«ጠቅላላ ጉባኤው አንድነታችንን ፍቅራችንን የምናጸናበት ነው፡፡» ዲ/ን ሙሉዓለም ካሣ
በዘንድሮው ጠቅላላ ጉባኤ የእርስዎ ድርሻ ምንድን ነው?
ለጠቅላላ ጉባኤው አባላትን የሚጠራው የአባላትና አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል ነው፡፡ በተጨማሪም በተዋቀረው ዐቢይ ኮሚቴ ጥሪዎችንና ቅስቀሳዎችን ማድረግ ነው፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው ምን ምን ክንዋኔዎች ይካሄዳሉ?
በጠቅላላ ጉባኤያት እንደማንኛውም ጊዜ የተለመዱ አሠራሮች አሉ፡፡ ለአባላቱ የማዕከሉ የ1 ዓመት የሥራ ክንውን ይቀርባል፡፡ በዚያም ላይ አባላት ይወያያሉ፡፡ ከዚያ ውጭ ለሚቀጥለው ዓመት የተዘጋጀ ዕቅድ ይቀርባል፡፡ ያንንም እቅድ ጠቅላላ ጉባኤው ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ማዕከሉ ለአባላቱ የሚያዘጋጃቸው የመወያያ አጀንዳዎች ይኖራሉ፡፡ በዚያም ላይ ይወያያሉ፡፡ ተጨማሪ መረጃዎች ካሉ እንዲሁ ለአባላት ይቀርባል፡፡ ከዚያም ውጭ የዋናው ማዕከል ተወካይ የሚያቀርበው ግምገማ ከዚያው ጋር የሚታይ ሲሆን አዲስ የሥራ አስፈጻሚ ምርጫም ይኖራል፡፡
ከጠቅላላ ጉባኤው ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ?
ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ዝግጅት ተደርጓል። አባላት በብዛት ይገኛሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ከ2000 በላይ ለሆኑ አባላት ጥሪ አድርገናል፡፡ በደብዳቤና በወረዳ ማዕከላት ደረጃ በአጭር የስልክ ጽሑፍ /SMS/ መልእክት አስተላልፈናል። ከጠቅላላ ጉባኤ አስቀድመን የአዲስ አበባ ማዕከልን አጠቃላይ አገልግሎት የሚዳስስ ዓውደ ርእይ ይፋ ሆኖ እስከ ጠቅላላ ጉባኤ ይቀጥላል። በዚህም አባላት አስተያየታቸውን በመስጠት ሱታፌያቸውን ያሳያሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ከዚህ ውጭ ለጠቅላላ ጉባኤው አባላት እንደከዚህ በፊት ሁሉ ሙሉ ቀን ስለሚውሉ የሚያስፈልጋቸውን የምሳና የመሳሰሉት ዝግጅቶች ከወዲሁ ተጠናቋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ካለበት ዘርፈ ብዙ ኃላፊነት አንጻርና የአ.አ ማዕከልም ካሉት የአባላት ብዛት አንጻር ጠቅላላ ጉባኤው ምን ዓይነት ወሳኝነት /ውጤት/ ይኖረዋል?
እንደሚታወቀው የአ.አ ማዕከል ለዋናው ማዕከል መቀመጫ ነው፡፡ ወይም አ.አ. ማዕከል ያሉ አባላት በዋናው ማዕከል ያገለግላሉ፤ ስለዚህ በርካታ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩት፣ ታላላቅ ሥራዎች ይሠራሉ ተብሎ የሚጠበቀው አ.አ ማዕከል ነው፡፡ እንደ አባላት ብዛትም ሲታይ በሺዎች የሚቆጠሩ አባላት የሚገኙት በዚህ ማዕከል ነው፡፡ ስለዚህ ለዋናው ማዕከል ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በመስጠት የአዲስ አበባ ማዕከል አባላት ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ መሠረት ለሚቀጥለው ጊዜ ለማኅበሩም ሆነ ለቅድስት ቤ/ክን በጎ ይሆናሉ ብለን በምናስባቸው ጉዳዮች ላይ አባሉ ጥሩ ሱታፌ በማድረግ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ብለን እንጠብቃለን፡፡ በዋናው ማዕከል፣ በአ.አ. ማዕከልና በወረዳ ማዕከል ያሉ አባላት በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የሚያነሷቸው ሐሳቦች በሙሉ በአጠቃላይ ማኅበሩ አዲስ አበባ ላይ ለሚሰጠው አገልግሎት ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ ይኸም አጠቃላይ ውጤቱ በማኅበሩ የሚያበረክተው ፋይዳ የጎላ ነው ብለን እናምናለን፡፡
ከጉባኤው ከአባላት ምን ዓይነት ተሳትፎ ይጠበቃል?
ይህንን ጊዜ ከባለፈው ጊዜ ተጠንቅቀን የመረጥንበት ምክንያት አለን፡፡ በተለይ ባለፈው ሳምንት ያላደረግነው በምረቃ ምክንያት ነው። ወቅቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚመረቁበት ነበር፤ የማኅበሩ አባላት ተመራቂዎችና አስመራቂዎች መሆን እድል ስላላቸው መርሐ ግብሩን ሐምሌ 23 እና 24 አድርገነዋል። ስለሆነም፣ በመጀመሪያ ደረጃ መገኘት የአባልነት ድርሻ በመሆኑ ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡ መገኘት አንዱ መብትም ግዴታም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚያ ውጭ በሚኖሩ ውይይቶች ላይ አስተያየታቸውን በመስጠት፣ የቀረ ነገር ካለ በመሙላት፣ የተጣመመውን በማቃናት በሚቀጥለው ደግሞ እንዲህ ይሁን በማለት ያለፈውን አስተያየት በመስጠት በሚመጣውም በመምከር ሱታፌያቸውን ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ውጭ የማዕከሉ ሥራ ማስፈጸሚያ ወይም ለዚህ የሚያስፈልገው አጠቃላይ በጀት ሙሉ በሙሉ በማዕከሉ የሚሸፈን አይደለም፡፡ አባላት በሚያደርጓቸው አስተዋጽኦዎች፣ ለመስተንግዶ የሚሆኑትን ሁሉ በማበርከት ነው፡፡ ስለዚህ ይህም ሌላኛው የአባላት ሱታፌ የሚጠበቅበት ይሆናል፡፡ ከምንም በላይ በዘንድሮው የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ስላለ አባላት ለማዕከሉ አገልግሎት ይሆናሉ የሚሏቸውን ወንድሞችና እኅቶች ከወዲሁ በጸሎታቸው እንዲያግዙ ይጠበቃል፡፡ በእነዚህ ዙሪያ የአባላት ተሳትፎ ከሚጀመርበት ከቅዳሜ ጠዋት 2፡00 ጀምሮ እስከ እሑድ ማታ 12፡00 ምንም ዓይነት መርሐ ግብር ሳይኖራቸው ይህንን እንደግዴታ ወስደው ከወዲሁ መርሐ ግብራቸውን አመቻችተው በዚህ እለት እንዲገኙ ይጠበቃል፡፡
ቀደም ብለው ጠቀስ እንዳደረጉት ዘንድሮ የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ይደረጋል፡፡ ያለፈው ሥራ አስፈጻሚ ነገሮችን ተደማምጦ በመቻቻልና በመንፈሳዊነት በማከናወን በቀጣዩ ምን ዓይነት ተመክሮ ያስተላልፋል?
የማኅበረ ቅዱሳን አንዱ ትልቁ እሴት መደማመጥ ነው። ከእኔ ይልቅ ወንድሜ ይሻላል እኅቴ ትሻላለች፤ የወንድሜ ይሰማ የእኅቴ ይሰማ አንዱ እሴታችን ነው፡፡ ተነጋግረን እንኳን መግባባት ቢያቅተን እግዚአብሔር ይግለጥልን ብለን አጀንዳዎችን እናሳድራለን፡፡
እኔ በግሌ በማዕከሉ አገልግሎት ውስጥ የተደሰትኩበት መግባባቱ መስማማቱ ነው፡፡ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ የሚያሰኝ መግባባትና ስምምነት ነበረን፡፡ ስለዚህ የሚቀጥለውም ሥራ አስፈጻሚ ይሄን ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እኛም የተረከብናቸው ወንድሞችና እኅቶች ይህንን ሲያደርጉ ነበር እርሱም ከቀደምቱ እንዲሁ ተቀብለው ነበር። በዚህ መልኩ ይኸው ይቀጥላል፡፡
አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ላንሳ፤ በፊት ለዋናው ማዕከል የአገልግሎት ክፍሎች እንዲሁም የሥራ አስፈጻሚና አመራር የሚመረጡት ወንድሞችና እኅቶች በአዲስ አበባ ማዕከልና በሌሎች ማዕከላት የአገልግሎትና የሕይወት ትሞክሮ ተፈትነው አልፈው ነው፤ ስለዚህ ብዙውን ጊዜ አዲስ አበባ ማዕከል እነዚህን ወንድሞችና እህቶች በአብዛኛው አሰልጥኖ የማቅረብ ልምድ አለው፡፡ አሁንስ ያለው አካሔድ ምን ይመስላል?
በማዕከላችን በኩል በዘንድሮው ተጠናክሯል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ልምድ የሚያስፈልጋቸው የአገልግሎት ሁኔታዎች አሉ፡፡ ወደ ሥራ አስፈጻሚ ሲመጣ የማኅበሩን አሠራር፥ የቤ/ክንን ጠቅላላ ሁኔታ፥ ሌሎችንም ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሁለገብ እይታን የሚፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ጥንካሬዎች በአገልግሎት፣ በሒደት፣ በውጣ ውረድ ውስጥ የሚመጡ አሉ፡፡ በትምህርት በሥልጠናዎች የምናገኛቸው ብርታቶችም አሉ፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ሁኔታዎች ይታያል እንጂ ከምንም አንስተህ ወደ ሥራ አስፈጻሚ አታስገባም። የዘንድሮው ተጠናክሯል ብዬ የማስበው የአ.አ. ማዕከል ከሌሎቹ በተለየ መልኩ የተተኪ አመራር ሥልጠና አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ለዋናው ማዕከል የአገልግሎት ክፍሎችና ለአ.አ ማዕከል አገልግሎት ክፍሎች የሚሆኑ የተተኪ አመራር አባላትን ተዘጋጅተዋል፡፡ በተወሰነ መልኩ የዘንድሮ ሥራ አስፈጻሚም ጠቅላላ ጉባኤው እነዚህን አባላትንና ሌሎችንም ያካትታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ በአገልግሎት የተፈተኑና ልምድ ያላቸውን ወንድሞችና እኅቶች የተተኪ አመራር ሥልጠና የወሰዱት ወደ ሥራ አስፈጻሚ ይገባሉ ብየም እገምታለሁ፡፡ ለተተኪ አመራርነት ስናሰለጥን ቀድሞውኑ ያሉበትን ሁኔታ የንዑስ ክፍል ኃላፊዎች፣ የክፍል ኃላፊዎች የመሠከሩላቸው ወንድሞችና እኅቶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አንተም እንዳነሳኸው ለዋናው ማዕከልም ሆነ ለአዲስ አበባ ማዕከል አገልግሎት ክፍሎች በልምድና በሥልጠና የተዘጋጁ አባላት ወደ ኃላፊነት ይሔዳሉ።
በመጨረሻ የሚያስተላልፉት ነገር ካለ?
የዘንድሮው ጠቅላላ ጉባኤ ሐምሌ 23 እና 24 2003 ዓ.ም ይካሔዳል፡፡ ሁለቱንም ቀን አባላት ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው እንዲቆዩ፤ እኛም እንደ ሥራ አስፈጻሚም ሆነ እንደማዕከሉ ጓጉተን የምንጠብቀው ዕለት ነው፡፡ አንድነታችንን ፍቅራችንን የምናጸናበት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ጠቅላላ ጉባኤ ሁሉም ሰው የሚገናኝበት ስለሆነ በደስታና በፍቅር የምንጠብቀው ነው፡፡ ለዚህ አገልግሎት መስተንግዶዎች ይኖራሉ በተዘጋጁ መስተንግዶዎች ለመስተናገድ፣ ጥያቄም ሐሳብም ያላቸው ደግሞ የሚመለከተውን አካል እየጠየቁ በዚያ መልኩ እንዲስተናገዱ እያሳሰብኩ ከሁሉም በላይ የጠቅላላ ጉባኤው ቀናት እስከሚደርስና በዚያው ጊዜም አባላት በጸሎታቸው እንዲያስቡን እንጠይቃለን፡፡
እግዚአብሔር ይስጥልን
አሜን አብሮ ይሰጠን፡፡