ማኅበረ ቅዱሳን በአዲስ ምዕራፍ!
ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ የመተዳደሪያ ደንቡ ጸድቆ ከተሰጠው ጀምሮ አገልግሎቱን የተሻለ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ ርእይዩን ከግብ ለማድረስ በሀገር ውስጥና በልዩ ልዩ የውጭ ሀገራት የአገልግሎት መዋቅርን ዘርግቶ ተተኪ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በማፍራት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ወጣቶች በሥነ ምግባር እንዲታነጹ በማድረግ ሀገርና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በዕውቀታቸው፣ በገንዘባቸውና በሙያቸው የሚያገለግሉ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እያፈራ ይገኛል። ይህንን መጠነ ሰፊ አገልግሎት ለማሳለጥና በሚፈለገው ልክ አገልግሎቱን ለማስሄድ ሁለተኛ ዙር ጽሕፈት ቤት መገንባት ግድ ሆኖበታል። ማኅበሩ እየተጠቀመበት ያለው ሕንጻ ዕለት ዕለት እያደገ ከመጣው የማኅበሩ የአገልግሎት መስፋት አንጻር ሲነጻጸር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በአሁኑ ሰዓት የሁለተኛ ዙር ጽሕፈት ቤት ግንባታ በይፋ ጀምሯል።