ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እና የ«ተሐድሶዎች» ቅሰጣ

                                    በእደማርያም ንርአዩ

ምድራችን እስከ ዕለተ ምጽአት ከመልካም ስንዴው ጋር እንክርዳዱን ማብቀሏ፤ ከየዋሁ በግ ጋር ተኩላውን ማሰለፏ፤ ከንጹሐን ሐዋርያት መካከል ይሁዳን ማስገኘቷ አይቀርም፡፡ እንክርዳዱ እንዳይነቀል ከስንዴው ጋር አብሮ በቅሎ፣ ተኩላው እንዳይጋለጥ በግ ይመስል ዘንድ ለምድ ለብሶ ከስንዴው ጋር ልዘናፈል፣ ከበጉም ጋር ልመሳሰል ብለው ያልሆኑትን ለመሆን እየታገሉ ለዓላማቸው መስለው የሚሠሩ ተቆርቋሪም ሆነው የሚቀርቡ በማባበል ቃል የሚጎዱ ከፍጥረት ጅማሬ እስከ ዘመን ፍጻሜ፤ ከመላእክት ከተማ እስከ ደብረ ዘይት ተራራ ጌታችን እስከሚገለጥበት ቦታ ከገነት እስከ ዛሬዋ መቅደስ ስተው እያሳቱ ክደው እያስካዱ ከዚህ ዘመን ደርሰዋል፡፡

ለዚህም ነው ሄሬኔዎስ /ከ 130-200 ዓ.ም/ የተባለ ሊቅ «በእውነቱ የስኅተት ትምህርት ወዲያው ታይቶና ታውቆ እንዳይገለጥ እርቃኑን ከቶ አይቆምም፡፡ ነገር ግን መስሕብነት ያለውን ልብስ በብልሃት ለብሶ በውጭ አምሮ ይገኛል፡፡ የሚሞኝ ሰው ካገኘ ለማታለል ከእውነትም የበለጠ እውነት መስሎ ይታያል፡፡» በማለት የገለጸው፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያን ከምሥረታዋ ጀምሮ ጠላት ዲያብሎስ በግብር የወለዳቸውን በመጠቀም እውነቱን ሐሰት በማለት ማሩን በማምረር ወተቱን በማጥቆር የዋሃንን በረቀቀ ስልቱ ተመሳስሎ የጸኑትን ደግሞ እርቃኑን ገልጦ      ጭንብሉን አውልቆ፤ ሲሆን ኃይለ ቃል አጣምሞ ሳይሆንለት ደግሞ ሰይፍ ስሎ ስንዴውን ለማጥፋት እንክርዳዱን    ለማብዛት ያለማቋረጥ ይሠራል፡፡ ያለ ድካም ይተጋል፡፡

ሰማዕታቱም ሞት በእጅጉ በሚፈራበት ዘመን ሞትን እየናቁ ወደ መገደያቸው በዝማሬ ሲሄዱ ያዩ      ሃይማኖታቸው ምንኛ እውነት ቢሆን ነው በማለት ብዙዎችን በሞታቸው ወለዱ የካርታጎው ጠርጠሉስ «አሠቃዩን፣ ስቀሉን፣ ንቀፉን፣ ኮንኑን፣ አቃጥሉን የእናንተ ክፋት ግፍና ጭካኔ የእኛ ንጽሕና ማረጋገጫ ነው፡፡ እናንተ በወገራችሁንና በቆረጣችሁን ልክ ቁጥራችን እልፍ ይሆናል፤ ደመ ሰማዕታት የክርስቲያኖች ዘር ነው፡፡» እንዳለው እንደ ሐሰተኛ ተቆጠሩ እንደ አበደ ውሻ ተወገሩ፤ እንደ ጥራጊ ቆሻሻ ተቃጠሉ፡፡ ስንዴ ስትርስ እንደምታፈራ ሁሉ ሲሞቱ ሌሎችን እያፈሩ ስብከተ ወንጌል ካጸናቸው መከራው የሳባቸው እየበዙ «ሞት ምንም አይደለም ክርስቶስ ተነሥቶአልና» እያሉ በሰማዕትነት ቀናቸው ለዘላለማዊ ሕይወት እየተወለዱ ያረፉበት ዕለትም እንደ ልደት ቀናቸው የሚከበር ሆነ፡፡

መከራ መገለጫቸው ስደት ኑሯቸው ቢሆንም እንኳን በትንሣኤ ተስፋ እየ ተጽናኑ መከራውን እንደ ኢምንት እየቆጠሩ ሳይጠራጠሩ ንግግር የማያውቁ ሲሆኑ ንግግር አዋቂዎችን በክርክር እየረቱ የተረቱትንም ሞትን እንዲንቁ ዘላለማዊ ሕይወትን እንዲናፍቁ አደረጉ፡፡

ገንዘው ሊቀብሯት ስም አጠራሯንም ሊያጠፏት መስሏቸው ለጊዜውም ቢሆን ላይ ታች ቢሉ «እኔ ዓለምን    አሸንፌአለሁ» ያለ አምላክ እንዴት ይሸነፋል ? ቀላያት ተነድለው፣ ምድርንና በውስጧ ያለው ሁሉ በውኃ በጠፋበት በኖኅ ዘመን ኖኅና ቤተሰቦቹን የያዛቸውን መርከብ ይሰብራትና ያጠፋት ዘንድ ውኃው መች ተቻለው ? መጽሐፍ «ውኃውም በምድር ላይ አሸነፈ» ቢልም የኖኅን መርከብ ያሸንፋት ዘንድ ግን አልቻልም፤ እግዚአብሔር ደጆቿንና መስኮቶቿን ራሱ ዘግቷቸዋልና፡፡ እግዚአብሔር የዘጋውንስ ማን ሊከፍተው ይችላል ? ውኃው ሌላውን ሁሉ ሲያሰጥምም መርከቢቷን ግን ከፍ ከፍ እያደረጋት ወደ ተራራው ጫፍ አደረሳት እንጂ መቼ አሰጠማት ?

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በዚህ ሁሉ መከራ የምትሰጥም ለሚመስላቸው ደጆቿን ለመስበር ለሚታገሉ በዙሪያዋ እንደ አንበሳ ለሚዞሩ «ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት» /ኢሳ. 45/ ከማለትስ ሌላ ምን እንላለን ? መሠረቷ ዐለት ነውና ብትወድቁበት ትሰበራላችሁ ቢወድቅባችሁ ትፈጫላችሁ ከማለት ሌላስ ምን እንናገራለን ? / ኢሳ 8/፡፡

ቤተክርስቲያንን በመከራ እየገፏት ወደ ተራራው ጫፍ ወደ ዘላለማዊ ዕረፍት ወደ ፍጹም ጽናት ያደርሷታል እንጂ መቼ ከአምላኳ ይለይዋታል ?

በዚህ ሁሉ ግን ስለ ጥርጥር ጥያቄአቸው ስለ ክህደት አቋማቸው ስለ ነቀፋና ትችታቸው በብርቱ ያለ ዕረፍት ቢዘበዝቡንም ነገር ሁሉ ለበጎ በሆነ በአምላካችን ፊት ወደ በለጠ ጽናት ወደ በለጠ ምርምር ወደ ጥልቅ ንባብ ወደ ታላቅ የሥራ በር መርተውናልና አናማርራቸው፡፡ ቅዱስ አውግስጢን «መናፍቃንን ስለ ጥርጥር         ጥያቄዎቻቸው ሁሉ እናመሰግናቸዋለን፤ የበለጠ እንድናጠና፣ በጥልቀትም እንድንመራመር አድርገውናልና» እንዳለው፡፡ የመናፍቃን መነሣት ለቤተክርስቲያን ትልቅ ጥቅም ነው፡፡ ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም «ሥራ የሞላበት ታላቅ በር ተከፍቶልኛል ተቃዋሚዎች ግን ብዙ ናቸው» ብሏል፡፡

በዚህ ጽሑፍ «ተቃዋሚዎች» በከፈቱልን የሥራ በር ጥቂት መቆየት ፈለግን፤ በሩ… እነሆ

ከአባቶች ትምህርት የራቀው ማን ነው ?

ራሱን እንደ «ለውጥ» አራማጅ እንደ «ተሐድሶ» ፋና ወጊ አንዳንዴም እንደ «ተሳዳጅ» አንዳንዴም እንደ «ሰማዕት» የሚቆጥረው ቡድን «ዛሬ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ከጥንቶቹ አባቶች ትምህርት የራቀች ናት» በማለት ራሱን ከአባቶቿ የሚያገናኛት ሐዋርያ አድርጎ አስቀምጧል፡፡ ለእግሮቹ ማረፊያ ፍለጋ ማነህ ለሚለው ጥግ መያዣ ሲሻው የጥንታዊያን አበውን ትምህርት ይጠቅሳል ስማቸውን በማንሣት የትምህርታቸውን ጫፍ በመጠንቆል በስማቸው ይሸፈናል፡፡ ክንብንብ ጭንብሉን ሲያወልቁበት ደግሞ «አባቶቼ» እንዳላላቸው ዞር ብሎ ደግሞ ይሰድባቸዋል፡፡ በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በሐዋርያውያን አበው በሊቃውንት ትምህርት ተስቦ ሳያምን ትምህርታቸውን እየሳበ ወደ ራሱ ሃሳብ ሊያገባቸው እየሞከረ በስማቸው እንድንቀበለው ይፈልጋል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወይም ጥቂት ጥቅሶች ብቻ እስኪመስል እንዳደረጉት ፕሮቴስታንት ወላጆቻቸው አንዲት መሥመር ትምህርታቸውን ብቻ፣ አንዲት ቃላቸውን ብቻ ይዘው ብዙውን ከራሳቸው ጨምረው የአበው ልጆች መስለው እንደተማሩ፣ የእነርሱ ወራሽ መስለው እንደተረከቡ ብዙዎችን ያደናግራሉ፡፡ ልባቸው ሰፊ አይደለምና ታግሰው አይመረምሩም፣ ጥቂት እንኳን ዝቅ ብለው አያነቡም፤ ብቻ «የአይሁድ ንጉሥ» የምትለዋን ቃል ከሰብአ ሰገል ሲሰማ ብዙ የማይመለስ ጥፋት እንዳጠፋ ሄሮድስ «ሊቀ ካህናት» «አስታራቂ» የሚለውን ቃለ ሲሰሙ ይደናበሩና ራሳቸውን ሌሎችንም ይዘው ለጥፋት ይፋጠናሉ፡፡ የአበውን ሙሉ ቃል የድምጻቸውንም ለዛ እየሰሙ እንደመከተል የተገላቢጦሽ እየመሩ ሊወስዱአቸው ይከጅላሉ፡፡ ታዲያ እንዴት «አባቶቼ» ይሏቸዋል? «አባቴ» ለማለት «ልጅ» ሆኖ መገኘት ግድ ይላል፡፡ እውነተኛ ልጅ ለመሆን ደግሞ በአባቱ ትምህርት ፍጹም መወለድን ይጠይቃል፡፡   

ይህ ቡድን «አባት» ብሎ ትምህርቱን እንደወረሰ ቃሉን እንደታጠቀ የሚናገርለት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ደጋግሞ ከአፉ አይለየውም ከብዕሩ አይነጥለውም፡፡ እውነት ይህ ቡድን «አባቴ» የሚለው ይህ ታላቅ     የቤተክርስቲያን አባት የዚህ ቡድን አባት ነው ? እስኪ ልጅ ነኝ የሚለውን ቡድን አባቴ ከሚለው ታላቅ አባት ትምህርት ጋር እያነጻጸርን «ልጅ» አይደለህምና፤ እርሱም አባትህ አይደለም፤ ሌላ አባትህን ፈልግ እንበለው፡፡

መናፍቃን በሚያሳትሙት መጽሔት ላይ ቃለ መጠይቅ የሰጠው የዚሁ ቡድን አባል መሪጌታ ጽጌ ስጦታው     በተለመደው የአበውን ትምህርት ድጋፍ ለማድረግ በሚያደርጉት ጉድፈራ አንዲት መሥመር እንኳን የማትሞላ ቃል በመምዘዝ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን «ክርስቶስ አማላጅ ነው» ? ለሚለው ፕሮቴስታንታዊ ትምህርቱ ታኮ ለማድረግ ይፈልጋል፤ እንዲህ በማለት «ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ በክርስቶስ በተገኘው እርቅ ካልሆነ በቀር በሌላ በማንም በኩል ጸሎትና ምልጃን ማቅረብ አልተቻለም…፡፡» /ትሪኒቲ ቁ.4 ገጽ 3/ የሚል ቃል በመጥቀስ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጌታችንን «አማላጅ» ብሎታል በማለት ሊቁን  የስሕተት ትምህርታቸው ተባባሪ ሊያደርጉት ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም ፍጹም የአበውን ፈለግ የተከተሉ የእነርሱን ሃይማኖት ያነገቡ መስለው ለመታየት ይከጅላሉ፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን በዚህ በፕሮቴስታንት መጽሔት ቃለ መጠይቅ የሰጠው ግለሰብ የሊቁን ትምህርት ቆንጽሎ ለስኅተቱ መደገፊያ ያድርገው እንጂ የሊቁን ሙሉ ጭብጥ ትምህርት ያላገናዘበ አንዲት መስመርን እንኳ ያልፈተሸ መሆኑ ይገልጽበታል፡፡

ቆንጽሎ የጠቀሰውን ቃል ብቻ እንኳን ብናየው አንድም ጌታችንን «አማላጅ» የሚል ትምህርት ከሊቁ አናገኝም፡፡

በክርስቶስ በተገኘው እርቅ ካልሆነ በቀር…

ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ «እግዚአብሔርም አየ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ፡፡ ሰውም እንደ ሌለ አየ፤ ወደ እርሱ    የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ፤ ተደነቀም፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት ጽድቁም አገዘው፡፡» /ኢሳ. 59÷16/ የሚለውን መሠረት አድርጎ ሰው ሁሉ በአንዱ በአዳም በደል ተጠያቂ ሆኖ፣ ባሕርይው ጎስቁሎ፣ ሕያውነትን አጥቶ፣ ባለ ዕዳ ሆኖ በኖረበት ዘመን የካህናቱ ጸሎት፣ የነቢያቱ ምልጃ፣ የቅዱሳኑ ልመና የሰውን ልጅ ከሲኦል ማውጣት፤ ገነትን መክፈት፤ ጎስቋላ ባሕርይውን ማደስ፤ የሰውን ጥንተ ተፈጥሮ ሳይወድቅ በፊት ወደ ነበረበት ንጽሕና መመለስ አልቻለምና ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ «በክርስቶስ በተገኘው እርቅ ካልሆነ በቀር» አለ፡፡

ጌታችን መገለጥ ያስፈለገበት መንገድ እንደ ነቢያቱና ካህናቱ ምልጃና ጸሎት አይደለም፡፡ ዕርቁ ኃጢአት የተዋሐደውን የሰው ልጅ ከኃጢአት ነጻ ማውጣት የተፈረደበትን የሞት ፍርድ በደሙ መፍሰስ፣ በሥጋው መቆረስ ማስወገድ፣ ገነትን መክፈትን ባሕርይውን ማደስ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ከሰው ወገን ይህንን ሊፈጽም የሚችል አልተገኘምና «ሰው እንደሌለ አየ» ተባለ፤ ራሱ የሰው ልጅ ገነትን መክፈት አልቻለም፤ ገነት ተዘግታበታለችና፡፡ ሞትን ማስወገድ አልቻለም፤ ሕያውነትን አጥቷልና፡፡ ከኃጢአት ነጻ አይደለም፤ ባለዕዳ ነውና፡፡ ታዲያ ለዚህ የሚያስፈልገው ሰው ሆኖ የሚክስለት ሰው የሆነ በሐዲስ ተፈጥሮ ይቅር ብሎ የሚታረቀውም አምላክ መሆን አለበትና ይህንን የሚያሟላ ቢጠፋ «የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ» አለ፡፡ ስለሆነም «የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት» እንዲል ክንዱ የተባለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ ተገልጦ እንደ ነቢያቱ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» እያለ ሳይሆን « እኔ ግን እላችኋለሁ» በማለት ተገለጠ፡፡ ነቢያት ምሳሌውን እየመሰሉት ትንቢት እየተናገሩለት ሱባኤ እየቆጠሩለት ኖሩ ጌታችን ግን እርሱ መሆኑን ስለ እርሱ መነገሩን… እንደ ተፈጸመ እየነገረን መጣ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም «በአምላካቸው በእግዚአብሔር አድናቸዋለሁ» ይላል፡፡ /ሆሴ 1÷3/ የተገለጠው እግዚአብሔር  ነው፤ ያለ እግዚአብሔር ይህ ሁሉ ሊሆን አይችልምና፡፡ በትምህርታቸው እየገሠጹ በኃይለ ቃላቸው እየመከሩ መጻኢያቱን እየተናገሩ በጸሎትና በምልጃ ሕዝቡን እየተራዱ የኖሩት ነቢያት /ቅዱሳን/ ይህን ፍጹም እርቅ ማምጣት አልተቻላቸውምና ነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ «በክርስቶስ በተገኘ እርቅ ካልሆነ በቀር» ያለው እንጂ ሊቁ ክርስቶስን «አማላጅ» የሚል አሳብ የለውም፡፡

በሌላ በማንም በኩል ጸሎትና ምልጃን ማቅረብ አልተቻለም

ይህ ከላይ የዘረዘርነው የጌታችን ሥራ አገልግሎት በራሱ በእግዚአብሔር ካልሆነ የሚሠራ ባለመሆኑ በፍጡር ሳይሆን በፈጣሪ ብቻ የሚሠራ በመሆኑ ፍጡራን በሆኑ በማናቸውም ይህን እርቅ ማምጣት አልተቻለምና «..በሌላ በማንም በኩል ጸሎትንና ምልጃን ማቅረብ አልተቻለም፡፡» በማለት ገለጸው፡፡ በአዳም የሞት ፍርድ የፈረደው እግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔር የፈረደውን እንዴት ፍጡራን ያነሣሉ? ስለዚህ «በክርስቶስ በተገኘው እርቅ ካልሆነ በቀር» አለ፡፡ እግዚአብሔርም ያስወጣውን ፍጡራን /ነቢያት፣ መላእክት፣ ካህናት/ ሊያስገቡት አይችሉምና «በሌላ በማንም በኩል» አለ እንጂ ሊቁ «ጸሎትንና ምልጃን» ሲያቀርብ የሚኖር «አማላጅ» አላለውም፡፡

ጽድቃችን ፍሬ፣ ጸሎታችን ተሰሚ፣ ደጅ ጥናታችን ግዳጅ ፈጻሚ እንዲሆን ዳግመኛ ሕይወት እንድናገኝ ለማድረግ ኃጢአትን አስወግዶልን ወደ ጥንት ክብራችን መልሶን አንድ ጊዜ ክሶ ያስታረቀንን እና የታረቀንን አምላክ ሁሌ «አማላጅ» በማለት ደጋግሞ እንደሚሠራ አድርጎ ማቅረብ የቃለ መጠይቅ ሰጪው የ«ጽጌ ስጦታው» እንጂ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት አይደለም፡፡ ደጋግሞ መሥራት ከፍጡራን የሚጠበቅም እንጂ ከፈጣሪ የሚጠበቅም አይደለም፡፡

የነቢያት፣ የካህናት፣ የቅዱሳኑ ጸሎትና ምልጃ ፍጹምን ዕርቅ አምጥቶ ሰውንም አድኖ ከሲኦል ወደ ገነት ማግባት የማይቻለው በመሆኑ ለሰው ልጅ ደጋግመው መጸለይ ዘወትር መሥዋዕት መሠዋት ሲያገለግሉ መኖርን ጠይቋቸው ነበር፡፡ ደጋግመው በማድረጋቸውም ድካም ስላለባቸው ፍጹም መፈወስ /ማዳን/ አለመቻላቸው ይታወቃል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ድካም የሌለበት የባሕርይ አምላክ በመሆኑ አንዴ ሠርቶ የሚያድን አንዴ ተናግሮ የሚያጸና በመሆኑ እንደ እነርሱ ዘወትር ምልጃን ሲያቀርብ አይኖርም፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ «..በክርስቶስ በተገኘው እርቅ» አለ እርቁን አንዴ አስገኝቷልና «በተገኘው» አለ የሚያስገኝልን እርቅ የለምና፤ «በተገኘው» የሚለው ቃል ጌታችን በመስቀል ላይ የሰጠንን ፍጹም እርቅ የሚያመለክት እንጂ «ሲያስታርቅ» ስለመኖሩ በማስታረቅ ሥራን እየደጋገመ ስለመፈጸሙ የሚያሳይ አይደለም፡፡ ሊቁ ይህንን ቃል ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት አግኝቶታል፤ «ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር እንመካለን፡፡» ከሚለው /ሮሜ. 5÷11/ መታረቁን አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ አግኝተናልና «..በልጁ ሞት ታረቀን» እንዲል፡፡ /ሮሜ. 5÷10/

ዳግመኛም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ «ብርቱ መድኃኒት አንድ ጊዜ በመደረጉ ጽኑውን ደዌ ያድናል፡፡ ብዙ ጊዜ የሚደረግ መድኃኒት ደካማ እንደሆነ ይታወቃልና፡፡» እንዳለው /ድርሳ 17 ቁ 96 -97/ የቀደሙት /የነቢያቱ ጸሎት የካህናቱ መስዋዕት /ደካማ ነበሩና/ በኃጢአት በባለዕዳነት/ ብዙ ጊዜ መሥዋዕት እየሰሠዉ ምልጃ እያቀረቡ ኖሩ፡፡ ጌታችንን ግን «ብርቱ መድኃኒት» ነውና አንድ ጊዜ ባደረገው የመስቀል ዕርቅ ጽኑ ደዌአችንን አስወገደልን፡፡ አሁን /መታረቁን ካገኘን በኋላ/ «አማላጅ ነው» «ሁልጊዜም በማያቋርጥ ሁኔታ… የምልጃ ተግባሩን ይፈጽማል፡፡» ማለት /በንስሐ የመታደስ አገልግሎት በጎ ፈቃደኛ ገጽ 69 ቁ.1 2002 ዓ.ም/ በየትኛውም አቀራረብ ጌታችንን ያለ ጥርጥር «ደካማ መድኃኒት ማድረግ» ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት፡፡      «ሁልጊዜም ሳያቋርጥ» ይፈጽማል ማለት አንዴ ማዳን የማይችል ነው ማለት ነው፡፡ ይህም በቅዱሳት መጻሕፍት ተደጋግመው ከተጠቀሱት «አንድ ጊዜ»  ከሚሉት ኃይለ ቃላት ጋር መላተም ነው፡፡

ይቆየን
ምንጭ፡ ሐመር ጥር 2003 ዓ.ም.

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር