Capital “C”

በድንቅነሽ ጸጋዬ

ሰኔ 1/2003 ዓ.ም.     

capital C

 
ዛሬ ደግሞ እንደ ሙአለ ሕፃናት ተማሪዎች Capital “C”ን እዚህ ምን አመጣት ትሉኝ ይሆናል፡፡ እኔም የትኩረት አቅጣጫዬ ስለ Capital “C” እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለ ትምህርት ሲነሣ ወላጆቻችን ሀ ብለው የጀመሩት በተለምዶ ቄስ ትምህርት ቤት ብለን በምንጠራቸው ሲሆን፥ ትምህርቱም ይሰጥ የነበረው የሁሉም አፍ መፈቻ ቋንቋ ባይሆንም አብዛኛው ሰው ይግባበት በነበረው የአማርኛ ቋንቋ ፊደል ሀሁ፣ አቡጊዳ፣ መልዕክተ ዮሐንስ ዳዊት…ወዘተ፥ ዘመናዊውን የአስኳላ ትምህርት ከመቀጠላቸው በፊት፥ እንደተማሩ እናውቃለን፡፡ ለዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዋነኛ የትምህርት ማዕከል ሆና አገልግላለች፡፡
ስማቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የገነነው የእንግሊዙ “ኦክስፎርድ” እና የአሜሪካው “ሃርቫርድ” ስመ ጥር ዩኒቨርሲቲዎች መነሻቸው ከቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ በዛሬው አኳኋን ተደራጅተውና በዘመናዊ ትምህርት ተውጠው ከመገኘታቸው በፊት የሃይማኖት ትምህርት ማሰልጠኛ ማዕከላት ነበሩ /የካቶሊክም ቢሆኑ/፡፡ ከዚህ የምንማረው ቁም ነገር፥ ዓለም ለደረሰበት የሥልጣኔ ቁንጮ የመድረስ ዋዜማውና መፍትሔው በሌሎች ላይ መንጠልጠል ሳይሆን በነባሩ /የራስ/ እሴት መሠረትነት ላይ ማነጹ እንደሆነ ነው፡፡ ለረጅም ዘመናት አገራችንን የመሩት ምሁራን ነገሥታቱና በየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የነበሩ ቁልፍ ሰዎች መገኛቸው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንደነበርም አይካድም፡፡
 
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፥ በየትኛውም አገር ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲማሩ ለትምህርት ያላቸው ፍላጎትና ተቀባይነት ብሎም የመረዳት ደረጃ ፈጣን ይሆናል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለቋንቋው እድገትና ተተኪ ለማፍራት የሚያደርገው አስተዋጽኦ ቀላል አይሆንም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም ለአፍ መፍቻ ቋንቋ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት እናገኛዋለን፡፡ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል በመጀመሪያ የተጻፈው ወንጌላውያኑ እንደተሰማሩበት የስብከት ቋንቋ፥ ቅዱስ ማቴዎስ በምድረ ፍልስጥኤም በዕብራይስጥ፤ ቅዱስ ማርቆስ ለሮማውያን በሮማይስጥ፤ ቅዱስ ሉቃስ ለመቄዶንያ በጽርዕ እና ቅዱስ ዮሐንስ ለኤፌሶን በዮናናውያን ቋንቋዎች መሆኑን እንረዳለን፡፡
በተጨማሪም ሐዋ.2÷1 እንደምናገኘው ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በገለጠላቸው 72 ቋንቋዎች ከተለያየ ሀገር ለበዓል የተሰበሰቡትን ሕዝቦች በየሀገራቸው ቋንቋ ወንጌልን ስላስተማሯቸው በዕለቱ 3000 ሰዎች አምነው ተጠምቀዋል፡፡ ይህም ሰው በአፍ መፍቻ ቋንቋው ሲማር ለመረዳት እና ወደ ተግባር ለመለወጥ ፈጣን እንደሆነ ያረጋግጥልናል፡፡

ሐዋርያዊት እና ዓለም አቀፋዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ለአፍ መፍቻ ቋንቋ ትኩረት በመስጠት ሁሉም ወንጌልን ተምረው ከሥላሴ ልጅነትን አግኝተው መንግሥተ እግዚአብሔርን እንዲወርሱ ባላት አቅም በሁሉም አህጉረ ስብከቶች በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡ እኛስ ልጆቻችንን እንዴት እያስተማርናቸው ነው? በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው? ቢያንስ ከሀገርኛ ቋንቋዎች በአንዱ? ወይስ ጥሩ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንዲሁኑ ከማሰብ? አብዛኛው ባለሀብትም/የትምህርት ቤት ባለቤቶች/ የወላጆች አስተሳሰብ ስለገባቸው ደረጃውን ባይጠብቅም የትምህርት ቤቱ ስም በእንግሊዝኛ ሲሆን ኢንተርናሽናል የሚል ተጨምሮበት፣ ማስታወቂያቸው በውጭ ዜጋ መሆን ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ ልክ ነዋ! በአገርኛ ቢጻፍ ማን ትኩረት ይሰጠዋል፡፡

ልጆቻችን በአፍ መፍቻቸው እየተማሩ ሌሎች የሀገራችንንም ሆነ የውጭ ቋንቋዎች ቢችሉ አይጠቅምም ባይ አይደለሁም፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየሆነ ያለው ግን “የራስን ጥሎ” በአብዛኛው ትምህርት የሚጀምሩበት ቋንቋ እንግሊዘኛ መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ ምን ችግር አለው የሚል አይጠፋም! ከአመታት በፊት የወንድሜን ልጆች ት/ቤት ልናደርስ እየሄድን የያዝኩትን መፍሔት ተቀብላ በፍጥነት Capital “C” አለችኝ፤ “ሐመር” ከሚለው ውስጥ “ር”ን ነጥላ በጣቷ እያመለከተችኝ፡፡ “ሐ” እና “መ”ን ግን እንደማታውቃቸው ስትገልጽልኝ በጣም ባዝንም አልፈረድኩባትም፡፡ A-for Apple, B-for Banana…. አየተባለች እንጂ በአፍ መፍቻዋ ፊደል እንድትቆጥር ከቤተሰብም ሆነ ከትምህርት ቤት እድል አላገኘችም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ብትሆንም የአማርኛ ውጤቷ እንደሌላው ትምህርት የሚደነቅ አይደለም፡፡ ታናሽ ወንድሟም ቢሆን የዚሁ ችግር ተጠቂ ስለሆነ በጥናት ወቅት የአባቱን እርዳታ የሚጠይቀው የአፍ መፍቻ ቋንቋው ለሆነው ነገር ግን ብዙም ለማይረዳው ለአማርኛ ነው፡፡ አንድ ቀን ነው “አባቢ ሐረግ ምን ማለት ነው?” አለው፡፡ አባትም የቻለውን ያህል ገለጸለትና በደንብ የተረዳ ስላልመሰለው በእንግሊዘኛ “Phrase እንደማለት” ሲለው ፈገግ ብሎ “ነው እንዴ” አለ! ይገርማል አማርኛን ለማስረዳት በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ማለት ነው፡፡
ሌላ ልጨምርላችሁ በመዲናችን ውስጥ ካሉ ስመ ጥር ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች በአንዱ የ5ኛ ክፍል መምህርት ጓደኛ አለችኝ፡፡ ተምሮ መፈተን፥ አስተምሮ መፈተን ያለነውና አማርኛ ትምህርት ልትፈትን ወደ ክፍል ዘለቀች ከተማሪዎቹ አንዱ ፈተናውን ተቀብሎ ”ጀምሩ“ ሲባል “ሚስ አልፈተንም” ብሎ እርፍ፡፡ “ለምን?” ሚስ ጠየቀች “አስኪ ተመልከችው ስትራክቸሩ /የፊደሉ ቅርጽ/ ሲያስጠላ” አላት፡፡ በዚህ አቋሙ በመጽናቱ ሚስም ሳታነብ፣ እሱም ሳይፈተን ቀረላችሁ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “የአማርኛ ፊደላት በዝተዋልና ይቀነሱ” የሚሉ አስተየየቶች መነሣታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ዛሬ የፊደል ቅርጻቸው ያስጠላል ያሉን ሕፃናት ነገ ከነጭራሹ አያስፈልጉንም ላለማለታቸው ምን ያህል እርግጠኞች ነን? ቅኝ ብንገዛ ኖሮ እንግሊዝኛ እንችል ነበር ብለው በቁጭት የሚናገሩ ወገኖች እንዳሉም ባይዘነጋ፡፡ ይህን ሲሉ ግን ጣሊያን በኢትዮጵያ በነበረችባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ አንድም ጣልያንኛ ቃል ያላወቁትን አስተውለዋል? አሁንስ ቢሆን በተዘዋዋሪ የአስተሳሰብ ቅኝ ተገዢዎች መሆናቸውንስ?
የዛሬ ሕፃናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች መሆናቸው ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የሀገራችን ባሕል ታሪክ እና የማንነታችን መገለጫ መዛግብቱ የተጻፉት ደግሞ በግዕዝ፣ በአማርኛ እና በሌሎች የብሔር ብሔረሰብ ቋንቋዎች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ሕፃናቱ የሀገራቸውን ባሕል፣ ታሪክ ማንነት ለመረዳት በውጭ ቋንቋ ተተርጉሞ ካልመጣ ላያነቡ ነው? ስለ እኛ በውጭ ቋንቋዎች የተጻፉትስ ምን ያህል ሚዛናዊ ሆነው ማንነታችንን ይገልጻሉ?
በሀገር ውስጥ ካሉ ሕፃናት ይህን ከተመለከትን በውጭ የኑሮ ውጥረት በበዛበት ቤተሰብ ተከታትሎ ባሕላቸውን፣ ታሪካቸውን በአጠቃላይ ማንነታቸውን እየተነገሩ ያላደጉ ሕፃናት እንዴት ይሆኑ? ይህን ስል ግን ባላቸው የተጣበበ ሰዓት በየቤታቸው እና በየአብያተ ክርስቲያናቱ ፊደል የሚያሰቆጥሩ ባሕላቸውና ታሪካቸውን የሚያስተምሩ መኖራቸውን ሳልዘነጋ ነው፡፡
ሐሳቤን ለማጠቃለል ያህል ወላጆችስ ይህ ጉዳይ አሳስቦን ያውቃል? ወይስ ጥሩ የውጭ ቋንቋ ስለተናገሩልን በቃ የዕውቀት ዳር የደረሱልን መስሎን ዝም ብለን ተቀምጠናል? የሚረከቧትን ሀገር ታሪክ፣ ባሕልና ማንነት የማያቁ ተተኪዎች እያፈራን መሆናችንንስ አስበነው እናውቃለን? እኔ ግን “ር”ን Capital “C” ስትለኝ በሁኔታው አዝኜ ዝም ባልል ኖሮ “ዘ”ን ኤች፣ “ረ”ን ኤል፣ “ጠ”ን ስሞል ኤም፣ “ዐ”ን ኦ፣ “ተ”ን ስሞል ቲ፣ “ሀ”ን ዩ፣ “ሠ”ን ደብልዩ ወዘተ ልትለኝ እንደምትችል አልጠራጠርም፡፡