የጳጉሜን ወር
በዓመት ውስጥ ካሉት ወራት የተለየች፣ ቀኖቿም ጥቂት እንዲሁም አጭር በመሆኗ የጳጉሜን ወር ተናፋቂ ያደርጋታል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን ኢትዮጵያ ካደላት ስጦታ አንዷ የሆነችውም ይህች ወር በዘመነ ዮሐንስ ስድስት ቀናት እንዲሁም ደግሞ በዘመነ ማርቆስ፣ በዘመነ ሉቃስና በዘመነ በማቴዎስ አምስት ቀናት ብቻ አላት፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አስትምህሮ የጳጉሜን ወር የዓመት ተጨማሪ ወር እንላታለን፡፡ ምዕራባዊያኑ ግን ተጨማሪ ቀን እንደሆነች በማሰብ በዓመቱ ባሉ ወራት ከፋፍለዋታል፡፡
ጳጉሜን የሚለው ስያሜ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም “ጭማሪ” ማለት ነው፡፡ በግእዝ “ወሰከ-ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ተውሳክ (ተጨማሪ) ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መዝገበ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት፤ ገጽ ፱፻፭)