ማእከሉ Tewahedo/ተዋሕዶ /የተሰኘ የስልክ አፕ አዘጋጀ

 

ጥቅምት 22 ቀን 2006 ዓ.ም.

በዳዊት ደስታ

 

የማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን Tewahedo /ተዋሕዶ የተሰኘ የስልክ አፕ/ በአይቲ ክፍል አዘጋጀ፡፡

 

በማእከሉ የተዘጋጀው አፕ የኢትዮጵያና የጎርጎሮሳዊያንን የዘመን አቆጣጠር አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ የፈለጉትን ዓመት የበዓላት እና አጽዋማት ቀናት በቀላሉ ማየት ያስችላል፡፡ የየቀናቱን የቅዳሴ ምንባብ በመጽሐፈ ግጻዌ መሠረት ያሳያል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓት የጠበቁ መዝሙራት፣ ስብከቶች፣ ትረካዎች እና የሬዲዮ ስርጭቶች ለአድማጭ እንዲመቹ በዓይነት ከፋፍሎ ያቀርባል፡፡ አፑን በመጠቆም የቤተ ክርስቲያንን ድምጽ በየትኛውም ጊዜና ቦታ /በመንገድ ላይ ሥራዎችን እያከናወኑ፣ በእረፍትና በመዝናኛ ቦታዎች/ ሆነው በስልክ እነዚህን መረጃዎች እንደሚያገኙ ማእከሉ በላከልን መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

ሌላው በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መረጃ እንዲያገኙ የሚያግዝ ሲሆን በቀጣይ በሀገር ውስጥና በውጭ ላሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በቀላል መንገድ ቤተ ክርስቲያንን የሚያውቁበትና ትምህርቷን የሚከታተሉበት የቴክኖሎጂ ውጤቶች በስፋት እንደሚሠሩ ማእከሉ አሳውቋል፡፡