የማይሞተው ሞተ!

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል

ጥቅምት ፳፮፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ልዑል ሆይ ክንድህን ስደድ

ናማ ውረድ

ና ተወለድ

ብለው ነቢያት በጾም ጸሎት ተጉ ጮኹ!

ጨለማውን አስወግዶ ብርሃኑን ያበራልን

አንጠፋ ዘንድ በፍጹም ፍቅር የራራልን

 

በግብዞች በአይሁድ ሥርዓት

በሕጋቸው እንደጻፉት

የሾህ አክሊል ተቀዳጅቶ

መጻጻውን ተጎንጭቶ

 …..

እርሱ ሞተ ሊሰጥ ሕይወት

ወየው በሉ አልቅሱለት፤

የእጁን መዳን ያገኛችሁ የጌንሴሬጥ ድውይ ሁሉ

ለኢየሱስ አልቅሱለት፤ ፍዳን ስላያት በመስቀሉ

የ፲፪ ዘመን ሥቃይ በልብሱ ጫፍ ………

በቅጽበት ውስጥ የጠፋልሽ

ተገረፈ፤ ተንገላታ፤ የማይሞተው ሞትን ሞተ፤ ……..

ያ ርኅሩኅ ቸር መዳኒትሽ

ኢያሮስ የት ነው ያለህ!

ያ’ዓለም ጌታ ተተፋበት ሴት ልጅህን ያዳነልህ!

እመቤቴ የልጅሽን መከራውን እንዴት ቻልሽው አልልሽም

ቅዱስ ዳዊት በእሳት ፈረስ ሰባቱ ኃያል …..

መላእክቱ ካንቺ መጥተው ቢያፅናኑሽም

ለሦስት ቀን የአንዱ ልጅሽ ከሞቱ ይልቅ አሟሟቱ ….

እያስነባሽ እህል ውኃ እንኳን አልቀመስሽም

አብ ሆይ ማረን!

መንፈስ ቅዱስ ተዘከረን!

በልጅህ ደም የተገዛን ለመሆኑ አላወቅንም ዋጋችንን

ጽድቃችንም የመርገም ጨርቅ ከንቱ ሆኖ

መኖሪያችን በሲኦል ቋት ተወስኖ

ለዘመናት ስንገረፍ በእሳት ላንቃ

ያበቃ ዘንድ ይህ እንግልት ይህ ሰቆቃ

እሰይ እሰይ ይኸው አሁን የምሥራች

የሞት ዐዋጅ ተሻረልን፤ ገነት ዳግም ተከፈተች

የጥሉ ግድግዳ ፍርሶ ሰላም ሆኗል ከላይም ከታች

፶፻፭፻ የንስሐ የጣር ዘመን ተፈፀመ

በደላችን ተሰርዞ በክርስቶስ ደም ታተመ::

 

‹‹በእንተ አቡነ አቢብ!››

ጥቅምት ፳፬፤፳፻፲  ዓመተ ምሕረት

በዐሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን በሮሜ ሀገር የተወለዱት ቅዱስ አባታችን አቡነ አቢብ የስማቸው ትርጓሜ “የብዙኀን አባት” አንድም ቡላ ማለት “የተወደደ፣ እግዚአብሔር የተለየ” ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ታላቅና ክቡር የሆነ አቢብ የተባለ መስተጋድል አባ ቡላ ተብሎም የሚታወቅ አባት በከበረች ዕለት ጥቅምት ሃያ አምስት (፳፭) እንዳረፈ ይጠቅሳል፡፡

አስቀድሞም ከሃዲው ንጉሥ መክስምያኖስ ክርስቲያኖች ላይ ባመጣባቸው ስደት ምክንያት አባትና እናታቸው አብርሃምና ሐሪክ ተሰደው ሲኖሩ ልጅን ባማጣታቸው በጸሎትና በጾም አምላካቸው እግዚአብሔርን በመለመናቸው መልአክ ለአብርሃም ተገልጾ “ይህ ፍሬ የአንተ ነው፤ እርሱም ወደ እኔ የሚቀርብ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ፈቃዱንም የሚፈጽም የአመረ መባዕ ነው” በማለት እግጅ መልካም ፍሬን ሰጠው፡፡ ደጉ ሰው አብርሃምም ከእንቅልፉ ነቅቶ ለሚስቱ በሕልሙ ያየውንና መልአኩ የነገረውን ሁሉ ነገራት፡፡ እርሷም ደስ ተሰኘች፤ ሁለቱም በአንድነት እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ የአብርሃም ሚስት ሐሪክ በፀነሰች ጊዜም በቤታቸው አደባባይ ሁለንተናው መልካምና ታላቅ ዛፍ በቀለ፡፡ በቅጠሉም ላይ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈ “በጽዮን አድሮ የሚኖር የያዕቆብ ፈጣሪ የእግዚአብሔር አገልጋይ ቡላ” የሚል ጽሕፈት አገኙ፡፡ በዚህም ጊዜ በተአምሩ ተደንቁ፡፡

ቀጥሎም መልኩ ያማረ ከብርሃናት ይልቅ ፊቱ የሚያበራ ወንድ ልጅን ወለደች፡፡ ከዚህም በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ክርስትናን ሳይስነሡ ሲያኖሩት እመቤታችን ድንግል ማርያም ለሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ለሰለባስትሮዮስ ተገልጣ ወደ አብርሃም ቤት በመሄድ ሕፃኑን እንዲያጠምቀው ስላዘዘችው የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው፡፡  ስሙንም “ቡላ” ብላ ሰየመው፤ ወላቹም በዚህን ጊዜ አደነቁ፡፡ ጸሎትም አድርጎ የቊርባን ኅብስትና ወይን የተመላ ጽዋ ከሰማይ ስለወረደ ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን ሕፃኑንና ወላጆቹን አቀበላቸው፡፡  በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ የአንድ ዓመት ልጅ ሲሆን “በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ አብ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው፤ በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ ወልድ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው፤ በባሕርይ በህልውና በመለኮት በአብ ከወልድ ጋር አንድ የሆነ መንፈስ ቅዱስ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው” ብሎ ተናገረ።

ጥቂት ዓመታት ካለፉም በኋላ በኅዳር ሰባት ቀን አባቱና እናቱ ዐረፉ፤ ሕፃን ቡላ ዐሥረኛው ዓመቱ ላይ ሌላ መከራ አጋጠመው፤ ሕዝቡን ለጣዖት መስገድ የሚያስገድድ መኮንን እንደመጣ በሰማ ጊዜም ሕፃኑ በፊቱ ቀርቦ የረከሱ ጣዖታትን ረገመ፡፡ በአካል ትንሽ መሆኑን የተመለከተው መኮንኑ ለጊዜው ቢያደንቅም በችንካር ቸንክረው፣ ሥጋውን ሰነጣጥቀው፣ ቆዳውንም ከአጥንቱ እንዲገፉት፣ እጁቹንና እግሮቹን በመጋዝ እንዲቀርጡ፣ በሶሾተልና በጦሮች አድርገው ከመንኮራኩር ውስጥ እንዲጨምሩት፣ ዳግመኛ በመንገድ ላይ እንዲጎትቱት አዘዘ፡፡ ሆኖም መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ስላዳነው ያለ ጉዳት ጤነኛ ሆነ፡፡ ቅዱሱ ሕፃን ቡላ ግን ሌላ መኮንን ጋር ሄዶ የረከሱ ጣዖታትን ገረመ፡፡ በዚህም ጊዜ መኮንኑ ተቆጥቶ ሚያዝያ ወር በባተ በዐሥራ ስምንተኛው ቀን ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ስላዘዘ ቆረጡት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ከሞት አስነሣው፡፡ በዚህም ጊዜ የመነኮስ ልብስንና አስኬማን በመስቀል ምልክት አለበሰውና እንዲህ አለው፤ “ከቅዱሳንና ከጻድቃን አንድነት ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር አዝዞአል፡፡”

ቅዱስ አባታችንም በዚህ ጊዜ ከደረቅ ተራራ ላይ ወጥተው በውስጧ እየታገደሉ ሲኖሩ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መስቀል በማሰብ ከረጅም ዕንጨት ላይ በመውጣት ራሳቸውን ወደታች ሁል ጊዜ ይወረውሩ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም በዛፍ ላይ ሲወረወሩ ሰይጣን በቅናት ተነሣስቶ ገደላቸው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አነሣቸውና “ከእንግዲህ ስምህ ቡላ አይሁን፤ አቢብ ይባል እንጂ፤ የብዙዎች አባት ትሆናለህና” አላቸው፡፡

ከዚህ ቀጥሎ አቡነ አቢብ የክርስቶስን ፍቅር በመጨመር ፊታቸውን ይጸፉ፣ ሥጋቸውን በጥቂት ይቆርጡ፣ ጀርባቸውን ሰባት ጊዜ ይገርፉ ነበር፡፡ ጌታችን በዚህ ጊዜም ከእርሳቸው ሳይለይ ይፈውሳቸው ነበር፡፡ በየእሑድም ቀን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደተወለደ፣ በሌሎች ቀኖችም እንደተያዘና ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበለ ሁኖ ይገለጽላቸው ነበር። በዚህም የተነሣ ለአርባ ሁለት ዓመታት ምግብ ሳይበሉና ውኃ ሳይጠጡ ከኖሩ በኋላ  ለዐሥራ ሁለት ወር በራሳቸው ተተክለው ሲኖሩ ናላቸው ፈስሶ አለቀ፡፡

የጌታችንን መከራ በአሰቡ ጊዜ በአንዲት ቀን ሰይፉን በአንጻሩ ተክለው ከዕንጨት ላይ በመውጣት በላዩ ወድቀው ሞቱ፤ ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምም ከአእላፍ መላእክት ጋር መጥታ “የእኔና የልጄ ወዳጅ ሰላምታ ይድረስህ” አለችው። ከበድኑም ቃል ወጥቶ “የሰማይና የምድር ንግሥት እመቤቴ ሰላምታ ይገባሻል” አላት፡፡ እርሷም በከበሩ እጆቿ ዳሥሣ ከሞት አስነሣቸው።

ቅዱስ አባታችን አቡነ አቢብ ከዚህ ዓለም ድካም የሚያርፉበት ጊዜ ሲደርስ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ በእጁ ልዩ የሆኑ አክሊሎችን የሚያበሩ ልብሶችንም ይዞ ተገለጠለትና እንዲህ አላቸው፤ “ወዳጄ አቢብ ሆይ፥ በማያልቅ ተድላ ደስታ ደስ አሰኝህ ዘንድ ወደ እኔ ና፤ ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ እኔ ኃጢአቱን አስተሠርይለት ዘንደ በራሴ ማልኩልህ፤ ወይም ለተራቆተ የሚያለብሰውን፣ ለተራበም የሚያጠግበውን፣ ለተጠማ የሚያጠጣውን፣ የገድልህን መጽሐፍም የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውንና የሚሰማውን፣ በጸሎትህም የሚታመኑትን ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እምራቸዋለሁ፤” ይህንም ብሎ አፋቸውን ሳማቸው፤ በደረቱም ላይ አድርጎ ወደ አየር አወጣቸው፤ የመላእክትንም ምስጋና በሰማች ጊዜ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች፤ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ገባች።

እነሆ ሰማዕቱ አቡነ አቢብ ምእመናን በሚቀምሱት የዕለት ምግብ አማካኝነት በነፍስም በሥጋም እንዲድኑ አስገራሚ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደተቀበሉ የሚናገር የገድል ተአምራታቸው ይህ ነው፡- ብዙዎች ስማቸውን ጠርተው በሚቀምሱት ምግብ አማካኝነት ከተለያዩ በሽታዎች የተፈወሱ አሉ፡፡ ይህ ቃል ኪዳናቸው ለሁላችን ይደረግልን ዘንድ ከመመገባችን አስቀድሞ የእግዚአብሔርን ስም እንጥራ (አቡነ ዘበሰማያትን ማለቱ ነው፡፡) ከተመገብን በኋላም የዕለት ምግባችንን ስለሰጠን እግዚአብሔርን እናመስግን፡፡ ዘወትር ከተመገብን በኋላ ሦስት ጊዜ ‹‹ስለ ወዳጅህ ስለ አቡነ አቢብ›› እያልን ሦስት ጊዜ እንቅመስ፡፡ አስቀድሞ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአቡነ አቢብ ተገልጦላቸው ‹‹…ወዳጄ አቢብ ሆይ! የሰውን ልጅ ለማዳን የተቀበልኩትን ሕማማተ መስቀል እያሰብህ ይህንን ሁሉ ገድል ፈጽመሃልና ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ?›› አላቸው፡፡ ንዑድ ክቡር ቅዱስ አባታችን አቡነ አቢብም ‹‹ጌታዬ አምላኬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! መቼም ሰው ሁሉ ሳይመገብ አይውልም፤ አያድርምና በተመገበ ጊዜ ስሜን ጠርቶ የተማጸነውን ማርልኝ›› አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አባታችን አቡነ አቢብ ለሰው ልጆች ያላቸውን ፍቅር ካደነቀ በኋላ ‹‹…ከማዕድ በኋላ ስብሐት ተብሎ የተረፈውን በእንተ አቢብ ብሎ ሦስት ጊዜ የተመሰገበውን ሰው ሁሉ እምርልሃለሁ›› በማለት ታላቅ የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡

ያልተጠመቀ አረማዊ አሕዛብም እንኳን ቢሆኖ ‹‹ስለ አቡነ አቢብ›› ብሎ ከተማጸነ ጌታችን ያንን ሰው ወደ ቀናች የእምነት መንገድ ሳይመራወና በንስሓ ሳይጠራው በሞት እንደማይወስደው ለአባታችን ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ለማዳን ትንሽ ምክንያትን የሚፈልግ ያለ ምክንያትም የማያድን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ እስከ ዘለዓለም ድረስ ይክበር ይመስገን! ሰው ተመግቦ እንኳን መዳን እንዲችል ይህን ድንቅ ቃል ኪዳን ለአባታችን ሰጥቷቸዋልና በየቀኑ በዚህ ቃል ኪዳን እንጠቀምበት፡፡ ተመግበን ከጨረስንና ስብሐት ካልን በኋላ ሦስት ጊዜ ‹‹በእንተ አቡነ አቢብ›› ብለን እንቅመስ፡፡ በጥቅምት ፳፭ ቀን በዓመታዊ የዕረፍት በዓላቸው ታስበው የሚውሉት ጻድቁና ሰማዕቱ አቡነ አቢብ የቃል ኪዳናቸው ረድኤት በረከት ይክፈሉን!

(ምንጭ፡ደብረ ሰላም ቃጭልቃ አቡነ አቢብ ገዳም ያሳተመው ገድለ አቡነ አቢብ፣ ገጽ ፻፭)

በእንተ ቅዱሳን ኀሩያን)

ርእሰ ዲያቆናት ወቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ

ጥቅምት ፲፯፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ርእሰ ዲያቆናት ወቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ የሹመቱ መታሰቢያ ጥቅምት ፲፯ ነው፡፡ ከሰባቱ ዲያቆናት መካከል ቀዳምት የሆነው ቅዱሱን የመረጡት እራሳቸው ሐዋርያት ናቸው፡፡ የስሙ ትርጓሜ “ፋና፣ አክሊል” የሆነ የእግዚአብሔር ልዩ ባለሟል፣ አጋእዝተ ዓለም ሥላሴን በክብሩ ለማየት የበቃ ሰማዕትም ነው፡፡

ፍጹም እምነት ያለው፣ መንፈሳዊ ቅናትን የተመላ እንዲሁም ተአምር የማድረግ ጸጋ የነበረው ቅዱስ ነበረ፡፡ በዘመኑ የሚያስተምራቸው ትምህርቶችም ሆነ ንግግሮቹ መንፈስ ቅዱስ የመላባቸው ስለነበሩ በመቃወም ይከራከሩት የነበሩትን ሁሉ መልስ አሳጥቶአቸዋል፡፡ በዚህም ነበር በቅንአት ተነሣሥተው በሐሳት ምስክር የከሰሱት፡፡ በኋላም ተፈርዶበት በድንግይ ተወግሮ የሰማዕትነትን አክሊል በተወለደበት ዕለት ጥር አንድ ቀን ተቀብሎአል፡፡

የቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት፣ አማላጅነት እና ተራዳኢነት አይለየን፤ ከበዓሉ በረከት ያሳተፍን፤ አሜን!

አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ

ጥቅምት ፲፫፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

በከበረች ጥቅምት ፲፬ ቀን አቡነ አረጋዊ ተሠወሩ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የመጡት ቅዱስ አባታችን ዘጠኙ ቅዱሳን የእግዚአብሔር አገልጋዮችን ኢትዮጵያ እስኪደርሱ ድረስ በመንገድ የመሯቸው እርሳቸው እንደሆኑ መጽሐፈ ስንክሳር ይገልጻል፡፡

የዘንዶ ጅራት በመያዝ ከደብረ ዳሞ ተራራ ላይ የወጡት፣ በዚያም ፍጹም ገድላቸውን የፈጸሙት ቅዱስ አባታችን አቡነ አረጋዊ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብለዋል፡፡ ስማቸውን ለሚጠራና መታሰቢያቸውን ለሚያደርግ እንደሚማርላቸውም ተነግሯቸዋል፡፡

ከመምህራቸው ከአባ ዻኩሚስ በተማሩት መሠረትም ለልጆቻቸው መነኰሳት ሥርዓተ ማኅበርን ሠርተውላቸዋል፡፡ ከዚያም በእግዚአብሔር ቸርነት እንደ ነቢያቱ ሄኖክና ኤልያስ ከዚህ ምድር ተሠውረዋል፡፡

የቅዱስ አባታችን አቡነ አረጋዊ ጸሎት፣ አማላልጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!!!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ጥቅምት ፲፬

የባሕረ ሐሳቡ ደራሲ ቅዱስ ድሜጥሮስ

ጥቅምት ፲፩፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ከምንባባት ዐውድ

አካሄዱን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ፣ እርፍ አርቆ፣ ድኮ ታጥቆ፣ ወይን አጽድቆ የሚኖር፣ የቀለም ትምህርት ብዙም ያልነበረው ሰው ድሜጥሮስ በቅን ልቡናው መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት ባሕረ ሐሳብን የደረሰ ቅዱስ ሰው ነው፡፡ ጌታ ባረገ በ፻፹(180) ዓ.ም የእስክንድርያ መንበር ዐሥራ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ተሹሟል። በሹመቱም ጊዜ በትህርምት ኗሪ ነውና አሁን አጽዋማትንና በዓላትን የምናወጣበትን ይህን የቁጥር ዘመን ባሕረ ሐሳብ ተገልጾለት ደርሶታል፤ ተናግሮታል፤ ተናግሮት ብቻም አልቀረም፤ ለሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ለሮሙ በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ሥር ለነበረው ለአባ ፊቅጦር፣ በቅዱስ ዮሐንስ መንበር ሥር ለነበረው ለኤፌሶኑ ሊቀ ጳጳስ በቅዱስ ጴጥሮስ ካልእ ሥር ለነበረው ለአንጾኪያው መንበር ለቅዱስ መክሲሞስ ዐራተኛ፣ ለኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ለአባ አጋብዮስ ልኮላቸዋል። እነርሱም ሐዋርያት ከአስተማሩት ትምህርት ጋር አንድ ቢሆንላቸው ተቀብለው ኑረውበታል፤ አስተምረውበታል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፬፥፵፩፣ ስንክሳር ኅዳር ፲)

ባሕርን ዘመን ሲል የት ይገኛል ቢሉ “እስመ በመዳልው ተደለወ ዓለም ወበመሥፈርት ሰፈራ ለባሕር፤ ዓለም በመስፈሪያ ተሰፍሯልና ባሕርንም በመስፈሪያ ሰፈራት” እንዳለ ዕዝራ (ዕዝራ ፪፥፴፯) ቅዱስ ዳዊትም “ዛቲ ባሕር አባይ ወረሐብ፤ ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት” ብሏል፡፡ (መዝሙረ ዳዊት ፻፫፥፳፭) ሐሳብንስ ቁጥር ሲልስ የት ይገኛል ቢሉ ለትኩነኒ ሐሳበ ብላለች ኦሪት፡፡ ነቢዩ ዳዊትም “ብፁዓን እለ ተሐድገ ሎሙ ኃጢአቶሙ ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኲሎ ጌጋዮሙ፤ መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው” ብሏል፡፡ (መዝሙረ ዳዊት ፴፩፥፩) ይህን የመሠለው ሁሉ ብዙ ነው። አንድም እንዳለ ባሕረ ሐሳብ ይለዋል፡፡ ባሕር አለው ባሕር እስኪለምዱት ያስፈራል። ከለመዱት በኋላ ግን ዘግጦ ጠልቆ ግጫውን ጭንጫውን ይዞ እስከመውጣት ይደረሳል፡። ይህም ባሕረ ሐሳብ እስኪለምዱት ያስፈራል፡፡ ከለመዱት በኋላ ግን በዓላትን አጽዋማትን አወጣጣቸውን ብቻ ሳይሆን ኢይዐአርግ ኢይወርዳቸውን ሠርቀ መዓልታቸው ሠርቀ ሌሊታቸውንም ያሳውቃልና።

ነገር ግን ከእርሱ በፊት አጽዋማት አይጾሙም፤ በዓላት አይውሉም ማለት አይደለም። ከእርሱ በፊት ገና በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ሳሉ ከምእመናን ጋር ጾምን ይጾሙ፣ ትንሣኤንም ያከብሩ ነበር። ጌታ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት የጾመውን ሥጋ ቅቤ አንቅመስ እንጂ እየዋልን እህል ውኃ ብንቀምስ እዳ እንደማይሆን ትንሣኤንም በመጋቢት በ፳፱ (29) ያከብሩ የነበረውን ከእሑድ አይውጣ እንጂ በሚያዝያ ይሁን ተለይቶ የነበረ ሰሙነ ሕማማት በአንድ ላይ እንዲሆን ያደረጉ ሐዋርያት ናቸው።

አበዊነ ሐዋርያት አፍለስዎ ለጾመ አርብዓ ወአስተላጽቅዎ ምስለ ጾመ ሕማማት፤ አባቶቻችን ሐዋርያት ተለይቶ የነበረውን አርባ ጾም ከጾመ ሕማማት ጋር አንድ አድርገውታል” እንዳለ አቡሻክር። አቆጣጠሩን ግን ለስብከተ ወንጌል ይፋጠኑ ስለነበር አንድም ወደፊት ድሜጥሮስ እንደሚነሣ በመንፈስ ቅዱስ አውቀው ለይተው አላስተማሩም። ከሐዋርያትና ከ፸(70) አርድዕት በኋላ የተነሡ መምህራንም እንዲሁ ከዘመን ብዛት የተነሣ ዕለቱ ቢጠፋባቸው ዐቢይ ጾምን የጥምቀት ሳኒታ ጥር ፲፩(11) ቀን ጀምረው በየካቲት ፳(20) ቀን ፈጽመው በዓልን ሳይሹ ያከብሩ ነበር። በዓላትን ሲሹ ደግሞ ሰሙነ ሕማማትን በመጋቢት ፳፪(22) ቀን ጀምረው በመጋቢት ፳፰(28) ቀን ፈጽመው በ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ትንሣኤን ያከብሩ ነበር። ከዚህም የተነሣ ዐቢይ ጾም ከእሑድ ውጭ በሌሎችም ቀን ሰኞም ማክሰኞም ይውል ነበር። በዚህ መንገድ ሲያያዝ መጥቶ ከቅዱስ ድሜጥሮስ ደርሷል። ይህም ድሜጥሮስ ከላይ እንዳልነው በሊቀ ጳጳስነቱ  ዘመን ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾምና ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ፣ በዓለ ደብረ ዘይት፣ በዓለ ሆሳዕና፣ በዓለ ትንሣኤና በዓለ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፣ በዓለ ርክበ ካህናትና ጾመ ድኅነት ከረቡዕ፣ በዓለ ዕርገት ከሐሙስ፣ በዓለ ስቅለት ከዓርብ ባይወጡ፣ ባይነዋወጡ ይመኝ ነበር፡፡ እነዚህ በዓላት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነበረበት ዘመን በእነዚህ ቀናት ውለዋልና፡፡

የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነው ብሎ ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረ (ምሳሌ ፲፩፥፳፫)፤ ይህም ቅዱስ ድሜጥሮስ ይህን በጎ ሐሳብ ሲመኝና ሲያስብ ለመንፈስ ቅዱስ የተመኙትን መግለጽ ልማድ ነውና  የታዘዘ መልአክ ወደ እርሱ መጥቶ ነገር በምኞት ይገኛልን? ሱባኤ ገብተህ አግኘው ብሎ ከሌሊቱ ፳፫ (23) ሱባኤ ከቀኑ ሰባት ሱባኤ ግባ” ብሎታል፤ ስለምን “ሌሊቱን አብዝቶ ቀኑን ለምን አሳነሰው” ቢሉ ቀን የታመመ ሲጠይቅ፣ የታሰረ ሲጎበኝ፣ ወንጌል ሲያስተምር ስለሚውል ቀኑን አሳጥሮ ሌሊቱን አስረዝሞታል፡፡ አያይዞም “የሌሊቱንም የቀኑንም ሱባኤ በሰባት እያበዛህ ከ፴ (ሠላሳ) ከበለጠ በ፴ ግደፈው” ብሎታል። እንደሚታወቀው አንድ ሱባኤ ማለት ሰባት ቀናት ናቸው፡፡ ሰባት ጊዜ ሃያ ሦስት መቶ ስድሳ አንድ ይሆናል፡፡ መቶ ስድሳ አንድን በሠላሳ ስንገድፈው/ስናካፍለው/ አምስት ዐውደ ወርኅ ሆኖ ዐሥራ አንድ ይቀራል፡፡ ይህ አበቅቴ ይሁንልህ ብሎታል።

የቀኑን ሰባት ሱባኤ በሰባት ስናባዛው ዐርባ ዘጠኝ ይሆናል፡፡ በሠላሳ ስንገድፈው /ስናካፍለው/ አንድ ጊዜ ደርሶ ዐሥራ ዘጠኝ ይተርፋል፤ ይህንን “መጥቅዕ” ይሁንልህ ብሎታል። በዚህ እየቀመረ በዓላትንና አጽዋማትን አውጥቷል።

የእግዚአብሔር ድንቅ ጥበብ የተገለጠለት ይህ ቅዱስ ሰው ድሜጥሮስ የስሙ ትርጓሜ “መስታወት” ማለት ነው። መስተወት የራቀውን አቅርቦ የረቀቀውን አጉልቶ እንደሚያሳይ እርሱም በባሕረ ሐሳብ ድርሰቱ የራቀውን አቅርቦ የረቀቀውን አጉልቶ ያሳያልና ነው፡፡ አንድም “ፀሐይ” ማለት ነው፡፡ ፀሐይ ጨለማን አጥፍቶ ብርሃን እንደሚሰጥ እርሱም የደነቆረውን ጨለማውን አእምሮ በብርሃን እውቀት ያጠፋዋልና።

ትውልደ ነገዱ ከእስክንድርያ የሆነው ይህ ቅዱስ ሰው አባቱ ደማስቆ ወይም እንድራኒቆስ አጎቱ ደግሞ አርማስቆስ ወይም አስተራኒቆስ ይባላሉ። ሁለቱም በረኃብ ምክንያት ወደ ሞአብ ሀገር ተሰደው ሲኖሩ የልዕልተ ወይን አባት አርማስቆ ሚጠት(መመለስ) ሳይደረግ ዕለተ ሞቱ በደረሰ ጊዜ የልጁን የልዕልተ ወይንን ነገር ከአሕዛብ እንዳያጋባት በመልካም ሥነ ምግባር እንዲያሳድጋት አደራ ሰጥቶት ሞተ። ልዕልተ ወይንም አባቷ ከሞተ በኋላ ከአጎቷ ቤት ከድሜጥሮስ ጋራ በአንድ ላይ አፈር ፈጭተው ውኃ ተራጭተው ዘንባባ ቀጥፈው አደጉ። ሁለቱም ለአካለ መጠን በደረሱ ጊዜ የነበሩበት ቦታ አሕዛብ የበዙበት ምእመናን ያነሱበት ስለነበር ለማን እናጋባቸው ብለው ካወጡ ካወረዱ በኋላ ለአሕዛብ አጋብተናቸው ሕንጻ ሃይማኖት ከሚፈርስ እርስ በእርሳቸው አጋብተናቸው ሕንጻ ሥጋ ቢፈርስ ይሻላል ብለው እርስ በእርሳቸው አጋብተዋቸዋል። ጻድቃን ሳይቀጣጠሩ ይገናኛሉ፤ እንደሚባለው ሁለቱም ፈቃዳቸው አልነበረምና ትዳሩን ካፈረሱ ለሌላ እንዳይድሯቸው አብረው ለመኖር ተስማምተው በአንድ አልጋ ተኝተው፣ አንድ መጋረጃ ጥለው፣ አንድ አንሶላ ለብሰው፣ ወንዶችና ሴቶች በሚተዋወቁበት ግብር ሳይተዋወቁ ፵፰/48/ ዓመት ኑረዋል።

በዚህ ግብርም ሲኖር የሕዝቡ ኃጢአት ተገልጾ እየታየው ሊቆርቡ ሲመጡ “አንተ በቅተሃል ቊረብ፤ አንተ አልበቃህም ቆይ” ባላቸው ጊዜ  በዚህም “በንጹሑ በማርቆስ ወንበር ሚስቱን ይዞ እያደረ ሲሾም ዝም ብንለው ደግሞ እንዲህ ይለን ጀመር” ብለው አምተውታል፡፡

በዚህ ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጾ “ኢትፍቅድ አድኅኖ ርእከ አላ ክሥት ሎሙ ክብረከ ዘሀሎ ማዕከሌከ ወማዕከለ ብሲትከ ከመ ኢይትሀጐሉ ሕዝብ በእንቲኣከ። ሕዝቡ አንተን እያሙ እንዳይጎዱ በአንተና በሚስትህ መካከል ያለውን ግለጽላቸው” ብሎታል። እርሱም “የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነማ ብሎ ሕዝቡን  እንጨት እንዲያመጡ አዘዛቸው። ያን አስደምሮ በእሳት አቃጥሎ ቅዳሴ ገባ፤ ቅዳሴውን ሲጨርስ ልብሰ ተክኖውን እንደለበሰ ማዕጠንተ ወርቁን ይዞ በእሳቱ መካከል ያጥን ነበር። አንድም “ከደመራው ላይ ቁሞ በእሳት አቃጥሉት” አላቸው። “በምን ምክንያት እንሽረዋለን ስንል በፈቃዱ ገብቶ ሊሞትልን ነው” አሉት። እርሱ ግን ምንም ሳይሆነው በመካከሉ እየተመላለሰ ያጥንና ይጸልይ ጀመር። ሚስቱንም ከምቅዋመ አንስት ከመካነ ደናግል ነበረችና አስጠርቶ ስትመጣ “ስፍሒ አጽፈኪ፤ ልብስሽን ዘርጊ” ብሎ ከፍሕሙ በእጁ እያፈሰ ከአጽፋ ላይ አደረገላትና አስታቅፎ “እየዞርሽ ተናገሪ” አላት፡፡ እርሷም ሦስት ጊዜ እየዞረች ፵፰ /48/ ዓመት ሲኖሩ በልማደ መርዓት ወመርዒዊ እንደማይተዋወቁ ገለጸችላቸው። ሕዝቡም ከጫማው ሥር ወድቀው “ኅድግ ለነ አበሳነ፤ አባታችን በድለናል ይቅር በለን” አሉት። እርሱም “ይኅድግ ይፍታሕ፤ እግዚአብሔር ይፍታ” ብሎ ናዟቸዋል፤ ኑዛዜም የተጀመረ በዚህ ጊዜ ነው።

የአባታችን ቅዱስ ድሜጥሮስ ጸሎት፣ ምልጃ እና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!

 

 

 

 

 

 

 

የንሂሳው ኮከብ

ጥቅምት ፬፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

በዐፄ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት፣ ዐሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የመጡት ግብጻዊው ቅዱስ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የትውልድ ስፍራቸው በላዕላይ ግብጽ ንሂሳ እንደሆነ ገድላቸው ይጠቅሳል፡፡

አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ የተባሉት ወላጆቻቸው እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ሰዎች እንደነበሩ ሆኖም ልጅ አጥተው ፴ (ሠላሳ) ዘመን ሲያዝኑ መኖራቸውንም ታሪካቸው ያነሣል፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም እናታቸው አቅሌሲያ ቤተ እግዚአብሔር ገብታ ከሥዕለ ሥላሴ ሥር ወድቃ ስትማጸን ክብሩ ከሰማይ ከፍታ የሚበጥ ልጅ እንኪ ተቀበይ የሚል ድምጽ ሰማች፡፡ ‹‹ሥልጣኑ ከሰማይ ከፍታ ከፍ የሚል ንጽሕናው ከሚካኤል ከገብርኤል የሚተካከል ክህነቱ እንደ መልከጼዴቅ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ነቢይ ኤልያስ የሆነ ልጅ እንቺ ተቀበይ›› አላት፡፡ አቅሌስያም በመጋቢት ፳፱ ቀን ፀንሳ በታኅሣሥ ፳፱ ቀን ደም ግባቱ እጅግ የሚያምር ወንድ ልጅ እንደወለደች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል መጥቶ ‹‹የዚህ ልጅሽ ስሙ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን›› አላት፡፡ ወዲያውም ሕፃኑ ተነሥቶ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሦስት ጊዜ ሰገደ፡፡ ዳግመኛም ‹‹ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጣኸኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን›› አለ፡፡

አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተፀነሱት መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን፣ የተወለዱት ደግሞ ታኀሣሥ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ)  ነው፡፡ አባታችን ዓይን በገለጡ ጊዜ ከሚታይ ነገር ላይ እንዲያርፍ እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ ተነሥተው «ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ዘዓውፃእከኒ እምጽልመት ውስተ ብረሃን» ብለው አመስግነዋል። አባታችን ለአምላክ ሰግደው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ካመሰገኑ በኋላ እናታቸው አላቀፈቻችውም፤ ጡትም አልጠቡም፡

ጻድቁ አባታችን አኗኗራቸው እንደ መላእክት በምድረ በዳ የነበር፣ በዝቋላ ተራራ ባለው ባሕር ውስጥ ፻ (መቶ) ዓመት ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ሰዎች ምሕረትን የለመኑና ምሕረትን ያሰጡ ቅዱስ ናቸው፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከ፭፻ (አምስት መቶ ዓመታት) በላይ በዚህ ምድር ላይ መኖራቸውንና ከትግራይ እስከ ሸዋ ባለው ክፍል ተዘዋውረው ማስተማራቸውን ገድላቸው ያትታል፡፡ በዚህም ምክንያት ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስንና ምድረ ከብድ ገዳማትን መትከላቸውን ታሪካቸው ያሳያል፡፡ ያረፉት በዐፄ ሕዝብ ናኝ ዘመን መጋቢት አምስት ቀን ነው፡፡ የምሕረት ቃልኪዳን የተቀበሉት ደግሞ ጥቅምት አምስት ቀን ነው፡፡ የከበረው በድነ ሥጋቸውም በምድረ ከብድ ይገኛል፡፡ ጻድቁ በትግራይ አቡዬ፣ በአማራው አቡነ፣ በኦሮሞዎች ዘንድ ደግሞ አቦ በመባል ይታወቃሉ፡፡

የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎታቸው ይማረን!

ምንጭ፡ – ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ፲፱፻፺፪ .

 

የእምነት አርበኛ

መስከረም ፳፰፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

ጽኑ ሰማዕት የእምነት አርበኛ፣ ጠላትን ተዋጊና ድል አድራጊ እናታችን ቅድስት አርሴማ የሰማዕትነት አክሊል የተቀበለችበት የከበረች በዓል መስከረም ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ይከበራል፡፡

እጅግ መልከ መልካም የነበረችው ሮማዊቷ ዕንቁ ከልጅነቷ ጅምሮ ራሷን በድንግልና ሕይወት ጠብቃ የኖረች ቅድስት እንደነበረች ታሪክ ይነግረናል። በዘመኑ ነግሦ የነበረው ከሀዲው ድዮቅልጥያኖስም መልኳ ውብ የሆነች ድንግል ሊያገባ ፈልጎ ከየሀገራቱ ቆንጆ መርጠው ያመጡለት ዘንድ አገልጋዮቹን አዘዛቸው፡፡ እነርሱም በፍለጋቸው በሮሜ አገር ባለች ቤተ ክርስቲያን ቅድስት አርሴማን በማግኘት ሥዕሏን ሥለው ለንጉሡ ላኩለት፡፡ እርሱም በእጅጉ ተደስቶ እንዲያመጧት በማዘዝ ወደ ሰርጉም እንዲመጡ ለመኳንንቱ ላከ፡፡ እርሷና አብረዋት የነበሩትም ደናግል ይህነን በሰሙ ጊዜ በማዘን ድንግልናቸውን ይጠብቅላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በመለመን ከሮም ተነሥተው በስውር የንጉሥ ድርጣድስ ግዛት ወደነበረችው ወደ አርመን ሸሽተው ሄዱ፡፡

ቅድስት አርሴማም ወደ አርመንያ ሀገር በገባች ጊዜ ከሃድያኑ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን የሚያምኑትን ክርስቲያኖችን ላይ መከራን ሲያጸኑባቸው ተመለከተችና አምላካችን ክርስቶስ “እኔ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን የማምን ክርስቲያን ነኝ” በማለት መሰከረች፡፡ የመልኳን ደም ግባትም በማየት ንጉሥ ድርጣድስም ለራሱ ስለተመኛት አምላክን እንድትክድ በብዙ ሽንገላን ሊሸነግሏት ቢሞክሩም አልሆነላቸውም፤ ፈርታ ትክዳለችም ብለው በማሰብ ክርስቲያኖች ለአናብስት ወደሚጣሉበት አደባባይ በመውሰድ የተራቡ አናብስትን በላያቸው ለቀቁባቸው፤ ቅድስት አርሴማ በዚህ ጊዜ ወደ አምላክ ጸሎት አደረገች፤ ድንቅ በሆነው ተአምሩም እግዚአብሔር አናብስቱ ወደ ቅድስቷ ሳይሆን  ወደ ንጉሡ ወታደሮች በመወርወር ብዙዎችን እንዲገድሉ አደረገ፤ በኋላም ተንበርክከው ሰገዱላት፡፡

ንጉሡም በሌላ መንገድ የቅድስት አርሴማን ሐሳብ ለማስቀየርና በግድ ለጣዖታቱ እንድትሰግድ ለማድረግ አሳስሮ አማልክቱ ወዳሉበት ቤተ ጣዖት ወሰዳት፤ ይህን ጊዜ በመስቀል ምልክት ብታማትብ በጣዖታቱ ላይ አድረው ሰዎችን የሚያስቱ አጋንንት እየጮኹ ሲወጡ ጣዖታቱ በመላ እየተሰባበሩ ወድቁ፤ ዳግመኛም እስር ቤት አስገብቶ ሊያስርባት ቢጥርም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ኅብስትን መገባት፡፡ ቀጥሎም ንጉሡ ወዳለበት እየጐተቱ ወስደው ሲያቆሟት ንጉሡ ይዞ ወደ እልፍኙ ሊያስገባት ከአደባባይ ተነሥቶ ድንግል አርሴማን በያዛት ጊዜ ቅድስቷ በላይዋ ላይ ባደረው የእግዚአብሔር ኀይል በምድር ላይ ጣለችው፤ ያን ጊዜ በንዴትና በአፍረት አገልጋዮቹን ራሳን እንዲቈርጡ አዘዛቸው። በዚህ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምን አስከትሎ ተገለጸላት። ስሟን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ምሕረትን እንደሚያደርግ ቃል ኪዳንን ገባላት፡፡ በክርስቶስ ፍጹም ፍቅር፣ በእምነት ጽናትና ተጋድሎ ዕጹብ ድንቅ የሆነው ገድሏን ፈጽማ አንገቷን በመሰየፍ መስከረም ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጅታለች።

የቅድስት አርሴማ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፤ በጸሎቷ ይማረን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

የኒቂያ ጉባኤ

መስከረም ፳፪፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

የአርዮስ ክህደት በተስፋፋበት በ፫፻፳፭ ዓ.ም የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት የማይቀበሉ መናፍቃን ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ጊዜውም ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ‹‹አብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ፤ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ! አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!›› የሚል ዐዋጅ የነገረበት ስለነበር ንጉሡ በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሄድ በየአገሩ ለነበሩ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡

ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ሊቃውንቱ በሱባኤና በጸሎት ከቆዩ እስከ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን ‹‹ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ›› ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ መካከል ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው›› ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም ‹‹ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይሁን›› ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት ፫፻፲፰ቱ የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው /ዘፍ.፲፬፥፲፬/፡፡

፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎችን ደንግገዋል፡፡

የቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!

 

ግሸን ማርያም

መስከረም ፳፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

የግሸን ማርያም ደብር መመሥረት ከግማደ መስቀል ጋር የተያያዘ ዋነኛ ምክንያት አለው፡፡ ግማደ መስቀሉ ከእስክንድርያ የገባው መስከረም ፲ ቀን ቢሆንም ኢትዮጵያ ‹‹ግሸን አምባ›› የገባበት፣ መቅደስ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውና ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለመላው ኢትዮጵያ በጽሑፍ በመዘርዘር የገለጹበትም መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡

በየዓመቱ መስከረም በባተ በ፳፩ኛው ቀንም በግሸን ደብር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ከበረከተ መስቀሉና ከቅዱሳን ዐፅም በረከት ለማገኘት ከየክፍለ ሀገራቱ እየመጡ ያከብራሉ፡፡ ምእመናንም በግሸን ማርያም ለመገኘት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይሄዳሉ፡፡ ኃጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ሁሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ‹‹ጤፉት›› በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ከበረከተ መስቀሉ ያሳትፈን፤ አሜን!!!

 

መስቀል

መስከረም ፲፬፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

ፍጹም ድንቅ የሆነው የጌታ ፍቅር የተገለጸበት፣ ሰላም የተበሠረበት፣ የነጻነታችን መገለጫ፣ የድኅነታችን መረጋገጫ ቅዱሱ መስቀል የተገኘበት ዕለት የከበረ ነውና በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ የመጀመሪያው ሰው አዳም በበደሉ ምክንያት ዕዳውን ይከፍለለት ዘንድ ሰው ሆኖ በሞቱ ሕይወትን የሰጠን አምላክ በመስቀል ተሰቅሎ ስለሆነም የመስቀሉ ነገር ለክርስቲያኖች ብዙ ትርጒም አለው፡፡

ለሰው ዘር በሙሉ በተገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ጌታችን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ፣ ሰው ሆኖ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ድኅነትን ለሰው ልጆች ሰጥቶ፣ በመስቀሉ ተጣልተው የነበሩ ሰባቱን መስተፃርራን (ሰውና እግዚአብሔርን መላእክትና ሰውን፣ ነፍስና ሥጋን፣ ሕዝብና አሕዛብን) አስታርቋል፡፡

በሐዲስ ኪዳን መስቀል የመዳን ምልክት መሆኑ የተረጋገጠበት በክርስቶስ ደም የተቀደሰ፣ የጠብ ግድግዳን ያፈረሰ፣ ቅድስናና ክብር ያለው የአበው ተስፋ የተፈጸመበት፣ ሰው ከውድቀቱ የተነሣበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር … እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ›› (መዝ. ፸፫፥፲፪) እንዳለው መድኃኒት የሆነው አምላካችን በመስቀሉ አዳነን፡፡ (ዮሐ. ፲፱፥፲፯፣ኤፌ. ፪፥፲፮፣ ቆላ. ፩፥፳)

ከበዓሉ በረከት ይክፈለን፤ አሜን!!!