ሕፃኑ ሰማዕት

ጥር ፲፬፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ግብዝና ደካማ የሆነው የሰውን ሥጋ አሸንፎ፣ መከራን ተቀብሎ፣ ችግርን ተቋቁሞ፣ ፈተናን አልፎ መንፈሳዊ ሕይወትን ለመኖርና ክርስቲያን ለመሆን የሚደረገው ትግል እራሱን የቻለ ተጋድሎ እንደሚያስፈልገው የታወቀ ነው፡፡ እውነተኛ ለሆነው የክርስትና እምነተና ኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት የሚከፈለው መሥዋዕትም የተለየ ስፍራ አለው፡፡

እሳት ሰንሰለቱን ሳይፈሩ፣ እራሳቸውን እጅግ ለበዛ ሥቃይ አሳልፈው የሚሰጡ ሰማዕታት የተለየ ክብር አላቸው፡፡ ፍጹም በሆነው የክርስቶስ ፍቅር ዓለም የሚያመጣባቸውን መከራ ለመቀበል በሙሉ ፈቃደኝነት ቆርጠው ተነሥተው ከአላውያን ነገሥታት አልያም ከመኳንንቶች ደግሞም ከከሃድያን ደርሰው በግልጽ ለእውነተኛው ጌታ በመመስከር እውነተኛ ምስክሮች ይሆናሉ፡፡

ከሁሉም የሚደንቀው ደግሞ ከእሳት ምድጃ ቢጥሏቸው፣ ከፈላ ውኃ ውስጥ ቢጨምሯቸው፣ ለአንበሳ እና አውሬ መብል አሳልፈው ቢሰጧቸው እምነታቸው ምንም አለመቀየሩ ነው፡፡ ለሚያምኑበትና ለሚመኩበት ኃይል ብርታት የሚሆን፣ መሐሪና ይቅር ባይ አምላካችን  ጻድቃንን ቅዱሳንን ሰማዕታት ለጠላት አሳልፎ የማይሰጥ ነውና መላእክቱን ልኮ ውኃውን እንደ ውርጭ የሚያቀዘቅዝ፣ እሳቱን ውኃ የሚያደርግ፣ የተራቡ አራዊት የቅዱሳንን እግርና እጅ እንዲልሱ የሚያደርግ ነው፡፡ ዳግመኛም ለልዩ ልዩ ለሥቃይ አሳልፈው ቢሰጧቸውም የክብር ባለቤት እራሱ ከሰማየ ሰማያት ከእልፍ አላፋት መላእክት ጋር ወርዶ እንዳጽናናቸው እንዲሁም እንዳጸናቸው ገድላቸው ይናገራል፡፡ (ገድለ ቅዱሳን)

በከበረች ሐምሌ ፲፱ ቀን የጌታችን ዕጹብ ድንቅ ሥራ በተገለጠባት ዕለት የሚያስደንቅ ገድል ያደረገ የሦስት ዓመቱ ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስ ገድልም ፍጹም ድንቅ ነው፡፡ በዚህች ቀን በፈላ የጋን ውኃ ውስጥ ቅዱሳኑ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ውኃውም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ይህንም ያደገረው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

የዘመኑ የአረማዊው መኰንን የእለእስክንድሮስ ወታደሮች ከሮም ወደ ወደ ተርሴስ ከእናቱ ጋር ሸሽቶ የገባውን ሕፃኑ ሰማዕት ይዘው ፈጣሪን ክዶ ከጣዖት እንዲሰግዱ በዓይነቱ ቢያሠቃዩትም ስላልተቀበላቸው በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲሆን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡

ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ሕፃኑ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብሎ ጥር ፲፭ ቀን አንገቱ ተቆርጦ የሰማዕትነት አክሊል ተቀብሏል፡፡ በተመሳሳይም እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ሰማዕት ሆናለች፡፡ ግሩምና ድንቅ የሆነው የሰማዕታት ገድል የሁላችንም አስተማሪና አስማሪ ነው፡፡ በእነርሱ ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት የእኛ ኃጢአት ይስተሠረይልናልና፡፡

የቅዱሳኑ ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ጥር፣ ፲፭ ቀን

 

 

 

የቃና ዘገሊላ ሰርግ

ጥር፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ዲያቆን ወልዳይ መረሳ

በአዲስ ኪዳን የዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጠቀሰው ዶኪማስ ሰርግ ባደረገበት ወቅት ድንግል ማርያምና ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የታደሙባት (ዮሐ ፪፥፩-፲፩ )፣ እንዲሁም የሐዋርያው ናትናኤል የትውልድ ሀገር ገሊላ ናት (ዮሐ ፳፩፥፪ )። ጌታ በዚሁ ስፍራ ሆኖ በመናገር በቅፍርናሆም ታሞ የነበረውን የሹሙን ልጅ ከሕመሙ ፈውሶታል። (ዮሐ ፬፥፵፫-፶፬ )

ቤተ ክርስቲያን በዓላትን በቅዱሳን ስም፣ በዕለቱ በተፈጸመው ድርጊት ወይም በቦታ ስም ትሰይማለች። ይህም “በአዳሪው ስም ማደሪያው ይሰየማል” እንደሚባለው እንጂ፣ ተአምራቱን የፈጸመው ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ቤተ ክርስቲያንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትን ተከትላ ጌታ ለገለጠበት ስፍራ ክብርና ቅድስና በመስጠት በዓሉን በቦታው ስም “ቃና ዘገሊላ” ብላ ታከብራለች። (ዘጸ.፫፥፭፣ ፪ ጴጥ. ፩፥፲፰) ምንም እንኳን በቃና የተደረገው ተአምር ጌታ ተጠምቆ በቆሮንቶስ ገዳም ከተፈተነ በኋላ በየካቲት ወር የተፈጸመ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ግን “የውኃውን በዓል ከውኃ በዓል ጋር” በማዛመድ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከጥምቀት ማግስት እንዲከበር አድርገዋል።

በዚህም መሠረት የቃና ዘገሊላ በዓል ከዘጠኙ የጌታ ንኡሳን በዓላት አንዱ ሆኖ ከዋዜማው ጀምሮ በዝማሬና በቅዳሴ በድምቀት ይከበራል። በዕለቱ የሚቀርቡት ንባባትና ዜማዎችም በቃና ዘገሊላ የተደረገውን ተአምርና ምሥጢር የሚዘክሩ ናቸው። ቤተ ክርስቲያናችን በዛሬው ዕለት የምታቀርባቸው ዝማሬዎችና የቅዱስ መጽሐፍ ንባባት በአንድ ዋና ነጥብ ላይ ያተኩራሉ፤ ይህም በቃና ዘገሊላ የተከናወነው የመጀመሪያው ተአምርና በውስጡ የያዘው ጥልቅ ምሥጢር ነው። ይህ ታሪክ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፪ ከቁጥር ፩-፲፩ ላይ በስፋት ተመዝግቦ ይገኛል። ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የዚህን ወንጌል ትርጓሜ እጅግ ረቂቅና ሰፊ በሆነ ምሥጢር ቢተነትኑትም፣ እኛ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ አቅማችን መጠን እነርሱ ካስተማሩት ጥቂቱን እንደሚከተለው በአጭሩ እንመለከታለን።

 የቃና ዘገሊላ ሰርግ

በሦስተኛው ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበር፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ እናቱ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። እርሱም “አንቺ ሴት፣ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት። እናቱም አገልጋዮቹን “እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። በዚያም እንደ አይሁድ ሥርዓት ለመንጻት የሚሆኑ ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ። ኢየሱስም “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው፤ እስከ አፋቸውም ሞሏቸው። “አሁን ቀድታችሁ ለሰርግ አዘጋጁ (ለአሳላፊው) ስጡት” አላቸው።አሳላፊውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደመጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። አሳላፊውም ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን ወይን ያቀርባል፣ ከጠጡ በኋላ ግን የተለወጠውን (መካከለኛውን) ያቀርባል፤ አንተ ግን መልካሙን ወይን እስከ አሁን አቆይተሃል” አለው።

ኢየሱስ ይህን የመጀመርያ ተአምር በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ። (ዮሐ ፪፥፩-፲፩) በዚህ ቅዱስ ሰርግ ላይ የጌታ ትሕትና ተገልጦበታል፤ ክብሩ ታውቋል፤ የድንግል ማርያም ርኅራኄና አማላጅነት ታይቷል፤ የጋብቻ (የምሥጢረ ተክሊል) ክብርም በተግባር ትምህርቱ ተሰጥቶበታል።

የጌታ ትሕትና መገለጥ

ክርስቶስ በቤተልሔም በከብቶች ግርግም ተወልዶ፣ በዮርዳኖስም በባሪያውና በአገልጋዩ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ የትሕትና አባት መሆኑ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው። አሁን ደግሞ “ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ (ድሀ አደረገ)” ተብሎ እንደተጻፈው፤ (ፊል ፪፥፯) በፍጥረታቱና በባሪያዎቹ ሠርግ ላይ እንደ ዋና የክብር እንግዳ ሳይሆን እንደ ማንኛውም እንግዳ ተገኘ። ያውም የወይን ጠጅ እንኳ ለታዳሚዎቻቸው በማያበቃቸው በድሆች የሰርግ ቤት ተገኘ።

ማንንም ሳይንቅ ከባሪያዎቹ ጋር እንደ አንዱ ታዳሚ ተቀመጠ። ያንን ታላቅ ተአምርም “እዩልኝ ስሙልኝ” ሳይል፣ ወይን በሚቀመጥበት በዚያ በጓዳ ጋኖቹ ዘንድ አደረገው። ይህም በሉቃስ ወንጌል (፲፬፥፯-፲፩) ላይ “አንድ ሰው ለሰርግ ቢጠራህ ከሁሉ በላይ ባለው የክብር ቦታ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የሚከበር ሰው ተጠርቶ ከሆነ፣ አንተንና እርሱን የጠራው መጥቶ ‘ለዚህ ሰው ስፍራ ልቀቅለት’ ይልሃል፤ ያን ጊዜም እያፈርህ ወደ መጨረሻው ስፍራ ትወርዳለህ። ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ የጠራህ ሰው መጥቶ ‘ወዳጄ ሆይ፣ ወደ ላይ ከፍ በል’ ባለው ጊዜ፣ አብረውህ በተቀመጡት ፊት ክብር ይሆንልሃል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይላል” ብሎ ራሱ ያስተማረውን ትምህርት በተግባር የፈጸመበት አርአያነት ነው። በዚህም እኛ እንዴት በትሕትና፣ ለሰው ታይታ ሳይሆን ከልብ ማገልገል እንዳለብን አስተማረን።

ክርስቶስ ማንነቱን መግለጡ

በቃና ሰርግ ቤት የተደረገው ተአምር የአዳዲስ አማኞችንና የሐዋርያትን እምነት ለማጽናትም የተደረገ በመሆኑ፣ ወንጌላዊው ዮሐንስ “ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” ይለናል። እመቤታችን ድንግል ማርያምም ጌታችን ማንነቱ የሚገለጥበት ጊዜ መድረሱን አውቃ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። ጌታችንም “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” ማለቱ፣ በወቅቱ ያልነበረው ይሁዳ መጥቶ ተአምሩን እንዲያይና ለወደፊት “እኔ በሌለሁበት ተአምር አድርጎ ለየኝ” የሚል ምክንያት እንዳይኖረው ለማድረግ እንደሆነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተርጒሞታል።

የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ ክብርና ርኅራኄ ወንጌላዊው ሲገለጽ ቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩን ሲጀምር “የኢየሱስ እናት በዚያ ነበረች” በማለት ክብሯን ይገልጻል። ወንጌላዊው በየትኛውም ስፍራ ስሟን በቀጥታ ከመጥራት ይልቅ “እናቱ” ወይም “የኢየሱስ እናት” እያለ ይጠራታል፤ ይህም ሐዋርያት ለእመቤታችን ያላቸውን ታላቅ አክብሮትና ድንግል ማርያም ያላትን የአምላክ እናትነት ጸጋ የሚያስረዳ ነው። ጌታችንም እናቱን “አንቺ ሴት” ማለቱ፣ አዳም ሔዋንን “ከአጥንቴ አጥንት ከሥጋዬ ሥጋ ናት” (ዘፍ ፪፥፳፫) እንዳላት ሁሉ፣ እርሷም የጌታ የሥጋዌው (የሰው የመሆኑ) ምክንያት መሆኗን ለማረጋገጥ ነው።

ድንግል ማርያም የወይኑ ማለቅ በሰርገኞቹ ላይ የሚያመጣውን ኃፍረት ተረድታ፣ እነርሱ ሳይጨነቁና ሳይጠይቋት ቀድማ በመለመን ርኅራኄዋን ገልጻለች። ጌታችንም የእናቱን ልመና ሰምቶ ውኃውን ወደ ወይን በመለወጥ ተአምሩን ፈጸመ።

ምሥጢረ ተክሊል

ጋብቻ ቅዱስ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ክርስቶስ ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በሰርጉ ላይ ተገኝቷል። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጸች ናት። ይህ ምሥጢርም በእግዚአብሔር ፊት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ የሚፈጸም መሆኑን ያስረዳል። ጌታችን በሰርግ ቤት እመቤታችንን “አንቺ ሴት” ብሎ መጥራቱ አዳም ሔዋንን “ከአጥንቴ አጥንት፣ ከሥጋዬ ሥጋ ናት” (ዘፍ ፪፥፳፫) እንዳላት ሁሉ፣ ስለ ሥጋዌው (ሰው ስለመሆኑ) የሚጠቁም ነው። ውኃውን ወደ ወይን መለወጡም የከበረ ደሙ ምሳሌ ነው። ስለሆነም ምሥጢረ ተክሊል በሥጋውና በደሙ የሚከብርና አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም ቅዱስ ሥርዓት ነው።

የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር በረከቱንና ረድኤቱን ያብዛልን። የአምላክ እናት ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ አትለየን።

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

 

 

 

ለፈጣሪ በበጎ ፈቃድ መገዛት ይገባል!

ጥር ፭፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ሰው በራሱ ፈቃድ በጎ አልያም በክፉ ሐሳብና ምኞት መጥፎ ሊሆን ይችላል፡፡ የአዳም ዘር ጥንተ ተፈጥሮውን ዐውቆና ተረድቶ በድንቅ ሥራው ለፈጠረው አምላክ ተገዢ የመሆን ፈቃድም የራሱ ነው፡፡ በውዴታ ብቻ ሳይሆን በግዴታም ለፈጣሪ መገዛት እንዳለብን ቅዱሱ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡

ታዲያ ዓለምን ሁሉ ከእነ ጓዟ ለፈጠረ አልፋና ዖሜጋ፣ ኤልሻዳይ ለሆነው እግዚአብሔር መገዛት በፍቅር መሆን ሲገባው ብዙኃኑ ሰው ግን አሻፈረኝ ብሏል፡፡ ይባስ ብሎም በራሱ ፈቃድ ያለ እግዚአብሔር አምልኮ ለመኖር መወሰኑ ሳያንስ ዓለምን መግዛት እንደሚቻለው እያሰበ ነው፡፡ ሰው በራሱ ጥበብ ተጉዞ ጨረቃን አልያም ሌሎች በሰማያት ላይ ያሉ ድንቅ ፍጥረታት ላይ መድረስ ቢችልም ወደ ላይ የመምጠቅ ኃይሉ የተገደበ እንደሆነ ግን ማመን አዳግቶታል፡፡ ምንም መሣሪያ ቢሠራ፣ ምንም ተጠብቦ ወደ ሰማይ መጓዝ ቢችል እርሱ ባወቀ እንጂ የትም መድረስ አንችልም፡፡ ‹‹እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፣ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን አወርድሃለሁ›› ተብሎ እንደተጻፈ (አብድ. ፩፥፬) ጥበብም ከእግዚአብሔር በመሆኑ እርሱን ባለመፍራት የሚደረግ ነገር ማንም ምንም ማድረግ አይቻለውም፡፡

አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ዛሬም ያለ ወደ ፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ አምላክ የሆነ ማንም ሊያሸንፈውም የማይችል ነው፡፡ በቸርነቱ ብዛት ዓለምን ሲፈጥርም መልካም በመሆኑ ነው፡፡ ሰው ግን አምላክነትን ሽቶ ክሕደት ፈጸመ፤ ኃጢአት ሠራ፤ ከክብሩም ተዋርዶ መከራና ሥቃይ፣ ረኀብ፣ ጥም፣ እንግልት፣ ልፋት፣ ገዓር፣ ኀሣር ወዳለባት ምድር ተጣለ፡፡ በዚህም ሆኖ ሰው አምላኩን መበደል አላቆመም፡፡ የተፈቀደለትን ትቶ ያልተቀደለትን፣ የታዘዘውን ሳይፈጽም ያልታዘዘውን፣ የማይገባውን በመሻትም ፈጣሪውን መዳፈር ቀጠለ፡፡ ኃጢአት መሥራቱ ሳያንስ አምላክ ላይ መድረስ፣ ወደ ላይ መጥቆ ፈጣሪን ተዳፈረ፡፡

በኖኅ ዘመን የተፈጸመው የባቢሎናውያን ድርጊትም የዚህ ማሳያ ነው፡፡ በክፉ ምክራቸው ተነሣሥተው ፈጣሪ ወዳለበት ለመድረስ የሰናዖር ግንብን ሠሩ፡፡ መጽሐፉም እንደሚነግረን  ‹‹እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም አለ። ‹‹ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።›› (ዘፍ.፲፩፥፩-፱)

ታሪኩን በመቀጠል ስናነበውም አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ የሰናዖርን ግንብ አፍርሶ ባቢሎናውያኑን በትኗቸዋል፡፡ የቅድስት ሥላሴ አንድነታቸውና ሦስትነታቸው የተገለጸበት ጥር ሰባት ቀን የከበረ በዓል እንደመሆኑ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡

ዓለማችን በጎርፍ እየተጥለቀለቀች፣ በመሬት መንቀጥቀጥ እየራደች፣ በሰደድ እሳት እየተለበለበች ያለችው የአዳም ዘር አምላኩን ክዶ፣ ሀብት፣ ሥልጣንና ኃይል በመሻት በኃጢአት ሰንሰለት ታስሮ የጠላት ዲያብሎስ ተገዢ በመሆኑ ነው፡፡ ወደ ላይ እየመጠቅን ሲመለስን ወደ ታች እየወረድን እንደሆነ ማን በነገረን? በሰው ሠራሽ ሥሪት የሚንቀሳቀሱ  ቁሳዊ አካላትን በመሥራት የአምላክን ክቡር ፍጡር ሰውን ለመተካትና ፈጣሪ ለመሆን፣ ከዚያም ባሻገር የተፈጥሮ ሂደትን በሚያዛባ መልኩ ዘር የመተካትን ሂደት ሰው ሠራሽ የማድረግ ጥረት አምላክነትን የመሻት ነው፡፡ ይህም የዳረገን ለከፋ ነገር መሆኑ በግልጽ የሚታይ ሆኗል፡፡ እኛ የማይገባንን ለማግኘት ስንጥር የሚገባንን ግን ተነጠቅን፡፡ ሰው የመሆን መብታችንን አጥተናል፡፡ በነጻ፣ ያለ ክፍያ ድንቅ ተደርገን ተሠርተን እኛ ግን በውድ ዋጋ ቁሳዊ አካልን ሸምተን የሰውን ሥራ ሁሉ እንዲሠራልን ተመኘን፡፡ የራሳችንን ክብር የሚያሳጣን ነገር መሆኑን ግን ለማወቅ ዓይነ ልቡናችን ታወረ፡፡

ጥበበኛ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪትም ሆነ በሕገ ወንጌል የገለጠልን ምሥጠር ድንቅ ሥራውን ብቻ ሳይሆን በክብር ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያሰጥ ነው፡፡ ከሁሉም አስቀድሞ ግን እርሱን መፍራት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው›› እንዲል፡፡ (ምሳሌ ፩፥፯) ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ ክብሩን አላወቀም፡፡ ስለዚህ የጥንተ ተፈጥሮአችንን አስታውሰን፣ የተፈጠርንበትን ምክንያትን ዐውቀንና ተድረተን፣ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር በበጎ ፈቃድ በመገዛት ልንኖር ይገባል፡፡

አምላካችን ቸርነቱንና ምሕረቱን ያብዛልን፤ ከበዓሉ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!

 

 

በዓለ ግዝረት

ጥር ፭፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

በዘመነ ብሉይ ግዝረት የተጀመረው በአባታችን አብርሃም ነበር፤ በዚያን ጊዜ የነበሩ ሕዘበ እግዚአብሔር ከአሕዛብ የሚለዩበትና ክብር የሚያገኙበት ሕግ መጽሐፊያዊ ግዝረት ነበር፡፡ ያም እንደ ጥምቀት ይሆንላቸው ነበርና ነው፡፡ (ዘሌ.፲፪፥፫)

የከበረ ወንጌል እንደገለጸው በዘመነ ሐዲስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በስምንተኛው ቀን ግዝረትን ፈጽሟል፡፡ “ጌታ ሰው መሆኑ ሕገ ኦሪትን ሊሽር ባለመሆኑ ሥርዓተ ግዘረትን ፈጽሞልናል፡፡” (መዝገበ ታሪክ ገጽ ፻፵፩)

በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል እንደተጻፈው “ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ወደ ግዘረት ቤት ወሰደችው፤ ገራዡ ምላጩን ይዞ ቀረበ፤ ነገር ግን ምላጩ እጁ ላይ ሳላ ውኃ ሆኖ ፈሰሰ። ጌታችንም በተአምራት የተገረዘ ሆኖ ተገኘ፡፡”  (ሉቃ.፪፥፳፩-፳፫)

የአምላካችን ድንቅ ሥራ ተነግሮ አያልቅምና በከበረች በጥር ፮ ቀን ሥርዓተ ግዝረትን የፈጸመልን ጌታ እኛም እርሱን አብነት አድርገን ወንድ ልጆችን በስምንት ቀናቸው እንድናስገርዝ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን ከጌታችን ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱና የመጀመሪያው የሆነውን የተቀደሰ ቀን ታከብረዋለች፡፡

ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!

 

 

 

 

ኖላዊ ኄር

ታኅሣሥ ፳፯፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ቸርነትና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ትዕግሥቱ የበዛ፣ የዓለም ቤዛ፣ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ቸር እረኛችን ነው፡፡ “አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ” በማለት እንደ ነገረን ቸር ጠባቂያችን ነው፡፡ (ዮሐ.፲፥፲፩)

የሰው ዘርም መከራና ፍዳ ከመላባት ጸአር ገአር ከበዛባት ከዚህች ምስቅልቅል እና አስከፊ ምድር በሰላም ተለይቶ የነፍስን ዕረፍት የሚያገኘው እንዲሁም መንግሥተ ሰማያትን የሚወርሰው በእውነተኛው የበጎች እረኛ እንደሆነ እራሱ ባለቤቱ ነግሮናል፡፡ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።

….መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ” እንዲል፡፡ (ዮሐ.፲፥፯-፲፮)

ቸሩ መድኃኔዓለም ከዚህ ዓለም የኃጢአት ማዕበል ስጥመት ጠብቆ፣ ካለንበት ችግርና መከራ አውጥቶ፣ ወደ ሰላማዊ መንገድ መርቶ፣ በሃይማኖት አጽንቶ፣ የነፍስን ዕረፍት፣ መንፈሳዊ ፍሬ እንድናፈራ፣ ርስተ መንግሥተ ሰማያት እንድወርስ ይርዳን፤ አሜን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር!

 

‹‹እኔ ሰላማዊ ነኝ!›› (መዝ.፻፲፱፥፯)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ታኅሣሥ ፳፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ሰላም  “ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ ዕርቅ፣ ፍቅር፣ አንድነት” ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፰፻፷፮) አንድ ሰው ሰላም አለው ሲባል ጤነኛ እና ለሰዎች ፍቅር ያለው ኅብረትን አንድነትን የሚወድ ማለት ነው፡፡ ሰላም ለሰዎች ሁሉ አስፈላጊና መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮችም አንዱ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ለማከናወን ቅድሚያ ሰላም መሆን አስፈላጊ ነው፤ በሕይወታችን ደስተኛ ሆነን ለመኖር፣ አእምሮአችንን ከጭንቀት ነጻ ለማድረግ፣ ለሰዎች መልካም ነገርን ለማሰብ እኛም ደስተኛ እና ጤነኛ ለመሆን ሰላማዊ መሆን አለብን፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ እንዲህ ይመክረናል፤ ‹‹…ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ…፡፡›› (ሮሜ ፲፪፥፲፰) ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር እኛ የሰላም ሰዎች ነገሮችን በትዕግሥት የምናልፍ፣ ለሰዎች መልካም የምናስብ ልንሆን ይገባል፡፡

ውድ ክርስቲያኖች! የሰላም መገኛው የት ነው?! ለመግቢያ ያህል ሰላም ስለሚለው ኃይለ ቃል ገለጽን እንጂ ርእሰ ጉዳዩን የመረጥነው ስለ ሰላም ምንነት በስፋት ለማብራራት አይደለም፤ ሰላማዊ ሰው ስለመሆን  እንጂ! በርእሳችን ላይ ‹‹እንዘ ሰላማዊ አነ፤ እኔ ሰላማዊ ነኝ›› የሚለውን ኃይለ ቃል የተናረው ልብ አምላክ ንጉሥ ዳዊት ነው፤ መተርጉማን አበው ነቢዩ ንጉሥ ዳዊት ይህንን ደስ የሚል ከመንፈስ ፍሬዎች መካከል አንዱ የሆነውን ቃል፤  ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት›› (ገላ.፭፥፳፪) መናገሩ ለምን እንደሆነ ሲያመሠጥሩ ከሕይወት ታሪኩ ክፍል አንዱን ይተርካሉ፤ ነገሩ እንዲህ ነው!

ንጉሥ ዳዊት በነቢዩ ሳሙኤል አማካኝነት ተቀብቶ ከነገሠ በኋላ ጎልያድን በመግደሉ በሕዝቡ ዘንድ ባገኘው ከበሬታ ምክንያት ንጉሥ ሳኦል ሊገድለው ተነሣ፤ ብላቴናው ነቢይ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ሸሽቶ ሄደ፤ በቀርሜሎስም ከባለሟሎቹ ጋር ተቀመጠ፡፡ በዚያም ናባል የሚባል ሰው ነበር፤ ሚስቱም አቢግያ ትባላለች ዳዊት በዚያ ስፈራ በመኖሩ የአካባቢውን ሰዎች ንብረት በሽፍቶች (በቀማኞች) እንዳይወሰድ ከለላም ሆነ፤ ዳዊትም የሚገባውን ግብር እንዲያገባ ለናባል መልእክተኞችን ላከ፤ ናባል ግን ከስጦታው ይልቅ ስድብንም ጨምሮ የእንቢታን ምላሽ ሰጠ፡፡ ንጉሥ ዳዊት በዚህ ተቆጥቶ ናባልና የእርሱ የሆኑትን ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ወሰነ፤ ይህንን ነገር የናባል ሚስት አቢግያ ሰማች፤ ከዚያም የሚገባውን እጅ መንሻ ይዛ ወደ ንጉሥ ዳዊት ገሰገሰች፤ ከእግሩም ሥር በግንባሯ ተደፍታ እጅ ነሣች፤ ሊወስድ  የመጣውን ርምጃ (ቅጣት) እንዳይፈጽም እንዲህ አለችው ‹‹…ወደ ደም እንዳትገባ አጅህም ራስህን እንዳታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው …›› (፩ኛ ሳሙ. ፳፭፥፳፮) እጅ መንሻውንም ሰጠች፤ ንጉሥ ዳዊትም የሰላም ሰው ነውና የአቢግያን የሰላም መልእክት ተቀብሎ ከጸብ ይልቅ ሰላምን፣ ከበቅል ይልቅ ይቅርታን መረጠ እንዲህም ሲል አመሰገነና ‹‹…ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ  እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ወደ ደም እንዳልሄድ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን  አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ…›› አላት፡፡ (፩ኛ ሳሙ. ፳፭፥፳፮) የሰላም ሰው ንጉሥ ዳዊት ስለ መልካምነቱ፣ ስለ ይቅርታው በትዕቢት የተገዳደረው ናባል ግን ተቀሥፎ ሞተ፡፡

ውድ ክርስቲያኖች! የሰላም መገኛው የት ነው ?!  ነቢየ እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊት ለተበደለ ሊፈርድ የበደለን ሊቀጣ በእግዚአብሔር የተመረጠ የሕዝቡ መሪ ሆኖ ሳለ በትዕቢት የተገዳደረው ናባል ያስቆጣውን ልቡን ብልህና አስተዋይዋ አቢግያ በሰላማዊ ንግግሯ አበረደችው፡፡ ንጉሠ ዳዊት ሰላሙን ከይቅርታው አገኘው፤ የበቀል ጉዞውን በትዕግሥት ገታው፤ በአንድ ሰው ምክንያት ጉዳዩ የማይመለከታቸውን ከመቅጣት (ከማጥፋትና) ደስታውን ከሚነጥቅ፣ ዕረፍቱን ከሚነሣ፣ ፍቅርን ከሚያሳጣ፣ ጤናውን ከሚያቃውስ፣ ከጸጸት አዘቅት ከሚከት ከሰላም እጦት ራሱን ጠበቀ፡፡

ውድ ክርስቲያኖች! የሰላም መገኛው የት ነው?!  ሰላምን ፍለጋ ዘምረናል፤ ጸልየናል፤ እኛ ሰላማዊ ለመሆን ምን ያህል ጥረናል! “ሰላም አውለን” ብለን ከቤት ስንወጣ ሰላማዊ ለመሆን፣ ጥላቻን በፍቅር፣ በደልን በይቅርታ ለመለወጥ ምን ያህል ጥረናል?! ጤናችንን የሚያቃውስ፣ ፍቅራችንን የሚያደፈርስ፣ አንድነታችንን የሚበታትን ጥላቻን፤ ከልባችን አንግሠን፣ ሰላማችንን የሚያርቅ ሰብእናችንን የሚያጎድፍ፣ ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚለየንን ቂም አርግዘን ሰላምን እንዴት ማግኘት ይቻላል?! አምላካችን ጥላቻን በፍቅር፣ በደልን በይቅርታ ቀይሮ ሰላማችንን ሰጠን፤ ‹‹..ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላምን እሰጣችኋላሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም…›› እንዲል፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፳፯)፤ ፈለጉን እንከተል እንመስለውም ዘንድ ‹‹ከእኔ ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና›› ብሎ ነገረን፤ በምግባራቸው ሊመስሉት የተከተሉት፣ መጠራታቸውን በመመረጥ መመረጣውን በመጽደቅ ያጸኑ ቅዱሳን አባቶቻችን የሰላምን ጥቅም በጥልቀት ተረድተው እኛም እንጠቀምበት ዘንድ እንዲህ ይመክሩናል!፤ ‹‹…በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ …፡፡›› (ሮሜ ፲፪፥፲፰)

ውድ ክርስቲያኖች! የሰላም መገኛው የት ነው ?! ሰላም ከራሳችን ይጀምራል፡፡ እያንዳንዳችን ሰላማዊ ከሆንን ሰላማዊ ቤተሰብ ይኖረናል፤ ሰላማችን ከእኛም አልፎ ለጎረቤት፣ ከፍ ሲል ለከተማ ከዚያም ለአገርና ለዓለም ይተርፋል፤ ሰላም ከየትም አይገኝም፤ የሰላም መፍለቂያዋ ከቂም በቀል ከራቀ፣ ከጥላቻ ከጸዳ፣ ፍቅርን ካነገሠ፣ አንድነትን ከመረጠ ልባችን ነው፤ ለዚህም ነው፡፡  ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌው ‹‹…አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና…›› በማለት የሚመክረን የሰላም መገኘዋ፣ የሕይወት መውጫ ከሆነ ልባችን ነውና፡፡ (ምሳ. ፬፥፳፫)

‹‹ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው ምላሱን ከክፉ፣ ከንፈሮቹንም ተንኮልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፤ መልካምንም ያድርግ፤ ሰላምን ይሻ ይከተላትም…፡፡›› (፩ኛ ጴጥ.፫፥፲፩፤መዝ.፴፫፥፲፬)

ውድ ክርስቲያኖች! የሰላም መገኛው የት ነው ?! ሰላምን ከፈለግናት ከራስ ወዳድነት እንለይ፤ ምክንያቱም ‹‹የዓለማችን ችግር ሁል ጊዜ ምንጩ ራስ ወዳድነት ነውና›› በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ፤ ሁለት መነኮሳት ስለ ሰላም መደፍረስ፣ ስለጸብ መነሻ ምን እንደሆነ መጠያየቅ ጀመሩ፤ አንደኛው እንዲህ ሲል ጠየቀ! ‹‹ሰዎች ሰላማቸውን የሚያጡት፣ ፍቅራቸው የሚደፈርሰው በምን ምክንያት ነው?››! አንደኛው በምሳሌ ያስረዳው ዘንድ የያዘውን ዳዊት (የጸሎት) መጽሐፍ ተቀበለውና እንዲህ ያስረዳው ጀመር፤ ‹‹ይህ ዳዊት (የጸሎት መጽሐፍ) ያንተ ነው፤ እኔ ግን እነጥቅህና የእኔ ነው እልሃለው፤ አንተ ደግሞ የእኔ ነው ትላለህ፤ የዚህን ጊዜ በመካከላችን ጸብ ይጀመራል፤ ፍቅራችን ይጎረብጣል፤ ሰላማችን ይናጋል›› በማለት አስረዳው፤ በምሳሌም በተግባር ለማሳየት ብሎ የጓደኛውን ዳዊት (የጸሎት) መጽሐፍ ነጠቀውና  ‹‹የእኔ ነው›› አለው፤ ያም የዋህ መነኩሴ ‹‹አይ የእኔ ነው፤ የአንተ አይደለም›› ማለት ሲገባው እርሱ ግን ‹‹እሺ የአንተ ነው፤ ውሰደው›› ብሎ የእራሱን የሆነ ዳዊት (የጸሎት መጽሐፍ) ተወለት! በመነኮሳት (በአባቶች) ዘንድ ፍቅር እንጂ ጸብ የለምና፤ የእኛ እንጂ የእኔ የሚባል ነገር የለምና! ሰላምን ከሌላ ሰው ከሩቅ ሳይሆን ከራሳቸን እንፈልጋት፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

 

‹‹እነርሱ በእምነት የእሳት ኀይልን አጠፉ›› (ዕብራውያን ፲፩፥፩)

ታኅሣሥ ፲፯፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ለብዙዎቻችን እሳትን የሚያጠፋው ውኃ ብቻ ይመስለናል፡፡ ለእግዚአብሔር የታመኑ ቅዱሳን ሰማዕታት የእሳትን ኃይል በትዕግሥታቸው እንዳጠፉትና ጸሎታቸውም ለእኛ በአማላጅነታቸው ለምንታመን ምእመናን ሁልጊዜም እንደሚያስፈልገን ፈልፈለ ማኅሌት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ምስክር ሆኖ ያስተምረናል፤ አጥፍኡ ኃይለ እሳት በትዕግሥቶሙ፤ ይብጽሐነ ወትረ ጸሎቶሙ፤በትዕግሥታቸው የእሳትን ኃይል አጠፉ፤ ጸሎታቸው ዘወትር ይድረሰን” እንዲል፤ (ድጓ ዘታኅሣሥ ፪)

በሐዲስ ኪዳን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እምነት ማለት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ ፣ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት››  በማለት የተናገረውን ቃል (ዕብራውያን ፲፩፥፩) በብሉይ ኪዳን አስቀድሞ በተፈፀመ ገድል እንድናውቀው የሠለስቱ ደቂቅ የባቢሎን የዱራ ሜዳ ገድልና የእምነት ጽናት ዓይነተኛ የሕይወት ትምህርት እንዲሆነን በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎልን እናገኛዋለን፡፡ እምነታችን እውነተኛ ሆኖ የሚገለጠው እግዚአብሔር በሚፈጽምልን የትድግና ሥራ ብቻ ሳይሆን መከራም ቢመጣ የመጣው እግዚአብሔር ፈቅዶ በመከራው ተፈትነን ካለፍን በኋላ እኛ ልጆቹ እንድናገኝ የፈለገውን ሰማያዊ አክሊልና ዋጋ እንድናገኝም ስለሚፈልግ መሆኑን ማመን ስንችል ነው፡፡

ጻድቁ አባታችን ቅዱስ ኢዮብ  እጅግ ብዙ መከራ ሲደርስበት ‹‹ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፤ ክፉውን ነገርስ አንታገሥምን?›› በማለት በደረሰበት ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በከንፈሩ ሳይበድል የሕይወቱን የፈተና ጊዜ ለማሳለፍ በቅቷል፡፡ (መጽሐፈ ኢዮብ ፪፥፲) የሠለስቱ ደቂቅ እውነተኛ እምነትም ለናቡከደነፆር በሰጡት ምላሽ ውስጥ የምናገኘው ነው፡፡ ንጉሥ ናቡከደነፆርም እኔ ላሠራሁት ምስል ስገዱ ባላቸው ጊዜ  ‹‹ናቡከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም፡፡ ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፤  ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን ፣ አማልክትህን እንዳናመልክ ፣ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት ዕወቅ›› አሉት፡፡ (ትንቢተ ዳንኤል ፫፥፲፭-፲፰)

ከዚህ በኋላ ወደ እሳት እንዲጨመሩ ንጉሡ አዘዘ፡፡ አይደለም እሳት ላይ ተጥደን በመልካም ሁኔታ ውስጥ ሆነን እንኳን የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ላቃተን ለእኛ፣ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳት መካከል ሆነው የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ብቻ ሳይሆን ረጅም ጸሎትን ሲያደርሱ

 

እንደነበር ማወቅ ምንኛ ግሩም ነው! (ወጸለዩ ማዕከለ እቶነ እሳት ነዋኃ ጸሎተ) (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ታኅሣሥ ፪)፡፡

በመከራ ላይ መከራ ቢያጸኑባቸው በምስጋና ላይ ምስጋና በመጨመር ታላቅ የሆነ የነገረ ክርስቶስ ትምህርትንም የያዘ ጸሎት ያደረሱት በእሳት ውስጥ ነው ቢባል ማን ያምናል፡፡ በጸሎታቸው እነርሱ ይህን ገድል ከፈፀሙ ከ፮፻ ዓመት በኋላ አምላክ የሰውን ሥጋ ለብሶ ተገልጦ እንደሚወለድ እና በዚህች ምድርም ፴፫ ዓመት እንደሚቆይ የሚያጠይቅ ነው፡፡

ሰው እግዚአብሔርን ካመነና ማመኑንም በሥራ ገልጦ ካከናወነ ፍጹም የሆነ የእግዚአብሔር ረድኤት ከእርሱ ጋር ስለሚሆን በሥጋ ዓይን ስናየው በሥጋው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስበት የሚችል እሳት እንኳን አቅም ያጣል፡፡ ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እሳት ወርውረው እንዲጨምሩ በንጉሡ የታዘዙትን ሰዎች የገደለ እሳት በመካከሉ የተገኙ ሠለስቱ ደቂቅ ላይ ግን አንዳች ጉዳት ማድረስ አልቻለም፡፡ የራሳቸው ጠጉር አንዲት ዘላላ እንኳ አልተቃጠለችም፤  ሰናፊላቸውም አልተለወጠም፤ ሽታቸውንም አልለወጠም፡፡ (ትንቢተ ዳንኤል ፫፥፳፯)

ጥንተ ጠላት ዲያቢሎስ በዓላውያን ነገሥታት ላይ አድሮ ዛሬም በእኛ ላይ የጥላቻን እሳት እያነደደ ከራሳችን አልፎ ለሀገራችን ኢትዮጵያም የሚተርፍ መከራን አኑሯል፡፡ የባቢሎንን እሳት በመስቀሉ በማቀዝቀዝ ሠለስቱ ደቂቅን ከእግዚአብሔር ተልኮ ያዳነው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በእኛና በሀገራችን ኢትዮጵያ እየነደደ እጅግ መከራ ውስጥ የከተተንን የጥላቻ እሳት እንዲያበርድልንና ሁላችንም የፍቅር ሰው እንድንሆን አማላጅነቱና ጠብቆቱ አይለየን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር!

 

ትሩፋን

ኀዳር ፳፮፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

 ቅዱሱ መጽሐፍ ትሩፋን ከጦርነት፣ ከስደት፣ ከምርኮ የተረፉትን ሰዎች እንደሚያመልክት ይነግረናል፡፡ “ትሩፍ” ጥሬ ቃሉ “የቀረ፣ የተረፈ፣ ቀሪ፣ ትርፍ” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ ፱፻፫) ናቡከደነፆር እስራኤልን ወደ ባቢሎን ማርኮ ከወሰዳቸው ከሰባ ዘመን በኋላ በባቢሎን የቀሩት ከተማረኩት ሽማግሎች ትሩፋን ይባላሉ። በንጉሡ ዘመነ መንግሥት ከኢየሩሳሌም ተማርከው ሰባ ዘመን በፋርስ በባቢሎን የሚኖሩ የእስራኤል ሕዝብ ትሩፋነ ባቢሎን እንደሆኑም መጽሐፍ ያስረዳናል። (ዕዝራ ፪፥፩)

በተለያዩ ዘመናት በአንድም በሌላ ምክንያት በሰዎች፣ በጎሳ፣ በማኅበረሰብ ዘንድ እንዲሁም በሀገራት መካከል በሚከሰት ጦርነት እልቂት አልያም የግፍ ግድያና ጭፍጨፋ የተነሣ የብዙዎች ሕይወት ይጠፋል፤ ታሪክ ለዚህ ቀደምት ምስክር እንደሆነ የምናውቀው እውነት ነው፡፡ የጦርነት ወሬ ደግሞ ለእኛ አዲስ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ እራሱ ጌታ በወንጌል ሲናገር  ‹‹ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፤ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል›› እንዳለው ምድር ላይ እነዚህ ሁሉ መከራዎች እየተከሰቱ እንደሆነ ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ (ማቴ.፳፬፥፮-፯)

ታዲያ የጦርነት አስከፊ ገጽታው እንጂ መልካም ጎኑ ምን አልባት እርሱ ባወቅና በፈቀደ ጠላትን ከሀገር የማስወጣቱ ተግባር ነው፡፡ በዚህም አብዛኛዎቻችን ጦርነትን በውዴታ ሳይሆን በግዴታ የምንቀበለው ነው፡፡ ከሁሉም አስከፊው ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን፣ ዘመድ አዝማዳቸውንና ወዳጆቻቸውን የሚያጡ ትሩፋን የሚገጥማቸው ሥቃይና ጉዳት ነው፡፡ በአንድ በኩል ከአሰቃቂ ግድያ አልያም ከሞት መትረፍ ቢያስደስትም በሌላ በኩል ግን የሚወዱትን ማጣት እጅግ አስከፊ ነው፡፡ ከምንም በላይ ግን የሞት ሞት የሆነው የነፍስ ሞት አሰቃቂ ነው፡፡

ሰዎች ሞትን እንፈራለን፤ የሥጋ ሞት አስጨናቂ እንደሆነ ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ኢትፍርህዎ ለሞት፤ ፍርህዋ ለኃጢአት፤ ሞትን አትፍሩ፤ ኃጢአትን እንጂ›› ይለናል፡፡ ሊያስጨንቀን የሚገባው በኃጢአት ምክንያት የሚመጣብንን የነፍሳችን ሞት እንጂ የሥጋ ሞት ሊሆን እንደማይገባ በዚህ ቃል እንረዳለን፡፡ ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ›› በሚለው አምላካዊ ቃል ሥጋዊ ሞት አይቀሬ በመሆኑም ምንም ለማንቀይረው  ነገር መጨነቁ ጥቅም የለውም፡፡ (ዘፍ.፫፥፲፱) 

የነፍስ እንጂ የሥጋ ጦርነት ትሩፋን ባንሆን እጅጉን ይመረጣል፡፡ ቃሉን ተረድተው፣ በሕጉ ኖረው ትእዛዙን የጠበቁ ጻድቃን ሁሉ በነፍሳቸው አትርፈው ከዚህ ዓለም ድካምና ዕረፍት በክብር እንደተለዩ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክር ናቸው፡፡ (ገድለ ቅዱሳን) አብነት መሆናቸውን ደግሞ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ሁላችን ማወቅ አለብን፡፡   እውነት ስለሆነው አንድ ጌታና አንዲት እውነተኛ ሃይማኖት ሲሉ መከራን በመቀበል በቀናው መንገድ ተጉዘው መልካም ፍሬን ያፈሩ ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት የነፍስ አትራፊዎች/ትሩፋን/ ናቸው፡፡

የልባችን መሻት የሁላችንም ምኞት መሆን ያለበት ይህ ነገር ሆኖ ሳለ፣ በመንፈስ ውጊያ ለማሸነፍ የሚያስችለንን ስንቃችንን ደግሞ ማከማቸት አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት፣ እኛ ግን እየተጨነቅን ያለነው በጊዜያዊ ችግርና ወቅታዊ የእርስ በርስ ጦርነት ላለመሞት ነው፡፡ የሥጋዊ ሞትን ፈርተን በምንዘናጋበት ጊዜ ግን ነፍሳችንን እንደ አንበሳ ነጥቀው ሊጥሏት ይችላሉና ይህንን እንፍራ!

ነፍስ ዘለዓለማዊ ስትሆን ሥጋ ግን ጊዜያዊ ነው፤ አላፊ ጠፊ የሆኑ ምድራዊ ነገሮችን ለሟሟላት በሚል በምድር ለመኖር ስንሻ ከሁለት ያጣም የመሆን ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ስለ ሥጋዊ ሞት ስናስብ መንፈሳዊ ዝለት ያጋጥመናል፤ በዚህም ጊዜ ነፍሳችን ትጎዳለች፤ ታድፋለች፤ ትመነምናለች፡፡

ሰው ጦርነትን ፈርቶ ሊሸሽ ይችላል፤ መሰደደም ሆነ መደበቅም አይከፋም፤ ግን ግልጽ የሆነውን አስከፊ ሁኔታና እየተካሄደ ያለውን ጦርነትም ይሁን እልቂት ማስቆም ካልተቻለ ሃይማኖታችን በሚፈቅድልን ተገቢ መንገድ ድምጻችንን ማሰማቱና መልእክት ማስተላለፍ እንጂ የጠላት ወገን ከሆኑ አካላት ጋር ግብ ግብ መፍጠር አልያም ጦርነት ውስጥ መግባት አላስፈላጊ ነው፡፡ ጠላት ፊት ለፊት መጥቶ ሊገለን ቢፈልግ እንኳን “ማኅተባችንን አንበጥስም” ብለን አንገታችንን ለሰይፍ ሰውነታችንን ለሞት አሳልፈን መስጠት ሰማዕትነት ነው፤ የክብር ሞትም ያሰጠናል፡፡

በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተለይም በዕረፍት በዓሏ በየወሩ ፳፩ ቀን የሚነበበው መልክአ ማርያም ‹‹ኃጥአን ከታላቅ የደስታ አደባባይ በተሰደዱ ጊዜ ምርኮ እሆንሽ ዘንድ ከእነርሱ ለይተሽ አስቀሪኝ›› ይለናል፡፡ (መልክአ ማርያም) ይህ ድንቅ ጸሎት የሚያመለክተን ከጦርነት ምርኮኝነት ለማምለጥ ማቀድ ሳይሆን ከኃጥአን ጎራ ላለመቆጠር መሻት እንዳለብን እንዲያውም የፍቅር ምርኮ መሆን እንደሚገባ ነው፡፡

ንጽሕት ቅድስት ከምትሆን የአምላክ እናት የተለመነው ይህ መማጸኛ ለሁላችን እንደሚሆን  እናምናለን፡፡ የነፍሳችንን ጥፋት የማይፈልገው አምላካችን አንዲያ ልጁን አሳልፎ ሰጥቶ ያዳነን ክብርት በሆነች እናቱ ድንግል ማርያም ነውና ታማልደን፣ ትለምንልን እና ትራዳን ዘንድ መማጸን የተገባን ነን፡፡ ከጠላት ሰይጣን የመንፈስ ውጊያ እንድታተርፈን፣ ምርኮዎቿ  እንድታደርገንን እንለምናት፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

 

የሥራ አጥነት ተጽዕኖ

ጥቅምት ፳፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

“በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርሷ ትበላለህ” የሚለው አምላካዊ ቃል ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡ (ዘፍ. ፫፥፲፯) ሰው በሠራው ኃጢአትና ጥፋት የተነሣ ከገነት ተባሮ ወደ ምድር ከመጣበት ጊዜ አንሥቶ እስካለንበት ጊዜ ድረስ የሥጋችንን በተለይም መሠረታዊ ፍላጎታችንን ሟሟላት የምንችለው ሥራ ሠርተን በምናገኘው ገንዘብና ቁሳዊ ነገሮች ነው፡፡

በዘመናት ሂደት ሰዎች በተለያዩ ችግሮችና መከራዎች ውስጥ ገብተው የሚዋዥቁበት ምክንያት አንድም በሥራ አጥነት ሳቢያ በሚያጋጥም የገንዘብ አቅም ማነስና ችግር በመሆኑ የምግብ አቅርቦት፣ የመጠለያ እጦትና የአልባሳት እጥረት ለረኃብ፣ ለመራቆት እንዲሁም ለተለያዩ በሽታዎች ባስ ሲል ደግሞ ለሞት ይዳርጋሉ፡፡

የሥራ አጥነት ችግር አስከፊነት ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በደረስንበት በዚህ ወቅት በተለይም ወጣቶች ከዚህ ለባሳ ችግር ተጠቂ ሆነዋል፡፡ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸው እንዲሁም በተሰጣቸው ተሰጥኦ ለፍተው፣ ጥረው፣ ግረው የመኖር ሐሳባቸው ከማንኛውም የዕድሜ ክልል የበለጠ በመሆኑ አእምሮአቸው ሥራ ሲፈታ ይረበሻል፤ ተስፋም ያጣሉ፤ ወደ ጭንቀትና የተለያዩ የሥነ ልቡና ቀውስ የሚገቡ ወጣቶች ቁጥርም ጥቂት አይባልም፡፡

በየዓመቱ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎችም ሆነ በዘመናዊ ትምህርት ብዙ ሳይገፉ በአጋጣሚዎች ተጠቅመው በሙያቸው አልያም በጉልበታቸው ሠርተው ለመኖር የሚጥሩ ወጣቶች በልዩ ልዩ የሀገራችን ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን ሥራ አግኝቶ በቋሚነት አንድ ቦታ ላይ ገንዘብም፣ ዕውቀትም ሆነ ልምድ ማካበት ያልቻሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህም እራሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ቤተ ሰቦቻቸው እንዲሁም ማኅበረሰቡ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፤ አብዛኞቻችን በእራሳችን፣ በዘመዶቻችንና በጎረቤቶቻችን ሕይወት የሰማነውና የተመለትነው ነገር ነው፡፡

በርካታ ወጣቶች የሱሰኝነት ተጠቂ የሆኑት በዚህ ምክንያት እንደሆነ ከገዛ አንደበታቸው ሰምተንም ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይም ወጣት ወንዶች ለዚህ ችግር ተጋላጮች ናቸው፡፡ ሱሰኝነት የሚያመጣው የጤንነት እክል ብቻ እንዳልሆነ ደግሞ የጤና ባለሙያዎች አበክረው ይናገራሉ፡፡ እንደ እነርሱ ገለጻ ከሆነ ሱሰኞች ከቤተ ሰቦቻቸው ጋርም ሆነ ከማንኛውም የማኅበረሰብ አካል ጋር መልካም ግንኙነት አይኖራቸውም፡፡ የተዛበ ቀኖችን በማሳለፋቸው የተነሣ ከማንም ጋር የሰላም ግንኑነት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ቀኑ ለእነርሱ ሌሊት፣ ሌሊቱ ደግሞ ቀን የሚሆንባቸው ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡ ንግግራቸው በአብዛኛው ቀና ያልሆነና የተጣመመ እንዲሁም ስድብና አጸያፊ ቃል የተቀላቀለበት ሲሆን ከሰዎች ጋር የመጣላቱ ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡ የሚወዷቸውንና የሚቀርቧቸውን ሰዎች ሳይቀር ስለሚያስቀይሙ በብቸኝነት ዓለም ውስጥ ይገባሉ፡፡

ሱሰኛ የሚሆኑ ወጣቶች ዓለማዊ ሕይወትን የሚኖሩ ብቻ ሊመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን በስመ ኦርቶዶክስ የሚኖሩና በሥራ አጥነት እንዲሁም በሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች ምክንያት ባክነው የቀሩ ብዙዎች እንዳሉ ማወቅ ይገባል፡፡

በዚህ ጊዜ ደግሞ የተጋፈጥነው ሌላ ትልቅ ችግር አለ፡፡ ከምዕራባውያን በኩል ወደ ሀገራችን የገባና የተስፋፋ ተብሎ የሚታመነው “የሰይጣን አማኞች ማኅበረሰብ” ወጣቶችን በገንዝብና ሌሎች ጥቅሞች በማጥመድ የጠላት መረብ ውስጥ እየከተቱ ይገኛሉ፡፡ በየአደባባይ እየተመለከትናቸው ያለነው የእምነቱ ተከታዮች ሳያውቁም ይሁን አውቀው ለሰይጣን እየተገዙ ነው፡፡ ድህነትን ሸሽተው፣ በቀላሉና በአጭር ጊዜ ችግራቸውን ፈትተው ገንዘብና ሀብት ለማካበት በሚደረግ ጥረት ነፍሳቸውን ካጡት ውስጥ ኦርቶዶክሳውያን እንዳሉበት ተአማኒ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ወጣቶቹ ታዲያ እያጡ ያሉትን መንፈሳዊነትም ሆነ እየገቡበት ያለውን አዘቅት በደንብ የተረዱ አይመስሉም፡፡ ብቻ የዕለት ጉርሰን ለሟሟላትና ከተቻለም በርከት ያለ ገንዘብ ለማግኘት ወደዚህ ዝቅተት ይገባሉ፡፡ በኋላ ግን ከገቡበት ለመውጣት ቢፈለግ እንኳን ቀላል እንዳልሆነ መገመት አያዳግትም፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን እያስተናገደች ያለችው አስተዳደራዊ ለውጥና ማኅበረሰባዊ አኗኗር ያመጣው የኑሮ ውድነትም ለዚህ ችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደረገ ነው፡፡ ቢያንስ መሠረታዊ ነገሮች ሁሉም ሊኖረው ይገባልና በእራሱ ለፍቶ እንዲያገኝ የማድረግ ዕድል ተጠያቂው አካል ሊያመቻች ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን እንደምትደግፍ አስቀድመን በጠቀስነው የአምላካችን ትእዛዝ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

    ይቆየን!

የአበባ ወር

መስከረም ፳፮፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

ጊዜ የተለያዩ ተፈጥራዊ ኩነቶችን ያስተናግዳል፤ በዓለም ላይ በሚከሰቱ የወቅቶች መፈራረቅም ምድር አንዳንዴ ስትበለጽግ ሌላ ጊዜ ደግሞ ትራቆታለች፡፡ በክረምት ወራት በሚዘንበው ዝናብ ስትረጥብ በበጋ ደግሞ በፀሐይና በሙቀቱ ትደርቃለች፡፡ በዘመነ መጸው በነፋሳት ስትናወጥ ፈክተው የሚያብቡት አበቦች ግን ያስውቧታል፡፡

ቅዱሱ ሰው አባ ጽጌ ድንግል የአበቦችን ዕጹብ ድንቅ ተፈጥሮና የላቀ ዋጋ በማወቁ ሳይሆን አይቀርም ከአበቦች ሁሉ በሚበልጥ አበባ ለምንመስላት ድንግል ማርያም አበቦችን ያበረከተላት፡፡ በዐሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሱት ሊቁ የደረሱት የማኅሌተ ጽጌ ድርሰት ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ቀን ድረስ ባለው ወቅት የእመቤታችን ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ ብሎም ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ እና መንከራተት እንዘክርበታለን፡፡

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት፣ አማላጅነትና ተረዳኢነት አይለየን፤አሜን!