በባሕረ ጥበባት /Encyclopedia of EOTC/ ዝግጅት ዙሪያ የምክክር ጉባኤ ተካሔደ
ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አስተባባሪነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕረ ጥበባት /Encyclopedia of EOTC/ ዝግጅት ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የምክክር ጉባኤ ተካሔደ፡፡
ግንቦት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ አስር ሰዓት ጀምሮ በሰሜን ሆቴል በተካሔደው የምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት /Encyclopedia of EOTC/ ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትን አስመልክቶ በማኅበሩ ሰብሳቢ በቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ ተገልጿል፡፡ በንግግራቸውም በተለያዩ ጊዜያት የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክና ቅርሶች አጥኚዎች፤ ጎብኚዎችና ምእመናን መረጃዎችን ማእከላዊና ሕጋዊ ከሆነ ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን አውስተው አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው፤ ሊቃውንቱ የሚያውቁት የቤተ ክርስቲያንን ማንንት የሚገልጽ መረጃ ማዘጋጀት፤ በተለያዩ ጊዜያት በዘርፉ የተሞከረው እውቀት በአንድ ላይ በማሰባሰብ የታሪክ ቅሰጣ ለማስቀረትና ለመከላከል እንዲቻል ይህንን ባሕረ ጥበባት ማዘጋጀት እንዳስፈለገ አብራርተዋል፡፡
በተካሔደው ውይይትም የሚዘጋጀው ባሕረ ጥበባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት፤ ታሪክና ሥርዓት እንዲይዝ እንዴት ተደርጎ ይዘጋጃል፤ ማነው የሚያዘጋጀው፤ አቅም / የሰው ሃይል፤ ገንዘብ . . ./ ፤ ተጀምሮ እንዳይቋረጥ ምን መደረግ አለበት፤ የባለሙያዎች ድጋፍ፤ የባለ ድርሻ አካላት ትብብር፤ የአሰራር ሥልቶች ዝግጅት፤ በስንት ጊዜ ይጠናቀቃል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሒዷል፡፡
በመጨረሻም በአማርኛና በእንግሊዝኛ የሚዘጋጀው የዚህ ባሕረ ጥበባት ባለቤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በገንዘብ በጊዜ በሰው ኃይል የተቀናጀ አደረጃጀት ያለው ሆኖ ሥራውን ግን ማኅበረ ቅዱሳን በበላይነት ቢመራው የተሻለ እንደሚሆን አስተያየት ቀርቧል፡፡ ለሥራው ግብአት የሚሆኑ አሳቦችንም ለማሰሳሰብ የምክክር ጉባኤው በተደጋጋሚ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡
በምክክር ጉባኤው ላይ ከሊቃውንት ጉባኤ፣ ከአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ኮሌጆች፤ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና መጻሕፍት ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፣ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራርና ሥራ አሰፈጻሚ አባላት ተገኝተዋል፡፡