Temerakiwoch.JPG

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከ15,000 በላይ የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎችን አስመረቀች።

ተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
Temerakiwoch.JPG

ማኅበረ ቅዱሳን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩና በግቢ ጉባኤያት ትምህርተ ሃይማኖት ያስተማራቸውን ከ15,000 በላይ ተማሪዎች በአባቶች ቡራኬ አስመረቀ። ተመራቂዎች የአደራ ቃልም ተሰጥቷቸዋል።

በአዲስ አበባና አካባቢዋ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች ዛሬ እሑድ ሐምሌ 17 ቀን 2003 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽና በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ተክለ ሳዊሮስ ሰ/ት/ቤት አዳራሽ ተመርቀዋል።

በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በተደረገው መርሐግብር የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስና የሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ተገኝተዋል።
BitsuanAbatoch2.JPG

ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ በሰጡት ቃለ ምዕዳን «ደክመው ያስተማሯችሁን ቤተ ክርስቲያናችሁንና ማኅበራችሁን እንዳታሳፍሩ በሕይወታችሁ ልትበረቱ ልትጸኑ ያስፈልጋል።» በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የማኅበሩ ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልእክት ”በዕድሜ ዘመናችሁ ሁሉ በክርስትና እምነት እና ሥርዓተ አምልኮ መጽናትን ዐቢይ ዓላማችሁ አድርጋችሁ እንድትይዙና እንድትመላለሱበት፤ በክርስቲያናዊ ሕይወት ከመጽናት በተጨማሪም ባገኛችሁት ዕውቀት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ተጠቅማችሁ ሀገራችንን ኢትዮጵያን ይልቁንም እናት ቤተ ክርስቲያናችሁን በምትችሉት ሁሉ እንድታገለግሉ ይኸውም ቃለ ዐዋዲያችን በሚያዘው መሠረት በሰ/ት/ቤትና በሰበካ ጉባኤ ተጨባጭ ተሳትፎ እንድታደርጉ” ብለዋል።
Dn.Yaregal.JPGዲ/ን ያረጋል አበጋዝ “ይዞ የተገኘው ወጣት” በሚል ርእስ የዕለቱን ትምህርት አስተምረዋል። “ጌታችን 5 እንጀራና 2 ዓሣ ሲያበረክት እነዚያን ይዞ እንደተገኘው ወጣት 5ቱን የስሜት ሕዋሳት ለእግዚአብሔር ማስገዛት ይዘን መገኘት ይኖርብናል።፡ከዚህም በተጨማሪ በ2 ዓሣዎች የተመሰሉትን ዕውቀት ሥጋዊና መንፈሳዊ እንዲባርክልን መለመን አለብን” ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በማኅበሩ የአዲስ አበባ ማዕከል መዘምራን “ወይቤሎሙ ሑሩ ወመሀሩና ሌሎችን መዝሙሮችን አቅርበዋል።”
ከግቢ ጉባኤያት የተውጣጡ ተመራቂ ተማሪዎችም በብፁዓን አባቶቻቸው፣ በቤተሠቦቻቸው፣ በወንድምና እህቶቻቸው ፊት።
«ጸውዖሙ ወባረኮሙ ወይቤሎሙ አማልክት አንትሙ ወደቂቀ ልዑል ኩልክሙ፣
 ወሰኑ ወሠርዑ ሃይማኖተ እንተ ኢትጠፍዕ።
ጠራቸው፣ ባረካቸውም እናንተ አማልክት ናችሁ፤ ሁላችሁ የልዑል ልጆች ናችሁ አላቸው። እነርሱም የማትጠፋ ሃይማኖትን ደነገጉ።» የሚለውንና ስለ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት የሚናገረውን ወረብ በቁም ዜማና ጽፋት ዘምረው ወርበውታል።
 
በማኅበሩ የሀገር ውስጥ ማዕከላትና ግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ክፍል የግቢ ጉባኤያት ክፍል አስተባባሪ አቶ እንዳለ ደጀኔ እንደገለጡት ምንም እንኳን በግቢ ጉባኤያቱ የሚሰጡትን የትምህርት ዓይነቶች በአግባቡ በመማር ለምርቃት መጽሔት የበቁት ከ15,000 በላይ ቢሆኑም ማዕከላቱ በሚያዘጋጇቸው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸው የምረቃ መርሐ ግብር የአደራ መስቀል የሚቀበሉት ከ32,000 ተማሪዎች በላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥ 42 ማዕከላትን፣ ከ400 በላይ ወረዳ ማዕከላትና ግንኙነት ጣቢያዎችን እንዲሁም 300 ግቢ ጉባኤያት ያቀፈ ሲሆን በዛሬው ዕለት የሚመረቁትን ጨምሮ ከ120,000 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በየአጥቢያቸው አስተምሮ በአባቶች ቡራኬ አስመርቋል። በአሁኑ ወቅትም ከ150,000 በላይ ተማሪዎችን በግቢ ጉባኤያት ሰብስቦ በማስተማር ላይ ይገኛል። ከሀገር ወጭ ደግሞ 4 ማዕከላትና 4 ግንኙነት ጣቢያዎች አሉት።