ክርስትና “አክራሪነት”ን የሚያበቅል ነገረ ሃይማኖታዊ መሠረት የለውም

ነሐሴ 21 ቀን 2005 ዓ.ም.
 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የሃይማኖት “አክራሪነት” ስጋት እንዳለ በተለያዩ ወገኖች የሚነሣ ሐሳብ አለ፡፡ የ “ሃይማኖት አክራሪነት” በሀገራችን የለም የሚል እምነት አይኖርም፡፡ “አክራሪነት” የሚተረጎመውም የራስን የሃይማኖት የበላይነት ለማስፈን ሲባል ሌላው የሃይማኖት ሐሳቡን እንዳይ ገልጥ፣ ተግባራዊ የአምልኮ ሥርዓቱን እንዳይፈጽም ማድረግ፣ በኃይል ወይም በዐመፅ ቦታ ማሳጣት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አንድ ቤተ እምነት ራሱ ከሚከተለው እምነት ውጪ ያሉ በቁጥር ትንሽ ወይም ብዙ ተከታይ ያሏቸው እምነቶች በአንድ ሀገር ወይም ቦታ መኖር የለባቸውም ብሎ ማመን ወይም ማድረግ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ የሰዎችን የፈቃድ ነጻነት፣ ምርጫ አለማክበር፤ አለመጠበቅ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰው አስተሳሰብ ደግሞ በምንም መስፈርት ቢመዘን ክርስትና ሊሸከመው የሚችለው አይደለም፡፡ የሚጋጨውም ከክርስትና መሠረታዊ ባሕርይና አካሔድ ጋር ነው፡፡ ክርስትና ወደ ሰዎች የመጣው በራሱ በሥግው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራና ቃል ነው፡፡ ጌታችን ወደ ሰዎች ቀርቦ ወደ እርሱ እንዲመጡ የሳባቸው የፈቃድ ነጻነታቸውን ጠብቆ ነው፡፡ በደዌ ነፍስ የተያዙትን በትምህርቱ፣ በደዌ ሥጋ የተያዙትን በተኣምራቱ ሲፈውስ ሁሉንም “ልትድን ትወዳለህን” እያለ ፈቃዱን ጠይቆ የፈጸመው ነበር፡፡ ልባቸው ወደ እርሱ ያዘነበሉትን “ተከተሉኝ” ብሎ ወደ መንግሥቱ እየጋበዘ ከእርሱ ኅብረት ደምሯቸዋል፡፡ “ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዐሳርፋችኋለሁ” ብሏቸዋል፡፡

ጌታችን ያለፈቃዳቸው ከጉባኤው የደመራቸው ወገኖች አልነበሩም፡፡ ተሰብስበውም ከነበሩት የሚያስተምረው ኃይለ ቃል ከምስጢሩ ታላቅነት የተነሣ የጸነናቸው ታዳሚዎች እንኳን ጥለውት በሔዱ ጊዜ አልተቃወመም፡፡ በእግሩ ስር የቀሩ ሐዋርያቱንም “እናንተስ ልትሔዱ ትወዳላችሁን” እያለ ደቀመዛሙርቱን እንኳን ፈቃዳቸውን ያረጋግጥ ነበር እንጂ፤ ከዋልኩበት ውላችሁ፣ ካደርኩበት አድራችሁ፤ አበርክቼ አብልቼ፣ በፍቅሬ ረትቼ፤ በተአምራቴ ፈውሼ፣ ተኣምራት የምትሠሩበትን ኃይል አልብሼ ካቆየኋችሁ በኋላ ስለምን ትተውኛላችሁ ብሎ አምላካዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ሊጫናቸው አላሰበም፡፡ በመሆኑም ክርስትና “ከአንተ ወደ ማን እንሔዳለን” ያሉ ቅዱሳን ሐዋርያትና በሐዋርያት ትምህርት የጸኑ፣ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚነሡ ምእመናን በፈቃዳቸው የሚኖሩበት ሃይማኖት ነው፡፡   

ጌታችን እንድንቃወም ያስተማረን ሌሎችን በኃይል ወደ እርሱ መሳብን ብቻ ሳይሆን ሊያስገድዱን የሚመጡ፣ መልካሙን እንዳንፈጽም የሚከለክሉንንም ቢሆን በኃይል ለመቋቋም መሞከርንም ነው፡፡ ጌታችን ለጴጥሮስ “ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉ፤ ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ” ያለው ለዚህ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ክርስትና በባሕርዩ “አክራሪነት”ን የሚያስተ ናግድበት መስክ የለውም፤ በጽኑም ይቃወመዋል፡፡

ክርስትና ሰዎች የእምነት ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ አይገ ድብም፡፡ ሌሎች በእምነቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄ እንዳያቀርቡም አይከለክልም፡፡ ስለያዘው እውነት በራሱ የሚተማመን ሃይማኖት ነው፡፡ ስለሆነም እርሱም ይሔንኑ መብት በጽኑ ይፈልገዋል፡፡ ለሚጠይቁት ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጀ፣ የራሱን የድኅነት መንገድ ለመመስከር የተሰማራ ሃይማኖት ነው፡፡ የክርስቶስን መንግሥቱንና ጽድቁን ለሚሹ ሁሉ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ ይጮኻል፡፡ ስለዚህ ክርስትና የ “አክራሪነት” ሐሳብ ከመሠረቱ ሊበቅልበት የማይችል ሃይማኖት ነው፡፡

በተግባርም ቢሆን ከቤተልሔም ዋሻ አንሥቶ እስከ ምድር ጥግ እንዲስፋፋ ያስቻለው በረድኤተ እግዚአብሔር ተደግፎ፣ በፍቅር ስቦ፣ በመግደል ሳይሆን በመሞት የብዙዎችን ነፍስ ለመታደግ የሚኖር ሃይማኖት በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የቃለ ሃይማኖቱን ኃይል የተአምራቱን ብዛት የአማኞቹን ጽናት አይተው የራሳቸውን እምነትና ፍልስፍና ለመጫን የሞከሩበትን አምልኮ ባዕዳንን ይከተሉ ከነበሩ ወገኖች ጀምሮ ሃይማኖትን የዕድገት፣ የነጻነት፣ የፍትሕ፣ የእኩልነት ወዘተ ጸር አድርገው እስከሚያስቡ የማርክሲዝም ሌኒንዝም ተከታዮች ድረስ የነበሩ “አክራሪዎች” ክርስትናን ሊያጠፉት ሲሞክሩ ታይቷል፡፡ ነገር ግን ሰይፋቸውን በትዕግስት ተቋቁሞ፣ እነርሱ እያለፉ እርሱ ሳያልፍ ዘላለማዊ ሆኖ እዚህ የደረሰ ሃይማኖት ሆኗል፡፡

ክርስትና በ“አክራሪነት” ሲመላለስ አልኖረም፡፡ በክር ስትና ስም የሚፈጸሙ ወይም በታሪክ ወስጥ የተፈጸሙ አሁን “አክራሪነት” ያልነው ጠባይ የተንጸባረቀባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩ እንኳን በክርስትና ስም ልንቀበለው የምንችለው አይሆንም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም “ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚል የፍቅር ቃል ሰጥተውናል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ሐዋርያዊ ውርስ ያላት ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ስትሆን እነዚህ ከላይ የተሰጡ፣ ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርትና ቅዱሳን ሐዋርያት ያስተላለፉትን መልእክት ታከብራለች፤ ትጠብቃለች፤ ነገረ ሃይማኖታዊ መሠረቷም ይኸው ነው፡፡

ስለዚህ ቤተክርስቲያን የእኔ ናቸው በምትላቸው ሕጋዊ መዋቅሮቿ፣ በመዋቅሮቿም ላይ የሚያገለግሉ አገልጋይ ካህናትና ምእመናን ሰንበት ትምሀርት ቤቶችና ማኅበራት ሁሉ ከላይ ከተጠቀሰው ክርስቲያናዊ መንገድ የወጣ በ”አክራሪነት” የሚታሰብባቸውን ተግባራት ሊፈጽሙ አይችሉም፤ ካደረጉም ቤተ ክርስቲያኒቱ ባላት ቀኖናዊ ሕግ መሠረት ይዳኛሉ፡፡ ይታረማሉ፤ ካልሆነም ይለያሉ፡፡

ቤተክርስቲያን ያላት ነገረ ሃይማኖታዊ ሐሳብ ይህ መሆኑን ከተስማማን፣ በዚህ መሠረታዊ አስተምህሮዋ ላይ ቅሬታ የሌለን ከሆነ፣ መልካምነቱን የምንረዳ ከሆነ፣ በዚህ ላይ ያልበቀለ፣ ያላፈራ፣ መልካም ያልሆነ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ካለ መመርመር ይገባል፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራልና፤ ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያፈራል፤ መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬን ማፍራት፣ ክፉ ዛፍም መልካም ፍሬን ማፍራት አይችልም፤ መልካም ፍሬን የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል እግዲህ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” /ማቴ 7፥17/ ያለው ቃሉን እናስባለን፡፡ 

 
ማኅበረ ቅዱሳንም ከዚህ የወጣ አካሒድ ሊኖረው አይችልም፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ያለ ሓላፊነት የሚሰማው የአገልግሎት ማኅበር ነውና፡፡ “አክራሪነት”ን በመቃወምና የሃይማኖቶችን መከባበር ተገቢነት አስመልክቶ በተደጋጋሚ በገለጻቸው አቋሞቹ አስታውቋል፡፡ ለዚህም በሐመር መጽሔት በግንቦት ወር 2001 ዕትም፣ ስምዐ ጽድቅ በርእሰ አንቀጹ በጥቅ ምትና በኅዳር 1999 ዕትም፣ መጽሔተ ተልእኮ ዘማኅበረ ቅዱሳን በምንለው የማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት መጽሔት በነሐሴ 2004 ዓ.ም ዕትም በዚሁ ጉዳይ ያለውን አቋም ገልጿል፡፡  

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ “አክራሪነት” እንዳለና አልፎ አልፎም “ማኅበረ ቅዱሳን” ብለው በስም ጠቅሰው ለመፈረጅ የሞከሩ በአንዳንድ አካባቢ ያሉ መንግሥት ያዘጋጀውን የውይይት መድረክ የተጠቀሙ አስፈጻሚዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ አልፎ አልፎ መንግሥት “አክራሪነት”ን ለመከላለከል ለሚወስዳቸው እርምጃዎች አጋዥ የሚሆን ውይይት በየደረጃው በሚያደርግበት አጋጣሚ የማኅበረ ቅዱሳንን ስም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይታያል ላሉት “አክራሪነት” ማሳያ አድርገው ማቅረባቸው ለማኅበሩ አባላት ደስ የሚያሰኝ አልነበረም፡፡

“አክራሪነት” ከላይ በጠቀስነው እሳቤ መሠረት የሚታይ ከሆነ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ላሳዩት የ‹‹አክራሪነት›› ጠባይ ግልጽና ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ያሻል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ ቀደምም ከማንም በፊት በሀገራችን የአክራሪነት ዝንባሌዎች እንዳሉ በማመልከት በኩል ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል፡፡ “አክራሪዎች” በተለያዩ አካባቢዎች አብያተክርስቲያናትን ሲያቃጥሉ ክርስቲያኖችን ሲያርዱ አካሔዱ መልካም አለመሆኑን በመጠቆም እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ በማሳሰብ ሀገራዊ ሓላፊነቱን ለመወጣት ሞክሯል፡፡ የሃይማኖቶች መከባበር በመላው ሀገሪቱ እንዲሰፍን ያለውን ቁርጥ አቋምም አንጸባርቋል፡፡

በእርግጥ ማኅበረ ቅዱሳን ቤተክርስቲያናችን ጠንካራ የአስተዳደር፣ የአሠራር፣ የአገልግሎት አካሔድ እንዲኖራት አቋም ይዞ የሚያገለግል ማኅበር ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ካህናትና ምእመናን ሁሉ የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቃል አክብረው፤ የሐዋርያትን የሊቃውንት አባቶችን የሃይማኖት ትምህርት፣ ሥርዓት፣ ታሪክና ትውፊት አውቀው እንደ ሃይማኖቱ ሕግና ሥርዓት እንዲመላለሱ ያተጋል፡፡ የተዘጉ አብያተ ክርስቲ ያናት እንዲከፈቱ፣ ሊቃውንቱ በረሃብ በችግር ተፈተው ከአገልግሎት እንዳይቦዝኑ ለማድረግ ይተጋል፡፡ የሌላ ቤተእምነት ተከታዮች በቤተክርስቲያን ትምህርት ላይ ለሚያነሧቸው ጥያቄዎች መልስ በመስጠት የዕቅበተ እምነት ሥራ ይሠራል፡፡

 

በኮሌጅና በዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ካደጉበት መንደር /ቀዬ/ ርቀው ወደ ተለያዩ ትምህርት ተቋማት ሲመጡ በአቅራቢያ በሚገኙ አጥቢያዎች ሰብስቦ በሃይማኖታቸው ተጠብቀው እንዲኖሩ፣ በመልካም ሥነምግባር ታንጸው ሀገራቸውንና ቤተክርስቲ ያናቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ፣ ከሱስና ከዝሙት ተጠብቀው ከደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ እንዲርቁ ያደርጋል፡፡ በጠረፋማ አካባቢዎች ስብከተ ወንጌልን ያስፋፋል፡፡ በጤናና ትምህርት ጉዳዮችም በማኅበራዊ አገልግሎት ተሳትፎ እንዲኖረው እየጣረ ነው፡፡ እነዚህ ተግባራቱ ሁሉ ከቤተክርስቲያኒቱ የአገልግሎት መንፈስ የተቀዱ ናቸው፡፡ ለየትኛውም ወገን ቢሆን የሚጠቅሙ እንጂ ስጋት የሚሆኑ ተግባራት አይደሉም፡፡ በሃያ ዓመት የአገልግሎት ቆይታውም ያስመዘገባቸው ውጤቶች በስጋት ሳይሆን በአስፈላጊነት ሊያስፈርጀው የሚችል ነው፡፡

ስለዚህ የትኛውም ወገን ቢሆን እውነታውን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ቸግሮች አሉ ቢባሉ እንኳን ተገቢነት ከሌላቸው ዘመቻዎች ቆጠብ ብሎ ከቤተክርስቲያኒቷ አባቶችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አግባብነት ያላቸው ውይይ ቶችን ማድረግ በቂ ይሆናል፡፡ ማኅበሩ የቤተክርስቲያኒቱ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሠራ ከሰጠው ተግባራት ውስጥ ወደ ‹‹አክራሪነት›› አምባ ያስገባውን ወሰን አለፈ ያስባሉትን ነጥቦች ነቅሶ ማሳየት፣ እንዲህ የሚያስብሉ የተፈጸሙ ተግባራትንና ተግባራቱን ማኅበሩ ሓላፊነት ወስዶ የፈጸመው ተግባር መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ማቅረብ አግባብ ይሆናል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ሁልጊዜም ቢሆን የሃይማኖት አባቶች የሚያዙትን እንጂ ከዚያ ተላልፎ በራሱ ፈቃድ የሚፈጽመው አንዳችም ተግባር አለመኖሩን መረዳት ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  • ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 21ኛ ዓመት ቁጥር 4 ነሐሴ 2005 ዓ.ም.