«ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ» ማቴ. 11፥28
እግዚአብሔር ሁሉን አዘጋጅቶ በመጨረሻ ለፈጠረው ለሰው ልጅ ያላደረገለትና ያልሰጠው ነገር የለም፡፡ ሁሉን ከማከናወኑ ጋር የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን ነገር በአባትነቱ ያውቃልና የሰው ልጅ በባሕርይው የሚያሻውን ነገር የሚያበጃጃት ገነት፣ የምትመቸውን ረዳት፣ የሚገዛቸውን ፍጥረታት ሁሉ ለሰው እንደሚገባ ሰጥቶታል፡፡ ከእነዚህ ተቆጥረው ከማያልቁ ሥጦታዎች አንዱ ደግሞ ዕረፍት ነው፡፡ «እግዚአብሔር የተናገረው ይህ ነው፤ ነገ ዕረፍት ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሰንበት ነው» ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ዕረፍት እንደሚያስፈልግ አውቆ የሰንበትን ቀን ሰጥቶአል /ዘጸ. 16.23/፡፡
«ሠርዐ ለነ ሰንበተ ለዕረፍተ ዚኣነ ፍስሓ ወሰላም ለእለ አመነ፤ ሰንበትን ለእኛ ዕረፍት ይሆን ዘንድ ሠራልን ደስታና ሰላም ለምናምን ሁሉ» እያልን በማለዳ ማመስገናችንም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ በባሕርይው ድካም የሌለበትና ዕረፍት የማይሻው አምላክ «ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ ዐርፎአልና» ተብሎ የተነገረው ከትንቢታዊ ትርጓሜው ባሻገር ሰንበት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ዕረፍት እንደሚያስፈልገው አውቆ ያዘጋጃት ማረፊያ መሆኗንና በተግባር «ዐረፈ» መባልን ፈጽሞ መስጠቱን ያስረዳል፡፡ ከሰውም አልፎ የምትታረስ መሬት እንኳን ዕረፍት እንድታደርግ ማዘዙም ለፍጥረቱ ዕረፍት የሚያስብ አምላክ ያሰኘዋል፡፡ እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል፡፡ ወደ ዕረፍቱ የገባ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እርሱ ደግሞ ከሥራው ዐርፎአልና /ዕብ. 4.9/፡፡
የዕረፍት ጽንሰ አሳብ ሥራን ሠርቶ ከማረፍ ጋር ብቻ የተያያዘ አለመሆኑ ግልጥ ነው፡፡ ሰው ሥጋዊ ብቻም ሳይሆን መንፈሳዊም ነው፡፡ ሰው የተሰኘውም በባሕርያተ ሥጋ ብቻ ሳይሆን በባሕርያተ ነፍስም ነው፤ ስለዚህ ዕረፍተ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ዕረፍተ ነፍስም ያስፈልገዋል፡፡ ሥጋዊ ዕረፍት የሰው ልጅ ከሥጋ ድካሙ የሚያርፈው ሲሆን መንፈሳዊ ዕረፍት ደግሞ ከኅሊና ውጥረት፣ ከጭንቀት በኃጢአት ምክንያት ከሚመጣ መታወክ የሚታረፍና ውስጣዊ ሰላም የሚገኝበት ነው፡፡
ዕረፍት በመንፈሳዊ መነፅርና በሥጋዊ መነፅር ሲታይ የተለያየ ትርጉም አለው፡፡ እግዚአብሔርን ባለማወቅ ለሚኖሩ ሰዎች ዕረፍት መስሎ የሚታያቸው ለመንፈሳውያን ድካም ነው፡፡ ክርስቲያኖች ዕረፍት ነው የሚሉት ደግሞ ለሌሎች ድካም ሆኖ ይሰማቸዋል፡፡
አምላካችን «ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ» ብሎ ሲናገር የሚያሳርፈን ዕረፍት ሥጋዊ ዕረፍትን አይደለም፡፡ «ወደ እኔ ኑ» የሚለውን ጥሪ የተቀበሉና የተከተሉት ቅዱሳንም ከእርሱ ያገኙት መንፈሳዊ ዕረፍትን እንጂ ሥጋዊ ዕረፍትን አልነበረም፡፡ ስለዚህም «በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም» በማለት ተናግረዋል /2ቆሮ. 7.5/፡፡ በእርግጥም እርሱን የተከተሉ ሁሉ ሥጋዊ ዕረፍትን አላገኙም፤ በነፍሳቸው ግን ፍፁም ዕረፍትን አግኝተዋል፡፡ በነፍሳቸው ያገኙት ዕረፍትም በሥጋ ማረፍን እንዳይፈልጉ አድርጓቸው «በመከራ፣ በችግር በጭንቀት፣ በመገረፍ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመጦም» ውስጥ እየኖሩ ተጋድሎአቸውን ፈጽመዋል/2ቆሮ. 6.5/፡፡
እግዚአብሔር «አሳርፋችኋለሁ» ያለው ዕረፍት ሰነፉ ባለጠጋ ለነፍሱ ሊሰጣት የወደደውን ዕረፍትም አይደለም፡፡ ይህ ሰነፍ ሰው እርሻው ፍሬያማ ስትሆንለት ጎተራውን አፍርሶ ሌላ ጎተራ ሊሠራ አቀደ፤ ለነፍሱም እንዲህ ሊላት ወደደ፤ «አንቺ ነፍሴ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ ብዪ ጠጪ፡፡» ይሁንና እግዚአብሔር በዚያች ሌሊት ነፍሱ እንደምትወሰድ ነገረው /ሉቃ.12.16-20/፡፡ ይህ ሰው የተመኘው ዕረፍት ከመብል ከመጠጥ፣ ከተከማቸ ሀብት የሚገኝን ዕረፍት ነበር፡፡ ስለዚህም በድንገት ተወሰደ «ያርፍ ዘንድ ተስፋ ባደረገ ጊዜ እበላለሁ፣ እጠጣለሁ፣ ባለ ጊዜ እንግዲህስ ደስ ይለኛል ገንዘብም በቃኝ ባለ ጊዜ የሚሞትባትን ቀን አያውቅም ገንዘቡን ሁሉ ለባዕድ ትቶ እሱ ይሞታል» የተባለው በእርሱ ተፈጸመ /ሲራ.11.19/፡፡ መብል፣ መጠጥ፣ የተከማቸ ሀብት ፍጹም ዕረፍትን አይሰጥም፡፡ እንዲያው በተቃራኒው ዕረፍትን ሲነሣም እናገኘዋለን፡፡ ሀብትን፣ መብልና መጠጥን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይዞት ለሚኖር ሰው ግን በጎ ሥራን ሠርቶበት ዕረፍትን ሊያገኝበት ይችላል፡፡
በሃይማኖት መንገድ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በተገቢው አረማመድ እስከሄዱ ድረስ የነፍስን ዕረፍት ያገኛሉ፡፡ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል- በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርስዋም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፡፡» የሚለው የጥሪ ቃል እዚህ ላይ ሊነሣ ይችላል /ኤር.6.16/፡፡ የክርስትና ሃይማኖት መንገድም የነፍስ ዕረፍት የሚገኝባት መሆኗ ርትዕት /የቀናች/ መሆኗን ያስረዳል፡፡ በነፍስ ዕረፍትን በማግኘት ፈንታ ሥጋዊ ደስታ የሚገኝበት መንገድ የሃይማኖት መንገድ አይደለም፡፡ ሃይማኖት በሥጋ እየደከሙ በነፍስ የሚያርፉበት፤ መከራን እየታገሡ፣ ሥቃይን እየተቀበሉ የልብ ዕረፍትን የሚያገኙበት ነው፡፡ በመከራም እያሉ እንኳን «ወደ ወጥመድ አገባኸን፤ በጀርባችንም መከራን አኖርህ፤ በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን፤ በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን፤ ወደ ዕረፍትም አወጣኸን» እያሉ ከቅዱሳን ጋር በማመስገን ከመከራ ባሻገር ያለውን የነፍስ ዕረፍት የሚቀበሉበት ሕይወት ነው /መዝ.65.11-12/፡፡
ለሰው ልጅ በተለይም ለክርስቲያን በእግዚአብሔር ዘንድ ከሚያገኘው ዕረፍት የሚልቅ ዕረፍት የትም አይገኝለትም፡፡ ቅዱስ አውግስጢኖስ የተባለ አባት «በአንተ ዕረፍት እስካላገኙ ድረስ ልቦቻችን ዕረፍት አይኖራቸውም» ብሎ እንደተናገረው «ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ» ወደ ሚለን አምላክ እስካልተጠጋን ድረስ ልባችን ዕረፍትን አያገኝም፡፡ ይኸው አባት በሌላ ጊዜም «ጌታ ሆይ ለራስህ ብለህ ስለፈጠርኸን ልባችን በአንተ ላይ እስኪያርፍ ድረስ ይባክናል» ብሎ ተናግሯል፡፡ ይህንን ጥሪ መቀበልም ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መቅረብ፣ እንደ ሕጉ እንደ ትእዛዙ ለመኖር መፍቀድ ነው፡፡ «እኔም አሳርፋችኋለሁ» ያለ አምላክ የከበደ ሸክማችንን አውርዶ የሚያሸክመን ልዝብ ቀንበርና ቀሊል ሸክም ደገኛይቱ ሕገ ወንጌልን አዘጋጅቶልናል፡፡ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የራቀ፣ ከሥጋ ወደሙ ከደጀ ሰላሙ የተለየ ሰው በቤቱ የሚገኘውን ዕረፍት በየትም ሥፍራ ሊያገኘው አይቻለውም፡፡ በኖኅ መርከብ ውስጥ የነበረችው ርግብ ከመርከቡ ወጥታ ማረፊያ እንዳጣች ሁሉ እንደርግብ የዋኀን የሆኑ ምእመናንም ከመርከቢቱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተለይተው ዕረፍት አይኖራቸውም፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመብላት፣ በመጠጣት፣ በመተኛት የማይገኝ በመራብ በመጠማት እንቅልፍ በማጣትና በመንገላታት የማይታጣ ፍጹም ዕረፍት አለ፡፡
«እኔም አሳርፋችኋለሁ!» የሚለው ቃል የሚነግረን ሌላው ዕረፍት ደግሞ ሁላችን የምንናፍቃትን ተስፋ የምናደርጋት ዘላለማዊት መንግሥቱን ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰማያዊት መንግሥቱን «ዕረፍት» ብሎ ይጠራታል፡፡ በቀደመው ዘመን እሥራኤል ከባርነት ወጥተው እንዲወርሱአት የተዘጋጀችው ከነዓን ዕረፍት ተብላ ትጠራ ነበር፡፡ የተፈታተኑኝ አባቶቻችሁ ፈተኑኝ፤ ሥራዬንም አዩ፤ ያቺን ትውልድ አርባ ዓመት ተቈጥቻት ነበር፤ ሁልጊዜ ልባቸው ይስ ታል፤ እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ፡፡ ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ» በማለት እንደተናገረ /መዝ. 94.9-11/
እኛ ክርስቲያኖች የምንናፍቃት ከነዓን ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ናት፡፡ እሥራኤል ፋሲካን አድርገው ከግብጽ ባርነት ነጻ ወጥተው ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው አርባ ዓመት ተጉዘው ከነዓንን /በቁጥር ጥቂቶች ቢሆኑም/ እንደወረሱ እኛም ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ ወጥተን ባሕረ ኃጢአትን ዘመነ ፍዳን ተሻግረን «በፋሲካችን ክርስቶስ» መከራና ሞት ነጻ ወጥተን በዚህች ዓለም ተጉዘን የምንወርሳት ከነዓን ኢየሩሳሌም ሰማያዊት /መንግሥተ ሰማያት/ ናት፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን በላከው ክታቡ እሥራኤል ሕጉን በመተላለፋቸው ወደ ቀደመችዋ ዕረፍት ወደ ከነዓን ስላለመግባታቸው ከዘረዘረ በኋላ «እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ፤ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ» በማለት አሳስ ቦናል /ዕብ.4.11/፡፡ በእርግጥም ዕረፍት መንግሥተ ሰማያትን ለማግኘት፣ «ወደ ዕረፍቱም አትገቡም» ከመባል ለመዳን መጠንቀቅና መትጋት ይገባናል፡፡ እሥራኤል ወደ ከነዓን ባይገቡ በሞተ ወልደ እግዚአብሔር ወደ ገነት ገብተዋል፤ እኛ ግን ወደ መንግሥተ ሰማያት ባንገባ ቆይተን የምንገባበት ሌላ ዕረፍት የለምና ወደ ዕረፍቱ ለመግባት እንትጋ!