ማኅበረ ቅዱሳን የጠራው የ”አጋርነት መግለጫ” መርሐ ግብር የለም!

ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

እሑድ ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 2007 ዓ.ም ማኅበረ ቅዱሳን እየደረሰበት ያለውን ክስ በመቃወም ለማኅበሩ ያለንን አጋርነት እንግለጽ በሚል ባልታወቁ አካላት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተጠራውን መርሐ ግብር አስመልክቶ፤ ማኅበሩ መርሐ ግብሩ እንዲደረግ ጥሪ ያላቀረበ መኾኑንና ስለጠራውም አካል ምንም ዓይነት ዕውቀት እንደሌለው የማኅበሩን ሕዝብ ግንኙነት በመጥቀስ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ማኅበሩ የሰጠውን አጭር መግለጫ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

 

ሰሞኑን በማኅበራችን ላይ የሚሰነዘሩ ክሶችና ስም የማጥፋት ቅስቀሳዎች እንዳሉ የሚሸሸግ አይደለም፡፡ በመሠረቱ ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ፈቃድ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ታቅፎ አገልግሎቱን በይፋ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያየ ዓላማ ካላቸው አካላት እንደማኅበር ያልተሰጠው መጥፎ ስም፣ የአገልግሎት ጉዞውም ያልተቀባው ጥላሸት የለም፡፡ ይሁን እንጂ በሚያጋጥመው ፈተና ሁሉ ከመዳከም ይልቅ ብርታትን እያገኘ፣ በእግዚአብሔር ኃይል፣በአበው ጸሎትና ምክር የአገልግሎት አድማሱን ከጊዜ ወደጊዜ እያሰፋ በመሄድ ማንም በጎ ኅሊና ያለው ሁሉ ሊመሰክረው የሚችል መጠነ ሰፊ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፤ ዛሬም በመስጠት ላይ ይገኛል፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነገም አገልግሎቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ስለኾነም ማኅበሩ ሰሞኑን የሚሰሙትን ክሶች ከወትሮው የተለዩ አድርጎ ሳይመለከት እነዚህን ተቋቁሞ በሚያልፍበት መንገድ ላይ እየሠራ፣ ስለቀጣይ አገልግሎቱም እየመከረ ይገኛል፡፡

 

በዚህም መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ ባለፉት ቀናት በማኅበሩ ላይ የተሰነዘሩበትን የሐሰት ክሶች አጣርቶ በአገልግሎት ጉዞው ላይ ያጋጠሙትን ወቅታዊ ችግሮች እንዲፈታለት በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ ለጥያቄውም ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ከሚጀምረው መደበኛ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መልስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም አባላቱን ሰብስቦ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል በአንድነት ያቆመ አምላክ ለማኅበሩ ከሳሾች ልቡና እንዲሰጥ እግዚአብሔር ቤተክርስያንንና የማኅበሩን አገልግሎት ከአጽራረ ቤተክርስቲያን እንዲጠብቅ እንደማኅበር አብዝቶ በመጸለይ ላይ ይገኛል፡፡

 

የማኅበሩ ወቅታዊ እንቅስቃሴና ዐቋም ይህ ኾኖ ሳለ፤ እሑድ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሚደረገው ዓመታዊ ዝክረ አበው የጸሎት መርሐ ግብር ላይ «ታላቅ አገር አቀፍ የማኅበረ ቅዱሳን አጋርነት መርሐ ግብር» ባልታወቁ አካላት እንደተጠራ ሰምተናል፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን በማኅበራችን ላይ እየተሰነዘሩ ባሉ መሠረተ ቢስ ክሶች ማኅበራችን ያዘነ ቢኾንም፤ ጉዳዩን አስመልክቶ አባቶች በተቀደሰ ጉባኤያቸው ተወያይተው መፍትሔ ይሰጡ ዘንድ በልጅነት ትሕትና አቤቱታ ከማቅረብ ያለፈ የተጠቀሰውን ጉባኤ እንዳልጠራና ስለጠራው አካል ማንነትም ምንም ዓይነት ዕውቀት እንደሌለው በአክብሮት ይገልጻል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ማኅበረ ቅዱሳን