ሀገር ዓቀፍ ዐውደ ጥናት ተካሔደ
ጳጉሜን 3 ቀን 2006 ዓ.ም.
እንዳለ ደምስስ
በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የተዘጋጀው 6ኛው ሀገር ዓቀፍ ዐውደ ጥናት ጳጉሜን 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በማኅበሩ ሕንፃ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሔደ፡፡
ለአንድ ቀን በተዘጋጀው ዐውደ ጥናት 6 በምርምር ማእከሉ የተመረጡ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመቄት ወረዳ የደብረ ገነት ናዙኝ ማርያምና የአቡነ አሮን መንክራዊ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ፤ ኪነ ሕንፃ፤ ተንቀሳቃሽ ቅርስና ያሉበት ሁኔታ በሚል ርዕስ በዲያቆን ፀጋዬ እባበይ በዲላ ዩኒቨርስቲ የአርኪዮሎጂ መምህር የመጀመሪያውን ጥናት አቅርበዋል፡፡
የደብረ ገነት ናዙኝ ማርያምና የአቡነ አሮን መንክራዊ ገዳማት የተረሱ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት መሆናቸውን የገለጹት ጥናት አቅራቢው፤ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱ በከፍተኛ ጉዳት በአደጋ ውስጥ እንደሚገኙና በጥናት ላይ የተደገፈ ጥገና እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
ናዙኝ ማርያም ሁለተኛው የኢትዮጵያ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ሙሴ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንዳነጿት አብራርተው፤ ቤተ ክርስቲያኗ ለአክሱማውያን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መሠረት፤ አለበለዚያም ለኋለኞቹ ድልድይ እንደሆነች በጥናታቸው ዳስሰዋል፡፡በመቄት ወረዳ ብቻ ከ19 በላይ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ሲገኙ 13ቱ በአቡነ ሙሴ፤ ሁለቱ ደግሞ በአቡነ አሮን እንደታነጹ ገልጸዋል፡፡
ሁለተኛው ጥናት ሥነ ምኅዳርን ያማከለ የአካባቢ ጥበቃ እቅድ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ደን የሥነ ምኅዳር አገልግሎት ለማሳደግ በሚል ርዕስ በመስፍን ሳህሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ጥናት ተማሪ የቀረበ ሲሆን፤ የደብረ ሊባኖስን ገዳም ደን የሥነ ምኅዳር አገልግሎት ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንደሚገባቸው በጥናት አቅራቢው ተገልጿል፡፡ ቀድሞ የነበረው ተፈጥሯዊ ደን መመናመን፣ በተለያዩ ምክንያቶች መሬቱ እየተራቆተ መምጣቱ፤ የአፈሩ መሸርሸር፣ ለጐርፍ አደጋ ገዳሙ መጋለጡንና የአካባቢው የአየር ጸባይ መለዋወጥ ገዳሙን ለከፍተኛ አደጋ እንዳጋለጠው ጠቅሰዋል፡፡
በዲያቆን ሔኖክ ሐይሉ /MA/ ከማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የቀረበው 3ኛው ጥናት የተቀናጀ ሃይማኖታዊ እና የምክክር /counseling/ መርህ የካህናትን የማማከር ክሂል በማሳደግ ረገድ ያለው ውጤታማነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንጻር በሚል ርዕስ ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ቢጋር አዘጋጅተው አቅርበዋል፡፡
የንስሐ አባቶች ከንስሐ ልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ዘመኑን የዋጀ ዘመናዊ የሥነ ልቦና የማማከር አገልግሎት ሥልጠና ቢወስዱ ውጤታማ የቤተ ክርስቢተያንን አገልግሎት ለመተግበር እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል፡፡ የንስሃ ልጆቻቸው ኃጢአታቸውን ተናዝዘው፤ ንስሃ ገብተው፣ ቀኖናቸውን ተቀብለው ወደ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የመቅረብ ሂደት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በጓደኝነት፤ በትዳር፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ለሚገጥማቸው መሰናክል የንስሐ አባቶች የሥነ ልቦና የማማከር አገልግሎት ላይ እውቀት ኖሯቸው ከልጆቻቸው ምክክር ቢያደርጉ አገልግሎቱን የተሟላ ሊያደርገው እንደሚችል በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
በሦስቱም ጥናቶች ላይ ከተጋባዥ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ምሁራንና ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ከሰዓት በኋላ በቀጠለው ዐውደ ጥናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብራና መጻሕፍት ይዞታቸው፤ ያካተቷቸው ምሥጢራትና ከባሕር ማዶ ስለሚገኙት መጻሕፍት በሚል ርእስ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህር ጥናታቻውን አቅርበዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩ አስደናቂ የብራና መጻሕፍት መካከል ቀዳሚዎቹ የዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊቃውንት ለምስክርነት የሚጠቀሙባቸው ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ የብሉይ፤ የሐዲስ ኪዳን፣ የጸዋትወ ዜማ፣ የጸሎትና የምስጋና መጻሕፍት፣ መጻሕፍተ ሊቃውንት እና የሃይማኖት መጻሕፍት፣ መጻሕፍተ መነኮሳትና ሌሎችም መጻሕፍት በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር ወጥተው በውጭ ሀገራት እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ዓለማት ያሉ ተመራማሪዎች እነዚህ ሁሉ ጥበባት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዳሉ በማወቃቸው መጻሕፍቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሀገራችን እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ እንደ ምሳሌም ጀምስ ብሩስ /ከ1768-1773/ መጽሐፈ ሔኖክን እና በርካታ መጻሕፍትን ይዘው እንደወጡ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሠረት በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት 1082፣ በእንግሊዝ 850፣ በጀርመን 734፣ በጣሊያን 550 ወዘተ የብራና መጻሕፍት እንደሚገኙ በጥናታቸው አካትተዋል፡፡
በዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ሓላፊ የቀረበው ጥናት የአማርኛ ሥርዓተ ጽሕፈት በቤተ ክህነት ሊቃውንት እይታ በሚል ርዕስ ሲሆን፤ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የፊደላት ምንጫቸው ከፈጣሪ የተገኘ፣ ለሄኖስ በሰማይ ሰሌዳ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጸና፤ የግዕዝ ፊደላት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሥራ ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡ አማርኛን በተመለከተም ከግዕዙ የወሰዳቸው 26 አናባቢዎች እንዳሉ ሆነው፤ በኋላ 7 ከዚያም /ቨ/ን በመጨመር 34 እናት ፊደላት /consonants/፤ እንዲሁም 4 ደቃልው /labioverals/ /ኰ፣ጐ፣ቈ፣ኈ/ ፊደሎች አሉት:: 20 ፍንድቅ ፊደላትን /ሏ፣ ሟ፣ ሷ፣ ሯ…./ በመጨመር የአገልግሎት አድማሱን ማስፋቱን በጥናታቸው ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም መሠረት 278 ድምጽ ወካይ ፊደላት /characters/ አሉት፡፡
ከፊደላት ጋር የሚከሰቱ ችግሮችን አስመልክቶም በአማርኛ ፊደል ገበታ ላይ ተመሳሳይ ድምጽ ያላቸው ስለሚገኙ፤ በአጻጻፍ ረገድ በርካታ ልዩነቶች መኖራቸው፤ ራብዕ ድምጸት ያላቸው ከግእዙ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ፊደላት መኖራቸው፤ ሳድስና ሳልስን እያቀያየሩ መጠቀም፣ ደቃልውና ፍንድቅ ፈደላትን በዝርዝር የመጠቀም ዝንባሌ፣ በመሠረታዊ ቃሉ ላይ የሌለውን ቃል መጨመር፣ የአናባቢዎች ቅጥል አለመለየት ችግሩን ይበልጥ እንዳሰፋው ጠቁመዋል፡፡
ይህ ችግር በምሁራን ዘንድ ሞክሼ ቃላት ይቀነሱ፤ አይቀነሱ የሚለው ሐሳብ ዛሬም ድረስ እያከራከረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አማራጮችንም በተመለከተ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ በ1973 ዓ.ም. ተመሳሳይ ድምጽ ያላቸው ፊደሎች ከገበታው ላይ ተቀንሰው በአንድ ፊደል ብቻ ይወከሉ የሚል ሲሆን፣ የቤተ ክህነት ሊቃውንት አቋም ደግሞ ፊደላት የፈጣሪን ቸርነት የሚገልጹ እና ከእሱ የተገኙ ስለሆኑ ሁሉም ጠንቅቆ ሊጽፋቸው ይገባል እንጂ በፍጹም ሊቀነሱ አይገባም፡፡ ፊደላቱ በሙሉ መንፈሳዊ፣ ተፈጥሯዊና ሙያዊ ትርጓሜ ስላላቸው ያንን ያጣሉ በማለት ይገልጻሉ፡፡
አማርኛ እንዴት ሥርዓተ ጽሕፈቱን ይጠብቅ የሚለውን እንደመፍትሔ ሲያቀርቡም የአማርኛ ሥርዓተ ጽሕፈት መጠበቅ ይገባዋል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን እየተጠቀምንበት የሚገኘውን የግዕዙን ሥርዓተ ሰዋሰውና የትውስት ቃላት እንዳሉ መጠበቅ ሲቻል ነው ብለዋል፡፡
የአማርኛ ፊደል የሚጽፍ ሁሉ ፊደላቱን እንዲጠነቀቅ ማስተማር፣ በባለሙያ የተሠናዱ የሥርወ ቃላት መዝገበ ቃላት እና የሰዋሰው መጻሕፍትን ማዘጋጀት፣ ያሉት ፊደላት እስካሁን ድረስ ሲጻፉ ኖረዋል በዚህም እጅግ በርካታ መጻሕፍትና የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች ተመርተዋል፣ አገልግሎትም እየሰጡ ስለሚገኙ የፊደላቱ መብዛትና መመሳሰል አሳሳቢ እንዳልሆነና ሥርዓተ ጽሕፈቱን ከቅድመ ትምህርት ቤት ጀምሮ በየደረጃው ወጥነት ባለው መንገድ ማስተማር ወዘተ.. እንደመፍትሔ አቅርበዋል፡፡
የመጨረሻው ጥናት ክርስቲያናዊ ጾም በሰው ልጅ ጤና ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ጾም ከተለያዩ ሃይማኖቶች አንጻር በሚል በዲያቆን ታደሰ አለሙ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ FDS እና የሥነ ምግብ የዶክትሬት ተማሪ ቀርቧል፡፡ በቀረቡ ጥናቶች ላይ በርካታ ሐሳቦችን በማንሳት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመጨረሻም የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከሉ ከቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትና ከተመራማሪ ምሁራን የሚቀርቡለትን ጥናቶች ጠቃሚነታቸውን መርምሮ ለውይይት ማቅረቡን እንደሚቀጥል፤ አቅሙ ያላቸው ተመራማሪዎች ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ምርምሮችንና ጥናቶችን እንዲያቀርቡ ማእከሉ እንደሚያበረታታ የማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር አባተ መኩሪያው ገልጸዋል፡፡



ቤተ ክርስቲያን በዓላውያን ነገሥታት አሰቃቂ ስደት በደረሰባት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕት ዓመታት ውስጥ ከተነሱት የቤተ ክርስቲያን አበው መካከል አንዱ የሆነውና ለዛሬው የተጋድሎውን ዜና በአጭሩ የምንመለከተው ሰማዕት ቅዱስ ሰራባሞን ዘኒቅዩስ ነው። አባቱ አብርሃም ይባላል፤ አያቱ የቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ አጎት ሲሆን የተወለደው በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም ነው። ሲወለድ ወላጆቹ “ስምዖን” ብለው ስም አወጡለት፤ “ሰራባሞን” የጵጵስና ስሙ ነው። የዐረብኛ እና የግዕዝ መጻሕፍት “ሰራባሞን” ሲሉት፣ የቅብጥና እንግሊዝኛ ምንጮች ደግሞ “ሰራፓሞን” ብለው ይጠሩታል።
ማኅበረ ቅዱሳን በ2006 ዓ.ም. ከዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ግቢ ጉባኤያት በርካታ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ በዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ቆይታቸው ያስመዘገቡት ውጤት ከፍተኛ በመሆኑም በርካቶች የተሸለሙትን ዋንጫና ሜዳልያ በሥጦታ ለማኅበሩ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡
ደስታ ሲገልጹ “ይህ ውጤት በሀገራችን በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ታሪክ በጥቂቶች ብቻ ሊመዘገብ የሚችል ከፍተኛ ውጤት ነው፡፡ ካስመዘገበው ውጤት ይልቅ ደግሞ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ በሕይወቱ አንድ ጊዜ ብቻ ሊገጥመው የሚችለውን እድል ውድ ሥጦታ ለማኅበሩ መሥጠቱ አስደንቆኛል፡፡ ብዙዎቻችንንም ያስተማረ ነው፡፡ ወደፊትም በሕይወቱ የተሳካ ጊዜ አሳልፎ ለሌሎች አርአያ እንዲሆን እመኛለሁ” ብለዋል፡፡
ማእከል የፈቃደ እግዚእ ኮሌጅ ተመራቂዎቹ ዘውዴ ደሴና ከፍያለው ስመኝ ለማኅበሩ ማእከላት ሜዳልያቸውን አስረክበዋል፡፡ እንዲሁም ከሐረር የሜንሽን አግሮ ቴክኒካል ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ ሰብሳቢ የሆነው ቃል ኪዳን ዓለሙ ሜዳልያውን በማእከሉ በኩል ለኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን እንዲሰጥለት አበርክቷል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2006 ዓ.ም. በማኅበሩ ሕንፃ መሰብሰቢያ አዳራሽ የሀገር ውስጥና የውጭ ማእከላት፤ የወረዳ ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ተወካዮች፤ የማኅበሩ ሥራ አመራርና ሥራ አሥፈፃሚ አባላት፤ የማኅበሩ ልዩ ልዩ ክፍል ተጠሪዎች፤ ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት አካሄደ፡፡
የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፈዎች ከነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤ የጸሎት፤ የመርሐ ግብር ትውውቅና ማስገንዘቢያ በጠቅላላ ጉባኤው አዘጋጅ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ በዶክተር ዳኝነት ይመኑ ቀርቧል፡፡ የእጽበተ እግር መርሐ ግብርም ተከናውኗል፡፡
አገልግሎት ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማትን በማጠናከር ረገድ፤ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማጠናከር ከአህጉረ ስብከቶች ጋር እየተሠሩ ስለሚገኙ በርካታ ተግባራት ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያትን በማጠናከር ረገድ፤ የማኅበሩን ተቋማዊ አቅም ለማሳደግ እየተሠሩና በመሠራት ላይ የሚገኙ ሥራዎች፤ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሔዎችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው በሁለተኛ ቀን ውሎው ብፁዕ አቡነ ሰላማ የምሥራቅ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ የተገኙ ሲሆን፤ በሰጡት ቃለ ምእዳን “ያሰባሰባችሁ እግዚአብሔር ነው፤ በእናንተ ኃይል አልተሰባሰባችሁም፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር አስነስቷችኋልና በጉዟችሁ ፈተና ሊገጥማችሁ ይችላል፡፡ ፈተና ደግሞ ያለ ነው፤ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ ከሚወድህ ይልቅ የሚጠላህ ይጠቅምሃል እንዲሉ አባቶቻችን ካልተፈተኑ ክብር አይገኝም፡፡ በአገልግሎታችሁ እንደጸናችሁ ሳትበሳጩ ልትጓዙ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ማኅበሩን ይባርክ” ብለዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ስልታዊ እቅድ አጋማሽ ዘመን ግምገማ በማስመልከት ከጥር 2005 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2006 ዓ.ም. የተከናወኑትን ሥራዎች ተገምግመው ሓላፊነት በወሰደው አጥኒ ቡድን ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርበዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤውም ውይይት በማድረግ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት ቀጣይ አፈጻጸማችን ምን መምሰል እንደሚገባው ለማሳየት ቢሞከር፤ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከስትራቴጂክ እቅዱ አንጻር አስታርቆ ማስኬድ፤ የክብደት አሥራር ሥርዓቱን ግልጽ ማድረግ፤ ግምገማው ከስልታዊ እቅዱ ጋር በደንብ ቢታይ የሚሉና ሌሎችም ጠቃሚ ነጥቦች ከተካተቱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ የጥናት ቡድኑ ከጠቅላላ ጉባኤው በተሰጡት ሃሳቦች መሠረት የግምገማውን ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመደበኛ ሥራ አመራር ጉባኤ እንዲያቀርብ፤ ሥራ አመራር ጉባኤውም አጽድቆ በሚመለከታቸው አካላት ተግባራዊ እንዲደረግ እንዲያስተላልፍ ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡




በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ሐምሌ 26 እና 27 2006 ዓ.ም በጀርመን ካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ያሉበትን ሁኔታ፣ የማኅበረ ቅዱሳንን ታሪክ፣ አገልግሎትና በየጊዜው ያጋጠሙትን ችግሮች እንዲሁም የቤተክርስቲያን አገልግሎት በአውሮፓ በተለይም በጀርመን ያለበትን ሁኔታ፣ የአመሠራረት ታሪከ እና መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የሚያስቃኝ ዐውደ ርእይ ተካሔደ።
ዐውደ ርእዩ ነሐሴ 3 እና 4 ቀን 2006 ዓ.ም በኮሎኝ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ላይ በአጥቢያው ሰበካ ጉባኤና በሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሓላፊ ፈቃድ ለምእመናን ለመታየት በቅቷል። ዐውደ ርእዩን የከፈቱት ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ሲሆኑ በዕለቱ የቀረበው ዐውደ ርእይ ጥንታዊ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ያሉበትን ሁኔታ ምእመናን እንዲረዱት የሚያደርግ በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእዩን በዚህ ቤተክርስቲያን ማካሔዱ ያስደሰታቸው መሆኑን ተናግረዋል። በመቀጠልም የድጓ እና የአቋቋም መምህር የሆኑት እና ከካርል ስሩህ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የመጡት ሊቀ ጠበብት ተክሌ ሲራክ ስለአብነት ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት እና በአሁኑ ወቀት ተማሪዎች ስላሉባቸው ቸግሮች ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት አባቶች፣ ምእመናንና ማኅበራት ሊያደርጓቸው ይገባል ያሏቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች ጠቁመዋል::
በማኅበረ ቅዳሳን ሐዋሳ ማዕከል በተለያዩ አምስት ቋንቋዎች የሚያስተምሩ 33 ሰባኪያነ ወንጌል በሐዋሳ ካህናት ማሠልጠኛ ለአንድ ወር በቀንና በማታ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችን እና ሥልጠናዎችን ሲከታተሉ ቆይተው ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሲዳማ፣ የጌዲኦ፣ የአማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ሐምሌ 27 ቀን 2006 ዓ.ም በሐዋሳ ደብረ ምጥማቅ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በድምቀት አስመረቀ፡፡
ተመራቂ ሰልጣኞቹ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ባልተስፋፋባቸው የገጠር አብያተ ክርስቲያናት መካከል ከሲዳማ፣ ከጌዲኦ፣ ከአማሮና ከቡርጂ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ ሲሆን፤ በሲዳምኛ፤ በጌዲኦኛ፤በኩየርኛ፤በቡርጂኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በአንድ ወር ቆይታቸውም ከሚሰጣቸው መንፈሳዊ ትምህርት በተጨማሪ በስብከት ዘዴ ላይ ያተኮረ የልምምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡