ጾመ ፍልሰታ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም

ኢትዮጵያ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት አገር ናት፡፡ ሊቃውንትም ነቢያት የተነበዩትን ትንቢት የቆጠሩትን ሱባዔ መሠረት በማድረግ ቅድስት ድንግል ማርያም በኪደተ እግሯ ኢትዮጵያን መባረኳን ያስተምራሉ፡፡ «ነቢዩ ዕንባቆም የኢትዮጵያ ድኳኖች ሲጨነቁ ዐየሁ፤» ዕንባ. 3፡7 ብሎ የተናገረው ቃለ ትንቢት እመቤታችን የኢትዮጵያን አውራጃዎች ለመባረኳ ማስረጃ መሆኑን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይተረጉማሉ፤ ያመሠጥራሉ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእናቱ አሥራት አድርጐ በመሥጠቱ በእርሷ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን የነገረ ድኅነት ምሥጢር በመከናወኑ ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተለየ ፍቅር አለን፡፡ የአብነት /የቆሎ/ ተማሪዎች በትምህርት ዓለም ከአንዱ ወደሌላው እየተዘዋወሩ /የአብነት/ ትምህርት ሲማሩ በእንተ ስማ ለማርያም፤ ስለማርያም እያሉ፡፡ የእመቤታችን ስም ስንቅ ምግብ ሆኗቸው ይጠቀሙበታል፡፡ ግሼን ደብረ ከርቤ የልጇ ግማደ መስቀል ከከተመበት አምባም የሚጓዙ ምእመናን «አንድ እፍኝ ሽምብራ አልያዝኩም ከቤቴ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ» እያሉ በፍቅሯ ተማርከው ግብር ሰፍረው ዕጣን ቋጥረው ሱባዔ እየገቡ ይማፀኗታል፡፡ እርሷም ከልጇ ዘንድ ባገኘችው የመወደድ ሞገስ ምልጃቸውን በመቀበል ጸሎታችውን በማሣረግ የእናትነት ሥራ ሥትሠራላቸው ኖራለች፡፡ ዛሬም እየሠራች ነው፡፡ እመቤታችን ከልጇ ያገኘችውን /የተቀበለችውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ በዐራቱ ማእዘን «ሰዓሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኝልን» የማይላት የለም፡፡
በፍቅሯ ተደስተው በአማላጅነቷ ተማምነው «የእመቤቴ ፍቅሯ እንደ ሰማይ ክዋክብት፣ እንደምድር አሸዋ በዝቶልኝ፣ እንደ ልብስ ለብሼው፣ እንደምግብ ተመግቤው» እያሉ ተማጽነው ልመናቸው ሠምሮ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው፣ ቅዱስ ያሬድ ዘኢትዮጵያና አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ያዘጋጁላትን፣ አባ ጽጌ ድንግል የደረሱላትን የምስጋና መጻሕፍት በመድገም እመቤታችን ዘወትር መማጸን የቀደምት ኢትዮጵያውያንም የዛሬዎች ገዳማውያንና ምእመናን ዕለታዊ ግብር ነው፡፡
ጌታችን ለቀደሙት ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን አማላጅ እና እናት ሆኗ እንድታገለግል በገቢርም በነቢብም ከአደራ ቃል ጋር አስረክቧል፡፡ በገቢር በቃና ዘገሊላ የሰውን ችግር ፈጥና የምትረዳ ርኅርኅሪት እናት አማላጅ መሆኗን አሳይቷል፡፡ «ለዚሁም የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል» ብላ ያቀረበችው ቃለ ምልጃ ምስክር ነው፡፡ እናት ሆኗ እንድታጽናናቸው በቅዱስ ዮሐንስ በኩል ከእግረ መስቀሉ ስር ሰባቱን አጽራሐ መስቀል ሲያስተጋባ ቅዱስ ዮሐንስን ጠርቶ «እኖኋት እናትህ፤ ድንግል ማርያምን ጠርቶ እነሆ ልጅሽ» ዮሐ. 19፡26፡፡ በማለት እመቤታችን የእናት ሥራ ለሁሉም ቅዱሳን ሐዋርያት እንድትሠራላቸው ምእመናንም ልጅ እንዲሆኗት በማያሻማ ቃሉ ተናግሯል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በእናትነት ከተረከቧት ጊዜ ጀምረው ልጇ በዕርገት በአካለ ሥጋ ሲለይ እንደ ልጅ አገልግለዋታል፡፡ በቤታቸው አኑረዋታል፤ ብትሠወርባቸው ፈልገዋታል፡፡ ብትርቃቸው ናፍቀዋታል፡፡ እርሷም ሲጠሯት ታደምጣቸዋለች፣ ሲፈልጓት ትገኝላቸዋለች፡፡ ይኸውም የሆነው ልጇ በአዳምና በልጆቿ ኃጢአት ምክንያት የፈረደውን ለራሱም ያላስቀረውን ሥጋዊ ሞት እናቱ ብትቀምስ በእናትነት የተረከቧት ቅዱሳን ሐዋርያት መካነ ዕረፍት ለይተው በንጹሕ በፍታ ከፍነው በጌቴ ሰማኒ እንደቀበሯት ስለ እመቤታችን የተጻፉ መጻሕፍት በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡
የእመቤታችን ሥጋዊ ዕረፍት «ከመ ትንሣኤ ወልዳ» እንደ ልጇ ትንሣኤ ነውና ሙስና መቃብር ሳያገኛት ከሦስት ቀናት ሥጋዊ ዕረፍት በኋላ ከሞት ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ በዕለተ ቀብሯ ያልተገኘው ቅዱስ  ቶማስ ደመና ጠቅሶ በደመና ሰረገላ ሲመጣ ዕርገቷን ይረዳል፡፡ እማኝ ደግሞ የተከፈነችበትን በፍታ /ጨርቅ/ ይቀበላታል፡፡ ለቅዱስ ቶማስ የተገለጠው የዕረፍቷ ምሥጢር ሌሎች ቅዱሳን ሐዋርያት እንዲገለጥላቸው ቢማጸኑ እመቤታችን ዳግም ተገልጻላቸው፡፡ ትንሣኤዋን ለማየት በቅተዋል፡፡
እነዚህ በቅድስናቸው የተመሠከረላቸው ቅዱሳን እመቤታችንን በሁለት ሱባዔ ማግኘታቸውን መሠረት በማድረግ በቤተ ክርስቲያናችን ከነሐሴ 1-16 በየዓመቱ አንደሚጾም ይታወቃል፡፡ ይህ እመቤታችንን የምንማጸንበት ጾመ ፍልሰታ ቤተ ክርስቲያናችን መፍትሄ የምትፈልግባቸውን ጉዳዮች ለእመቤታችን የምታቀርብበት ሰዓት ነው ብለን እናምናለን፡፡
ኢትዮጵያ የእመቤታችን አሥራት አገር ስትሆን እመቤታችን ለኢትዮጵያውያን እናት መሆኗ እየተነገረ ለምን በፈተና ውስጥ አለፍን? ልጇ በአሥራት ኢትዮጵያን የሰጠባት ሀገር አባቶች ማስፈራሪያ ሲደርስባቸው መንፈሳዊነት /ኀይለ መንሳዊ/ ተዘንግቶ ሥጋዊ ጥበብ በቤተ ክርስቲያን መድረክ ሲታይ ምን ይባላል? «እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ» ማቴ. 24፡15፡፡ የተባለው ቀን ደርሶ ይሆንን?
ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዓመታት ለገጠማት ችግር መፍትሔ እመቤታችን እጅ ላይ አለ ብለን እናምናለን፡፡ እመቤታችን ብትሠወርባቸው አባቶች ሱባዔ ገብተው እንዳገኟት የፍቅር እናት ናትና ፍቅር አንድነት እንድትሰጠን እርሷን መማጸን፤ የዶኪማስን ጓዳ እንደሞላች የጐደለውን እንድትሞላ ውዳሴዋን እየደገሙ ድንግልን መማጸን ያስፈልጋል፡፡
በውዳሴ ማርያም፣ በጸሎተ ማርያም የሚመካ በጉልበቱ አይመካም፡፡ ጊዜ ረዳኝ ብሎ በወገኖቹ ላይ ግፍ አይፈጽምም፡፡ ስለዚህ በዚህ በወርኀ ጾም እመቤታችን ምልጃዋ ከአገራችን፣ ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር እንዲሆን በሱባዔ እንማጸናት፡፡
በጾመ ፍልሰታ ከሊሂቅ እስከ ደቂቅ በማስቀደስ፣ በጾምና በጸሎት ሁለቱን ሳምንታት እንደሚያሳልፉት ይታወቃል፡፡ በሱባዔው የቤተ ክርስቲያናችን ችግሮች የሚወገድበት ምእመናን በበረከት የሚጐበኙበት ቅድስና የሚሰፍንበት መንፈሳዊነት ትልቅ ከበሬታ የሚገኝበት ጾም እንዲሆን ሁሉም ምእመን መትጋት አለበት፡፡
ሁለቱ ሳምንታት በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እየተገኘን ምሕላ የምናደርስበት፣ የተጣላነውን ይቅር ለእግዚአብሔር፣ የበደልነውን የምንክስበት ጾም መሆን አለበት፡፡
ቀናቱን እየቆጠርን እስከተወሰነው ሰዓት ብቻ መጾም ብቻ በሕይወታችን መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ እመቤታችን የአገራችን አሥራት የሁላችን እናት በመሆኗ የእናትነት ሥራ እንድትሠራልን በሚገባ ልንማጸናት ይገባል እንጂ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ሱባዔ ብለን ውዳሴ ማርያም በደገመ አፋችን ሰው የምናማ በሰው ሕይወት ገብተን የምንፈተፍት ከሆነ እመቤታችንን አናውቃትም፡ እመቤታችንም አታውቀንም፡፡ ስለዚህ ጾመ ፍልሰታን እስኪ ሁላችን ኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ ልጆች ድንግልን በአንድ ድምፅ እንጥራት፡፡
የእመቤታችንን ጾመ ፍልሰታ፤ እንደ ብርሃን ተስፋ በማድረግ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚተጉ አባቶች እና ምእመናን ለተሰደዱ፣ ለተራቡ፣ በፈተና ውስጥ ለሚገኙ ይማጸኑ እንላለን፡፡ ውዳሴ ማርያሙ፤ ሰዓታቱ ጨለማን ተገን አድርጐ ከሚቃጣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ድርብ ኀይል አለው፤ እስኪ ለቅድስና፣ ለንጽሕና ለመንፈሳዊነት ቅድሚያ እንስጥና የእግዚአብሔርን ብድራት እንጠብቅ፡፡ ጾመ ፍልሰታ መንፈሳዊነት፣ እውነት፣ ቅድስና የጠራ አሠራር፣ በቤተ ክርስቲያን የሚሰፍንበት እንዲሆን እንመኛለን፡፡
 
                                                             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ …/ዮሐ.3-19/

ብርሃን ወደ ዓለም ስለመጣ፣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነው፡፡ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፡፡ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጐ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፡፡ /ዮሐ.3-19/

ለዚህ እትም መልእክታችን መግቢያ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ከእውነት ይልቅ ሐሰትን የመረጡ ሰዎችን ማንነት ለመግለጥ የተናገረውን አምላካዊ ቃል መርጠናል፡፡ ብርሃን እውነት፤ ብርሃን የጠራ አሠራር፤ ብርሃን የዘመድ አሠራር ባላንጣ፤ ብርሃን የሕገ ሲኖዶስ መከበር፤ ብርሃን የቤተ ክርስቲያን ልዕልና መገለጫ ነው፡፡ ጨለማ ግን የብርሃን ተቃራኒ ነው፡፡

ካሳለፍነው ወርኃ ግንቦት መጋመሻ ጀምሮ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን የአስተዳደር ችግር በሠለጠነ መንገድ፣ በመወያየት፣ በመተማመን ለመፍታት ሁሉም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ባለፈው እትም ከመንበረ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት የወጣውን መረጃ መሠረት በማድረግ አሰንብበናል፡፡

በቤተ ክርስቲያን አባቶች ዘንድ ተፈርቶ ይፋ ሳይወጣ ለዘመናት ሲጉላላ የቆየው የአስተዳደር ችግር፣ የቤተ ዘመድ አሠራር፣ ሙስና፣ ተገቢውን ሰው በተገቢ ቦታ አለመመደብ፣ የተዝረከረከ የሒሳብ አሠራር እና ተገቢ ያልሆነ የሀብት አጠቃቀም ችግር ይፋ ወጥቶ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ በቃለ ጉባዔ ሰፍሮ መቀመጡ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ዕድገት አንድ እርምጃ ነው፡፡

«አትስረቅ፣ መመለጃ አትቀበል፣ እውነቱን እውነት በሉ» የተባሉት አምላካውያት ቃላት መመሪያዋ በሆነ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሠናይ ይልቅ እኩይ ሥነ ምግባሮች በቅለው ሐዋርያዊ ጉዞዋን በፍጥነት እንዳይካሔድ የኋሊት ሲጓተት እያዩ «ሆድ ይፍጀው» ብለው ማለፍ ቀርቶ ብፁዓን አባቶች ችግሮችን አፍረጥርጠው መነጋገራቸው ያስደስታል፡፡

በቤተ ክርስቲያን አባቶች መኖራቸው የታመነባቸው ችግሮች እንዲፈቱ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሥራ አስፈጻሚ አባላት መመረጣቸውም ይታወሳል፡፡ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጣቸው ሓላፊነት መሠረት የቤተ ክርስቲያን ችግር ለመፍታት ሲንቀሳቀሱ በተፈጠረው አለመግባባት ችግሩ ወርኃ ሐምሌ ላይ ደርሷል፡፡ እኛም የተፈጠረው ችግር ከምንም በላይ የቤተ ክርስቲያን ክብር ባስቀደመ መልኩ እንዲፈታ ሐሳባችን ሰንዝረናል፡፡ በመግቢያችን እንደጠቀስነው «ብርሃን ወደ ዓለም ስለመጣ» የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር ይፈታ ስለተባለ፤ ሥራቸው ክፉ የነበረው «የዘመድና የብልሹ አሠራር ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር መፍታት ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ወደ ብርሃን አንመጣም አሉ፡፡ ጨለማን ተገን አድርገው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ቤት መዝጊያ ሰበሩ፣ ፎከሩ፣ አስፈራሩ፣ ዛቱ፣ ቆይ ትኖራላችሁ አሉ፡፡ ዛቻና የድብደባ ሙከራ የተፈጸመባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንደገለጹት ድርጊቱ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ዝቅ ያደረገና አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው «ክፉን የሚያደርግ ብርሃንን ይጠላልና ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም» እንደተባለው  ክፉ የሚያደርጉ ቤተ ክርስቲያንን የሚመዘብሩ ሰዎች ብርሃንን ስለሚፈሩ ነው፡፡

ብርሃን እውነትን የሚፈሩ የጨለማው ቡድን አካላት፤ «በሊህ እገሪሆሙ ለኪኢወ ደም፤ ደም ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው» «ሐሳር ወቅጥቃጤ ውስተ ፍኖቶሙ፤ ጥፋት ጉስቁልና በመንገዳቸው አለ፤ የሰላም መንገድ አያውቋትምና እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም» ሲል ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት የገለጣቸው ዓይነት ናቸው፡፡ መዝ. 13-6፡፡ በኃይል፣ በዛቻና በማስፈራሪያ የቤተ ክርስቲያን ችግር ስለማይፈታ የእነዚህ ቡድኖች ዓላማ ቤተ ክርስቲያን ወደተሳ ሳተ ጐዳና የሚመራ ነው፡፡ የጨለማ ቡድን ዘመቻ ከቤተ ክርስቲያን ልጆች አልፎ ወደ ብፁዓን አባቶች አምባ መደረሱ እጅግ ያሳዝናል፡፡

ሕገ ሲኖዶስ እንዳይከበር እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የጨለማው ቡድን አባላት» እውነት ተድበስብሶ እንዳይወጣ የሚያደርጉት እኩይ ጥረት ከሠመረ ቤተ ክርስቲያን «ቤትየሰ ትሰመይ ቤተ ጸሎት አንትሙሰ ረሰይክምዋ በአተ ፈያት ወሠረቅት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ትባላላች እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ» አደረጋችኋት፡፡ የሚለው ዕጣ ይገጥማታል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከጨለማ አስተዳደር ወደ ብርሃን እንድትወጣ «እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጐ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል» እንደተባለ የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር እንዲፈታ ጨለማ የሆኑ ወደ እውነት እና ወደ ብርሃን መምጣት አለባቸው፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተመረጠው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሥራውን እንዲቀጥል እገዳ እንደተነሳለት ከመንበረ ፓትርያርክ የተሰጠው መግለጫ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ የመረጣቸውና ሓላፊነት የተሰጣቸው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አሉ የተባሉ ችግሮች እንዲፈቱ ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን ሓላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ያለው ብልሹ አሠራር መፈታት ከምእመናን ጀምሮ እስከ መንግሥት አካላት እንደ ሚደግፉት እናምናለን፡፡

ችግሩን ለመፍታት ሐሳብ የሰጡ ብፁዓን አባቶችን የማሸማቀቅ አሳፋሪ ተግባር ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ስለተፈጸመባቸው መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይገባል፡፡ የብፁዓን አባቶች ዓላማ መንፈሳዊ ዓላማ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ችግር ከመፍታት ውጪ የተለየ አንዳች ዓላማ እንደሌላቸው ከሰጡት ሐሳብ መረዳት ይቻላል፡፡

በመሆኑም ምንጊዜም የሕዝብን በሕይወት የመኖር መብት የሚያስከብረው መንግሥት ጨለማን ተገን አድርገው የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ነፃነት ደፍረው በብፁዓን አባቶቻችን ላይ የመዝጊያ ሰበራ፣ የድብደባ ሙከራ የፈጸሙ አካላትን በቁጥጥር ስር አውሎ የእርምት ርምጃ መወሰድ አለበት፡፡

ከሀገር ሀገር ዞረው «በእንተ ስማ ለማርያም» ብለው የተማሩ አባቶች ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ በእግርና በፈረስ ተዘዋውሮ ቤተ ክርስቲያን ያገለገሉ «ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሕገ ሲኖዶስ ይክበር» በማለታቸው ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ የመዝጊያ ሰበራ ሲፈጸምባቸው መሰማት ቤተ ክርስቲያን ወደየት እየተጓዘች ነው ያሰኛል፡፡

በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች መከራ መቀበል የአባቶች ሕይወት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል በቅዱስ መሰዊያው ፊት ቃል ኪዳን የገቡት አባቶቻችን ስለቤተክርስቲያን ክብር ዛቻና እንግልት ቢፈጸምባቸው እንኳ መከራውን በአኮቴት ተቀብለው ሓላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በሰላማዊ መንገድ በሠለጠነ መንገድ ችግሮች እንዲፈቱ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ መወያየት የጀመሩትን ከፍጻሜ ማድረስ አለባቸው፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ የሰበካ ጉባኤ አካላት፣ በአጠቃላይ ምእመናን ምን ጊዜም እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን በማዕበል የምትገፋ መሆኗን ተረድተው በተፈጠረው ችግር መረበሽ የለባቸውም፡፡ የተፈጠረው የአስተዳደር ችግር በጠራና አስተማማኝ በሆነ መንገድ እስከሚፈታ ድረስ በመረጋጋት፣ በጾም፣ በጸሎት መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡

«የገበያ ግርግር ለቀጣፊ ያመቻል» እንዲሉ የተፈጠረውን ችግር መነሻ በማድረግ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ምዝበራ፣ ዘረፋ፣ ሕገ ወጥ ድርጊት እንዳይስፋፋ ምእመናን የቤተ ክርስቲያን ንብረት ንብረታቸው፤ ሕልውናዋ ሕልውናቸው ስለሆነ ቤተ ክርስቲያናቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡

 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የቅርሶች ዘረፋን ለመከላከል

የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የረጅም ዘመን ታሪክና የበርካታ ውድና ምትክ የሌላቸው እንዲሁም ማንኛውም መጠን ያለው ገንዘብ የማይተካቸው ታሪካዊና ዓለማቀፋዊ እውቅና ያላቸው ቅርሶች ባለቤት ነች፡፡ እነዚህ ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶቻችን ከቀደምት አባቶቻችንና አያቶቻችን የወረሰናቸው እኛም በተራችን ጠብቀንና ተንከባክበን ለቤተክርስቲያን ዕድገትና ለሀገራዊ ልማት እያዋልን ለመጪው ትውልድ የምናስተላልፋቸው መተኪያ የሌላቸው እሴቶቻችን ናቸው፡፡ ቅርሶች ያለፈውን፣ ነባሩንና ተተኪውን ትውልድ የሚያገናኙ የኅብረ ትውልድ ድልድዮች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእነዚህ ንዋይ ሊተምነው የማይችል ቅርሶች ግምጃ ቤት መሆኗ እና እኛም ልጆቿ የዚህ ታሪክ ተረካቢዎች በመሆናቸን መንፈሳዊ ፍስሐ ይሰማናል፡፡

ስለ አገራችን ቅርስ ሲነሣ በአብዛኛው በቅርስነት የተመዘገቡትና የሚጎበኙት የቤተክርስቲያናችን ቅርሶች ናቸው፡፡ ይህም ሁኔታ የኢትዮጵያ ታሪክና የቤተክርስቲያን ታሪክ የማይነጣጠሉ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች አድርጓቸዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የሀገሪቱ ዜጎች ስለ ቅርስ ጥበቃ የሚኖረን ግንዛቤ ለታሪካችን ካለን አመለካከት የሚነሳ ነው፡፡ አንድ ሕዝብ ቅርስ አለው ስንል ታሪክ አለው፣ ክብር አለው፣ ተደማጭነት እንዲያገኝ የሚያደርግ ማሰረጃ አለው ማለት ስለሆነ ለቅርስ የሚደረግ እንክብካቤና ጥበቃ በታሪክ መዘክርነት ለሚቀርብ ማስረጃ የሚደረግ ጥበቃ መሆኑን ተገንዝበን ለቅርስ ጥበቃው ከግል ፍላጎትና እምነት ነፃ ሆነን ሀገራዊና ሕዝባዊ አስተያየትን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡
 
ይሁን እንጂ ዛሬ ብዙ ሃይማኖታዊ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቅርስ ሀብት እንዳለን ስንገልጽ፣ በርካታ ቅርሶቻችንን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ማጣታችን መዘንጋት የለብንም፡፡ እንዲሁም እያየን ነው፡፡ ይልቁንም አሁን በእጃችን ካለው የቅርስ ሀብታችን አብዛኛዎቹ አንድም ባሳለፍናቸው የእርስ በእርስ ግጭቶችና ያለተቋረጡ የባዕድ ወራሪዎችን ለመከላከል በተደረጉ ጦርነቶች ወድመዋል ተመዝብረዋል፡፡ ከዚያም ያለፈው በራሳችን ሰዎች፣ በወራሪ ኃይሎች፣ በጎብኚዎች፣ በተመራማሪነት ስምና በልዩ ልዩ ዲኘሎማሲያዊ መብቶች ሽፋን በየጊዜው በሚመጡ ግለሰቦች ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡
 
በጦርነት የወደመውን የቅርስ ሀብታችንን «የፈሰሰ ውሃ» እንዲሉ አበው መፍትሔ ባናገኝለትም እንኳ እጅግ ድንቅ የሆኑ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ እንዲሁም ባሕላዊ ቅርሶቻችን ታሪኩ ታሪካቸው ባሕሉ ባሕላቸው፤ ሆኖ በማይዘክሩለት ባዕዳን ሀገራት እጅ ተከማችተው ይገኛሉ፡፡ ለእነዚህ አካላት የገቢ ምንጭ ሆነዋል እነዚህን ቅርሶች ስለ ሀገሩ ባሕል፣ ታሪክና ሃይማኖት እንዲሁም ወግ ለማጥናት የፈለገ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ ከፍተኛ ገንዘብ  በማውጣት ያባቶቹን ሀብትና የእሱነቱን መገለጫ የታሪክ ቅርስ መረጃዎችን ለማግኘት በባዕዳን ሙዚየሞችና ቤተ መጻሕፍት እየዞረ የመንከራተቱ መራር እውነት በብዙ ወንድሞቻችን አንደበት በየጊዜው የሚነገር ነው፡፡ ይሄን እውነት እነርሱ እንኳን ብንለው ችግሩ ከቶ ሊያስረሳን አይችልም፡፡
 
ለዚህም አብነቶችን ማንሣት ይቻላል፡፡ በእንግሊዝ ሠራዊት የተዘረፈውን አንድን የመጾር መስቀል ፎቶ ግራፍ ለማንሳት ብቻ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ገንዘብ ቅርሱን በያዘው ክፍል መጠየቁ እንዲሁም የቅዱስ ላሊበላ አፍሮ አይገባ መስቀላችንን ከቤልጅም በከፍተኛ ዋጋ መግዛታችን የቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን ናቸው፡፡
 
ይህ አልበቃ ብሎ ቅርሶቻችን ያለ አግባብ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር እየወጡ በአሜሪካና አውሮፖ በመረጃ መረቦች አማካ ኝነት በግልጽ እየተቸበቸቡ ይገኛሉ፡፡ ዛሬም ቅርሶች የሚገኙባቸው አድባራት፣ ገዳማትና አብያት ክርስቲያናት፣ ተቋማት መካነ ቅርሶች መደፈራቸውና በውስጣቸው የሚገኙ ብርቅና ድንቅ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶች መዘረፋቸው አልተገታም፡፡
 
ቅርሶች ለጊዜያዊ አፍቅሮተ ንዋይ ሲባል ያለ አግባብ የመዘረፋቸው የመበላሽታቸውና የመባከናቸው መርዶ አልቆመም፡፡ ከዚህ አንፃር ይህ ወቅት ለእኛ ለአሁን ትውልድ ወጣቶች፣ ለቤተክርስቲያን አባቶችና ለመንግሥት ሁለት ሊታለፉ የማይችሉ ፈተናዎች ለምርጫ ከፊት ለፊታችን ተደቅነዋል፡፡ እነዚህ ምርጫዎች አንድም ቅርሳችንን ሕገ ወጥ ዝርፊያ ማስቆም፣ ያለ አግባብ የተዘረፉትን ለማስመለስ በተጀመረው ጥረት ሳይታክቱና ሳይሰለቹ መቀጠልና በእጃችን ያሉትን ጠብቆና ተንከባክቦ ለቤተክርስቲያን ዕድገትና ለሀገር ልማት እያመቻቹ ለተተኪው ትውልድ በማስተለለፍ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መውጣት፤ ወይም አሁን በአብዛኞቻችን እየተደረገ እንዳለው ዘረፋና ጥፋቱን በግዴለሽነት በመመልከት ድሀ ደካማና መረጃ አልባ ሀገር እና ቤተክርስቲያን ለትውልድ ጥሎ በማለፍ የታሪክና ትውልድ ተወቃሽ መሆን ናቸው፡፡
 
ያለ ማወላወል ለማንኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ አገልጋይ ካህናት እንዲሁም ሀገር ወዳድ እና ቅን ዜጋ ምርጫ ሊሆን የሚገባውና የሚሆነው የመጀመሪያው ነው፡፡ በመጀመሪያው ምርጫችን መሠረት ከመንግሥት ለቅርስ እንክብካቤ የሚጠበቀው ሚና ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብና ለማልማት በርካታ ሕጐችን፣ አዋጆችንና ፖሊሰዎችን ማውጣቱንና ዓለም ዓቀፋዊ እና አህጉራዊ የቅርስ ስምምነቶችን መፈራረሙ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ በሕገ መንግሥቱ አንቀጸ 91 ላይ ስለ ቅርስ መደንገጉ የቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ መውጣቱ፣ የባሕል ፖሊሲ መቀረጹ እና ሀገሪቱ ቅርሱን አስመልክቶ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን መፈራረሟ የሚያሳየው መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ነው፡፡
 
ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መፈራረምና ሕጎችንና አዋጆችን ቢወጡም አሁን የሚታየውን የቅርስ ዘረፋ ቀጥሏል፡፡ በቅርስ ዘረፋ ተሰማርተው ለተያዙት ሰዎች የሚሰጠውም ቅጣት ለሌሎች አስተማሪ ባለመሆኑም ለዘራፊዎች መበራከት ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡ የቅርስ ዘረፋን አስመልክቶ ቀድሞም ሆነ አሁን  ተሻሽለው የወጡት ሕጎችና አዋጆች ግን ጉዳዩን አስመልክተው ያወጡት የቅጣት ውሳኔ ከፍተኛ ነበር፡፡ በቅርስ ጉዳይ ላይ በወጡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚደረጉት ቅርሶች ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር በሕገ ወጥ መንገድ እንዳይተላለፍ ለመከላከል በማሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያም እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በመፈራረሟ በስምምነቱ  ተጠቃሚ ልትሆን ይገባት ነበር፡፡ ሀገራችን ከውጪ ወደ ውስጥ የምታስገባው ቅርስ ባይኖረም፤ ከእርሷ ግን ብዙ ቅርሶች በሕገ ወጥ መንገድ የተዘረፋት ቅርሶች ወደ የሀገራችው እንዳመለሱ ያዛል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ እና የተዘረፍብን ቅርሶችን ወደ ሀገር ለማስመለስ እየተደረገ ያለው ጥረት ጥሩ ቢሆንም በውጪ ካለን የቅርስ ብዛት አንፃር ሲመዘን ከቁጥር የሚገባ ባለመሆኑ በዚህ ረገድ የሕገ አስፈጻሚ አካላት ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ቅርሶችን አስመልክቶ የወጡት ሕጎች በትክክል እንዲፈጸሙ ገቢራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
 
የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች የእምነቱ ተከታዮች የቅርሰ ዘረፋን ሕገ ወጥ ዝውውርን ይበልጥ የመንከባ ከብና የመጠበቅ ግዴታ እንዳለብን ልናውቅ ይገባል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 2ዐ9/1992 ዓ.ም ላይ የቅርስ ባለቤት የሆነ ሰው በእጅ የሚገኘውን ቅርስ ተገቢውን  ጠበቃና እንክብካቤ ካላደረገ… ለቅርሱ አጠባበቅ የሚወጡ ደንቦችንና መመሪያዎችን ያላከበረ እንደሆነ ወይም በይዞታው እንዲጠቀምበት በተሰጠው መሬት ላይ የሚገኝ ቅርስ በሚገባ የማይጠብቅ ከሆነ ወይም ቅርሱን የሚያሰተላልፍ ሰው የቅርሱን ማስተላለፍ ለባለስልጣኑ /ለመንግሥት/ ያላሳወቀ እንደሆነ… ይህን አስመልክቶ የወጣውን አዋጅ የማያስፈጸም ከሆነ እሰከ ስድስት ወር እስራት እንደሚቀጣና ወይም እስከ 1 ሺሕ አምስት መቶ ብር እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡
 
በየጊዜው ትኩረት እየተሰጣቸው አዋጆች ገቢራዊ እንዲሆኑ  የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ክትትል ማድረግ አለባቸው፡፡ በቅድሚያ የአገራችን ሕዝብ ሁሉ የኢትዮጵያ መገለጫና የቱሪስት መስህብ የሆኑ ቅርሶች የአገራቸው ሀብት በመሆናቸው በባዕዳን ሲዘረፉ ሲቃጠሉ በቸልታ መመልከት የለባቸውም፡፡ ምእመናንም ቀደምት አበው ቀን በጽሕፈት ሌሊት  በጸሎት ተገተው ያዘጋጇቸው መጻሕፍት የገዳሟቸው ገዳማት ያካበቷቸው ንዋያተ ቅድሳት የእምነታቸው መገለጫ በመሆናቸው በእኔነት ስሜት ሊጠብቋቸው፤ ተዘርፈው ሲሄዱ ጥብቅና ሊቆሙላቸው ይገባል፡፡

የቅርስ ባለቤት የሆነችው ቅድስት ቤተክርስቲያን በየገዳማቱና አድባራቱ የሚገኙ ቅርሶቿን ሥርዐት ባለው መንገድ መመዝገ ብና ስለ ቅርሶቿ ተጨባጭ የሆነ መረጃ መስጠት አለባት፡፡ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋርም በመቀናጀት ቅርሶች ሲዘረፉ፣ ሲቃጠሉ በፍጥነት ለሕግ አስፈጻሚ አካላት ተገቢን እገዛ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ ይኸውም ባለቤት በማጣት በግለሰቦችና በእግዚቢትነት ተይዞ የሚገኝ ቅርሶቿን ለማስመለሰ ይረዳታል፡፡
 
በአጠቃላይ ቅርሶች የሀገራችን ሀብታት የቀደሙት አበው ሥልጣኔ መገለጫ ዛሬ ላይ ቁጨ ብለን የትላንትን የምናይባቸው የክብራችን ገላጭ የእኛነታችን መለያ አሻራ በመሆናቸው በኅብረት እንክብካቤ ልናደርግላቸውና ጥብቅና ልንቆምላቸው ይገባል፡፡
የሕግ አስፈጻሚ አካላት ቢሆኑም በቅርስ ዙሪያ የወጡ ሕጎችንና አዋጆችን በትክክል መፈጸማቸውን ይከታተል፤ የቅርስ ዘረፋን እና ሕገወጥ ዝውውርን ለመግታት ሕጎች በትክክል ሊፈጸሙ ይገባል፡፡

 

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር