መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
አባ ገሪማ ዘመደራ
ከዚያም በትግራይ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ መደራ ከሚባል ቦታ ገብተው በዓት ሠርተው ለ፳፫ ዓመታት በትኅርምት ኖረው መልካም ተጋድሏቸውንና የቀና አካሔዳቸዉን በፈጸሙ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኔ ፲፯ ቀን ተገልጦ ስማቸውን የሚጠሩትን፣ መታሰቢያቸዉን የሚያደርጉትን፣ ገድላቸዉን የሚጽፉ፣ የሚያነቡና የሚተረጕሙትን፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹትንና የሚያገለግሉትን ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍላቸው ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ አባ ገሪማም ይህንን ታላቅ ሀብት የሰጣቸዉን እግዚአብሔርን አመስግነው ከተደሰቱ በኋላ በብርሃን ሠረገላ ተነጥቀው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በተለይ በገዳማቸው በመደራ አባ ገሪማ የተሠወሩበት ሰኔ ፲፯ ቀን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡
ሰኔ ሚካኤል – ካለፈው የቀጠለ
ስለዚህም የዚህን ታላቅ የከበረ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ለማድረግ መታገል ይገባናል፡፡ እርሱ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን ዘንድ በዘመናችን ዅሉም ይጠብቀን ዘንድ፤ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይ ዘንድ፤ መከራችንንም ያርቅ ዘንድ፤ የምድራችንንም ፍሬ ይባርክ ዘንድ፤ ፈቃዱንም ለመሥራት ይረዳን ዘንድ፤ ከእኛ ወገን የሞቱትን ዕረፍተ ነፍስ ይሰጥ ዘንድ፤ ወደ መንገድ የሔዱ አባቶቻችንና ወንድሞቻተንን ወደ ቤቶቻቸው በሰላም፣ በጤና ይመልሳቸው ዘንድ፤ በመካከላችንም ፍቅር ያደርግልን ዘንድ፤ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ፤ የክርስቶስ ወገኖች የኾኑ መኳንንቶቻችንንም ጠብቆ በወንበሮቻቸው ላይ ያጸናቸው ዘንድ፤ የሳቱትንም ወደ ቀናች ሃይማኖቱ ይመልሳቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ ይለምናልና፡፡
ሰኔ ሚካኤል – የመጀመርያ ክፍል
ያን ጊዜም ባለ ጠጋው ወደ መጋቢው እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ፤ ‹‹ይቺን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው፡፡ ማንም ዐይወቅ፡፡›› በመካከላቸውም የሚተዋወቁበትን ምልክት ጽፎ አሸጋት፤ ለባሕራንም ሰጠው፡፡ ለመንገዱም የሚኾነውን ስንቅ ሰጠው፡፡ ባሕራንም ተነሥቶ ጉዞውን ጀመረ፡፡ ሲጓዝም ሰንብቶ የአንዲት ቀን ጉዞ ሲቀረው እነሆ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ‹‹አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው›› አለው፡፡ ‹‹ወደ ዕገሌ አገር ወደ ቤቱ ለማድረስ ከአንድ ባለ ጠጋ የተጻፈች መልእክት ናት›› አለው፡፡ ‹‹ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ›› አለው፡፡ እርሱም ስለ ፈራ ሰጠው፡፡
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የኖላዊነት ተልእኮው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰቡ
ሐዋርያዊ ተልእኮን በሚመለከትም ማኅበረ ቅዱሳን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በማዘጋጀት በአማርኛ ቋንቋ እና አፋን ኦሮሞ ትምህርተ ወንጌል ከመስጠቱ ባሻገር ምእመናንን በማስተባበር ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት የገንዘብ ድጋፍ በማድረጉ የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን መደሰታቸውን ብፁዕነታቸው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ይበልጥ ለማፋጠን ይቻል ዘንድ ማኅበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትንና መንፈሳውያን መዝሙራትን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች በማሠራጨት አገልግሎቱን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
አርአያነት ያለው ተግባር በአዳማ ማእከል
አገልግሎቱን በአግባቡ ለመስጠት እንዲቻል ልዩ ልዩ ድጋፍ ላደረጉ የመንግሥት ተቋማትና የሥራ ሓላፊዎች፤ ለበጎ አድራጊ ምእመናንና በአገልግሎቱ ለተሳተፉ ወገኖች ዅሉ ሰብሳቢው በማኅበሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ እኛም እንደ ዝግጅት ክፍል የቤተ ክርስቲያናችንን መንፈሳዊ ተልእኮ ይበልጥ ለማጉላት፤ የአገራችንን ስም በመልካም ጎን ለማስጠራት ይቻል ዘንድ አዳማ ማእከል ከላይ የተጠቀሱትንና እነዚህን የመሰሉ አርአያነት ያላቸው ተግባራቱን አጠናክሮ ቢቀጥል፤ የሌሎች ማእከላት፣ የሰንበት ት/ቤቶች እና የማኅበራት አባላትም ይህን የማእከሉን ፈለግ ቢከተሉ መልካም ነው እንላለን፡፡
ጾመ ሐዋርያት እና ጾመ ድኅነት
በዚህ ዓመት ጾመ ሐዋርያት ግንቦት ፳፰፤ ጾመ ድኅነት ደግሞ ግንቦት ፴ ቀን ይጀመራሉ፡፡ በመኾኑም የምንጠቀመው በራሳችን መልካም ተግባር፤ የምንወቀሰውም በራሳችን መጥፎ ድርጊት መኾኑን ተረድተን ይኼ የቄሶች፤ ይኼ የመነኰሳት ነው የሚል ሰበብ ሳንፈጥር ዅላችንም በአንድነት ብንጾማቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘው ጸጋና ሀብት ይበዛልናልና ራሳችንን ለጾም እናዘጋጅ፡፡
የዘመነ ጰራቅሊጦስ ምንባባት
በዓለ ጰራቅሊጦስ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የተሰጠበት፤ ብዙ ሺሕ ምእመናን የሥላሴን ልጅነት ያኙበት ዕለት በመኾኑ ‹የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓሉ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ሲኾን፣ በያዝነው ዓመትም ግንቦት ፳፯ ቀን ይዘከራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ሰንበት (ከኀምሳኛው ቀን) ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሰንበት ያለው ጊዜም (ስምንቱ ቀናት) ‹ዘመነ ጰራቅሊጦስ› ወይም ‹ሰሙነ ጰራቅሊጦስ› ይባላል፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ስለ መውረዱና በምእመናን ላይ ስለ ማደሩ የሚነገርበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ሰሙን በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር፣ የሚሰጠውም ትምህርት የመንፈስ ቅዱስን በሐዋርያት ላይ መውረድ የሚመለከት ነው፡፡
በዓለ ጰራቅሊጦስ
‹መንፈስ ቅዱስ ወረደ› ሲባል፣ በሰዉኛ ቋንቋ መንፈስ ቅዱስ ከከፍታ ወደ ዝቅታ፣ ከሩቅ ወደ ቅርብ መምጣቱን ወይም መምጣቱን ለመናገር አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በሐዋርያት ላይ አድሮ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትን፣ ጥበብንና ልዩ ልዩ ጸጋን ማደሉን ለማስረዳት ነው እንጂ፡፡ ይኸውም ሥራዉን በሰው ላይ መግለጡን፣ ጸጋዉንም ማብዛቱን ለማመልከት የሚያገለግል ቋንቋ ነው፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ወረደ የሚለው ትምህርት መንፈስ ቅዱስን በቦታ፣ በጊዜና በወሰን መገደቡን አያመለክትም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በዓለሙ ዅሉ የሞላ ነውና፡፡ በሰው ላይ አድሮ ጥበብን ሲገልጥ ግን ‹ሞላ፤ አደረ፤ ወረደ› ተብሎ ይነገራል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለጊዜው ለሐዋርያት ቢሰጥም፣ በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይገደብ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ በምእመናን ላይም አድሮ ይኖራልና፡፡
ዘመነ ዕርገት – ካለፈው የቀጠለ
ከዅሉም በላይ መድኀኒታችን ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንደ ዐረገ እና ዳግም ለፍርድ ተመልሶ እንደሚመጣ በስፋት የሚነገርበት ወቅት ነው – ዘመነ ዕርገት፡፡ ‹‹እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ! ወደ ሰማይ እየአያችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ፣ ወደ ሰማይ ሲሔድ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሐዋ.፩፥፲፩)፡፡ እኛም ሞት የማያሸንፈው አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች እንደ መኾናችን በሞት ከመወሰዳችን በፊት (በምድር ሳለን) ለሰማያዊው መንግሥት የሚያበቃ መልካም ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ እናም ሕሊናችን በጽድቅ ሥራ እንዲያርግ (ከፍ ከፍ እንዲል) ዘወትር በሃይማኖታችን እንጽና፤ በክርስቲያናዊ ምግባር እንበርታ፤ በትሩፋት ሥራ እንትጋ፡፡
ዘመነ ዕርገት
በነግህ (ከቅዳሴ በፊት የሚነበበው) ወንጌል ደግሞ ሉቃስ ፳፬፥፵፭ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ ቃሉም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት እንደሚወርድ፣ የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል መከራ እንደሚቀበል፣ እንደሚሞት፣ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፣ ወደ ሰማይ እንደሚያርግና ዳግም እንደሚመጣ በነቢያት የተነገረው ትንቢት መፈጸሙን፤ ለዚህም ቅዱሳን ሐዋርያት ምስክሮች መኾናቸውን ማለትም በመላው ዓለም እየዞሩ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ እንዲሰብኩና በሰማዕትነት እንዲያልፉ፤ እንደዚሁም ሰማያዊ ሀብትንና ዕውቀትን እስኪያገኙ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ መታዘዛቸውን ያስረዳል፡፡ ይህ ምሥጢር ለጊዜው የሐዋርያትን ተልእኮ የሚመለከት ይኹን እንጂ ለፍጻሜው ግን ዅላችንም ቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩትን ቃል አብነት አድርገን የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና የማዳኑን ሥራ አምነን፣ ሌሎችንም በማሳመን በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር እንደሚገባን፤ እግዚአብሔር አምላካችን ኃይሉን፣ ጸጋውን፣ ረድኤቱን እንዲያሳድርብንም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን መለየት እንደሌለብን የሚያስገነዝብ መልእክት አለው፡፡