የሐዋርያት አማናዊ ጥምቀት እንዴትና መቼ ተከናወነ?

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና

የሊቃውንት ጉባኤ አባል

መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ አስቀድሞ ‹‹የሙት ልጆች ትኾኑ ዘንድ አልተዋችሁም፡፡ እኔ ወደ እናንተ እመጣለሁና ገና ጥቂት ጊዜ አለ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህም ዓለም አያየኝም፡፡ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፡፡ እኔ ሕያው ነኝና እናንተም ሕያዋን ትኾናላችሁ፤›› በማለት ለአባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት የማይለወጥ አምላካዊ ጽኑ ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበረ (ዮሐ. ፲፬፥፲፰-፲፱)፡፡ ይኸውም ‹‹እንደ ሙት ልጆች እንድትኾኑ ሐሙስ ማታ እንደ ተለያኋችሁ አልቀርም፡፡ እኔ ከጥቂት ቀን (ከሁለት ቀናት) በኋላ በትንሣኤ ወደ እናንተ እመጣለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ዓለሙ አያየኝም፤ እኔ በማይራብ፣ በማይጠማ፣ በማይታመም፣ በማይሞት ሕያው ሥጋ እነሣለሁና እናንተም በልጅነት ሕይወት ልዩ ሕያዋን ትኾናላችሁ›› ሲላቸው ነው፡፡

ከዚያ በፊት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን ‹‹ዅላችሁ በዚህች ሌሊት እንደማታውቁኝ ትክዱኛላችሁ›› በማለት ትተውት እንደሚሸሹና ከመካከላቸው የሚክደውም እንደ ነበረ ደጋግሞ ነግሯቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ዅሉም ቢክዱህ እኔ ፈጽሜ አልክድህም›› ብሎታል፡፡ ጌታችንም የልብን ያውቃልና ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ›› ሲል እንደሚክደው አስረግጦ ነግሮታል፡፡ የአምላክ ቃል አይታበይምና የአይሁድ ጭፍሮች ጌታችንን በያዙት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ዅሉ ትተው ሸሽተዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ›› ሲሉት ‹‹የምትሉትን ፈጽሞ አላውቀውም›› ብሏል (ማቴ. ፳፮፥፶፮፤ ማር. ፲፬፥፳፯-፶)፡፡

ጌታችን ከሙታን ተለይቶ በተነሣ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት ‹‹ተነሥቶአል፤ ከዚህ የለም፤›› ብለው ለቅዱሳት አንስት እንደ ነገሩአቸውና ራሱ ጌታችንም በመንገድ ተገልጦ እንዳነጋገራቸው ለቅዱሳን ሐዋርያቱ ሲያበሥሯቸው ሙቶ ይቀራል ብለው ተስፋ ቈርጠዋልና እንደ ተነሣ አላመኗቸውም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ከእነርሱ መካከል ለሁለቱ ወደ ገጠር ሲሔዱ በሌላ መልክ ተገልጦላቸዋል፡፡ እነርሱም ጌታችን እንደ ተገለጠላቸው ሔደው ለባልንጀሮቻቸው ነግረዋል፡፡ እነርሱንም ቢኾን አላመኗቸውም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ተገልጦላቸዋል፡፡ አሁንም መነሣቱን ያዩ ደቀ መዛሙርትን አላመኗቸውም ነበር፡፡ ጌታችንም ስለ ሃይማኖታቸው ጉድለት ገሥፆአቸዋል፤ የልባቸውንም ጽናት ነቅፏል (ማር. ፲፮፥፲፪-፲፬)፡፡ በዚህ ኹኔታ ለቅዱሳን ሐዋርያት ካሣ ሳይፈጸም ከስቅለት በፊት በኅፅበተ እግር ተጠመቁ ቢባል እንኳ ትንሣኤውን አላመኑም ነበር፡፡ እንዳውም የክርስቶስ ትንሣኤ ተረት እንደ መሰላቸው ተጽፋል (ሉቃ. ፳፬፥፲፩)፡፡ አንድ ሰው ከካደ ደግሞ ልጅነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለ ኾነም የሐዋርያት ጥምቀት እግር በመታጠብ እንዳልኾነ እንረዳለን፡፡

እርግጠኛው የቅዱሳን ሐዋርያት ጥምቀት ግን ካሣ ከተፈጸመ በኋላ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከሃሊነቱ ዲያብሎስን ድል ነሥቶ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በተነሣ ጊዜ ነው፡፡ ቀድሞውንም አምስት ሺሕ ከአምስት መቶው ዘመን ሲፈጸም ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በአደባባይህ ተመላልሼ፣በመስቀል ተሰቅዬ አድንሃለሁ፤›› ብሎ ለአዳም በሰጠው ተስፋ መሠረት ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ዅሉንም በእርሱ ይቅር ብሎ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በምድርና በሰማይ ላሉ ሰላምን አደረገ (ቆላ. ፩፥፳)፡፡ ‹‹በውኂዘ ደሙ ቅዱስ አንጽሖሙ ለመሐይምናን ወለሕዝብ ንጹሓን፤ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን አዳነ፤›› እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም (የእሑድ ውዳሴ ማርያም)፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ክርስቶስም ስለ ሰው ኃጢአት አንድ ጊዜ ሙቶአልና ጻድቅ እርሱ እኛን ወደ እግዚአብሔር ያቀርበን ዘንድ ስለ እኛ ኃጢአት በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ነው፡፡ በእርሱም በወኅኒ ወደሚኖሩ ነፍሳት ሒዶ ነጻነትን ሰበከላቸው›› በማለት ጌታችን በዕለተ ዓርብ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ መለየቱንና በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን ማውጣቱን አስረድቶናል (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፰-፲፱)፡፡

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ በዓለመ ነፍስ በሲኦል ሥቃይ ውስጥ የነበሩትን ነፍሳት ሕያው በኾነ ደሙ አንጽቶና ቀድሶ ወደ ገነት ከመለሰ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹እግዚአብሔርነቱ ግን የሞትን ማሰሪያ ፈቶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው፡፡ ሞት እርሱን ሊይዘው አይችልምና፤›› እንዳለው ጌታችን ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ሞትን ድል ነሥቶ እሑድ በመንፈቅ ሌሊት ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ እንደ ተነሣም በቀጥታ ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት ነው የሔደው፡፡

ደቀ መዛሙርቱም አይሁድን ስለ ፈሩ ደጁን ቈልፈው ተሰብስበው የነበሩበት ቤት ሳይከፈት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እነርሱ ገብቶ በመካከላቸው ቆመና ‹‹ሰላም ለእናንተይኹን!›› አላቸው፡፡ እነርሱም ፈሩ፤ ደነገጡ፡፡ ጌታችንም ‹‹እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤›› አለና እጆቹንና እግሮቹን፣ ጎኑንም አሳያቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ጌታችንን ባዩት ጊዜ ደስ አላቸው፡፡ ማለትም ፍርኃቱ ተዋቸው፤ ጥርጣሬው ተወገደላቸው፡፡ ፈጣሪያቸው ሙቶ እንደ ተነሣ አመኑ፤ ተረዱ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ መልኩ ካሳመናቸው በኋላ ዳግመኛ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይኹን! አብ እኔን እንደ ላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኋለሁ፤›› አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እፍ አለባቸው፤ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ (ዮሐ. ፳፥፳፩-፳፪)፡፡

‹‹እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ በፊቱም ሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፡፡ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ኾነ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዘፍ. ፪፥፯)፣ አዳም በተፈጠረ በዐርባ ቀኑ እግዚአብሔር አምላክ በፊቱ እፍ ብሎ ያሳደረበትን ልጅነት ዕፀ በለስን በልቶ ቢያስወስዳት ዳግማይ አዳም ክርስቶስ አዳም ስላጠፋው ጥፋት ደሙን በመስቀል ላይ አፍስሶ፣ ውድ ሕይወቱን ክሦ በቅዱሳን ሐዋርያት ፊት ‹‹እፍ›› በማለት ልጅነትን ዳግመኛ አሳደረባቸው፡፡ በዚህም ቀድሞ በዕፀ በለስ ምክንያት የሔደች ልጅነት በዕፀ መስቀል ምክንያት ተመለሰች፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት የትንሣኤ ዕለት እንደ ተጠመቁ ራሳቸው በመጽሐፈ ኪዳን እንደሚከተለው ገልጸውታል፤

‹‹… ኮነ እምድኅረ ተንሥአ አስተርአየነ ወተገሠ እምቶማስ ወማቴዎስ ወዮሐንስ ወተፈወስነ (ወአእመርነ) ከመ ተንሥአ እግዚእነ … ወይቤለነ ‹አማን አማን እብለክሙ ኢትከውኑ ውሉደ እግዚአብሔር ዘእንበለ በመንፈስ ቅዱስ›፡፡ ወተሰጠውናሁ ወንቤ ‹እግዚኦ ሀበነ መንፈሰ ቅዱሰ› ወነፍሐ ላዕሌነ ኢየሱስ፡፡ ወእምድኅረ ነሣእነ መንፈሰ ቅዱሰ ይቤለነ ‹አንትሙ እለ መንግሥተ ሰማያት ዘእንበለ ኑፋቄ ልብ›፤ … እንዲህ ኾነ፤ ጌታችን ከተነሣ በኋላ ተገለጠልን፡፡ በቶማስ በማቴዎስና በዮሐንስ እጅ ተዳሰሰ፡፡ ጌታችን እንደ ተነሣም አወቅን፡፡ እርሱም ‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ቅዱስ ካልተወለዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች አትኾኑም› አለን፡፡ እኛም ‹መንፈስ ቅዱስን ስጠን?› ስንል መለስንለት፡፡ ኢየሱስም በእኛ ላይ ‹እፍ› አለ፡፡ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበልን በኋላ ‹እናንተ ጥርጥር በሌለው ልብ የመንግሥተ ሰማያት ባለቤቶች ናችሁ› አለን፤›› (መጽሐፈ ኪዳን አንቀጽ ፩)፡፡

‹‹ማን ይናገር የነበረ›› እንዲሉ ቅዱሳን ሐዋርያት እስከ ትንሣኤ ድረስ መንፈስን (ልጅነትን) ሳይቀበሉ ቆይተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ እነርሱ በመጣ ጊዜ በንፍሐት መንፈስ ቅዱስን እንዳሳደረባቸው ራሳቸው በግልጥ ተናግረዋል፡፡ በጌታችን ቀኝ ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ በክርስቶስ ደም ካሣ እንደ ተፈጸመ፣ ልጅነት እንደ ተመለሰ ሲያረጋገጥ ጌታችንን ‹‹ዳግመኛ በመጣህ ጊዜ በመንግሥትህ አስበኝ?›› ቢለው ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ‹‹እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ፤›› ብሎታል (ሉቃ. ፳፫፥፵፫)፡፡ ወገኔ ሆይ! ስለዚህ የሐዋርያት ጥምቀት የትንሣኤ ዕለት ለመኾኑ ከዚህ የበለጠ ማስረጃ ምን አለ? ማወቅ ለሚሻ ቅን ልቡና ላለው ከዚህ በላይ የቀረበው ማስረጃ በቂ ነው፡፡ ተጨማሪ ማስረጃ ካስፈለገ ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ ያስቀመጥናቸውን ጥቅሶች መመልከት ይቻላል፤

  • ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ›› (ሐዋ. ፳.፳፰)፤ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል፤›› (ዕብ.፲.፲)፡፡
  • ‹‹ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡ …፤›› (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፪)፡፡
  • ‹‹በክቡር በክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ እናንተ ታውቃላችሁ፤›› (፩ኛ ጴጥ. ፲፰፥፲፰)፡፡
  • ‹‹… ከኃጢአታችን ላጠበን፤ በደሙ ላነጻን …፤›› (ራእ. ፩፥፮)፡፡
  • ‹‹… ተገድለሃልና በደምህም ከሕዝብና ከአሕዛብ ከነገድም ዅሉ፤ ከወገንም ዅሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃልና፤›› (ራእ. ፭፥፱)፡፡

እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች የልጅነት ክብር (ጥምቀት) ለሐዋርያት የተሰጠው የክርስቶስ ደም ከፈሰሰ በኋላ ነው እንጂ ከዚያ በፊት በኅፅበተ እግር እንዳልኾነ በግልጥ ያስረዳሉ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡