Kaleawadi

ቃለ ዓዋዲ

ጥቅምት 13 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ኅሩይ ባ


Kaleawadiቃለ ዓዋዲ ቀጥተኛ ትርጉሙ “የአዋጅ ነጋሪ ቃል” ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ብሎ የተነበየለት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ነበር፡፡ /ኢሳ.40፥1፵፥፩/ ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዊ ልደት ስድስት ወራትን ቀድሞ የተወለደው ቅዱስ ዮሐንስ ጥርጊያውን እያስተካከለ ሰዎችን ለንስሐ እየጠራ ለአማናዊው በግዕ ለኢየሱስ ክርስቶስ አዘጋጅቷቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብም /ቃለ ዓዋዲ/ ሦስቱ ጾታ ምእመናንን/ ካህናት፣ ወንዶች እና ሴቶች/ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እየተመሩ ሕይወታቸውን እንዲጠብቁ ስለሚያውጅ ቃለ ዓዋዲ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ቃለ ዓዋዲ የተባለው መጽሐፍ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለውን አስተዳደራዊ መዋቅር ያካተተ የሕግ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህም ብቻ ሳይወሰን ከምእመናን ጀምሮ እስከ ካህናት ድረስ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መብትና ግዴታ በውሉ የሚያስገነዝብ መመሪያም ነው፡፡

 

ቃለ ዓዋዲ ቤተ ክርስቲያናችን የምትመራበት የሕግ መጽሐፍ ነው ሲባል፤ ቃለ ዓዋዲ ከመኖሩ በፊት ቤተ ክርስቲያን በምን ትተዳደር ነበር? የሚል ጥያቄ ያስነሣ ይሆናል፡፡ ይህንን ጥያቄ የምንመልሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ለረዥም ዘመን በሓላፊነት አገልግለው በሞተ ሥጋ የተለዩንን የአባ አበራ በቀለን የአንድ ወቅት ቃለ ምልልስ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አባ አበራ በቀለ እንዳሉት “ቃለ ዓዋዲ ከመፈጠሩ በፊት ቤተ ክርስቲያናችን ትመራበት የነበረ አስተዳደራዊ መዋቅር አላት ከኒቂያ ጉባኤ በፊትም ቢሆን የአስተዳደር ሥርዓት ነበራት፡፡ ከሁሉ በፊት ግን እንደ ሕግ ሆኖ የሚመራት ዋናው የሕግጋት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ እርሱም የሃይማኖትና የሥነ ምግባርን ሕግ የያዘ ነው፡፡ በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ዘመን አባቶቻችን በዚህ ሲገለገሉ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይመሰክራል ወደ ሀገራችንም ስንመጣ ፍትሐ ነገሥቱ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡

 

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ መንግሥት ከአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ ንግሥ ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ድረስ አንድነት ነበራቸው፡፡ ቤተ መንግሥት ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ይገባ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ወደ መንግሥት አስተዳደር ትገባ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ፍትሐ ነገሥቱ በሁለቱም ወገኖች ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በዓፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ አዳዲስ ሕጎች ሲወጡ ፍትሐ ብሔሩና ወንጀለኛ መቅጫው ሲወጣ የፍትሐ ነገሥቱ አሠራር እየቀዘቀዘ በአዲስ እየተተካ ሄደ፡፡ እንደሚታወቀው ፍትሐ ነገሥት ሁለት ክፍል አለው እርሱም፡-

 

  • ፍትሕ መንፈሳዊና
  • ፍትሕ ሥጋዊ በመባል ይታወቃል፡፡

 

ፍትሕ መንፈሳዊ አሁንም በቤተ ክርስቲያን ተጠብቆ እየተሠራበት ነው፡፡ የሥጋዊ አስተዳደሩ ደግሞ በቤተ መንግሥት በኩል በሌላ አዋጅ ተተክቷል፡፡”

 

በዓለመ መላእክት፣ በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት፣ መላእክትና ሰዎች እግዚአብሔርን ያመልኩበት የነበረ ሥርዓት አለ፡፡ በዘመነ አበው፣ በዘመነ መሳፍንት፣ በዘመነ ነገሥት፣ በዘመነ ነቢያትና በዘመነ ሐዲስም ይህ ሥርዓት የጸና ነው፡፡ የሥርዓት አስፈላጊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ የተቀመጠ በመሆኑ አሁንም ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ለማኅበረ ምእመናን ሥርዓት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለ ሥርዓት፣ ያለ ሕግ፣ ያለ ደንብ፣ ያለ መዋቅር የምትሠራው ምንም ዓይነት አገልግሎትና ድርጊት የለም፡፡ ሊቀ ጉባኤ እንዳሉት የሕግ ሁሉ ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጎ በፍትሕ መንፈሳዊና በፍትሕ ሥጋዊ ተጣምሮ አገልግሎቱን ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ፍትሕ ሥጋዊ ወደ መንግሥት አስተዳደር ተጠቃልሏል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን ራሷን ችላ የምትመራበት ሕግ እንዲጸድቅላት በጠየቀችው መሠረት ከምእመናን ምጣኔ ሀብታዊ ጋር በተገናዘበ መልኩ ሁሉንም የሚያሳትፍ መዋቅር በሁለተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና የመጀመሪያው ቃለ ዓዋዲ ጥቅምት 14/፲፬ ቀን 1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ታተመ፡፡ ቃለ ዓዋዲው ከመውጣቱ በፊት ረቂቁ  ለፓርላማ ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ለምእመናን እንዲደርስ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ በነጋሪት ጋዜጣ መልክ ወጣ፡፡ ይህ ቃለ ዓዋዲ ከ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም እስከ 1970/፲፱፻፸ ዓ.ም ለአምስት ዓመታት ያህል እንዳገለገለ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ አያይዘው ገልጠዋል፡፡

 

የቃለ ዓዋዲው ተቀዳሚ ዓላማ

ሀ. ቅድስት፣ ከሁሉ በላይ ሐዋርያዊትና አንዲት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅና አገልግሎቷም የተሟላ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ሓላፊነት የሚወጡት ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ድረስ የሚገኙት የሥራ ሓላፊዎች ናቸው፡፡

ለ. የካህናት የኑሮ ደረጃ የተሻለ ሆኖ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በትጋት እንዲወጡ ማድረግ፡፡

ሐ. የምእመናን ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እንዲጨምር እና ያሉትንም በምግባር በሃይማኖት ማጽናት፤ በመንፈሳዊ ዕውቀት እንዲበለጽጉ ማገዝ፤ ሁኔታዎችንም ማመቻቸት፡፡

መ. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንዲሻሻል የገቢ ምንጮችና ልማቶች ተበራክተው በገንዘብ አቅም የጎለበተች ቤተ ክርስቲያን ሆና ከተረጂነት እንድትላቀቅ ማድረግ ነው፡፡

 

እነዚህን ዓላማዎች ግቡ አድርጎ የተመሠረተው ቃለ ዓዋዲ አፈጻጸሙ እንዲሳካ ከምእመናን ጀምሮ ሥልጣነ ክህነት እስካላቸው አገልጋዮች ድረስ የሠመረ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ምእመናን ስለ ቃለ ዓዋዲ ያላቸው ግንዛቤ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዞ ምቹ መሆን የካህናት ድርሻ ብቻ የተሟላ አያደርገውም፡፡ የምእመናንም ድርሻ ከፍተኛውን ድርሻ መያዝ አለበት፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ለተወሰኑ አካላት ብቻ የማንተወው በመሆኑ የእነሱና የእነሱ ሓላፊነት ብቻ እንደሆነ ማሰብ የለብንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሦስቱም ጾታ ምእመናን ናትና ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

 

ቃለ ዓዋዲ ተደንግጎ ጸድቆ ሰበካ ጉባኤ ተቋቁሞ በሥራ ላይ ውሎ አሁን ካለበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ በ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶችን በመጥራት የመጀመሪያውን የቃለ ዓዋዲ ረቂቅ ለውይይት አቅርበዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በሸዋ ሀገረ ስብከት በዐሥራ አንድ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ስለ ቃለ ዓዋዲ ለካህናትና ለምእመናን ማብራሪያ በመስጠት አዲሱን እቅድ አስተዋውቀዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ልኡካንን መድበው በየአህጉረ ስብከት እየተዘዋወሩ እንዲያስተምሩ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

ሆኖም ካህናቱና ምእመናኑ ተወካዮችን መርጠው ሰበካ ጉባኤና ቃለ ዓዋዲ የሚባል በባህላችን የማይታወቅ አዲስ አሠራር መጣብን ብለው ለንጉሠ ነገሥቱ /ኀይለ ሥላሴ/ አቤቱታ እስከማቅረብ ደርሰው ነበር፡፡

 

ይህንና የመሳሰሉትን ችግሮች ተሻግሮ በአገልግሎት ላይ የሚገኘው ቃለ ዓዋዲ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ ከወጣበት ከ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ጀምሮ ለ5/፭ ዓመታት አገልግሎ በ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም የተለያዩ ማሻሻያዎች ታክለውበት ለሁለተኛ ጊዜ ታትሟል ከ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም እስከ 1991/፲፱፻፺፩ ዓ.ም መግቢያ ድረስ ለሃያ አንድ ዓመታት ያገለገለው ቃለ ዓዋዲ ዳግመኛ ተሻሽሎ ለሦስተኛ ጊዜ በ1991/፲፱፻፺፩ ዓ.ም ታትሟል፡፡

 

ጥቅምት 7-11/፯‐፲፩ ቀን 2004/፳፻፬ ዓ.ም 30/፴ኛው መደበኛ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የኢሉባቡርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አሳሳቢነት ቃለ ዓዋዲው ለአራተኛ ጊዜ እንዲሻሻል አሳብ አቅርበዋል፡፡ ምልዓተ ጉባኤውም ቃለ ዓዋዲው ተሻሽሎ እንዲወጣ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል፡፡ የጉባኤው የውሳኔ አሳብ የሚፈጸመው በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ የጉባኤውን የውሳኔ አሳብ እንዲመለከተው ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡

 

በ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው ቃለ ዓዋዲ በ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣበት ምክንያት በተለይ በ1966/፲፱፻፷፮ ዓ.ም በሀገራችን የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረቷን መንግሥት በውርስ ሲወስደው የገቢ ምንጮች ደረቁ፡፡ የኮሚኒስቱ ፓሊሲ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የማይመችም ነበር፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎች በመንግሥት ተወረሱ፡፡ በመጀመሪያው ቃለ ዓዋዲ ስለ መሬት ርስትና ስለ ቤት ኪራይ የሚናገር አንቀጽ ነበረው፡፡ ይህ ድንጋጌ ለደርግ መንግሥት ጥቅም አላስገኘለትም፡፡ ስለዚህ ተስፋፍቶና ተሻሸሎ እንዲታተም ግድ በመሆኑ በ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም በሚያዝያ ወር ተሻሽሎ ወጣ፡፡

 

ለሦስተኛ ጊዜ በ1991/፲፱፻፺፩ ተሻሽሎ እንዲታተም ያስፈለገበት ምክንያት ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ካህናትና ዲያቆናት ለመሆን የበቁ አገልጋዮች በዘፈቀደ ሳይሆን በደብሩ አስተዳዳሪ ተመስክሮላቸው የትምህርት ደረጃቸው ታይቶ ክህነቱን እንዲቀበሉ፣  ወጣት ዲያቆናት ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት እየገቡ እንዲማሩና ካህናቱም የሰንበት ትምህርት ቤቶች መርሐ ግብርን ከሚያስተምሯቸው በተጨማሪ በጸሎት ጀምረው በጸሎት እንዲዘጉ፣ የቤተ ክህነት አገልጋዮች ዕድሜ ጣራ 60/፷ ዓመት እንዲሆን፣ ከደመወዛቸውም ከመቶ እጅ የተወሰነ እንዲከፍሉ፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ፣ ሥራ አስኪያጅ ሥልጣንና ተግባር የወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት ሥልጣንና ተግባር እያለ በመጠኑ የተገለጸውን ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ከቅዱስ ፓትርያርኩ የሚጠበቀውን ሥልጣንና ተግባር በስፋት አብራርቶ ለማስቀመጥ ታስቦ ነው፡፡

 

በ2004/፳፻፬ ዓ.ም 30/፴ኛው መደበኛ አጠቃላይ ዓመታዊ ጉባኤ ሲካሄድ ለአራተኛ ጊዜ እንዲሻሻል ያስፈለገው በቃለ ዓዋዲው እየታየ ያለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ክፍተት ነው፡፡ ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያን በቋሚ ሠራተኛነት ቀጥራ ከምታሠራቸው ሠራተኞች መካከል ጥቂቶቹ ገንዘብ ሲያጎድሉ በቤተ ክህነት ሒሳብ መርማሪዎች ኦዲት ተደርገው ባለዕዳ መሆናቸው ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ ዕዳቸውን መክፈል ያልቻሉትን ሕገ ወጥ ሠራተኞች በፍርድ ቤት ለመክሰስ አግባብ ባለው የሕግ አካል ቢጠየቁም የቤተ ክህነት ሒሳብ መርማሪዎች የሒሳቡን ሥራ ለማከናወን ሕጋዊ ዕውቅና የላቸውም? የሚል መከራከሪያ በማንሣት ጉዳያቸው በፍጥነት እንዳይታይና እልባት እንዳይሰጠው ይከራከራሉ፡፡ በቃለ ዓዋዲው ሕገ ደንብ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ ባሉት መዋቅሮች የሒሳብ በጀት ክፍል ስላለ በዚህ ክፍል ሒሳቡ እንዲመረመር ያዛል፡፡

 

በመሆኑም ቃለ ዓዋዲ የሒሳብ ጉዳዮችንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተነተነበት አንቀጹ ለፍትሕ መንፈሳዊና ለፍትህ ሥጋዊ በማያሻማ ሐተታ ቢብራራ አግባብ ባለው የሕግ አካል ለመክሰስም ሆነ ለመጠየቅ ያስችላል፡፡

 

የቃለ ዓዋዲ ሕገ ደንብ ለምእመናን ለካህናትና ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ያለው ጠቀሚታ የጎላ ነው፡፡ በሥርዓተ ተክሊል በቅዱስ ቁርባን የተጋቡ ባለትዳሮች ቢጋጩ ወደ ፍርድ ቤት ከሚሔዱ ይልቅ በፍትሕ መንፈሳዊ ቢዳኙ ምንኛ ደስ ይላል፡፡ ካህናትም የቃለ ዓዋዲውን ሕገ ደንብ ጠብቀውና አስጠብቀው ዐሥራት በኩራቱን ሰብስበው ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያንን ወደ ተሻለ እድገት ቢያሸጋግሩበት መልካም ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተቃና እንዲሆን እንደ ቃለ ዓዋዲው ድንጋጌ ሓላፊነትን መወጣት ከተቻለ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ካለባት አስተዳደራዊ ችግር መላቀቅ ትችላለች፡፡

 

ባለፈው ዓመት ቃለ ዐዋዲው እንዲሻሻል የቀረበው አሳብ መክኖ እንዳይቀር ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ሕገ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ከተሻሻለ መዋቅሮቻችን ከተጠናከሩ አገልጋዮችም በሞያቸው በሓላፊነትና በተጠያቂነት መሥራት የሚችሉት የደንባችን አጥር ሲጠብቅ ነው፡፡

 

ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ለሁሉም ናት፡፡ ማንም ቢመጣ ማንም ቢሄድ ቤተ ክርስቲያን ሁሉን ታሳልፋለች፤ እሷ ግን አታልፍም፡፡ እኛ ብናልፍ ሥራችን ሕያው ምስክር ሆኖ እንዲኖር በሕጋችን መሻሻል ላይ በደንብ እንምከርበት፣ በሚገባ እናስብበት፣ በብስለት እንወያይበት፡፡ በምክክራችን ጊዜ ባለሞያዎችን እናሳትፍ፤ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን አዲስና ብሩህ ተስፋ ዛሬን እንሥራበት፡፡

 

“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” /ሐዋ.20፥28/፳፥፳፰

 

እግዚአብሔር አምላካችን ቤተ ክርስቲያናችንን ከጥፋት ይጠብቅልን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል

ቤተ ክርስቲያንን ጠብቋት

ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

አባ ዘሚካኤል

ቅድሚያ ለቤተ ክርስቲያን እንቁም! ምን እንደምትልም እንጠብቃት (እንስማት)!

“ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ ዘሎቱ ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳተ ከመ ትርአዩ ቤተ ክርስቲያኑ ለክርስቶስ እንተ አጥረያ በደሙ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (የሐዋ.20፥28)፡፡

 

ፓትርያርክ ለመሾም:-

  • ሁሉም ድርሻው እስከምን እንደሆነ ይወቅ!
  • የሲመቱ ሂደት ምንም ይሁን ምን የተዋሕዶ ምእመናንን ሊከፋፍል በሚችል መንገድ ለሚሠሩ በር አንክፈት!
  • አንድነታችን የበለጠ እንዲጸና እንጸልይ!

 

ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ፡ ’አሁንም ራሳችሁን ጠብቁ’ የግእዙ ትርጓሜ ሲል’፣ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ’ለራሳችሁ ተጠንቀቁ’ ይላል፡፡

 

ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው፣ የቅዱስ ጳውሎስን የማስጠንቀቂያ ምክር በጊዜው የመንጋው ጠባቂ ለሆኑት አባቶች መጀመሪያ “ራሳችሁን ጠብቁ’ ነው ያላቸው፡፡ በመሆኑም ይህን የቅዱስ ጳውሎስ ምክር የተረዱ አባቶቻችን ከሁሉ በፊት  ራሳቸውን በመልካም መንገድ ማቆምን ቅድሚያ ሰጥተዋል፡፡ በመሆኑም ራሳቸውን ከእምነት ለመለየት ከሚፈታተኗቸው:-በሥጋዊ ድካም ከሚመጡ ይሁን በሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች ከሚነሡ እኩያት አሳቦችና ተግባራት ራሳቸውን ጠብቀው ይኖራሉ። ከሌላ ስለሚመጣው ፈተና ምክንያት ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል ”ወአነ አአምር ከመ ይመጽኡ እምድህሬየ ተኩላት መሰጥ እለ ኢይምህክዋ ለመርዔት፤ ከኔ በኋላ ለምእመናን የማያዝኑ ሰውን እየነጣጠቁ ወደ ገሃነም የሚያወርዱ ሐሰተኞች መምህራን እንዲነሡ አውቃለሁ” (ማቴ፣ 7: 15) ይላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ዋናው ነገር ሐሰተኛ መምህራን ሊያሳስቱ የሚሞክሩት ምእመናንን ብቻ አይደለም ታላላቆችንም ነው እንጂ፤ ከዚህ በፊት ከታየው ልምድ ለቤተ ክርስቲያን የጠቀሙ በመምሰል አባቶችን ወደ አላሰቡት ስህተት የሚጥሉ አሉ፣ ሰይጣን እንኳን ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ሊፈታተን ቀርቦ የለምን? ከላይ በተመሳሳይ ”ከኔ በኋላ ለምእመናን የማያዝኑ ሰውን እየነጣጠቁ ወደ ገሃነም የሚያወርዱ ሐሰተኞች መምህራን እንዲነሡ አውቃለሁ” ተብሏልና፡፡  ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ ነገር ለምሳሌ፣ መከፋፈል እንዲፈጠር ሊያደርግ የሚችል ምክንያት እንዳይገኝ በየግል መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ቀጥሎም ጳጳሳትን በቡድን ማለትም ሲኖዶሱን ’ራሳችሁን ጠብቁ’ ማለት በመካከል የሚፈጠር አለመግባባት እና ሌላም ምክንያት እንዳይለያያችሁ ቀድማችሁ ጥንቃቄ አድርጉ ሲል ነው፡፡ በመከፋፈል ለሰይጣንና ለሠራዊቱ የተከፈተ በር፣ ከተከፈተ በኋላ እንኳን መልሶ ለመዝጋት ይቅርና የበሩን መዝጊያውን ለማግኘት የሚቸግር ይሆናል፡፡ ካለፈው የመከፋፈል ልምድ እንደ ተረዳነው፣ በሁለት መከፈል ሳይበቃ መዘዙ ወደ ብዙ ትንሽ ክፍፍል ጭምር ማምራቱን  መዳኘትና መግታት ወደ ማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ይህ ሁኔታ ወደፊት ምን ሊሆን እንደሚችል አምላክ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በጸሎት እንጠይቀው፡፡

 

“ወኵሎ መራዕየ፣ ምእመናንን ሁሉ ጠብቁ፡፡ ዘሎቱ ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳተ፣ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳት አድርጎ የሾማችሁ እናንት ዕቀቡ ጠብቁ” ብሎአል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሹመት ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ማንም ሰው ደግም ይሥራ ክፉ፣ የሚሾመው ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡” ከመ ትርአዩ ቤተ ክርስቲያኑ ለክርስቶስ እንተ አጥረያ በደሙ፣ በወርቀ ደሙ የዋጃትን የምእመናንን አንድነት ትጠብቋት ዘንድ የሾማችሁ፡፡” አባቶች የሚጠብቁት የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑትን ምእመናንን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ስንል የምእመናን አንድነት በመሆኑ፣ ከአባቶች ጠብቆት ውስጥ ምእመናንን ከመከፋፈል፣ ከኑፋቄ፣ ወዘተ በሽታ መከላከል ዋናው ተግባር ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ምእመናን በሀገር ውስጥ ሲኖዶስ፣ በውጭ እና ከዚህም ከዚያም የሌለ በሚል ተከፋፍለን በመለያየት ተውጠን ከርመናል፡፡ እግዚአብሔር ሲኖዶሱን” ወኵሎ መራዕየ፣ ምእመናን ሁሉ ጠብቁ” በማለቱ ሁሉም ምእመናን ከመሰናከል የሚድኑበት፣ ከፋፋዮች ምክንያት የሚያጡበት፣ መናፍቃን የሚያፍሩበት፣ አንድነትን የሚያመጣ ቁርጥ ውሳኔ የሚሻበት ወቅት ነውና መንጋው በመከፋፈል ከመጥፋት አባቶች እንዲታደጉት ጊዜው ግድ ይላል፡፡

 

የመንጋው ጠባቂዎች የተባሉት ቅዱስ ሲኖዶስ በዋናነት ሲሆን ከሊቃነ ጳጳሳት ቀጥሎ በቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች በተዋረድም ሀገረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነትና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉትን ሲሆን፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር መንጋ የተባሉት መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ምእመናንን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ከነዚህም ዋና ውሳኔ ሰጭው የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

 

ቅዱስ ሲኖዶስ የፓትርያርኩ፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት መሪው መንፈስ ቅዱስ የሆነ ዐቢይ ጉባኤና የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት ነው፡፡ በማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወሰነው ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ ይሆናል፡፡ ፓትርያርኩ ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ሊለውጡ አይችሉም፡፡ፓትርያርኩንም መርጦ የሚሾመው ይኸው ጉባኤ ነውና፡፡ ሁሉም ክርስቲያን በእኩል መረዳት ያለበት የሲኖዶስ አባላት ሲመረጡ እንደ ሕግ እግዚአብሔር መሆኑንና እግዚአብሔር ሳይፈቅድ ጳጳስ መሆን እንደማይቻል ነው፡፡ ሁለተኛም የተሰጣቸው ሓላፊነት ከእግዚአብሔር እንደመሆኑና የዘወትርም ሥራቸው በመሆኑ፣ ሁልጊዜም መንጋውን በመጠበቅ ለቤተ ክርስቲያን ስጋት የሆነውን ጉዳዮች በመለየት ጥንቃቄ ያደርጋሉ ብለን ማመን ይኖርብናል፡፡

 

እኛ ምእመናንም ደግሞ ማሰብ ያለብን አይነተኛ ነገር አለ፣ ይህም ለመንጋው ጠባቂዎች በትክክል ታዛዣቸው ነን? በጎቻቸው ነን ወይ?  ብለን እራሳችንን መመርመር አለብን፡፡ ለንባብ የበቃ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንኳን እንደሚታየው ትኩረት ሳይሰጠው ከመታለፉ አልፎ እንደውም ማጣጣል ሲደረግበት ነው የሚስተዋለው፡፡ በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ አባቶቻችንን እንድንጠራጠር የሚያደርጉንን ወሬዎችን በመስማት ወሳኞቹ እኛ ሳንሆን አስቀድመን መሆን አለበት ብለን ወስነን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚወስነው ጋር እንዳንጋጭ ከወዲሁ፣

 

  1. ከማን መስማት እንዲገባን መመርመር የለብንም ይሆን?

  2. አስቀድመን ለመወሰንስ እኛ ማን ነን?

  3. የቅዱስ ሲኖዶስ ከሳሽ መሆን ይጠቅመን ይሆን?

  4. የቅዱስ ሲኖዶስ መሪ መንፈስ ቅዱስ ነው ካልን መንፈስ ቅዱስ አይጠብቃቸውምን?

  5. ቤተ ክርስቲያን የሾመቻቸው ሊቃውንት ከሃምሳ በላይ ሊቃነ ጳጳሳት አንድ ላይ ሆነው መክረው የሚወስኑት ውሳኔ ሳንቀበል በአንድ ሚዲያ ላይ አሰማምሮ ወይም አጣጥሎ በተጻፈ ጽሑፍ የምንረበሽ እና የምንፈተን ከሆን ስህተቱ የማን ይሆን?

  6. መረጃዎችን ማወቅ ጥሩ ሲሆን፣ ነገር ግን ከእምነት አንጻር የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የማጣጣል ሁኔታ የመልካም ይሆን?

 

የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማንሣትና ቀድሞ ሰው ካለው ልምድ እንዲሁም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር መጪውን ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ጋር መቆም እንዴት ይኖርብን ይሆን? ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም እስከ አሁን ከተለያዩ ጽሑፎች እንዳነበብነው፣ ከተለያዩ አስተያቶች እንደ ሰማነው፣ በጣም የሚገርመው መቼም፣ ምንም ሊጣጣሙ የማይችሉ አሳቦች ከተለያዩ ጽንፈኞች ሲቀርቡ ተስተውለዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ባንድ ወገን መጀመሪያ እርቁ ይቅደም በሚል በሚገባ መረጃ አሳማኝ ነገር ሲቀርብልን በሌላ ወገን የእርቁ አካላት የተባሉ ጨርሶ የእርቅ አሳብ እንዳልተነሣ ሁሉ እንደገና ለእርቁ መፈጸም እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሁኔታ አደረጉ ወይም ለአዲስ መለያየት መንገድ ይከፍታል የሚያሰኝ መረጃ ተቀናብሮ የቀረበ ስናይ እንዴት ይሆን ይህ አሳብ የሚታረቀው? መቼ ይሆን እርቁ የሚፈጸመው? የሚል ጥያቄ እንድናነሣ ሁላችንንም ግድ አይለን ይሆን? በዚህ የተዘበራረቀ ሁኔታ አባቶችስ የምርጫውን ጉዳዩ እስከ መቼ ሊያቆዩት ይችሉ ይሆን? በዚህ ሁኔታ ላይ ባለድርሻ አካላት ሳያምኑበትና በወቅቱ ለቤተ ክርስቲያን ይጠቅማታል ብለው ባልወሰኑት የኛ ማጉረምረም ምን ጽድቅ ይፈጽም ይሆን? ሁል ጊዜም ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳት አባላቶቿ ከአባቶች መንፈሳዊ እልባትና ከቅዱሳት መንፈሳውያን መጻሕፍት ምክር ይልቅ በዓለማውያን ፍልስፍና ስንደገፍ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ”እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም። ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን” (1 ቆሮ 2: 13-16) ይለናል።

 

ሌላው ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ይጠቅማል ያሉትን ከምርጫው ጋር የተያያዙ የተለያዩ አሳቦች ሲያቀርቡ ተስተውለዋል፡፡ ግብአቱ መልካም ነው፣ በተለይ ሚዲያዎችን የሚከታተሉ ምእመናን፣ የሚጻፉ አሳቦችን ሁሉ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በላይ በማድረግ የማየቱን ጉዳይ ነው፡፡ መረዳት ያለብን ፍሬ አሳብ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሚዲያ እንደተጻፈ ሊያውቁም ላያውቁም ይችላሉ፣ በግድም የማወቅ ግዴታ የለባቸውም፡፡ ብፁዓን አበው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሥራቸውን መሥራት አለባቸው እንጂ ተቀባይነትን ለማግኘት ሁል ጊዜ ወደ ሚዲያ መቅረብ አለባቸው አንልም፡፡ በየሚዲያዎች ሁሉም እንደፈቃዱ የጻፈውን ሁሉ ለማስፈጸም ደፋ ቀና ማለት አለባቸውም ልንል አይገባም፡፡ ከማንም ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ሕግና ጊዜውን በዋጀ ውሳኔ ቤተ ክርስቲያንን መምራት ስላለባቸው ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ፡፡ በአባቶች ውሳኔ ማንም ጣልቃ መግባት የለበትም፡፡ የሚወሰነውን ሁሉ በእውነት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በአግባቡ መቀበል ይኖርብናል፡፡ ሁሉም እንዲህ ቢያረግ ማለትም ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ቢገዛ ቤተ ክርስቲያን አንድነትዋ ይጠበቃል፣ መለያየት አይኖርም፣ አንድነታችን ይጸናል፣ ከፋፋይ ያፍራል፣ ይልቁንም ሰይጣን ይመታል፣ በመስቀሉ እውነተኛ ፍቅር ይቀጠቀጣል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሚለየንን ሰይጣን ይቀጥቅጥልን!!!

 

በመሆኑም ቅዱስ ሉቃስ” ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሯቸው (የሐዋ. ሥራ.4፥32)” እንዲል፤ በአንድ ሲኖዶስ ውሳኔ ማዘዝና መታዘዝ ስንተዳደር ነው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው፡፡ ይህ ሲሆን ነው ፍቅርና አንድነት የሚመጣው እንጂ በየቦታው ለራሳችን እንደ ራሳችን አሳብ መምህር ካቆምን እንናገራለን እንጂ በሕይወታችን ዘመን እርቅና አንድነትን ሳናያት ልናልፍ እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር በሕይወታችን ዘመን የቤተ ክርስቲያንን አንድነቷን ያሳየን!!! ሳናይ አይውሰደን ብለን መመኘትና መጸለይ ይገባናል፡፡

 

ባጠቃላይም የአሁኑ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ፣ የፓትርያርክ ምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም እንደሚለው፣ በዓለም ያሉ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ሁሉ በጉዳዩ ያገባቸዋል፤ (ይህንን ስንል ተመሳስለው የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች በመምሰል የኑፋቄና የጸብ መንገድ ሁል ጊዜ የሚምሱትን ሳይጨምር መሆኑን መገንዘብ ያሻል)፡፡  ነገር ግን በፓትርያርክ ምርጫ እያንዳንዱ ሰው ድርሻው እስከምንድነው? የዚህ ጥያቄ ምክንያት፣ ምእመናን በተለይ በውጭ አገር ያሉ የተለያየ ሚድያ ስለሚከታተሉ፤ ሚዲያዎቹ በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያኗን ጥቅም የሚፈልጉ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ  የፖለቲካ፣ የተሐድሶ ወዘተ ዓላማና ጥቅም ያላቸው ከወዲሁ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት የራሳቸውን ግምት በመስጠት ምእመናንን የሚያንጽ ወይም የሚረብሽ አሳብ ስለሚበትኑ፤ ከዚህ የተነሣ አንዳንድ ግለሰቦች በራሳቸው ፓትርያርክ የመረጡ ያህል እከሌ ይሁን እስከ ማለት የደረሱ አሉ፡፡ በመሆኑም ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አንጻር የፓትርያርክ ምርጫ ሥርዓትን በመረዳት:-

 

  • ሁሉም ድርሻው እስከምን እንደሆነ ይወቅ!
  • የሲመቱ ሂደት ምንም ይሁን ምን የተዋሕዶ ምእመናንን ሊከፋፍል በሚችል መንገድ ለሚሠሩ በር አንክፈት!
  • አንድነታችን የበለጠ እንዲጸና እንጸልይ!
  • በተለያየ ቤተ ክርስቲያንን በማይወክሉ ሚዲያዎች የሚቀርቡ ነገሮች ሁሉ እንደ ቤተ ክርስቲያን ውሳኔ ሊታዩ አይችሉምና በጥንቃቄ መረጃዎችን እንይ
  • ምእመናንን ሊከፋፍል የሚችሉ ወሬዎች እየተለቀቁ ስለሆነ በጥንቃቄ እንከታተል
  • ሚዲያዎችም ጥንቃቄ ቢያደርጉ በጎ ሚያሰኝ ነው፣ ምእመናንን በመከፋፈል የሚገኝ ጽድቅ የለምና፡፡
  • እግዚአብሔር ከፈቀደው በቀር ማንም ሊመረጥ አይችልምና ከወዲሁ ተረብሸን የወደፊቱ ክርስትናችን ፍቅር የጎደለው እንዳይሆን እንጠንቀቅ
  • ሊመርጡ /ሊወስኑ/ ለሚችሉ ባላደራዎች ፈንታውን እንስጥ እንጂ በማንወስነው ጉዳይ አስቀድመን አንፈርጅ
  • ይልቁንም ሁሉን ማድረግ ለሚቻለው እግዚአብሔር አደራ እንስጥ፡፡

 

በዚህ በቃ ይበለን! ከዚህ በላይ በመከፋፈልና በመለያት እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት አያሳየን!!!

 

ወስብሐት ለእግዚአበሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመሰቀሉ ክቡር አሜን!!!

እነሆ ክረምት አለፈ

 

ጥቅምት 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ


“እነሆ ክረምት አለፈ ዝናሙም አልፎ ሄደ አበባው በምድር ላይ ታየ የመከር ጊዜ ደረሰ የቁርዬውም ድምጽ ተሰማ በለሱ ጎመራ ወይኖቹም አበቡ” መኀ.2፥11-13

 

ከዚህ ቀድሞ እንደተመለከትነው ክረምት ወርኀ ማይ/ውኃ/ ወርኀ ልምላሜ ወንዞች የሚሞሉበት ደመናና ጉም የሚሳብበት ሰማይ በደመና ተሸፍኖ የእግዚአብሔርን ጥበብ የሚያስተምርበት በመብረቅ በነጎድጓድ ድምጽ ታጅቦ ኀይለ እግዚአብሔርን የሚያስረዳበት መሆኑን ተመልክተን ነበር፡፡ አሁን ግን መግቦቱን ጨርሶ እነሆ ክረምት አለፈ ጊዜውንም በክረምት ከሚታየው ልምላሜ ቀጥሎ ለሚመጡ ለአበባና ለፍሬ አስረክቦ ከልምላሜ ቀጥለው የምናያቸው አበባና ፍሬ የሚያስተምሩት ቁም ነገር አለና፡፡

 

ከአበቦች ምን እንማራለን?

አበቦች ውብና ማራኪ አስደሳች ከመሆናቸው የተነሣ የሰው ልጅ በሙሉ አበቦችን ይፈልጋል ምድርም በአበቦች አጊጣ ተሸልማ ስትታይ ክረምት ከለበሰችው ልምላሜ ይበልጥ ታስደስታለች፡፡ “አሰርገዎ ለሰማይ በከዋክብት ወለምድርኒ አሰርገዋ በሥነ ጽጌያት” ሰማይን በከዋክብት አስጌጠው ምድርንም በአበቦች ደምግባት ሸለማት” ብሎ ቅዱስ ያሬድ ዘምሯል፡፡ ከዚህ የምንረዳው አምላካችን የሁሉ ጌጥ መሆኑን ነው፡፡ መጽሐፈ ኪዳን “ሠርጎ ዓለም ሣራሪሃ ለምድር ወኩሎ ተከለ ለሠርጎ ዓለም፡፡” የዓለም ጌጥ ምድርን የፈጠራት ሁሉንም ለዓለም ጌጥ ፈጠረ” ተብሎ ተጽፏል፡፡ በሜትር የማይለካ ሰማይን በከዋክብት፣ በፀሐይ፣ በጨረቃ ስፋቷ በዐይነ ገመድ የማይመጠን ምድር በአበባ ማስጌጥ ከቻለ ለሦስት ክንድ ከስንዝር የሆነ የሰውን ልጅ ማልበስ ማስጌጥ መሸለም ለምን አይችልም? ይችላል እንጂ፡፡ ታዲያ ከላይ የተመለከትናቸው ሁሉ የሚናገሩት የእግዚአብሔርን ከሓሊነት ነው፡፡ አፍ ሳይኖራቸው ይናገራሉ፤ አንደበትም ሳይኖራቸው ይመሰክራሉ፡፡

 

ከዚህ የተነሣ ጌታችን ሲያስተምር እንዲህ አለ “ወበእንተ አራዝኒ ምንተኑ ትሄልዩ ርዕዩ ጽጌያተ ገዳም ዘከመ ይልህቁ ኢይፈትሉ ወኢይጸምው ወባህቱ እብለክሙ ከመ ሰሎሞን ጥቀ ኢለብሰ በኩሉ ክብሩ ከመ አሐዱ እምዕሉ” ማቴ.6፥28፡፡

 

ስለ ልብስስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ! እንዴት እንደሚያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ! አይደክሙም አይፈትሉም ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞን ስንኳን በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም” ብሎ አበቦች ከእግዚአብሔር አግኝተው ነው ጌጥን ውበትን ተጎናጽፈው የሚኖሩት ለእነዚህ አበቦች ውበትን መውደድን የሰጠ እግዚአብሔር ለእኛም ይሰጠናል ብሎ ማመን የሚገባ መሆኑን በመግለጽ ሰው ምን እለብሳለሁ በምን አጌጣለሁ ብሎ ከመጨነቅ ይልቅ እግዚአብሔር በተፈጥሮ ውብ አድርጎ የፈጠረው እንደሆነ በማሰብ የጎደለው ሁሉ ከእግዚአብሔር የሚገኝ እንጂ በጭንቀት በመወጠርና በማማረር እንደማይገኝ ይልቁንም አበቦችን እንዲህ ያስጌጠ አምላክ ለእያንዳንዳችን የሚያስፈልገንን ሁሉ መስጠት የሚችል መሆኑን ማወቅ የተሻለ ነው፡፡ የእኛ ድርሻ መቀበል እንጂ መጨነቅ ሊሆን እንደማይገባም ያስተምረናል አበቦች ይህን ውበት ያገኙት በመጨነቅ አይደለም ሰውስ ከአበባ እንዴት ያንሳል?

 

በትክክል ሰው አበባን ይመስላል አበባ ያብባል በመልካም መዓዛው ከሰው ጀምሮ እስከ ጥቃቅን ፍጥረታት ድረስ ይማርካል ከአበባ ላይ መስፈር የሚፈልጉት ንቦች ብቻ አይደሉም ትንኞችና ዝንቦችም ጭምር እንጂ፡፡ ንቦች ማር ይሠሩበታል ዝንቦችና ትንኞች ደግሞ ቆሻሻቸውን ያራግፉበታል፡፡ ከዚህ በኋላ አበባው ይጠወልጋል ይረግፋል የሚከቡት ንቦችም ሆኑ ትንኞችና ዝንቦች አይፈልጉትም፡፡ አበባ በጊዜ ማራኪና አስደሳች ቢሆን ሲደርቅ ግን የሚፈልገው የለም የሚረግጠው እንጂ፡፡ አበባ ሲደርቅ አበባ መሆኑ እንኳን ይዘነጋል፡፡ በዚያን ጊዜ ወዳጁ ሁሉ ይርቀዋል ያን ጊዜ ወዳጅ የሚሆነው መደፋት አሊያም እሳት ብቻ ነው፡፡

 

ሰውም በእውነቱ ይህን ይመስላል ሲወለድ እናት አባት ዘመድ አዝማድ ወዳጅ በመወለዱ ይደሰታል፡፡ ሲያድግ አንተ ልጅ የማነህ አቡሽዬ የሚለው የሚስመው የሚከበው ይበዛል ሁሉም ምነው እንደዚህ ልጅ በሆንኩኝ አይ ልጅነት እያለ ይመኛል፡፡ ልጁ ካደገ በኋላ ግን እንደ አበባው ደረቅ እያለ የሚያስከፋ የሚያሳዝን፣ የሚያሰቃይም ሕይወቱ አላዋቂ አጫጅ እንደ አጨደው የፈረስ ሳር  ምስቅልቅል ያለ ሀዘንና መከራ የከበቡት ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን አበባውን ዝንቦች ትንኞች እንዲሁም ማር መሥራት የሚችሉ ንቦች እንደሚከቡት ሰውንም እንደመአር የሚጣፍጥ መልካም ሥራ እንዲሠራ የሚረዱት መላእክት ይከቡታል ይረዱታል፤ ይላላኩታል በአንጻሩ ደግሞ እንደ ቆሻሻ የኀጢአትን ክምር የሚጭኑበት አጋንንት እንደ ትንኝና ዝንብ ከበው ኅሊናውን በክፉ ሐሳብ ያቆሽሹታል፡፡ በመላእክት ተከቦና ታጅቦ መልካም ሥራ ሲሠራ እግዚአብሔርንም ሰውንም ራሱንም መላእክትንም ያስደስታል፡፡ በፍቅሩም አሕዛብን ይማርካል፡፡ በሌላ መልኩ አጋንንት እንደዝንቦችና ትንኞች በላዩ ላይ ሰፍረው የኀጢአት ቆሻሻቸው መጣያ አድርገውት ክፉ እየሠራ ሲታይ እግዚአብሔርንም መላእክትንም ሰውንም ያሳዝናል አበባው ደርቆ ሲወድቅ እንደሚያስጠላ እርሱም ያንን ይመስላል፡፡

 

ከዚህ የተነሣ ነው ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ያስተማረው “ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው፡፡ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው፡፡ ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል” ኢሳ.40፥6-8 የሰው ልጅ ሕይወቱ እንዲህ እንደ ሣር ጠፊ እንደ አበባም ረጋፊ ከሆነ በዚህ ጊዜው ንስሐ መግባት ሥጋውን በልቶ ደሙን መጠጣት፤ ስርቆትን፣ ዝሙትን፣ ሐሰትን፣ ትዕቢትን፣ ተንኮልን፣ ክፋትን፣ ቂምን፣ በቀልን፣ ሥጋዊና ሰይጣናዊ ቅናትን አስወግዶ ወደ ፈጣሪው መቅረብ ይገባዋል፡፡ አበባ ዕድሜው አጭር ነው፡፡ ሰውም እንደዚያው ስለሆነ ሰው ሞትን መቅደም አለበት እንጂ ንስሐ ሳይገባ በሞት መቀደም የለበትም፡፡ ሰው በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው ሞትን ማሰብ መቻል ይገባዋል፡፡ “አብድ ውእቱ ዘይሄሊ ካልአ ዘእንበለ መቃብሩ ወርስቱ” እርስቱ ከሆነው ከሞትና ከመቃብር ሌላ የሚያስብ ሰነፍ ነው” እንዲል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ

 

በሌላ መልኩ አበባን ስንመለከተው የሚወድቀው፣ የሚረግፈው ፍሬ ለማስገኘት ነው፡፡ አበባ ሲኖር በመአዛው ሰውን ያስደስታል፡፡ ሲረግፍም በፍሬው ይጠቅማል፡፡ ሰው ሲኖርም ሲሞትም ፈጣሪውን የሚያስደስት መሆን አለበት እንጂ ያለፍሬ ንስሐ መሞት የለበትም፡፡ “ግብሩኬ እንከ ፍሬ ሰናየ ዘይደልወክሙ ለንስሐ” ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ማቴ.3፥8

 

“እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ይቆረጣል፡፡ ወደ እሳትም ይጣላል ማቴ.3፥10 ተብሏልና፡፡ ሰውም መልካም ፍሬን አፍርቶ፣ ንስሐ ገብቶ፣ ተዘጋጅቶ፣ የሰማይ ቤቱን ሠርቶ፣ መንግሥተ ሰማያትን ሽቶ፣ ራሱን በንስሐ የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ፣ ሰውቶ፣ ከእግዚአብሔር ተጠግቶ፣ መኖር አለበት፡፡ በጭፈራ በስካር የተሰጠውን ጊዜ ማቃጠል ራስንና እግዚአብሔርን መበደል ከቃለ እግዚአብሔር መኮብለል በኀጢአት ገደል መውደቅ በዚህም እንደታላቅ ሰው መመጻደቅ አይገባም፡፡ ጊዜ መሣሪያ እንጂ መቀለጃ አይደለም፡፡ መጽደቂያ እንጂ መኮነኛ፣ መነሻ እንጂ መውደቂያ፣ መሣሪያ እንጂ መክሰሪያ፣ ሊሆን አልተሰጠም፡፡ ታዲያ በዚህ እንደ አበባ በተሰጠን ጊዜ መጠቀም ድርሻችን ነው፡፡ ስለ አበባ ይህን ያክል በጥቂቱ ካልን፡-

 

ከፍሬስ የምንማረው ምንድር ነው?

አበባው ሲያልፍ ፍሬው ይተካል፡፡ ስለፍሬው ለመነጋገር ከዛፎች መነሣቱ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ የአበቦችም የፍሬዎችም ተሸካሚ ወይም አስገኝ ዛፎች ስለሆኑ ያለ ዛፍ ፍሬን ማሰብ ከባል በፊት ልጅ እንደማለት ነውና፡፡ ዕፅዋት፣ አዝርዕት አትክልት ሲያፈሩ በአንድ መንገድ ብቻ አያፈሩም በራሳቸው የሚያፈሩ አሉ፡፡ በጎናቸው የሚያፈሩ አሉ፤ በሥራቸው የሚያፈሩ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ምሳሌነት ያላቸው አስተማሪዎች ናቸው በራሳቸው የሚያፈሩት በራሳቸው ጥረው ግረው የሚኖሩ ሰዎች  አምሳል ናቸው፡፡ በጎናቸው የሚያፈሩት ሚስት አግብተው፣ ልጅ ወልደው፣ በሐብታቸው ነግደው፣ በንብረታቸው ተጠቅመው የሚኖሩ ሰዎች አምሳል ናቸው፡፡

 

በሥራቸው የሚያፈሩት ሎሌዎቻቸውን ሠራተኞቻቸውን አዝዘው ልከው የሚኖሩ ሰዎች አምሳል ናቸው ይህ ሰሙ ነው ወርቁ ግን “አንዱ መቶ አንዱ ስልሣ አንዱ ሠላሳ ፍሬ ሰጠ” ማቴ.13፥8-10፡፡

 

በራሳቸው የሚያፈሩት የባለመቶ ክብር አምሳል ናቸው፡፡ በጎናቸው የሚያፈሩት የባለ ሥልሳ ክብር በሥራቸው የሚያፈሩት የባለ ሠላሳ ክብር አምሳል ናቸው፡፡

 

ከነዚህም አዝርዕት፣ ዕፅዋት፣ አትክልት ወገን በራሳቸው በጎናቸው በጫፋቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ወፍ ጠርጥሮት፣ ጠላት ለቅሞት የሚቀሩ አሉ፡፡ በሥራቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ከወፍ ከጠላት ሰውረው የሚያስቀሩ አሉ እነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

 

በራሳቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ወፍ ጠርጥሮት፣ ጠላት ለቅሞት የሚቀሩ በዚህ ዓለም ብዙ ትሩፋት፣ ብዙ ምግባር ሠርተው ይዩልን፣ ይሰሙልን፣ ይወቁልን ብለው በከንቱ ውዳሴ ተጎድተው በወዲያኛው ዓለም ሳይጠቀሙ የሚቀሩ ሰዎች አምሳል ናቸው፡፡

 

በሥራቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ከወፍ ከጠላት ሰውረው የሚያስቀሩ በዚህ ዓለም ሲኖሩ ብዙ ትሩፋት ምግባር ሰርተው አብልተው አላበላንም፣ አጠጥተው አላጠጣንም፣ አልብሰው አላለበስንም እያሉ ክብራቸውን ሸሽገው በወዲያኛው ዓለም የሚጠቀሙት አምሳል ናቸው፡፡

 

ዳግመኛም ከአንድ መሬት በቅለው የሚበሉ የማይበሉ፣ የሚጣፍጡ የማይጣፍጡ፣ ሬትና መርዝ፣ ወይንና ትርንጎ ይገኛሉ፡፡ ሬትና መርዝ የኀጥአን፣ ወይንና ትረንጎ የጻድቃን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ከአንድ መሬት በቅለው በመጣፈጥና በመምረር እንዲለዩ ጻድቃንና ኀጥአንም ከአንድ ከአዳም ከአራቱ ባሕርያት ተፈጥረው በምግባርና በሃይማኖት፣ በክህደትና በኀጢአት፣ በክፋትና በበጎነት ተለይተው ሲኖሩ ጻድቃን ወደ ጎተራው መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ፡፡ ኀጥአን ግን አይገቡም፡፡ ወደ ገሃነመ እሳት ይወርዳሉ እንጂ፡፡ “ፍሬያቸው ሐሞት ነው፡፡ ዘለዓለም መራራ ነው” እንዲል ዘዳ.32፥33፡፡

 

እነዚህ አዝርዕት፣ አትክልት፣ ዕፅዋት በየዘራቸው ይበቅላሉ እንጂ ያለ ዘራቸው አይበቅሉም፡፡ ፍሬም አይሰጡም፡፡ እንደዚሁም ጻድቃንና ኀጥአንም ያለ ዘራቸው ያለ ቤታቸው አይበቅሉም፡፡

 

“ወእምፍሬሆሙ ተአምርዎሙ እስመ ዕፅ ሠናይ ፍሬ ሰናየ ይፈሪ ወዕኩይሰ ዕፅ ፍሬ እኩየ ይፈሪ” ማቴ.7፥16-18


“ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያደርጋል”

 

ከአዝርዕት ከአትክልት ክረምት ለምልመው በጋ የሚደርቁ ክረምት ደርቀው በበጋ የሚለመልሙ አሉ፡፡ በክረምት ለምልመው በበጋ የሚደርቁት በዚህ ዓለም ሳሉ በልተው፣ ጠጥተው፣ ለብሰው፣ ሞግሰው በዚያኛው ዓለም የማይጠቀሙት ናቸው፡፡ እንደነዌ ያሉ ሉቃ.16፥25

 

ክረምት ደርቀው በጋ የሚለመለሙት በዚህ ዓለም ሲኖሩ ተርበው ታርዘው ጎስቁለው በወዲያኛው ዓለም የሚጠቀሙ ሰዎች አምሳል ናቸው፡፡ እንደ አልዓዛር እንደ ኢዮብ ያሉ ናቸው፡፡ ኢዮ.2፥1፣ ሉቃ.16፥19 ስለዚህ እኛም የሰው ልጆች መራራ ሳይሆን ጣፋጭ፣ ጠላት የሚለቅመው ሳይሆን፣ ከጠላት የሚሰውረውን ፍሬ፣ ክረምት ለምለሞ በጋ የሚደርውን ሳይሆን ክረምት ደርቀው በጋ የሚለመልሙትን መሆን አለብን፡፡

 

እግዚአብሔር በቸርነቱ በምሕረቱ ይርዳን፡፡

ይቆየን

ዘመነ ጽጌ

ውጤታማ ለመሆን በውይይት ማመን

መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

ወልደ ማርያም


የአምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሥርዓተ ቀብር ከተፈጸመ ሳምንታት ተቆጠሩ፡፡ ፓትርያርኩ ዐርፈው መንበረ ፕትርክናው ባዶ መኾኑ ከተረጋገጠበት ዕለት ጀምሮ መንበሩን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ይበቃል ያለውን አካል የመሾም፤ የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የማስቀጠል ሓላፊነት የተጣለበት ቅዱስ ሲኖዶስ አምስት ዋና ዋና ተግባራትን ፈጽሟል፡፡

 

የመጀመሪያው ፓትርያርኩ ማረፋቸው እንደተሰማና እንደተረጋገጠ በፓትርያርኩ በኩል ቤተ ክርስቲያኗ የሰበሰበቻቸውን ሀብታት በአግባቡ እንዲጠብቁ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ፓትርያርኩ ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ ከንጋቱ 11 ሰዓት አካባቢ ዐርፈው በዕለቱ ወደ 7፡30 አካባቢ ይኖሩበትና በቢሮነት ይገለገሉባቸው የነበሩትን ቤቶች አሽጓል፡፡ ሁለተኛው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መሠረት መንበረ ፕትርክናውን የሚጠብቅ፤ ቀጣዩ የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ እስኪመረጥ ድረስ ሲኖዶሱን በበላይነት የሚመራ፣ /ህየንተ ፓትርያርክ/ ኾኖ የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊ አስተዳደር የሚመራ ዐቃቤ መንበር መምረጥነው፡፡ በዚሁም ነሐሴ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ከያዙት የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጵጵስና በተጨማሪ ዐቃቤ መንበር ኾነው እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል፡፡

 

ሦስተኛው /በይፋ የተገለጠ ነገር ባይኖርም/ ከወቅቱ ቋሚ ሲኖዶስ ጋር ቀጣዩ ፓትርያርክ ከመመረጡ በፊት ሊሠሩ የሚገባቸውን ተግባራት የቤተ ክርስቲያኗን ሁሉን ዐቀፍ አስተዳደራዊ ፈርጆች አጥንቶ የሚታረመውን አርሞ የሌለውን አዘጋጅቶ ለምልዐተ ጉባኤ የሚያቀርብ ሰባት አባላት ያሉት የሊቃነ ጳጳሳት ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ መምረጡ ነው፡፡ ዐራተኛው የቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት ለክብራቸውም በሚገባ መልኩ እንዲፈጸም ማድረጉ ነው፡፡ አምስተኛው እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያኗ መልካም መሪ ይሰጥ ዘንድ የጸሎት ዐዋጅ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማወጅ ነው፡፡

 

ከላይ ያየናቸው የቅዱስ ሲኖዶሱ ተግባራት አፈጻጸማቸው በይፋ የታየ መግለጫም የተሰጠባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጭ በአሁኑ ወቅት ቅዱስ ሲኖዶሱ ምን እየሠራ እንዳለ እየተሰጠ ያለ መግለጫ የለም፡፡ ይህ ጽሑፍ ቀጣዩን የቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አመራረጥ አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሊሔድበት የሚገባውን መስመር በአጭሩና በመጠኑ ይጠቁማል፡፡

 

1. መቅደም ያለበትን ማስቀደም፡- ቤተ ክርስቲያናችን ባለፉት ሁለት ዐሠርት ዓመታት ጥሩ ተጓዘች፣ በአንጻሩም ቢኾን ኢኮኖሚዋ አደገ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት የሚገሠግሠው ምእመን ቁጥር ጨመረ ቢባልም ሒደቱን በከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተተ፣ ቤተ ክርስቲያኗን ለዘመናት አስከብረው ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ አድርገው ያቆዩዋት ዕሴቶቿን ክፉኛ ሲገዳደር የቆየ አንድ መሠረታዊ ችግር አለ፡፡ ይኸውም የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደር በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ እንዲከፋፈል ያደረገና በአባቶች መካከል የተከሠተ የመለያየት ችግር ነው፡፡ ይህ ልዩነት ለሃያ ዓመታት ምእመኑን ሲያደናግር የኖረ፣ በሁለቱ ጎራ ያሉ አባቶችም እርስ በርስ ተወጋግዘው ቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ አልባ እንድትመስል አድርጎ ያቆየ፣ ለብዙ ሥጋውያን ሰዎች ዓላማ ማስፈጸሚያነትም ሲያገለግል የኖረ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኗ አሁን በዚያ መጠላለፍና አልሸነፍ ባይነት – ስትናጥበት ከቆየችበት ችግር የምትላቀቅበት መልካም አጋጣሚ ላይ ትገኛለች፡፡ በመኾኑም ቤተ ክርስቲያኒቱን ይመራ ዘንድ የተሰየመው ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ለሃያ ዓመት የዘለቀ ልዩነት አጥብቦ ቤተ ክርስቲያኗን ወደ ቀደመ የአንድነት ጉዞዋ መመለስ አለበት፡፡ ይህን ሲያደርግም የሚከተሉትን ጉዳዮች በጥንቃቄ ሊያጤን ይገባል፡፡

 

ሀ. የችግሩን መንሥኤ ከመሠረቱ ማጥናት፡- ከላይ የገለጽነው የመከፋፈል ችግር የብዙ ትንንሽ ችግሮች ውጤት ነው፡፡ ዝርዝራቸውን ትተን መገለጫቸውን ብናይ ፖለቲካዊ ዓላማ፣ ሀብት የማካበት ዓላማ፣ የግል ክብርና ምቾት ፍለጋ ዓላማና ቤተ ክርስቲያኗን በኑፋቄ የማወክል ዓላማ ናቸው፡፡ እነዚህን ዓላማዎች በየግላቸው ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት መጠናቸው ቢለያይም በሁለቱም ጎራዎች አሉ፡፡ እነዚህ አካላት ልዩነቱን በመጠቀም ዓላማዎቻቸውን ሲያሳኩና ለማሳካት ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ በመኾኑም በሁለቱም በኩል ያሉ አባቶች ቤተ ክርስቲያኗ የምትናፍቀውን ሰላም አስፍነው በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖር ደገኛ ተግባር ለመፈጸም፤ የችግሩን ምንጮች አጥንተው በመለየት እነዚህን አካላት በምክርም በተግሣጽም ማረም ወይም መለየት ይገባቸዋል፡፡

 

ለ. የዕርቁን አስፈጻሚዎች በጥንቃቄ መምረጥ፡- በአባቶች መለያየት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኗ ከተከፈለችበት ጊዜ አንሥቶ በኦፊሴል ያልተገለጹትን ጨምሮ ሁለቱንም አካላት በመወከል በሚቀመጡ አባቶች አማካኝነት በርካታ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን ድካሞቹ ሁሉ ውጤት አላመጡም፡፡ ለዚህ ከሚሰጡት ምክንያቶች አንዱ የሚወከሉት አባቶች ችግሩ እንዲፈታ በማድረግ በኩል የማስፈጸም ብቃት ማነስ ወይም ለማስፈጸም ጠንክሮ አለመሥራት ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን መካከል የሚከሠትን ችግር ለመፍታት ምድራዊ ጥበብና ቀመር ቦታ የላቸውም፡፡ «እንዲህ ቢባል እንዲህ በሉ» የሚለው ቅደመ ውትወታም አያስፈልግም፡፡ «እንዲህ ብል እከሌ ምን ይላል?» ወይም «የምናገረውን እከሌን ልጠይቅ» የሚሉት ደካማ አስተሳሰቦችም ሊኖሩ አይገባም፡፡በመኾኑም በቀጣይ ይህንን ሁሉም የሚናፍቀውን አንድነት እውን ለማድረግ ከሁለቱም ወገን የሚመረጡት አባቶች እውነትንና አንድነትን በማስቀደም ራሳቸውን ኾነው የሚወያዩ መኾን ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም በሁለቱም በኩል ያሉት አባቶች ይወክሏቸው ዘንድ በሚመርጧቸው ሰዎች  ብቃት ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

 

ሐ.  የዕርቅ ውይይቱ በሁሉም አካላት በኩል እንዲጀመር ማድረግ፡- ይህ ችግር እንዲፈታ በማድረግ ሥልጣንና ሓላፊነት ያላቸው በሁለቱም በኩል ያሉ አባቶች እንደ ኾኑ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ሃያ ዓመታት መሠረታዊው የአባቶች ልዩነት ያቆሰላቸው በርካታ አካላት በሁለቱም በኩል በየደረጃው አሉ፡፡ እነሱም በሁለቱም በኩል ያሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ናቸው፡፡ ምንም እንኳን አባቶች በዕርቅ ከተዋሐዱ እነዚህ አካላት አሻፈረኝ ብለው እንደተለያዩ ይቀራሉ ባይባልም የእነሱም መወያየት ዕርቁን የተሟላ ያደርገዋል፡፡ የአባቶችን መዋሐድ የማይፈልጉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችንም ለመለየት ያግዛል፡፡

 

2.    በቀጣዩ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ላይ በጥብዓትና በግልጽ መወያየት መጀመር፡- ባለፉት ሃያ ዓመታት የቤተ ክርስቲያን ችግር ገዝፎ ይታይ የነበረው በኢትዮጵያና በአሜሪካ አብያተ ክህነት መካከል ብቻ አልነበረም፡፡ እዚህ አዲስ አበባም በተለያዩ ጊዜያት በቤተ ክህነቱ አስተዳደርና በቅዱስ ሲኖዶሱ አመራር ላይም ችግሮች ታይተዋል፡፡ ችግሮቹ ገዝፈው የቤተ ክርስቲያኗን ምልዐት እስከ ማወክና ምእመኑን ወደ ቀቢጸ ተስፋ እስከ መክተትም ደርሰው ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ቅድስና የማይስማሟት ዘረኝነት፣ ሙስናና አድሎአዊነት በይፋ ታይተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና አገልግሎት የሚጠበቀውን ያህል ዘመናዊ አልሆነም፡፡ አህጉረ ስብከት በልማት አገልግሎት መጓዝ ያለባቸውን ያህል አልተጓዙም፡፡ ለዚህ ሁሉ በብዙዎች እንደ ምክንያት ይጠቀስ የነበረው የቅዱስ ፓትርያርኩ የአስተዳደርና የአመራር ችግር ነው፡፡ አከራካሪ ነው፡፡ የኾነው ኾኖ አሁን ይህ ምክንያት በዜማነት የሚነሣበት ጊዜ አልፏል፡፡ ለሃያ ዓመታት በምክንያትነት ሲነሡ የነበሩት ቅዱስ ፓትርያርክ የሉም፡፡ እንደ ሥራቸው ወደሚከፍላቸው አምላክ ሔደዋል፡፡ ስለዚህ የሲኖዶሱ አባላት ሌላ ምክንያት ፈጥሮ የሚቀጥሉትን ሃያ ዓመታትም ተመሳሳይ ዜማ ሲያዜሙ ላለመኖር በመንበረ ፕትርክናው ስለሚያስቀምጡት አባትና ስለሚቀመጥበት አግባብ እንዲሁም ስለ ቤተ ክርስቲያኗ ቀጣይ አስተዳደራዊ መልክእ መወያየትና ቀጥተኛ መስመር ማስቀመጥ አለባቸው፡፡

 

3.    ችግሮችን አጥንተው ለውሳኔ የሚያቀርቡ ልዩ ልዩ ጉባኤያትን ማቋቋም፡- ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኗን መንፈሳዊ አስተዳደር በበላይነት የሚመራ፣ በባለሞያዎች ተጠንቶ በሚቀርብለት መሠረታዊ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ነው፡፡ ይህ እንዲኾን ደግሞ አስፈላጊውን አቅጣጫ ለአስፈጻሚው አካል መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ ከተጠቀሱት ተግባራት በተጨማሪ ማድረግ ያለበት የቤቱን መሠረታዊ ችግሮች ሙያዊ በኾነ መንገድ አጥንተው ከነመፍትሔ ሐሳባቸው  የሚያቀርቡ የባለሞያዎች ቡድኖችን ማቋቋም ነው፡፡ ቡድኖቹም በተወሰነላቸው ጊዜ የቤተ ክርስቲያኗን መሠረታዊ ችግሮች ከመፍትሔ ሐሳቦች ጋር እንዲያቀርቡለት መመሪያና ትእዛዝ መስጠት፣ ለሥራቸው ቅልጥፍናም አስፈላጊው ሎጂስቲክስ እንዲሟላላቸው ማድረግ  ይጠበቅበታል፡፡ የቀደመ አገልግሎቷን ለማስቀጠል 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የደረሰች ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት ሙያዊና አስተዳደርንና አሠራርን መከተል ይጠበቅባታል፡፡ ለዚያ ደግሞ አሁን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን መወጣት ኖርበታል፡፡ አሁን በሚታየው ሁኔታ ሦስት የባለሙያዎች ቡድኖች እንዲቋቋሙ ግድ ይላል፡፡ እነዚህም የገንዘብና የንብረት አስተዳደር ጥናት ቡድን፣ የሰው ኃይል ጥናት ቡድንና የቤተ ክርስቲያን መዋቅርና አሠራር ጥናት ቡድን ናቸው፡፡ እነዚህ ቡድኖች በየተሰጧቸው አርእስት ያሉትን ጉዳዮች ፈትሸው ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት የመፍትሔ ሐሳቦችንና የአሠራር መንገዶችን አጥንተው ያቀርባሉ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም በሚቀርቡለት ሰነዶች ዙሪያ ተወያይቶ ይወስናል፡፡

4.    ጣልቃ ገብነትን በጥንቃቄ መከታተል፡- የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች የሚመነጩት ከውስጥም ከውጭም ነው፡፡ በተደጋጋሚ ሲነሡ የቆዩትና በመነሣት ላይ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ሙሉ በሙሉ በውስጧ ባሉ አካላት /ምእመናን፣ ካህናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የቤተ ክህነቱ ሠራተኞች፣/ ድካም ብቻ የመጡ አይደሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ዐውቃም ይሁን ሳታውቅ በገቡባት ባዕዳን እጆች የተነሣ  ችግር ላይ ስትወድቅ ቆይታለች፡፡ እነዚህ የባዕዳን እጆች አሁንም በቤተ ክህነታችን አሠራር ድርሻ እንዲኖራቸው መፈቀድ የለበትም፡፡ ስለዚህ አሁን ሁሉም ዐይኑን አፍጥጦ እንዲኾን የሚጠብቀው ሒደት ከየትኛውም ውጫዊ አካል ተፅዕኖ በጸዳ መልኩ እንዲኾን ሓላፊነት ያለበት ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ ምልዐት መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያኗ በመስቀለኛ መንገድ ላይ በቆመችበት ሰዓት ወደደጉ የመምራት ሓላፊነት ያለባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከፍተኛ ድርሻ አለባቸው፡፡ እነሱ ከየትኛውም ጫና ነጻ በኾነ መልኩ እንዲመሩ ደግሞ የሚመለከተን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁላችን በምንችለው ሁሉ ልናግዛቸው ያስፈልጋል፡፡

 

5. በቤተ ክርስቲያኗ ቀጣይ ጉዞ ላይ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ ምልዐት በየደረጃው እንዲወያዩ ቢደረግ፡- ወቅቱ ሁሉም የቤተ ክርሰቲያኗ አካላት ስለ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ቀጣይ ጉዞ ስለ መሪዎቿና አመራር ሥልታቸው፣ ስለ አገልግሎቷና አገልጋዮቿ ብቃት በስፋት መወያየት ያለባቸው ጊዜ ነው፡፡ በዘርፉ ምሁራን በቃልም በመጻፍም እንደሚገለጠው ዘመናዊ አመራር የጋርዮሽ ተግባር ነው፡፡ ይህ አባባል ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ተግባራዊነቱ ወሳኝ በኾኑ ጉዳዮች ዙሪያ ሁሉም አካላት እየተወያዩ ለቤተ ክርስቲያኗ ይበጃሉ የሚባሉ ሐሳቦችን ወደ ዋናው ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲልኩ ሲኾን ነው፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶሱ ለውይይቱና ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች መቃናትና ቀጥተኛነት እሱ የሚመራቸው አካላት /የቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ ሰበካ ጉባኤያት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምሁራን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ወዘተ/ በየመልኩ እንዲወያዩ አቅጣጫ መስጠት አለበት፡፡ እነዚህ አካላትም የቅዱስ ሲኖዶስን አባላት ግብዣ በመቀበል ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡

 

ስናጠቃልል፡- በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያናችን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ የምዕራፉ ወሳኝነትም ቤተ ክርስቲያኗ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተረድታ ወደ ፊት የምትራመድበትን አቅጣጫ ለማስቀመጥ በጥንቃቄ መራመድ ያለባት ጊዜ ላይ በመኾኗ ነው፡፡ ጥንቃቄው ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗን ለመምራት እግዚአብሔር መርጦ ያስቀመጣቸው አባቶች ድርሻ ብቻ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የወለደቻቸው ልጆቿ ሁሉ ለእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ቀጣይ መልካም ጉዞ በሚችሉት ሁሉ መወያየት ይበጃል ያሉትን ሐሳብ ሁሉ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም ይሰምር ዘንድ ደግሞ የእኔ ሐሳብ ብቻ ተቀባይ ይሁን ከሚል መገዳደር ርቆ ሁሉንም በፍቅር ማድረግና የፍቅር አምላክ የመሠረተልንን ቤተ ክርስቲያን በፍቅር ልንኖርባት ያስፈልጋል፡፡ ለሁሉም ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረተ መሥርቶም ያጸና አምላክ ደጉን ሁሉ ያድርግልን፡፡

 

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን

የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የፖትርያርክ ምርጫ የሚመለከት ረቂቅ ሕግ

መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

ወልደ ማርያም

ምዕራፍ 1

የዐቃቤ መንበሩን ምርጫ በተመለከተ

 

አንቀጽ 1

  • መንበረ ፓትርያርኩ በሞት ወይም በሌላ ምክንያት በመንበሩ ላይ ባይኖር ቅዱስ ሲኖዶስና ሚሊ ካውንስሉ /የምዕመናን ጉባኤ/ በዕድሜ አንጋፋ በሆነው ጳጳስ በሚጠራው ጉባኤ ሰብሳቢነት ቅዱስ ሲኖዶሱ ተሰይሞ ከ7 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ዐቃቤ መንበር ይሰይማል፡፡ የተመረጠውም አባት ዐቃቤ መንበር በመሆን ያገለግላል፡፡ ብሔራዊ ዐዋጅ /republican decree/ ታውጆ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ፣ ትውፊትና ሥርዓት መሠረት ሕጋዊ የሆነው ፓትርያርክ ሹመት ይፈጸማል፡፡

 

ምዕራፍ 2

ለመንበሩ የሚመጥን ሰው ምርጫ

 

አንቀጽ 2

ለፓትርያርክነት ሹመት የሚወዳደር ሰው የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡

  1. በትውልድ ግብጻዊ በሃይማኖቱም የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት አባል የሆነ፡፡

  2. የቤተ ክርስቲያንን ሕግ፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚያዘውን የሚያሟላ፣ መነኩሴ የሆነ በጋብቻ ሕይወት ያልተወሰነ /ሜትሮፓሊታንም ሆነ ጳጳስ/ ይህ ቅድመ ሁኔታ ይጠበቅበታል፡፡

  3. ዕድሜው ከአርባ ዓመት ያላነሠ በገዳም ከ15 ዓመት ላላነሠ ጊዜ የኖረ፡፡

አንቀጽ 3

  • ዐቃቤ መንበሩ የሚመራው 18 አባላት ያሉት ቅዱስ ሲኖዶስ የመረጠው የሜትሮፓሊታን የጳጳስነትና ከሚሊ ካውንስሉ /ከምእመናን ጉባኤ/ የተውጣጣ 18 አባላት ያሉት ጉባኤ ለመንበረ ጵጵስናው የሚወደደሩ እጩዎችን ዝርዝር ይይዛል፡፡

  • ኮሚቴው በመንበሩ ላይ ተቀምጦ የነበረው ፓትርያርክ ሥፍራው በሞት ወይም በሌላ ሁኔታ በለቀቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መሰየም ይኖርበታል፡፡ የዚህን ኮሚቴ ስብሰባ የሚጠራው ሊቀ መንበሩ ነው፡፡ ሊቀ መንበሩ ከሌለ ወይም ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ከተፈጠረበት አስቀድሞ የተመረጠው ሜትሮ ፓሊተን የሊቀ መንበሩን ሥፍራ ተክቶ ይሠራል፡፡ ጉባውንም ይጠራል፡፡

  • ጉባኤው የሚካሄደው የሁለቱም ጥምር ጉባኤ አባላት 2/3ኛው ያህል ሲገኙ ነው፤ ምልዓተ ጉባኤው ካልተሟላ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ ይቀጠራል፡፡ ሁለተኛው ምልአተ ጉባኤ ስብሰባውን የሚካፈሉት አባላት ቢሟሉም ባይሟሉም የተገኙት አባላት በአብላጫ ድምጽ የሚወስኑት ውሳኔ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡

 

አንቀጽ 4

  • ለፓትርያርክነት የሚወዳደረው እጩ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በስድስት ሜትሮ ፓሊታን ጳጳሳትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ወይም በሚሊ ካውንስሉ /የምእመናን ጉባኤ/ አስቀድመው ተመርጠው ያገለገሉ ወይም አሁን እያገለገሉ ያሉ አባላትን ይሁንታ የያዘ የጽሑፍ ድጋፍ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

  • ይሁንታ ያገኙበትን ድጋፍ ሲያቀርቡ የድጋፍ ደብዳቤ የተሰጠበት ቀንና ሰዓት ተመዝግቦ ደረሰኝ ይሰጣቸዋል፡፡

 

አንቀጽ 5

  • የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአንቀጽ 4 ላይ በተቀመጠው መሠረት በ15 ቀን ውስጥ ተሰብስቦ የድጋፍ ደብዳቤዎችን ይመረምራል፤ ሕጉን የተላለፈውን ያስወግዳል፡፡ በሕጉ መሠረት የመጡለትን ድጋፎች ይቀበላል፡፡

  • ኮሚቴው በተቀመጠው የማስረከቢያ ቀን የእጩዎችን ዝርዝር ካይሮ ለሚገኘው የፓትርያርክ ጽ/ቤትና በሌሎችም ሥፍራዎች ላሉ ጽ/ቤቶች ያስረክባል፡፡ የደረሰበትንም ውሳኔ በአረብኛ ቋንቋ ካይሮ ውስጥ በጋዜጣ እንዲታተም ያደርጋል፡፡

 

አንቀጽ 6

  • ለፓትርያርክነት መንበር የሚወዳደር ማንኛውንም እጩ የነጋሪት ጋዜጣ በወጣ በ15 ቀን ውስጥ ለመንበረ ጵጵስናው የማይመጥን ተወዳዳሪ አለ ብሎ ካመነ ለኮሚቴው ሊቀ መንበር /ሰብሳቢ/ ማስታወሻ ሊጽፍ ይችላል፡፡ አሳማኝ የሆነ ነጥብም ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ለአመልካቹ ደረሰኝ ይሰጠዋል፡፡

  • የቀረበውን ቅሬታ ኮሚቴው ተቀብሎ ከመረመረ በኋላ ኮሚቴው ውሳኔውን ያሳውቃል ኮሚቴው በአንቀጽ 2 ላይ የተቀመጡትን ነጥቦች ያላሟላ እጩ ካገኘ የማንንም ውሳኔ ሳይጠብቅ እጩውን የመሰረዝ ሥልጣን አለው፡፡ ለፓትርያርክነት እጩ ለመሆን ሁኔታዎችን ያሟሉ የመጨረሻዎቹን እጩዎች ያሳውቃል፡፡ የመጨረሻዎች ተወዳዳሪዎች የድጋፍ ደብዳቤ ያላቸው ሁነው ቁጥራቸው ቢያንስ አምስት ቢበዛ ሰባት መሆን ይኖርበታል፡፡ ስማቸውም በፊደል ተራ ቁጥር ይቀመጣል፡፡

 

አንቀጽ 7

  • ኮሚቴው የመጨረሻውን የፓትርያርክ ምርጫ ቀን ያሳውቃል፡፡ የመጨረሻውን ዝርዝር በፓትርያርኩ መኖሪያ በር ካይሮና በሌሎች አካባቢዎች ባሉ ጽ/ቤቶች ይለጥፋል፡፡ በዝርዝሩ ግርጌ ኮሚቴው ዕጩው የተመረጠበትን ቀን በማሳወቅ መራጮች ድምጽ እንዲሰጡ ይጋብዛል በተቀመጠው ቀንና ሥፍራ በየቀኑ ታትመው በሚወጡ ሦስት ጋዜጦች ካይሮ ውስጥ የምርጫውን ቀንና ሥፍራ ያሳውቃል፡፡ የምርጫ ቀኑ የእጩዎች ዝርዝር ከተገለጠበት ጀምሮ ከ30 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይከናወናል፡፡

 

ምዕራፍ ሦስት

የፓትርያርኩ ምርጫ ድምጽ ሰጪዎች

 

አንቀጽ 8

  • በፓትርያርኩ ጽ/ቤት መራጮች ድምጽ የሚሰጡበት ሳጥን ይዘጋጃል፤ መራጮች በትውልድ ግብጻውያንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ባላቸው ግንኙነት በሃይማኖታቸውና በመልካም ግብራቸው የተመሰከረላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

 

ድምጽ ከሚሰጥበበት ጠረጴዛ የሚቀመጡ አስመራጮች

  1. የፓትርያርኩ መንበር ባዶ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በጎርጎራውያን ቀመር መሠረት ዕድሜው 35 ዓመት የሞላው፡፡
  2. የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ምሩቅ ወይም በግብጽ መንግሥታዊ ተቋም ተቀጥሮ ያገለገለ ወርሃዊ ገቢው 480 የግብጽ ፓውንድ ያላነሰ ወይም በባንክ፣ በካምፓኒ ተቀጥሮ የሚሠራ፣ ወይም በተመሳሳይ የሥራ ገበታ የተሰማራ፣ ገቢው ከ600 የግብጽ ፓውንድ ያላነሰ፣ ወይም ታክስ የሚከፍል ግብጻዊ ሆኖ ገቢው ከ100 የግብጽ ፓውንድ ያላነሰ መሆን ይኖርበታል፡፡
  3. በአንቀጽ 2 በተቀመጠው መሠረት በአስመራጭ ኮሚቴው ተቀባይነትን ያገኘ፡፡

አንቀጽ 9

  • ሦስት ካህናት፣ ሁለት የጠቅላላ ሚሊ ካውንስሉ/ የምእመናን ጉባኤ/ አባላት ወይም አሁን ወይም አስቀድሞ አባል የነበሩ ተመራጮች ያሉበት ኮሚቴ ድምጽ ሰጪዎች የሰጡትን ድምጽ ለመቁጠር ይሰየማል፡፡ ዐቃቤ መንበሩ የኮሚቴውን አባላት ይመርጣል ከካህናት መካከል በዕድሜ፣ ወይም በሌላ ቅድመ ሁኔታ ከፍ ካለው ጀምሮ ወደታች ያሉትን ሁሉ ሊመለከት ይችላል፡፡

 

ይህ ኮሚቴ በጽሑፍ በቀረበው ዳታ መሠረት የድምጽ ሰጪዎችን ድምጽ ከሚከተሉት ክፍሎች ይወስዳል፡፡

  1. ሜትሮ ፓሊታን፣ ጳጳሳት፣ የገዳማት አስተዳዳሪዎች ተመራጮችና ፍላጎት ያላቸው መራጮች፡፡

  2. ካይሮ ከሚገኙ መንፈሳውያት ማኅበራት ጉባኤ አባላትን፣ የአህጉረ ስብከት ተመራጮችን፣ በከተማዎች ያሉ የክርስቲያናዊ ሕግ አስፈጻሚዎች፣ በከተማ ያሉ ታዋቂ መራጮችን፡፡

  3. ከመላው ካይሮ 24 ቀሳውስት 7ቱ ከአሌክሳንድርያ የሆኑ፡፡

  4. የቀድሞ ጊዜና የአሁን የመጅሊስ አልሚሊስ የኮፕቲክ ፓርላማ አባላት፡፡

  5. የጠቅላላ ሚሊ ጉባኤ የቀድሞና የአሁን አባላት፡፡

  6. የጠቅላላ ሚሊ ጉባኤ የቀድሞና የአሁን አባላት፡፡

  7. በአስመራጭ ኮሚቴው የተመረጡ  ከካይሮ 72 አስመራጮች ከእነርሱም መካከል 24ቱ ከአሌክሳንድርያ የሆኑ፡፡

  8. ከእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት የተመረጡ 12 ድምጽ ሰጪዎች ሜትሮፓሊቲኑ ወይም ጳጳሱ በሚመራው ኮሚቴ የተመረጡ፡፡

  9. ወይም የአህጉረ ስብከት ጳጳሳት 5 መራጮች የተካተቱበት አካል፡፡

  10. ዕለታዊ ጋዜጣ አዟሪዎችና ዋና አዘጋጆችም እነርሱም የጋዘጠኞች ማኅበር አባላት የሆኑ፡፡

 

የመጀመሪያወቹ አምስቱ ድምጽ ሰጪዎች /መራጮች/ ዝርዝር ዐቃቤ መንበሩ በሚልከው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

በ6ኛው ተራ ቁጥር የተቀመጡ ድምጽ ሰጪዎች ዝርዝር በአስመራጭ ኮሚቴው ይላካል፡፡

በ7ኛ ተራ ቁጥር የተላኩ ድምጽ ሰጪዎች በሜትሮ ፓሊታን አማካኝነት ይላካሉ፡፡

በ8ኛው ምድብ ላይ ያሉ ድምጽ ሰጪዎች በጋዜጠኞች ጉባኤ አማካኝነት ይላካል፡፡

የፓትርያክነት ምርጫ ቅስቀሳው ከተጀመረ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ የመራጮች ዝርዝር ያለምንም ክፍያ ይከናወናል፡፡

 

አንቀጽ 10

  • የመጨረሻውን የመራጮችን ዝርዝር እንደተጠቃለለ በአረብኛ ቋንቋ በሚታተሙ ሦስት ጋዜጦች ካይሮ ውስጥ ይገለጣል፡፡

  • ስማቸው በስህተት በመጨረሻው ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተ መራጮች ዝርዝሩ እንዲስተካከል ማመልከት ይችላሉ፡፡ ጉዳዩም ዐቃቤ መንበሩ በሚመራው ኮሚቴ ይታያል፡፡ ከምርጫ አስፈጻሚ መካከል የተመረጡ ሁለት አባላት አብረው ይሆናሉ፡፡ ከሁለቱ አንዱ ካህን ይሆናል፡፡ ይህ ኮሚቴ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻው ይሆናል፡፡ ነገር ግን በስድስተኛውና በሰባተኛው ተራ ቁጥር በአንቀጽ 9 የገለጥነውን መራጭ ኮሚቴው አለመቀበሉ አስፈላጊ መስሎ ከታየው የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው ተቀባይነት ያላገኙ መራጮችን ተክተው የሚመዘገቡ ሌሎች መራጮችን መውሰድ መብት አለው፡፡

አንቀጽ 11

  • ስማቸው በምርጫው ጠረንጴዛ ላይ የተካተተ መራጮች ስማቸው ሓላፊነታቸው ሥራቸው ዕድሜአቸው ወደ ምርጫ የገቡበት ጊዜ የምርጫ ቁጥራቸውን የሚያሳይ መታወቂያ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህንን መታወቂያ የመስጠቱ ሓላፊነት የምዝገባ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይም የአጥቢያ ሜትሮፓሊን ወይም ጳጳስ ይሆናል ይህም መራጩ በሚኖርበት አካባቢ ነው፡፡

  • መራጮች መታወቂያቸውን ለመውሰዳቸው መፈረም ይኖርባቸዋል፡፡ መታወቂያውን የሰጠው ወገን ፊርማውን ያስቀምጣል፡፡ ከምርጫው አስቀድሞ ባሉት 15 ቀናት የሚከናወን ይሆናል፡፡

 

2. የምርጫ ሂደት

አንቀጽ 12

  • አስመራጭ ኮሚቴው ዐቃቤ መንበሩን ሰብሳቢ ሦስት ካህናት በቅዱስ ሲኖዶስ የተመረጡ ሦስት አካላት በሰያሚ ኮሚቴው /nomination committee/ የተመረጡ ከምርጫው ከሦስት ቀን አስቀድሞ ይሠየማሉ፡፡ የቃለ ጉባኤውን ሥራ ሰብሳቢው ደስ ያለውን ሰው በመሰየም ያስይዛል፡፡

  • በኮሚቴው ሰብሳቢ ጥያቄ የምርጫ ሂደቱን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲከታተለው ይደረጋል፡፡ ሰብሳቢው ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ለመገኘት ባይቻለው ከሜትሮ ፓሊታን መካከል  የሰብሳቢውን ሥራ ተክቶ ይሠራል፡፡ ከኮሚቴው አባላት የጎደለ ቢኖር ከአጠቃላይ ምርጫ ጉባኤው መካከል የሚተካ ሰውን ሰብሳቢው ይመርጣል፡፡

 

አንቀጽ 13

  • ምርጫው በሚካሄድበት ቀን አስቀድመን የገለጥነው ኮሚቴ በፓትርያርኩ ቤት መገኘት ይኖርበታል፡፡ ምርጫው ከ 3፡00 ሰዓት እስከ ቀኑ 11፡00 ሰዓት ድረስ ይከናወናል በቀኑ በ11ኛው ሰዓት ድምጽ መስጠት ያልቻለ መራጭ ቢኖር ኮሚቴው ዝርዝራቸውን ተናግሮ ሁሉንም ድምጽ ይሁንታ እስከሚያገኝ ሥራውን ይቀጥላል፡፡

 

አንቀጽ 14

  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሚመጡ ድምጽ ሰጪዎች በስተቀር /እነርሱ በራሳቸው ወይም ሕጋዊ በሆኑ ወኪሎቻቸው አማካኝነት የሚፈጽሙት ሆኖ ስም ዝርዝርራቸው በምርጫ ጠረጴዛው ላይ ከሰፈረ ውጪ በሕጉ ላይ እንደተቀመጠው

  1. ሜትሮፓሊቲንና ጳጳሳት፡፡
  2. የንጉሡ ተወካይ፡፡
  3. በመላው ግብጽ የታወቁ 24 ሰዎች ይህም በንጉሡ በፕሬዝዳንቱ የሚሰየሙ ይካተታሉ፡፡

 

አንቀጽ 15

  • በምርጫ ጠረጴዛው ላይ አስቀድሞ የስም ዝርዝርራቸው ባለ መራጮች ቁጥር ልክ ካርዶች ይዘጋጃሉ፤ ካርዶቹ በሊቀ መንበሩ /በምርጫ ኮሚቴ ስብሰባው ማኅተም መታተም  ይኖርባቸዋል፤ ለእያንዳንዱ መራጭም ይሰጣል፤ ወደ ምርጫው አደባባይ ሲመጡ ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ካርዱ የመራጩ ስም የምርጫ ቁጥር ይኖረዋል፡፡ ድምጽ ሰጪው ካርዱን ለመውሰዱ ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀው መዝገብ ላይ በፊርማው ያረጋግጣል፡፡

  • ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት ውስጥ ካርድ ያልወሰዱ ካሉ፣ ካርዱ የሌሉ ሰዎች ካርድ በሚቀመጥበት ኤንቨሎፕ ውስጥ ይቀመጣል፡፡ ለምርጫ ኮሚቴው ሊቀመንበርም ይሰጣል፡፡ ኤንቨሎፑን ካሸገ በኋላ ቀዶ ማኅተም ያደርግበታል፡፡

  • በአስመራጭ ኮሚቴው የተመረጡ 6 ድምጽ ሰጪዎች ያሉበት ኮሚቴ ከምርጫው 3 ቀን አስቀድሞ ካርዶቹን ያስረክባል ምርጫውንም ይቆጣጠራል፡፡

 

አንቀጽ 16

  • ድምጽ ሰጪዎች በአስመራጭ ኮሚቴ ፊት ሲቀርቡ ለጸሐፊው የምርጫ ካርዶቸውን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ጸሐፊው ካርዱን አትሞ ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀው ሳጥን ውስጥ ይከታል፡፡ መራጮች የምርጫ ወረቀት ይጧቸዋል የመረጡትን ሰው ስም ይይዛል፡፡

  • የዕጣ መጣሉ ሁኔታ በተወሰነ አግባብ ውስጥ የሚካሄድ ነው፡፡ ድምጽ የሚሰጠው ሰው ለድምጽ መስጫ በተከለለ ምስጢራዊ ቦታ ሊመርጥ ያሰበውን ዕጩ ያስቀምጣል፡፡ ድምጽ ሰጪዎች በምርጫ ወረቀቱ ላይ ምልክት ባያስቀምጡ ማንነታቸውን የሚገልጽ ነገር ባይኖረው ወረቀቱ ዋጋ አይኖረውም፡፡

 

አንቀጽ 17

  • የምርጫ ሂደቱ ከተጠቃለለ በኋላ ኮሚቴው የመራጭ ሰዎችን ካርድ ይቆጥራል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ቁጥር ከመራጮች ካርድ እና ከቀሪዎች ካርድ ጋር ተደምሮ የተመዝጋቢዎችን አጠቃላይ ቁጥር መስጠቱ ይመሳከራል ይህም የኢትዩጵያ ተወካዮች ቁጥር ጨምሮ ነው፡፡

  • ጸሐፊው ይህንን ሁኔታ በቃለ ጉባኤው ላይ ካሰፈረ በኋላ ኮሚቴው ድምጹን ይለያል ከምርጫው ጋር በተያያዘ ጉዳዮች ላይ ውሳኔውን ያሳልፋል፡፡ እያንዳንዱ መራጭ በሰጠው ድምጽ ላይ ያሰፈረውን አስተያየት ተአማኒነት ይመረመራል፡፡

  • ኮሚቴው የሚሰጠው ይሁንታ አስተያየት ምስጢራዊ ነው፡፡ ውሳኔውንም የሚተላለፈው በሚቆጠረው ድምጽ ይሆናል፡፡ የተሰጠው ድምጽ እኩል ሲሆን ዐቃቤ መንበሩ የሚሰጠው ውሳኔ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

  • የድምጽ ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላ ሊቀ መንበሩ የመጨረሻዎቹን ሦስት እጩዎች ስም ዝርዝር ያሳውቃል፡፡ እነርሱም የብልጫውን ድምጽ ያገኙ ናቸው፡፡ የኮሚቴው ጸሐፊ ሁለት ኮፒ ቃለ ጉባኤውን ያረቅቃል ዐቃቤ መንበሩ ይፈርምበታል፡፡ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካዮችም ይፈርማሉ፡፡

  • ምርጫው በተካሄደበት እሑድ ምዝገባው ይካሄዳል፡፡ ይሄውም ከላይ ለተገለጸው ሚኒስትር መ/ቤት 1 ኮፒ ቃለ ጉባኤ ይላካል/ቀሪው ካይሮ በሚገኘው የመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት ይቀመጣል፡፡ የምርጫ ሂደት ወረቀቶች በኤንቨሎፕ ቀይ ማኅተም ታትሞባቸው በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ይቀመጣሉ፡፡

 

አንቀጽ 18

  • በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ዐቃቤ መንበር ዕጣው የሚጣልበትን ሁኔታ ያመቻቻል፡፡ በዕጣ መጣሉ ሂደት ያሸነፈውን ዕጩ ስም ዐቃቤ መንበሩ ፈርሞበት ሁለት ኮፒ ቃለ ጉባኤ ይጻፋል፡፡ በምርጫ ኮሚቴው ስምና ፊርማ ይጸድቃል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም ፊርማቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ የዕጩ ጥቆማ አስተባባሪ ኮሚቴም እንዲሁ ፊርማቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ አንዲ ኮፒ ለሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ይላካል፡፡

  • በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መሠረት የተሾመው ፓትርያርክ በመላ ሀገሪቱ ይገለጣል፡፡

 

ምዕራፍ 4

ጠቅላላ ደንብና ከጊዜ ጋር የተያያዙ ደንቦች

 

አንቀጽ 19

አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የዕጩ አፈላላጊ ኮሚቴው /nomination committee/ በዚህ ሕግ ውስጥ የተቀመጠውን ጊዜ የማሳጠር ሥልጣኑ አለው፡፡ ይህም በጋራ በሚደረግ ውሳኔ ነው፡፡

ሃይማኖታውያን መስለው ከሚመጡ መናፍቃን ተጠንቀቁ ማቴ 7፥15

መስከረም 8 ቀን 2005 ዓ.ም.


አባ ዘሚካኤል

  • የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያቆየችውን ትውፊት፣ ቅርስና ሀብት፣ ቋንቋና ዜማ  የመቀራመቱ  ዘመቻ ይቁም!

ትላንት ተዋሕዶን በማናናቅ ምእመናኑን ለማስኮብለል ያልተሳካላቸው መናፍቃን፣ ዛሬ ደግሞ ስልት ቀይሰው የተዋሕዶን ታሪክ፣ ግዕዝ ጠቀሳና ያሬዳዊ ዜማን ያደነቁ በመምሰልየመፈታተናቸው አንድምታው ምን ይሆን? የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያቆየችውን ትውፊት፣ ቅርስና ሀብት የመቀራመቱ ድፍረትሳ ተመሳስሎ ተጠግቶ ማንነትዋን ለመጋራት ይሆን?ዓላማው መጀመሪያ ምእመኑን የማዘናጋት ቀጥሎ አንድነን ለማለትና ወደመናፍቅነት ለመሳብ ከዚያም እንደ ሰለጠነው ዓለም ፍጹም ዓለማዊ ለማድረግ ይሆንን?

 

መጽሐፍ ተዓቀቡኬ እምሐሳውያን ነቢያት እለይመጽኡ ሀቤክሙ በአልባሰ አባግዕ፣ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡ ሐሰተኞች፣ መናፍቃን፣ መምህራን ተጠንቀቁ፣ ወእንተ ውስጦሙሰ ተኩላት መሰጥ እሙንቱ፡፡በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላ ናቸው፣ ቢመረምሩዋቸው ግን ሰውን እየነጠቁ ወደ ገኀነም የሚያወርዱ የሰይጣን ሰራዊት ናቸው፡፡ (ወንጌል አንድምታማቴ 7፥15)

 

ይህን የወንጌል አሳብ እንደሚያስረዳን መናፍቃን ዓለማውያን የሚጠነስሱት ሴራና ፈጠራ ጌታችን መድኀኒታችንኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረው የማስጠንቀቂያ ትንቢት ቃል ውጭ የሆነ ያልታወቀ፣ ያልተረዳአዲስ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡አስቀድሞ”በስሜ ይመጣሉ” ብሎ ተናግሯልና፡፡ ለዚህምቀጥሎ የተመለከተውን የበግ ለምድ ምሳሌ ዝርዘር እንመልከት፣

 

  1. የበግ ለምድ ለብሰው የሚመጡ ተኩላ ያላቸውእውነተኛ መስለው የሚመጡ ሐሰተኞች መምህራንን ነው፣ ነገር ግን በእውነተኛ ሃይማኖት ጸንተው ያሉትን ክርስቲያኖች ተመሳስለው ገብተው በተለያየ ዘዴ ምእመኑን በመቀሰጥናከእምነቱ በማናጋት ወደገሃነም ለማውረድ የሚሠሩትን የዲያብሎስንሠራተኞች ነው፡፡

  2. የበግ ለምድ መልበስምሳሌ የሚያሳየውማስመሰያአሠራራቸውን፣ ድራማ መሰል ጥረታቸውን ነው፡፡ተኩላ ለምድ የሚለብስሆኖ አይደለም፣ ተኩላ ለምድን ከሚለበስ ቢበላው ይመርጣልና፡፡ መናፍቃንም የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ባትኖር ይመርጣሉ፣ ነገር ግን ሊውጡት ያሰቡትን ምእመን እንደ ተኩላ ለመንጠቅ ያመቻቸው ዘንድ የቤተ ክርስቲያኗን ግእዝና ዜማ የወደዱ መስለው መታየት የጀመሩትምእመኑን ለማዘናጋት የፈጠሩት አዲሱ ዘዴ ነው፡፡ ነገር ግን ግብራቸው የተኩላ ግብርእንዲመስል፣ ለነዚህ ቀሳጥያን ጌታችንአስቀድሞ ሲመስልባቸው የበግ ለምድ ለብሰው የሚመጡ ተኩላ ነጣቂ አላቸው፡፡ ይህም ተኩላ በግን ለመምሰል የበግን ቆዳ ቢለብስ እንዳይዋሐደውና በግን እንዳይመስል እነሱም እንደ ድራማ ትምህርቱን ልስበከው፣ ዜማውን ላዚመው፣ ቅዳሴውን ልቀድሰው፣መዝሙሩን ልዘምረው ወዘተ ብለው ቢጥሩ እውነተኛውን የተዋሕዶ አገልጋይ፣ አማኝእና ክርስቲያን መሆን አይቻላቸውም፡፡

  3. የበግ ለምድ የተባለው ምሳሌ፣ለምድ የበግ አካል የነበረ እንጂ የተኩላ አካል አይደለም፣ተኩላው ከላይ ለምዱን ቢደርበው አካል ሆኖት ደመ ነፍስ እንዳይዘራና ተኩላ በግ እንዳይሆን ሁሉ መናፍቃንም የተዋሕዶን አሠራር ሳያምኑበት በማስመሰልና ማቅረብ ቢሞክሩም እንኳን ውጤቱ ሕይወት አልባ ዳንኪራ፣ በቀቢጸ ተስፋ ያቀረቡት ሙሾ አስመስሎባቸዋል፡፡ በእሁኑ ወቅት የጀመሩት የተዋሕዶ ምእመናን የሚወዱትን ግዕዝ መጥቀስ፣ ያሬዳዊ ዜማን አስመስሎ ለማቅረብ የተሞከረው ሕይወት አልባ እንቅስቃሴየዚህ ማሳያ ነው፡፡የተዋሕዶ ሕዝብ ማስተዋል ያለበትይህን ሕይወት አልባ ሩጫ፣ ክርስቲያን ሳይሆኑ ክርስቲያንን ለማታለል ያደረጉት  የቅስጥ ድራማ መሆኑን ነው፡፡

 

በወንጌል ትርጓሜ እነዚህን ቀሳጥያን በሁለት ዓይነት ይገልጻቸዋል፣

  1. ሃይማኖተኛ የሚመስሉ መናፍቃን መምህራን

  2. መንፈሳውያን የሚመሰሉ ሥጋውያን መምህራን ይላቸዋል፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት ሁለቱ በተገቢው ሃይማኖት ላልተረዱ ሰዎች አደገኛ ናቸው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ይገልጻቸዋል ስለመናፍቅነታቸው፣ የዋጃቸውን ጌታ ክደው … የሚያጠፋ ኑፋቄ አሾልከው ያገባሉ፡፡ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሏቸዋል፡፡ ስለ ሥጋዊነታቸው ደግሞ … ይልቁንም በርኲሰት ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱ … ነውረኞችና ርኲሳን … ምንዝር የሞላባቸው ኀጢአትንም የማይተው ዓይኖች አሏቸው የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፣ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው የተረገሙ ናቸው (1ጴጥ 2፥1-16)ይላል፡፡

 

እነዚህ ሃይማኖተኛና መንፈሳውያን የሚመሰሉ የቤተ ክርሰቲያን ጠላቶችን ከላይ ከቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው፣ ምእመናን ማንነታቸውንና ዓላማቸውን መረዳት አለብን፡፡ ማንነታቸው መጽሐፍ እንደጠቀሰው ተኩላነት ነው፣ ማለትም ምንም ግእዝ ቢጠቅሱ ወይም ላላዋቂ ያሬዳዊ ዜማ ያዜምኩ ቢመስሉ እነሱ በልባቸው ከሃዲያን ናቸው፡፡ዓላማቸውም በመመሳሰልአቀራረብ ተቀባይነትን አግኝተው፣ ይህን እግዚአብሔርን የሚያከብር ሕዝብ ከእምነቱ ለማናጋት ነው፡፡

 

በመመሳሰል ”የማይጸኑ ነፍሳትን ያታልላሉ” እንዲል፣ ክርሰቲያን ልብ ሊለው የሚገባው ዋናው ነገር፣ የተዋሕዶ ተጻራሪዎች ሁሉ ሁል ጊዜ የመመሳሰል ስልታቸውን በመቀያየር ያልጸኑትን ምእመንዋን መሻማት የዘመናት አሠራራቸው እንደሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ የፖርቱጋል ካቶሊክ ሚሲዮናውያን የካቶሊክ እምነትን ወደ አገራችን ለማስገባት በተለይ ቤርሙዴዝ፣ አንድሬ አብያዶ፣ ጴጥሮስ ፖኤዝና አልፎኑስ ሜንደዝ ወዘተ ተልከው ነበር፡፡ ከእነዚህ አብዛኞቹ ወደ አገራችን ሲመጡ ሆን ብለው አጥንተው ግእዝን መናገርናየያሬዳዊን ዜማ እስከማዜም የደረሱ ነበሩ፡፡ እንዲያውም በሮም ቫቲካን የኢትዮጵያ ኮሌጅ በማቋቋም የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያንን ቋንቋግእዝን የሚናገሩና ያሬዳዊን ዜማ የሚያዜሙ ነጮችን በመላክ የጎንደርን ቤተ መንግሥት እንዴት ሲያተራምሱት እንደ ነበሩ ታሪክያስረዳናል፡፡ ዛሬም የመመሳሰል ዓላማቸውን እውን ለማድረግ በአገር ውስጥ እንቅስቃሴአቸው የተለያየ ገጽታዎች ሲያሳዩ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ይህንኑ ክብር ታቦትና ማኅሌት የሚወድ ህዝብን ለማታለልና ወደራሳቸው ለማስገባት አንድ ነን የሚል ስብከት፣ በዋና ዋና ከተሞች ባላቸው የጸሎት ቤት ታቦት አለን፣ ማኅሌት ይቆማል ሲሉ፣ ፕሮቴስታንት በበዙበት በሚመሰላቸው አካባቢ ደግሞ ፕሮቴስታንትንመመሳሰልይስተዋልባቸዋል፡፡ ሌሎችምየመመሳሰል አባዜ የተጠናወታቸው መናፍቃን እና ሥጋውያን እንደተለመደው ውጫውያንም ሆኑ የአገራችን በተለይ ከተዋሕዶ የወጡ ማለትም በቀሳጢዎች የተበሉ ካፈርኩ አይመልሰኝ እንዲል በቁጭት ሁል ጊዜ ይህንን ሕዝብ በመጎምዠት ለአጋንንት አሳልፈው ለመሰጠት ሲቋምጡና ለመንጠቅ ሲተጉይገኛሉ፡፡

 

ከላይ በግልጽ ለይተን አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ማንነት ባጭሩ ማብራራት እንደሞከርነው ሁሉ፣ ለምን ስልታቸውን መቀያየር አስፈለጋቸው የሚለውን ማየት ግድ ይለናል፡፡ ስልታቸውን መቀያየር ያስፈለገበት ምክንያት የተዋሕዶ እምነትና ሥርዓት አንዳች የማመን ፍላጎት አድሮባቸው አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን ሲወቅሱና ሲከሱ ነበርና፡፡

 

ለዚህ ምክንያት የደረሰባቸውን ክስረት መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ይህም፡-

  1. የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባደረገችው ጸረ ተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ ህዝቡን በማስተማሯ ህዝቡ እኲይ ተግባራቸውን ስለተረዳ

  2. ህዝቡ ራሱ መልስ በመስጠት ራሱን መከላከል ስለጀመረ

  3. በስህተት መንገዳቸው ተጉዞ የነበረው ሕዝብ ወደ ቤቱ መመለስ ስለጀመረ

  4. ቤተ ክርስቲያኗን በማጥላላት ያደረጉት ዘመቻ በመክሸፉ እንደማያዋጣቸው ስለተረዱ

  5. ከቤተ ክርሰቲያኗ ህዘቡን እየደለሉ በማስኮብለል የሚያገኙት ይሁዳዊ ምንደኝነት ስለቀረባቸው

  6. የካሴት ሽያጭ፣ የህዝቡ መዋጮ ወዘተ ገቢ ስለቀረባቸው ፤ ወዘተ ነው፡፡

 

ከላይ የተዘረዘረውና ሌላም የኪሳራ ምክንያቶቻቸውሳይወዱ በግድ ልባቸውን ጸፍቶ አፋቸውን ከፍቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ክርስቲያኑ ሁሉ ይህን ሁኔታ በቀላሉ ማየትናበዝምታ ማለፉ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ክስረት ያናጋው መናፍቅ ከዚህ የበለጠ ሌላ የድፍረት ዘዴ ለመፍጠር መሞከሩ አይቀሬ ነው፡፡ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይበግእዝና በያሬዳዊ ዜማ ያዘጋጁት ዝግጅት ገበያ ተኮርያውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናንን ማእከል ያደረገ መሆኑን ነው፡፡ልንረዳው የሚገባን አንዳንድ ምእመናን የማስመሰል ተንኮላቸውን ባለመረዳት ካሴታቸውን መግዛትና ማዳመጥ ሁለት አደጋ ያመጣባቸዋል፣ አንደኛው በመናፍቅ መንፈስ የተዘጋጀው ዜማ ማዳመጥ ራሱ ቆይቶ መናፍቅ ሚያደርግ መሆኑን፣ ሁለተኛው የመናፍቃን ከኪሳራቸው አንዱ ገንዘብ በመሆኑ አማኙን ህዝብ የሚያስቱበትን ገንዘብ ለነሱ መገበር ራሱ ከመናፍቅነት አይለይም፡፡

 

የአሁኑየለየላቸው መናፍቃን ወዳጅ የመምስል ስልታቸው ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ተኩላ በግን ለመምሰል ቆዳ ብትደርት ተኩላነቷን እንዳይቀይር ሁሉ ምእመናንን ያታልላሉ መስሎአቸው አንዴ ግእዙን አንዴ ዜማውን ያልኩ ቢመስላቸውም ”ዪህቺ ጠጋጠጋ … ” እንዲሉ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ይህ መሰሪነታቸው ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ዓላማቸው የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ ታሪኳን ተናጋሪ፣ ዜማዋን ወዳጅ፣ ጥንታዊነቷን አክባሪ ወዘተ በመምሰል የህዝቡን ልብ ለማግኘት የተዘየደ ዘዴ ለማንም አይጠፋውም፡፡ ነገር ግን ዘዴው ጊዜ ያለፈበት ድሮ በነ ዐጼ ሱሱንዮስ ዘመን እነ አልፎኑስ ሜንደዝ የሞከሩት ነገር ግን እነ ዐጼ ፋሲል አውቀውት ምላሽ የሰጡበት፣ የማይረሳ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ መሆኑ ወገኔ ትዝ ሊለው ግድ ይለዋል፣ የብዙ ክርስቲያን ደም ተከፍሎበታልና፡፡ አሁንም ይህች መመሳሰልና ቀይ መስመር መጣስ የነ አልፎኑስ ሜንደዝ ድፍረት ጋር አንድ ናትና ከወዲሁ ካልታሰበባት በኋላ ከባድ ዋጋ እንዳታስከፍል ስጋታችን ነው፡፡

 

ዋናው ጉዳይ ባለፈው በተካሄደው የጸረ ተሐድሶ ዘመቻ መናፍቃን የፈራረሰባቸውን ሁለንተናዊ ክስረት ማለት በቤተ ክርሰቲያኗ ውስጥ ምእመኑን መናፍቅ የማድረግ ቅሰጣ ሲመታባቸውና ሴራው ሲከሽፍባቸው፣ ውድቀታቸውን መልሶ ለመገንባት ስፖንሰራቸው የሰጣቸው አዲሱ አሰራር  በግልጽ ውዳሴ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንቋንቋ ግእዝ፣ ዜማዋ፣ ታሪኳ ወዘተ ማቅረብ ነው፡፡ ይህ የለየላቸው መናፍቃን ደርሶ የቤተ ክርስቲያኗወዳጅ መምሰል ለኛ አዲስ ነገር አይደለም፤ ተሐድሶቹም ሲጠቀሙበት የነበረ ስልት ነው፡፡ የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ በሚለው መጽሐፍ (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያየማኅበረ ቅዱሳን ዶክሜንቴሽን ክፍል፣ ቁጥር 1፣ ሚያዝያ 2003 ዓም ገጽ 58)  እንደተጠቀሰው ተሐድሶዎች ያቀዱት ዋና ጉዳይ ተሐድሶ እንኳን እንደሆነ የማያውቅ ግን ተሐድሶ የሆነ ትውልድ መፍጠር እና ሳያውቀው የሚደግፍ ቲፎዞ ማፍራት ነበር፡፡ ማለትም በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ሆኖ የመናፍቅን ዶግማ የተቀበለ የእነሱን ዜማ የሚያዜም ወዘተ ቡድን ማመቻቸት ነበረ፡፡ ስልቶቹን መጽሐፉ እንዲህ ይጠቅሳቸዋል፣

 

  • ተቆርቋሪ መምሰል፣ ገንዘብና እርዳታ በመስጠት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማትና ሕዝቡን መያዝ እና ቲፎዞ እንዲሆን ማድረግ፣

  • ኦርቶዶክስን የማያውቅ፣ ፕሮቴስታንት የሆነ፣ ነገር ግን ተሐድሶ (ፕሮቴስታንት) መሆኑን እንኳ የማያውቅ ምእመን ማፍራት፡፡ ማተብ ያሰረ፣ ነጠላ የሚያጣፋ፣ እምነቱና መንፈሱ ግንፕሮቴሰታንት የሆነ፣ ሆኖም ፕሮቴስታንት ነኝ የማይል (ፕሮቴስታንት መሆኑን ሳያውቅ ስለተለወጠ)፣ ”እኔ ኦርቶዶክስ ነኝ” እያለ የሚናገር(ሀርድ ዌሩ ሳይቀየር ሶፍት ዌሩ የተቀየረ)ትውልድ ማፍራት ነው፡፡

 

እንዲሁም በዚህ ወቅት ፕሮቴስታንቱ በግልጽ መሰደቡንና መወገዙን በውስጥ አድርገው በውጪ ውዳሴ የጀመሩት፣ የኦርቶዶክስ ምእመናንን በመመሳሰል ለመሳብና ቢቻላቸው ፕሮቴስታንት ለማድረግ ባይሆንም ቲፎዞ ለማድረግ፣ እንዲሁም ቲፎዞ በመሆን መካከል  በሚፈጠረው ያለመግባባት ክፍተት ያልጸኑትን ለማግኘት ነው፡፡

 

ባጠቃላይምከላይ እንደገለጽነው መናፍቃን ምን ጊዜም የተወሰነ ሃይማኖታዊ የትውፊት፣ የዶግማ፣ የሥርዓት ወዘተ ገደብ የሌላቸው በመሆኑ የሌላውን መንጋ ለመቀሰጥ ቢቻላቸው በማጥላላት ባይቻላቸው በመመሳሰል ራሳቸውን እየለዋወጡ የተለያየ ስልት እንሚጠቀሙ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ለመመሳሰል በሚያደርጉት ቅሰጣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያቆየችውን ትውፊት፣ ቅርስና ሀብት እንዲሁም ግእዝ ቋንቋና ያሬዳዊ ዜማን ማንም እንደፈለገ አስመስሎ ባልተገባ መንገድ የመቀራመቱ ድፍረት ቤተ ክርስቲያን እንዴት ታየዋለች? ያውም ቤተ ክርስቲያን የማትፈቅደው የመናፍቅ ድርጅት በሀብቷ ላይ ሲፈነጭ፣ ይህስ ጉዳይ ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል? አንድ ተቋም ያላትን ሀብት ያለፈቃዷ ማንም መጠቀም ይችላልን? ምእመናን በሙሉ በተለይ የሕግ ባለሙያ ልጆቿ እንዲነጋገሩበት የሚስፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ምእመናን መገንዘብ የሚገባን መናፍቅ ያወጣውን የቅስጥ ዜማ ያሬዳዊ መስሎን በመጠቀም የዓላማቸው ሰለባ እንዳንሆን አንዱ ለሌላው ማሳሰብና ማስረዳት ተገቢ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበግ ለምድ ለብሰው ማለት እውነተኞች መስለው ከሚመጡ ሐሰተኞች፣ ሃይማኖታውያን መስለው ከሚመጡ መናፍቃን፣ መንፈሳውያን መስለው ከሚመጡ ሥጋውያን መምህራን ተጠንቀቁ ብሎ አስተምሮናልና እንጠንቀቅ፣ እርስ በርሳችንም እንጠባበቅ፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡


አዲስ ዓመት

ጳጉሜን 5 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዳዊት ደስታ

ኢትዮጵያ የወራት ሁሉ መጀመሪያ መስከረም ነው፡፡ ይህ ወር ዘመን መለወጫ፣ ዕንቁጣጣሽ፣ ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል፡፡ ስለ አዲስ ዓመት በተለያየ ስም የመጠራቱ ታሪካዊ አመጣጥና ስያሜ መነሻ አሳቡ ምን እንደሆነ እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

 

ዘመን መለወጫ

ዘመን መለወጫ መስከረም ወር የሆነበት ምክንያት “ብርሃናት /ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ሌሊቱ ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱን ጠንቅቀው ቢቆጥሩ 364 ቀናት ይሆናል፡፡ “ሌሊቱም ከቀኑ ጋራ ይተካከላል፡፡ ዓመቱም ጠንቅቆ ቢቆጥሩት ሦስት መቶ ስልሳ አራት ቀን ይሆናል፡፡ /ሄኖክ.26፥44/ “ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድሱ” /ሰ.ኤር.5፥21/ እንዲል፡፡

በዘመነ ኖኅ ዓለምን ንፍር ውኃ አጥለቅልቆት ከቆየ በኋላ ዳግመኛ ውኃው የጎደለበት በመሆኑ /ኩፋሌ 7፥1/ “በመጀመሪያው ወር መባቻም ምድር ታየች” እንዲል፡፡

 

ዕንቁጣጣሽ

ዕንቁጣጣሽ የተባለበት ምክንያት አንደኛ “ዕንቁ – ዕፅ አመጣሽ” ብሎ የአበባውን መፈንዳት ያመለክታል፡፡ ሁለተኛ ኖኅ ለሦስቱ ልጆቹ አህጉራትን በእጣ ሲያካፍላቸው አፍሪካ ለካም ደረሰችው፡፡ በአፍሪካ ምድርም ሲገባ በመጀመሪያ ያረፈው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሀገሪቱም በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፡፡ ወሩ ወርኀ መስከረም በመሆኑ ደስ ብሎት ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል፡፡ ሦስተኛው /1ነገ.10፥1-10/ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሣባ /አዜብ የንጉሡን ጥበብ ከመስማት ማየትን መርጣ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ከብዙ ሠራዊቶቿ ጋር የእጅ መንሻ በመያዝ ሄደች፡፡ ንጉሡም በደስታ ተቀብሎ እርሱም “እንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንሽ” በማለት አራት አይነት ቀለም የሚታይበት በቀንና በሌሊት የምታበራ ቀለበት ሰጥቷታል፡፡ ወሩም ወርኀ መስከረም ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት እንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜ ወጥቷል፡፡

 

ቅዱስ ዮሐንስ

ሦስተኛው የአዲስ ዘመን ስያሜ ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡ የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ እንዲሆን ለኢትዮጵያ ዐውደ ዓመት መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር አባቶች ወስነዋል፡፡ /ድርሳነ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1-3/ መጽሐፈ ስንክሳር “የመስከረም ወር የተባረከ ነው፡፡ እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው፡፡ የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ቀኑ እየጎደለ ይሄዳል” እንዲል፡፡

 

በአጠቃላይ ዘመን መለወጫ ከላይ ባየናቸው የተለያየ ስያሜ ይጠራ እንጂ ዘመኑ አዲስ እየተባለ ቢጠራም አዲስ መሆን ያለበት ወርና ወቅቱ ብቻ ሳይሆን የእኛ የክርስቲያኖች ሥርዓት ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውነታችሁን አታርክሱ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነውና እያለ በመዋዕለ ሥጋዌው ያስተምር ነበር፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ በኀጥያት፣ በተንኮል፣ በክፋት የቆሸሸው ሰውነታችን በንስሓ፣ በቅዱስ ቊርባን፣ በመልካም ተግባር አዲስ ልናደርገው ይገባናል፡፡

Kiduse Rufyele

መልአከ ሰላም ወጥኢና

ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

Kiduse Rufyele

ጳጉሜን፡- “ጭማሪ፣ ተወሳክ፣ አምስት ቀን ተሩብ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ ጳጉሜን 13ኛ ወር ትባል እንጂ በውስጧ የያዘቻቸው ቀናት ቁጥር በአንድ ሳምንት ካሉ ቀናት ያነሱ ናቸው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ኢትዮጵያን ብቸኛዋ የዓለማችን ባለ 13 ወራት ሀገር እንድትሆን ያስቻለች ልዩ ወር ናት፡- ወርኀ ጳጉሜን፡፡

 

ጳጉሜን ገዝፋና ጎልታ የምትታየው በመንፈሳዊ  ዓለም ነው ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ በዚህ የተነሣ በርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች ወርኀ ጳጉሜን በጾምና በጸሎት /በሱባኤ/ ያሳልፏታል፡፡ በተለይም እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በቅዱስ ሩፋኤል ዕለት ሰማያት የሚከፈቱበት /ተርኅዎ ሰማይ/ መሆኑን በማመን ምእመናን ወደ ፈፍላጋት በመሄድ እንዲሁም በጳጉሜን ቀናት በሚዘንበው ዝናብ በመጠመቅና በረከትን ይሻሉ፡፡ ጸሎታቸውንም ከምንገባም በበለጠ ያቀርባሉ፡፡

 

ወርኀ ጳጉሜን የጌታችን ምጽአት የሚታሰብባት በመሆኗ የሚዘመረው መዝሙር፣ የሚነበቡ ምንባባትና ቅዱስ ወንጌሉ እንዲሁም የሚሰበከው ምስባክ ይህንኑ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ፡-

 

“ከመ ንተ መብረቅ ዘይወፅእ እምጽባሕ ወያስተርኢ እስከ አረብ ከማሁ ምጽአቱ ለወልደ እግዚአብሔር ምስለ ኀይለ ሰማያት በንጥረ መባርቅት/ከ/ ምስለ አላፍ መላእክት /ከ/ ወኲሎሙ ሊቃነ መላእክት /ከ/ አክሊለ አክሊላት ዲበ ርእሶሙ” ይህም ማለት፡-


“መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንዲታይ በመባርቅት ፍጥነት፡ – ሰማያውያን ኀይላት ከብዙ መላእክትና የመላእክት አለቆች ጋር በካህናት ራስ ላይ ያሉት አክሊሎች መገኛ የሆነው የሾህ አክሊል ደፍቶ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሁ ይመጣል” ማለት ነው፡፡

 

በየዓመቱ ጳጉሜን ሦስት ቀን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓልም በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት፣ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ይህም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ከከበሩት ቅዱሳን መላእክት ሦስተኛው ነው፡፡ መጽሐፍ፡-  “ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል፡፡ /ጦቢት 12፥15/

 

መላእክት ሲፈጠሩ የማይሞቱ፣ የማይራቡ፣ ጾታ የሌላቸው ዝንተ ዓለም በቅድስና ጸንተው እንዲያገለግሉና ፈጻምያነ ፈቃድ እንዲሆኑ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከአንዱ ዲያብሎስና ከተከታዮቹ አጋንንት በቀር ቅዱሳን መላእክት ሁሉ በተፈጠሩበት ዓላማ ጸንተው ያሉና የሚኖሩ ናቸው፡፡ በዚሁ አገልግሎታቸውም የእግዚአብሔርንና የሰውን በጎ ፈቃድ ሲፈጽሙ ይኖራሉ፡፡ ያለማቋረጥ ፈጣሪያቸውን ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት አንዱ መልአከ ጥኢና ወሰላም /የሰላምና የጤና መልአክ/ የሚባለው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡

 

“ሩፋኤል” የሚለው የስሙ ትርጓሜ ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ ማለት ነው፡፡

በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ሆነ ቁስል ይፈወስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” መጽሐፈ ሄኖክ 6፥3 ይላል፡፡ ለቆሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው ለማሕጸን ችግር ሁሉ ለሴቶች እረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም ሕፃኑ አርባ ቀን ሞልቶት፣ በማሕፀን እያለ “ተስእሎተ መልክዕ” /በሥላሴ አርአያ መልኩ መሳል ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ/ ቅዱስ ሩፋኤል አይለየውም፡፡ በወሊዳቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማሕፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀላል፡፡

 

ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነት ያለን ረቂቅ ርኩስ መንፈስ ያውቃል፡፡ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በወለተ ራጉኤል ጭን ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል፡፡ /ጦቢት.3፥8-17/

 

“ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው” /ሄኖክ 3፥5-7/ በዚህ መሠረት ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ /ሄኖክ፤2፥18/ የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቁስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ “በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም ቁስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል፡፡ /ሄኖክ.10፥13/

 

የጦቢትን ልጁ ጦቢያን በሰው አምሳል ተገልጦ ከተራዳው በኋላ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ ራሱን ሲገልጥ “የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው” /ጦቢት.12፥15/

 

የቅዱስ ሩፋኤል በዓሉ የሚከበርባቸው ምክንያቶችም ሁለት ናቸው፡፡ እነርሱም አንደኛው በዓለ ሢመቱን ምክንያት በማድረግ ሲሆን ሁለተኛው የቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ስለሆነ ነው፡፡ ይኸውም በመጽሐፈ ስንክሳር እንዲህ ተመዝግቧል፡፡ ከእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ በደሴት የታነጸች ቤተ ክርስቲያኑ በከበረ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን በውስጧ ተአምር የተገለጸባት የከበረችበት ነው፡፡

 

ይህም እንዲህ ነው፤ ሀብትም ሴት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መጥታ ሳለ ከእርሷ ጋርም ብዙ ሰው ነበረ፡፡ ከባሏም የወረሰችው ብዙ ገንዘብ አላት፡፡ በሊቀ ጳጳሳቱ ቤት አንጻር ያለውን ኮረብታ አስቆፈረችው በዚያም የወርቅ መዝገብ ተገለጠ፡፡ በዚያም ወርቅ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን አነፀ፤ ከእርሳቸውም አንዲቱ የመላአክት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል በስሙ የታነፀች ይህች ናት፡፡ ሥራዋንም በፈጸመ ጊዜ እንደዛሬው በዚች ቀን አከበራት፡፡ ብዙ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጸች፤ ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና፡፡ የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔርም በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮሁ፡፡ ያን ጊዜ ይህ የከበረ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ እንዲህ አለው “እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም!” አንበሪውም ጸጥ ብሎ ቆመ፡፡ አልታወከም፡፡ በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆነ” ይላል፡፡

 

በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በወርኀ ጳጉሜን ከሚታሰቡት እና ከሚከበሩት በዓላት መካከል ጳጉሜን 2 ቀን የሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ በዓለ ዕረፍቱ፣ እንዲሁም ጳጉሜን 5 ቀን የነቢዩ አሞጽ ዕረፍት ይጠቀሳሉ፡፡

 

ፈጣሪያችን ከሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል እና ከቅዱሳኑ በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡

ቤተ ክርስቲያንና የፓትርያርክ ምርጫ

ነሐሴ 25 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

ቤተ ክርስቲያን አንዲት፣ ቅድስት፣ ኩላዊትና ሐዋርያዊት መሆኗን ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን ሁሉ ይቀበላሉ፤ በመሠረተ እምነታቸው ውስጥም አካትተው በጸሎትና በአስተምህሮ ይጠቀሙበታል፡፡የዚህ መሠረታዊ ምክንያቱ ደግሞ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ይህ ትምህርት ቢኖርም ነገር ግን መልእክቱን በአግባቡ ካለመረዳት የተነሣ እነ አርዮስና መቅዶንዮስ በትውፊት ከሐዋርያት ጀምሮ የመጣውን የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ መሠረት መቀበልን ቸል ብለው በራሳቸው መንገድ ሔደው ስለሳቱ በጉባኤ ኒቅያ በማያሻማ መንገድ ቤተ ክርስቲያን አንዲት፣ቅድስት፣ ሐዋርያዊት እና ኩላዊት መሆኗን አስቀመጡ፡፡ በኋላ በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ደግሞ ሁላችንም እንድንጸልይበት በተዘጋጀው አንቀጸ ሃይማኖት ላይ (ጸሎተ ሃይማኖት) ‹‹ ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት›› የሚለው የጸሎታችን መፈጸሚያ እንዲሆን ተደነገገ፡፡ በዚህም መሠረት እነዚህን ዓለም አቀፍ ጉባኤያት የሚቀበሉ ሁሉ የሚቀበሉትና የሚመሩበት መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት /doctrine/ ሆነ፡፡

ይሁን እንጂ እየዋለና እያደረ ሲሔድ ቃላቱን ተርጉመው የሚረዱበት ሁኔታ እንደገና እየተለያየ መጣ፡፡ ለምሳሌ ያህል ከዚሁ አንቀጸ ሃይማኖት የሚነሱትን ሦስት መሠረታዊ ልዩነቶች ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ራሱ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ መረዳት ላይ ያለው ልዩነት ነው፡፡ በፕሮቴስታንቱ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በአንድ ቦታ የተሰባበሰቡት ሰዎች ኅብረት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አለፍ የሚሉትም ቢሆን በምድር ያለውን የአማኞቻቸውን ኅብረት አንድ መንጋ እንዲሁም በሰማይ ያሉትን ደግሞ ሁለተኛ መንጋ አድርው በአንድ እረኛ ሁለት መንጋ ሀሳብ የሚያራምዱ እንደ ሆኑ የምዕራባውያን ጽሑፎች ያሳያሉ፡፡ በምሥራቃውን ትውፊት ወይም በኦርቶዶክስ ግን ‹ቤተ ክርስቲያን› ማለት በምድር ያሉት ምእመናንና ተጋድሏቸውን የፈጸሙ ቅዱሳን ኅብረት ወይም አንድነት ናት፡፡ “እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አእጹቂሃ..” “ሥሮቿ በምድር ቅርንጫፎቿም በሰማይ ያሉ” የሚለው የቅዱስ ያሬድ ትምህርትም ለዚህ ትልቅ አስረጂ ነው፡፡ በሰማይ ያሉት በዚህ በእንግድነት ከምንኖርበት ምድር ተጋድሏቸውን ፈጽመው ሀገራቸው ገብተው ሽልማታቸውን ተቀብለው በድል ዝማሬ ላይ ያሉ ሲሆን በዚህ ያለነው ደግሞ በዕድሜ ዘመናችን እየተጓዝን ያለንና ገና ተጋድሏችን ያለፈጸምን መሆናችን እሙን ነው፡፡ ሆኖም በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንና ብልቶቹ በሆንለት በቤተ ክርስቲያን ራስ በክርስቶስ አንድ ስለሆንን ቤተ ክርስቲያን አንዲት ብቻ ናት፤ መንጋው አንድ እረኛውም አንድ፡፡ ለምሳሌ በእኛም ሆነ በሌሎቹ ኦርቶዶክሶች ያለውን ቅዳሴ በአስተውሎት ብንመረምረው ይህን ዶግማ ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡ ወደ ፊት በደንብ የምናየው ቢሆንም ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መነሻውና መሠረቱ ይህ ነው፡፡

ታዲያ ይህን ‹‹ ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት›› የሚለውን አንቀጹ ራሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ በመሆኑ ሁሉም ቢቀበሉትም በትርጉም ግን ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ የሮማ ካቶሊክ ‹አንድነትን›› በሮማው ፓፓ ሥር በመተዳደር ስትተረጉመው ኦርቶዶክሶቹ ግን አንድነት የሚገለጸው ዓለም በሙሉ በአንድ በመተዳደሩ አይደለም፤በምድር ተጋድላቸውን እያደረጉ ያሉ ምእመናንን በአንድ ምድራዊ ሃይማኖታዊ ተቋም አስተዳደርም የአነድነቱ ምንጭ አይደለም፤ ነገር ግን አማናዊ ሥጋውንና ደሙን ስንቀበልና የክርስቶስ ብልቶች ስንሆን ያን ጊዜ በአንዱ በክርስቶስ አንድ እንሆናለን ግንዱ አንድ ስለሆነ በዚያ የወይን ግንድ ያሉ ምእመናን ሁሉ በዚያው ግንድ ላይ በመሆናቸው ወይም አካሉ በመሆናቸው አንድ ናቸው፤ቤተ ክርስቲያንንም አንድ የሚያሰኛት ይህ የአንዱ ክርስቶስ ብልትነታችንንና አንድ አካል መሆናችን ነው ፡፡ “…ይዌልጦሙ በቅጽበት አባላተ ክርስቶስ ይኩኑ፤ በኃይለ ጥበቡ መንክር ወዕጹብ ኪኑ” “ድንቅና ዕፁብ በሆነ በጥበቡ ኀይል የክርስቶስ አካላት ይሆኑ ዘንድ በቅጽበት ይለውጣቸዋል፡፡” እንዳለ የመልክአ ቁርባን ደራሲ፡፡የኦርቶዶክሳውያን ትርጓሜ ይህን መንፈሳዊነትንና ከክርስቶስ ጋር ያለንን ውሕደት መሠረት ያደረገ ነው፡፡

 

ከዚሁ ጋር በትልቁ መሠረት የሚሆነው ደግሞ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት›› የሚለው እምነት ነው፡፡ እዚህም ላይ ትልቅ ልዩነቶች አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርዊት ናት የምትባለው መቼ ነው የሚለውን ጥያቄ ሲመልሱ ኦርቶዶክሳዊያን ሦስት ነገሮች ሲሟሉ ነው ይላሉ፡፡ የመጀመሪያው ሢመተ ጵጵስና ወፓትርያርክን የሚመለከት ነው፡፡ ይህም አንዲት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት የምትባለው ጌታ ከሾማቸው ከሐዋርያት አንሥቶ ያልተቋረጠ ክትትል ያለው የሢመት ሐረግ ሲኖር ነው፡፡ ለምሳሌ የእኛ ከቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ አንሥቶ ሳይቋረጥ እስከ ቄርሎስ ስድሰተኛ (116ኛው) ፓትርያርክ ከደረስ በኋላ ለእኛ 117ኛ ሆነው አባ ባስልዮስ ኢትዮጵያዊ ተሾሙ፡፡ አሁን 121ኛው አባ ጳውሎስ ሆኑ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊት የሚያሰኘው ደግሞ ሐዋርያዊ ትዉፊትን ተቀብላ የምትተገብር መሆኗ ነው፡፡ ከእነዚህም አንዱ ጳጳሳትን በተለይም ፓትርያርኮችን የምትመርጥበት ሐዋርያዊ ትዉፊት ወሳኙ ነው፡፡ ሦስተኛው ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ የሚያሰኛት ደግሞ ሐዋርያዊ ክትትሉን የጠበቀ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ነው፡፡ ዶግማ የሚባለውም የዚህ ትርጓሜ ውጤት ነው፡፡

 

ከእነዚህ ነጥቦች ተነሥተን የእኛን ቤተ ክርስቲያን ሂደት (Experiance) መዳሰስ ቅድሚያ የሚሰጠው ሆኖ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም አንደኛ በታሪካችን ውስጥ ከነበሩት ጠንካራ ጎኖች ብቻ ሳይሆን ከድከመቶቹም የምንወስዳቸውን ጥቅሞች በቅርበት ለመመርመር፤ ሁለተኛም ከዚያ ተነሥተን ወደፊት የምንሔድበትን ለማየት ስለሚጠቅም ነው፡፡

 

ቀደም ብለን እንደገለጽነው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት የምትባለው ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ሲመተ እድ ባለተቋረጠና ክትትል ባለው ሐዋርያዊ ክህነት (Apostolic succession)እስካሁን በመኖሯና ሐዋርያዊ ትውፊትንም ከዚያው ሳትወጣ የምትፈጽም በመሆኗ ነው፡፡ ሆኖም በታሪካችን ሐዋርያዊ ትውፊትና ቀኖና የተፈተኑበት ጊዜ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ ከሁለት ሺሕ ዓመት አገልግሎት አንጻር ሲታይ አጋጣሚዎች ጥቂትና ጊዜዎቹም አጫጭር ቢሆኑም ከትፊዉቱ የመውጣትና የውጤቱንም መከራና ፈተና ማጨድ እንደነበረ ግን ታሪካችን ያስረዳል፡፡ ምንም እንኳ ዘመኑ ትንሽ ዕድሎቹም ጥቂት የነበሩ ቢሆኑም ያስከተሉት ጥፋትና ጉድለት ግን ትንሽ አልነበረም፡፡ሆኖም በየዘመኑ የነበሩ አባቶች ከችግሮቹ እየተማሩ ትውፊታቸውን አጥብቆ ወደመጠበቅ በመመለስ ከችግራቸው ወጥተዋል፡፡ ለመሆኑ ቀኖናውና ትውፊቱ ምንድን ነው?

 

ትውፊቱ

የቤተ ክርስቲያንን የጵጵስናና የፕትርክና ሹመት ታሪክ ጸሐፊዎች መነሻ የሚያደርጉት ጌታችን ሐዋርያትን የመረጠበትን ሁኔታና በሐዋርያት ሥራ ላይ የተገለጸውን የማትያስን ምርጫ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ‹‹ ሐዋርያዊት›› በሚያሰኟት በእነዚህ ሁለት የምርጫ ክስተት ውስጥ ሦስት መሠረታዊ መስፈርቶችን እንደ ምሳሌ ይወስዳሉ፡፡ እነዚህም

 

1ኛ) የሐዋርያት ከተርታው ሰው ውስጥ መመረጣቸው

ታሪክ ጸሐፊዎቹ እንደሚሉት ሁሉን ማድረግ የሚቻለው ጌታ ከምሁራነ ኦሪት ቅኖቹን መምረጥና ማብቃት መለወጥ እየተቻለው እነርሱን ትቶ ከተርታ ሰዎች ምንም ካልተማሩትና ምንም ልምድም ሆነ ዕውቀት የሌላቸውን መርጦና አምጥቶ አስተምሮ ቅዱሳን ሐዋርያትን የሾመው ወደ ፊት ፓትርያርኮች ከአነሥተኛው መዓርግ እየተመረጡ እንዲሾሙ ሲያሰተምረን ነው ይላሉ፡፡ እንዲያውም እንደ ቅዱስ ጳውሎስና እንደ አጵሎስ ያሉትን ምሁራነ አሪት እንደሚመልሳቸው እያወቀና ክብራቸውንም በተለይ ቅዱስ ጳውሎስ ቁጥሩም መዓርጉም ከሐዋርያት ሆኖ ሳለ መጀመሪያ ያልተመረጠው ምርጫው መንፈሳዊነትን እንጂ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ እንዳይሆን ሥርዓት ሲሠራልን ነው በማለት ያስረግጣሉ፡፡ ጌታ ሐዋርያትን ከመረጠ በኋላ ግን አስተምሯቸዋል፤ በዚህም መሠረት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በተገቢው መንገድ ለአገልግሎትና ለምሥጢራት በሚያስችል ሁኔታ ከተማረና በርግጥ መንፈሳዊ ሆኖ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጠብቆ ከተመረጠ ሌላውን ዕውቀት ከራሱ ከጌታ ሊያገኘው ይችላል ባዮች ናቸው፡፡

2ኛ)የሰዎች ድርሻ

በቅዱስ ማትያስ ምርጫ ሒደት ውስጥ ከተገኙት ሁለት መሠራታዊ ትውፊቶች አንዱ ደግሞ ሐዋርያት መጀመሪያ ሁለት ሰዎችን መርጠው ድርሻቸውን መወጣታቸው ነው፡፡ ስለዚህ አባቶችን በመምረጥ ሒደት ሓላፊነት ያለባቸው አካላት አሉ፡፡ እነዚህ አካላት ግን ልክ እንደ ሐዋርያት ሊሾም ከታሰበው በላይ ቁጥር ያላቸውን መርጠው ማቅረብ አለባቸው፡፡ ሐዋርያት አንድ ሰው በይሁዳ ለመተካት ሲፈልጉ ሁለት እንዳቀረቡት ሁሉ ለመጨረሻው አባትነት ለፓትርያርክም አባቶች መምረጥ ያለባቸው ከአንድ በላይ መሆን አለበት፡፡

3ኛ) የእግዚአብሔር ምርጫ

ቅዱሳን ሐዋርያት ማትያስንና በርናባስን (ዮሴፍን) ከመረጡ በኋላ ከሁለቱ አንዱን የመምረጡ ድርሻ ግን የእግዚአብሔር ነበረ፡፡ ስለዚህ ማንኛችንም ቢሆን ከሐዋርያት ልንበቃ አንችልምና በወደደው መንገድ የእግዚአብሔርን የመምረጥ ዕድል የሰጠ መሆን አለበት፡፡የጥንታዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትውፊትም በእነዚህ መሠረቶች ላይ የተገነባ የሰውንና የእግዚአብሔርን ድርሻ በግልጽ የሚያስቀምጥ ነበር ይላሉ፡፡

ቀኖናውስ?

‹‹የእግዚአብሔርን መንጋ በእውቀት ለመጠበቅ ፍጹም የሆነ የሰው እጥረት አለ፡፡… ትክክለኛ የቀኖና እውቀትም የለም፡፡ ኃጢአትን ለመሥራት ሙሉ ነጻነት አለ፡፡ ሰዎች በአማላጅ ክህነትና እልቅና በተሾሙ ጊዜ ውልታቸውን ለመመለስ ሲሉ ቀኖናዊ ጥፋቶችን ቸለል ይላሉ፡፡›› ባስልዮስ ዘቂሳርያ /Basil of Caesaria, To the Italians and Gauls, letter 92/

“አንድ ጳጳስ በድርቅና በረሃብ፣ በተሾመባት ከተማ ትንሽ መሆን፣ በሕዝቡ ማነስ፣ በቂ ገቢ በሀገረስብከቱ ባለመኖሩና በመሳሰሉት ምክንያት ከተሾመባት ከተማ ወይም መንደር ተነሥቶ ወደ ሌላ አይሂድ፤ ከዚህ የተሻለ ይሰጠኝ ብሎም አይጠይቅ፤ እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር የሚከፈለው ዋጋ አለውና” ይላል፡፡ በዚህ መሠረት

1ኛ) አንድ (ሊቀ) ጳጳስ ወደ ፕትርክና ቢመጣ እንደሚስት የምትቆጠርለትን ሀገረ ስብከቱን በማቅለሉና ሌላ የተሻለች መንበር (ሚስት) በመፈለጉ ምክንያት ብቻ የተነቀፈ ነው፡፡

2ኛ) ለፕትርክና ሲሾምም ጳጳሳቱ እጃቸውን የሚጭኑበት ‹‹ በ…ሀገር እና…ከተማ›› ብለው ስለሆነ ሁለተኛ እንደ ማግባት ተቆጥሮ እንደ ዝሙት ያስቀጣዋል ወይንም ክህነቱን ያሳጣዋል ይላሉ፡፡

3ኛ) ጌታ እንዳደረገው ወደ ላይኛው ሥልጣን የሚመጡት ከታችኛው ከአበ ምኔትነትና በታች ካለው እንደሆነ ትውፊቱ ያስገድዳልና፡፡

ይህንን ሀሳብ በትክክል ለመረዳት ግን የፓትርያርክን መሠረተ ሀሳብ በደንብ መፈተሽና በትክክለኛው ሁኔታ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በሐዋርያት ትውፊት መሠረት ፓትርያርክ ወይንም ፖፕ የሚለው ቃል ራሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ከ232-247 ዓ.ም. ድረስ በእስክንድርያ መንበር በተሾመው በአባ ሔራክልዮስ ዘመን ነው፡፡ ይህም ማለት ፓትርያርክነት በክህነት መዓርግ ብልጫ የለውም ማለት ነው፡፡ ልክ በዲያቆንና በሊቀ ዲያቆን ወይም በጳጳስና በሊቀ ጳጳስ ወይም ደግሞ በቄስና በቆሞስ መካከል የሥልጣነ ክህነት ልዩነት እንደሌለው ሁሉ በጳጳስና በፓትርያርክም መካከል የሥልጣነ ክህነት መበላለጥ የለም፡፡ ይህም ማለት ዲያቆንን ሊቀ ዲያቆን በማድረግ ሒደት ድጋሚ የዲቁና ሥልጣን እንደማይሰጠው ሁሉ ወይም ድጋሚ ክህነት ቢሰጠው ውግዘት ያለበት እንደሆነው ሁሉ በፕትርክና ጊዜም የሚሰጠው ክህነት የጵጵስና ከሆነ ድጋሜ ክህነት ተሰጠው ስለሚያሰኝና በሁለተኛ ሀገረ ስብከትም ተሾመ የሚለውን ትርጉም የሚያመጣው ምሥጢር ይህ ስለሆነ ነው ጳጳስ ሀገረ ስብከቱን ትቶ ፓትርያርክ እንዳይሆን ቀኖናው የሚከለክለው፡፡ ይህ ከሆነ ፓትርያርክ ማለት የትክክል የበላይ ( Father among equals) ነው እንጂ የጳጳሳት ሁሉ ፍጹም የበላይ( father above equals) አይደለም፡፡ እንግዲህ ግብጾች እየጠበቁት ነው የሚባለው ይህ ነው፡፡

ሙሉውን እዚህ በመጫን ያንብቡ