ጋብቻና ጾታ

ክፍል አራት

ዲያቆን ዘሚካኤል ቸርነት
ጥር ፳፮፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

የክርስቲያናዊ ጋብቻ መነሻውም መድረሻውም እግዚአብሔር ነው፡፡ በቅዱስ ጋብቻ ሁለቱ ወንድና ሴት በቅዱስ ቊርባን አንድ ይሆናሉ፡፡ መንግሥቱን ከሚያወርሰን ጋር ኪዳን ሳንገባ ጋብቻን ብንጀምር እንደ ብሉይ ኪዳን ዓለማዊ፣ ምድራዊ፣ ሥጋዊ ልጅ ለመውለድ፣ የፍትወት ፈቃድን ለመፈጸም ወይም ለመረዳዳት ብቻ ዓለማውን ያደረገ ይሆናል፡፡ በክርስቲያናዊ ጋብቻ ግን እነዚህ ራሱ እግዚአብሔር የሚሰጠን ስጦታዎች ሲሆኑ በእምነታችን ጸንተን በበጐ ምግባር ከኖርን ደግሞ ሰማያዊ መንግሥቱን እንወርሳለን፡፡

በአምላካችን እግዚአብሔር ፈቃድ ያልሆነ ጋብቻ ግን ለመንግሥተ ሰማያት (ለሚቀጥለው ሕይወት) ስንቅ የማይሆን፣ በሞት የሚፈጸም የሚዘጋ የሚደመደም፣ ከመቃብር የማይዘል ይሆናል፤ በዚህም ሒሳብ የጋብቻ ግቡ መሞት ይሆናል፡፡ ይህም ለመሞት መኖር፣ ለመሞት መጋባት፣ ለመሞት መውለድ፣ ለመሞት መረዳዳት ለመሞት መተጋገዝ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር በኪዳኑ ውስጥ ሲኖር ግን ኪዳኑ ዓላማው ከሞት ባሻገር እና ሙሉ እንዲሆን ያደርገዋል፤ ሕይወት ይሰጠዋል፡፡ በዚህ እግዚአብሔር በሌለበት የወንድና የሴት ኪዳን ውስጥ ሁለቱም ፍጥረት በመሆናቸው የሚሰጡትም ፍጥረታዊ ጉዳይ ብቻ ይሆናል፤ በጋብቻ ውስጥ የሚሰጥ ፍጥረታዊ ነገር በዚሁ ምድር የሚያበቃ በመሆኑ እንዳያበቃ እግዚአብሔር የግድ አስፈላጊው ይሆናል፡፡

ጋብቻን በሰፊው እንድንረዳው የጋብቻን አጀማመር በጥቂቱ መመልከት ይገባል፡፡ ባለፉት ክፍሎች እንደተመለከትነው ስለ ሰው ልጅ ክብርና ጾታ የተመለከትን ሲሆን አሁን ደግሞ የጋብቻ መሥራች የሆኑትን አዳምና ሔዋንን እንመለከታለን፡፡ አዳምና ሔዋንን ስናስብ ብዙዎቻችን የማናስተውለው ያላቸውን ቅድስና ነው። አዳም ቅዱስ አባታችን ሲሆን ሔዋን ደግሞ ቅድስት እናታችን ናት። አዳምና ሔዋን እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ይታሰባሉ፡፡ አዳምና ሔዋን ስማቸው በስንክሳር ይጠራሉ፤ ይመሰገናሉ፡፡ ስማቸው ስመ ክርስትናችን ሆኖ ሊሰየምልንና የእኛ ጠባቂ ቅዱስ ተደርገው ሊሰጡን ይችላሉ፡፡

ቅዱስ ሄሬኔዎስ እንዲህ ይላል፡- “ግኖስቲኮች አዳም አልዳነም ይላሉ፤ ቤተ ክርስቲያን ግን መዳኑን ትሰብካለች” በማለት ከእነዚያ መናፍቃን እንደምትለይ አስተምሯል።” አዳምና ሔዋን የሚለው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች የተጸውዖ ስም ነው፡፡ አዳምና ሔዋን በጋራ ሰው በሚለው የባሕርይ ስም ይጠራሉ፡፡ ሰው በነፍሱ መልአካዊ ባሕርይና በሥጋው እንስሳዊ ባሕርይ አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ በመሆኑም ሰው የሚለው መጠሪያ ለወንድና ለሴት የወል መጠሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡

መጽሐፍም ይህን ሲያስረዳ “እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡” (ዘፍ.፩፥፳፯) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ሰው የሚለው ለወንድም ለሴትም የሚያገለግል የወል ስም ነው፡፡ አዳም የተፈጠረው ሙሉ ሰው ጎልማሳ ሆኖ ነው፡፡ አዳም ማለትም ሦስት ትርጒሞች አሉት፡፡ ትርጓሜውም፡- ያማረ፣ የተዋበ /መካከለኛ ለቁመና ሲሆን እና ከመሬት የተፈጠረ ማለት ነው፡፡ የሔዋንን አፈጣጠር በተመለከተ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- “እግዚአብሔር አምላክም አለ፤ ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚረዳውን ጓደኛ እንፍጠርለት እንጂ…. እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ላይ እንቅልፍን አመጣ፤ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አጥንቶች አንድ አጥንት ወስዶ ስፍራውን በሥጋ መላው፤ እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። ያን ጊዜም አዳም አለ፤ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፤ ሥጋዋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከባልዋ ተገኝታለችና ሚስት ትሁነኝ…” በማለት እጅግ ግልጽ በሆነ መልኩ የሔዋንን መፈጠር ይነግረናል፡፡

እግዚአብሔር ሔዋንን ሲፈጥር አዳምን ለመፍጠር እንዳደረገው ከምድር አፈር አላነሣም፤ “ከአዳም ጎን አንዲት አጥንት ብቻ ወስዶ ሴት አድርጎ ሠራት፤ ኦሪት ዘፍጥረት የሴትን መፈጠር የሚናገረው ግን ከአዳም ጎን ስትፈጠር የነበረውን ሁኔታ ሲተርክ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ አስቀድሞ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ተብሎ ተጽፏል ወንድና ሴት የሚለው የሚያመለክተው አዳም ሲፈጠር ሔዋን በአዳም ጎን መሆኗን ለመግለጽ ነው፡፡

ከሊቃውንት መካከል ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እንዲህ ይላል፡- “ወንድና ሴት አድርጎ ሠራቸው አለ፡፡ ይህንን ያለውም ሔዋን በአዳም ውስጥ እንደሆነች ለመግለጽ ነው። ይህቺውም ከእርሱ የወጣች የጎኑ አጥንት ናት፡፡ በአካሉ ውስጥ ግን አለችና፡፡ በአካሉ ውስጥ ብቻ ያለችም አይደለም፤ በነፍሱ እና በመንፈሱ ውስጥም ጭምር አለች እንጂ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከአዳም በወሰዳት አጥንት ላይ ቅርጽ ሰጥቶ አስዋባት እንጂ አልጨመረባትምና፡፡ እንግዲህ ለሔዋን የሚስማማ ሁሉ በአጥንት እያለች ከተሠራላት፣ ያቺን አጥንት እንደ አንድ ሰው ቆጥሮ ወንድና ሴት አድርጎ ሠራቸው ቢል ትክክል ነው” በማለት ተርጉሞታል፡፡ አዳም እንስሳት የእርሱ ረዳት እንዳልሆኑ ተረዳ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሔዋንን ረዳት አድርጎ ፈጠረለት::

አዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ እግዚአብሔር አምጥቶበት ከጎኑ አጥንት ሔዋንን ፈጠረ። አዳምና ሌሎች ፍጥረታት (እንስሳት) ከምድር አፈር ተፈጠሩ። ሔዋን ግን ከአዳም ጎን የተገኘች ናት። (፩ኛጢሞ. ፪፥፲፫) አዳም መጀመሪያ ተፈጠረ፤ ከዚያን ሔዋን ይላል። “እግዚአብሔርም አለ፤ ሰውን በመልካችንና በምሳሌያችን እንፍጠር፤….ወንድና ሴትም አድርጎ ፈጠራቸው” የሚለው ኃይለ ቃል ሔዋን በአዳም ጎን ውስጥ በአንድነት መኖሯን፤ ሔዋን ከአዳም ጎን በህልውና ከመገለጧ በፊት መኖሯን ያስረዳናል።”

“አምላካችን እግዚአብሔርም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው” (ዘፍ.፪፥፯) በሚለው ኃይለ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ሊነግረን የፈለገው ሰው የሥጋና የነፍስ ተዋሕዶ አንድነት መሆኑን ነው፤ ይህ ባይሆን ኖሮ ሥጋን ከምድር አፈር አበጀው፤ ከዚያ በኋላ ነፍስን ፈጠረለት ባለ ነበር፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ይህን ጥያቄ ሲመልስ እንዲህ ይላል፤ “አዳም በአካለ ነፍሱና በአካለ ሥጋው መቀዳደም መከታተል አለበትን? ቢሉ የለበትም፤ በአካለ ሥጋውና በአካለ ነፍሱስ መቀዳደም መከታተል ቢኖርበት ንግበር ሥጋ፤ ሥጋን እንፍጠር፤ ወንግበር ነፍስ፤ ነፍስንም እንፍጠር” ባሉ ነበር በማለት በአካለ ሥጋውና በአካለ ነፍሱ መቀዳደም አለመኖሩን ነገረን፡፡

የሰው ልጅ ከእንስሳት በክብር ከፍ ብሎ በስድስተኛው ቀን ተፈጠረ፡፡ ከአፈር ተሠርቶ በተሠራበት ሳይሆን በሠራው እጅ በቅዱስ እግዚአብሔር ከበረ፤ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ “አርአያ የተባለው ነጻ ፈቃዳችን በመሆኑ በፈቃዳችን እግዚአብሔርን ወደ መምሰል እናድጋለን” ይላል፡፡ በዚህም አርአያ እግዚአብሔርን በነጻ ፈቃድ ተርጉሞታል፤ በዚህ ፈቃዳችን ማግባትን መመንኮስንም እንመርጣለን፤ ሁለቱም እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ስለሚያደርሱን፡፡

በጋብቻ ወደ እግዚአብሔር መምሰል ማደግ አለብን፤ መልክ አለን፤ ወንድ እና ሴት የሚባል ይህንን መልክ ወደ እንስሳዊ ጸባይ አለማውረድ ይገባል፤ እንደ ዓለም ሐሳብ በጣም ካወረድነው ወደ እግዚአብሔር መምሰል ማሳደግ ይከብደናል፤ ለሰው የተሰጠው ገነትን ያበጃት ዘንድ ነው፤ ስለዚህ እኛም ትዳራችንን ማበጃጀት እንደሚያስፈልገን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ሠርቶ ቢሰጠን እንኳን የምናበጃጀው ነገር አለ፤ አይደለም ባለቤቱ የሰጠን በዚህ ምድር የተጀመረው ትዳር ይቅርና ገነትን ያበጃት ዘንድ ለሰው ልጅ ሥልጣንን ሰጥቷል፤ ጋብቻን ለማበጃጀት ደግሞ ቀድሞ ትዳርን ማወቅ ይገባል፡፡

የሰው ልጅ ሦስት ዓለማት ውስጥ ይኖራል፡፡ አንዱ ዓለም ለሌላው ዓለም መዘጋጃዎች ናቸው፡፡ የእናቱ ማኅፀን፣ ይቺህ ምድር እና መንግሥተ ሰማያት ናቸው፡፡ የእናት ማኅፀን ተስሎተ መልኩ ተሠርቶ የሚያልቅበት ሲሆን አካላቱን ዓይኑን፣ አፍንጫውን፣ ሌላውንም በዚኛው (የእናቱ ማኅፀን በተባለ ዓለም ውስጥ) አይጠቀመውም፡፡ በዚህ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ብቻውን ነው፡፡ ከዚህ ዓለም መውጣት መወለድ ስንለው ለማኅፀን ግን መሞት ነው፡፡

ሁለተኛው ዓለም የምንኖርባት ዓለም በመጀመሪያው ዓለም በተፈጠሩ አካላቶች እንጠቀማለን፤ በሥርዓት ካልተፈጠሩ አጠቃቀማችን ላይ መገታት ሊገጥመን ይችላል፡፡ እንዴት እንደሚሠሩ ራሱ አናውቅም፤ ለምንበላው ምግብ ዓቅማችን እስከ መዋጥ ድረስ ነው፡፡ ከዚያ ያለፈው እንዴት ሕይወት ሆኖ ደም ውስጥ እንደሚሠራም ሌላው እንዴት ቆሻሻ እንደሚሆን ጭምር አናውቅም፡፡ ለሰው ልጅ በዚህ ምድር ሦስት የተለያዩ ነገሮች ይሰጡታል፤ ዕድሜ፣ ዕውቀትና ሀብት፡፡ እነዚህም ሦስቱ በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው ለቀጣዩ ዓለም የሚያዘጋጁን እንጂ ለወዲያኛው ምድር (ዓለም) አይጠቅሙም፤ ረጅም ዕድሜ ኖርን፣ አጭር፣ ተማርን አልተማርን፤ ደኸየን፤ በለጸግን፤ ለቀጣዩ ዓለም (መንግሥተ ሰማያት) ምን ሊጠቅም?

ይቆየን!