አባ ገሪማ ዘመደራ
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረን በጉባኤ ኤፌሶን የተወገዘውን፣ በኋላም በጉባኤ ኬልቄዶን ጊዜ በመለካውያን አማካኝነት የመጣውን የሁለት አካል፣ ሁለት ባሕርይ የኑፋቄ እምነት አንቀበልም በማለታቸው በባዛንታይን ነገሥታት ስቃይ የጸናባቸው ተስዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳን መነኮሳት ከሶርያና ከታናሽ እስያ ተሰደው በአልአሜዳ ዘመነ መንግሥት በ፬፻፹ ዓ.ም ወደ አገራችን ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ በዘመኑ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትም ከአባቶቹ በወረሰው የደግነትና እንግዳ ተቀባይነት ባህሉ በፍቅር ተቀብሏቸዋል፡፡
እነዚህ ዘጠኙ ቅዱሳን በመላው ኢትዮጵያ ተዘዋውረው ወንጌልን ሰብከዋል፤ በወቅቱ ብሔራዊ ቋንቋ የነበረዉን ግእዝን በሚገባ አጥንተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስትና ከጽርዕ ቋንቋዎች ወደ ግእዝ ተርጕመዋል፡፡ እንደዚሁም ገዳማትንና አብያተ ክርስቲያናት አሳንጸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ከፈጸሟቸው መንፈሳውያን ተልእኮዎች፣ ካደረጓቸው ተአምራትና መልካም ሥራዎች አኳያ ቅዱሳን በሚል መዓርግ ትጠራቸዋለች፤ በስማቸውም ጽላት ቀርፃ በዓላቸውን ታከብርላቸዋለች፡፡ ዘጠኙ ቅዱሳን የሚባሉት አባቶች፡- አባ አሌፍ፣ አባ አረጋዊ፣ አባ አፍጼ፣ አባ ሊቃኖስ፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጉባ፣ አባ ይምአታ፣ አባ ጰንጠሌዎን እና አባ ጽሕማ ናቸው (የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ.ታ፣ አባ ጎርጎርዮስ ዘሸዋ፣ ፲፱፻፺፩ ዓ.ም፤ ገጽ ፳፫-፳፬)፡፡ በዛሬው ዝግጅታችንም ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የኾኑትን የአባ ገሪማን ታሪክ በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤
በሮም አገር መስፍንያኖስ የሚባል ንጉሥ ነበረ፤ ሚስቱም ሰፍንግያ ትባላለች፡፡ መካን ስለነበረች በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በመማጸን ልጅ እንዲሰጣት እግዚአብሔርን ስትለምን ከኖረች በኋላ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ይስሐቅ አለችው፡፡ የያን ጊዜው ይስሐቅ የኋላው አባ ገሪማ በመንፈሳዊ ሥርዓት ካደገ በኋላም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምሮ በዲቁና ማገልገል ጀመረ፡፡ ይስሐቅ ወላጅ አባቱ ሲሞትም በአባቱ ዙፋን ተተክቶ ለሰባት ዓመታት ሮምን በንጉሥነት ሲያስተዳድር ከቆየ በኋላ በዋሻ ይኖሩ የነበሩት አባ ጰንጠሌዎን ዘጾማዕት ‹‹ይስሐቅ ሆይ፣ ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዋቸውና የማያልፈዉን የክርስቶስን መንግሥት ትሻ ዘንድ ወደ እኔ ና›› ብለው መልእክት ላኩበት፡፡ መልእክቱ እንደ ደረሰውም መንግሥቱን ትቶ በሌሊት ወደ አባ ጰንጠሌዎን ሲሔድ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ በብርሃናውያን ክንፎቹ ተሸክሞ ዐሥር ወር የሚወስደዉን መንገድ በሦስት ሰዓታት አስጉዞ ከአባ ጰንጠሌዎን በዓት አደረሰው፡፡
አባ ይስሐቅ (አባ ገሪማ) በአባ ጰንጠሌዎን እጅ ከመነኰሱ በኋላ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ተጠምደው ቆዳቸው ከዐፅማቸው እስኪጣበቅ ድረስ ተጋድሎ ሲፈጸሙ ቆዩ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መደራ ሔደው በእግዚአብሔር ኃይል ድንቆችንና ተአምራትን እየያደረጉ፣ በሽተኞችን እየፈወሱ፣ አጋንንትን እያስወጡ ብዙ ዓመታት ኖሩ፡፡ ካደረጓቸው ተአምራት መካከልም በጠዋት ሥንዴ ዘርተው፣ በሠርክ ሰብስበው መሥዋዕት ካሳረጉ በኋላ በማግሥቱ ከግራር ዛፍ ላይ በሬዎችን አውጥተው ሥንዴዉን አበራይተው ሰባ ሰባት የእንቅብ መሥፈሪያ መሰብሰባቸው አንደኛው ሲኾን፤ በዓለት ላይ የተከሏት ወይን ወዲያው በቅላ፣ አብባ ፍሬ እንድታፈራ ማድረጋቸውና በወይኑም መሥዋዕት ማሳረጋቸው ደግሞ ሌላኛው ተአምር ነው፡፡ አባ ገሪማ መጽሐፍ እየጻፉ ሳሉ ፀሐይ ሊጠልቅ በተቃረበ ጊዜ ጸሎት አድርሰው ጽሕፈታቸዉን እስኪፈጽሙ ድረስ እንደ ኢያሱ ፀሐይን በቦታው እንዲቆም ማድረጋቸውም በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቧል፡፡ ከእጃቸው የወደቀው ብርዕ ወዲያው በቅሎ፣ አቈጥቍጦ እንደ አደገ፤ ምራቃቸዉን ትፍ ያሉበት ሥፍራም እስከ ዛሬ ድረስ ሕሙማንን እንደሚፈውስ መጸሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡
በአንዲት ዕለትም መቅኑናቸውን ተቀብለው ከመነኮሳት ጋር ሲሔዱ መንገድ ላይ ቤተ ክርስቲያን አግኝተው ሲጸልዩ ካህናቱ ቅዳሴ እንዲያሟሉላቸው ጠየቋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ምግብ በልተው ነበርና ‹‹አንችልም›› ሲሉ አባ ይስሐቅ ምግብ አልተመገቡም ነበርና መቅኑናቸዉን አስቀምጠው ቅዳሴውን አሟሉ፡፡ ባልንጀሮቻቸው ግን በልተው የቀደሱ መስሏቸው ወደ አባ ጰንጠሌዎን መጥተው ‹‹ቀሲስ ይስሐቅ ከበላ በኋላ ቀደሰ›› ብለው ከሰሷቸው፡፡ አባ ጰንጠሌዎንም አባ ይስሐቅ ሲመለሱ ‹‹የምጠይቅህ ምሥጢር ስላለኝ ሰዎችን ከአጠገብህ ገለል አድርጋቸው›› ሲሏቸው አባ ይስሐቅም ‹‹ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ ዕንጨቶችና ድንጋዮችም ገለል ይበሉ›› ብለው መለሱላቸው፡፡ ወዲያዉኑም ዕንጨቶችና ድንጋዮች አንድ ምዕራፍ ያህል ከቦታቸው ሸሹ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ጰንጠሌዎን ‹‹ኦ ወልድየ ይስሐቅ ገረምከኒ፤ ልጄ ይስሐቅ ሆይ! ገረምኸኝ›› እያሉ አደነቋቸው፡፡ አባ ገሪማን ሳያዉቁ የከሰሷቸው መነኮሳትም ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡ አባ ገሪማ ተብለው መጠራት የጀመሩትም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ‹‹ገሪማ ገረምከኒ አስኬማከኒ አልባቲ ሙስና፤ አባ ገሪማ አስገረምኸኝ፡፡ ለምንኵስናህም እንከን የለባትም›› በማለት ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ አመስግኗቸዋል፡፡
ከዚያም በትግራይ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ መደራ ከሚባል ቦታ ገብተው በዓት ሠርተው ለ፳፫ ዓመታት በትኅርምት ኖረው መልካም ተጋድሏቸውንና የቀና አካሔዳቸዉን በፈጸሙ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኔ ፲፯ ቀን ተገልጦ ስማቸውን የሚጠሩትን፣ መታሰቢያቸዉን የሚያደርጉትን፣ ገድላቸዉን የሚጽፉ፣ የሚያነቡና የሚተረጕሙትን፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹትንና የሚያገለግሉትን ስማቸውን በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍላቸው ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ አባ ገሪማም ይህንን ታላቅ ሀብት የሰጣቸዉን እግዚአብሔርን አመስግነው ከተደሰቱ በኋላ በብርሃን ሠረገላ ተነጥቀው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በተለይ በገዳማቸው በመደራ አባ ገሪማ የተሠወሩበት ሰኔ ፲፯ ቀን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን፤ በረከታቸዉም ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
ምንጭ፡-
- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፲፯ ቀን፡፡
- መዝገበ ታሪክ ክፍል ፪፣ መ/ር ኅሩይ ኤርምያስ፣ ገጽ ፺፱-፻፡፡