ፍርድ ለነነዌ÷ ሥልጣን ለነነዌ

የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ


ኮናኔ በርትዕ÷ ፈታሄ በጽድቅ÷ የሆነው መድኀኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ጻፍት ፈሪሳውያንን በቋንቋቸው በዕብራያስጥ ቢያስተምራቸው “እንደ ሙሴ፡- ባሕር ከፍለህ÷ ጠላት ገድለህ÷ ደመና ጋርደህ÷ መና አውርደህ፣ እንደ ኢያሱ፡- በረድ አዝንመህ÷ ፀሐይ አቁመህ÷ እንደ ጌዴዎን፡- ፀምር ዘርግተህ ጠል አውርደህ፣ እንደ ኤልያስ ሰማይ ለጉመህ እሳት አዝንመህ ልታሳየን እንወዳለን” የሚል ጥያቄ በቀረበለት ጊዜ የሰጣቸው ምላሽ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷ ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት  አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ÷ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈረዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና÷ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” የሚል ነው፡፡ ጻፍት ፈሪሳውያንን ምልክት ያስፈለጋቸው ዋነኛ ምክንያት በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ለማመን አልነበረም፤ ይልቅስ እንደ ዘማ ሴት ምልክት በምልክት እየተደራረበ ማየትን በመናፈቅ ነው፡፡

 

በመጽሐፍ ቅዱሳችን በተደጋጋሚ እንደተገለጠው የአይሁድ ማኅበረሰብ ሁሉ የጌታችንን የባሕርይ አምላክነቱን አይተው ይረዱ ዘንድ ከሌሎቹ ይልቅ በእነርሱ መኖሪያና መንደር እየተዘዋወረ ድንቅ ሥራን ሠርቷል÷ ድውያነ ሥጋን በተአምራት÷ ድውያነ ነፍስን በትምህርት አድኗል፣ ሙታንን አንሥቷል (ማቴ.8÷28-34፣ ማቴ.9÷18-26፣ ዮሐ.9÷1 እስከ ፍጻሜ ምዕራፍ )፡፡ ነገር ግን ቤተ አይሁድ የእጁን ሥራ አይተው፣ የቃሉን ትምህርት ሰምተው ሊያምኑበት እየተገባቸው አላመኑበትም፡ አሁንም አሁንም እየመላለሱ ምልክትን ታሳየን ዘንድ እንወዳለን ይሉ ነበረ(ማቴ.12÷38)፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላካት ክታቡ “መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ” በማለት የአይሁድን መሻት (ፈቲው) ምን እንደሆነ ገልጦ ተናግሯል፡፡(1ኛ.ቆሮ. 1÷22)፡፡ ነባቤ መለኮት የተሰኘው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃንስ ወደ ዓለም የመጣው ነው፡፡በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ ዓለሙ ግን አላወቀውም፡፡ ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፡፡ ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡” በማለት መናገሩ የሚታወቅ ነው(ዮሐ.1÷9-12)፡፡የቃሉን ትምህርት ሰምተው፣ የእጁን ተአምር አይተው ሊያምኑበት እየተገባቸው በአንጻሩ ከሀገራችን ውጣልን የሚል ቃል ይናገሩት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፡፡ ጌታችንም “ ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው።”(ማር.6÷4) በአይሁድ መካከል እየተመላለሰ ማስተማሩ፣ ተአምር ማድረጉ÷ጌታችንን እንዲያምኑትና እንዲያከብሩት አላደረጋቸውም፡፡ ይልቁንም በገዛ ወገኖቹ ተይዞ ባልተገባ ፍርድ ለሞት ተላልፎ እንዲሰጥ ሆነ እንጂ፡፡

 

እንግዲህ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን በአይሁድ ላይ ተነስተው ይፈርዱባቸው ዘንድ ሥልጣንን ያሠጣቸው ዋነኛው ምክንያት በነቢዩ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተው  ከእግዚአብሔር ጋር ስለታረቁ ነው (ዮና.3÷10) ፡፡ ቁጥራቸው ከመቶ ሃያ ሺህ በላይ የነበሩና ግራና ቀኛቸውን የማይለዩ ተብሎ የተጻፈላቸው በአሁኑ ጊዜ ኩዌት ቀድሞ ነነዌ ትባል በነበረችው ከተማ የሚኖሩ ሰዎች እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባለመመላለሳቸው ምክንያት የሚመጣባቸውን መቅሰፍት በንስሐ፣ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው እንዲያርቁት እንዲያስተምራቸው ነቢዩ ዮናስን አዘዘው (ዮና.1÷2) ፡፡ በአጭር ቃል በነቢዩ ዮናስ አማካኝነት የተላለፈውን መንፈሳዊ ትእዛዝና መመሪያ ተቀብለው ተግባራዊ በማድረጋቸው የሚመጣባቸውን መዐት ማራቅ ቻሉ፡፡ “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም”(ዮና.3÷10) መምህረ ዮናስ፣ የዮናስ ፈጣሪ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ መካከል እየተመላለሰ በሠራው ሥራ አለማመናቸው፣ በኀጢአታቸው ተጸጽተው ንስሐ አለመግባታቸው እንደሚስፈርድባቸው ነገራቸው፡፡ በዕለተ ምጽአት (በፍርድ ቀን) በአይሁድ ላይ ለመፍረድ የነነዌ ሰዎች ተነስተው “እኛ እግዚአብሔርን ባለመወቅ÷ እርሱንም በማሳዘን፡- በኀጢአትና በበደል ሥራ ተጠምደን ስንኖር ነቢዩ ዮናስን ልኮልን ባስተማረን ጊዜ ንስሐ ገብተን ምሕረት ቸርነቱ ተደረገልን፤ እናንተ ግን የዮናስ አምላክ፣ የዮናስ ፈጣሪ በመከከላችሁ እየተመላለሰ ያስተማረውን ትምህርት ባለመቀበላችሁ÷ የእጁን ተአምራት አይታችሁ ባለማድነቃችሁ ሊፈረድባችሁ ይገባል፤” ብለው ይፈርዱባችኋል አላቸው፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት ሕዝበ እግዚአብሔር እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት እስራኤላውያን የተደረገላቸውን ቸርነት ማድነቅ ሲገባቸው ነገር ግን አልተጠቀሙበትም፡፡ ወደ እነርሱ ከእግዚአብሔር ተልከው የሄዱትን ነቢያት፣ መምህራን  የእግዚአብሔር ሰዎችን ቃላቸውን ከመስማት ይልቅ÷ እኩሌቶቹን አሳደዱ፣ እኩሌቶቹን ደበደቡ፣ እኩሌቶቹን ገደሉ፡፡ቀዳሜ ሰማዕታት ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ እንደተናገረው ፡-“ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም።” (የሐዋ.ሥራ.7÷52-53)፡፡

 

ከነነዌ ሰዎች  የምንማረው ምንድር ነው?

1ኛ. የእግዚአብሔርን ቃል መስማትና ለመፈጸም መነሣትን፤ ሰብአ ነነዌ አስቀድመው ፈቃደ እግዚአብሔርን የማያውቁ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በትእዛዘ እግዚአብሔር ለመኖር የሚያስችላቸው ቃሉን እንኳ የሚነግራቸው ነቢይ ስላልነበራቸው በኃጢአት ተጠምደው መኖራቸው ታውቋል፡፡ “እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ  ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” የሚለው የእግዚአብሔር ቃል የሚያስረዳን እኒህ የነነዌ ሰዎች ቃለ እግዚአብሔርን አለማወቃቸውን ነው፡፡ ይህንኑ አለማወቃቸውን ያሳውቃቸው ዘንድ ነቢዩ ዮናስ ያስተማራቸውን  የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ፈጽመዋል፡፡(ዮና.3÷4)

 

በዚህ ዘመን ያለን ሰዎች ከምንቸገርባቸው ምክንያቶች አንዱ ቃሉን ለመስማትና ለመፈጸም ያለን ትጋት ደካማ መሆን ነው፡፡ አምላካችን “ይሰሙኝስ ዘንድ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘች ናት ለመስማትም አይችሉም እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ደስም አያሰኛቸውም” ብሎ የተነገረው ቃል እንዳይፈጸምብን ልናስብ ይገባናል፡፡ (ኤር.6÷10) ከዚህ ላይ አብሮ መታየት የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ ቃሉን ከመስማት ባሻገር እንደቃሉ መኖር የሚገባ መሆኑን ነው፡፡ ብዙዎቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን ቃላት በማወቅ ደረጃ እናውቃቸው ይሆናል፤ ነገር ግን ማወቃችን ወደ ሕይወት (ወደ ተግባር) የተሻገረልን ስንቶቻችን እንሆን? እንጃ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” በማለት የሰጠንን መንፈሳዊ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያሻናል፡፡(ያዕ.1÷22) ንስሐን የሚቀበል ልዑል እግዚአብሔር ኀጥአን ልጆቹን ከርኩሰታቸው ያጠራቸው ዘንድ በነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ ባስተላለፈው የንስሐ ጥሪ ውስጥ “…እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ…” የሚል ቃል ተናግሯል(ኢሳ.1÷19)፡፡ እንግዲህ ልብ እናድርግ “እሺ” ብሎ ለቃሉ ምላሽ መስጠትና መታዘዝ የተለያዩ ነገራት ናቸው፡፡ ብዙዎቻችን “እሺ” እንል ይሆናል፤ ነገር ግን ታዝዘናል? እንደ ፈቃዱስ ኖረናል? የነነዌ ሰዎች ግን ከዮናስ አንደበት የተላለፈውን መመሪያ (ቃለ እግዚአብሔር) ሰምተው ተግባራዊ አድርገዋል÷ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ ፡-“ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ ጮኾም፡፡ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ፡፡ የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ ለጾም አዋጅ ነገሩ÷ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡”(ዮና.3÷4-5)፡፡ እንግዲህ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፥ አባቶቻችሁ እኔን የፈተኑበት የመረመሩበትም አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ሆነ፥ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ” (ዕብ.3÷8-9) ተብሎ እንደተነገረ፤ ቃሉን በሰማን ጊዜ ልቡናችንን ከጥርጥር፣ ከትዕቢት አንጽተን ለንስሐ እንድንበቃ ፈጣሪያችን ይርዳን!

 

2ኛ. ነቢየ እግዚአብሔር ዮናስን  አክብረው መገኘታቸው፤  ከነነዌ ሰዎች ከምንማራቸው ተግባራት ሁለተኛው ነገር የእግዚአብሔር ሰዎችን አክብሮ መቀበልን ነው፡፡ “ከየት መጣህ? ዘርህ ምንድር ነው?…” የሚሉና እነዚያን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ነቢዩን አላስጨነቁም፡፡ ከእግዚአ ነቢያት፣ ከእግዚአ ካህናት የተላከ መሆኑን በመረዳት አክብረው፣ ተግሳፁንም ተቀብለው እንዳስተማራቸው ሆነው ተገኙ እንጂ፤ “ነነዌ ትጠፋለች፣ ነነዌ ትገለነጣለች፣ ትጠፋላችሁ የምትለን የምታሟርትብን አንተ ማነህ” በማለት ለሰይፍ ለእሳት አልዳረጉትም፡፡  “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ÷ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር÷…”(ማቴ.23÷37) በማለት መድኀኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረባት የኢየሩሳሌም ሰዎች እንኳ ፊት፡- ነቢያትን፣ የእግዚአብሔርን ሰዎች፤ ኋላም ሐዋርያትን ያሳደደችና የወገረች መሆኗን ገልጦ ተናግሯል፡፡

 

በዳዊት መዝሙር ውስጥ “እግዚኦ መኑ የኀድር ውስተ ጽላሎትከ፡፡ ወመኑ ያጸልል ውስተ ደብረ መቅደስከ…ዘያከብሮሙ ለፈራሀያነ እግዚአብሔር፤ አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?”(መዝ.14÷1-4) የሚል ቃል ይገኛል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቅዱሳን ነቢያትን፣ ሐዋርያትን ካህናትን በአጠቃላይ ከእግዚአብሔር የተላኩትን ማክበር እነርሱን የላከ ፈጣሪን ማክበር ነው፡፡ እነርሱን መቀበል የላካቸውን መቀበል ነው፡፡ ይህም ሊታወቅ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ በሰጣቸው ሐዋርያዊ ተልእኮ ውስጥ፡-“እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል÷ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል” በማለት የተናገረውን ልብ ይሏል፤(ማቴ. 10÷40) በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደተጠቀሰው ያ ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ሲወጣ አንካሳ ሆኖ የተወለደውና በቤተ መቅደስ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረውን ሰው÷ ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ “ወደ እኛ ተመልከት” በማለት ባዘዙት ጊዜ ወደ እነርሱ ተመልክቶ ከደዌው ለመፈወስ ችሏል፡(የሐዋ.ሥራ.3÷4-6) እኛም ወደ ቅዱሳን ገድል፣ ቃል ኪዳናቸው… ብንመለስ ወደ እግዚአብሔር መመለሳችን እንደሆነ አስበን÷ በቅዱሳኑ ጸሎት ምልጃና ቃል ኪዳን ለመጠቀም እንችል ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት አይለየን፡፡

 

3ኛ ኃጢአት በደልን አምኖ ንስሐ መግባትን ከነነዌ ሰዎች ልንማረው የሚገባን ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን በኀጢአት በበደል እንዲጸኑ ከሚያደርጓቸው ሁኔታዎች አንዱ ምክንያተኝነት ወይም ለራስ ይቅርታ ማድረግ ነው፡፡ በኀጢአታችን ንስሐ መግባት እየተጠበቀብን ነገር ግን ለፈጸምነው ስህተት ሌላ ምክንያት ስናቀርብ እንሰማለን፡፡ ይህ ነገርም ቅጣታችንን ያበዛው እንደሆነ እንጂ በበደል ከመጠየቅ ነጻ አያደርገንም፡፡ በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ እንደተገለጠው “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል፡፡”(ምሳ.28÷13) የነነዌ ሰዎች የሚያተምሩን አንዱ ነገር ኀጢአት በደልን መታመንን ነው፡፡ ስለሆነም ለበደላችን ምክንያትን የምንደረድር ሰዎች ምን ያህል ከጸጋ እግዚአብሔር እንደተራቆትን ልናስብ ልንጸጸትም ይገባናል፡፡ ንጉሥ ዳዊት ቤርሳቤህን አስነውሮ÷ ኦርዮንን ባስገደለ ጊዜ እግዚአብሔር በነቢዩ በናታን አድሮ ስለኀጢአቱ ሲወቅሰው፡-“ዳዊትም ናታንን፦ እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው።” ተብሎ ነው የተጻፈው(2ኛ.ሳሙ12÷13)፡፡ ኃጢአት በደላችንን ብናምን እንደ ቅዱስ ቃሉም በካህናትም ፊት ቀርበን ብንናዘዝ አምላካችን ከኀጢአታችን ሊያነጻን የታመነ ነው፡፡ “በኀጢአታችን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡”ተብሎ እንደ ተጻፈ፡(1ኛ.ዮሐ.1÷8-9) እንግዲህ ከዚህ በመማር እንደ ሰብአ ነነዌና እንደ ዳዊት ኀጢአታችንን በማመንና ንስሐ በመግባት ምሕረት እንድናገኝ አምላካችን ይርዳን፡፡ዳዊት ኀጢአቱን በታመነ ጊዜ “ናታንም ዳዊትን፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኀጢአትህን አርቆልሃል አትሞትም” ብሎታል፡፡ “የነነዌ ሰዎችም ከክፉ መንገዳቸው እንተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም፡፡” (2ኛ.ሳሙ12÷13፤ዮና.3÷10)

 

4ኛ ፍጹም የሆነ የጾም የጸሎት ሕይወትን እንማረለን፤ ሰብአ ነነዌ ባለማወቅ ሠርተውት ሊመጣባቸው ካለ መአት ለመዳን፣ ወደ እግዚአብሔርም ለመመለስ የተጠቀሙበት የጾም የጸሎት መንገዳቸው ፍጹም ሊያስተምረን ይገባል፡፡ በትንቢተ ኢዩኤል ላይ ፈጣሪያችን  እግዚአብሔር፥ “በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ።” (ኢዩ.2÷12)ብሎናል፡፡ ስለሆነም በፍጹም ልባችን (ያለ ተከፍሎ ልቡና) ወደ ፈጣሪይችን ተመልሰን ቸርነት ምሕረቱን ደጅ ልንጠና ይገባናል፡፡ የነነዌ ሰዎች ለሦስት ቀንና ለሦስት ሌሊት  በፍጹም ልቡናቸው ተጸጽተው፣ ጹመው ጸልየው  ምሕረትን አግኝተዋል፡፡ እኛ በቁጥር ከዚያ የበለጠውን ጾመን፣ ጸልየን ልመናችን ምላሽ ያላሰጠን ለምንድር ነው? በእርግጥ ጾም ጸሎታችን በፍጹም ልቡና የቀረበ ነው? በትንቢተ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል ቃልተጽፎ እናነባለን፡- “ስለ ምን ጾምን አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን÷ አንተም አላወቅህም? ይላሉ፡፡እነሆ÷ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ÷ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ፡፡ እንሆ÷ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን?ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን?እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን?እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል።”(ኢሳ.58÷3-9)

 

እንግዲህ ከነነዌ ሰዎች ተምረን ጾም ጸሎታቻንን÷ ከቂም፣ ከበቀል፣ ከአመጻና…ይህን ከመሳሰለው የሥጋ ፈቃድ ሁሉ ለይተን በፍጹም ልባችንና በፍጹም ሰውነታችን ወደ እግዚአብሔር በመመለስ÷ ንጹህ መስዋእት አድርገን ልናቀርበው ይገባናል፡፡  ፈጣሪያችን ልኡል እግዚአብሔር ወርሃ ጾሙን የንስሐ የምሕረት ያድርግልን! ለሰብአ ነነዌ የተለመነ ለእኛም ይለመነን! አሜን!!