሣ ክርስትና የሚፈተንባቸው አጋጣሚዎች ደግሞ በርካታ ናቸው፡፡

ይህንም በሁለት መንገድ ማየት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ፈተና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ብዙ ተስፋ በመጣል ሳይንስና ቴክኖሎጂን እንደ አዳኝ (Savior) መቁጠር ነው፡፡ ይህ በምዕራቡ ዓለም ትልቅ ፈተና እየሆነ መጥቷል፡፡

በርግጥ የሳይንስን ታሪክ እና ፍልስፍና ያጠኑ ምሁራን እንደሚጠቁሙት ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዋናው ጥቅሙ የሰውን ልጅ የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማቅለል እና ለማሳለጥ እንደሆነ እና ከዚያ ያለፈ በሳይንስ ላይ የተጣለ ተስፋ ባለፉት ፬፻ ዓመታት እንዳልተሳካ ነግረውናል፡፡

በመጀመሪያዎቹ የ’አብርሆት’ ዘመናት (በ፲፮ኛው መ/ክ/ዘመን አካባቢ) ሳይንስ የሰውን ልጅ ሕይወት በእጅጉ እንደሚቀይር እና ምድርን ገነት የሚያደርግ እንደሚሆን ይገመት ነበር፡፡ ነገር ግን እንደተባለው አልሆነም፡፡ ይልቁንም ከዚያ በኋላ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሁለቱ ታላላቅ የዓለም ጦርነቶች ያደረሱት የሚሊዮኖች ሞትና ሥቃይን ነው፡፡ በዓለም ላይ የተከማቸው እና በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ የሚችለው የኒዩክሌር የጦር መሣሪያዎች ክምችት (Nuclear Arsenal) ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት የጥቅሙን ያህል ጉዳቱ ብዙ እና አደገኛ እንደሆነ ያስገነዝበናል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሳይንስ ለጥናት የሚጠቀምበት ዘዴ (Scientific Method) በእግዚአብሔር መንፈስ የተቃኙት የቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምህሮ ባለማካተቱ ሳይንስ ገና ከጅማሬው በሕይወት ትርጉም ያልሰጠ (Life Values) የተገደበ እና ጉድለት ያለበት ነበር፡፡ በመሆኑም የሰውን ልጅ የዕለት ተዕለት ኑሮ ከማቅለል ውጭ የሕይወት ትርጉም ያላቸውን ዘላለማዊ ጥያቄዎቹን ሊመልስ መንፈሳዊ ዕሴቶቹንም ሊያስቀጥል አልቻለም፤ ወደፊትም አሁን ከሚሄድበት መንገድ የተሻለ የመንፈሳዊ ሕይወት ሊኖረው አይችልም፡፡

ይህም የሳይንስን ፍልስፍና በሚያጠኑ እውነተኛ ምሁራን ዘንድ የታወቀ ቢሆንም በተራው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ዘንድ ግን ብዙ ጊዜ ሳይንስ ካቅሙ በላይ የሆነ ተስፋ ሲጣልበት እናያለን፡፡ ይህ ያለአግባብ ተስፋ ብዙ ሰዎች እግዚአብሔርን መፈለጋቸውን እንዲተዉ እና ሳይንስን ሃይማኖት አድርገው እንዲያዩ አድርጓቸዋል፡፡ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ይህን ማወቅ እና ራሳችን ከዚህ አስተሳሰብ መጠበቅ ይገባናል፡፡ ካልሆነ ግን “በሰው የሚታመን፣ ሥጋ ለባሽንም ክንዱ የሚያደርግ፣ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው” የሚለው ቃል ይደርስብናል፡፡ (ኤር. ፲፯፥፭)

ሌላው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈተና ሰውን በክፉ ምኞት ማማለሉ እና በቀላሉ ከኃጢአት ጋር የሚገናኝ ማድረጉ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የመቀያየር አባዜ ተጠናውቷቸው የሚናውዙ ብዙዎች ናቸው፡፡ በኢንተርኔት የዝሙት ምስሎችን (Pornography) በመመልከት እንዲሁም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች (Facebook እና የመሳሰሉት) ያለአግባብ ብዙ ጊዜ የሚያጠፉ እና አእምሯቸውን እና ኅሊናቸውን የሚያበላሹትም ጥቂቶች አይደሉም፡፡

እኛ እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያንነታችን ቴክኖሎጂን በአግባቡ እና በሚያስፈልግበት ጊዜ እና ቦታ መጠቀምን መልመድ ይኖርብናል፡፡ ካልሆነ ግን ከክርስትና እና ከዘላለማዊ ሕይወታችን የሚነጥለን የዘመኑ የዓለም ወጥመድ ይሆናል፡፡

ሠ. ከሉላዊነት እንግዳ አስተሳሰቦችን መዋጋትን መዋጋት፡-

ከሉላዊነት ጋር ተያይዞ በዓለም ላይ ብዙ “እንግዳ” አስተሳሰቦች ይደርሱናል፡፡ ብዙዎቹ አስተሳሰቦች አዲስ ባይሆኑም በመረጃ ሉላዊነት የተነሣ በሌላው የዓለም ክፍል አዲስ ያልሆኑት እኛ ዘንድ አዲስ የሚሆኑበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች አእምሮውን አምታተውበት ራሱን  ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚያርቅ ይኖራል፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ግን ልቡናችንን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ማጽናት አለብን፡፡ ሐዋርያው “ልዩ ልዩ በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ይጽና” እንዳለው አዲስ ነገር በሰማን ቁጥር የምንደነግጥ እና የምንደናበር መሆን የለብንም፡፡ (ዕብ. ፲፫፥፱) ልባችን በጸጋ እንዲጸና ምን ማድረግ አለብን? ኦርቶዶክሳዊ ክርስትናን በሚገባ ለመረዳት መጣር፣ ራስን ከኃጢአትና ከክፉ ምኞት ለመጠበቅ መጋደል፣ በንስሓ ውስጥ ሆኖ ከቅዱስ ቊርባን አለመራቅ፣ ጸሎትን ማዘውተር የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ጥረቶች ማድረግ አለብን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ “ዓለምን የሚያሸንፈው እምነታችን ነው” እንዳለው እምነታችን በጸጋ እግዚአብሔር ማጽናት ይገባናል፡፡ (፩ኛዮሐ.፭፥፭)

ረ. ኃጢአትን የተለማመደ መጤ ባህል መስፋፋትን መግታት፡-

ባለንበት ዘመን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ተግዳሮት ከሚሆኑ ነገሮች በዘመናዊነት ስም እየተስፋፋ ያለው የክፉ ባህል ወረርሽኝ አንዱ ነው፡፡ እውነተኛ ዘመናዊነት በዘመን ላይ መሠልጠን እንጂ ዘመን ያመጣው መጥፎ ነገር ሰለባ መሆን አይደለም፡፡

በዚህ ዘመን ልንሸሻቸው ከሚገቡን ክፉ ነገሮች አንዱ እየተስፋፋ ያለውን ኃጢአትን የተለማመደ ባህል ነው፡፡ የእኛ የኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ባህላችን ክርስቲያናዊ ነው፡፡ አሁን ግን እንግዳ የሆነ እና ኃጢአት ትክክል ሆኖ የሚቆጠርበት ባህል አኗኗራችን እየተፈታተነው ይገኛል፡፡ ይህ እያጠቃቸው ያሉ ደግሞ ለመገናኛ ቴክኖሎጂ እና “ለዘመናዊነት” ቅርብ የሆኑ በከተማ የሚኖሩ ወጣቶችን ነውና እንቅስቃሴውን ልንገታው ይገባል፡፡

ወጣቶች ልንገነዘበው የሚገባው ኃጢአት ዘመናዊነት እንዳልሆነ ነው፡፡ ይህም ማለት ከማኅበረሰባዊ ዕሴቶቻችንና ከሃይማኖታችን አስተንህሮ ባፈነገጠ የመጤ ባህል ተፅዕኖ ሥር ነውደቅ በኃጢአት ወጥመድ ውስጥ መውደቅ እንጂ መዘመን (ዘመናውያን መሆን) አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ኃጢአት ዘመናዊነት አይደለም ምንለው፡፡ ዘመናዊነት ዘመን የወለዳቸውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ዘመኑን ለዋጀ አገልግሎት ማዋል ነው፡፡ ሁል ጊዜ የማያረጀው ዘመናዊነት እና አዲስነት ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው፤ ሁል ጊዜ አዲስ ሆኖ የሚኖር እና የማይለወጥ እግዚአብሔር ብቻ ነውና፡፡ (መዝ. ፻፩፥፳፭-፳፰፣ ራእይ. ፳፩፥፭) የአካል መቆሸሽ በምንም አመክንዮ ዘመናዊነት እንዳልሆነ ሁሉ በኃጢአት መቆሸሽም ዘመናዊነት ሊሆን አይችልም፡፡ ዲያብሎስ ኃጢአትን ከጥንት ጀምሮ ብዙ ጭምብል አልብሶ ያመጣል፤ በዘመናችን ደግሞ የሥልጣኔን ጭምብል ለብሶ ነው የመጣው፡፡ ምንም ቢሆን ግን ኃጢአት ከኃጢአትነቱ ሊወጣ አይችልም፡፡

ከእኛ ከክርስቲያኖች የሚጠበቀው ግን ባህልን መቀደስ እንጂ በክፉ ነገር መወሰድ አይደለም፡፡ ጌታችን “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ … እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” ማለቱ እኛ ዓለምን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ እንደሚገባን ሲነግረን ነው፡፡ ለዚህም ከእኛ በኩል ጥረት ይፈለጋል፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ደግሞ ኃይል ይገኛል፡፡ (ማቴ. ፭፥፲፫-፲፬፣ ዮሐ. ፲፭፥፭)

እንግዲህ ከላይ የዘረዘርናቸውን ነገሮች በክርስትና ትዕዛዛት እየመረመርን መልካሙን በመያዝ፣ ክፉውን በመተው ዘመኑን መዋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ጌታችን በወንጌል እንዳስተማረን እኛ ዓለምን ወደ ብርሃን ማምጣት ይገባናል እንጂ ዓለም ወደ ጨለማው የሚጎትተን ልንሆን አይገባም፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *