ጥር 11 ቀን 2005 ዓ.ም
በእንዳለ ደምስስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበረው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በድምቀት ተከበረ፡፡ ጥር10 ቀን 2005 ዓ.ም. ከዋዜማው ጀምሮ በተከናወነው የከተራ በዓል ታቦታት ከመንበራቸው በመውጣት ምእመናንን እየባረኩ በብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ቀሳውስት፤ በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ምእመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህር በማመራት በድምቀት ተከብሯል፡፡
በተለይም በአዲስ አበባ የአስራ አንድ አድባራትና ገዳማት ታቦታት በቀሳውስት ሽብሸባና ዝማሬ፤ በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝማሬ፤ በምእመናን እልልታ ታጅበው አመሻሽ ላይ ጃን ሜዳ ወደሚገኘው ጥምቀተ ባህር ደርሰዋል፡፡
በሌሎችም አካባቢዎች ተዘዋውረን እንደተመለከትነው በቅዱስ ራጉኤል፤ በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል፤ በደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖትና በጎላ ቅዱስ ሚካአል፤ በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም በቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድኋድ በነበረው ሥነ ሥርዓት ሃማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ ወጣቶች ታቦታቱ የሚያልፉበትን መንገድ ምንጣፍ በማንጠፍ፤ቄጤማ በመጎዝጎዝ ቀሳውስቱና መዘምራን በዝማሬ ፤ ምእመናን በሆታና በእልልታ አጅበው አቅራቢያቸው ወደሚገኘው ጥምቀተ ባህር አምርተዋል፡፡
ጃንሜዳ በነበረው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናል፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የአድባራትና ገዳማት ተወካዮች ፤ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ፤ በበአሉ ላይ ለመገኘት ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የአገር ጎብኚዎች፤ የተዘጋጀላቸውን ቦታ በመያዝ ሥነ ሥርዓቱን የተከታተሉ ሲሆን የ2005 ዓ.ም. ተረኛ የሆነው የገነተ ኢየሱስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንዲሁም የቤተክርስቲያኑ ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በየተራ ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡
በመቀጠልም እለቱን በማስመልከት በአቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ የደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ እንዲሁም የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እለቱን በማስመልከት ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በሰጡት ቃለ ምዕዳን “የእግዚአብሔር ቸርነት ሰፊ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልዑለ ባሕርይውን ዝቅ አድርጎ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ዮሐንስ ወዳለበት ቦታ ለመጠመቅ መጥቷል፡፡ ዮሐንስን አጥምቀኝ ማለቱ ለእኛ አብነት ለመሆንና ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ለመመሥረት ሲል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ዮሐንስ ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሔዶ አጥምቆት ቢሆን ኖሮ ምእመናን ቀሳውስቱን እቤታችን ድረስ መጥታችሁ አጥመቁን እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንሔድም ባሉ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሌላት እንዳትሆን ሥርዓትን ለማስተማር ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባሕር፤ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ “ጥምቀትን በየዓመቱ የምናከብረው እግዚአብሔርን ለማመስገን ነው፤ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ እርሱ ነውና፡፡ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የሰጠ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነውና ከሦስቱ አካል አንዱ አካል መሆኑን በአደባባይ የገለጠበት ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን በዓል ነው” በማለት እለቱን በማስመልከት የገለጹ ሲሆን በብፁዕነታቸው ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
ከበዓሉ ፍጻሜ በኋላ ካነጋርናቸው የውጪ ዜጎች መካከል፤ “ሚስተር ጆራ እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከስዊድን ነው፡፡ ክርስቲያን ነኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ የመጣሁት ከአስራ አራት አመት በፊት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለብዙ ጊዜያት ኢትዮጵያ መጥቼ የኢትዮጵያን የጥምቀት በዓል አክብሬያለሁ፡፡ ይህንን ሥነ ሥርዓት ባየሁ ቁጥር ሁልጊዜ እደነቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ፍፁም የተለየ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ያላት ሀገር ናት፡፡ በመላው ዓለም እንደዚህ ዓይነት ደማቅ ክብረ በዓል የሚያከብር የለም፡፡ በጣም የተለየ ነው፡፡ ይህንንም በማየቴ በጣም ተደስቻለሁ” በማለት ነበር የተሰማውን ስሜት የገለጸው፡፡
የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ምሽቱን በመቀጠል ትምህርት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የተሰጠ ሲሆን በእለቱ ተረኛ በሆኑት በገነተ ኢየሱስና በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላትም በተለያዩ ቋንቋዎች ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን የአቡነ ጎርጎርዮስ የአብነትና የዜማ መሳሪያዎች ማሰልጠኛ ክፍል አባለት በገና በመደርደር በዓሉን አድምቀውታል፡፡ በተጨማሪም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዜማዊ ድራማ በምሽቱ ለነበረው ምእመን በማቅረብ ሲያገለግሉ አምሽተዋል፡፡ሌሊቱንም በሊቃነ ጳጳሳት እየተመራ ጸሎቱ የቀጠለ ሲሆን የቅዳሴ ሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡
ከለሊቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እየተመራ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ ክቡር አቶ ታደሰ በንቲ፤ በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፤ አገር ጎብኚዎች፤ የየአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን በማስመለከት ጸሎተ ወንጌል በማድረስ መርሐ ግብሩ ተጀመረ፡፡ ጸበሉም ተባርኮ ለምእመናን በመርጨት የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ቀጠለ፡፡
በዋዜማው ያሬዳዊ ዝማሬ በማቅረብ የበዓሉ ድምቀት የነበሩት የገነተ ኢየሱስና ቅደስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዱሁም የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን የአጫበር ቆሜ ወረብም የመርሐ ግብሩ አንድ አካል ነበር፡፡
ዝማሬው እንደተጠናቀቀ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እለቱን በማስመልከት ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡ ባሰተላለፉት ትምህርትም “በዓላችን የሰላማችን ፤የአንድነታችን ምልክት ነው፡፡ መሠረቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ አደባባይ ተገኝቶ የእኛን ችግር ያስወገደበት ፤ ነፃነታችንን ያገኘንበት፤ የኀጢዓት ደብዳቤያችን የተቀደደበት፤ዮርዳኖስን ተሻግረን በአንድነት ድኅነት መንግስተ ሰማያትን ያየንበት እለት ነው፡፡ ዛሬ በአንድነት በዘመነ ፍዳ የተዘጋው ጆሯችን የአብ ድምጽ የሰማበት ቀን ነው፡፡” ብለዋል፡፡
በመቀጠል የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እየተስፋፋች ነው፡፡ በዓሉ እጅግ የደመቀ ነው፡፡ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ እጅግ የደመቀ በዓል ስላዘጋጃችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ” በማለት ደስታቸውን የገለጹ ሲሆን የግብጽ አምባሳደር፤ አንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ ክቡር አቶ ታደሰ በንቲ ንግግር አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርስ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምዕዳን “እኛ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ የምናከብረው የጥምቀት በዓል ብሔራዊ በዓላችን ነው፡፡ መገለጫችንም ነው፡፡ ድኅነተ ስጋ ወነፍስ ያገኘንበት ቀን በመሆኑ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል፡፡
በብፁዕነታቸው ቡራኬም የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡ በጥር 12 ከሚከብሩት የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ታቦታት በስተቀር ከየአድባራቱና ገዳማት ወደ ጥምቀተ ባሕር መጥተው የነበሩት ታቦታት በመጡበት ሁኔታ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ዘማርያን እንዲሁም በምዕመናን ታጅበው ምዕመናንንና አካባቢውን እየባረኩ በድምቀት እንደወጡ በድምቀት ተመልሰዋል፡፡
የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከበረ
በእንዳለ ደምስስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበረው የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በድምቀት ተከበረ፡፡ ጥር10 ቀን 2005 ዓ.ም. ከዋዜማው ጀምሮ በተከናወነው የከተራ በዓል ታቦታት ከመንበራቸው በመውጣት ምእመናንን እየባረኩ በብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ቀሳውስት፤ በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ምእመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህር በማመራት በድምቀት ተከብሯል፡፡
በተለይም በአዲስ አበባ የአስራ አንድ አድባራትና ገዳማት ታቦታት በቀሳውስት ሽብሸባና ዝማሬ፤ በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝማሬ፤ በምእመናን እልልታ ታጅበው አመሻሽ ላይ ጃን ሜዳ ወደሚገኘው ጥምቀተ ባህር ደርሰዋል፡፡
በሌሎችም አካባቢዎች ተዘዋውረን እንደተመለከትነው በቅዱስ ራጉኤል፤ በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል፤ በደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖትና በጎላ ቅዱስ ሚካአል፤ በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም በቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድኋድ በነበረው ሥነ ሥርዓት ሃማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ ወጣቶች ታቦታቱ የሚያልፉበትን መንገድ ምንጣፍ በማንጠፍ፤ ቄጤማ በመጎዝጎዝ ቀሳውስቱና መዘምራን በዝማሬ ፤ምእመናን በሆታና በእልልታ አጅበው አቅራቢያቸው ወደሚገኘው ጥምቀተ ባህር አምርተዋል፡፡
ጃንሜዳ በነበረው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናል፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የአድባራትና ገዳማት ተወካዮች ፤ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ፤ በበአሉ ላይ ለመገኘት ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የአገር ጎብኚዎች፤ የተዘጋጀላቸውን ቦታ በመያዝ ሥነ ሥርዓቱን የተከታተሉ ሲሆን የ2005 ዓ.ም. ተረኛ የሆነው የገነተ ኢየሱስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንዲሁም የቤተክርስቲያኑ ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በየተራ ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡
በመቀጠልም እለቱን በማስመልከት በአቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ የደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ እንዲሁም የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እለቱን በማስመልከት ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በሰጡት ቃለ ምዕዳን “የእግዚአብሔር ቸርነት ሰፊ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልዑለ ባሕርይውን ዝቅ አድርጎ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ዮሐንስ ወዳለበት ቦታ ለመጠመቅ መጥቷል፡፡ ዮሐንስን አጥምቀኝ ማለቱ ለእኛ አብነት ለመሆንና ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ለመመሥረት ሲል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ዮሐንስ ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሔዶ አጥምቆት ቢሆን ኖሮ ምእመናን ቀሳውስቱን እቤታችን ድረስ መጥታችሁ አጥመቁን እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንሔድም ባሉ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሌላት እንዳትሆን ሥርዓትን ለማስተማር ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባሕር፤ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ “ጥምቀትን በየዓመቱ የምናከብረው እግዚአብሔርን ለማመስገን ነው፤ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ እርሱ ነውና፡፡ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የሰጠ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነውና ከሦስቱ አካል አንዱ አካል መሆኑን በአደባባይ የገለጠበት ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን በዓል ነው” በማለት እለቱን በማስመልከት የገለጹ ሲሆን በብፁዕነታቸው ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
ከበዓሉ ፍጻሜ በኋላ ካነጋርናቸው የውጪ ዜጎች መካከል፤ “ሚስተር ጆራ እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከስዊድን ነው፡፡ ክርስቲያን ነኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ የመጣሁት ከአስራ አራት አመት በፊት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለብዙ ጊዜያት ኢትዮጵያ መጥቼ የኢትዮጵያን የጥምቀት በዓል አክብሬያለሁ፡፡ ይህንን ሥነ ሥርዓት ባየሁ ቁጥር ሁልጊዜ እደነቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ፍፁም የተለየ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ያላት ሀገር ናት፡፡ በመላው ዓለም እንደዚህ ዓይነት ደማቅ ክብረ በዓል የሚያከብር የለም፡፡ በጣም የተለየ ነው፡፡ ይህንንም በማየቴ በጣም ተደስቻለሁ” በማለት ነበር የተሰማውን ስሜት የገለጸው፡፡
የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ምሽቱን በመቀጠል ትምህርት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የተሰጠ ሲሆን በእለቱ ተረኛ በሆኑት በገነተ ኢየሱስና በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላትም በተለያዩ ቋንቋዎች ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን የአቡነ ጎርጎርዮስ የአብነትና የዜማ መሳሪያዎች ማሰልጠኛ ክፍል አባለት በገና በመደርደር በዓሉን አድምቀውታል፡፡ በተጨማሪም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዜማዊ ድራማ በምሽቱ ለነበረው ምእመን በማቅረብ ሲያገለግሉ አምሽተዋል፡፡
ሌሊቱንም በሊቃነ ጳጳሳት እየተመራ ጸሎቱ የቀጠለ ሲሆን የቅዳሴ ሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡