መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
የማኅበረ ቅዱሳን ወቅታዊ የአዘክሮ መልእክት
የማኅበሩ አባላትና ወዳጆቹ፣ እንዲሁም የአገልግሎት አጋሮቹና ተባባሪዎቹ ዂላችሁ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉልንን ምክሮች ከማዘከርና ዂልጊዜም ቢኾን ከክፉው ተጠብቀን መልካም የኾነውን አርአያና አብነት ከማድረግ ልንቆጠብ አይገባንም፡፡ በትንሹ እና ሕይወታችንን በሙሉ ሳይኾን ከትርፋችን የምናገለግላት ቤተ ክርስቲያናችን በምድር ላይ እንዳሉ ሌሎች ተቋማት የዚህ ዓለም አደረጃጀትና አሠራር ብቻ የሚመራት ምድራዊ ተቋም ሳትኾን ረቂቅነትን እና መንፈሳዊነትንም ገንዘብ ያደረገች አካለ ክርስቶስ እንደ መኾኗ መጠን የምንፈጽመው ዂሉ መንፈሳዊነት ከጎደለው፣ ርባና ቢስ መኾኑን ለአፍታም ቢኾን ልንዘነጋው የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ ለድርጊቶቻችን አብነት የምናደርገውም ቅዱስ ዮሐንስ እንዳስተማረው ብልሆቹን፣ መልካሞቹንና ደጎቹን እንጂ ሞኞቹን፣ ክፉዎቹንና ተንኮለኞቹን ሊኾን አይችልም፡፡ በዚያውም ላይ ከቅዱሳት መጻሕፍት ምክር ልንወጣ አይፈቀድልንም፡፡ ራሱ ጌታችን ‹‹ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ›› አለን እንጂ የተቃዋሚዎቻችን ሰይፍና ጎመድ ልንይዝ አልፈቀደልንም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ወገኖቻችንም ፍሬ ቢሶች እንዳይኾኑ፥ በሚፈለገውም ሥራ ጸንተው እንዲገኙ በጎ ምግባርን ይማሩ፤›› (ቲቶ. ፫፥፲፬) በማለት እንደ ገለጸው ከቤተ ክርስቲያን ወገን የኾናችሁ ዂሉ፣ በውጭ እንዳሉት ወደ ፍሬ ቢስነት ከሚወስድ ማንኛውም መንገድ ልትቆጠቡ ይገባችኋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በ፳፮ ዓመታት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ያበረከተው አስተዋጽዖ – ክፍል ሦስት
ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከትናንት እስከ ዛሬ
ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተመሠረተ ሕጋዊ ማኅበር እንደመኾኑ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አመራርና አስፈጻሚ አባላቱን እየወከለ በአጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ ስብከተ ወንልን በማስፋፋት፣ አዳዲስ ምእመናንን በማስጠመቅ፤ ለገዳማትና አብነት ትቤቶች ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ፤ ለአባቶች የስብከተ ወንጌልና ከአስተዳደር ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን በመስጠት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስፋፋት ያከናወናቸው ዐበይት ተግባራቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ከአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ጋር ተካተው ሲቀርቡ መቆየታቸውም የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ለአብነትም በጠረፋማ አካባቢዎች ስብከተ ወንጌልን በማዳረስ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከስድሳ ዘጠኝ ሺሕ ለሚበልጡ አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን ማሰጠቱ፤ ለአብነት መምህራን እና ደቀ መዛሙርት ወርኃዊ የገንዘብ እና አስቸኳይ የቀለብ ድጋፍ ማድረጉ፤ የአብነትና ዘመናዊ ት/ቤቶችን፣ የመጠጥ ውኃና ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት ማስገንባቱ፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኙ ከሁለት መቶ ሺሕ በላይ የሚኾኑ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ትምህርተ ወንጌል ማስተማሩና ዐርባ አምስት ሺሕ ያኽሉን ማስመረቁ፤ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ከሰባት መቶ ዐሥር ሺሕ በላይ ልዩ ልዩ የመዝሙር ቅጂዎችንና የኅትመት ውጤቶችን እንደዚሁም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሐመር መጽሔቶችንና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጦችን ማሠራጨቱ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት ተካቶ በ፴፭ኛው አጠቃላይ መንፈሳዊ የሰበካ ጉባኤ ላይ መቅረቡ የሚታወስ ነው (ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት፣ ጥቅምት ወር ፳፻፱ ዓ.ም፤ ገጽ 75)፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በ፳፮ ዓመታት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ያበረከተው አስተዋጽዖ – ክፍል ሁለት
ማኅበረ ቅዱሳን በ፳፮ ዓመታት ያበረከታቸው አገልግሎቶች – ክፍል አንድ
ዘመነ ጽጌ
ከአምስቱ የዘመነ መጸው ክፍሎች መካከልም የመጀመሪያው ክፍል ‹ዘመነ ጽጌ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ያሉትን ፵ ቀናት ያጠቃልላል፡፡ ‹ጽጌ› ቃሉ ‹ጸገየ አበበ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም አባባ ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ጽጌ› ደግሞ ‹የአበባ ወቅት፣ የአበባ ጊዜ፣ የአበባ ዘመን› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ዕፀዋት በአበባ የሚያጌጡበት፣ ምድር በአበቦች ኅብረ ቀለማት የምታሸበርቅበት፣ ወንዞች ንጹሕ የሚኾኑበት፣ ጥሩ አየር የሚነፍስበት፣ አዕዋፍ በዝማሬ የሚደሰቱበት፣ እኛም የሰው ልጆች ‹‹አሠርጎካ ለምድር በሥነ ጽጌያት፤ አቤቱ ምድርን በአበቦች ውበት አስጌጥሃት›› እያልን የዘመናት አስገኚ እና ባለቤት የኾነውን ልዑል እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት፤ ከዚህም ባሻገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር ከገሊላ ወደ ግብጽ ምድር መሰደዷን የምናስብበት ወቅት ነው፡፡
ብዙኃን ማርያም
ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን ‹‹ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ›› ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ መካከል ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው›› ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም ‹‹ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን›› ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡
፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎች ደንግገዋል፡፡ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት ‹ብዙኃን ማርያም› እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡ እነዚህ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው (ዘፍ. ፲፬፥፲፬)፡፡
የሕንዱ ፓትርያርክ የመስቀል በዓልን በአዲስ አበባ አከበሩ
በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተመሠረተችው የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ስትኾን፣ በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሰባክያነ ወንጌልና ካህናት እንደዚሁም ወደሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን እንዳሏትና ሠላሳ በሚኾኑ አህጉረ ስብከቷ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በመወጣት ላይ እንደምትገኝ ታሪኳ ያስረዳል፡፡ በ፳፻፲ ዓ.ም የሚከበረውን በዓለ መስቀል በማስመልከት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተዘጋጀው ልዩ ዕትም መጽሔት በገጽ 12 – 13 እንደተጠቀሰው፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ካልዕ በሕንድ ምሥራቅና ማላንካራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ቶማስ መንበረ ፓትርያርክ ሰባተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማርቶማ ዲዲሞስ ቀዳማዊን በመተካት ከስምንት ዓመታት በፊት ስምንተኛው ፓትርያርክ ኾነው ተሹመዋል፡፡
የምስል ወድምፅ ዝግጅቱ ተመርቆ በነጻ ተሠራጨ
በመናፍቃን ተታለው የተወሰዱ ምእመናንን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ እና በሚሊዮን የሚቈጠሩ ወገኖችን በማስተማር የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ማድረግ ማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ ነድፎ ከሚያከናውናቸው ዐበይት ተግባራቱ መካከል መኾናቸውን የጠቀሱት ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ውብእሸት ኦቶሮ ናቸው፡፡ የምስል ወድምፅ ዝግጅቱን ለምእመናን በነጻ ለማዳረስ መወሰኑ ማኅበረ ቅዱሳን ሕዝበ ክርስቲያኑ በሃይማኖቱ ጸንቶ እንዲኖር ለማበረታታት እና የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲፋጠን ለማድረግ የሚተጋ ማኅበር ለመኾኑ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል – ዋና ጸሐፊው፡፡ ከዚህ የበለጠ ብዙ ሥራ ከማኅበሩና ከምእመናን እንደሚጠበቅም አስታውሰዋል፡፡
በሁለት ቋንቋዎች ብቻ የሚግባቡና በቍጥር ከዐሥር ሚሊዮን የማይበልጡ ምእመናን የሚገኙባት የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከስምንት በላይ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዳሏት ያወሱት አቶ ውብእሸት፣ ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎችን የሚጠቀሙና ወደ አምሳ ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን ባለቤት ለኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ ብቻ በቂ አለመኾኑን ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ይህን ጉዳይ የተገነዘበው ማኅበረ ቅዱሳን፣ የአየር ሰዓት በመከራየት በአሌፍ የቴሌቭዥን ጣቢያ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ በማስታወስ መንፈሳዊ የቴሌቭዥን መርሐ ግብሩን አጠናክሮ ለመቀጠል ያመች ዘንድ በገንዘብም፣ በቁሳቁስም፣ በሐሳብም ምእመናን ድጋፍ እንዲያደርጉ ዋና ጸሐፊው ጠይቀል፡፡
ዘመነ ክረምት – የመጨረሻ ክፍል
ዘመነ ክረምት ዕፀዋቱ በስብሰው ከበቀሉ፣ ካበቡና ካፈሩ በኋላ የሚጠቅሙት በሪቅ፣ በጎተራ እንደሚሰበሰቡ፤ እንክርዳዶቹ ደግሞ በእሳት እንደሚቃጠሉ ዅሉ እኛም ተወልደን፣ አድገን፣ ዘራችንን ተክተን እንደምንኖር፤ ዕድሜያችን ሲያበቃም እንደምንሞት፤ ሞተንም እንደምንነሣና መልካም ሥራ ከሠራን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደምንገባ፤ በኀጢአት ከኖርን ደግሞ በገሃነመ እሳት እንደምንጣል የምንማርበት ወቅት ነው፡፡ በመኾኑም ሰይጣን በሚያዘንበው የኀጢአት ማዕበል እንዳንወሰድና በኋላም በጥልቁ የእሳት ባሕር እንዳንጣል ዅላችንም ቅዱሳት መጻሕፍትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁልንን የቃለ እግዚአብሔር ዘር በእርሻ ልቡናችን በመዝራት (በመጻፍ) እንደየዓቅማችን አብበን፣ ያማረ ፍሬ አፍርተን መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡